በሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የአስተዳደር ጥፋት የሚመለከት ምርመራ ለማካሔድ ስለአስተዳደር በደል በሚቀርብ አቤቱታ ሊጀመር ይችላል፡፡ ማለትም ተቋሙ በራሱ አነሳሽነት ከሚያደርገው ምርመራ በስተቀር ሁሉም በእንባ ጠባቂ በኩል የሚደረጉ ምርመራዎች ሥረ መሠረቱ ለተቋሙ የሚቀርብ አቤቱታ ነው፡፡
የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት በአዋጅ ቁጥር 1/1995 አንቀፅ 74 እና አንቀፅ 75 የጠቅላይ ሚኒስትሩን እና የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሥልጣን እና ተግባር በቅደም ተከተል አስቀምጧል። የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት ከህግ የመነጨ ሥልጣን ሊኖራቸው ስለሚገባ የተቋማቱን ሥልጣንና ተግባራት ለመወሰን በተለያዩ ጊዜያት አዋጆች መውጣታቸው ይታወሳል። የፌደራል መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣንና ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት እንዲያስችለው የአስፈፃሚ አካላትን አደረጃጀት፣ ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ (55) መሰረት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፌደራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን አዋጅ ቁጥር 1097/2018 ወጥቶ ነበር።
ባለንበት ዘመን ሕገ መንግሥት ወይም ስለመንግሥት አሠራርና አመራር የሚደነግግ ሕግ የሌሎው ሀገር ለማግኘት ያስቸግራል፡፡ ሳስበው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መደንገግና በዛው ልክ መቆጣጠር ያስፈለገበት መሠረታዊ ምክንያት የሰው ልጅ ካለፈባቸው የችግርና የጦርነት ውጤት የቀሰመው አብይ መፍትሔ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ አብዛኞቹ ሀገራት በሕገ መንግሥታቸው ውስጥ ከሚያካትቱት መሠረታዊና ጥቅል ድንጋጌዎች መካከል የመንግሥት ሥልጣንና ተግባር፣ የዜጎች መሠረታዊ መብትና ግዴታ፣ የመንግሥት አስተዳደርና የሥልጣን ክፍፍል እንዲሁም የአሠራር ሁኔታ ይገኙበታል፡፡