Font size: +
28 minutes reading time (5528 words)

በሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የአስተዳደር ጥፋት አቤቱታና የአቤቱታ አያያዝ አመራር

በሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የአስተዳደር ጥፋት የሚመለከት ምርመራ ለማካሔድ ስለአስተዳደር በደል በሚቀርብ አቤቱታ ሊጀመር ይችላል፡፡ ማለትም ተቋሙ በራሱ አነሳሽነት ከሚያደርገው ምርመራ በስተቀር ሁሉም በእንባ ጠባቂ በኩል የሚደረጉ ምርመራዎች ሥረ መሠረቱ ለተቋሙ የሚቀርብ አቤቱታ ነው፡፡

ስለአቤቱታ አቅራቢ

ለእንባ ጠባቂ ተቋም አቤቱታ የሚቀርበው መብቴ ተጥሶብኛል በሚል ሰው፣ ወይም በሚስት ወይም በባል ወይም በቤተዘመድ ወይም በወኪል ወይም በሦስተኛ ወገን ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ዓረፍተ ነገር ከግል ተበዳይ ውጭ ያሉ አቤቱታ ለማቅረብ የሚችሉ ሰዎች ማንነት የሚሸፈነውና የሚወሰነው በሌሎች አግባብነት ባላቸው ሕጐች ነው፡፡ ባል፣ ሚስትና ቤተዘመድ ተብሎ የተጠቀሰው በቤተሰብ ሕግ በተመለከተው መሠረት የሚወሰን ሲሆን ወኪል በፍትሐብሔር ሕግና በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ውክልና በሚመለከቱ ድንጋጌዎች የሚሸፈን ነው፡፡ በአዋጅ ቁጥር 211/1992 አንቀጽ 22 ሥር አቤቱታ ለማቅረብ ከሚችሉ ሰዎች መካከል የተዘረዘረው “ሦስተኛ ወገን” የሚለው ሀረግ ምን ያመለክታል? ይህ ሦስተኛ ወገን ለአቤቱታ መነሻ በሆነው ነገር ላይ ጥቅም ወይም መብት ያለው ሰው ነው? ወይስ ማንም የፈለገ ሰው ስለአንድ የአስተዳደር በደል ለእንባ ጠባቂ ተቋም አቤቱታ ማቅረብ ይችላል? የሕጉ መንፈስ ምንድ ነው? ለምሳሌ በስኮትላንድ የእንባ ጠባቂ ሕግ መሠረት የኅብረተሰቡ አካል በሆነው ሰው ላይ ደርሷል ስለተባለው የአስተዳደር በደል የኅብረተሰቡ አባል የሆነ ሌላ ሰው ስለበደሉ ለእንባ ጠባቂ ተቋም አቤቱታ ለማቅረብ ይችላል፡፡ ነገር ግን በአዋጁ “ሦስተኛ ወገን” ተብሎ የተመለከተው በአገሪቱ ውስጥ በአድቮኬሲ ሥራ ላይ የተሰማሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶችን ያጠቃልላል?

በሌላ በኩል በአዋጅ ቁጥር 211/1992 አንቀጽ 24/2/ በተመለከተው መሠረት “የሕዝብ አንባ ጠባቂ ተቋም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው በራሱ አነሳሽነት ምርመራ የማካሔድ ሥልጣን አለው”፡፡ ተቋሙ በራሱ አነሳሽነት ምርመራ ሲያካሔድ ምንን መሠረት ያደርጋል?

