Font size: +
7 minutes reading time (1482 words)

ንብረት የማፍራት እና ፍትሐዊ ዳኝነት የማግኘት መብት: ከወቅታዊው የሕገ-ወጥ መሬትና ንብረት ማስመለስና ማፍረስ ጋር በተያያዘ

አሁን አሁን በተለያዩ የሃገራችን ክልሎች በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ ዙርያ በሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ከተሞች ላይ ከዕለት ወደዕለት በዜጎች የመዘዋወር መብት፤ንብረት የማፍራት፤ የእኩልነት እና ፍትህ የማግኘት ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሕግ ማስከበር ሰበብ ሲጣሱ ማዬት የዕለት ተዕለት ተግባራዊ ኩነት እየሆነ መጥቷል፡፡

የዚህ አጭር ጽሑፍ መነሻ ነጥብም በሕግ ማስከበር ሰበብ ለረዥም አመታት ከማህበረሰቡ ጋር በመቀላቀል ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ንብረት ያፈሩ ዜጎች ላይ በሕገ ወጥነት ሰበብ እየተወሰደ ያለውን ከገዛ ቤታቸውና ንብረታቸው የማፈናቀል እርምጃን በተመለከተ ዜጎች መብቶቻቸውን በሕግ አግባብ እንዴት ማስከበር እንዳለባቸው የሚያሳይ ፍኖተ ሕግ ነው፡፡

የህጉን ዝርዝር ነጥብ ከመመልከታቸን በፊት አሁን መሬት ላይ ያለው እውነትን በጨረፍታ ለመመልከት መሞከሩ ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባ ዙርያ የሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች መካከል የሰበታ ከተማ አስተዳደር፤ የቡራዩ ከተማ አስተዳደር፤ የለገጣፎ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም የሱሉልታ ከተማ አስተዳደር የከተሞቻቸውን የማስተር ፕላን ጋር ተቃራኒ የሆኑ እንዲሁም ቀድሞ ካሳ የተከፈላቸው እና በሕገ ወጥ መንገድ ከመንግስት እውቅና ውጭ ንብረት ያፈሩ ወይም በተለምዶ ወቅታዊ አጠራሩ ሕገ ወጥ ግንባታዎችን  አጭር የማስጠንቀቂያ ጊዜ በመስጠት ነዋሪዎቹ ለዓመታት ይኖሩበት የነበረውን በጉልበታቸውና በጥሪታቸው ያፈሩትን ሃብቶቻቸውን በሃይል ድርጊት እንዲፈርስ በማድረግ በተጨባጭ ዜጎች ከሃብት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ መደረጉ ለብዙ ቅሬታ መነሻ ነጥብ ሆኖ መገኘቱ ነው የዚህ ጽሑፍ መነሻ ነጥብ፡፡ በመሆኑም ዜጎች ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈጸምባቸው በምን አግባብ መብቶቻቻውን ማስከበር እንደሚችሉ ከኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት እና ከአዋጅ ቁጥር 721/2004 ጋር በማመሳከር ረጂ ናቸው ብዬ ያሰብኳቸውን ነጥቦች ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡  

በቅድሚያ የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 25 መሰረት ማንኛውም ሰው ልዩነት ሳይደረግበት በሕግ እኩል ያልተነጣጠለ እና አድሏዊ ባልሆነ መልኩ ጥበቃ እንደሚደረግለትና  እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት እንዳላቸው በማያሻማ ቋንቋ የማይገረሰሰ ሰብዓዊ መብት እንደሆነ ደንግጎ ይገኛል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከጉዳያችን ጋር ተያያዥነት ባለው መልኩ በዚሁ ሕገ መንግስት አንቀፅ 32 ላይ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በመረጠው የሃገሪቱ አካባቢ የመዘዋዋርና የመኖርያ ቤት የመመስረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሃገር የመውጣት ነፃነት እንዳለውና በአንቀጽ 40/7ም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በጉልበቱ ወይም በገንዘቡ በመሬት ላይ ለሚገነባው ቋሚ ንብረት ወይም ለሚያደርገው ቋሚ መሻሻል ሙሉ መብት አለው በማለት እርስ በርስ ተመጋጋቢ እና ተደጋጋፊ በሆነ መልኩ የዜጎችን ንብረት የማፍራትና በሃገራቸው በነፃነት የመዘዋወር ዲሞክራሲያዊ መብቶችን በዝርዝር ይጠቅሳል፡፡

