የልማድ አቤቱታ የፍርድ ጥራት ላይ ያለው ተፅዕኖ

 


መነሻ ነገር

መኳንንት ከሕግ ትምህርት ቤት ተመርቆ ሲወጣ ግር ያለው ነገር የትምህርቱና የአተገባበሩ ልዩነት ነው፡፡ በአብዛኛው በንድፈ ሐሳብ አስተምህሮና ትንተና ላይ የሚተኮረው ትምህርቱ በተግባር ከሚታየው የፍርድ ቤት ነባራዊ ሁኔታ ጋር አልታረቅ ብሎት ተቸግሯል፡፡ ይህን ችግሩን ያባባሰው ደግሞ ከቤተሰቡ አንዱ የወራሽነት የምስክር ወረቀት ከፍርድ ቤት እንዲሰጠው በማሰብ አቤቱታውን እንዲያዘጋጅለት ሲጠይቀው ነው፡፡ አቤቱታውን አዘጋጅቶ ለቤተሰቡ አባል ቢሰጠውም በአንዱ ክልል ከሚገኘው የወረዳ ፍርድ ቤት የገጠመው ነገር ሌላ ነው፡፡ ቤተ ዘመዱ በፍርድ ቤቱ አቤቱታው በትክክል አለመጻፉ ተነግሮት በፍርድ ቤቱ ደጃፍ ከሚገኙት ራፖር ጸሐፊ ተጽፎ እንዲመጣ ተመከረ፡፡ ሰውየውም የተባለውን ፈጽሞ አቤቱታው ተቀባይነት አግኝቶ የወራሽነት የምስክር ወረቀት አገኘ፡፡ የመኳንንትና የራፖር ጸሐፊው አቤቱታ ልዩነት ቀላል ነበር፡፡ የመኳንንት አቤቱታ ፍሬ ነገሩን በአጭር የሚገልጽ፣ የሕግና የማስረጃ ትንተና የሌለው፣ ግልጽ ዳኝነትን የሚጠይቅ ነበር፡፡ የራፖር ጸሐፊው አቤቱታ ግን ረዥም፣ ውስብስብ የሕግ ቃላትን የሚጠቀም፣ በብዙ የሕግ ድንጋጌ የተዘበዘበ ነበር፡፡ ይህን የተረዳው መኳንንት አምስት ዓመት የተማረበት የሕግ ትምህርት ሥልጠና የማይፈልግና በፍርድ ቤት ተግባራዊ ረብ የሌለው መስሎት ተከዘ፡፡ የተወሰኑ ዓመታትን በሕግ ሙያ አገልግሎት ካሳለፈ በኋላ ግን ለዘመናት የዳበረውን ልምድ መስበር አስቸጋሪ ስለመሰለው ራሱን በተወሰነ ደረጃ ከተለመደው አሠራር ጋር አቀራረበ፡፡ አሁን ለአቤቱታ ርዝመት ጭንቀት የለውም፣ የሕግ ድንጋጌዎችን በዓይነት ለመዘብዘብ፣ የሕግና የማስረጃ ትንታኔዎችን ለማግተልተል ቀዳሚ አይገኝለትም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፍርድ ቤቶች የአሠራር ማሻሻያ በማድረግ፣ የሬጅስትራርና ተያያዥ ሥራዎችን የሚሠሩ ሰዎች ከሕግ ትምህርት ቤት የተመረቁ፣ የሕግ ሥልጠና ያገኙ መሆናቸው የተወሰነ ለውጥ ማምጣቱን ያምናል፡፡ ያም ሆኖ አሁንም የአቤቱታ ፎርም፣ ይዘት፣ እና ሕጋዊ ብቃት አሰፋፈር/አተያይ ላይ ምሉዕ ለውጥ አለመምጣቱን መኳንንት ያምናል፡፡ ሰሞኑን ያጋጠመው የሬጅስትራር ሠራተኞች ድርጊት ለዚህ አስረጅ ነው፡፡ መኳንንት ሕጉን ተከትሎ ያዘጋጀውን የመከላከያ መልስ ምንም ዓይነት የሕግ ድንጋጌ ያልጠቀሰ መልስ የሕግ አቤቱታ አይሸትም ሲሉት እጅጉን ተበሳጨ፡፡ ጸሐፊውም ይህን በሰማ ጊዜ ትንተና ባይበዛውም በዚህ ጽሑፍ የአቤቱታን ምንነት፣ መሥፈርት፣ የብቃት አተያይ በአጭሩ ለግንዛቤ በሚመች መልኩ ለመዳሰስ ሙከራ አደረገ፡፡

