Font size: +
14 minutes reading time (2827 words)

በፍትሐብሔር ክርክር ቅድመ-ሙግት ሂደት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች

የዚህ ጽሑፍ ዋና ትኩረት  ከሙግት በፊት ያሉ ሥነ-ሥርዓታዊ ሂደቶች አንድን ክርክር ላይ ያላቸዉን  ሚና ማጉላት እና ፋይዳቸዉን ማሳየት ነዉ፡፡ በፍትሐ ብሔር ክርክር ሂደት ቅደመ ሙግት የሚባለዉ ለክርክሩ መሪ ጭብጥ ተይዞ ግራ ቀኙ ማስረጃ ማሰማት ከመጀመራቸዉ በፊት ያለዉ ሂደት ነዉ፡፡ በፍትሐ ብሔር ክርክር ዋናዉ ሙግት የሚጀምረዉ ጭብጥ ተይዞ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 257 እና ተከታይ ድንጋጌዎቹ ተከራካሪዎች ማስረጃዎቻቸዉ የሚያስረዷቸዉን ጭብጥ እያስመዘገቡ ማስረጃ ማሰማት ሲጀምሩ ነዉ፡፡ ከዋናዉ ሙግት በፊት ባለዉ  የቅድመ ሙግት ሂደት በዋናነት ክስና ማስረጃ ማቅረብ፣ መጥሪያ ማድረስ፣ መልስ እና ማስረጃ መቅረብ፣ ክስ መሰማት እና የክስ መቃወሚያዉ ላይ የመወሰን ተግባሮች ይፈፀማሉ፡፡ ይህ የክርክር ሂደት ክርክሩን ለመምራት ዋና መሰረት የሆነዉ ነዉ፡፡ የክርክሩ አቅጣጫ የሚወሰነዉም በዚህ የክርክር ደረጃ ላይ  በሚሰሩ ስራዎች ነዉ፡፡ ክርክሩን ግልፅ እና አጭር በሆነ ሂደት ለመፈፀም የሚያስችለዉም የቅድመ ሙግት ሂደቱ ጤናማ መሆን ከቻለ ነዉ፡፡

ክርክሩ ሳይንዛዛ እንዲያልቅ ከተፈለገ በቅደመ ሙግት ሂደት መከናወን ያለባቸዉ ነገሮች ሁሉ ጥንቅቅ ብለዉ መከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ክርክሩ ወደ ኋላ እንዳይመለስ ከተፈለገም በቅድመ ሙግት ሂድት የሚከናወነዉ መጥሪያ አደራረስ ሰርዓት በተገቢዉ መንገድ መፈፀም ይኖርበታል፡፡ ከሙግት በፊት በዳኛዉ ሆነ በሬጅስትራር  ሊከናወኑ የሚገቡ ብዙ ጉዳዮች ያሉ ቢሆንም ለዚህ ጽኁፍ ዓላማ ሲባል ሶስት ጉዳዮች ላይ ብቻ ትኩረት ይደረጋል፡፡ የመጀመሪያዉ ክስ እና መልስ ሲቀርብ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 145 መሰረት እንዲቀርብ የሚጠየቀዉን ማስረጃ ይመለከታል፡፡ ሁለተኛዉ መልስ በሬጅስትራር የማቀባበል ስርዓት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጉዳዮች ናቸዉ፡፡ ሶስተኛዉ ክስ ከመስማት ጋር በተገናኘ መቃወሚያ እና ፍሬ ነገር ክርክሮች የሚደረጉበት ሁኔታ ይመለከታል፡፡ ይህ ጽሑፍም ሶስቱን ጉዳዮች በሕግ ያላቸዉን ማዕቀፍ እና ተግባራዊ አፈፃፀማቸዉን በመዳሰስ ከሥነ-ሥርዓት ሕጉ ዓላማ አንፃር ለክርክር ፍጥነት፣ ግልፅነት እና ፍትሐዊነት ያላቸዉን አስተዋጽዖ ይዳስሳል፡፡

ሀ. በፍ/ብ/ስ/ሕ/ቁ 145 መሰረት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚቀርብ ማስረጃ

በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 145 መሰረት የሚቀርቡ ማስረጃዎች በሁለት ዓይነት ሁኔታ የሚቀርቡ እንደሆኑ ከድንጋጌዉ መረዳት ይቻላል፡፡ አንደኛዉ አማራጭ ፍርድ ቤቶች በራሳቸዉ አስተያየት እንዲቀርብ ትዕዛዝ የሚሰጡት ሲሆን   እንደ ነገሩ ሁኔታ ፍርድ ቤቱ ትክክለኛ ፍትሕ ለመስጠት እና ነገሩን ለመወሰን አመች ነዉ ብሎ ሲያምን  በማንኛዉም የክርክር ደረጃ ሊቀርብ የሚችል ነዉ፡፡ ሁለተኛዉ አማራጭ ተከራካሪ ወገኖች ሲያመልክቱ የሚቀርብ ነዉ፡፡ በተከራካሪዎች አመልካችነት እንዲቀርብ የሚጠየቀዉ ማስረጃ አቀራረብ ፍርድ ቤቱ በራሱ አስተያየት ከሚያስቀርበዉ የተለዬ መንገድ ይከተላል፡፡  በመርህ ደረጃ ተከራካሪ  ወገኖች ማስረጃዎቻቸዉን ሁሉ ከክስ እና መልሳቸዉ ጋር አጠቃለዉ ማቅረብ ስላለባቸዉ እንደፈለጉ  እና በፈለጉት የክርክር ደረጃ የሚያቀርቡበት እድል በሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ ነዉ፡፡ ከጅምሩ ተከራካሪ ወገኖች በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲቀርቡላቸዉ የሚጠይቋቸዉ ማስረጃ ማንኛዉንም ማስረጃ ሳይሆን ማቅረብ የማይችሉትን ማስረጃ ነዉ፡፡ እነዚህ ማስረጃዎች ደግሞ በበቂ ምክንያት ወይም ሳይገኙ ቀርተዉ በክርክሩ ሂደት እንዲቀርቡ ካልተጠየቀ የግዴታ ክስ እና መልስ ሲቀርብ በማስረጃ ዝርዝር እንዲቀርቡ የሚጠየቁ ናቸዉ፡፡ ክስ እና መልስ ሲቀርብ ማስረጃም አብረዉ እንዲቀርቡ የሚያስፈልገበት ዋና ዓላማ የክርክሩ መናሻ አካል የሚሆኑት በክሱ እና በመልሱ የጠቀሱት ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን በግራ ቀኙ የሚቀርቡ ማስረጃዎችም የክርክሩ አካል መሆን ስለሚኖርባቸዉ ነዉ፡፡የክርክር ጭብጥም የሚመሰረተዉ በክስና መልስ ከተገለፁ ነገሮች ብቻ ሳይሆን ማስረጃዎችም የጭብጥ አካል ሆነዉ ምዘና ስለሚደረግባቸዉ የግድ ቀድመዉ እንዲቀርቡ ይጠበቃል፡፡ በፍ/ብ/ስ/ሕ/ቁ 233 ተከሳሽ ለክሱ መልስ እንዲሰጥ የሚላክለት ክሱ እና ከክሱ ጋር የቀረበዉ ማናቸዉም በአስረጅነት የቀረቡ ማስረጃ ጭምር እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ይህ የሚያመለክተዉ ተከሳሽ መልስ የሚሰጠዉ በክሱ ለተገለፁ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን በማስረጃዎችም ላይ እንደሆነ ነዉ፡፡ በተመሳሳይ ከሳሽ ክስ ሲያቀርብ ማቅረብ የማይችለዉ ማስረጃ እንዳለ ገልፆ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 145 መሰረት ማስረጃ እንዲቀርብለት በሚጠይቀዉ ማስረጃ ላይም ተመሳሳይ ዉጤት ይኖረዋል፡፡ ክሱ ለተከሳሽ ከመድረሱ በፊት ከሳሽ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 145 እንዲቀርብለት የጠየቀዉ ማስረጃ ክሱ ለተከሳሽ ከመላኩ በፊት እንዲቀርበ ተደርጎ  ከክሱ ጋር በተከሳሽ መልስ እንዲሰጥበት ይጠበቃል፡፡ ተከሳሽ መልስ ሲያቀርብ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማስረጃ እንዲቀርብለት ከጠየቀ ማስረጃዉ ክስ ሲሰማ ቀርቦ የክርክሩ አካል እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡

በተግባር የሚታየዉ ከዚህ የተለየ ነዉ፡፡ በፍርድ ቤት በሚቀርቡ በአብዛኛዉ ተከራካሪ ወገኖች በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲቀርቡላቸዉ የሚጠይቋቸዉ ማስረጃዎች ከሁለት መመዘኛዎች አንፃር በተግባር ያለዉን ክፍተት የሚያሳዩ ናቸዉ፡፡

አንደኛዉማስረጃዎች በፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ሊያሟሉ የሚገባቸዉ ሁኔታዎች ባልተሟሉበት ሁኔታ ማስረጃዎች እንዲቀርቡ የሚታዘዝበት አሰራር ነዉ፡፡ በሥነ-ሥርዓት ሕጉ በግልፅ እንደተቀመጠዉ ተከራካሪዎች በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲቀርብ ሊጠይቁ የሚችሉት ማስረጃዉን በራሳቸዉ ለማቅረብ የማይችሉ መሆኑን ሲያሳዩ ነዉ፡፡ ሆኖም በተግባር ተከራካሪዎች በራሳቸዉ ሊያቀርቧቸዉ የሚችሉትን ማስረጃዎች ሁሉ እንዲቀርቡላቸዉ ሲጠይቁ ይታያል፡፡ ለምሳሌ፡- በአንድ ፍርድ ቤት መዝገብ የተሰጠን ዉሳኔ ማስረጃ ማድረግ የሚፈልግ ተከራካሪ ወገን በራሱ የዉሳኔ ግልባጭ ጠይቆ ማግኘት እና ከማስረጃዎቹ ጋር ማቅረብ እየቻለ ፍርድ ቤቱ እንዲያስቀርብ ሲጠየቅ ይስተዋላል፡፡ ፍርድ ቤቶችም ተከራካሪዎች ማቅረብ የሚችሉትን ማስረጃ ራሳቸዉ እንዲያቀርቡ ከማስደረግ ይልቅ እንዲቀርብ ትዕዛዝ የሚሰጡበት ሁኔታ ፍርድ ቤቶችን አከራክሮ ከመወሰን ሚናቸዉ አዉርዶ  ተከራካሪዎችን በመተካት ማስረጃ የማሰባሰብ ስራ እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ተከራካሪዎች ራሳቸዉ ማቅረብ የሚችሉት ማስረጃ ፍርድ ቤት ለማስቀረብ ትዕዛዝ ሲሰጥም ለተጨማሪ ቀጠሮ ምክንያት ስለሚሆን ክርክር የማራዘም ዉጤት ይኖረዋል፡፡

