Font size: +
14 minutes reading time (2816 words)

ወደኋላ ሄዶ ተግባራዊ የሚያደርጉ የታክስና ጉምሩክ ሕግ ድንጋጌዎች ሕገ መንግሥታዊነት

 . ወደኋላ ሄዶ ተግባራዊ የሚያደርጉ የታክስና ጉምሩክ ሕግ ድንጋጌዎች ሕገ መንግሥታዊነት 

የታክስና የጉምሩክ ሕጎች ስንል ምን ማለታችን ነው? ከሕገ መንግሥቱ ጋር ያላቸው ዝምድናስ ምን ይመስላል ?

በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/08 አንቀጽ 2(36) መሠረት የታክስ ሕግ ማለት የጉምሩክ ሕግን ሳይጨምር የታክስ አስተዳደር አዋጅ፣ የፌደራል የገቢ ግብር አዋጅ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ፣ የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ፣ የቴምብርና የተርን ኦቨር ታክስ አዋጅ፣ ታክስ/ቀረጥ/ክፍያ ለመጣል የሚወጣ ሕግ እንድሁም እነዚህን አዋጆች መሠረት በማድረግ የሚወጡ ደንብና መመሪያዎችን ያካትታል፡፡ የጉምሩክ ሕግ ማለት ደግሞ በጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/06 አንቀጽ 2(39) መሠረት የጉምሩክ አዋጁን፣ አዋጁን ተከትለው የሚወጡ የጉምሩክ ደንብና መመሪያዎችን እንድሁም የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን /የአሁኑ ገቢዎች ሚኒሰቴር/ የሚያስፈፀማቸውን ሌሎች ሕጎች ያካትታል፡፡

ለዚህ ፅሁፍ ዓላማ ትኩረት የምናደርግባቸው በግብር ከፋዩ እንድሁም በአስመጭና ላኪዎች ዘንድ ሕጉ ወደኋላ ሄዶ ተግባራዊ ሊደረግ አይገባም፤ ሕጉ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም በማለት በግብር ይግባኝ ኮሚሽን እና ፍ/ቤቶች ክርክር የሚነሳባቸው ሕጎች ላይ ነው፡፡

 . የታክስና የጉምሩክ ሕጎች የፍትሐብሔር ሕግ ናቸው ወይስ የወንጀል ሕግ ወይስ ሁለቱንም? Are they civil laws or criminal laws or both?

ይህን ፅንሰ ሀሳብ በተመለከተ በአንዳንድ የሕግ ባለሙያዎችና በግብር ይግባኝ ኮሚሽን ዘንድ እነዚህን ሕጎች እንደ ፍትሐ ብሄር ሕግ /civil and administrative laws/ የማየት ዝንባሌ አለ፡፡ ይህም በ1996 ዓ.ም እንደወጣው የወንጀል ሕግ በግልፅ የወንጀል ሕግ የሚል ስያሜ ስለሌለውና በአብዛኛው ስለ ፍትሐብሔራዊ /ገንዘብ ነክ/ ጉዳይ የሚዳስስ ሕግ ነው ከሚል የመነጨ ነው፡፡ ይሁን እንጅ እነዚህ ሕጎች የፍ/ብሄር ወይም የወንጀል ሕግ ናቸው የሚለውን ለመለየት ህጎቹን በዝርዝር ማንበብና መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/06 በተመለከተ ከአንቀጽ 166-174 ያሉት ድንጋጌዎች ስለ ጉምሩክ ወንጀሎች እና ቅጣታቸው በዝርዝር የሚደነግጉ ሲሆን ከዚህ ውጭ ያሉት ድንጋጌዎች ደግሞ ስለ ፍትሐብሔራዊ ወይም ገንዘብ ነክ ጉዳይ ወይም ስለ አስተዳደራዊ ጉዳይ የሚደነግጉ ናቸው፡፡ የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/08ን ለማስፈፀም የወጣው የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/08 ስንመለከትም በአዋጁ ከአንቀጽ 106-133 ያሉት ድንጋጌዎች ስለ ታክስ ወንጀሎች እና ቅጣታቸው በዝርዝር የሚደነግግ ሲሆን ሌሎቹ ድንጋጌዎች ደግሞ ስለ ፍትሐብሔራዊ ወይም ገንዘብ ነክ ጉዳይ ወይም ስለ አስተዳደራዊ ጉዳይ ይደነግጋሉ፡፡ ይህም የሚያሳየው የታክስና የጉምሩክ ሕጎች የፍትሐብሔር ሕግና የወንጀል ሕግ ድምር ወጤት መሆናቸውን ነው፡፡ እነዚህ ሕጎች የፍትሐብሔር እና የወንጀል ሕግ ከመሆናቸው በተጨማሪ የስነ ስርዓት ሕጎችም /procedural laws/ ጭምር ናቸው፡፡ የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር ከአንቀጽ 152-155 ያሉት ድንጋጌዎች አዋጁ የሚፈፀምበትን ስነ ስርዓት ያስቀምጣሉ፡፡ የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/08 ከአንቀጽ 52-60 እንድሁም ከአንቀጽ 86-94 ያሉት ድንጋጌዎች የገቢ ግብር አዋጁ የሚፈፀምበትን ስነ ስርዓት /መቼ፣የት፣እንደት፣ለማን…..ወዘተ/ የሚለውን ጉዳይ ይደነግጋሉ፡፡ የፌደራል የታክስ አስተዳደር ደንብ ቁጥር 407/09 ከአንቀጽ 9-18 ያሉት ድንጋጌዎችም የገቢ ግብር አዋጁ የሚፈፀምበትን ዝርዝር ስነ ስርዓት የሚደነግጉ ናቸው፡፡  ስለዚህ እነዚህን ሕጎች ስንተረጉም ያላቸውን የፍትሐብሔር፣ የወንጀል እና የስነ ስርዓት ሕግ ባህሪነት ከግምት ባስገባ በሆነ መንገድ መሆን አለበት፡፡ እነዚህ ሕጎች ዘርፈ ብዙ ዘርፎች ያላቸው ሕጎች ናቸው የሚለውን ከተረዳን ይህን ዘርፋቸውን መነሻ በማድረግ የሚነሳውን ትችት /critics/ በቀጣይ እንመለከተዋለን፡፡

. የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/08 የፌደራል ገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/08 እና የገቢ ግብር ደንብ ቁጥር 410/09 እንድሁም የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/06 ሕገ መንግሥታዊነት

  1. በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/08 አንቀጽ 137 (1) ላይ በግልፅ እንደተደነገገው አዋጁ ስራ ላይ ከመዋሉ በፊት/retroactively/ በተፈፀመ ድርጊት ወይም አለማድረግ ምክንያት በተሰጠ የታክስ ውሳኔ ላይ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ ይህ አዋጅ በፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ የወጣውና ስራ ላይ የዋለው ነሀሴ 14 ቀን 2008 ዓ.ም ነው፡፡ ይህም የአዋጁ አንቀጽ 139 (2) እና (3) ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው አዋጁ ከነሀሴ 14 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ተፈፃሚ እንደሚሆን ያሳያል፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች መረዳት የሚቻለው የታክስ ውሳኔው ከነሀሴ 14/2008 ዓ.ም በፊት በማናቸውም ጊዜ የተሰጠ ቢሆንም አዋጁ ወደኋላ ሄዶ ተፈፃሚ የሚሆን መሆኑን ነው፡፡ ይሁን እንጅ የታክስ ውሳኔው ከነሀሴ 14 ቀን 2008 ዓ.ም በፊት የተሰጠ ቢሆንም አዋጁ ወደኋላ ሄዶ ተፈፃሚ የማይሆንባቸው ልዩ ምክንያቶች አሉ፡፡

1.1 ከነሀሴ 14 ቀን 2008 ዓ.ም በፊት ሊከፈል ሲገባ ባልተከፈለ ታክስ ላይ የሚጣል አስተዳደራዊ ቅጣት በስራ ላይ በነበሩት የታክስ ሕጎች ፍፃሜ መሠረት ያገኛል፡፡

የዚህ ልዩ ሁኔታ ተፈፃሚነት እስከምን ድረስ ነውWhat was the scope of application of this exception? አስተዳደራዊ ቅጣት ስንል ምን ማለታችን ነው? ወለድ ወይስ ቅጣት ወይስ ሁለቱንም ያጠቃልላል ?

በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/08 አንቀጽ 2(24) መሠረት ቅጣት ማለት የታክስ ሕግ በመጣሱ ምክንያት በአዋጁ ክፍል 15 ምዕራፍ 2 ወይም በሌላ ሕግ የሚጣል አስተዳደራዊ ቅጣት ነው፡፡ ይህን አንቀጽ ከአዋጁ አንቀጽ 2(16) ጋር ስንመረምረው አስተዳደራዊ ቅጣት ማለት ቅጣትን ብቻ የሚያመለክት መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ምክንያቱም ሕጉ አስተዳደራዊ ቅጣት የሚል ትርጉም የሰጠው ለቅጣት እንጅ ለወለድ ስላልሆነ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አስተዳደራዊ ቅጣቶችን በዝርዝር የሚደነግገው የአዋጁ አንቀጽ 101-115 አስተዳደራዊ ቅጣት የሚል ርዕስ በመስጠት የሚያወራው ስለ ቅጣት እንጅ ስለወለድ አለመሆኑ አስተዳደራዊ ቅጣት የሚለው ፅንሰ ሀሳብ ቅጣትን ብቻ ያመላክታል የሚለውን ክርክር ያጠናክርልናል፡፡ ይህም ከነሀሴ 14 ቀን 2008 ዓ.ም በፊት ሊከፈል ሲገባ ባልተከፈለ ታክስ ላይ የሚጣል አስተዳደራዊ ቅጣት በስራ ላይ በነበሩት የታክስ ሕጎች መሠረት ፍፃሜ የሚያገኘው ባልተከፈለው ታክስ ላይ የሚጣለው ቅጣት ብቻ መሆኑን ያሳያል፡፡ ባልተከፈለው ታክስ ላይ የሚጣለውን ፍሬ ግብር እና ወለድ አያካትትም፡፡ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ የሚጣለው የቅጣት መጠን፣ የቅጣቱ መጠን ከፍሬ ግብሩ መጠን ጋር ያለው ግንኙነት …ወዘተ በቀድሞው የታክስ ሕግ መሠረት ይዳኛል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ሚኒስቴሩ ቅጣት ከፍሬ ግብሩ በበለጠ ሁኔታ መጣል ይችላል፡፡ ምክንያቱም የቀድሞው የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/94 ቅጣት ከፍሬ ግብር መብለጥ የለበትም በማለት እንደ ታክስ አስተዳደር አዋጁ ገደብ ስለማያስቀምጥ ነው፡፡ ስለዚህ ልዩ ሁኔታው እነዚህን ጉዳዮች ለመዳኘት የምንጠቅሰው ድንጋጌ ይሆናል ማለት ነው፡፡