አቤቱታ ምንድን ነው?

በዕለት ተዕለት የሕይወት ተሞክሮ ለማንኛውም አካል በቃል ወይም በጽሑፍ የሚቀርብ ጥያቄ፣ ማመልከቻ፣ ይግባኝ አቤቱታ ይባላል፡፡ በሕግ ሙያ ግን ‹‹አቤቱታ›› ወይም ‹‹Pleading›› የሚለው ቃል በፍርድ ቤት የሚቀርብ ማመልከቻን ሁሉ የሚያካትት አይደለም፡፡ ፍርድ ቤት ለመዋሉ ማስረጃ የሚጠይቅ፣ የውሳኔ ግልባጭ እንዲሰጠው የሚጠይቅ ወዘተ በሕጉ ቃል አቤቱታ አቅርቧል ለማለት አያስችልም፡፡ ለቃሉ ፍቺ የሚሰጠው ብላክስ የሕግ መዝገበ ቃላት ‹‹Pleading is a formal document in which a party to a legal proceeding (esp. a civil lawsuit) sets forth or responds to allegations, claims, denials or defenses›› በሚል ይገልጸዋል፡፡ በዚህ ትርጉም መሠረት አቤቱታ ማለት በአንድ የሕግ ሙግት ተከራካሪ የሆነ ወገን ሙግት ለመጀመር ወይም ለቀረበ ጥያቄ፣ ዳኝነት፣ ክህደት ወይም መከላከያ መልስ ለመስጠት የሚያቀርበው መደበኛ ሰነድ ነው፡፡ በዚህ ፍቺ መሠረት አቤቱታ መብት የሚጠየቅበት ወይም ለቀረበ ጥያቄ መልስ የሚቀርብበት ነው፡፡

የኢትዮጵያ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግም ለአቤቱታ ተመሳሳይ ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ አንቀጽ 80(1) የአቤቱታ ጽሑፍ ማለት ከሳሽ የሚጠይቀውን ሁሉ ዘርዝሮ የሚገልጽ ጽሑፍ፣ ተከሳሽ የሚሰጠውን የመከላከያ ጽሑፍ፣ የተከሳሽ ከሳሽ የሚያቀርበውን የክስ ጽሑፍ፣ የይግባኝ ማቅረቢያ ጽሑፍ ወይም በሌላ ዓይነት ተጽፎ ለፍርድ ቤት የሚቀርብ የክስ መነሻ ወይም ለዚሁ የሚሰጠውን መልስ የሚመለከት ማናቸውም የጽሑፍ ማመልከቻ ማለት ነው ሲል ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ ከዚህ ትርጉም በመነሳት አቤቱታ ማለት ሙግት ለመጀመር ወይም ለተጀመረ ሙግት መልስ ለመስጠት የሚቀርብ የጽሑፍ ማመልከቻ መሆኑን መረዳት አያስቸግርም፡፡ ሕጉ በገላጭነት (By illustration) እንደገለጸው የክስ፣ የመልስ፣ የይግባኝ ማመልከቻ ከአቤቱታ ምድብ የሚወድቁ ናቸው፡፡

