Font size: +
9 minutes reading time (1887 words)

‘ጠባቂ የሌለው ጠበቃ’ ጥቂት ስለ ኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያዎች ማህበር

መነሻ ነጥብ

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማህበር በ1958 ዓ.ም.በእድርና እቁብ አይነት ቅርጽ የተመሰረተ ድርጅት ነው፡፡ በሰዓቱ ከአርባ የማይበልጡ አባላት የነበሩት ሲሆን አባሎቹም በከተማይቱ አዲስ አበባ የጥብቅና አገልግሎት የሚሰጡ ነበሩ፡፡ ይህ ማህበር የተደራጀና የአባላቱን እንዲሁም የተከበረ ሙያ የሆነውን የጥብቅና ሙያ ለማስጠበቅና ለመጠበቅ ሳይሆን በማህበርተኞች መካከል ለሚፈጥሩ ማህበራዊና ሰዋዊ ችግሮች ለመረዳዳት ተብሎ የተመሰረተ ተቋም ነበር፡፡ ይህ ስብስብ በተመሰረተ በአመቱ ማለትም በ1959 ዓ.ም. በቀድሞው አጠራር የሀገር ግዛት ሚኒስቴር ተመዝግቧል፡፡ ከአብዮቱም በኋላ የኢትዮጵያ የጠበቆች ማህበር የሚለውን ስያሜ የያዘ ሲሆን በማህበሩ ውስጥ ጠበቆች፣ የሕግ መምህራን፣ ዳኞች፣ የሕግ ጉዳይ ፀሐፊዎች እና ሌሎችም አባል ሆነው ይሰሩ ነበር፡፡ ስሙን ቀይሮ የመጣው ማህበር የግብርና የዓላማ ለውጦችንም በማድረግ ደረጃውን የጠበቀ የጥብቅና ሙያ እንዲኖር ግንባር ቀደም ዓላማው አድርጎ ተነሳ፡፡ በወቅቱም ልክ አሁን እንዳለው ተመሳሳይ አሰራር የጥብቅና ፍቃድ በማሳየትና የአባልነት ክፍያ በመክፈል አባል መሆን ይቻል ነበር፡፡

ብዙ ያነጋገረው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማሕበራት አዋጅ ማለትም አዋጅ ቁጥር 621/2000 ከወጣ በኋላም ማህበሩ በድጋሚ ምዝገባ የማህበሩን ስያሜ ከኢትዮጵያ የጠበቆች ባለሙያዎች ማህበር ከሚለው ወደ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማህበር ለውጦ ተመዝግቧል፡፡ የስም ለውጡ በሁለት አበይት ምክንያቶች የመጣ ነው፡፡ አንደኛው በክልሎች ላይ የጠበቆች ማህበር የሚለው ስያሜ ስላለና ይህንን ተመሳሳይ ስም ሌላ ማህበር መጠቀም አይችልም በማለት ሲሆን ሁለተኛው ዐብይ ምክንያት ደግሞ ማህበሩ ላይ ተሳታፊ የነበሩ አባላት ጠበቆች ብቻ ስላልነበሩ የጠበቆች ሳይሆን የሕግ ባለሙያዎች ቢባል ሁሉንም አካታች ስለሚሆን መልካም ነው በሚል ነው፡፡ በአሁን ሰዓት ማህበሩ ከሰባት መቶ ያልበለጡ አባሎች ያሉት ሲሆን ወርሀዊ መዋጮውም ሀምሳ ብር ነው፡፡

  1. የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማህበር ሚናዎች

በአዋጅ ቁጥር 199/92 እንዲሁም ይህንን አዋጅ ለማስፈፀም በወጣው ደንብ ቁጥር 57/1999 ላይ እንደተጠቀሰው ማህበሩ[2] በፍትህ ሚኒስቴር (በአሁን ሰዓት የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ) ውስጥ ሦስት ሚናዎች ያሉት ሲሆን እነዚህም የጥብቅና ፍቃድ ገምጋሚ ኮሚቴ፣ የጠበቆች የሥነ-ሥርዓት (ዲሲፕሊን) ኮሚቴ እንዲሁም የጥብቅና ሙያ መግቢያ ፈተና አዘጋጅና የችሎታ ብቃት መለኪያ ቦርድ ውስጥ ይሳተፋል፡፡

