Font size: +
6 minutes reading time (1251 words)

በሕግ አምላክ!

አገሬው ስለ ሕግ ሃያልነት ሲናገር "በሕግ አምላክ ሲባል እንኳን ሰው ወራጅ ውሃ ይቆማል" ይል ነበር፡፡ ሕግ ተፈጥሮንም እስከማቆም ሃይል እንዳለው አድርጎ ለመግለፅ ምን ዓይነት በሕግ የፀና እምነት ቢኖር ነበር ያስብላል፡፡ በሕግና ፍትሕ ላይ እምነት ያለው ሕዝብ ያለማንም አስገዳጅነት ለሕግ ተገዢ ነው፡፡ ክስተቶችንም ተከትሎ ለሕግ ያለውንም እምነት በተለያዬ መንገድ ይገልፃል፡፡ ግጭቶችን በጉልበት ከመፍታት በሕግ መፍታት ተመራጭ እንደሆነም ያምናል፡፡ በጉልበቱ አዳሪ ሲገጥመው ሰይፍን በሰይፍ ከመመለስ በሕግ አምላክ ቢል ይመርጣል፡፡ ከማትረባ ጉልበት በሕግ አምላክ ይሻላል የሚለውም ለዚህ ይመስላል፡፡ ስለዚህ የሕግ መከበር ሕበረተሰቡ ስለሕግና ፍትሕ ባለው አመለካከት ይወሰናል ማለት ነው፡፡ ሕግ በሕበረተሰቡ ውስጥ በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ እንዲያመጣ ከተፈለገ እያንዳንዱ ሰው ስለሕግ ያለው አመለካከት አብሮ መመለወጥና ማደግ ይኖርበታል፡፡ ሕበረተሰቡ ለሕግና ፍትሕ ያለው አመለካከት ሁለት ነገሮችን ይገልፅልናል፡፡ በአንድ  በኩል ሕብረተሰቡ ስለሕግ ያለውን እምነት ሲገልፅልን በሌላ በኩል ደግሞ የሕግ መከበር ያለበትን ደረጃ ያሳየናል፡፡

ዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት ሳይዋቀር በፊት አገሬው ስለሕግ የበላይነት የፀና እምነት ነበረው ማለት እንችላለን፡፡ አስገዳጅ ነገር ሳይኖር በአገር ደንብ ብቻ መንገድ ላይ ባላጋራውን ሲያገኘው በሕግ አምላክ ብሎ ተላላፊው መንገደኛ ጉዳዩን እንዲመለከትለት ያደርግ ነበር፡፡ ተላላፊው መንገደኛም ዳኝነቱን ተቀብሎ የግራ ቀኙን ጉዳይ ሰምቶ ይፈርዳል፡፡ ውሳኔው ከተስማማቸው ይፈጽማሉ ካልተስማቸው በአካባቢው ወዳለው ጭቃ ሹም ተያይዞ መሄድ ነው፡፡ ይህን ተላላፊ መንገደኛ ዳኛ የሕግ ሙሁር አበራ ጀንበሬ የመንገድ ዳሩ ፍርድ ቤት(የመንገድ ዳር ዳኛ) በማለት ሲገልፁት ከሳቴ ብርሃን የአማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ "ዳኛ የውሃ ወራጅ ዳኛ" በማለት ይገልፀዋል፡፡ ስያሜው ምንም ይሁን ተላላፊውን መንገደኛ ዳኛ፣ ባላጋራዎችን ተከራካሪ አድርጎ ሲያቆማቸው የነበረው ያገር ደንብና ልማድ፣ፈቃደኝነትና ለሕግና ፍትሕ የፀና እምነት መኖር  እንጅ ሌላ አስገዳጅ ሃይል አልነበረም፡፡