የአቤቱታ ዓላማ

የአቤቱታ ዓላማን ማወቅ ይዘቱን ለመወሰን ጠቃሚ ይሆናል፡፡ አቤቱታን ከዓላማው ውጭ ማዘጋጀት ለፍትሕ የሚጠቅምና ሙግትን የሚያዘገይ ስለሚሆን የተወሰኑ የአቤቱታ ዓላማዎች ለመጥቀስ እንሞክር፡፡ በመጀመሪያ የአቤቱታ ዓላማ የተከሰሰ ወገን የቀረበበትን ክስ ማሳወቅና ተከሳሹ የበኩሉን መከላከያ እንዲያቀርብ መርዳት ነው፡፡ ከሳሽ በሚያቀርበው የክስ አቤቱታ ተከሳሽ ማን፣ በምን የሕግ ወይም የውል መሠረት፣ ምን እንደከሰሰውና ምን እንደሚፈልግ ይረዳበታል፡፡ ሁለተኛው አቤቱታው ለፍርድ ቤቱ ያለው ጥቅም ነው፡፡ ለፍርድ ቤት የሚቀርቡ አቤቱታዎች ፍርድ ቤቱ ጭብጥ እንዲመሠርት፣ የሙግቱን ወሰንና የሚቀርቡትን ማስረጃዎች እንዲወስን ይረዱታል፡፡ ከሳሽ በአቤቱታው እንዲወሰንለት የጠየቀው ተከሳሹ ግን የካደው የፍሬ ነገር ወይም የሕግ ክርክር በፍርድ ቤቱ ጭብጥ ሆኖ ይመሠረታል፡፡ በሙግት ሒደት ተከራካሪ ወገኖች ከተመሠረቱት ጭብጦች ወሰን ያለፈ ክርክር ማቅረብ የማይችሉ ሲሆን፣ በግራ ቀኙ የሚቀርበውና በፍርድ ቤቱ የሚመረመረው ማስረጃም ከጭብጡ ጋር የተያያዘ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በሕጉ መሠረት የተዘጋጀ አቤቱታ ዓላማ ፍርድ ቤቶች ግራ ቀኙን የሚያከራክረውን ነጥብ እንዲለዩ ማስቻል ነው፡፡ ሌላው የአቤቱታ ዓላማ ፍትሕ እንዲመጣና ሙግት እንዲፋጠን ማስቻል ነው፡፡ አቤቱታ በተከራካሪ ወገኖች መካከል ያለውን እውነታ በዝርዝር ካስቀመጠ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን በሚገባ ተገንዝቦ ፍትሕ ለመስጠት ያስችለዋል፡፡ የአቤቱታው ይዘት ደግሞ ረዥም፣ የማይገባ፣ ውስብስብና የተደበላለቀ ከሆነ ሙግትን የሚያዘገይ በመሆኑ፤ አቤቱታ በማጠሩ ግን ሙሉ ሐሳብን በመግለጽ ፍትሕ እንዲፋጠን የመርዳት ዓላማ ይኖረዋል፡፡

የአቤቱታ ደንቦች

አቤቱታ ከላይ የተገለጹትን ዓላማዎች ለመፈጸም ሕጉ ባስቀመጠው ደንብ መሠረት ሊፈጸም ይገባል፡፡ ሕጉ አቤቱታ በአዘገጃጀቱ፣ በሚከተለው ፎርምና በይዘቱ ሊከተላቸው የሚገባቸውን መሥፈርቶች  በግልጽ አስቀምጧል፡፡ እነዚህ መሥፈርቶች  በደምሳሳው የአቤቱታ የቴክኒክ /Technical requirements/ እና የሕግ /Legal requirements/ መሥፈርቶች  በሚል ሊጠሩ ይችላሉ፡፡ ቴክኒካል የሚባሉት ከአዘገጃጀትና ከሚከተሉት ፎርሞች ጋር ተያይዞ በሕጉ የተቀመጡ መሥፈርቶች ሲሆኑ፣ አቤቱታ ቴክኒካል መሥፈርቱን ማሟላቱን የማረጋገጥ ኃላፊነት የሬጅስትራሩ ነው፡፡ በሥነ ሥርዓት ሕጉ ትርጓሜ መሠረት ‹‹ሬጅስትራር›› ማለት የፍርድ ቤት መዝገብ ሹሙንና ረዳቱን ወይም በፍርድ ቤቱ መዝገብ ቤት ውስጥ የሚገኙትን የመዝገብ ሠራተኞችና ጸሐፊዎች አጠቃልሎ የሚይዝ ቃል ነው፡፡ በአሁኑ የፍርድ ቤት አሠራር የሬጅስትራር ሥራዎች በአብዛኛው በአንድ ሰው የሚከወኑ ሥራዎች ሲሆን፣ ሌሎቹ ረዳቶች ከምዝገባ፣ ከጽሑፍ፣ ከማኅተም ወዘተ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ይሠራሉ፡፡ የአቤቱታ የሕግ ብቃት /Legal sufficiency/ የሚታየው በዳኞች ሲሆን፣ ይህም አቤቱታው በይዘቱ ሕጉ የሚጠይቀውን መሥፈርት ስለማሟላት አለማሟላቱ የሚረጋገጥበት ነው፡፡