ከብዙ ሀገሮች ልምድና ተሞክሮ ማየት እንደሚቻለው በጥብቅና ሙያ ላይ የሚሳተፉት ሰዎች ብቃት፣ ሰብእና እና ተገቢነት ያላቸው መሆናቸውን የመቆጣጠርና ተገቢም ሆኖ ሲያገኘው የጥብቅና ፍቃዳቸውን የመንጠቅ መብት ስልጣን ያለው ይኸው የሕግ ባለሙያዎች (Bar Association) ነው፡፡ ለምሳሌ በታላቂቱ ምድር አሜሪካ የጠበቆችን ማህበር (American Bar Association) የጠበቆችን ፈተና የማውጣት፣ የሥነ-ምግባር ደንብ የማውጣት፣ እንዲሁም የጠበቆችን ከመልካም ሥነ-ምግባር ውጪ ያለ ተግባር ላይ ሲገኙ ፈቃድ መሰረዝ ካሉት ሰፊና ጥልቅ ስልጣኖች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያ ተሞክሮ እንደሌሎች ጉዳዮቻችን ሁሉ የኋልዮሽ የሆነና ከዓለም ተሞክሮ በተቃራኒው የቆመ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ማንኛውም የሕግ ባለሙያ ጥብቅና ፍቃድ አወጣለሁኝ ቢል ይህንን ፈቃድ ለማግኘት መመዝገብም መፈተንም ያለበት በአሁኑ አጠራሩ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ነው እንጂ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ጋር አይደለም፡፡ አንድን ጠበቃ ከሙያና መልካም ሥነ-ምግባር ህሊና ከሚያዘው ውጪ ኪሳራና ጉዳት አድርሶብኛል የሚል አካል ቢኖርው መጠየቅ ያለበት ለፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ነው እንጂ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ጋር አይደለም፡፡ የጠበቆች ሥነ-ምግባር ምን ምን እንደሆኑ ማገላበጥ ያለበት የሀገሪቱ ሕግጋት እንጂ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች የውስጥ ደንቦችና መተዳደሪያን አይደለም፡፡ ማንኛውም የሕግ ድጋፍ ማግኘት የሚፈልግ ዜጋ ነፃ የሕግ አገልግሎት (pro bono legal service) ማግኘት ካለበት የሚያገኘው ከፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ነው እንጂ ፍላጎትና አቅም ያላቸው ባለሙያዎች ስብስብ የሆነውን የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ጋራ አይደለም፡፡ እነዚህ ሁሉ ማህበሩን ጥርስ የሌለው አንበሳ አድርገውታል፡፡ ወደ ጠበቆች መብት ስንመጣ ደግሞ ማህበሩ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተፅእኖ ሥር መሆኑ በዚህም ምክንያት ጠበቆች የሚከራከሩለት ሰው “ደንበኛ” አላቸው እንጂ የሚከራከርላቸውና መብታቸውን የሚያስጠብቅላቸው የሞያውን ልእልና የሚያስጠብቅ ማህበር አሳጥቷቸዋል፡፡

አንዳንዶች ጠንካራ የሕግ ባለሞያዎች እንዳይኖር ያደረገው አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ሆን ብሎ ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ይህ ምንም እርባና የሌለው ነጥብ ነው ብሎ ለመናገር ባያስደፍርም የመንግስት ጠንካራ ማህበር እንዲኖር አለመፈለግ ከሆነ ግን መነሻ ነጥቡ ወደ ቀድሞ መንግስታት ይወስደናል፡፡