ሕዝብ ስለሕግና ፍትሕ ባለው የፀና እምነት ብቻ አገር ይዳኝ እንደነበር ሌላ ምሳሌ እንመልከት፡፡ በአዶልፍ ፓርለሳክ ተፅፎ ተጫኔ ጆብሬ መኮንን በተረጎመው የሃበሻ ጀብዱ መፃፍ የተገለፀ ነገር ነው፤ ታሪኩ 1928 ዓ.ም  አካባቢ አዲስ አበባ ገበያ ላይ የተመለከተው ነበር፡፡ ለአንባቢ እንዲመችና የነገሩን ሥር እንዳልስተው ቢረዝምም ተርጓሚው እንደፃፈው ሙሉ ታሪኩን ላስቀምጠው፡-

"በጨርቅ ተራ ሁለት ገበያተኞች ይጨቃጨቃሉ፤ጨርቁን የሚገዛው ሰውየ እጅግ በጣም ረጅም ሲሆን ሻጩ ደግሞ በጣም አጭር ነው፡፡ እናም ገዥ በሚችለው መልኩ ክንዱን ዘርግቶ፣ጣቶችን ወጥሮ አስር ክንድ ለካና ምልክት አደረገ፡፡ ሻጩ ደግሞ በሚችለው ሁሉ ጣቶችን ወጥሮ አስር ክንድ ለካና እሱም ምልክት አደረገ፡፡ ሁለቱ በለኩት መካከል ከአንድ ክንድ የሚበልጥ ልዩነት መጣ፡፡ ገዥው ሻጩን አውቆ ክንዱን ሳይወጥር ይለካል ሲል አመረረ፡፡ ሻጩ በምኒልክ እየማለ ሃቀኛ ነጋዴ መሆኑን እግዚአብሔርን ምስክርነት ጠራ፡፡ በዚህ መሀል ብዙ ወሬኛ ገበያተኞች ከበቧቸው፡፡ በነዚህ ወረኞች ፊት ሁለቱም ደጋግመው ቢለኩም ልዩነቱ ተመሳሳይ ነበር፡፡ እናም መግባባት ባለመቻላቸው ያላቸው ብቸኛ አማራጭ ዳኛ ፍለጋ መሄድ ነበርና ሸማቸውን አያይዘውና አቆላልፈው፣ ጎን ለጎን ግራና ቀኝ እጃቸውን በነጠላቸው ጫፎች ሸብ አድርገው አስረው ከቋጠሩ በኋላ ወደ ገበያው ሽምጋይ ዳኛ በብዙ ወረኞች ታጅበው ሄዱ፡፡