ሁለተኛዉ መመዘኛ ማስረጃዉ የሚቀርብበት የክርክርን ደረጃ ይመለከታል፡፡  በተግባር ያለዉ አፈፃፃም ከሳሽ ክስ ሲያቀርብ እንዲቀርብለት የሚፈልገዉን ማስረጃ በማስረጃ ዝርዝሩ ገልፆ ቢያቀርብም ቀድሞ ማስረጃዉ ቀርቦ ተከሳሽ መልስ እንዲጥበት ሲደረግ አይታይም፡፡ በተመሳሳይ ተከሳሽ መልስ ሲሰጥ በማስረጃ ዝርዝሩ እንዲቀርብለት ቢጠይቅም ቀድሞ ቀርቦ ክስ ሲሰማ የክርክሩ አካል አይደረግም፡፡ በአብዛኛዉ ተከራካሪዎች እንዲቀርቡላቸዉ የሚጠይቋቸዉ ማስረጃዎች እንዲቀርቡ የሚደረጉት ክስ ተሰምቶ፣ምስክር ተሰምቶ ክርክሩ ከተጠናቀቀ በኋላ ክርክሩ ሊወሰን ጫፍ ሲደርስ ነዉ፡፡ የሚቀርቡ ማስረጃዎች ላይ ግራ ቀኙ በጽኁፍ አስተያየት እንዲሰጡበት እድል የሚሰጥበት ሁኔታ ቢኖርም ማስረጃዎች የሚቀርቡት ክርክሩ ከተጠናቀቀ በኋላ በመሆኑ ራሱን የቻለ ሌላ የክርክር ምዕራፍ እንዲኖረዉ አድርጓል፡፡ በሌላ አገላጽ ክርክሩ ከተጠናቀቀ በኋላ የሰነድ ማስረጃ እንዲቀርብ የሚሰጠዉ ትዕዛዝ ራሱን የቻለ የክርክር ምዕራፍ ሲሆን ይታያል፡፡ በቀረበዉ ማስረጃ ላይ ግራ ቀኙ የየራሳቸዉን ሃሳብ ስለሚያቀርቡበት ነገሩን ለማጣራት ተደጋጋሚ ትዕዛዞች ስለሚሰጡ ረጅም ጊዜ ይወስዳል፡፡ ክሱ ሲቀርብ ጀምሮ ቅድሚያ እንዲቀርብ ቢደረግ ማስረጃዉ ላይ የሚደረገዉ ማጣራት እኩል ከክርክሩ ጋር ሊጠናቀቅበት የሚችልበት እድል አለ፡፡ያለዉ አሰራር  ግን ማስረጃዉ ቅድሚያ ስለማይቅርቡና ነገሩ ሊወሰን ሲል እንዲቀርብ ስለሚደረግ ሌላ የክርክር ምዕራፍ ሆነ እንዲቀጥል ያደርገዋል፡፡ይህ ሁኔታ አንድ ክርክር መጠናቀቅ የሚኖበትን ጊዜ እንዲራዘም የማድረግ ዉጤት እንዲኖረዉ ከማድረግ አልፎ በአንድ ክርክር ሁለት የክርክር ምዕራፍ እንዲኖር እያደረገ ይገኛል፡፡

ለ. መልስ በሬጅስትራር ማቀባበል  

አንድ ክስ ተከፍቶ ሲቀርብ  ጉዳዩ ለሚመራለት ችሎት ከመቅረቡ በፊት ሬጅስትራር የቀረበዉ የክስ አቤቱታ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 222 መሰረት አንድ ክስ ማሟላት ያለበትን ነገሮች አሟልቶ መቅረቡን፣ከክሱ ጋር የሚቀርቡ ሰነዶች ዋናዎቹንና ግልባጮቹን እና በከሳሹ የቀረበ መሆኑን የማረጋገጥ ስራ እንደሚሰራ በግልጽ በፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ተደንግጓል፡፡ ሬጅስትራር ክስን መርምሮ እንደሚያሳለፍ ሁሉ መልስ እንደሚቀበል በሕጉ በግልፅ የተቀመጠ ነገር ባይኖርም አመላካች ድንጋጌዎች አሉ፡፡  ሬጅስትራር ክሱ ላይ የሚመረምረዉ ነገር፣ዋናዉ እና ግልባጩን የሚያረጋግግጠዉ ሰነድ እንዲሁም በሚመለከተዉ አካል መቅረቡን የማረጋገጥ ስራ በተመሳሳይ መልስ ሲቀርብ የሚሰራ በመሆኑ  መልሱን መርምሮ መቀበሉ ከሕግ ዉጪ ነዉ ሊያስብለዉ የሚችል አይደለም፡፡ የፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 238(1) ድንጋጌ መንፈስም መረዳት የሚቻለዉ መከላከያ ማስረጃ ሲቀርብ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 229 በተቀመጠዉ መሰረት በሬጅስትራር በኩል ሊመረመር እንደሚገባ ነዉ፡፡ ካለዉ ጥቅም አንፃር ሲታይም መሰረታዊ ከሆኑ የዳኝነት ስራዎች ወጪ የሆኑ ጉዳዮች በሬጅስትራር መረጋገጣቸዉ ለስራዉ ዉጤታማነት ተገቢ ከመሆኑም በላይ የዳኞችን የስራ ጫና የመቀነስ ዉጤት ይኖረዋል፡፡ ሆኖም መዝገብ ተከፍቶ ክሱ ከዳኛ ፊት ቀርቦ ክርክሩን ለማስቀጠል ለችሎት ከተመራ በኋላ መልስ ለማቀባበል ወደ ሬጅስትራር የሚመለስበት አሰራር የስራዉን ጥራት ከማረጋገጥ እና ጫናዉን ከማቅለል ባለፈ ምን ዓይት ዉጤት እንደሚኖረዉ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ዉጤቱን ለመመዘን በቅድሚያ ለመልስ መቀባበል ወደ ሬጅስትራር የሚመለስበት አሰራር ማየት ተገቢ ነዉ፡፡