ይህም የሚያሳዬው ማንኛውም ሰው ኢትዮጵያዊም /ኦሮሞ፤ አማራ፤ ትግሬ፤ ወላይታ፤ ጋሞ፤ ጉራጌ፤ ጋምቤላ፤ አፋር ወ.ዘ.ተ/ ሆነ በህጋዊ መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ የሚንቀሳቀስ የውጭ ዜጋ በሃገሪቱ የትኛውም ቦታ ተንቀሳቅሶ በእኩልነት ያለምንም አድሎ ንብረት የማፍራት ሙሉ መብት እንዳለው ገላጭ ነው፡፡ በመሆኑም ነባራዊ ሁኔታው ላይ ዝርዝር ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም ከላይ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ በሆኑት አካባቢዎች እየተወሰደ ነው ተብለው የተገለፁት በሕገ ወጥ ስም ቤት የማፍረሱ ተግባር ከሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተለያየ ምክንያት የመጡና መኖሪያቸውን በነዚሁ አካባቢ ያደረጉ የተለያዩ ብሄር፤ብሄረሰቦች ነዋሪዎች መሆናቸውን ከተለያዩ ሚዲያዎች ለመገንዘብ እንችላለን፡፡ ይህም የዜጎች መግባቢያ እና መተዳደርያ ሰነድ በሆነውና የህጎች የበላይ ተደርጎ የሚቆጠረውን ሕገ መንግስቱ ላይ በግልፅ የተጠቀሰውን የእኩልነት ሰብዓዊ መብት የሚጥስ እና መንግስትንም የሚያስጠይቅ ድርጊት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

ከዚህ ባሻገር ከላይ የተጠቀሰውን ዜጎች ሕገ-መንግስታዊ መብት ተላልፎ መንግስት በዜጎች ላይ እርምጃ ቢወስድ ኤጎች መብቶቻቸውን ለማስከበር ሊከተሉት የሚገባ የሕግ መስመር ምንድነው ከተባለ ከዚህ በታች በተገለፀው ህጋዊ መስመር ዜጎች መብቶቻቸውን ማስከበር ይችላሉ መንግስትም ይህንን መንገድ የመከተል ግዴታ አለበት፡፡

በቅድሚያ  በአዋጅ ቁጥር 721/2004 የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ መሰረት የከተሜነት እና የከተሞች ከዕለት ወደዕለት የማደግ ፍላጎት እንዲሁም መሬትውስን ሃብት በመሆኑ ይህንን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለተፈለገለት ዓላማ ብቻ በህጋዊ መንገድ ማስተላለፍ ተገቢ ስለሆነ አዋጁ ሊወጣ ችሏል፡፡ በዚህ አዋጅም መሰረት ከያዝነው ነጥብ ጋር የሚገናኙ ነጥቦች ላይ ትኩረት ማድረጉ አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ እንደሚከተለው ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡

በዋንኛነት የዚህ ጽሑፍ አንባቢ መገንዘብ ያለበት ሕገ ወጥነትን የሚደግፍ ጽሑፍ አለመሆኑንና ሕገ ወጥነት በራሱ በተገቢው የሕግ መስመር እርምጃ ሊወሰድበት የሚገባ መሆኑን ጽሑፊው ያምናል፡፡ ሆኖም ግን ለረጅም ጊዜያት መንግስት እና ተገቢው የአስተዳደር እርከንና መዋቅር ባለበት ከተማ ውስጥ አሁን ላይ ሕገ-ወጥ ተብለው ለፈረሱ እና ሊፈርሱ የተዘጋጁ ቤቶች ላይ ይኄው መንግስታዊ መዋቅር ከግንባታው ጊዜ አንስቶ ሳያውቀው የተፈጸመ አንዳች ድርጊት በሌለበትና ለነዚሁም ግንባታዎች አስፈላጊውን መሰረት ልማት ካሟላ በኃላ በተግባር ህጋዊነታቸውን ሲያረጋግጥ በሰነድ ግን ሕጋዊ አይደላችሁም ማለት ሥነ-አመክንዊ መሰረት የሌለው ድርጊት በመሆኑ ይህንኑ የሕግ መስመር ማስያዙ ተገቢ መስሎ ስለታየኝ ይህንን ጽሑፍ ለማዘጋጀት መገደዴን እንድትረዱት እፈልጋለሁ፡፡