ብቸኛው የገበያው ፈላጭ ቆራጭ ዳኛ ከፍ ብላ ከተሰራች አንዲት ባለ ሁለት ቆርቆሮ መደብር ላይ ተኮፍሶ ተቀምጧል፡፡ የሚንጫጫውን ወረኛ ፀጥ ካሰኘ በኋላ በትዕግስት ሁለቱንም ባለጉዳዮች አዳመጠ፡፡ ሁለቱም በእምዬ ምኒልክ እየማሉና እግዜሩን ምስክርነት እየጠሩ ችግራቸውን ለዳኛው አስረዱ፡፡ ገዥም ሻጭም ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እየጮሁ ዳኛውን ለማሳመን ሞከሩ፡፡ ዳኛው ሁለቱን በትዕግስት ካዳመጠ እና ከቦ የሚያዳምጠውን የገበያ ወረኛ ዝም ካስበለ በኋላ፣ ወደ ሁለቱ ባለጉዳዮች እያየ መጀመሪያ ገዥው አስር ክንድ እንዲለካና ምልክት እንዲያደርግ አዘዘው፡፡ ወዲያው ሻጩንም አስር ክንድ እንዲለካና ምልክት እንዲያደርግ አዘዘው፡፡ሁለቱም ጨርቁን ለክተው ምልክት አድርገው እንደጨረሱ ዳኛው ጨርቁን ተቀብሎ፣ መጀመሪያ ገዥው ለክቶ ምልክት ያደረገበት ቦታ ላይ በመቀስ ቆረጠው፡፡ ወዲያው ቀጥሎ ሻጩ ምልክት ያደረገበት ቦታ ላይ ቆረጠውና ሁለቱም እውነታ አላቸው፣ እግዚአብሔር ያውቃል አለና ፍርዱን ሲሰጥ፣ በእምዬ ምኒልክ ሁለታችሁም እውነት አላችሁ፡፡ ግን እንዳትጣሉ፡፡ ገዥው በሻጩ አጭር ክንድ መስማማት ስላለበት፣ ነጋዴውም ከዚህ ትርፍ እንዳያገኝ ልዩነት ያመጣውን ጨርቅ ለዳኝነቱ ዋጋ ለራሱ አስቀርቶ ሁለቱን ባለጉዳዮች አሰናበታቸው፡፡ በዳኛው ፍርድ ሁለቱም ተደስተዋል፡፡ ነጋዴው ገዥው ሰውየ በእሱ አጭር ክንድ የተለካ ጨርቅ በመግዛቱና በረጅሙ ክንድ ባለመጠቀሙ፣ ገዥው ደግሞ ነጋዴው ባለችው አጭር ክንድ እየለካ ከፍ ያለ ትርፍ ባለማግኘቱ፣ ወረኞችም ሳምንቱን ሙሉ የሚያወሩት ወሬ በማግኘታቸው፣ ዳኛውም ከጨርቋ በተጨማሪ ጥቂት ቤሳ ሳንቲሞች በመስራቱ፣ ብቻ ሁሉም ተደስተው ዳኝነቱ ተበተነ፡፡ የንጉሥ ሰሎሞንን ፍርድ የሚያስተካክል ፍርድ ይልወታል ይኼ ነው፡፡" በማለት ያየውን ፅፏል፡፡ ይህ ትልቅ ምሳሌ ነው፡፡ ሻጩም ገዡም ፍላጎታቸው ባይሞላም ገለልተኛ የሆነ አካል ስለዳኛቸው ደስ ብሏቸው ውጤቱን ተቀብለዋል፡፡  ለሕግና ፍትሕ በጎ አመለካከት ማለት እንዲህ ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ ያለማንም አስገዳጅነት ወዶ ለሕግ  ተገዥ  መሆን ማለት ነው፡፡

ሕዝብ በሕግና ፍትሕ የፀና እምነት ሲኖረው ያለማንም አስገዳጅነት ሕግንና ዳኝነትን ያከብራል፡፡ ዳኝነቱ ትክክል ባይሆንም እንኳ ለአገር ደንብ ሲል ውጤቱን ይቀበላል፡፡ በፍርድ ከሄደው በቅሎው  ይልቅ ያለፍርድ የሄደው ቆሎው የሚያንገበግበው ለሕግ ያለው ትልቅ ክብርና እምነት ነው፡፡  እንዲህ ዓይነት የዳበሩ  የልማዳዊ ሕግ አሰራር እና የተጠየቅ ሙግት የአማራ ባህላዊ ቅርስ እንደነበርና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎችም ይታይ እንደነበር ብዙ አጥኝዎች ገልጸዋል፡፡ ልምዱም እንዳይቀር በሕግ ደረጃም እውቅና ተሰጥቶትም ነበር፡፡  በ1934 ዓ.ም የወጣውና ስለፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥራ አካሄድ ለመወሰን የወጣ አዋጅ አንቀፅ 23 ደንበኛ ፍርድ ቤት በያለበት እስኪቋቋም ድረስ ገና ካልቆመበት ቦታ ላይ ትናንሹን ነገር እንደ አገር ልማድ  በኢትዮጵያ ሕግ እንዲታይ በእርቅም መንገድ ለመጨረስ እንዲቻል አዋጁ አይፀናበትም በማለት አስቀምጦ ነበር፡፡ የፍትሕ ተቋሞች በዘመናዊ መልኩ ሳይደራጁ ገና  ሕዝብ በአገር ደንብና ልማድ ብቻ ይዳኝ ነበር፡፡ ጥናት ቢጠይቅም ለሕግ የነበረውም ከበሬታ በአገር ደንብና ልማድ በሚዳኝበት ጊዜ የነበረው ከአሁኑ የሚሻል ይመስላል፡፡ አሁን በሕግ አምላክ ሲባል ሰው አይደለም ወራጅ ውሃ ይቆማል ብሎ የሚያስብ ፈልጎ ማግኘት ይከብዳል፡፡ በሕግ አምላክ ቁም ቢባል ሂድ ክሰስ የሚለው ወይ የሚሮጠው ይበዛል፡፡ ጭራሽ ተላላፊውን መንገደኛ ዳኛ አድርጎ ጉዳይን  መፍታት የማይቻል ነው፡፡ ምናልባት የፍትሕ ተቋሞች ስላሉ ይሆናል፡፡ ቢሆንም በፍትሕ ተቋሞችም በሕግ አምላክ ተብሎ ሲቀርብ ለሕግና ፍትሕ ያለው አመለካከት በጎ ስለሆነ የሚቀርበው ጥቂቱ ነው፡፡ በፍትሕ ተቋሞች ከሚቀርበው የሚበዛው ባለመቅረብ የሚመጣውን ሃላፊነትና ቅጣት በመፍራት ይመስላል፡፡ በፍርሐት ሕግን ማክበር ጤናማ አይመስልም፡፡ ሕግ ማክበር አንዱ የግብረ ገብ ግዴታና የመልካም ዜጋ መገለጫ ነው፡፡ ሕግን ሲመቸኝ አከብረዋለሁ ሳይመቸኝ እጥሰዋለሁ የሚል አመለካከት ትክክል አይደለም፡፡ ትክክል እና ፍትሐዊ ያልሆኑ ሕጎችን ማክበር ተገቢ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ክርክር እንዳለ ሆኖ ሕግን ማክበርና በጎ አመለካከት መኖር ለአንድ ማሕበረሰብ አስፈላጊው ነገር ነው፡፡  ያኔ ዘመናዊ የፍትሕ ተቋሞች ሳይኖሩ ዳኝነት በአገር ልማድና ደንብ ሲሰጥ በነበረበት ወቅት ሕዝቡ ስለሕግና ፍትሕ በጎ አመለካከት ነበረው፡፡ ሕግን የሚያከብረው አስገዳጅ ተቋም በሌለበት ሁኔታም ነበር፡፡