1.2 ከነሀሴ 14 ቀን 2008 ዓ.ም በፊት ተጀምሮ ከዚህ ቀን በኋላ በጉባኤ በመታየት ላይ ያለ ጉዳይ በቀድሞው የታክስ ስነ ስርዓት ሕጎች መሠረት ይዳኛል፡፡ በጉዳዩ ላይ የታክስ ውሳኔ ከዚህ ቀን በፊት ተሰጥቶ በውሳኔው ላይ ቅሬታ ቀርቦ በጉባኤ በመታየት ላይ ያለ ጉዳይ /pending cases/ በተጀመረበት ጉዳይ ይቀጥላል፡፡ ይሁን እንጅ የዚህ ድንጋጌ መሰረታዊ ነገር ቅሬታው ከነሀሴ 14 ቀን 2008 ዓ.ም በፊት ለጉባኤው መቅረብ ያለበት መሆኑ ነው፡፡ ከነሀሴ 14 ቀን 2008 ዓ.ም በፊት በኋላ እንደ አድስ የቀረበ ከሆነ ግን አዋጁ ወደኋላ ሄዶ ይሰራል ማለት ነው፡፡ የልዩ ሁኔታው ተፈፃሚነት እስከዚህ ድረስ ነው፡፡

1.3 ከነሀሴ 14 ቀን 2008 ዓ.ም በፊት በወቅቱ መቅረብ እየነበረበት የአቤቱታው እና የይግባኝ ማቅረቢያው ጊዜ ካለፈ የታክስ አስተዳደር አዋጁ ረጅም የአቤቱታ እና የይግባኝ ማቅረቢያ ጊዜ የሚሰጥ ቢሆንም ለይግባኝ ባዩ ጥቅም ሲባል አዋጁ ወደኋላ ተመልሶ አይሰራም፡፡ ይህም አዋጁ ቸልተኛ ቅሬታ አቅራቢዎችን /negligent complaints/ የማያበረታታ መሆኑን ያሳያል፡፡

በአጠቃላይ የታክስ አስተዳደር አዋጁን የተፈፃሚነት ወሰን ስንመለከተው በመርህ ደረጃ ወደኋላ ሄዶ የሚሰራ ሲሆን በልዩ ሁኔታ ግን ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የሚሰራ መሆኑን ከድንጋጌወቹ መረዳት ይቻላል፡፡ ሕጉ በዚህ ሁኔታ መውጣቱ የህጋዊነት መርህን ይቃረናል አይቃረንም የሚለውን እና ሌሎች ትችቶችን /critics/ ከታች በዝርዝር እንመለከተዋለን፡፡