ይህን የአዋጁን አንቀጽ 24 ንዑስ አንቀጽ 2 ድንጋጌ ከአዋጁ አንቀጽ 6 ስለተቋሙ ሥልጣንና ተግባር ከሰፈረው ድንጋጌ ጋር አያይዞ ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ ድንጋጌ በተመለከተው መሠረት ተቋሙ “አስፈጻሚ አካላት የሚያወጧቸው አስተዳደራዊ መመሪያዎች፤ የሚሰጧቸው ውሳኔዎችና አሠራሮቻቸው የዜጐች ሕገ መንግሥታዊ መብቶችንና ሕጐችን የማይቃረኑ መሆናቸውን ይቆጣጠራል፡፡” የዜጐች ሕገ መንግሥታዊ መብቶች የተባለው በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ሕገ መንግሥት በአጠቃላይ በምዕራፍ ሦስት ሥር የተገለጹ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን እንዲሁም በክልሎች ሕገ መንግሥቶች የተመለከቱ መብቶች የሚያካትት ሲሆን ሕጐች የሚለው በፌዴራልና በክልሎች ሕግ አውጪዎች የሚወጡ ሕገ መንግሥታዊ ሕጐች ለማለት ነው፡፡ የአሰፈጻሚ አካላት አጠቃላይ ተግባራት ከሕገ መንግሥትና ሌሎች ሕጐች ጋር የሚጣጣሙ ስለመሆናቸው ጥርጣሬ የሚያሳድር ከሆነ በቁጥጥር ሥራ ወቅት የተገነዘባቸውን የአስተዳደር በደሎችን መሠረት በማድረግ ሌላ ተጨማሪ አቤቱታ ማቅረብ ሳያስፈልግ የሕዝብ እንባ ጠባቂ አስተዳደራዊ ጥፋትን አስመልክቶ ምርመራ ማጣራት ይቻላል፡፡ በመሆኑም የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በዚህ አኳኋን የሚያደርገው ምርመራ በአዋጅ ቁጥር 211/92 አንቀጽ 6 ንዑስ አንቀጽ 3 በተደነገገው መሠረት አስቀድሞ አስተዳደራዊ ጥፋቶች እንዳይፈፀሙ በቅድሚያ ለመከላከል ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ በተጨማሪም በቁጥጥር ወቀት የሚፈጠር ጥርጣሬ መሠረት በማድረግ ተቋሙ የሚያካሔደው ምርመራ የተፈጸመውን የአስተዳደር በደል በተመለከተ መፍትሔ ለመሻት ይረዳል፡፡ እንደዚሁም ተቋሙ አስተዳደራዊ ጥፋቶችን ለማሻሻል የሚያደርገው ጥናት በራሱ በአስተዳደር በደል ላይ ምርመራ ሊካሔድ እንደሚገባ ሊጠቁም ይችላል፡፡ ስለዚህ ተቋሙ ከላይ ከተጠቀሱት አንዱ ወይም ሌላውን መሠረት በማድረግ በራሱ አነሳሽነት የአስተዳደር በደል ላይ ምርመራ ማካሔድ ይችላል፡፡

በሌላ በኩል የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ምርመራ መሠረት ያደረገው የቀረበለትን አቤቱታ በሆነ ጊዜ መርማሪው ከአቤቱታ አቅራቢ ሁለት በምርመራ ሂደት በጣም ጠቃሚ የሚሆኑ መረጃዎች ማግኘት መቻል አለበት፡፡ እነዚህም ፡

ሀ. አብዛኛውን ጊዜ የአንድ አቤቱታ መንስዔና መነሻ ስለሆነው ወይም ስላልሆነው ነገር አቤቱታ አቅራቢው በተቃራኒው ያለው ፍላጐት (expectation) ስለሆነ መርማሪው በየደረጃው ነገሩን መረዳትና ማወቅ ያለበት በመሆኑ ስለነገሩ አስረጂ የሚሆኑ ማናቸውም መረጃዎች በተለይም አቤቱታ አቅራቢው ከተመርማሪው አስተዳደር አካል ጋር ያደረጋቸው ምልልሶችን የሚያመለክቱ መጻጻፎችና ሰነዶች መቀበል አለበት፡፡ ምክንያቱም ስለአጠቃላይ ሁኔታ ጠልቆ የሚያውቀው አቤቱታ አቅራቢው ራሱ ስለሆነ በእጁ የሚገኙ መረጃዎችን ሊሰጥና በእጁ የሌሉ ነገር ግን ሌላ ቦታ የሚገኙ መረጃዎች ያሉበትን ቦታ መጠቆም ይችላል፡፡

