መግቢያ
ቼክ ጥሬ ገንዘብን ተክቶ በመገበያያነት አገልግሎት ላይ የሚውል የሚተላለፍ የንግድ ወረቀት አይነት ነው። በሀገራችን በቼክ መገበያየት እጅግ የተለመደ ተግባር ሲሆን ቼክም ሌሎች የሚተላለፉ የንግድ ሰነዶች ካላቸው እውቅናና ተቀባይነት በላቀ አገልግሎት ላይ እየዋለ ያለ እና በህብረተሰቡም ዘንድ እውቅና ያለው ሰነድ ነው። በሰነዱ ላይ ህብረተሰቡ የጣለው እምነትና በስፋት አገልግሎት ላይ መዋሉም በሰነዱ ላይ በተለያዩ ጊዜያት እና በስፋት የፍርድ ቤት ክርክሮች እንዲነሱ አንዱ ምክንያት እንደሆነ እሙን ነው። ታዲያ በዚህ ሰነድ በስፋት አገልግሎት ላይ መዋልና በሕጋችን ውስጥ ሰነዱን አስመልክቶ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ማሻሻል እና ክፍተቱን መሙላት አስፈላጊና ለሰነዱ ቀጣይነትም አስተማማኝ ዋስትና ነው።
በዚህ አጭር ጽሑፍ ውስጥም በተለይም ቼክን በተመለከተ በስፋት የሚያጋጥመውንና በሕጋችን ሽፋን የተሰጠውን የቼክ የክፍያ ይቁም ትዕዛዝ (Stop Payment Order) በተመለከተ ጥቂት ምልከታ ለማድረግ ነው። በጉዳዩ ላይ በስፋት አንባቢዎች ግንዛቤን ከፈለጉ ጸሐፊው የኢትዮጵያ የባንክ እና የሚተላለፉ የንግድ ሰነዶች ሕግ በሚል የታተመውን መጽሀፍ ማንበብ እንደሚችሉ በዚሁ ለመግለጽ እወዳለሁ።