  1. በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/08 አንቀጽ 102 መሠረት አዋጁ ከሀምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ በተገኘ ገቢ ላይ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ ይሁን አንጅ አዋጁ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣው ነሀሴ 12 ቀን 2008 ዓ.ም ነው፡፡ ይህም አዋጁ የወጣው ነሀሴ 12 ቀን 2008 ዓ.ም ሆኖ እያለ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ተፈፃሚ መሆን ሲገባው ወደ ኋላ በመሄድ ከሀምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ተፈፃሚ እንደሚሆን ያሳያል፡፡ በዚህ ላይ የሚነሳውን ትችት/critics/ ከታች እንመለከተዋለን፡፡
  2. ይህ በእንድህ እንዳለ የሚኒስትሮች የገቢ ግብር ደንብ ቁጥር 410/09 አንቀጽ 71 ደንቡ ከሀምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ በተገኘ ገቢ ላይ ተፈፃሚ እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡ ይሁን እንጅ ደንቡ በሚኒስቴሮች ምክር ቤት የወጣው ነሀሴ 19 ቀን 2009 ዓ.ም ነው፡፡ ይህም ደንቡ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ተፈፃሚ መሆን ሲገባው ወደ ኋላ በመሄድ ተፈፃሚ እንድሆን የተደነገገ መሆኑን በግልፅ ያሣያል፡፡
  3. በጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/06 አንቀጽ 1 እና 183 መሠረት አዋጁ 859/2006 ዓ.ም ተብሎ የሚጠራ ሲሆን አዋጁ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣው ግን ህዳር 30 ቀን 2007 ዓ.ም ነው፡፡ የአዋጁ ስያሜ መሰጠት ያለበት አዋጁ በወጣበት ዓመተ ምህረት መሆን ሲገባው አዋጁ ወደኋላ ሄዶ እንደሚሰራ በማስመሰል አዋጅ ቁጥር 859/06 ብሎ ስያሜ መስጠት ዓላማው ምን እንደሆነ ግልፅ አይደለም፡፡ አዋጁ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ይሰራል የሚል ክርክር ለማንሳት ይሁን ወይም ከስያሜ ስህተት የመጣ ይሁን ግልፅ አይደለም፡፡ ይሁን እንጅ አዋጁ በወቅቱ ሲወጣ ምንም ዓላማ ይኑረው የአዋጁ ስያሜ እና የወጣበት ጊዜ መለያየቱ ከሕግ አወጣጥ መርህ ውጭ በቸልተኝነት የወጣ ሕግ መሆኑን ያሳያል፡፡

ከእነዚህ የመሸጋገሪያ ድንጋጌዎች በመነሳት አዋጁና ደንቡ ወደ ኋላ ሄዶ የሚሰራበት አግባብ ሕገ መንግሥታዊ ነው አይደለም የሚለውን እናያለን፡፡ የህጎቹን ሕገ መንግሥታዊነት በተመለከተ የሕግ ባለሙያዎች ሁለት አይነት ክርክር ያነሳሉ፡፡

አንደኛው የመከራከሪያ ሀሳብ እነዚህ ሕጎች ሕገ መንግሥቱን አይቃረኑም ከሚሉ ባለሙያዎች የሚነሳ ነው፡፡ የሚያነሱትም ምክንያት ሕገ መንግሥቱ የፍትሐብሔር ሕግ (የታክስና የጉምሩክ ሕግን ጨምሮ ) ወደኋላ ሄዶ አይሰራም በሚል በግልፅ አልከለከለም፡፡ ሕገ መንግሥቱ የከለከለው የወንጀል ሕግ ወደኋላ ሄዶ ተፈፃሚ የማይሆን መሆኑን ነው፡፡ የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 22 በግልፅ የሚደነግገው የወንጀል ሕግ ወደኋላ ሄዶ የማይሰራ መሆኑን ነው፡፡ የፍትሐብሔር ሕግ ወደኋላ ሄዶ አይሰራም በሚል እንደ ወንጀል ሕጉ አልከለከለም፡፡ ስለዚህ ዝምታው የፍትሐብሔር ሕግ ወደኋላ ሄዶ እንዲሰራ ሕገ መንግሥቱ ይፈቅዳል፤ ባይፈቅድ ኖሮ እንደ ወንጀል ሕጉ ይከለክል ነበር የሚል ክርክር ያነሳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የታክስና የጉምሩክ ሕጎች ወደኋላ ሄደው መስራታቸው ሕገ መንግሥቱን አይቃረንም በሚል ሀሳባቸውን ይደመድማሉ፡፡ ይህ የክርክር ሀሳብ የሚተችበት ምክንያት አለ፡፡ የትችቱ አንደኛው ምክንያትም ይህ የክርክር ሀሳብ የታክስና የጉምሩክ ሕጎችን የወንጀል ሕግ ይዘት ያላቸው ሕጎች መሆናቸውን ካለመገንዘብ የቀረበ በመሆኑ ነው፡፡ ይሄውም የታክስና የጉምሩክ ሕጎች የፍትሐብሔርና የወንጀል ሕግ ድምር ውጤት መሆናቸው ነው፡፡ እነዚህ ሕጎች የሚደነግጉት የፍትሐብሔር ተጠያቂነትን ብቻ ሳይሆን የወንጀል ተጠያቂነትን ጭምር ነው፡፡ የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/08 አንቀጽ 106-133 ስለ ታክስ ወንጀሎች እና ቅጣታቸው በዝርዝር ይደነግጋሉ፡፡ የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/06 አንቀጽ 166-174 ስለ ጉምሩክ ወንጀሎች እና ቅጣታቸው በዝርዝር ይደነግጋሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው ሕገ መንግሥቱ የፍትሐብሔር ሕግ (ታክስና ጉምሩክ ሕግ) ወደኋላ ሄዶ አይሰራም በሚል እንደ ወንጀል ሕጉ ያልከለከለ በመሆኑ ሕገ መንግሥቱን አይቃረኑም የሚል ክርክር የምናነሳ ከሆነ እነዚህ ሕጎች በውስጣቸው የወንጀል ድንጋጌዎችንም ስለያዙ የወንጀል ጉዳዩም ወደኋላ ሄዶ ይሰራል የሚል ድምዳሜ ላይ የምንደርስ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ደግሞ በግልፅ ሕገ መንግሥቱን ይቃረናል፡፡ ምክንያቱም ሕገ መንግሥቱ በግልፅ የወንጀል ሕግ ወደኋላ ተመልሶ አይሰራም በሚል ስለሚደነግግ ነው፡፡ ከላይ እንደገለፅኩት የታክስና የጉምሩክ ሕጎች የፍትሐብሔር፣ የወንጀልና የስነ ስርዓት ሕግም ጭምር ስለሆኑ ህጎቹ ወደኋላ ሄደው መስራታቸው ሕገ መንግሥቱን አይቃረንም የሚለው መከራከሪያ ውሀ የሚቋጥር አይደለም፡፡ ምክንያቱም በኢፌድሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 22(1) መሠረት የወንጀል ሕግ ወደኋላ ሄዶ አይሰራም ስለሚልና ይሄ ክልከላም ከወንጀሉ ጉዳይ ጋር ተያይዞ በአንድ ኮድ ለተደነገገው የፍትሐብሔር ሕግም ስለሚሰራ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ አንደኛ በታክስና በጉምሩክ ሕጎች ውስጥ የፍትሐ ብሄሩም ሆነ የወንጀል ጉዳዩ አብረው በአንድ ኮድ ነው የተቀመጡት ፤ ሁለተኛ የህዝብን ጥቅም /public interest/ የሚጠብቀው የወንጀል ሕግ ወደኋላ ሄዶ አይሰራም ከተባለ የግል ጥቅምን /private interest/ የሚጠብቀው በታክስና ጉምሩክ ሕጉ ውስጥ የተቀመጠው የፍትሐብሔር ሕግ ወደኋላ ሄዶ የሚሰራበት አመክንዮ /logic/ የለም፡፡