ለ. አቤቱታ አቅራቢው እንዲሆን ወይም እንዲደረግለት የሚፈልገው ነገር ምንድነው የሚለው ነው፡፡ አቤቱታው በግልጽ የሚዳሰስና የሚታይ (objective) ነገር ላይ ለምሳሌ መለካት በሚቻልበት ሁኔታ አንድ አገልግሎት በተወሰነው ሰዓትና አኳኋን መስጠት ወይም ሁኔታን በሚገልጽ (subjective) ለምሳሌ አንድን አገልግሎት ያለአድሎኦ፣ ትክክለኛና ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ (fairly) በተገቢው አኳኋን ማግኘት መሠረት ባደረገ ፍላጐት ጥያቄ ላይ የሚያጠነጥን ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ መርማሪው የአቤቱታ አቅራቢው ቅሬታ በአንዱ ወይም በሁለቱም ላይ መሆኑን መረደት አለበት ፡፡

በእርግጥ ሁለቱንም መሠረት በማድረግ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን መርማሪው ማስተናገድ አለበት፡፡ ይሁን እንጂ በተገቢው አኳኋን አገልግሎት ማግኘት (subjective) ተመርኩዞ የሚቀርበው አቤቱታ በጣም ውስብስብ ከመሆኑ የተነሣ ለአቅራቢው ከሆነው ነገር /ከተሰጠው አገልግሎትና አቤቱታ አቅራቢው መሆን ነበረበት ብሎ /ከሚያስበው/ ከሚገምተው ነገር መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ አስቸጋሪ ስለሚሆን መርማሪው ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ከባድ ሥራ ይጠብቀዋል፡፡ በሌላ በኩል መለካት በሚቻልበት ሁኔታ አንድን አገልግሎት በተወሰነ ጊዜ/ሰዓት/እና አኳኋን መስጠት በሚመለከት በቀረበ አቤቱታ የሆነው/የተደረገው ነገርና ምን መሆን/መደረግ እንደነበር ከተቀመጠው መለኪያ ተነስቶ በቀላሉ ለማወቅ ስለሚቻል ምርመራውን አካሔዶ ድምዳሜ ላይ መድረስ ይህን ያህል አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ከመጀመሪያ ጀምሮ ከአቤቱታ አቅራቢው ጋር ተገቢውን የሀሳብ መለዋወጥ (conversation) ማድረግ አቤቱታ የቀረበበትን ጉዳይ ግልጽ ለማድረግና አቤቱታ አቅራቢው የሚፈልገውን/የሚጠይቀውን ነገር ለማወቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡

እንግዲህ ምርመራው በተሳካ ሁኔታ እየተስተካከልና እየጐለበት እንዲሔድ በጣም ወሳኙ ነጥብ የተወሰኑ አግባብነት ያላቸው የአቤቱታ ጭብጦችን ይዘት በግልጽ/በሚገባ መረዳትና ማቀናበር ነው፡፡ ምክንያቱም በርካታ አቤቱታዎች በአንድ ጭብጥ ብቻ ዙሪያ የሚሽከረከሩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከላይ እንደተመለከተው የምርመራ አስኳል አቤቱታ አቅራቢው ላይ በተፈጠረው ክስተት/በሆነው ነገር/እና እሱ እንዲደረግለት ከሚጠብቀው ወይም ከሚፈልገው ነገር መካከል ያለውን ነገር (ክፍተት) የፈጠረው ሁኔታ ነው፡፡ ስለዚህ መርማሪው ምክንያትና ውጤት መካከል ያለውን ግንኙነት ወይም ሁኔታ መለየት አለበት፡፡ አብዛኛውን ጊዜ አቤቱታ አቅራቢው ማስረጃ ማቅረብ የሚችለው ከምክንያት ይልቅ ስለጉዳዩ ውጤት ጉድለት ነው፡፡ ነገር ግን መርማሪ የውጤትን ጉድለት ብቻ ሳይሆን በቀላሉ ከሚታዩ ምክንያቶች ወጣ ብሎ አርቆ በማሰብ አቤቱታ አቅራቢው ከአስተዳደር አካል በትክክል ምን እንደሚፈልግና እንደሚጠይቅ ማወቅና መወሰን አለበት፡፡ ምክንያቱም በምርመራ ሥራ ሂደት መርማሪው በመሠረታዊ ምክንያት ላይ ትንተና አካሔዶ አቤቱታውን በመተርጐም አጠቃላይ ስለምርመራው ዕቅድ ማውጣት ሚችለው በዚህ ደረጃ ነው፡፡