አቤቱታ ሊያሟላቸው የሚገቡ የቴክኒካል መሥፈርቶች  ከአቤቱታ አዘገጃጀትና ከፎርም ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ የሥነ ሥርዓት ሕጉ በአንቀጽ 80(2) 92 93 222 223 234 327-330 በዝርዝር ያስቀመጣቸው ሲሆን፣ ዋናዋናዎቹን ለመመልከት እንሞክር፡፡

በአንቀጽ 80(2) ላይ ሦስት መሥፈርቶች ተቀምጠዋል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት የመጀመሪያው መሥፈርት ማንኛውም የአቤቱታ ጽሑፍ ሁሉ በቀለም የተጻፈ ወይም በታተሙ ፎርሞች በቀለም ጽሕፈት የተሞላ ወይም በጽሕፈት መኪና የታተመ መሆን አለበት፡፡ ሁለተኛው መሥፈርት አቤቱታው በሥነ ሥርዓት ሕጉ አንደኛ ሠንጠረዥ በአባሪነት ከታተመው ፎርም ጋር ተመሳሳይ መሆን አለበት፡፡ ሕጉ የተለያዩ ፎርሞች እንደ ጉዳዩ ዓይነት ያዘጋጀ ሲሆን፣ ተከራካሪ ወገኖች አቤቱታቸው በተመሳሳይ ፎርም እንዲኖረው ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ፎርሙ አቤቱታዎች በወጥነት ተመሳሳይ እንዲሆኑ፣ መሠረታዊ ፍሬ ነገሮች እንዳይቀሩ እንዲሁም የገለጻው ቅደም ተከተልን ለመረዳት እንዲያስችል የሚያደርግ በመሆኑ ጠቃሚነቱ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ያም ሆኖ አቤቱታ እንደ ጉዳዩ አግባብነት ሊጠብ ሊሰፋ፣ ሊያጥር ሊረዝም እንደሚችል ግንዛቤ ሊወስድ ይገባል፡፡