አቶ ተፈሪ ብርሀኑ በኢትዮጵያ የጥብቅና ፍቃድ መሰረቱን እንዲሁም በጠበቃ ላይ የሚቀርብን የቅሬታ ክስ ተቀብሎ የመመርመርና የማገድ ሥልጣን በ1934 ዓ.ም. በወጣው የዳኝነት ሥራ አካሄድ አዋጅ  አንቀጽ 20 መሰረት የተሰጠው በቀድሞው አጠራረ ለፍርድ ሚኒስቴር ነው ሲሉ ታሪካዊ ዳራውን ወደ 1934 የወሰዱት ቢሆንም[3] በተደራጀና ጠንከር ባለመልኩ የሕግ ቅርፅ ያለው የጠበቆች ሙያን ለማስተዳደር የወጣው የሕግ ክፍል ማስታወቂያ (Legal Notice) ቁጥር 168/1952 ነው፡፡ ይህ አዋጅ በአንቀጽ 3 ላይ በግልፅ ሰፍሮ እንደምናገኘው ማንኛውም የሕግ ባለሙያ ጠበቃ ለመሆን ቢመኝ በፍትህ ጽ/ቤት መመዝገብ አለበት ብሎ ደንግጓል፡፡ ስለሆነም የጠበቃን ፍቃድ ከመንግስት አስፈፃሚ ጋራ አቆራኝቶ የማየት ነገር ከጥንቱም የነበረ ነው ብሎ መደምደም ያስችላል፡፡ እዚህ ላይ ምናልባትም ሊነሳ የሚችለው መከራከሪያ በዛን ወቅት ሲጀመርስ የሕግ ባለሙያዎች ማህበር መች ነበር የሚል ይሆናል፡፡ [4]

በእርግጥ መንግስት ለዚህ አይነት አስተያየቶችና ቅሬታዎች የሚመልሰው አያጣም፡፡ መንግስት በተለያዩ መድረኮች የተለያዩ ምክንያቶችን ሲደረድ የሚሰማ ሲሆን በዋነኝነት ግን አሁን ባለው የጠበቆች ስግብግብነት (ጥብቅናን ከድህነት አረንቋ መውጫ የአቶ መስፍን ታፈሰን አገላለፅ ለመጠቀም የጥብቅና ሙያን እንደ ኖህ መርከብ አድርጎ መውሰድ [5])፣ ብቃት ማነስና መተዋወቅን መሰረት አድርጎ የተዘረጋ አሰራር የሰፈነበት በመሆኑ የፍቃድ አሰጣጥ ለሕግ ባለሙያዎች ማህበር ቢሰጥ አብላጫውን የማህበረሰቡ ክፍልና ይልቁንም “ፍትህ” ይዛባል የሚል ነው፡፡

ይህንንም ለማሳየት አንድን ሙያና ፍትህን እናገለግላለን ያሉ ሁለት ማህበራት ማለትም የኢትዮጵያ ጠበቆች ማህበርና የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማህበር አይንህን ላፈር ተባብለው መከፋፈላቸው እንዲሁም አንዳንድ በማህበሩ ውስጥ ያሉ ጠበቆች የተከሰሱባቸውን የሥነ-ምግባር ጉድለት ክሶች ህያው ምስክር አድርጎ ያቀርባል፡፡ ይህንንም ሀሳብ የሕግ ሎሬቱ አቶ ታምሩ ወንድምአገኘሁ ሲደግፉት በዓለማችን ላይ ካሉ እጅግ ደካማው የጠበቆች ማህበር የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማህበር ነው ይላሉ፡፡ [6] ይሁንና እኚሁ የሥነ ሕግ ሊቅ ዐቃቤ ሕግ ምን ማለት ነው ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱም ዐቃቤ ሕግ ማለት የመንግስት ጠበቃ የመንግስት ሕግ አማካሪ ነው፤ ስለዚህ የወንጀልም ሆነ የፍ/ብሔርን የመንግስት ክስ የሚይዘው ዐቃቤ ሕግ ነው ማለት ነው፡፡ ጠበቃ ደግሞ በሁለቱም በኩል የግል ተከሳሽ ጠበቃ መሆን ይችላል፤ ስለዚህ ፈቃጁ መንግስትን ወክሎ ወይንም ዐቃቤ ሕግ ሆኖ በሚከራከርበት ጉዳይ ከዚያ ጉዳይ ፈቃድ ያገኘው ጠበቃ ቆሞ በሚከራከርበት ጊዜ ተፈጥሮአዊ ግጭት ይፈጠራል፡፡ ስለሆነም ይህንን ማስቀረት እምንችለው ይህንን ስልጣን ለባለቤቱ በመመለስ ነው ብለው አጥብቀው ይከራከራሉ፡፡ [7]

