በጣልቃ ገብ እና የተያዘ ወይም የተከበረ ንብረት ይለቀቅኝ  አቤቱታ ላይ የዳኝነት ይከፈላል?

ለዚህ ጽሑፍ  መነሻ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 41 አንድ ሰው በተጀመረ ክርክር መብቴ ይነካል፤ ወደ ክርክሩ ጣልቃ ገብቼ ልከራከር ብሎ ሲጠይቅ እና በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 418 ለፍርድ ማስፈፀሚያ የተያዘ ወይም የተከበረ ንብረት ይለቀቅልኝ በማለት አቤቱታ ሲያቀርብ የዳኝነት ይከፈላል ወይስ አይከፈልም የሚለው ጉዳይ ነው፡፡

የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ መሠረት አድረገው የሚደረጉ ክርክሮች ቅድሚያ የዳኝነት ሊከፈልባቸው እንደሚገባ በቁጥር 215 ተቀምጧል፡፡ ለዚህ ጽሑፍ በማዕከልነት የቀረበው በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 41 መሠረት ጣልቃ ሲገባ እና በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 418 መሠረት ለአፈፃፀም የተያዘ ወይም የተከበረ ንብረት ይለቀቅልኝ በማለት አቤቱታ ሲቀርብ የዳኝነት ይከፈላል ወይስ አይከፈልም የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ በባለሙያዎች ሁለት ዓይነት አቋምና አሠራር ሲንፀባረቅ ይታያል፡፡ የሁለቱን  አቋምና አሠራር ከነምክንያታቸው መመልከቱ ልዩነቱን በማጥበብ ወደ አንድ የተቀራረበ አሠራር ሊያመጣ ስለሚችል ለያይቶ መመልከቱ ተመራጭ ነው፡፡

የመጀመሪያው አቋምና አሠራር በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 41 እና 418 መሠረት አቤታቸውን የሚያቀርቡ ወገኖች የዳኝነት ሊከፍሉ አይገባም የሚለው ነው፡፡ የአቋሙ አራማጆች መከራከሪያቸው በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 41 አንድ ሰው ቀድሞ በተጀመረው ክርክር መብቴ ወይም ጥቅሜ ይነካል በማለት አቤቱታውን የሚያቀርበው የቀደሙት ተከራካሪ ወገኖች የዳኝነት በከፈሉት ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ጉዳዩ ዳኝነት የተከፈለበት ሆኖ እያለ በድጋሚ ጣልቃ የሚገባውን ሰው ዳኝነት ክፈል ማለት ያላግባብ ለአገልግሎቱ ሁለት ጊዜ ማስከፈል ነው፡፡ በተጨማሪም ጣልቃ የሚገባው ያለፍላጎቱ በተጀመረው ክርክር ጥቅሙና መብቱ ሊነካበት ስለሚችል በመገደድ ስለሆነ ተገዶ በገባበት ክርክር የዳኝነት ክፍል ማለቱ የሥነ ሥርዓት ሕጉ ዓላማ ባለመሆኑ የዳኝነት ሊከፍል አይገባም፡፡ አቤቱታውን ብቻ በማቅረብ ወደ ክርክሩ በመግባት መብትና ጠቅሙን ማስከበር አለበት በማለት ምክንያታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 418 የሚቀርቡ አቤቱታዎች የዳኝነት ሊከፈልባቸው አይገባም በማለት መከራከሪያቸውን የሚያቀርቡት አቤቱታውን ተከትሎ ሊሰጥ የሚችለውን ውሳኔ ይዘት በመመልከት ነው፡፡ የሚጠየቀው ዳኝነት ለአፈፃፀም የተያዘ ወይም የተከበረ ንብረት ይለቀቅልኝ የሚል በመሆኑ የሚሰጠው ውሳኔ ሊለቀቅ ይገባል ወይም አይገባም የሚል እንጅ መብት የሚሰጥ ውሳኔ ባለመሆኑ ዳኝትነት መከፈል የለበትም፡፡ ፍርድ ቤቱ አቤቱታው ሲቀርብለት ለአፈፃፀም ምክንያት የሆነውን ውሳኔ በሚሽር መልኩ ውሳኔ መስጠት አይችልም፡፡ ውሳኔው ንብረቱ ለአፈፃፀም ይውላል ወይስ አይውልም፤ ሊለቀቅ ይገባል ወይስ አይገባም የሚለው ላይ ስለሆነ መብት በማይሰጥ ውሳኔ ላይ ዳኝነት ማስከፈሉ ተገቢ አይደለም በማለት ይከራከራሉ፡፡

