በኅብረተሰብ ጤና ዘርፍ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሚባል ለውጥ ካስመዘገቡ አገሮች ተርታ ትመደባለች፡፡ የጤና አገልግሎትን በቀበሌ ደረጃ ለማስፋፋት፣ በተለይም በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የኅብረተሰብ ክፍል ማዕከል ያደረገና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የተቸረውን የጤና ኤክስቴንሽን መርሐ ግብር ተግባራዊ በማድረግ፣ የዓለም መንግሥታት ድርጅትን የጤና የሚሊኒየም ግቦችን ለማሳካት ችላለች፡፡ እንደ አብዛኛው ታዳጊ አገሮች ሁሉ ባለፉት ዓመታት የመንግሥት የጤና ፕሮግራሞችና የአጋር ድርጅት ትኩረቶች ውስጥ ወባ፣ ኤችአይቪ/ኤድስና ሳንባ ነቀርሳ የመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎች የመከላከልና ቁጥጥር ሥራ፣ እንዲሁም የሕፃናትና እናቶች ጤናን ማሻሻል በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የአገሪቱ የበሽታዎች ሥርጭት ሁኔታ በለውጥ ሒደት ላይ ያለ ሲሆን፣ በተለይም በከተማዎችና በዙሪያቸው ባሉ ሥፍራዎች በመስፋፋት ላይ የሚገኙት የልብ፣ የመተንፈሻ አካላት፣ ስኳርና ካንሰርን የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ይጠቀሳሉ፡፡
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እየተስፋፉ በመምጣታቸው ምክንያት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን የትኩረት አቅጣጫ የሚያሳይ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ብሔራዊ የድርጊት መርሐ ግብር ስትራቴጂ (National Strategic Action Plan (NSAP) for Prevention & Control of Non Communicable Diseases in Ethiopia) በ2007 ዓ.ም. ተዘጋጅቷል፡፡ ለእነዚህ በሽታዎች ወይም የጤና ሁኔታዎች ዋነኛ ምክንያቶች ተብለው ከተለዩት መካከልም ማንኛውንም ዓይነት የትምባሆ ምርት መጠቀም፣ ከመጠን በላይ የአልኮል መጠጦችን መውሰድ፣ በቂ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግና ለጤና ተስማሚ ያልሆኑ ምግቦችን ማዘውተር ይጠቀሳሉ፡፡
ከብሔራዊ የድርጊት መርሐ ግብር ስትራቴጂው በተጨማሪ በተመሳሳይ ዓመት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች አጋላጭ ከሚባሉት ዋነኛ መንስዔዎች አንዱ የሆነውን የትምባሆ ምርትን በሚመለከት፣ በዓለም የጤና ድርጅት የወጣውን የትምባሆ ምርት ቁጥጥር ማዕቀፍ ኮንቬንሽን አፅድቋል፡፡ ተግባራዊነቱን የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን እንዲከታተል ኃላፊነት በአዋጅ ቁጥር 822/2007 ሰጥቷል፡፡
በዚህ አዋጅ መሠረት የትምባሆ ምርት ቁጥጥር ማዕቀፍ ኮንቬንሽን ማፅደቂያ በከፊል ለማስፈጸም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከሁለት ዓመት በፊት የትምባሆ ቁጥጥር መመርያ አውጥቷል፡፡ የትምባሆ ቁጥጥር መመርያው ከአፈጻጸም ጋር በተያያዘ የተለያዩ ክፍተቶች ቢኖሩበትም፣ ሕፃናትንና ታዳጊ ወጣቶችን በእጅጉ ሱስ አስያዥ የሆነው ኒኮቲክ ለሚባለው ንጥረ ነገር ተጋላጭነት ለመቀነስና ብዛት ባላቸው አገሮች እያደገ በመጣው የትምባሆን ምርት ጣዕም መቀየሪያ እንዳይጨመርበት በመከልከል፣ ሊመሰገን የሚገባው የሕግ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ተመሳሳይ የሆኑ ድንጋጌዎች የያዘ የትምባሆ ምርት ቁጥጥርን መመርያ በተወሰኑ ክልሎችና በከተማ አስተዳደር ደረጃ ጭምርም የወጣ ሲሆን፣ ይህን ዓይነት ምርት በክልሎች ውስጥ ለሽያጭ ማቅረብ፣ መሸጥና ማከፋፈል የተከለከለ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ባወጣው የትምባሆ ምርት ቁጥጥር መመርያ ቁጥር 28/2007 መሠረት፣ የትምባሆ ምርት የሺሻ ትምባሆን ጨምሮ ማንኛውንም በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ከትምባሆ ቅጠል የተዘጋጀ በማጨስ፣ በመሳብ፣ በማኘክ፣ በማሽተት ወይም በሌላ መንገድ የሚወሰድ ንጥረ ነገርን እንዲያካትት ሆኖ ተተርጉሟል፡፡ ይህ ማለት ትምባሆ በስፋት በሚታወቀው የሲጋራ ምርት ብቻ ሳይወሰን የሚታኘክን፣ እንዲሁም የተለያዩ የማጨሻ መሣሪያዎችን በመጠቀም የሚጨስ እንደ ሺሻ ትምባሆ ያለን ምርት ያካትታል፡፡ ይህ የትምባሆ ምርት ትርጉም በተወካዮች ምክር ቤት በፀደቀው የትምባሆ ምርት ቁጥጥር ማዕቀፍ ኮንቬንሽን ጋር የተጣጣመ ሆኖ፣ የሺሻ ትምባሆን ወይም በባህላዊ መንገድ የሚዘጋጅ ጋያን በግልጽ እንዲያካትት ሆኖ ነው የተቀመጠው፡፡