Font size: +
3 minutes reading time (650 words)

ተደራሽ ግን ርካሽ ዳኝነት - የኦሮሚያ ወረዳ ፍርድ ቤቶች ምልከታ

በዳኛው ገጠመኝ እንጀምር። የአንዱ የኦሮሚያ ወረዳ ፍ/ቤት ዳኛ ለተዘዋዋሪ ችሎት በሕዝብ ትራንስፖርት እየሄደ ነበር። መኪናው ውስጡ ሞልቶ ረዳቱ ከላይ ለመጫን ይቃጣዋል። መኪናው ላይ የተፃፉ ጥቅሶች እንቅጩን ይናገራሉ።

"ታሪፍ እንጂ ትራፊክ የለም፣ ጠጋ ጠጋ በሉ" 
"የሰው ልጅ ክቡር ነው፣ ትርፍ ሰው የለም ግቡ"
"ሞላ የሰው ስም ነው፣ገባ ገባ በሉ"

ወዘተ። 

እና ዳኙዬ ተጣብቆ ቆሞ ከቦታው ደረሰና ችሎት ስራውን ይጀምራል። መኪና ውስጥ ወንበር ላይ ተቀምጦ የነበረ ባለ ጉዳይ ውጭ ቆሞ ከጓደኛው ጋር "ቆሞ የመጣው ሶዳ (አማቻችን) እዚህ ደርሶ ወንበር አገኘ" እያለ ይሳለቃል። ችሎት ተደፈረ? ፖሊስ የለም። የቀበሌ ታጣቂ እንኳን የለም።

 
ሰውየው ተራ ደርሶት ተጠራና ይገባል። ዳኛው ከንግግሩ ላይ ንዴት ይነበባል። ሰውየው ግን ቀላል ፎጋሪ አይደለም "ቅድም እኮ ዳኛ መሆንህን ባውቅ እነሳልህ ነበር" ብሎ ፈገግ አለ። ከፈገግታው ጥፊ ይሻላል። ችሎት ተደፈረ? የለም የለም! ይህ የዳኛው እውነተኛ ገጠመኝ ነው።

በ1994 ዓ.ም ተሸሽሎ የወጣው የኦሮሚያ ክልል ሕገ መንግሥት አንቀጽ 76(3) እያንዳንዱ ወረዳ ፍርድ ቤት እንደሚኖረው ይደነግጋል። ይህ አንቀጽ ስለ ፍርድ ቤቶች ከሚደነግገው የሕገ መንግሥቱ ክፍል ውጭ የወረዳዎችን መዋቅር በሚደነግግ ርዕስ ሥር ይገኛል። 


በክልሉ በያመቱ አዳዲስ ወረዳዎች ይቋቋማሉ። አንድ ቀበሌ የሚያስፈልገውን መሠረተ ልማት ከመንግስት ለመጠየቅ መጀመርያ ወረዳ መሆን ይኖርበታል። እናም በተጨባጭ ባለው እውነታ ወረዳዎች የሚቋቋሙት ምንም መሠረተ ልማት በሌለበት ትናንሽ ቀበሌዎች ሲሆን ለመንግስት መስሪያ ቤት የሚሆን ደሳሳ ቤት በኪራይ እንኳን በማይገኝበት መንደር ነው። በሕገ መንግሥቱ መሠረትና በተጨባጭም ቀበሌዋ ወረዳ ከተባለችበት እለት ጀምሮ የወረዳ ፍርድ ቤት ሊኖራት ይገባል። በዚህ ሁኔታ የሚቋቋሙት ጉሊት ፍ/ቤቶች ጣሪያና ግርግዳ ያለው ቤት ጠፍቶ የዞን አስተዳደር በሚሰጣቸው ድንኳን ውስጥም ለመስራት ይገደዳሉ።

እንዲህ አይነቶቹ ፍርድ ቤቶች የሚቋቋሙት በክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት እቅድና ዝግጁነት ሳይሆን በአስተዳደር ግፊት መሆኑ እሙን ነው። ለወረዳ ፍርድ ቤቶች የሚሆን መሥሪያ ቤት የሚያሰራው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሳይሆን የወረዳው አስተዳደር ነው። ቤት እንዲሰራ በጀት ለማስያዝ የሚደረገው ስግደት ወገብ ቆራጭ መሆኑን የወረዳዎቹ ፕሬዚደንቶች ያውቃሉ። የፍ/ቤት ነፃነት የሚለውን ቀልድ ብታወራ ይሳቅብሃል። የወረዳው አስተዳዳሪ ያልተሰራውን አናሰራም ከማለትም አልፎ የተሰራውንም ለማስፈረስ ስልጣን አለው። ፍ/ቤቷ የወረዳው ንብረት አይደለች?