ሕግን የሚያስከብሩ የፍትሕ ተቋሞች እና አስፈፃሚ ሃይል ከተደራጀ በኋላ ሰው ለምን ለሕግና ፍትሕ በጎ አመለካከቱ ቀነሰ የሚያስብል ጥያቄ ይነሳል፡፡ ይህ ጉዳይ በራሱ ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ ነው፡፡ ሆኖም ግን ሕዝብ በሕግና ፍትሕ የፀና እምነት የሚኖረው በምን ሁኔታ ውስጥ እንደሆነ በመዳሰስ ምላሹን ልናገኘው እንችላለን፡፡  ሕግ በፈቃደኛነት የሚከበረው እኔን ይጠብቀኛል ሌላውንም ያስከብራል የሚል አስተሳሰብ መነሻ አድርጎ ነው፡፡ ሕግ ጥቅሜን ያስጠብቃል ከክፉም ይከላከለኛል የሚል አስተሳሰብ ካለ ሕዝብ ያለማንም አስገዳጅነት የተፈቀደውን በማድረግ የተከለከለውን በመጠየፍ ለሕግ ያለውን ተገዥነት ያሳያል፡፡ የፍትሕ ተቋሞችም ቢሆኑ ሕጉን ተከትለው ጥቅሜን ያስከብራሉ ከጥቃትም ይከላከሉልኛል የሚል አስተሳሰብ ሲኖር ሕዝብ ፍትሕን በራሱ ከመስጠት ይልቅ ጉዳዩን ወደ ፍትሕ ተቋሞች በማቅረብ ያለውን እምነት ይገልፃል፡፡ በራስ እጅ ፍትሕ መስጠት፣ ጉቦ፣ መደለያ እና ሌሎች ያልተገቡ አካሄዶችን በመጠቀም ፍትሕ ለማግኘት የሚሞከረው ከሌላ ምክንያት በመነሳት አይደለም፡፡ ዋናው ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ቢሆንም ሌላው ጎኑ በፍትሕ ተቋሞች ላይ ያለ የላላ እምነት ነው፡፡ ፍትሕ ተቋሞች ጥቅሜን አያስከብሩልኝም የሚል እምነት ባልተገባ መንገድ ፍትሕን ለማግኘት መነሻ ምክንያት ይሆናል፡፡ አንድ ማሕበረሰብ ለሕግ አምላክ ለሚለው ምልጃ ተገዢ የሚሆነው በሕጉና በፍትሕ ሥርዓቱ የባለቤትነት ስሜት ሲኖረውና የሚሰሩት ለእኔ ነው ብሎ ማመን ሲጀምር ነው፡፡ ይህ የኔነት ስሜት ካልተፈጠረ ሕግን የሚያከብረው የግብረ ገብ ግዴታ ስለሆነ ሳይሆን በፍርሐት ነው፡፡ለፍትሕም በጎ አመለካከት አይኖረውም፡፡