ሁለተኛው የክርክር ሀሳብ ደግሞ ከላይ የጠቀስናቸው የታክስና የጉምሩክ ሕጎች ሕገ መንግሥቱን ይቃረናሉ፤ሕገ መንግሰታዊ አይደሉም ከሚሉ ባለሙያዎች የሚቀርብ ነው፡፡ እኔም ይህንን ሀሳብ ከሚጋሩ ባለሙያዎች አንዱ ስሆን ከላይ የጠቀስናቸው ወደኋላ ሄደው ተፈፃሚ የሚሆኑ የታክስና የጉምሩክ ሕጎች ሕገ መንግሥቱን ያቃረናሉ፡፡ ምክንያቱም፡-

1. የሕገ መንግሥቱ መግቢያ እኛ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች "በሀገራችን ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ድሞክራሲ ለማምጣት……..ወዘተ " ከዚህ ቀን ጀምሮ በተወካዮቻችን አማካኝነት ይህን ሕገ መንግሥት አውጥተናል ማለቱ በራሱ የህጋዊነት መርህን /principle of legality/ ያሳያል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በመግቢያው ላይ ከዚህ ቀን ጀምሮ ሕገ መንግሥት አፀደቅን ይላል እንጅ ወደኋላ ሄዶ ይሰራል አይልም፡፡ እንዴውም ከዚህ በፊት የተዛባ ታሪካችንን / የኋላ ታሪካችንን/ ለማረም ከነሀሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም ጀምሮ ተፈፃሚ የሚሆን ሕገ መንግሥት ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም አፀደቅን ይላል እንጅ የኋላ ታሪካችንን ለማረም ሕገ መንግሥቱ ወደኋላ ሄዶ ይሰራል አይልም፡፡ የሕገ መንግሥቱ መግቢያ በቁጥር 1 እና 3 ላይ ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ ሳይሆን ከነሀሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም ጀምሮ ስራ ላይ የሚውል መሆኑን መደንገጉ ሕገ መንግሥቱ ወደ ፊት እንጅ ወደኋላ ሄዶ የማይሰራ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህም የሀገሪቱ ሕግ ቁንጮ የሆነው ሕገ መንግሥት ከወጣበት ቀን ጀምሮ የሚሰራ መሆኑን ያሳያል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አውጭዎች ፍላጎትም /intention of the legislator/ ሕገ መንግሥቱ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ወደፊት እንድሰራ ማድረግ መሆኑን ከመግቢያው መረዳት ይቻላል፡፡  የሕገ መንግሥቱ መግቢያ ሁለት አንድምታ /two ways of interpretation in one expression/ አለው፡፡

. ሕገ መንግሥቱ በራሱ ወደ ፊት እንጅ ወደኋላ ተመልሶ የማይሰራ መሆኑን ነው፡፡ ምክንያቱም የሕገ መንግሥቱ ባለቤትና አውጭዎች ከዚህ ቀን ጀምሮ ተፈፃሚ የሚሆን ሕግ አወጣን እንጅ ከመውጣቱ በፊት ለተፈፀሙ ድርጊቶች ወደኋላ ሄዶ ተፈፃሚ የሚሆን ሕግ አወጣን ብለው አላስቀመጡም፡፡