የወረዳ ፍርድ ቤት ሁለት ደረጃ ከፍ ያለ ፍርድ ቤት ነው። ከዚህ ዝቅ ያሉ ሁለት ችሎቶች አሉ። ከወረዳ ፍ/ቤት አንድ ደረጃ ዝቅ ብሎ በቀበሌ ደረጃ የሚሰራ የወረዳው ፍ/ቤት 'ቋሚ' ችሎት የሚባል አለ። እዚያው ቀበሌ አስተዳደር ውስጥ አንድ ክፍል ውስጥ አንድ ዳኛና አንድ የሕግ ኦፊሰር ተመድበው ይሰራሉ። ቋሚ የሚያስብለው በስራ ቀናት ሁሉ 'ችሎት' ስለሚኖር ነው። ችሎቱ ሁሉንም አይነት ጉዳይ የሚያይ ሲሆን በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ችሎት አስከባሪ (ፖሊስ) የለም። የሚሰራበት ክፍል የቀበሌ አስተዳደር ቤት በመሆኑ ከችሎቱ ደጃፍ የፈለገ ጫጫታ ሊኖር ይችላል። 'ችሎት' ተደፈረ ብትል ይሳቅብሃል። ችሎት ላይ አንድ ለእስር የሚያበቃ አስገዳጅ ውሳኔ ቢሰጥ ፅፈሀው መዝገብህን ጠቅልለህ ትሄዳታለህ እንጂ ማስፈፀም አትችልም።

ከቋሚ ችሎት አንድ ደረጃ ዝቅ ያለ 'ተዘዋዋሪ' ችሎት የሚባልም አለ። ይህ አይነቱ ደግሞ መዝገቦችን በቦርሳ ይዞ የቀበሌው ገበያ በሚውልበት እለት አንድ ቀበሌ ወይም ጎጥ በመሄድ ለጊዜው የቀበሌው ሊቀ መንበር ቢሮ ውስጥ የሚሰራ ችሎት ነው። ችሎትና ገበያውን የሚለየው የቤቱ ግርግዳ ብቻ ነው። ስፋቱ ሁለት ሜትር በምትሆን መንገድ ማዶ (ፊት ለፊት) ሙዚቃው ሌላ ቀበሌ የሚሰማ የቀበሌው ታዋቂ ጠጅ ቤት ሊኖር ይችላል። ባለ ጉዳይ እዚያው ጠጅ ቤት ተቀምጦ አንድ ሁለት እያለ መጠራቱን ቢጠባበቅስ? ሁሉም ያሻውን ሸማምቶ በተረፈው ቀማምሶ ይመጣልሃል።

ከላይ የጠቀስኳቸው የወረዳ እና ቅርንጫፎቹ ችሎቶች አላማቸው የዳኝነትን አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ነው። እርግጥ ነው ዳኝነት ተደራሽ መሆን አለበት የሚለው ያስማማናል። ባንፃሩ ደግሞ ርካሽ መሆን የለበትም። ፍርድ ቤቶች በህግ የተሰጣቸው ክብር አላቸው። ክብራቸው የሚገለፀው ችሎት ፊት ቆሞ 'ክቡር ፍርድ ቤት' በሚል ባዶ ቃላት ሳይሆን የሚሰጡትን ፍርድ በማስፈፀምና አልፈፅምም ያለውን አካል በህግ አግባብ አስገድዶ በማስፈፀም ጭምር ነው። ሰዎች ጉዳያቸውን ወደ ፍርድ ቤት የሚያመጡት በብዙ መልኩ ሞክረውት አልሳካ ሲላቸው ህግ ጉልበት አለው ያስፈፅምልናል በሚል ግምት ነው። አቅም የሌለው ደካማ ለፍ/ቤት አቤት የሚለው በህግ ጉልበት ተማምኖ ነው። 


ባለ ጉዳይ (በተለይም ከሳሹ ወገን) ጉዳዩ በተጠቃሾቹ  ችሎቶች እንዲታይለት አይፈልግም። ምክንያቱም አካባቢው ራሱ የፍርድ ቤት ድባብ የለውም። ለምሳሌ አንዱ በወንጀል ጉዳይ ተጎጂ የነበረ ሰው በዳዩ በሶስት ወር እስራት ሲቀጣ "በመደበኛው ችሎት ቢሆን እንዲህ ደመ ከልብ አልሆንም ነበር። በግድ እዚህ ይታይልህ ተብዬ በነፃ ለቀቁብኝ።" ብሎ ነበር።

እነዚህ ችሎቶች ለታለሙለት ለተደራሽነት የተቋቋሙ ሳይሆን ለሪፖርት አላማ ብቻ የሚያገለግሉ ናቸው። ይህን ያህል መዝገብ ህዝቡ ያለበት ድረስ ዘልቀን ሰርተናል ለማለት ለይስሙላ የሚሰራ ስራ መሆኑን ልብ ይባል። ጠበቃና የህግ አማካሪዎች፣ የህግ ጉዳይ ፀሃፊዎች ድርሽ የማይሉበት ችሎት ባለ ጉዳዮቹ በጉዳያቸው ላይ በሚፈልጉት መጠን ክርክር ሳያደርጉበት; ምንም ነገር ባልተሟላበት ሁኔታና በሁከት በተሞላ መንደር ውስጥ እንደ ነገሩ የሚሰጥ ዳኝነት ርካሽ ነው።

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

በክልል የተገደበው የመዘዋወር ነፃነት
የተሻሻለው የአማራ ክልል የገጠር መሬት አዋጅ እና አከራካሪው የይርጋ ድንጋጌ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 05 October 2024