ችግሩ ምናባዊ እንዳልሆነ ለማስረዳት በአንድ ወቅት ለዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ስመ-ጥር ጠበቃ ያጫወተውን መጥቀስ ተገቢ ነው፡፡ ጠበቃው ታዋቂና ተፅእኖ ፈጣሪ የሚባል ጋዜጠኛን ወክሎ ግለሰቡ ላይ ለተነሳው የወንጀል ክስ ጥፋተኛ አይደለም በማለት ይከራከራል፡፡ ፍ/ቤቱም የሁለት ወገኖች የማስረጃና የሕግ ክርክር ከሰማ በኋላ ተጠርጣሪውን ጥፋተኛ ነህ ብሎ ፍርድ ይሰጣል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ጠበቃው ለጋዜጠኞች አስተያያቱን ይሰጣል፡፡ ይህንን አስተያየት በሰጠ ማግስት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ (በአሁኑ አጠራሩ) ጠርቶ ፍቃድህ ይሰረዛል ወይንም ለሰጠኸው አስተያየት ማስተባበያ መግለጫ ስጥ ተብሎ እንደነበር አጫውቶታል፡፡

ሌላው የማህበሩ ሚና በሥነ-ምግባር(ዲሲፕሊን) ኮሚቴ ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ኮሚቴ ውስጥ  በኢትዮጵያ የሕግ ማህበር በኩል ሁለት ተወካዮች፣ ከዳኞች ሁለት ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሁለት ተወካዮች ናቸው፡፡ ጠበቃው ላይ ለሚነሱ ክሶች በዚህ ኮሚቴ አማካኝነት ማሳካት አዳጋች ነው ብሎ መናገር ከእውነት የራቀ አይሆንም፡፡ አንደኛ ኮሚቴው ላይ የሚሳተፉ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ሳይሆን ማህበሩን ወክለው ነው የሚሳተፉት፡፡ ስለሆነም የማህበሩ አላማ ግብ እንጂ የራሳቸውን ፍላጎት አያራምዱም ማለት ነው፡፡ ከማህበሩ አላማዎች መካከል የጠበቃውን መብት ማስጠበቅና ፍትህ እንዲሰፍን ማድረግ የሚሉት አበይት አላማዎች ይገኙበታል፡፡ ማህበሩ በኮሚቴው ውስጥ የጠበቃውን መብት አስጠብቃለሁ ካለ (ማለትም የጠበቃው ጠበቃ መሆኑ ነው) በማስረጃ ምዘና ጊዜ እጠብቀዋለሁ ስላለው ጠበቃ ያደላል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የግድ ከሁለተኛው አበይት አላማው ማለትም ፍትህን ከማረጋገጥጋራ ተፈጥሮአዊ ተቃርኖ ውስጥ ይከተዋል፡፡   ይህንን እንኳን በደጋፊና ገፊ ምክንያቶች ብናልፈው የማህበሩ ተወካዮች በቁጥር ስለሚበልጡ የጠበቃውን መብት ማስጠበቅ አይችሉም ማለት ነው፡፡ ይህም የማህበሩ ስልጣን የወረቀት ላይ ነብር ያደርገዋል፡፡

የጥብቅና ሙያ መግቢያ ፈተና አዘጋጅና የችሎታ ብቃት መለኪያ ቦርድ ላይ ያለው ስልጣን ከሌሎች ስልጣኖችና ሚናዎች በአንጻራዊነት ስልጣኑን በደንብ መተግበር የሚያስችል ነው፡፡ ምክንያቱም ጠበቃው በተግባርም በትምህርትም (Academic knowledge) ተፈትኖ የወጣ በመሆኑ አግባብነት ያላቸውን ጥያቄዎችን ማንሳቱ አሌ የማይባል እውነት ነው፡፡

