የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 እራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ከአዲስ አበባ እና ከድሬዳዋ ከተሞች ላይ የገፈፈ ስለመሆኑ እና የመፍትሔ አቅጣጫዎቹ፡፡
እራስን በራስ የማስተዳደር መብት የፌዴራል ሥርዓትን በሚከተሉ አገሮች የተለመደ አሰራር ሲሆን በዋናነትም ክልሎች ወይም ራስ ገዝ አስተዳድሮች ከፌዴራል መንግስቱ ተፅእኖ ውጪ የራሳቸው ሕግ አውጪ፤ ሕግ ተርጓሚ (የዳኝነት አካል) እንዲሁም የህግ አስፈፃሚ አካላት ኖሯቸው በcheck and balance መርህ ክልላቸውን ወይም አካባቢያቸውን የሚያስተዳድሩበት ቁልፍ ቃል-ኪዳናቸው ነው፡፡
ይህ እራስን በራስ የማስተዳደር መብት በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አንቀፅ 39(3) ለኢትዮጵያ ብሄር፤ ብሄረተሰቦች፤ ሕዝቦች የሰጠ እንዲሁም በአንቀፅ 49(2) ላይ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን እንዳለው የሚደነግግ ሲሆን በአንፃሩ የድሬዳዋ አስተዳደር ግን ይሄን መብት ሕገ-መንግስቱ እንደነፈገው የሚታወቅ ግልፅ ሐቅ ነው፡፡
በመሆኑም የዚህ ጽሑፍ ዋናው ትኩረት ከዳኝነት አካላት ውስጥ አንዱ ከሆነው የድሬዳዋ እና የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድሮች የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤን የዳኝነት ስልጣን ከሕገ-መንግስቱ (እራስን በራስ ከማስተዳደር መብት ለአዲስ አበባ ከተማ ከተሰጠ መብት አንፃር)፤ ከፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጁ እና ከተሞቹ ከሚመሩባቸው አዋጆች አንፃር ያሉ የሕግ ጉዳዮችን/ችግሮችን በንፅፅር በወፍ በረር በመዳሰስ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማመላከት ነው፡፡