የይግባኝ የዳኝነት ክፍያ አግባብነትን በተመለከተ

ግምቱ ተለይቶ የሚታወቅ የፍትሐ ብሔር ክርክር ጉዳይ በመያዝ በፍርድ ቤት ክስ የሚመሰርት ወይም የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ የሚያቀርብ ማንኛውም ተከራካሪ በፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ቁጥር 215/1 እና ስለ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ገንዘብ አከፋፈል በ1945 ዓ/ም በተደነገገው ደንብ መሠረት የዳኝነት ክፍያ ይከፍላል። በዚህ ክሱን በከፈተበት ፍርድ ቤት በተሰጠው ውሳኔ ቅር የተሰኘ ተከራካሪ ደግሞ የይግባኝ አቤቱታውን ይግባኝ ለመስማት ሥልጣን ወዳለው ፍርድ ቤት ያቀርባል። ይህ የይግባኝ አቤቱታ እንዲሰማለት ደግሞ በሥር ፍርድ ቤት የከፈለውን የዳኝነት ክፍያ 50% መክፈል ይጠበቅበታል። የዚህ አጭር ማስታወሻ ዓላማም የዚህ የይግባኝ የዳኝነት ክፍያ አግባብ የማይሆንበትን ኹኔታ መጠየቅ ነው።  

ከሶስቱ የመንግሥት አካላት አንደኛው የሆነው ፍርድ ቤት በተለያዩ ምክንያቶች (በማስረጃ ምዘና፣ በሕግ አተረጓጎምና አተገበባበር ወዘተ) ለተገልጋዩ/ለተከራካሪው ተገቢውን እና ትክክለኛውን አገልግሎት/ውሳኔ ባለመስጠቱ ምክንያት ተከራካሪው ውሳኔውን ለማሳረም የሚያወጣው የይግባኝ የዳኝነት ክፍያ አግባብነት በሁለት ተከፍሎ ሊታይ ይገባል። ይኸውም፣ ይግባኝ ባዩ በሥር ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ አግባብ አይደለም ተብሎ በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሚሻር ከሆነ፣ ቀድሞውኑ ወደ ይግባኝ የሄደው በሥር ፍርድቤቱ ሥህተት ነውና የከፈለው የይግባኝ የዳኝነት ክፍያ ተመላሽ ሊደረግለት ይገባል። ነገር ግን የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትም የሚፀና ከሆነ ይግባኝ ባዩ ላገኘው አገልግሎት የዳኝነት ክፍያውን ሊከፍል ይገባል።

ይህ የይግባኝ የዳኝነት ክፍያ ይግባኝ ባይ ጉዳዩ በይግባኝ ከታየለት በኋላ የረታ ወይም የቀድሞው ውሳኔ የተሻረለት ከሆነ የወጪና ኪሣራ ዝርዝር በማቅረብ ከተረቺው ሊጠይቅ ይችላል የሚል መከራከሪያ ሊቀርብ ይችላል። ነገር ግን ከዚህ ጋር በተያያዘ የሕጉ አንድምታ እና የሰበር ውሳኔዎች ትርጓሜ ሁል ጊዜ ተረቺ ወጪና ኪሣራ ሊሸፍን ይገባል የሚባለው ከቅን ልቦና ውጪ ሌላኛውን ተከራካሪ ለወጪ የዳረገ ተከራካሪ ካለ ብቻ ነው እንጂ በሁሉም ጉዳዮች ወጪና ኪሣራ ይሸፍናል ማለት እንዳልሆነ መገንዘብ ይቻላል። ከዚህ ባለፈም አሁን አሁን በሰፊው እየተለመደ የመጣው «ግራ ቀኙ ወጪያቸውን ይቻሉ» የሚል ትዕዛዝ ይህ እንዳይቻል ያደርጋል።

በመሆኑም፣ ይህ ሀሳብ ቢተገበር ሁለት ጥቅም አለው። አንደኛው ጥቅም አንድ ተከራካሪ ያለጥፋቱ በመንግሥት አካል (በሥር ፍርድ ቤት) በተሰራበት ስህተት በይግባኝ መንገላታቱ ሳያንስ ለተጨማሪ ወጪ ከመዳረግ የሚያድነው መሆኑ ነው። ከላይ እንደገለፅነው የውሳኔው በይግባኝ መሻር የሚያመላክተው የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ሥህተት መሆኑን ነው። ሁለተኛው እና ዋነኛው ጥቅም ግን መንግሥት እንደማንኛውም ግለሰብ እና አገልግሎት ሰጪ ሁሉ ራሱ በዘረጋው አሰራር ከገዛ ራሱ ሥህተት ተጨማሪ ገቢ ማግኘት የለበትም የሚለውን መሠረታዊ የፍትሐዊነት ዕሳቤን በመተርጎም የፍትሕ ተደራሽነትን ማጎልበት ነው።

በአጭሩ የዚህች አጭር ማስታወሻ ድምዳሜ በይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ታይቶ የተሻረ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ የተከፈለ የዳኝነት ክፍያ ለይግባኝ ባዩ ተመላሽ ሊሆን ይገባል የሚል ነው፤ ምክንያቱም ለዚህ ወጪ የተዳረገው በሥር ፍርድ ቤቱ ሥህተት ነውና።

  6483 Hits

በጣልቃ ገብ እና የተያዘ ወይም የተከበረ ንብረት ይለቀቅኝ  አቤቱታ ላይ የዳኝነት ይከፈላል?