ከአንቀጽ 80(2) ሊወስድ የሚገባው ዋና የቴክኒክ መሥፈርት አቤቱታው ፍሬ ነገርን እና ፍሬ ነገርን ብቻ የሚገልጽ፣ መብት የሚጠየቅበትን ወይም የመከላከያውን ምክንያት በአጭሩ የሚገልጽ ወይም የያዘ መሆን ይገባዋል፡፡ ይህ መሥፈርት በአብዛኛው በተግባር የሚጣስ በመሆኑ አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል፡፡ አቤቱታ ሊገልጽ የሚገባው ፍሬ ነገርን ለዚያውም ጠቃሚ ፍሬ ነገር /Material fact/ ብቻ ነው፡፡ አቤቱታ የሕግ ትንተና፣ የማስረጃ ገለጻ፣ መደምደሚያ ሊገልጽ አይገባም፡፡ ፍሬ ነገር ማለት ጠቃሚ የሆኑ ቃላትን በመጠቀም የተከወነውን ድርጊት፣ የተፈጸመውን ነገር መዘርዘር ማለት ነው፡፡ ጭብጥ ለመመሥረት የማይጠቅሙ፣ መብትን የማያስረዱ፣ ዳኝነት የማያስፈልጋቸውን ፍሬ ነገሮች ማካተት ፍትሕን ስለሚያጓትት መጨመሩ ተገቢ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ብድር ወስዶ ያልከፈለን ሰው ለመክሰስ የሚቀርብ ክስ በሁለቱ ወገኖች መካከል የብድር ውል መፈጸሙን /ዓይነቱን፣ ቀኑንና ቦታውን/ በውሉ ግዴታ ተከሳሽ ያለበትን ግዴታና አለመፈጸሙን፣ እንዲሁም የሚጠይቀውን ዳኝነት ዝርዝር /ያልከፈለው ዋና ገንዘብ፣ ወለድ፣ ወጪ ወዘተ./ እንዲከፈለው መጠየቅ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ውጭ የሕግ ትንተና ማያያዝ ካስፈለገ በተለየ ሰነድ በተጨማሪነት ማያያዝ ይገባል፡፡ ሆኖም ይህ አሠራር በተግባር ባለመኖሩ ደፍሮ ያቀረበ ተከራካሪ ወገን ከሬጅስትራሩ እምቢታ ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ ሌላው ፍሬ ነገር ሊገለጽ የሚገባው በአጭሩ ነው፡፡ በተለይ የሕግ ባለሙያ ክህሎት የሚገለጸው ሐሳብን በአጭር ቃላት በመግለጽ በመሆኑ ችላ ሊባል የማይገባው መሥፈርት ነው፡፡ አቤቱታ ከረዘመ ተከሳሽ የቀረበበትን ክስ ለመረዳት ይቸግረዋል፤ ዳኛውም ጭብጥን ለመመሥረት ፈተና ይሆንበታል፡፡ አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች እንደሚሉት የአቤቱታ አስተጣጠር ከሴቶች አጭር ቀሚስ አስተጣጠር ጋር ይመሳሰላል፡፡ አጭር ቢሆንም አስፈላጊ/ጠቃሚ የሆነውን ነገር የሚገልጽ (የሚሸፍን) ሊሆን ይገባል፡፡ አቤቱታም አጭር ሆኖ ፍሬ ነገር በሚገባ የሚገልጽ ሊሆን ይገባዋል፡፡

ሌሎች የቴክኒክ መሥፈርቶች አቤቱታውን ማረጋገጥ፣ በአቤቱታው ላይ መፈረምና ለጉዳዩ ማስረጃ የሚሆኑትን የሰነድና የሰው ማስረጃዎች ዘርዝሮ ማቅረብ ነው፡፡ የማረጋገጥ ዓላማ ሙግቱ እውነትን መሠረት አድርጎ እንዲከናወንና በሐሰት የቀረበ ክርክር ካለ በሐሰት ማስረጃ /Perjury/ ተከራካሪውን ወገን ለመጠየቅ ነው፡፡ አቤቱታ ላይ መፈረም ፈቃድን ከመግለጽ፣ አቤቱታውን ያቀረበውን ሰው ድጋፍ ከመግለጽ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ‹‹ማስረጃም ኋላ በሚደረገው የሙግትና የማስረጃ መስማት ደረጃ የሚኖሩትን ክርክሮች ለተከራካሪው ወገንና ለፍርድ ቤቱ መግለጽ ነው፡፡ ፍሬ ነገርና ማስረጃ ክስ፣ መከላከያ፣ መልስ ሲቀርብ ተጠቃለው ካልቀረቡ ኋላ በሚደረገው ሙግት ያልተጠቀሰውን ፍሬ ነገር/ማስረጃ መሠረት አድርጎ ሙግት ማቅረብ አይፈቀድም፡፡ ሕጉ አቤቱታን በማሻሻል፣ አዲስ ማስረጃ የሚቀርብበትን ሁኔታ የሚፈቅዱ የተለያዩ ድንጋጌዎች ስላሉት የተወሰኑ መፍትሔዎች ባያጠፉም፤ ሕጉ በጠባቡ ስለሚተረጎም ተከራካሪ ወገኖች አቤቱታቸውን ሲያዘጋጁ ፍሬ ነገርና ማስረጃዎችን አጠቃለው እንዲያቀርቡ ይመክራሉ፡፡