ሌሎች ከሕገ መንግሥቱ በታች ያሉ ሕጎችም የሕገ መንግሥቱን ፈለግ በመከተል ሕጉ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተፈፃሚ እንደሚሆን ወይም /proactive/ በሆነ መንገድ መውጣት እንዳለበት የሚጠቁም ነው፡፡ ምክንያቱም የሀገሪቱ የበላይ ሕግ የሆነው ሕገ መንግሥት ከወጣሁበት ቀን ጀምሮ ተፈፃሚ እሆናለሁ ካለ ሌሎች ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርገው የሚወጡና ሕገ መንግሰቱን መጣስ /መቃረን/ የማይችሉ ሕጎችም በዚሁ መልክ መውጣት አለባቸው የሚል መልዕክት እያስተላለፈ ነው ማለት ነው፡፡ ሰለዚህ የታክና የጉምሩክ ሕጎች ወደኋላ ሄደው ተፈፃሚ እንድሆኑ በአዋጅና በደንብ መደንገጉ ሕገ መንገስቱን ይጥሳል ፤መጣስ ብቻ ሳይሆን ሕገ መንግሥቱ አታድርግ ያለውን ነገር ሕግ አውጭው አካል ያደረገ መሆኑን ያሳያል፡፡

2. ሕገ መንግሥቱ ከመግቢያው በተጨማሪ በአንቀጽ 22 (1) ላይ ማንኛውም የወንጀል ሕግ ተፈፃሚ የሚሆነው ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ነው በሚል ይደነግጋል፡፡ የወንጀል ሕግ ወደኋላ ተመልሶ አይሰራም በማለት በግልፅ ይደነግጋል፡፡ ሕጉ ከመውጣቱ በፊት ለተፈፀመው ድርጊት ወደኋላ ሄዶ አይሰራም በማለት በመግቢያው ላይ የተገለፀውን የህጋዊነት መርህ ይበልጥ ያጠናክረዋል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ መረዳት የሚቻለው ሕግ ተፈፃሚ የሚሆነው ከወጣበት ቀን ጀምሮ መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን የወንጀል ሕጉ ወደኋላ ሄዶ መስራት ተጠርጣሪውን የሚጠቅመው ከሆነ ግን ሕጉ ወደኋላ ሄዶ ይሰራል፡፡ ይህ ድንጋጌ የሚያሳው የህጋዊነት መርህ ልዩ ሁኔታ /exception/ ያለው መሆኑን ነው፡፡ ይሄውም ልዩ ሁኔታው ተፈፃሚ የሚሆነው፡-

  • በወንጀል ጉዳይ ላይ
  • ወንጀል ብቻ መሆኑ ሳይሆን ወደኋላ ሄዶ መስራቱ ተከሳሹን የሚጠቅመው ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም የወንጀል ሕጉ ወደኋላ ሄዶ የሚሰራው ተከሳሹን ሲጠቅመው ብቻ እንጅ መንግስትን የሚጠቅመው ሆኖ ሲገኝ አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱ በልዩ ሁኔታ ሕግ ወደኋላ ሄዶ ተፈፃሚ ይሆናል የሚለው በወንጀል ጉዳይ ላይ ተከሳሹን የሚጠቅም ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የፍትሐብሔር ሕግ ተከሳሹን የሚጠቅመው ቢሆን እንኳን ወደኋላ ሄዶ ይሰራል አላለም፡፡ ከሕገ መንግሥቱ መግቢያና ከአንቀጽ 22(1) መረዳት የሚቻለው ሕግ ወደ ፊት /proactively/ ተፈፃሚ መሆኑን ነው፡፡ ሆኖም የታክስና ጉምሩክ ሕጎች የፍትሐብሔርና ወንጀል ሕግ ድምር ውጤት በመሆናቸውና በአንድ ኮድ ስር ተደንግገው የሚገኙ ሕጎች በመሆናቸው ሕገ መንግሥቱ በግልፅ የወንጀል ሕግ ወደኋላ ሄዶ አይሰራም የሚለው ድንጋጌ ከወንጀሉ ጋር አብረው በአንድ ኮድ ለተሰነዱት የህጎቹ ፍትሐብሔራዊ ወይም አስተዳደራዊ ክፍል ሕግም ስለሚሰራ የታክስና የጉምሩክ ሕጎች ወደኋላ ሄደው ተፈፃሚ መሆናቸውና በዚሁ አግባብ በሕግ ደረጃ መውጣታቸው ሕገ መንግሥቱን ይጥሳሉ፡፡ ጉዳዩን ይበልጥ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ የሚያደርገው ደግሞ የታክስና የጉምሩክ ሕጎች /የፍትሐብሔርና የወንጀል ሕጎች/ ወደኋላ ሄደው ተፈፃሚ እንዲሆኑ የተደነገጉት ለግለሰብ ጥቅም ሳይሆን ለመንግስት ጥቅም ሲባል መሆኑ ነው፡፡

