የሰው ልጅ ወደዚች ምድር ከመጣበት /ከተወለደበት/ እለት አንስቶ እስከ ሕይወቱ ፍፃሜ ድረስ በዚች ምድር ላይ የሚኖረው ለተወሰነ ጊዜ ነው፡፡ የሰው ልጅ በዚች ምድር ላይ ዘላለማዊ አይደለም፡፡ ለያንዳንዱ ሰው በፈጣሪው የተጠው የምድር ቆይታ ጊዜ አለው፡፡ ይህ የምድር ላይ ቆይታው በአይቀሪው ሞት ይጠናቀቃል፡፡ የሰው ልጅ ወደዚች ምድር ከተቀላቀለበት እለት አንስቶ እስከ እለተ ሞቱ ድረስ የሕግ መብት አለው፡፡
የኢትዮጵያ የውርስ ሕግ ኑዛዜ ማለት ምን ማለት እንደሆነ የሰጠው ትርጉም ባይኖርም አንድ ኑዛዜ ህጋዊ ውጤት እንዲኖረው ማሟላት የሚገባቸውን መስፈርቶች ምን ምን እንደሆኑ በዝርዝር የሚያስቀምጡ የሕግ ድንጋጌዎችን ከፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 857 እስከ 908 ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ ጽሁፍ ኑዛዜ በምን አግባብ ቢደረግ በሕግ ዘንድ ውጤት ይኖረዋል፤በውርስ ሕጋችን ላይ የተቀመጡት የኑዛዜ አደራረግ ስርዓቶች አስገዳጅነታቸው እስከምን ድርስ እንደሆነና ኑዛዜ በፍርድ ቤት ቢጸድቅ ሊያስገኝ የሚችለው ውጤትና ባለመጽደቁ የሚያመጣው ተጽእኖ ምን እንደሆነ ከውርስ ሕግ እና አስገጋጅ ከሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ውሳኔዎች አንጻር በአጭሩ ዳሰሳ ለማድርግ ተሞክሯል፡፡