ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት ያላቸው ደረጃ

 

1.    ስለዓለም አቀፍ ሕግ በአጭሩ

ዓለም አቀፍ ሕግ በሉዓላዊ አገሮች መካከል ያለን ግንኙነት ወይም በአገሮችና እንደተባበሩት መንግሥታት ያሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መካከል ያለን ግንኙነት የሚገዛ የሁሉ አቀፍ ደንቦች እና መርሆዎች ሥርዓት ነው። በሌላ አነጋገር «International law is the universal system of rules and principles concerning the relations between sovereign States, and relations between States and international organizations such as the United Nations» የሚል ትርጉም ተሰጥቶት እናገኘዋለን። ቀደም ባሉት ጊዜያት በዓለም አቀፍ ሕግ እና በየሐገሩ በሚገኙ ዜጎች፣ ሉአላዊ ባለሆኑ አካላት (Transnational Corporations) እና መንግሥታዊ ባለሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች (International Non-Governmental Organization) ቀጥተኛ ግንኙነት ያለነበረ ቢሆንም አሁን አሁን ግን ይህ የታሰበው ቀጥተኛ ግንኙነት በስፋት እየታየ መሆኑን ዓለም አቀፍ ምሁራንን እያስማማ ነው።

ይሁን እንጂ ዓለም አቀፋዊ የሆነ ማዕከላዊ ሕግ አውጭ ባለመኖሩ፣ አለፎ አልፎ ከሚታዩት በስተቀር ዓለም አቀፍ ሕግን ውጤታማና ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲከበር የሚያደርጉ የእርምጃ ዘዴዎች ባለመጎልበታቸው፣ እራሱን የቻለ የተጠናከረ ማዕከላዊ አስፈጻሚ አካል ጎልቶ አለመታየቱ (የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ሳይዘነጋ መሆኑ ይታወቃል) ፣ ክርክሮችን ተቀብሎ እልባት የሚሰጠው ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤትም ስራውን የሚያከናውነው እና ችሎት የሚቀመጠው አለመግባባት የታየባቸው አገሮች በራሳቸው ፍቃደኝነት ጉዳያቸውን ሲያቀርቡለት እንጂ አስገድዶ የማስቀረብ ሥልጣኑም ሆነ ተቋማዊ አደረጃጀት የሌሉት መሆኑ እና ዓለም አቀፍ ሕግ በዓለም ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ በሆኑ አገሮች ጥቅምና አምሳል የተፈጠረ በመሆኑ እና አፈፃፀሙም በእነሱ ተጽዕኖ ሥር በመውደቁ ፍትሃዊነቱ አጠያያቂ ነው፣ የደሃ ሐገሮችን ጥቅም አያስጠብቅም የሚሉ ትችቶችን ወ.ዘ.ተ. ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ዓለም አቀፍ ሕግ የሚባል ነገር እንደ ሕግ የመቆም ብቃት የለውም የሚሉ ወገኖች እየበረከቱ መጥተዋል። በተለይ የሕግ መሠረታዊ ባህሪ ነው ተብሎ የሚታሰበውን የአስገዳጅነት ተፈጥሮ አልተላበሰም በሚል የሕግ ዋጋ የለውም እያሉ ክፉኛ ያብጠለጥሉታል።  ሌሎች ደግሞ እንደ ሕግ ባለመከበሩና በመጣሱ ምክንያት ብቻ ሕግ ከመሆን የሚያግደው ነገር የለም ባይ ናቸው። እንደዚያም ከሆነ ብሄራዊ ሕጎችስ በተደጋጋሚ ሲጣሱ ይታዩ የለምን? ሲሉ በአጽእኖት ይጠይቃሉ፣ እናም የዓለማችን ግንኙነት እየሰፋ በመጣበት በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፍ ሕግን አሳንሶ መመልከትም ይሁን ጭራሽ እልውናውን መፈታተን እውነታን ያላገናዘበ ድምዳሜ ነው ሲሉም ትችት ያቀርባሉ።   

ዓለም አቀፍ ሕጎች በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ልንመድባቸው እንችላለን። እነሱም ዓለም አቀፋዊ የመንግሥት ሕግ (Public International Law) እና ዓለም አቀፋዊ የግል ሕግ (Private International Law) በማለት ሲሆን ዓለም አቀፋዊ የመንግሥት ሕግ በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ራሳቸውን በቻሉ ነፃ እና ሉአላዊ አገሮች መካከል የሚፈጠረውን የሁለትዩሽ ወይም ከዚያ በላይ ግንኙነቶች የሚገዛና የሚቆጣጠር ሕግ ነው። በሌላ በኩል ዓለም አቀፋዊ የግል ሕግ በፍትሐብሄር ጉዳዩች ዙሪያ የሚፈጠሩ ግንኙነቶች እና አለመግባባቶች በሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ አገሮች ዜጎችን በተፎካካሪነት ያሳተፈ ሲሆን አልያም የሌሎች አገር ተወላጆች ንብረት በአንዲት አገር የሚገኝ ከሆነ እንዲሁም የውጭ አገር ዜጎች አንዳንድ የፍትሐብሄር ድርጌቶችን ለምሳሌ ውርስ፣ ውል፣ ከውል ውጭ የሚያስጠየቁ ኩነቶችን የፈፀሙ እንደሆነ አለመግባባቱ መፍትሄ የሚያገኘው በዓለም አቀፍ የግል ሕግ አማካኝነት ነው።   

Continue reading
  16756 Hits