ስለዚህ ሕገ መንግሥቱ በግልፅ የወንጀል ሕግ መንግስትን ሳይሆን ተከሳሹን የሚጠቅም ሆኖ ሲገኝ ብቻ በልዩ ሁኔታ ተፈፃሚ ይሆናል እያለ የታክስና የጉምሩክ ሕጎች /የፍትሐብሔርና የወንጀል ሕጎች/ ለመንግስት ጥቅም ሲባል ወደኋላ ሄደው መስራታቸው ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን ነው፡፡

3. በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 79 የተደነገገውን የፍ/ቤቶችን የዳኝነት ነፃነት የሚጥስ በመሆኑ ሕገ መንግሥቱን ይቃረናል፡፡ በኢፌድሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 79 (1-3) መሠረት የዳኝነት ስልጣን ለፍ/ቤት የተሰጠ ሲሆን ከማናቸውም አካል ተፅዕኖ (ሕግ አውጭውንና አስፈፃሚውን ጨምሮ) ነፃ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ መረዳት የሚቻለው አንድ ፍ/ቤት የሰጠውን ውሳኔ ሕግ አውጭው ሕግ በማውጣት ሕግ አስፈፃሚው በማስፈፀም አቅሙ መሻር የማይችል መሆኑን ነው፡፡ የፍ/ቤት ውሳኔ የሚሻረው በሕግ የተቀመጠውን ስነ ስርዓት ተከትሎ በይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ወይም በሰበር ሰሚ ፍ/ቤት ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይም የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 15 በመዝገብ ቁጥር 85718 አንድ ፍ/ቤት ጉዳዩን ለማየት ስልጣን ሳይኖረው የሰጠው ውሳኔ ቢሆን እንኳን ውሳኔው በይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት እስካልተሻረ ድረስ አስገዳጅ፣ ተፈፃሚነት ያለው እንዲሁም ህጋዊ ውሳኔ ነው የሚል አስገዳጅ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ይህም ሀሳብ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 212 ላይ በግልፅ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ስለዚህ የታክስና የጉምሩክ ሕጎች በፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ከወጡበት ቀን በፊት ወደኋላ ሄደው ተፈፃሚ እንዲሆኑ መደንገጉ ፍ/ቤቶች ሕጉ ከመውጣቱ በፊት በነበረው ሕግ መሠረት የሰጡትን ውሳኔ ሌላ ወደኋላ ሄዶ የሚሰራ ሕግ በማውጣት ሕግ አውጭው የፍ/ቤትን ውሳኔ እየሻረ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የፍ/ቤትን ውሳኔ በእጅ አዙር እንደመሻርና በዳኝነት ነፃነቱ ላይ ጣልቃ መግባት ነው፡፡ ለምሳሌ በቀድሞው የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/94 እና ደንብ ቁጥር 78/94 አንቀጽ 15(3) መሠረት አንድ ድርጅት የካፒታል ንብረቶችን (አክሲኖችን) ሲያስተላልፍ የዋጋ ግሽበት ማስተካከያ /inflation adjustment/ ይደረግለት ነበር፤በአሁኑ የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/08 አንቀጽ 59(7)(ለ) እና የገቢ ግብር ደንብ ቁጥር 410/08 አንቀጽ 56(1) መሠረት ግን ለአክሲዮን ሽያጭ የዋጋ ግሽበት ማስተካከያ አይደረግም ፤ማስተካከያ የሚደረገው ለምድብ "" (ለማይንቀሳቀስ ንብረት) ነው፡፡ ይሄ ሕግ ደግሞ በፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ከወጣበት ቀን በፊት ማለትም ከነሀሴ 19 ቀን 2009 ዓ.ም በፊት ወደ ኋላ ሄዶ ከሀምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ደንቡ ከመውጣቱ በፊት (እስከ ነሀሴ 19 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ) አንድ ጉዳዩ የቀረበለት ፍ/ቤት በቀድሞው ሕግ መሠረት ለአክሲዮን ሽያጭ የዋጋ ግሽበት ማስተካከያ ይደረጋል በማለት የሰጠውን ውሳኔ የአሁኑ ደንብ ወደ ኋላ ሄዶ ከሀምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ተፈፃሚ ስለሚሆንና የዋጋ ግሽበት ማስተካከያ ለአክሲዮን ሽያጭ አይደረግም በሚል ስለሚደነግግ የፍ/ቤቱን ውሳኔ ደንቡ እየሻረው ነው ማለት ነው፡፡