አሁን ባለዉ የፍርድ ቤቶች አሰራር መዝገብ ተከፍቶ ለችሎት ሲቀርብ  ዳኛዉ ሁለት ቀጠሮዎችን ይሰጣል፡፡ አንዱና ቀዳሚዉ ቀጠሮ በሬጅስትራር በኩል መልስ ለመቀባበል ሲሆን ቀጣዩ ቀጠሮ ለክስ መስማት ተብሎ የሚሰጥ ነዉ፡፡ መልስ ማቀባበሉ ስራ በሬጅስትራር ከተከናወነ ቀጣዩ ቀጠሮ ክስ መስማቱ ይሆናል፡፡ ከዚህ አሰራር ጋር ተያይዞ የሚነሳዉ በሬጅስትራሩ የመልስ ማቀባበሉ ቀጠሮ ባልተፈፀመ እና መልስ ለማቀባበል በሚቀጠርበት ዕለት  ተለዋጭ ትዕዛዞች  መሰጠት በሚያስፍልግበት  ወቅት ምን መሆን ይኖርበታል የሚለዉ ነዉ፡፡ ባለዉ አሰራር በሬጅስትራር መልስ ቀረበ አልቀረበ፣ተለዋጭ ትዕዛዝ መስጠት ቢያስልግ ባያስፈልግም በዕለቱም ምንም የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ ሬጅስትራሩ በዕለቱ የቀረበዉን ነገር በመመዝገብ ቀደም ብሎ ተቀጥሮ ለነበረዉ ክስ መሰማት ቀጠሮ መዝገቡን ያስተላልፋል፡፡ በዚህ አሰራር መልስ ለመቀበል በተቀጠረበት ዕለት ሊፈፀሙ የሚችሉ ተግባሮች ሳይከናወኑ ክስ በሚሰማበት ቀጠሮ ዳኛዉ እንዲፈጽማቸዉ እንዲሻገሩ ይደርጋል፡፡ ነገሩን ግልጽ ለማድረግ መልስ በሚቀባበልበት ወቅት ሊሰጡ የሚችሉ ትዕዛዞችን ማየት አስፈላጊ ነዉ፡፡

መልስ ለመቀበል በተቀጠረበት ዕለት መልስ ሊቀርብም ላይቀርብም የሚችልበት እድል ይኖራል፡፡ በዚህ ቀጠሮ ሊሰጡ ከሚችሉት የትዕዛዝ አማራጮች ዉስጥ  አንደኛ ተከሳሹ መጥሪያ ደርሶት ካልቀረበ ወይም በራሱ ጉድለት ምክንያት መልሱን ሳያቀርብ ከቀረ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 199(1) መሰረት በዚያዉ በቀጠሮዉ ቀን የጽሁፍ መልስና ማስረጃዎቹን የማቅረብ መብቱ የሚታለፈዉ (default proceeding) ነዉ፡፡ ሁለተኛ  ተከሳሽ መልሱን ይዞ ቀርቦ የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ወይም የመቻቻል ጥያቄ ካቀረበ ክስ ከመሰማቱ በፊት ከሳሽ መልስ እንዲሰጥበት ትዕዛዝ የሚሰጥበት ነዉ፤ይህም የሚደረገዉ መልስ በቀረበ በዕለቱ ነዉ፡፡ ሶስተኛ ተከሳሹ መልስ ሲሰጥ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 40(2) በአባሪነት ወይም በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 43 መሰረት ዋቢ እንዲገባለት የሚጠይቀዉ ወገን ካለ በተመሳሳይ  ትዕዛዙ የሚሰጠዉ የመልስ መቅረቡን ተከትሎ ነዉ፡፡ አራተኛ ከሳሽ  መጥሪያ ለማድረስ ተከሳሹ ያላገኘዉ መሆኑን ከገለፀ አማራጭ የመጥሪያ አፈፃፀም ሂደቶች እንዲፈጸሙ ትዕዛዝ የሚሰጠዉም መልስ ለመቀበል በተቀጠረበት ዕለት ነዉ፡፡ አምስተኛ ከሳሽ ለተከሳሽ ክሱን ለማድረስ መጥሪያ ወጪ ካላደረገና ክርሩን ሳይከታል ከቀረ፣ መጥሪያ ወጪ  ካደረገ በኋላ መጥሪያ ማድረሱን ወይም የገጠመዉን ነገር ቀርቦ ካላስረዳ ለተከሳሽ መጥሪያ መድረስ አለመድረሱ ሳይረጋገጥ ወደ ፊት ቀጠሮ ሊሰጥ ስለማይችል በተመሳሳይ የቀጠሮዉ ምክንያት በከሳሽ ጉድለት እንዳልተፈጸመ ተቆጥሮ መዝገቡ እስከ መዝጋት የሚደርስ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ እነዚህ ትዕዛዞች ሁሉ መልስ ለመቀበል በተቀጠረበት ዕለት ሊሰጡ የሚችሉ ናቸዉ፡፡ ትዕዛዞቹም የሚሰጡት በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 199(1) መሰረት በዚያዉ ቀጠሮ እንጅ ሌላ ቀጠሮ ጠብቀዉ  ሊሆን እንደማይገባ ግልጽ ነዉ፡፡ 