እናም በሃገሪቱ ሕገ መንግስት አንቀፅ 37/1/ መሠረት ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ስልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት እንዳለው በመሰረታዊ መብቶች ውስጥ የገለፀ በመሆኑ ዜጎች መብታቸውን ሊያሳጣ የሚችል ሁኔታ ሲያጋጥም በተለይም በሕገ-ወጥነት ሰበብ ከቤት ንብረታቸው እንዲነሱ የሚያስገደድ ድርጊት ሲያጋጥም በአዋጅ ቁጥር 721/2004 ላይ የተጠቀሱትን ከዚህ በታች የተገለፁትን ህጋዊ ቅደም ተከተሎችን በመከተል መብቶቻቸውን ማስከበር ይችላሉ፡፡

በአዋጁ አንቀፅ 26/4/ መሰረት አግባብ ያለው አካል በሕገ ወጥ መንገድ የተያዘን የከተማ ቦታ በዚህ አዋጅ አንቀፅ 27 መሠረት የማስለቀቂያ ትዕዛዝ መስጠትና ካሣ መክፈል ሳያስፈልግ የ7 ስራ ቀናት የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ብቻ ለባለይዞታው በአካል በመስጠት ወይም በቦታው በሠፈረው ንብረት ላይ በመለጠፍ የማስለቀቅ ስልጣን ይኖረዋል በማለት ደንግጎ እናገኛለን፡፡ ሆኖም ግን በዚህ አንቀፅ ውስጥ ሰፊ ትርጉም የሚያሻውና በማስረጃ ተመዝኖ ሊረጋገጥ የሚገባ ነጥብ ያለ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ይህም ‘’ በሕገ ወጥ መንገድ የተያዘን የከተማ ቦታ’’ ይህ ቃል አሻሚ ከመሆኑ ባሻገር ይህ ቦታ በሕገ ወጥ መንገድ የተያዘ መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት የመንግስት ድርሻ መሆኑን እና የማስረት ሸክሙም መንግስት ላይ የወደቀ መሆኑን ያሳያል፡፡ ስለሆነም አግባ ያለው አካል የተባለው አካል በቂ ማስረጃ ሎኖረው ይገባል፡፡ ስለሆነም በማስረጃ የሚረጋገጥና ሊስተባበል የሚችል እውነት የተገኘ እንደሆነ ገለልተኛ የሆነ አካል ጉዳዩን ሊመረምረውና ተገቢውን ውሳኔ ሊሰጠው ይገባል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም በዚህ ጉዳይ ላይ እንደጭብጥነት የሚነሳ ነጥብ አለና ይኄውም ‘’ ይዞታው በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘ ነው ወይንስ አይደለም የሚል’’ ስለሆነም ይህ ጭብጥ በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 37 በተገለጸው አግባብ ፍትሃዊ የዳኝነት አካል ተገቢው ማጣራት ተደርጎ ውሳኔ እስከሚያገኝ ድረስ ክርክር የተነሳበት ንብረት ላይ እርምጃ መውሰድ ተገቢነት የሌለውና መንግስታዊ ሕገ-ወጥነት አመላካች ሊሆን ይችላል፡፡ ታዲያ ይህ ጭብጥ በሕግ መስመር ይፈታል ካልን የአቤቱታና ቅሬታ ሥነ ሥርዓቱ እንዴት ነው የሚለው ምላሽ የሚስፈልገው ነው፡፡

አንደኛ፡- በአዋጁ አንቀፅ 28 ላይ የማስለቀቂያ ትዕዛዝና ማስጠንቀቂያን የተመለከቱ አቤቱታዎች እንዴት መቅረብ እና ለማን መቅረብ እንዳለባቸው ጠቅሷል፡፡ ይኄውም

  1. በዚህ አዋጅ አንቀፅ 27/1 መሰረት የማስለቀቂያ ትዕዛዝ የደረሰው ወይም ትዕዛዝ በተሰጠበት ንብረት ላይ መብቴ ወይም ጥቅሜ ይነካብኛል የሚል ማንኛውም ሰው ትዕዛዙ በደረሰው 15 የሥራ ቀናት ውስጥ ያለውን አቤቱታ ከዝርዝር ምክንያቱና ማስረጃው ጋር አግባብ ላለው አካል ማቅረብ ይችላል፡፡
  2. በዚህ አወዘጅ አንቀፅ 26/4 መሠረት ማስጠንቀቂያ የደረሰው ሰው ማስጠንቀቂያው በደረሰው በ7 የሥራ ቀናት ውስጥ አቤቱታውን አግባብ ላለው አካል ማቅረብ ይችላል፡፡
  3. አግባብ ያለው አካል የቀረበለትን አቤቱታ በአግባቡ በማጣራት ውሳኔ መስጠትና ውሳኔውን ለአቤቱታ ኣቅራቢው በጽሑፍ ማሳወቅ አለበት፡፡ የቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት ያላገኘ እንደሆነ ምክንያት በግልፅ በውሳኔው ውስጥ መገለፅ አለበት፡፡