ከላይ የተመለከትናቸው የቴክኒክ መሥፈርቶች አለመሟላታቸው በሬጅስትራሩ ከተረጋገጡ ተከራካሪ ወገን አቤቱታው ይሰረዝበታል፤ እናም አስተካክሎ በመጣ ጊዜ እንደገና የሚታይለት ይሆናል፡፡ ሆኖም ሬጅስትራሩ ተገቢ ባልሆነ ምክንያት ካልተቀበለው የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 232 በሚፈቅደው መሠረት በአምስት ቀናት ለዳኛው ቅሬታ ሊያስገባ ይችላል፡፡ የአቤቱታው የቴክኒክ መሥፈርት መሟላቱ በሬጅስትራሩ ከተረጋገጠ ግን የሕግ ብቃቱ ይመረመር ዘንድ አስፈላጊው የሬጅስትራር ሥራ ተፈጽሞ ለዳኛው ይቀርብለታል፡፡ ዳኛው አቤቱታው የክስ ምክንያት መኖሩን፣ የሥረ ነገር ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት መቅረቡን፣ ሕጉ በሚጠይቀው መሠረት ክሱ፣ መልሱ፣ ወይም ይግባኙ መዘጋጀቱን ወዘተ. በመመርመር የሕግ ብቃቱን መርምሮ ብይን ይሰጣል፡፡ ይህ የዚህ ጹሑፍ ዓላማ ባለመሆኑ የሕግ ብቃት ምንነቱን፣ የምርምራ ውጤቱን ወዘተ. በዚህ ጹሑፍ አንመለከተውም፡፡

በተግባር የሚስተዋሉ ክፍተቶች

ከተመለከትናቸው የአቤቱታ ደንቦች ውስጥ ምን ያህሉ በአግባቡ እንደሚፈጸሙ ለማወቅ ጥናት ይጠይቃል፡፡ ጥናቱ ይህንን ያህሉ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ አቤቱታዎች በሕጉ መሠረት ሳይሆን በልማድ የሚዘጋጁ ናቸው ለማለት ካልሆነ በቀር አተገባበሩን ከዕለት ተዕለት ተሞክሮ መግለጽ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ ፍርድ ቤቶች የሚቀርቡት አብዛኞቹ አቤቱታዎች በሕግ ባለሙያዎች (በጠበቆች፣ በነገረ ፈጆች፣ ነፃ የሕግ ድጋፍ በሚሰጡ ተቋማት) የሚዘጋጁ አይደሉም፡፡ ሰማንያ በመቶ የሚሆነው የአገራችን ሕዝብ በገጠር አካባቢ መኖሩን፣ የሕግ ባለሙያዎች ቁጥር ማነስና የሚጠይቁት ዋጋ የሚቀመስ አለመሆኑን ወዘተ. ካሰብን ይህን መደምደሚያ መቀበል ለህሊና አይጎረብጥም፡፡ አብዛኛው አቤቱታ የሚዘጋጀው በሕግ ሙያ ባልሠለጠነ ራፖር ጸሐፊ ወይም በባለጉዳዩ በመሆኑ የሕጉን መሥፈርት ስለማሟላታቸው ምስክርነት ማግኘት ይከብዳል፡፡ በመነሻችን የተመለከትነው የመኳንንት አጋጣሚ ነባራዊ ሁኔታው የሚወክል ነው፡፡ አቤቱታው እንደነገሩ ይዘጋጃል፤ በእርግጠኝነት የሚያሟላው የማረጋገጥ፣ የፊርማ፣ የማስረጃ ዝርዝር የማያያዙን ሁኔታ ነው፡፡ አቤቱታው ከሚዘጋጅበት ፎርምና የቃላት አጠቃቀም አንፃር ሰፊ ክፍተቶች  ይታያሉ፡፡