በተግባር ባለዉ አሰራር ወይም በሬጅስትራር መልስ በመቀባበሉ ምክንያት መልስ ለመቀበል በተቀጠረበት ዕለት ሊሰጡ የሚችሉ ትዕዛዞች ሁሉ በዕለቱ እንዳይሰጡ የማድረግ ዉጤት አስከትሏል፡፡ ይህ የሆነበት ዋና ምክንያት መልስ በሬጅስትራር የማቀበባል ስራ በሚሰራበት ዕለት መልስ ካልቀረበና መልስ ቀርቦም ተለዋጭ ትዕዛዝ መስጠት ካስፈለገ በዕለቱ ትዕዛዝ የሚሰጠበት አሰራር ስላልተፈጠረ ነዉ፡፡ አሰራሩ ክስ ለመስማት በተቀጠረበት ዕለት ዳኛዉ የሚጠብቀዉን ክስ የመስማት ስራ ብቻ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ ክስ በሚሰማበት ዕለት ዳኛዉ የሚጠብቀዉ ስራ ክስ መስማት ብቻ ሳይሆን መልስ መቅረብ አለመቅረቡን፣ መልስ ካልቀረበ መጥሪያ የደረሰ መሆን አለመሆኑን፣ መልስ ከቀረበም የተከሳሽ ከሳሽነት ወይም የመቻቻል ጥያቄ መቅረብ አለማቅረቡን፣በክርክሩ አባሪ ወይም ዋቢ እንዲገባ የተጠራ ወገን መኖር አለመኖሩን የማረጋገጥ እንዲሁም መጥሪያ ደርሶ መልስ ካልቀረበ መልስ የማቅረብ መብትን የማለፍ ስራ ይጠብቀዋል፡፡ በሌላ አገላለጽ  ክስ በሚሰማበት ዕለት ዳኛዉ ትኩረቱ ክስ መስማት ላይ ብቻ ሳይሆን ክስ ከመሰማቱ በፊት ባሉ ሂደቶች ሊፈፀሙ የሚገባቸዉ ነገሮች መሟላት አለመሟላታቸዉን ተመልሶ እንዲያጣራ የሚያደርግ ነዉ፡፡ ከጅምሩ ክስ ለመሰማት መቀጠር ያለበት ክስ ከመሰማቱ በፊት ያሉ ሂደቶች መፈፀማቸዉ ተረጋግጦ ነዉ፡፡ ከክስ መሰማት በፊት ያሉ ሂደቶች ገና ይፈፀማሉ በሚል በታሳቢነት ክስ ለመስማት እንዲቀጠር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ አይፈቅድም፡፡ አሰራሩ በተለያዩ የክርክር ሂደቶች የሚሰጡ ትዕዛዞችንም በአንድ ላይ በመስጠት ሥነ-ሥርዓት ሕጉ የክርክር ሂደት ላይ ብዥታን ይፈጥራል፡፡ ለምሳሌ፡-በሥነ-ሥርዓት ሕጉ የተለያዬ ሂደት ያላቸዉን   የጽሁፍ መልስና ማስረጃዎቹን የማቅረብ መብትን ማለፍ (default proceeding) እና በሌለበት (ex-parte) በአንድ ቀጠሮ እንዲሰጡ የማድረግ ዉጤትን ይፈጥራል፡፡ መጥሪያ ባልደረሰ እና ተለዋጭ ትዕዛዝ በሚሰጥበት ወቅትም ክስ ለመስማት የተቀጠረዉን ቀጠሮ  ቀይሮ ወደ ኋላ ይመልሰዋል፡፡  በተጨማሪም ሕጉ በሚያስቀምጠዉ መሰረት በቀጠሮዉ ዕለት መሰጠት ያለባቸዉ ትዕዛዞች በሙሉ እንዳይሰጡ ያደርጋል፡፡ ይህ አሰራር  ደግሞ ሥነ-ሥርዓታዊ ካለመሆኑ በተጨማሪ ለአንድ ቀጠሮም ቢሆን ክርክሩን የማራዘም ዉጤት ይኖረዋል፡፡ ተከራካሪ  ወገኖችንም ለድካም እና ለእንግልት ይዳርጋል፡፡

ሐ. ክስ መስማት

ከክስ መስማት ጋር በተገናኘ በተለይም የክስ የመጀመሪያ ደረጃ  መቃወሚያ በቀረበበት ክርክር  በተለያየ መልኩ ክሱ ሲሰማ ይስተዋላል፡፡ አብዛኛዉ በሚባል ደረጃ በፍርድ ቤቶች ያለዉ አሰራር  ክስ  ሁለት ጊዜ የሚሰማ ሲሆን መቃወሚያዉ እና ፍሬ ነገር ክርክር ተብሎ በመነጣጠል የሚሰማ ነዉ፡፡ በፍሬ ነገሩ/በዋናዉ ጉዳይ ላይ ክስ የሚሰማዉ የክስ መቃወሚያዉ ከታለፈ ብቻ ሲሆን የክስ መቃወሚያ በፍሬ ነገሩ ወይም በዋናዉ ጉዳይ ላይ ከመገባቱ በፊት መወሰን አለበት ከሚል አስተሳሰብ የመጣ ነዉ፡፡ ይህ አሰራር እያደበረ በመምጣቱ ተገቢነቱና አዋጭነቱ  ከሥነ-ሥርዓት ሕጉ እና ዓላማዉ  አንፃር መዳሰስ አስፈላጊ ነዉ፡፡