ስለሆነም ከዚህ በላይ በአንቀፁ እንደተገለጸው ህጋዊ ባለይዞታ የሆነ እና በህጉ አግባብ ተገቢው የማስለቀቂያ ትዕዛዛ የተሰጠበት ሰው በ15/አስራ አምስት/ ቀናት ውስጥ አቤቱታ የማቅረብ መብት ያለው ሲሆን ሆኖም ግን በያዝነው ጭብጥ ላይ ሕገ-ወጥ ባለይዞታ ነህ የተባለ ሰው ማስጠንቀቂያው በደረሰው በ7/ሰባት/የሥራ ቀናት ውስጥ/ቅዳሜ እና እሁድ ጨምሮ/ በ9/ዘጠኝ/ ተከታታይ ቀናት ውስጥ ቅሬታውን ለሚመለከተው የከተማ አስተዳደር ማቅረብ ይችላል፡፡ ቅሬታውን የተቀበለው አግባብ ያለው የከተማ አስተዳደር ለቀረበው አቤቱታና ቅሬታ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ለአቤቱታው  ተገቢውን ምላሽ በጽሑፍ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ ይህ የከተማ አስተዳደሩ የጽሑፍ ምላሽ ነው እንግዲህ ለቀጣዩ የሕግ የመብት ጥያቄ ስርዓትን ለመከተል አጋዥ የሚሆነው፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ለቀረበለት ቅሬታ የጽሑፍ ምላሽ ከሰጠ እና ውሳኔውን ያጸና መሆኑን ከገለፀ ቀጣዩ አካሃሄድ በአዋጁ አንቀፅ 29 መሰረት በክልሉ ወይም በከተማ አስተዳደሩ ለተቋቋመው ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ ውሳኔው በጽሑፍ ከደረሰበት ቀን ጀምሮ ባሉት 30/ሰላሳ/ ቀናት የቅሬታ አቤቱታውን በመያዝ ይግባኝ ለመጠየቅ ይችላል፡፡ ጉባዔውም የቀረበለትን ይግባኝ መርምሮ በ30 ቀናት ውስጥ መርምሮ ውሳኔ መስጠት ያለበት ሲሆን የሰጠውንም ውሳኔ በጽሑፍ ለተከራካሪ ወገኖች ማሳወቅ ግዴታ አለበት ሲል ደንግጓል፡፡ ይግባኝ ሰሚ ጉባዔው አግባብ ያለውን የስር አስተዳደር አካሉን ውሳኔ ቢያጸና የህጉ ውጤት ምንድነው ቢባል ቀጣዩ አቤቱታ እሚሆነው በካሳ ክርክር ላይ ብቻ ለመደበኛ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ይግባኙን ማቅረብ እንደሚቻል ይገልፃል፡፡ ይህ ማለት ይግባኝ ሰሚ ጉባዔው በሕግና በፍሬ ነገር ክርክሮች ላይ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ በመሆኑ ይግባኝ የማይባልበት ነው በማለት ህጉ አትቷል፡፡

እንግዲህ ይህ ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ የሚሰጠው ዳኝነት ከተፅዕኖዎች ነጻ ነው ወይ ተብሎ ቢጠየቅ አዋጁ በአንቀጽ 30/7/ ላይ ጉባዔው ከሕግ በስተቀር ከማናቸውም ተፅኖዎች ነፃ ይሆናል በማለት ደንግጓል በተቃራኒው ደግሞ በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 8 ደግሞ ጉባዔው ስራውን በሚያከናውንበት ጊዜ በመደበኛው የፍትሃ ብሄር ሥነ ሥርዓት ሕግ አይመራም፡፡ ሆኖም በክልሉ ወይም በከተማ አስተዳደሩ በሚወሰን በተቀላጠፈ ሥነ ሥርዓት ይመራል ሲል በቀጥታ የከተማ አስተዳደሩ ወይም የክልሉ ውሳኔ ሰጭ አካል በጉዳዩ ላይ በሥነ- ሥርዓት ሰበብ ለጉዳዩ አቅጣጫ መስጠት እንደሚችል ይገልፃል፡፡ ይህም ጉባዔውን ከፖለቲካዊ ውሳኔዎችና ተፅዕኖዎች የጸዳ ነው ለማለት እንዳይቻል ያደርገዋል/በዚህ ጉዳይ ወደፊት በሰፊው እመለስበታለሁ/፡፡ ሆኖም ግን ማንኛውም ቅሬታ ያለበት ወገን ይህንን የሕግ ስርዓት በመከተል መብቱን ለማስከበር እንደሚችል ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡

ሆኖም ግን በዚህ አቤቱታ ሂደት ውስጥ አግባብ ያለው አካል በሕግ የተጣለበትን ኃላፊነት ማለትም ለሚቀርብለት አቤቱታ የጽሑፍ ምላሽ መስጠት ሲኖርበት ይህንኑ ባይሰጥ ሊኖር የሚችለው የሕግ ውጤት ምንድነው ቢባል መስርያ ቤቱ በራሱ ሕገ-ወጥ ነው በማለት አፍን ሞልቶ ምላሽ መስጠት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም አንድን ድርጊት ሕገ-ወጥ የሚያስብለው በሕግ የተደነገገን አድርግ የተባለን ነገር አለማድረግና አታድርግ የተባለን ነገር ማድረግ ነውና፡፡

በስተመጨረሻም፡- አግባብ ያለው አካል የሚባለው መንግስታዊ አካል አብዛናውን ጊዜ የሕግን አግባብ ከመከተል ይልቅ በደመ-ነፍስ ውሳኔዎችን መወሰን እና መተግበር የሚቀናው አካል ነው፡፡ ስለሆነም 7/ሰባት/ቀን ሰጥቶ በ7/ሰባት/ ቀን ውስጥ የዓመታት ጥሪት ውጤት የሆነውን ቤት የሚያፈርሱ አካላት ዜጎች ላይ የማይተካ ጉዳት እንደሚደርስ ቢያውቁም በቸልተኝነት ለሚወስዱት እርምጃ በፍትሃብሄር ከድርጊቱ በጊዜያዊነት እንዲቆጠቡ ለማድረግ ሁከት ይወገድልኝ አቤቱታ በማቅረብ ጊዜያዊ መፍትሄ ማግኘት ይቻላል፡፡ ስለሆነም2/ሁለቱን/ የሕግ መስመሮች በመከተል ዜጎች መብቶቻቸውን ማስከበር ይችላሉ ባይ ነኝ፡፡

ማጠቃለያ እና አስተያየት

መንግስት በአዋጁ አንቀፅ 31/2/ መሠረት የማስለቀቂያ ትዕዛዛ ወይም ማስጠንቀቂያ የተሰጠበትን መሬት መረከብ የሚችለው

ሀ. ትዕዛዙ ወይም ማስጠንቀቂያው የደረሰው ሰው በአዋጁ አንቀፅ 28/1/ እና 2/ መሠረት አቤቱታ ሳያቀርብ ከቀረ

ለ. አቤቱታው ቀርቦ ውሳኔውን ውድቅ የሚያደርግ ውሳኔ ሲሰጥ እና በውሳኔው ላይ ይግባኝ ሳይቀርብ ሲቀር፤ እና በመሳሰሉት ህጋዊ አግባቦች ብቻ መሆኑን በመገንዘብ ሕገ-ወጥ ተግባር ናቸው ያላቸውን ተግባራት በሕገ-ወጥ መንገድ እንዳያበላሸው እና መንግስታዊ ሕገ-ወጥነት እንዳይጎለብት ሙያዊ አስተያዬቴንና ምክሬን እየለገስኩ በዚህ ጽሑፍና ሙያዊ አስተያየት ላይ የመሰላችሁን አስተያየት ከዚህ በታች በተጠቀሰው አድራሻ ላይ መስጠት ትችላላችሁ፡፡

ማስታወሻ፡- ይህ ጽሑፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተዘጋጀ በመሆኑ ወደፊት በሰፊውና በጥልቀት የሃገሪቱንና የክልሎችን ሕገ-መንግስት፤ አዋጆች፤ ደንበች እና መመርያዎችን በማጣቀስ የተሻለ የሕግ አስተያየት ለማቅረብ የምሞከር መሆኔን ለማሳወቅ እወዳለሁ፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ወደኋላ ሄዶ ተግባራዊ የሚያደርጉ የታክስና ጉምሩክ ሕግ ድንጋጌዎች ሕገ መንግሥታ...
ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር፤ አንድምታዎቹ እና ተግዳሮቶቹ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 13 December 2024