ይህ ጠበቃውን በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪነው የሚጠብቀው፡፡ አንደኛ ፈተና መግቢያ ቦታ (entry point) እንጂ ከፈተና በኋላ ከላይ ለማየት እንደተሞከረው በምንም አይነት ሁኔታ አይጠብቅም፡፡ ሁለተኛ ወደ ጥብቅና ሙያ የሚገቡ ባለሙያዎችን ብቁነት በመጠበቅ ትልቁን የጥብቅና ሙያ እንጂ ጠበቃን እንደ ግለሰብ አይጠብቅም፡፡

ይህ ጥርስ አልባ ድርጅት መሆኑ ደግሞ ሦስት አይነት ተፈጥሮአዊ ችግሮችን አምጥቷል፡፡ አንደኛው መብቱና ሙያውን በደንብ አድርጎ ሊጠብቅለት የማይችል ድርጅት ውስጥ ሰዎች በባህሪያቸው የመሳተፍ ፍላጎት የላቸውም፡፡ ይህም ደግሞ ከ4,000 በላይ ጠበቆች ባሉበት አዲስ አበባ ማህበሩ ያሉት ከ700 የማይበልጡ አባላት መሆኑ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ቁጥር ሲያንስ ተደማጭነትም የተሻለ ሀሳብ መሰለልንም ማሰከተሉ የማይታበል ሀቅ ነው፡፡ ጠበቃው በሚያያቸው የእለት ተእለት ተግዳሮቶችና ክፍተቶች መሰረት በማድረግ አዲስ ህጎች እንዲወጡና የፈር ቀዳጅነት ሚናውን (pace maker role) እንዳይወጣ አድርጎታል፡፡

 ሁለተኛ የማህበሩ አባሎች ትንሽ በመሆናቸው ከአባላት ክፍያ የሚገኘው ገቢ አነስተኛ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ያሉትም አባላት ክፍያቸውን በአግባቡ አይከፍሉም፡፡ ስለሆነም የገንዘብ ነፃነት የሌለው ማህበር በመሆኑ እንደሌሎቹ ድርጅቶች እጁን ለምፅዋት መዘርጋቱ አልቀረም፡፡ ይህም የሙያውን ክብር ዝቅ ከማድረጉም በተጨማሪ የማህበሩንም አላማዎች በለጋሽ ድርጅቶች ላይ የተመረኮዘ አድርጎታል፡፡

ሦሰተኛው ደግሞ እምነት የሚጣልበት ተቋም እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ የሙያ አንዱ መገለጫውና የማዕዘን ድንጋይ የሚያደርገው ህብረተሰብን ማገልገል ሲሆን በሙያው አማካኝነት የሚገኝ ጭፍጫፌ ጥቅም ግን የእግረ መንገድ ትርፍ (incidental benefit) ነው፤ ነገር ግን በሀገራችን ከዚህ ተገላቢጦሽ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

በዘርፉ ላይ ተጠያቂ የሚባሉ ምሁር የጥብቅናን ሙያ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት ያለውን ሲገልፁ የሕግ ሥነ-ምግባር ምንም ያህል በአገራችን አይከበርም ቢባል ስህተት አይሆንም አብዛኛዎቹ ጠበቆች የሚመለከቱትን የዕለት ጥቅማቸውን በመሆኑ ጥብቅናን ሙያ አድርጎ ከመቁጠር ይልቅ እንደ ንግድ ይቆጥሩታል፡፡ በአሁን ሰዓት ግን ጠበቆች የሚገባቸውን ክብር ያላገኙና ምንም እምነት ያልተጣለባቸው ናቸው፡፡ መዝገብ ከችሎት ወደ ችሎት እንኴን በተላላኪ አማካኝነት መፈፀሙን በማንሳት የጠበቆች እምነት የዚህን ያህል የወረደ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ይህ አገላለፅ አሁን ያለውንም ጊዜና እውነት የሚገልፅ መሆኑን ሲታይ ሙያው ላይ የህብረተሰቡ እምነት እጅግ ዝቅ ያለ መሆኑን እንረዳለን፡፡ [8]

  1. ምን ይደረግ

እንደ ጥብቅና ያለ እጅግ የተከበረ ሙያ ችግሮች በአንድ ተቋም ወይም ግለሰብ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ነው ብሎ መገመት አይቻልም፡፡ ስለሆነም የተለያዩ አካላት የየራሳቸው ድርሻ መወጣት አለባቸው፡፡