4. ሌላው የሕጉ ስህተት ወደኋላ ሄዶ መስራትን እንደ መርህ /principle/ ማስቀመጡ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕግ ተቀባይነት ባለው የሕግ አወጣጥ መርህ /commonly accepted legislative drafting principle/ መሠረት መርህ /principle/  መጀመሪያ ይገለፃል ከዚህ በኋላ ልዩ ሁኔታ ይቀመጣል፡፡ ከላይ ባነሳኋቸው የታክስና ጉምሩክ ሕጎች ላይ መርህ መሆን ያለበትና መጀመሪያ መቀመጥ ያለበት የሕጉ የወደፊት ተፈፃሚነት /proactive application/ ነበር፡፡ ነገር ግን እንደመርህ በመጀመሪያ የተቀመጠው የሕጉ ወደኋላ ሄዶ ተፈፃሚ መሆን ሲሆን እንደልዩ ሁኔታ የተቀመጠው ደግሞ የሕጉ የወደፊት ተፈፃሚነት /proactive application/ ነው፡፡ ለምሳሌ በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/08 አንቀጽ 137(1) መሠረት የሕጉ ወደኋላ ሄዶ ተፈፃሚ መሆን መርህ ነው፤መጀመሪያ ተቀምጧል፤ በአንቀጽ 139(1) መሠረት ደግሞ  የሕጉ የወደፊት ተፈፃሚነት እንደ ልዩ ሁኔታ ነው የተቀመጠው፡፡ ይህ ከሕግ አወጣጥ መርህ ውጭ የሆነ ነገር ነው፡፡   

  

መ. ሕገ መንግሥቱን የጣሰ ሕግ ምን ይሆናል ?

በኢፌድሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9 (1) መሠረት ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን ሕግ ተፈፃሚነት የለውም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይህንን ቢያስቀምጥም አዋጁና ደንቡ ሕገ መንግሥቱን ስለሚቃረን አንፈፅምም፤አንገዛም ማለት አንችልም፡፡ ምክንያቱም በሕግ የበላይነት /rule of law/ መርህ መሠረት ማንኛውም ሰው ከሕግ በታች ስለሆነ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 መሠረት ለፌደሬሽን ምክር ቤት አቅርበን ሕጉ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ /unconstitutional/ ነው የሚል ውሳኔ እስካልተሰጠ ድረስ ሕጉ ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡፡ ይህንን ኢ-ሕገ መንግሥታዊ የሆነ ሕግ ሕገ መንግሥታዊ ለማድረግ ከሕግ ባለሙያወች፣ጠበቃወች እና ከፍ/ቤቶች ምን ይጠበቃል፡፡

/ቤት ----- በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 84(2) መሠረት የታክስና ጉምሩክ ጉዳዮች ሲመጡለት ጉዳዮቹን በተለይም የተነሳው የሕግ ክርክር የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል አያስፈልገውም የሚለውን በጥንቃቄ በመመርመር የሕገ መንግሥት ትርጉም የሚያስፈልገውን ለሕገ መንገስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ መምራት፤

ጠበቃዎች ------ በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 84(2) መሠረት የታክስና የጉምሩክ ጉዳዮችን የሚይዙ ጠበቆች የያዙትን ጉዳይ በተለይም የሚያነሱትን የሕግ ክርክር መነሻ በማድረግ የሕገ መንግሥት ትርጉም የሚያስፈልገውን ለሕገ መንገስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ማመልከት፤

ባለስልጣኑ/ሚኒስቴሩ------- ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመነሻ ሀሳብ በማቅረብ ጉዳዩን ተመልክቶት የማሻሻያ አዋጅ እንድያወጣ ማድረግ ይጠበቅበታል፤

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ------ ከላይ የጠቀስናቸውን የታክስና የጉምሩክ ሕጎች እንደገና ተመልክቶ ወደኋላ ሄዶ ይሰራል የሚለውን የህጎቹን ድንጋጌ በአዋጅ ማንሳት/ማሻሻል/ ይጠበቅበታል፡፡

የሕግ ባለሙያዎች ----- የታክስና የጉምሩክ ጉዳዮችን የምንከታተል የባለስልጣኑ ባለሙያዎች ሕገ መንግሥቱን የሚቃረኑ ሕጎችን በመለየት ለባለስልጣኑ የበላይ ሃላፊ በማቅረብ ጉዳዩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ሕጉ እንድሻሻል ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

                 የመፍትሄ ሃሳብ

1. ሕግ አውጭው ሕግ ሲያወጣ ሕገ መንግሥቱን በአግባቡ መመርመርና ሕገ መንግሥታዊ ሕጎችን ማውጣት አለበት፡፡

2. ሚኒስቴሩም ሕገ መንግሥታዊ የሆኑ ሕጎች እንዲወጡ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግና የወጡት ሕጎች ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ከሆኑም በፓርላማ እንዲታረሙ የማድረግ ግደታም ጭምር አለበት፡፡

 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

‘ኮማንድ ፖስት’ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተሰጠ ልዋጭ ስም?
ንብረት የማፍራት እና ፍትሐዊ ዳኝነት የማግኘት መብት: ከወቅታዊው የሕገ-ወጥ መ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 21 November 2024