ክስ የሚሰማዉ በጽሑፍ ክስ እና መልስ ተሰብስቦ እንዳበቃ ቀጥሎ ባለዉ የመጀመሪያዉ ቀነ ቀጠሮ እንደሆነ ግልፅ ነዉ፡፡  ክስ የሚሰማበት ሂደት በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 241 በተቀመጠዉ መሰረት ሲሆን ተከራካሪ ወገኖች አለመቅረባቸዉ የሚያስከትለዉን ዉጤት የሚገልጹት ድንጋጌዎች የፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 69(2)፣70(ሀ) እና 73 ክርክሩ እንዲሰማበት የተወሰነዉ ዕለት የሚሉትም ከመልስ መቀባበል ቀጥሎ ያለዉን የመጀመሪያ ቀነ ቀጠሮ  ነዉ፡፡ በዚህ ዕለት ተከራካሪዎች ስላቀረቡት ክስ እና መልስ ግልጽ ያልሆነዉን ነገር ግልጽ እንዲደርጉ የሚመረመሩበት፣እምነት እና ክህደት ቃላቸዉን የሚሰጡበት እና ስለክርክራቸዉ ማብራሪያ እንዲሰጡ የሚደረጉበት ነዉ፡፡ ይህ የክርክር ደረጃ በክስና መልስ የተጠቀሱ ነገሮች ማስረጃዎችን ጨምሮ ክርክር የሚቀርብበት ሂደት ነዉ፡፡ የክስ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያም ቀርቦ ከሆነ የመልሱ አካል እስከሆነ ድረስ ክርክር ይደረግበታል፡፡ በፍሬ ነገር ደረጃም የግራ ቀኙን ክስና መልስ መነሻ በማድረግ የሚመረመረዉ በዚሁ ዕለት ነዉ፡፡ ይህ የክርክር ደረጃ አንድ ቀን የሚደረግ ለመሆኑ ከድንጋጌዉ በግልጽ መረዳት የሚቻል ነዉ፡፡ የክስ መሰማቱ ሂደት እንደተጠናቀቀ ቀጣዩ የሚሆነዉ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ቀርቦ ከሆነ መቃወሚያዉን አስቀድሞ መወሰን መቃወሚያ ካልቀረበ ለክርክሩ መሪ ጭብጥ በመያዝ ማስረጃ የማሰማት ወይም ዋና ሙግት ሂደቱ ይቀጥላል፡፡ የፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 244(1) በግልጽ እንደሚያመላክተዉ  በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ ዉሳኔ የሚሰጠዉ ማስረጃ ተቀብሎ ከመመርመሩ  በፊት ወይም ምስክሮች ከመሰማቱ በፊት እንደሆነ ነዉ፡፡ ይህ ድንጋጌ በግልጽ የክስ መቃወሚያ ሊወሰን የሚችለዉ  ማስረጃ ተቀብሎ ከመመርመሩ ወይም ምስክር ከመሰማቱ በፊት እንደሆነ የሚገልፅ እንጅ በዋናዉ ጉዳይ ላይ ክርክር ከመደረጉ በፊት አይልም፡፡ ሕጉ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እና የፍሬ ነገር ክርክርን በሁለት ደረጃ ከፍሎ ማከራከር አስፈላጊ እንደሆነ ታስቢ አድርጎ ቢሆን ኖሮ የፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 244(1) ድንጋጌ መቃወሚያዉ ከፍሬ ነገር ክርክሩ በፊት መወሰን አለበት በማለት ያስቀመጥ ነበር፡፡ ድንጋጌዉ በግልፅ የሚያመላክተዉ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 241 መሰረት ክሱና መልሱ ላይ የቀረበዉ ጠቅላላ ነገር በክስ መስማቱ ዕለት መጠናቀቅ እንዳለበት ሆኖም በፍሬ ነገሩ ጭብጥ ተይዞ ማስረጃ ከመሰማቱ በፊት መቃወሚያዉ መወሰን እንዳለበት የሚገልፅ ነዉ፡፡ ይህን የሚያጠናክረዉ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 246(1) የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዉ እንደተወሰነ ፍርድ ቤቱ የሚያደርገዉ ስራ  ቀጣዩን የክርክር ሂደት የሚመራዉን የክርክር ጭብጥ መለየት እንደሆነ የሚገልፀዉ ነዉ፡፡ እነዚህ ድንጋጌዎች ከፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 241 ጋር በጥምረት ሲታዩ ክስ የመስማት ዕለት አንድ ጊዜ እንደሆነ፣ ክስ የሚሰማዉም ግራ ቀኙ በክሳቸዉና በመልሳቸዉ እንዲሁም ማስረጃቸዉን መነሻ በማድረግ እንደሆነ፣በዕለቱ ግልጽ ያልሆነን ነገር ማብራራት፣የሚታመን እና የሚካድን በመጠየቅ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያም የመልስ አካል እንደመሆኑ ክስ በሚሰማበት ክርክር ተደርጎበት የሚጠናቀቅ ሲሆን የፍሬ ነገሩ ክርክርም በዕለቱ የሚያልቅ ነዉ፡፡ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ መቃወሚያዉ ቀድሞ እንዲወሰን የሚያስቀምጠዉ በፍሬ ነገሩ ላይ ጭብጥ ተይዞ ማስረጃ ከመሰማቱ እና ከመመርመሩ በፊት እንደሆነ እንጅ ክርክሩን ከፍሬ ነገሩ ተነጥሎ እንዲታይ በሚል አይደለም፡፡

በተግባር የሚታየዉ እና እንደ ሕግ እየዳበረዉ የመጣዉ አሰራር ግን ከሕጉ ጋር አብሮ የሚሔድ አይደለም፡፡ አሰራሩ ክስ መስማትን የመቃወሚያ እና የፍሬ ነገር ክርክር ብሎ በሁለት ደረጃ የከፈለ ነዉ፡፡ ይህ አሰራር በዋናነት ሶስት መሰረታዊ ችግሮችን ይፈጥራል፡፡

አንደኛዉ ከሕግ ዉጪ መመራትን ያስከትላል፡፡ ሕጉ በግልፅ ክስና መልስ መቀባል ቀጥሎ ያለዉን የመጀመሪያ ቀነ ቀጠሮ ክርክሩ የሚሰማበት ወይም ክስ የሚሰማበት ዕለት በማለት ለዚህም የፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 241 በአንድ ጊዜ ክስ ተሰምቶ የሚሰማበትን ሂደት አስቀምጦ እያለ ክስ መስማትን በሁለት ዘርፍ መክፈል ከሕግ ዉጪ  የሆነ አሰራር ነዉ፡፡ ይህ ደግሞ ፍርድ ቤቶችን በሥነ-ሥርዓት ሕግ ከመመራት  ይልቅ ከሥነ-ሥርዓት ዉጪ የመመራት ባህል እንዲያዳብሩ ያደርጋል፡፡

