ይህ አጭር ጽሑፍ ጠበቆች በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት የተረጋገጠላቸውን ሙያቸውን የመምረጥ መብት ከስራቸው ባህሪ አንፃር ከጥብቅና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥና አስተዳደር አዋጅ፣ ከንግድ ሕጉ እና ከሐምሌ 01/2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐምሌ 10/2017 ዓ.ም ከፀደቀው የፌደራል ገቢ ግብር (ማሻሻያ) አዋጅ ቁጥር 1395/2017 አንፃር ዳሰሳ ለማድረግና የግል ምልከታን ለማስፈር ነው፡፡ መልካም ንባብ!
በተለምዶ የሕግ ባለሙያዎች በንግዱ ዘርፍ ለሚንቀሳቀሱት ተወዳዳሪ ኃይሎች የተጋለጡ አልነበሩም፡፡ ይህ በሲቪል ሎው የሕግ ሥርዓት ተከታይ ሃገራት በአድቮኬቶችና ላቲን ኖታሪዎች እንዲሁም በኮመን ሎው የሕግ ሥርዓት ተከታይ ሃገራት በባሪስተሮች፣ ሎሊሳይቶሮች እና ኮንቬሮች መካከል ተመሳሳይ እውነታ ነበር፡፡ በእነዚህ በሁለቱ ሥርዓት የሕግ ሙያ ቁጥጥር የሚተገበረው በቀጥተኛ የመንግሥት ቁጥጥርና በላቀ ሁኔታ ደግሞ በራስ አስተዳደር (self regulation) ባለሙያዎች በተቀረፁ ሕጎች በመተዳደር ነው፡፡ ይህ የሕግ ሙያ ቁጥጥር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእነዚህ ሥርዓቶች በፈጠረው የፀረ-ውድድር ተፅዕኖ ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ እየተተቸ ይገኛል፡፡
መነሻ ነጥብ
የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማህበር በ1958 ዓ.ም.በእድርና እቁብ አይነት ቅርጽ የተመሰረተ ድርጅት ነው፡፡ በሰዓቱ ከአርባ የማይበልጡ አባላት የነበሩት ሲሆን አባሎቹም በከተማይቱ አዲስ አበባ የጥብቅና አገልግሎት የሚሰጡ ነበሩ፡፡ ይህ ማህበር የተደራጀና የአባላቱን እንዲሁም የተከበረ ሙያ የሆነውን የጥብቅና ሙያ ለማስጠበቅና ለመጠበቅ ሳይሆን በማህበርተኞች መካከል ለሚፈጥሩ ማህበራዊና ሰዋዊ ችግሮች ለመረዳዳት ተብሎ የተመሰረተ ተቋም ነበር፡፡ ይህ ስብስብ በተመሰረተ በአመቱ ማለትም በ1959 ዓ.ም. በቀድሞው አጠራር የሀገር ግዛት ሚኒስቴር ተመዝግቧል፡፡ ከአብዮቱም በኋላ የኢትዮጵያ የጠበቆች ማህበር የሚለውን ስያሜ የያዘ ሲሆን በማህበሩ ውስጥ ጠበቆች፣ የሕግ መምህራን፣ ዳኞች፣ የሕግ ጉዳይ ፀሐፊዎች እና ሌሎችም አባል ሆነው ይሰሩ ነበር፡፡ ስሙን ቀይሮ የመጣው ማህበር የግብርና የዓላማ ለውጦችንም በማድረግ ደረጃውን የጠበቀ የጥብቅና ሙያ እንዲኖር ግንባር ቀደም ዓላማው አድርጎ ተነሳ፡፡ በወቅቱም ልክ አሁን እንዳለው ተመሳሳይ አሰራር የጥብቅና ፍቃድ በማሳየትና የአባልነት ክፍያ በመክፈል አባል መሆን ይቻል ነበር፡፡