መግቢያ
ቼክ በተግባር በሰፊው ከሚሰራባቸውና በሕግ ከተቀመጡት ንግድ ሰነዶች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ በቼክ ላይ እምነት የሚታጣበት ከሆነ የንግድ ዝውውር ደህንነት (security of transaction) ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተፅዕኖ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ የንግድ ሥራው እያደገ በመጣ ቁጥር በቼክ የሚደረጉ የንግድ ልውውጦች የሚጨምሩ እንደሚሆን የሚታመንና በተግባርም የሚታይ ነው፡፡ የቼክ ዝውውር እየጨረ እንደመጣም መገመት አያዳግትም፡፡ እየጨመረ የመጣውን የቼክን ዝውውር አስተማማኝነት ለማሳደግ ሕጎች ሥርዓቱን ሊቆጣጠሩት ይገባል፡፡ በዚህም መሠረት በእኛ ሀገር የንግድ ሕጉ እና የወንጀል ሕጉ ይህንኑ የቼክ ጉዳይ በዋናነት ይህን ሥርዓት ዘርግተው ይገኛሉ፡፡ ባብዛኛው የቼክ ጉዳይ የሚያከራክር ጉዳይ የሌለበት ቢሆንም አልፎ አልፎ ግን አከራካሪ ጉዳዮች መታየታቸው አልቀረም፡፡ ይህ ጽሑፍ ዓላማውም በቼክ ዙሪያ ያሉትን አስፈላጊ የሕግ ድንጋጌዎችንና አስገዳጅ የፍርድ ውሳኔዎችን ማሳወቅና በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለአከራካሪ ጉዳዮች የጸሐፊውን እይታ ማንፀባረቅ ነው፡፡
ቼክ ምንድ ነው?
በንግድ ሕጉ ላይ የቼክ ዓይነቶች፡ የስርዝ ምልክት ያለበት ቼክ (crossed cheque)፣ ከሂሳብ ውስጥ የሚገባ ቼክ (cheques payable in account) እንዲሁም የመንገድ ቼክ(travellers cheque) የሚባሉ ሲኖሩ የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ግን እነዚህን ወደ ጎን በመተው በንግድ ሕጉ ቁጥር 827 ጀምሮ የተቀመጠውን መደበኛ የቼክ ዓይነት ላይ ያተኩራል፡፡