ሁለተኛዉ የክርክር ሂደት መፋለስን ያስከትላል፡፡ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 69፣70(ሀ) እና 73 መሰረት ክስ በሚሰማበት ዕለት ተከራካሪዎች ሳይቀርቡ ሲቀሩ የሚያስከትለዉ ዉጤት በግልጽ ተመላክቷል፡፡ ዉጤቱ ተከሳሹ ከቀረ በሌለበት ክርክሩ እንደሚቀጥል፣ተከሳሽ እና ከሳሽ ሳይቀርቡ ሲቀሩ መዝገቡ ሊዘጋ እንደሚችል ተደርጎ ተቀምጧል፡፡ ክስ መስማቱ በመቃወሚያዉ እና በፍሬ ነገር ላይ ተነጣጥሎ የሚሰማ ከሆነ ተከራካሪዎች ሳይቀርቡ ቢቀሩ በሌለበት ክርክሩ የሚቀጥለዉ ወይም መዝገቡ የሚዘጋዉ ለየትኛዉ ክርክር እንደሆነ ለመፈፀም ያስቸግራል፡፡ በዚህ ሁኔታ ተከሳሹ በሌለበት ክርክሩ እንዲቀጥል ሊወሰን የሚችለዉ በመቃወሚያ ክርክር ወቅት ሲቀር  ነዉ ወይስ በፍሬ ነገር ክርክር ወቅት ሲቀር የሚለዉ ምላሽ መስጠትም አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ በተግባር እንደሚገጥመዉ በመጀመሪያ ቀነ ቀጠሮ  በሚደረገዉ መቃወሚያ ክርክር ቀርቦ ክርክሩን ያደረገ ተከሳሽ በፍሬ ነገር ክርክር ወቅት ሲቀር በሌለበት ክርክሩ እንዲቀጥል ይባላል፡፡ እንደ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ የመጀመሪያ ቀነ ቀጠሮ የሚባለዉ ክስና መልስ መቀባባል አብቅቶ ክሱ የሚሰማበት የመጀመሪያዉ ቀን ነዉ፡፡ በዚህ ቀን የቀረበ ተከሳሽ ክሱ በሚሰማበት ዕለት የተገኘ በመሆኑ በሌለበት ክርክሩ ሊቀጥል አይችልም፡፡  ሆኖም በአሰራር በተፈጠረዉ ሁለተኛ የክርክር ደረጃ ወይም የፍሬ ነገር ክርክር ወቅት አልቀረበም ተብሎ በሌለበት ክርክሩ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡ በሌላ በኩልም በጀመሪያዉ ቀነ ቀጠሮ ሳይቀርቡ የቀሩ ተከራካሪዎች በመጀመሪያ ቀነ ቀጠሮ አለመቅረባቸዉ ተመዝግቦ ክርክሩ በሌሉበት እንዲቀጥል ወይም ከሳሽ ከሆነ እንዲዘጋ ማድረግ እየተቻለ ምንም ሳይባል የመቃወሚያዉን ክርክር አሳልፎ በሁለተኛ ምዕራፍ በሚደረገዉ የፍሬ ነገር ክርክር ሲቀርብ የክርክሩ አካል ሆኖ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡ እንደ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ቢሆን ተከሳሽ በሌለበት ክርክሩ እንዲቀጥል ወይም ከሳሽ ከሆነ መዝገቡ እንዲዘጋ የሚደረገዉ ከመልስ ማቀባባል ቀጥሎ ባለዉ የመጀመሪያ ቀጠሮ ካልቀረበ ነበር፡፡ ያለዉ አሰራር ግን ሁለት የክርክር ቀን የዘረጋ በመሆኑ በአንዱ ያመለጠዉ በሌላዉ የሚገባበት፣የመጀመሪያዉን ቀጠሮ አክብሮ የቀረበ ወገን በሁለተኛዉ የክርክር ዘርፍ ባለመገኘቱ ከክርክሩ ዉጪ የሚደረግትን ወጥነት የሌለዉ አሰራር እንዲዘረጋ አድርጓል፡፡ ይህ የሆነበት ዋና ምክንያት ሕጉ አንድ ጊዜ ያደረገዉን ክስ መስማት በልምድ ሁለት ጊዜ እንዲደረግ በመደረጉ ነዉ፡፡

ሶስተኛዉ ችግር ለቀጠሮ መራዘም እና መጓተት ምክንያት መሆኑ ነዉ፡፡ የሥነ-ሥርዓት ሕግ ዋና ዓላማዉ ክርክሮች በተፋጠነ፣ግልጽ እና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ ክርክሮች እንዲቋጩ ማድረግ ነዉ፡፡ ይህን ለማሳካትም በሥነ-ሥርዓት ሕጉ የተቀመጠዉ የእያንዳንዱ ቀጠሮ ጊዜዉ እና ሂደቱን ጠብቆ በጥብቅ መፈፀምን ይጠይቃል፡፡ ከሥነ-ሥርዓት ዉጪ ክስ መስማትን የመቃወሚያ እና የፍሬ ነገር ክርክር ብሎ በሁለት ዘርፍ ማከራከር በአንድ ቀን የሚያልቅን ስራ በሁለት ቀን እንደመስራት የሚያስቆጥር ነዉ፡፡ ይህ አሰራር ደግሞ የፍርድ ቤቶችን ጊዜ እና አቅም ከማባከኑ በተጨማሪ ተከራካሪ ወገኖች ላልተፈለገ ጊዜ ክርክራቸዉ እንዲራዘም ያደርጋል፡፡  በተጨማሪም የክርክሩ ዘርፍ በመቃወሚያ እና በፍሬ ነገር ተብሎ የሚከፈል በመሆኑ በመሃከል ያልተፈለጉ መጓተቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት ይሆናል፡፡

እንደ መዉጫ!