አንዳንዶቹ አቤቱታዎች ረዥም፣ ጠቃሚ ያልሆኑ ፍሬ ነገሮችን የሚዘበዝቡ ናቸው፡፡ ወደ ጉዳዩ በቀጥታ ከመግባት ይልቅ ከጉዳዩ ጀርባ ያለውንና የማይያያዝ ጉዳዩን በማንሳት በብዙ ገጽ የሚቀርብ አቤቱታ አለ፡፡ እንዲህ ዓይነት አቤቱታ ለሚከላከለው ሰው አስቸጋሪ፣ ለፍርድ ቤትም ጭብጥ ለመመሥረትና ጉዳዩን መርምሮ ፍርድ ለመስጠት ያስቸግረዋል፡፡ የዚህ ምንጩ አለማወቅና በዳኞች ላይ የሚታጣ መተማመን ነው፡፡ አንዳንዱ ነገር ሲያበዛ ጉዳዩን ያስረዳ ይመስለዋል፡፡ ለራሱ እስኪገርመው ድረስ በቃል ሙግት የሚያቀርበውን ሃተታ በክስ ወይም በመከላከያ መልስ አቤቱታው ላይ ያካትተዋል፡፡ ሁለተኛው የዚህ ችግር ምንጭ ዳኞች ጉዳዩን ሊረዱት ስለማይችሉ፣ የትኛውን ጭብጥ አድርገው የትኛውን እንደሚተው፣ በየትኛው የሕግ ድንጋጌ ውስጥ እንደሚወድቅ እንደሚወስኑ ለማወቅ ስለሚያስቸግር ሁሉንም ዘብዝቦ የማቅረብ ልማድ ነው፡፡ ዳኛው ከአቤቱታው ፍሬ ነገሩን እንጂ ዋናውን የሕግ ክርክር ስለማይረዳ አቤቱታውን አሳጥሮ ክሱ ሲሰማ የማሳመን ብቃትን ተጠቅሞ ዳኛውን ማሳመን ተገቢ ነው፡፡

አንዳንዶቹ አቤቱታዎች ከፍሬ ነገር ይልቅ የሕግ ሙግትና የማስረጃ ትንተና የሚበዛባቸው አሉ፡፡ እነዚህ አቤቱታዎች ትንሽ ፍሬ ነገር ብዙ የሕግ አንቀጽ የሚይዙ ሲሆን፣ አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች የሕግ ዕውቀታቸውን ለመራቀቅ የሚጠቀሙበት መድረክ አቤቱታ ሆኗል፡፡ ሕጉ እንዲህ ዓይነት የሕግና የማስረጃ ትንታኔዎች በተጨማሪ ጽሑፍ እንዲያያዝ ቢጠይቁም፣ የሕግ ባለሙያዎቹ ከማያያዝ ይልቅ በአቤቱታ ማካተት ይቀናቸዋል፡፡ አንዳዴም ክርክር ለማራዘምና ለማወሳሰብ ሆን ብለው የሚጨምሩ ባለሙያዎች አይጠፉም፡፡ ራፖር ጸሐፊዎቹማ የሚያካትቱት የሕግ ድንጋጌዎች ብዛት ደንበኞቻቸውን የሚያስደስት ይመስል መዘብዘብ መርሃቸው ሆኗል፡፡ ከላይ በመግቢያው እንደተመለከትነው መኳንንትን የመሰሉትን የሕግ ባለሙያዎች የሕግ አንቀጾች ካልበዙ የሕግ ባለሙያ አቤቱታ አቤቱታ አይሸትም በማለት አንዳንድ ሬጅስትራሮችም ተፅዕኖ ያደርጋሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ጠቃሚ ፍሬ ነገሮች እንዲታለፉ፣ ጉዳዩ በአግባቡ እንዳይረዳ የማድረግ ውጤት ስላላቸው ሃይ ባይ ይፈልጋሉ፡፡