3.1. ከመንግስት

መንግስት ሀገር የሚባለውን ትልቅ አካል ከሚያቋቁሙ አንደኛው አካል ነው፡፡ መንግስት በስሩ ያሉትን ተቋማት እንደ ልጆቹ በማየት ሊረዳቸው፣ ሊያግዛቸው ይገባል፡፡ እውነት ነው መንግስት የሕግ ባለሙያዎች ማህበር ችግር ስላሉበት ሙሉ ፍቃድ መስጠት ስልጣንን መስጠት ተገቢ አይደለም የሚለው ስጋት ተጨባጭና እውነትነት ያለው ነው፡፡

ይሁንና ማንኛውም ድርጅት ወይም ተቋም ከስህተት እና ከችግሮች ነፅቶ አያውቅም፡፡ እራሱ መንግስት ከፍተኛ ችግር እንዳለበት ይታወቃል፡፡ ይልቁንም አሉ የሚላቸውን ችግሮች በቅርበት በመነጋገር፣ስልጠና በመስጠት ፣ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ አንዲወስዱ በማድረግ ማኅበሩ ወደ ተሻለ ደረጃና በሁለት እግሩ እንዲቆም መርዳት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ከተፈለገ የጠበቆች ሚና[9] ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ መንግስት ልዩና ከፍተኛ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባዋል፡፡

 

3.2  ከማህበሮቹ

እላይ ጠቀስ ለማድረግ እንደተሞከረው ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁን ሰአት ለጠበቃውና ለሕግ ማህበረሰቡ ቆሜያለሁ የሚሉ ሁለት ማህበሮች አሉ፤እነዚህም የኢትዮጵያ ጠበቆች ማህበርና የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማህበር ናቸው፡፡ በ1967 ዓ.ም. በኢትዮጵያ አብዮት ወቅት ኢህአፓና መኢሶን “እናሸንፋለን”“እናቸንፋለን”፣“ወዝ አደሩ”“ላብ አደሩ” በሚሉ የቃላት ጨዋታ እንደተከፋፈሉ ሁሉ እነዚህም ማህበራት ምንም አይነት መሰረታዊ ልዩነቶች ሳይኖራቸው ክፍፍል መፈጠሩ ያስገርማል፣ ያሳዝናልም፡፡ አንድ መሆን ያቃተው ማህበር እንዴት ነው መንግስት ትልቅ እምነት ጥሎ የፍቃድ አሰጣጥን ስልጣን የሚሰጠው፣ አንድ መሆን ያቃተው እንዴት ነው ከመንግስት ጋራ የሚደራደረው የፍትህን ልዕልና ከፍ የሚያደርገው ሙያውን የሚያስከብረው፡፡ እነዚህ የማህበር መሪዎች ህሊናቸውን ፈርተው እርሱም ካልሆነ ምን ይሉኛልን ፈርተው ይህም ካልሆነ ትውልድና ሙያውን አስበው ወደ አንድ ማህበር ቢመጡ መልካም ነው፡፡ [10]

3.3. ከጠበቆች

በሁሉም ጠበቆች አፍ ላይ የሚደመጠው ጥብቅና ትልቅና የከበረ ሙያ እንደሆነ ነው፡፡ ለትልቅነቱ የሚገባውን ክብር የሰጡ ግን እጅግ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በአፍ የተደረገ ሰበካ ራስን ከማታለል ለጊዜው የሚያሰፈልገውን ያህል ቁሳዊ ነገርን ከማሟላት አልፎ ትውልድንና ሀገርን የሚጠቅም ነገር አያደረግም፡፡ ጠበቆች በሕግ ባለሙያዎች ማህበር አባል በመሆን የሚችሉትን ሊያደረጉና ሊያግዙ ይገባል፡፡ ማህበሩ የሰውም የገንዘብም እጥርት እንዳለበት የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ለመገንዘብ ችሏል፡፡ በገንዘብ አቅማቸው እጅግ የፈረጠሙ በእውቀታቸውም አንቱ የተባሉ ጠበቆች ማህበሩን እንዳለም አያውቁም፡፡ ስለሆነም ማህበሩን ከነችግሮቹ ቀረብ ብለው ሊያግዙት ዳተኛ የሆኑትንም ሊያነቁና ስማቸውን በማይጠፋው ታሪክ ላይ ሊፅፉ ይገባል፡፡ ቸር ያሰማን፡፡