 

እንደ መውጫ

 

የሕግ መኖር ዋና ዓላማው የረገና ሰላማዊ የሆነ ሕብረተሰብ መፍጠር ነው፡፡ ውጤቱ እንዲያምርም ሕብረተሰቡ ስለሕግና ፍትሕ ያለው አመለካከት ወሳኝነት አለው፡፡ ሕዝብ ሕግን ወዶ እና ፈቅዶ ሲያከብረው እና ፈርቶ ሲያከብረው ያለው ውጤት ይለያያል፡፡ በፈቃደኛነትና ወዶ ሕግን የሚያከብር ሰው ሕግን ማክበር የግብረ ገብ ግዴታ እንደሆነ የሚያምን ነው፡፡ በሁሉም ቦታና በሁሉም ሁኔታዎች ሕግን ስለሚያከብር የሕግ መከበር ደረጃው ከፍተኛ ይሆናል፡፡ በፍርሐት ብቻ ሕግን ማክበር ግን በሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ ስለሆነ አጋጣሚው ሲገኝ ሕጉ ስለማይከበር ለማሕበረሰብ አደገኛ ነው፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው ስለሕግና ፍትሕ በጎ አመለካከት መኖሩ ለሕግ መከበር ቀዳሚ ሁኔታ ነው፡፡ ይህንን በጎ አመለካከት ለመፍጠር ደግሞ  በሕዝቡና በፍትሕ ተቋሞች የሚጠበቅ ግዴታ አለ፡፡  አንደኛ የሕዝብ ተባባሪነት ነው፡፡ ሕዝብ ከፈቃደኛነት ላይ የተመሰረት ሕግን የማክበር አመለካከት ሊኖረውና ሊያዳብር ይገባል፡፡ ስለ ሕግና ፍትሕ በጎ አመለካከት እንዲኖረው መስራትም ይጠይቃል፡፡ ሕግን ማክበር፣ የሌላውን አለመመኘት፣ አለመስረቅ፣ አለመግደል ተጠያቂነት ከመፍራት ሳይሆን የግብረ ገብ ግዴታዎች እንደሆኑ አስቦ የሚፈፅም የሕዝብ ስብስብ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የፍትሕ ተቋሞቻችን እምነት እንዲጣልባቸው ማድረግ ይጠይቃል፡፡ ሕዝብ ፍትሕ ተቋሞች ቀርቤ ጥቅሜን አስከብራለሁ፤ለእኔም የሚከላከል ተቋም አለኝ በሚልበት ደረጃ እንዲደርስ የፍትሕ አገልግሎቱን ማሳደግ ይገባል፡፡ በሕብረተሰቡ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ከመፍጠር ይልቅ ያልተገባ ፍርሐትን የሚፈጥሩ አፋኝ ሕጎችንም ማስወገድ ይጠይቃል፡፡ እነዚህ ጥምር ስራዎችን መስራት ከተቻለ በሕግ አምላክ ለሚለው ምልጃ ወዶ ተገዥ የሕብረተሰብ ስብስብ መፍጠር ይቻላል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

The Right to Liberty and Privacy Right in Europe a...
ሕዝባዊ ፍርድ፣ ፍርድ ቤቶች እና ገላጋይ ዳኞች

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 14 December 2024