በአጠቃላይ በሁለቱ የሥነ ሥርዓት ሕግ ድንጌዎች የዳኝነት ሊከፈል አይገባም በማለት የሚከራከሩት ወገኖች ለክርክራቸው መሠረት የሚያደርጉት በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 41 ጉዳዩ ቀድሞ ክርክሩን በጀመሩት አካሎች ዳኝነት የተከፈለበትና ለአንድ ጉዳይ ሁለት ጊዜ ዳኝነት ሊከፈል የማይገባ  መሆኑን በመጥቀስና ጣልቃ ገቡ ወደ ክርክሩ የሚገባው ጥቅሙ ላይ ክርክር ስለተጀመረበት በመገደድ ነው የሚል ነው፡፡ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 418 ለክርክቸው መሠረት የሚያደርጉት አቤቱታውን ተከትሎ ሊሰጥ የሚችለው ውሳኔ ለአቤቱታ አቅራቢው ለአፈፃፀም ምክንያት የሆነውን ውሳኔ በመሻር መብት ሊሰጠው አለመቻሉን በመግለፅ ነው፡፡ ሌላው የሚያነሱት ክርክር በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 41 እና 418 አቤቱታ የሚያቀርቡ ወገኖች ሕግ አውጭው የዳኝነት እንዲከፍሉ ቢፈልግ ኖሮ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 358 እና 359(1)  እንደተቀመጠው አቤቱታው የዳኝነት ተከፍሎበት ይቅረብ በማለት በግልጽ አስገዳጅ በሆነ መልኩ ያስቀምጥ እንደነበር ነው፡፡ ሕግ አውጭው በዝምታ ማለፉ የዳኝነት እንዲከፍሉ እንደማይገደዱ ያመላክታል በማለት ይከራከራሉ፡፡

ሁለተኛው አቋምና አሠራር በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 41 እና 418 አቤቱታ ሲቀርብ የግድ ዳኝነት ሊከፈል ይገባል የሚለው ነው፡፡ የዚህ አቋምና አሠራር አራማጆች የዳኝነት በሁለቱም የሥነ ሥርዓት ድንጋጌ አቤቱታ ሲቀርብ የዳኝነት ሊከፈል ይገባል የሚሉት የዳኝነት ክፍያ የሚከፈለው ፍርድ ቤቱ ለሚሰጠው የዳኝነት አገልግሎት መከፈል ስላለበትና የክርክር ሂደቱ ልቅ እንዳይሆን ስለሚያስችል ነው፡፡ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 41 ጉዳዩ ላይ የዳኝነት በቀደሙት ወገኖች ቢከፈለም ጣልቃ ገቡ ፍርድ ቤቱ በክርክር ሊነካ የሚችለውን መብቱን እንዲጠብቅለት አገልግሎት የጠየቀው ለግሉ ነው፡፡ አንድ ሰው አገልግሎት ሊያገኝ የሚገባው በጠየቀው ልክና ለአገልግሎቱ በሚከፍለው መጠን ነው፡፡  ጣልቃ ገቡም ወደ ክርክሩ የገባው ሳይፈልግ ሌሎች በጀመሩት ክርክር በመገደድ ቢሆንም  ጣልቃ ገቡ ሳይፈልግ ወደ ክርክር ለገባበት እና ለሚደርስበት ኪሳራ ሥነ ሥርዓቱ ራሱን የቻለ የወጭና ኪሳራ መጠየቂያ መንገድ ስለዘረጋለት ተገዶ ክርክር ጀመረ በሚል ምክንያት ከዳኝነት ክፍያ ነፃ ሊሆን አይባውም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ምንም እንኳን በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 418 የሚቀርብ አቤቱታ ላይ የሚሰጠው ውሳኔ ለአፈፃፀም ምክንያት የሆነውን ውሳኔ በመሻር ለአቤቱታ አቅራቢ መብት የማይሰጠው ቢሆንም ለአፈፃፀም ማስከበሪያ ሊውል የነበርን ንብረት እንዲለቀቅ ውሳኔ እንዲሰጥ መጠየቁ ራሱን የቻለ ዳኝነት ነው፡፡ አቤቱታ አቅራቢው የተያዘው ወይም የተከበረው ንብረት ይለቀቅልኝ በማለት የሚጠይቀው ፍርድ ቤቱ በሚሰጠው ውሳኔ ተጠቃሚ ሊሆን ስለሚችል ነው፡፡ በዚህም መሠረት የዳኝነቱን አገልግሎት አስካገኘ ድረስ የዳኝነት ክፍያው ሊከፈል ግድ ይላል በማለት ይከራካረሉ፡፡

እንደዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ የሁለተኛው አቋምና አሠራር የዳኝነት ክፍያን መሠረታዊ ፅንሰ ሃሳብ የተከተለ ነው ብሎ ያምናል፡፡ የዳኝነት ክፍያ ትርጉም በግልጽ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ተገልፆ አይገኝም፡፡ ስለዳኝነት ክፍያ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 215 ክሶች በከሳሽነት ሆነ በተከሳሽ ከሳሽነት ሲቀርቡ ተገቢው ዳኝነት በታሪፍ ይከፈልባቸዋል ከማለት ውጪ የዳኝነት ክፍያ ምንድን ነው የሚለውን ቀጥተኛ ትርጉም አይመልስም፡፡ የዳኝነት ክፍያ ቀጥተኛ ትርጉም በግልጽ ባይቀመጥም በሥነ ሥርዓት ሕጉ ስለዳኝነት ክፍያ ከሚናገረው ድንጋጌ የዳኝነት ክፍያ ማለት ፍርድ ቤቶች ለሚሰጡት የዳኝነት አገልግሎት የሚከፈል የአገልግሎት ክፍያ ማለት እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ አገልግሎት ሰጪ የሆነ ማንኛውም አካል አገልግሎቱን በሚያቀርብበት ጊዜ ሥራውን ለማከናወን የራሱ የሆነ ወጭ የሚጠይቁ በመሆኑ  ከተጠቃሚው ህብረተሰብ በምላሹ የአገልግሎት ግብዓት ሊሟላበት የሚችል ክፍያ የሚጠይቁበት አሠራር አለ፡፡ ፍርድ ቤቶች አንድ የመንግሥት አካል እንደመሆናቸው ለሚሰጧቸው የዳኝነት አገልግሎቶች ተመጣጣኝ የሆነ የዳኝነት ክፍያ ይጠይቃሉ፡፡ የዳኝነት ክፍያው የሚሰጠውን  አገልግሎት ለማከናወን አስፈላጊ የሆኑ ግባቶችን ለማሟላት፣ ቀጣይነት ያለውና ተገልጋዩን ማኅበረሰብ ወጥነት ባለው ሁኔታ እንደ አገልግሎቱ ዓይነት በመክፈል ተጠቃሚ የሚሆንበትን አሠራር እንዲያፀና ያደርጋል፡፡ 

የዳኝነት ክፍያ ለሚሰጠው አገልግሎት ምላሽ ገቢን መሰብሰብ አንዱ ዓለማው ቢሆንም   በተጨማሪም የክርክር ሂደቱ ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ያስችላል፡፡ የዳኝነት ክፍያ በራሱ ተከራካሪዎች ሳይገባቸው በፈለጉ ቁጥር ወደ ክርክር እየገቡ የክርክሩን ሂደት በማጓተት ከሥነ ሥርዓት ዓለማ ውጭ እንዳይሠራ ያደርጋል፡፡ የሥነ ሥርዓት ሕጎች መደበኛ ሕጎችን በተቀላጠፈ መልኩ ተፈፃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ተቀዳሚ መርሃቸው ስለሆነ የክርክሩ ሂደት ጥብቅ የሆነ አካሄድን የሚጠይቅ ነው፡፡ የክርክሩን ሂደት ጥብቅ በሆነ አካሔድ እንዲጓዝ ለማድረግ የዳኝነት አገግሎት ክፍያ ወሳኝነት የሚኖረው ክርክሩ ልቅ እንዳይሆን መቆጣጠሪያ መንገድ ነው፡፡ በሕግ ትርጓሜ መርሆዎች ውስጥ ግብ ተመልካች ትርጓሜ (purposive or teleological interpretation) የምንለው ግልጽ በሆነ ሁኔታ ሕጎች ባልተቀመጡና የአሠራር ላይ ልዩነት የሚፈጥሩ ሲሆን ሕጉን የሚተረጉመው አካል ሕጉ የወጣበትንና ሊደርስበት ያሰበውን ግብ መመልከት እንዳለበት የሚናገር ነው፡፡ በሁለቱ የሥነ ሥርዓት ድንጋጌዎች የዳኝነት ይከፈላል ወይስ አይከፈለም ወደሚለው መደምደሚያ ለመድረስ የሥነ ሥርዓት ሕጉን ዓላማ እንደአጠቃላይ የዳኝነት ክፍያን ዓለማ ደግሞ በተለየ ሁኔታ መመልከት ግድ ይላል፡፡ የሥነ ሥርዓት ሕጎች በራሳቸው ግብ ሊሆኑ የማይችሉ መደበኛ የሕግ ድንጋጌዎች ባለተንዛዛ፣ በተቀላጠፈ፣ ወጭ ቆጣቢና ተገማች በሆነ መልኩ ነፍስ እንዲዘራባቸወና ተፈፃሚ እንዲሆኑ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ዝቅ ስንል በሥነ ሥርዓት ሕግ ሥር የዳኝነት ክፍያ ዓላማም ዋና መሠረቱ የሥነ ሥርዓት ሕጉን ዓላማ ለማሳካት አንዱ አሠራር ሆኖ የተቀመጠ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህ ማለት የዳኝነት ክፍያ ፍርድ ቤቱ የተቀላጠፈና ተገማች የሆነ አገልግሎት እንዲሰጥ ማስፋፊያ የሚሆን ገቢ የማስገኘት ዓላማ ሲኖረው በሌላ በኩል ፍርድ ቤቶች የሚያካሂዷቸውን ክርክሮችን በዳኝነት ክፍያ ጥብቅ በማድረግ ያልተንዛዛና ለወጭ የማይዳርግ ክርክር እንዲካሄዱ ይረዳል፡፡ ስለዚህ እንደ አጣቃላይ የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ዓላማ ለማሳካት የዳኝነት ክፍያ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 41 እና 418 መከፈሉ ተገቢነት ያለው ይመስላል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ሕግ የማታከብረው ከተማ
በገጠር መሬት የመጠቀም መብትን በዋስትና ማስያዝና አርሶ አደሩ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 23 May 2024