በተነሱት ሶስት ጉዳዮች ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ማስተካከል የሚቻለዉ ሕጉን እንደ ተፃፈ በመተግበር መሆኑ የሚታመን ቢሆንም በአንዳንድ ሁኔታዎች ላይ ችግሩን ለመፍታት ሕጉን እና አሰራሩን ማቀናጅትና ማስተሳሰር ይጠይቃል፡፡ የመጀመሪያዉን ጉዳይ በተመለከተ በተከራካሪዎች የሚቀርቡ ክርክሮችን ከመጀመሪያዉ ጀምሮ ማስረጃዎችንም የሚያካትት መሆን ይኖርበታል፡፡ ከሳሽ በማስረጃ ዝርዝሩ በፍርድ ቤት እንዲቀርብለት የሚጠይቀዉ ማስረጃ ካለ አስቀድሞ ማስረጃዉ ተሰብስቦና ተጠቃሎ ተከሳሹ መልስ እንዲሰጥበት ሊደረግ ይገባል፡፡ ተከሳሹም መልስ ሲሰጥ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲቀርብለት የሚጠይቀዉ ማስረጃ ካለ መልስ ማቅረቡን ተከትሎ ማስረጃዉ ቀድሞ እንዲቀርብ እና የክስ መስማቱ አካል እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በክርክር ሂደት ለትክክለኛ ፍትሕ  አስፈላጊ ሲሆን ማስረጃ እንዲቀርብ የሚደረግበት ሁኔታ ቢኖርም ማስረጃ የማሰባሰቡ ስራም ከክስ መስማት በፊት ሊጠናቀቅ ይገባል፡፡ ይህንን ማድረግ ከተቻለ ክርክሩ ከተጠናቀቀ በኋላ የሰነድ ማስረጃ እንዲቀርብ እየተባለ የሚሰጠዉን እና ከዋናዉ ክርክር ያልተናነሰ መመላለስ የሚፈጀዉን ሌላ የክርክር ምዕራፍ ማስቀረት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም ፍርድ ቤቶች በተከራካሪዎች ጠያቂነት የሚመጡ ማስረጃዎች ተከራካሪዎች ራሳቸዉ ማቅረብ የማይችሏቸዉ መሆናቸዉን ማረጋገጥና መመርመር ይኖርባቸዋል፡፡ ይሄም ፍርድ ቤቶች አከራክሮ የመወሰን ሚናቸዉን እንዲያስጠብቁ ይረዳል፡፡

ሁለተኛዉ ጉዳይ በተመለከተ ከፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 238(1) ድንጋጌ ይዘት እና ክስና መልስ በሬጅስትራር ተመርምረዉ እንዲቀርቡ ከሚደረግበት ዓላማ  አንፃር በሬጅስትራር በኩል መልስ የማቀባበል ስራ መሰራቱ ተገቢነት አጠያያቂ ሊሆን የሚገባ አይደለም፡፡ ሆኖም አሰራሩን ከሥነ-ሥርዓት ሕጉ ጋር አዋህዶ መፈፀም የማይቻል ከሆነ ክርክሩ ላይ አሉታዊ ዉጤት ይኖረዋል፡፡ መልስ በሬጅስትራር በሚቀባበልበት ዕለት የቀጠሮ ምክንያት ባለመፈፀሙ ወይም የሚቀርቡ መልሶችን ተከትሎ  ተለዋጭ ትዕዛዝ መስጠት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ በዕለቱ መዝገቡ ዳኛዉ ፊት ቀርቦ ትዕዛዝ የሚሰጥበት ሁኔታ እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ማድረግ ዳኞች ከሚኖራቸዉ የቀጠሮ ፖሊስ ወይም በዕለቱ ሊኖራቸዉ ከሚችለዉ ሌላ ስራ አንፃር ምቹ ሊሆን እንደማይችል የሚጠበቅ ቢሆንም ሥነ-ሥርዓት ሕጉ  የሚለዉ እንዲፈጸም ከተፈለገ ብቸኛ አማራጭ በዕለቱ  ትዕዛዝ እንዲሰጥ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ተግባራዊ ማድረግ ካልተቻለ አሰራሩ በክርክሩ ከሚኖረዉ አዎንታዊ ዉጤት ይልቅ አሉታዊ ዉጤቱ እንዲጎላ ያደርገዋል፡፡ መልስ ለመቀበል በተቀጠረበት ዕለት መሰጠት ያለባቸዉ ትዕዛዞች በቀጠሯቸዉ ቀን እንዲሰጡና የተገለፁት ችግሮች እንዲቀረፍ መልስ የማቀባበሉ ስራ በችሎት ሊሆን የሚገባዉ ነዉ፡፡

ሶስተኛዉ ጉዳይ መቃወሚያ እና ፍሬ ነገርን ለያይቶ ክስ የሚሰማበት ስርዓትን በተመለከተ ሕጉ ግልጽ እና የማያሻማ በመሆኑ ሕጉን መተግባር ያስፈልጋል፡፡ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ቀድሞ መወሰን አለበት በማለት በግልፅ ያስቀመጠዉ ክስ የሚሰማበትን ቀን ከሁለት ለመክፈል አስቦ ሳይሆን በፍሬ ነገሩ ላይ ማስረጃ ከመሰማቱ እና ከመመዘኑ በፊት በመቃወሚያ የሚቋጭ ከሆነ በአጭር ዕልባት እንዲያገኝ በሚል ነዉ፡፡ ክስና መልስ ሲሰማ በክሱና መልሱ የተጠቀሱ መከራከሪያዎች ሁሉ ተነስተዉ ክርክር የሚደረግባቸዉ እንደመሆኑ ክስ መስማቱን ለመቃወሚያ እና ለፍሬ ነገር ብሎ መክፈል አያስፈልግም፡፡ ከክስ መስማት ቀጥሎ ያለዉ የክርክር ሂደት ዋናዉ ሙግት የሚጀመርበት ወይም ግራ ቀኙ በፍሬ ነገሩ ላይ በተያዘዉ ጭብጥ ላይ ማስረጃዎቿቸዉ የሚያስረዱላቸዉን ነገር እያስመዘገቡ ማስረጃ የሚያሰሙበት የክርክር ሂደት እንደሆነ ግልፅ ነዉ፡፡ መቃወሚያዉ ቀድሞ መወሰን አለበት የሚባለዉም ፍሬ ነገሩን መነሻ በማድረግ ማስረጃ ከመሰማት ወይም ከመመርመሩ በፊት እንጅ በፍሬ ነገሩ ላይ ክርክር ከመደረጉ በፊት አለመሆኑን መረዳትና ሥነ-ሥርዓቱን በትክክል መተግበር ያስፈልጋል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የሕገ-መንግሥት ፍርድ ቤት፡ የብሔርና ብሔረሰቦች ሉዓላዊነት መቃብር
አዲሱ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ 1234/2013 ምን አዲስ ነገር ይዟል - በ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 18 September 2024