 

ለዚህ ጽሑፍ  መነሻ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 41 አንድ ሰው በተጀመረ ክርክር መብቴ ይነካል፤ ወደ ክርክሩ ጣልቃ ገብቼ ልከራከር ብሎ ሲጠይቅ እና በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 418 ለፍርድ ማስፈፀሚያ የተያዘ ወይም የተከበረ ንብረት ይለቀቅልኝ በማለት አቤቱታ ሲያቀርብ የዳኝነት ይከፈላል ወይስ አይከፈልም የሚለው ጉዳይ ነው፡፡

የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ መሠረት አድረገው የሚደረጉ ክርክሮች ቅድሚያ የዳኝነት ሊከፈልባቸው እንደሚገባ በቁጥር 215 ተቀምጧል፡፡ ለዚህ ጽሑፍ በማዕከልነት የቀረበው በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 41 መሠረት ጣልቃ ሲገባ እና በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 418 መሠረት ለአፈፃፀም የተያዘ ወይም የተከበረ ንብረት ይለቀቅልኝ በማለት አቤቱታ ሲቀርብ የዳኝነት ይከፈላል ወይስ አይከፈልም የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ በባለሙያዎች ሁለት ዓይነት አቋምና አሠራር ሲንፀባረቅ ይታያል፡፡ የሁለቱን  አቋምና አሠራር ከነምክንያታቸው መመልከቱ ልዩነቱን በማጥበብ ወደ አንድ የተቀራረበ አሠራር ሊያመጣ ስለሚችል ለያይቶ መመልከቱ ተመራጭ ነው፡፡

የመጀመሪያው አቋምና አሠራር በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 41 እና 418 መሠረት አቤታቸውን የሚያቀርቡ ወገኖች የዳኝነት ሊከፍሉ አይገባም የሚለው ነው፡፡ የአቋሙ አራማጆች መከራከሪያቸው በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 41 አንድ ሰው ቀድሞ በተጀመረው ክርክር መብቴ ወይም ጥቅሜ ይነካል በማለት አቤቱታውን የሚያቀርበው የቀደሙት ተከራካሪ ወገኖች የዳኝነት በከፈሉት ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ጉዳዩ ዳኝነት የተከፈለበት ሆኖ እያለ በድጋሚ ጣልቃ የሚገባውን ሰው ዳኝነት ክፈል ማለት ያላግባብ ለአገልግሎቱ ሁለት ጊዜ ማስከፈል ነው፡፡ በተጨማሪም ጣልቃ የሚገባው ያለፍላጎቱ በተጀመረው ክርክር ጥቅሙና መብቱ ሊነካበት ስለሚችል በመገደድ ስለሆነ ተገዶ በገባበት ክርክር የዳኝነት ክፍል ማለቱ የሥነ ሥርዓት ሕጉ ዓላማ ባለመሆኑ የዳኝነት ሊከፍል አይገባም፡፡ አቤቱታውን ብቻ በማቅረብ ወደ ክርክሩ በመግባት መብትና ጠቅሙን ማስከበር አለበት በማለት ምክንያታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 418 የሚቀርቡ አቤቱታዎች የዳኝነት ሊከፈልባቸው አይገባም በማለት መከራከሪያቸውን የሚያቀርቡት አቤቱታውን ተከትሎ ሊሰጥ የሚችለውን ውሳኔ ይዘት በመመልከት ነው፡፡ የሚጠየቀው ዳኝነት ለአፈፃፀም የተያዘ ወይም የተከበረ ንብረት ይለቀቅልኝ የሚል በመሆኑ የሚሰጠው ውሳኔ ሊለቀቅ ይገባል ወይም አይገባም የሚል እንጅ መብት የሚሰጥ ውሳኔ ባለመሆኑ ዳኝትነት መከፈል የለበትም፡፡ ፍርድ ቤቱ አቤቱታው ሲቀርብለት ለአፈፃፀም ምክንያት የሆነውን ውሳኔ በሚሽር መልኩ ውሳኔ መስጠት አይችልም፡፡ ውሳኔው ንብረቱ ለአፈፃፀም ይውላል ወይስ አይውልም፤ ሊለቀቅ ይገባል ወይስ አይገባም የሚለው ላይ ስለሆነ መብት በማይሰጥ ውሳኔ ላይ ዳኝነት ማስከፈሉ ተገቢ አይደለም በማለት ይከራከራሉ፡፡

Continue reading
  11730 Hits