የእነዚህ ችግሮች ውጤት የሥነ ሥርዓት ሕጉ ዓላማ እንዳይፈጸም ማድረግ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የሥነ ሥርዓት ሕግ ዓላማ አንድን ለፍርድ ቤት የቀረበ ጉዳይ ፍትሐዊ በሆነ መልኩ፣ በፍጥነትና ኢኮኖሚን ባገናዘበ መልኩ እልባት መስጠት ነው፡፡ አቤቱታ ረዥምና ውስብስብ ከሆነ፣ የፍሬ ነገር ገለጻ ሳይሆን የሕግና የማስረጃ ትንተና ከሆነ ጉዳዩን ለመረዳት ያስቸግራል፡፡ ዳኞች ተገቢውን ጭብጥ ለመመሥረት፣ ማስረጃ ለመስማትና ፍርድ ለመስጠት ይቸገራሉ፡፡ አለበለዚያም ጉዳዩ ወዳልተፈለገ ውጤት ሊገፋ ይችላል፡፡ ይህም ፍትሕ እንዳይኖር በማድረግ የግለሰቦች መብት እንዲበደል የማድረግ ውጤት ይኖረዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሕጉን ያልተከተሉ አቤቱታዎች (ርዝመትና የትንታኔ ብዛት) ጉዳዮች በፍርድ ቤት በፍጥነት እንዳይስተናገዱ በዚህም የተነሳ ተከራካሪዎች ብዙ ወጪ እንዲያወጡ ምክንያት ይሆናል፡፡ ለፍርድ ጥራት መጓደልም የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ዳኛው ጭብጡን እንዳይረዳው፣ እንዲወሳሰብበት፣ ለማሳጠር በመሞከር ወሳኝ ፍሬ ነገር እንዲዘል፣ ክርክሩ መስመር እንዲለቅ የማድረግ አቅም ይኖረዋል፡፡
መፍትሔው ሊጠቁሙት እንጂ ሊፈጽሙት ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ ሥርዓትን ከልማድ ማላቀቅ ፈጣኝ ስለሆነ፡፡ አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች ከሰይጣን ልማድ ይፈትናል ይላሉ፡፡ ያም ሆኖ የተወሰነ ነገር ማለት ይቻላል፡፡ እስካሁን የተወሰዱት የተለያዩ መፍትሔዎች እንደተጠበቁ ሆነው ተጨማሪ ሥራዎች ያስፈልጋሉ፡፡

የችግሩ ምንጭ ሕጉ ሳይሆን አሠራሩ በመሆኑ መፍትሔው አሠራሩን ማስተካከል ነው፡፡ ተከራካሪዎች፣ ጠበቆችና ነገረ ፈጆች ሕጉን ተከትለው አቤቱታ እንዲያዘጋጁ ማስገደድ ያስፈልጋል፡፡ ሬጅስትራሮች በምክንያት በሕጉ መሠረት፣ ዳኞች አቤቱታዎች አጥረውና ግልጽ ሆነው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ በመስጠት፣ ፍርድ ቤቶች ግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት ለውጥ እንዲመጣ ጥረት ማድረግ ይገባል፡፡ ሕጉን ካልተከተልን ልማዱ ወጥነት ወደሌለው አሠራር ይወስደናል፡፡ ከላይ በመግቢያ የተመለከትነው መኳንንትም ያጋጠመው ችግር የተማረው ትምህርት ትክክል ባለመሆኑ ሳይሆን የተማረው በልማድ በመሻሩ ነው፡፡ በዘመናዊ ዓለም የሕግ ሥርዓቱ ከሕጉ ልማዱን የሚመረጥ ከሆነ የፍርድ ቤት ሙግቶች አሰልቺ፣ ፍትሐዊና የተንዛዙ ስለሚሆኑ ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊንቀሳቀሱ ይገባል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Letters of Credit in General
የሰበር ፍርድ ያለማክበር ልማድና ውጤቱ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 09 February 2023