 የግርጌ ማስታወሻ 

[1] ይህንን ፁሁፍ አይቶ አሰተያየቱን ለሰጠኝ አቶ ዘረገእግዛብሔር አብዛን አመሰግናለሁኝ፡፡

[2] አዋጁ የሚለው በጥቅል የጠበቆች ማህበር ይሁን እንጂ በተግባር ግን  የኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያዎች ማህበር ንቁ ተሳተፎ አለው፡፡

[3]ተፈሪ ብርሀኑ፣ የጠበቆች እና የሕግ አማካሪዎች የሕግ ሰነ ምግባር፣ የኢትዮጵያ ሕግ መፅኔት ቅፀ 8 ቁጥር 2

[4]እዚህ ላይ ግረማዊ ንጉስ ነገሰት ኃ/ስላሴ ሰለጠበቆች መደራጀት ጠቆም አድረገው ነበር ማለት ያችላል፡፡ 1957 ለተመራቂ ተማሪዎች ንግግር ሊያደረጉ የሚከተለውን ብለው ነበር፡፡ ” …..ኢትዮጵያ ከዓለም ውሰጥ ዘመናዊ የሆነ የሚያኮራ ሕግ አላት ለማለት ያሰደፍራል፡፡ ያሰደሰታል፡፡ ነገር ግን እንደ ሕጉ መሻሻል መጠን የሕግ ባለሙያዎች በትምህረታቸውና በሥራቸው የሠለጠኑና የተጠናቀቁ መሆን አለባቸው፡፡ ሕግ መሻሻል ያገር መሻሻል የተያያዘና የተሳመረ ነው፡፡ ” (ሰረዝ የተጨመረበት) ምንጭ የኢትዮጵያ ሕግ መፀኔት ቅፀ 2 ቁጥር 1 መቅድም ይመልከቱ፡፡

[5]በአንድ ጥናታዊ ፀሁፍ ውይይት ውቅት የተናገሩት ነው፡፡

[6]ከጠበቃና የሕግ አማካሪ አቶ ታምሩ ወንድምአገነሁ ጋራ የተደረገ ቆይታ

[7]ዝኒ ከማሁ

[8]እላይ ቁጥር 3 ላይ የተጠቀሰውን ይመልከቱ

[9]በአንድ ውቅት ግረማዊ ንጉሰ ነገሰት ቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ህዳር 15 ቀን 1957 ዓ.ም.ለአዲስ አበባ ዩንቨረሲቲ(በአሁን አጠራሩ) የሕግ ፋክልቲ ለማታ ክፍለ ጊዜ የመጀመሪያ ተመራቂ ተማሪዎች ንግግር ሲያደረጉ በዳኝነት እውነት መፈለግ ለሥራም ምርጥ ሰው መፈለግ ግዴታ ነው፡፡ የሚመረጠውም ሕግን ከተማሩና ከራሳቸው ሥራቸውን ከሚያሰበልጡ መሀከል ነው፡፡ ጠበቃም በዕውነት ከሰራ ዳኛ ነውብለው ነበር፡፡ ይህም ጥብቅና ሙያ ከዳኝነትም እኩል አሰፈላጊ እንደሆነ ያሰገነዝበናል፡፡ እላይ ቁጥር 3 ላይ የተጠቀሰውን ይመልከቱ

[10] በቅርቡ ሁለቱ ማህበሮች አብሮ ለመሰራት መስማማታቸውን መደበኛ ባልሆነ ውይይት ለዚህ ፁሁፍ አዘጋጅ አጫውተውታል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የፍርድ ቤት ወይስ የችሎት ስልጣን? (Jurisdiction of Courts or ...
የልዩ ምርመራ ኦዲት ግኝቶችና የወንጀል ውጤታቸው

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Sunday, 08 September 2024