የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 145 አፈፃፀም ላይ የሚስተዋል መሠረታዊ የአሠራር ግድፈት

በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 145 ላይ አንድ ምስክር በፖሊስ ምርመራ ወቅት የሰጠው ቃል ዓቃቤ ሕግ ወይም ተከሳሹ ባመለከተ ጊዜ የተሰጠውን ምስክርነት ርድ ቤቱ ሊመለከተው እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ ይህ መብት የተሰጠው ለዓቃቤ ሕግ እና ለተከሳሽ በእኩል ደረጃ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ በሚባል አኳኋን እየተጠቀመበት ያለው ዓቃቤ ሕግ ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ በማስረጃነት የቆጠረው ምስክር በማንኛውም ምክንያት በችሎት ቀርቦ መመስከር ባልቻለ ጊዜ ሁሉ ዓቃቤ ሕግ የሚጠቅሰው ሥነ ሥርዓት የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 145 ነው፡፡ በችሎት የቀረቡ ምስክሮች አጠራጣሪ ወይም የቀረበውን ክስ በሚገባ የማያስረዱ ሲሆን ዓቃቤ ሕግ ፊቱን ወደ 145 ያዞራል፡፡ 145 የዓቃቤ ሕግ የማስረጃ ክፍተት ማሟያ እየሆነ መጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቶችም ይህንንኑ ለፖሊስ የተሰጠ የምስክርነት ቃል በአብዛኛው ተቀብለው በማስረጃት ሲጠቀሙበት ይሰተዋላል፡፡

የዚህ ጽሑፍ መሠረታዊ ማጠንጠኛም የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 145 ያለአግባብ በዓቃቤ ሕግና በፍርድ ቤቶች ጥቅም ላይ ውሏል የሚለው ነጥብ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህን ሁኔታ በሚከተሉት ሦስት ነጥቦች እንዴት ተገቢ እንዳልሆነ ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡

1.  በተከሳሹ መስቀለኛ ጥያቄ፣ በፍርድ ቤቱማጣሪያ ጥያቄ ያልቀረበለት፣ ተገቢው መኃላ ፈጽሞ ምስክርነቱን ያልተሰጠንምስክርነት ቃል በማስረጃነት መቀበል ሕገ መንግሥታዊ ስላለመሆኑ

አንድ ተከሳሽ ጥፋተኛ እስኪባል ንፁህ ነው፡፡ ይህ ንጹህነቱ ጥፋተኛ እስኪባል ድረስ ከሚረጋገጥባቸው የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ደረጃዎች አንዱ የቀረበበትን ምስክር በጥያቄዎቹ መፈተን ሲችል ነው፡፡ ተከሳሽ የቀረበበትን ምስክር ሲጠይቅ ለፍርድ ቤቱ የሚያሳየው እውነት ከመኖሩም ባላይ ፍርድ ቤቱ ስለ ምስክሩ ታማኝነት፣ ስለምስክርነቱ ክብደት እና ተገቢነት የሚረዳው እውነት ይኖራል፡፡ በተከሳሽ መስቀልያ ጥያቄ ያልቀረበለት ምስክር ምስክር ሳይሆን ቃል አቀባይ ነው፡፡ በጥያቄ የሚመሰከረው ምስክርነት እውነትና ያልተመረመረ ምስክርነት ምስክርነት ሳይሆን የአቋም መግለጫ ነው፡፡ ለዚህም ነው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20 ላይ የተከሰሱ ሰዎች የቀረቡላቸውን ምስክሮች የመጠየቅ መብት የተጎናጸፉት፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 136 እና ተከታዮች ድንጋጌዎችም ስለምስክርነት ሥርዓት ቁልጭ ተደርጎ ተቀምጧል፡፡ በሥነ ሥርዓት ሕጉ አንድ ምስክር በአንድ ተከሳሽ ላይ እንዲመሰክር ሲደረግ ስለ እውነት በሚያምንበት ነገር የመማል በሚመሰክርበት ጊዜ ለተከሳሽ መስቀልያ ጥያቄዎች እንዲሁም ለፍርድ ቤቱ የማጣሪያ ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ ምናልባትም እንደ ክርክሩ ደረጃ ከኤግዚቢቶች፣ ቀደም ሲል ከተሰጠው ምስክርነት ከነገሮች ጋር የተዛመዱ ፈታኝ የመስቀልያ ጥያቄዎች ይቀርቡለታል፡፡ በነዚህ ሂደቶች አልፎ የሰጠው ምስክርነት ከጉዳዩ ጋር ተገቢነት ያለው፣ የማስረዳት ክብደቱ ከፍተኛ የሆነ፣ እምነት የሚጣልበት ምስክርነት ሰጥቶ ከሆነ በርግጥም ተከሳሹ በዚህ ምስክር ምስክርነት ንጹህ ሆኖ የመገመት ካባው ወልቆ ጥርጣሬ ላይ ሊወድቅ ይችላል፡፡ ይህን ማስተባበል ባለመቻሉም ወንጀለኛ ተብሎ ቢፈረጅ የፍትሕ ሥርዓቱ የሚፈልገው ተገቢ ሁነት ነው እና እሰይ እንጂ ለምን ሊባል አይችልም፡፡

በሕገ መንግሥቱም ሆነ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተቀመጡ የመማል፣ በክስ ሂደቱ የቀድሞ ጥፈተኝነት ያለመግለፅ፣ ዋና ጥያቄ መስቀለኛ ጥያቄ እና ድጋሜ ጥያቄ የመጠየቅና የመጠየቅ፣ በተለየ ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር በግልፅ ችሎት የመዳኘት፣ ጉዳዮች ዓላማው በተድበሰበሰ፣ ግልፅነት በጎደለው፣ ተገቢው ጥያቄ ባልቀረበበት፣ እምነት በማይጣልበት፣ ሀሰት በሆነ ምስክርነት ንፁህ የሆኑ ሰዎች ወንጀለኛ እንዳይባሉ ለመከላከል ለተከሳሹ መብት ዘብ ያቆማቸው መሠረታዊ የወንጀል ክርክር መግለጫዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ ሂደቶች ያላላፈን በአንድ ወቅት ፖሊስ ሲጠይቀው ለፖሊስ የሰጠው ቃል ለጠፋ ምስክር፣ ለተንሻፈፈ ማስረጃ፣ ለጎደለ ምስክርነት ማሟያ የምናደርገው ከሆነ ከፍ ሲል የተገለፀው መሠረታዊ የወንጀል ክርክር ሂደቶችን አስፈላጊነት መካድ ይሆንብናል፡፡

Continue reading
  17101 Hits