አቤቱታ መገምገም

የሕዝብ እንባ ጠባቂ መርማሪ የመጀመሪያ ዋና ሥራ እንዲመረምር የተጠየቀውን ነገር በትክክል ጠንቅቆ ማወቅ ነው፡፡ በምርመራ ሥራ የቀረበውን ጥያቄ/አቤቱታ በትክክል ለይቶ ማወቅ እንደሚገመተው ቀላል አይደለም፡፡ እንዲያውም ይህ በመርመራ ሥራ ሒደት ዋና ቁልፍ ተግባር ነው፡ አቤቱታ አቅራቢዎች ቅሬታ ስላስነሳው ነገር ምን እንደተከሰተ/እንደሆነ/ እና አንድ ነገር እንዴት በሚጠብቁት አኳኋን እንዳልሆነ የራሳቸው የሆነ አመለካከትና ግንዛቤ አላቸው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ተመርማሪው የአስተዳደር አካልም ስለተከሰተውና ስለሆነው ነገር እንዲሁም ያ ነገር ለምን እንደሆነ የራሱ ምክንያትና ግንዛቤ አለው፡፡ ነገር ግን ከግራ ቀኙ በተለየ ሁኔታ መርማሪው የቀረበውን አቤቱታ ለመመርመር የሚያስችል ራሱ የደረሰበት ግልጽና ተጨባጭነት ያለው የክርክር ነጥብ ሊያገኘው ይገባል፡፡

እንደተባለው ማናቸውም ምርመራ ተመርማሪው አስተዳደር አካል ማድረግ ከነበረበትና ለአቤቱታ አቅራቢው በተደረገው መካከል ክፍተት/ልዩነት/እንዳለ ለማግኘት የሚደረግ ትንተና ነው፡፡ በአቤቱታ ላይ ትንተና በማድረግ መርማሪው ቀጥታ ምርመራ ውስጥ ከመግባቱ አስቀድሞ ምርመራ የሚካሔድበትን ነገር ግራ ቀኙ ወገን መረደት በሚችሉት አኳኋን ይተረጐማል፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ምርመራው የሚከተለውን በመለየት ቅድመ ተከተሉን በመያዝ መከናወን አለበት፡፡ ይኸውም

ሀ. ምን ሊደረግ ይገባ ነበር? (ምንድነው ይጠበቅ የነበረው?

ለ. ምንድነው የተደረገው? በእርግጥ ምን ተከሰተ?

ሐ. በ “ሀ” እና በ “ለ” መካከል ልዩነት አለ?

መ. ልዩነት አለ ከተባለ ለምን?

ሠ. ልዩነት የለም ከተባለ አቤቱታ አቅራቢው ለምን በተደረገው ነገር

ሳይረካ በሌላ መልክ አሰበ?

ረ. በ“መ” ምክንያት የተፈጠረው ነገር እድምታ ምንድነው?

ሠ. የተፈጠረው/የተከሰተውን የአስተዳደር ጥፋት ለማረምና ለማስተካከል

ምን ሊደረግ ይገባለ ?

ሸ. ጥፋቱ እንደገና እንዳይከሰት ለማስወገድ ምን ሊደረግ ይገባል ? የሚሉ ናቸው፡፡

መርማሪ የሚቀርብለትን አቤቱታ ሲመረምር ከላይ የተመለከተውን መሠረታዊ ቅድመ ተከተል ሊጠቀምና ሊጠብቅ ይገባል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ እነዚህን የመለየት ችሎታ ከመርማሪ መርማሪ ሊለያይ ይችላል፡፡ አተረጓጐምም እንደዚሁ ሊለያይ ይችላል፡፡ ነገር ግን አቤቱታውን በሥነ ሥርዓት በአግባቡ መገምገም የ“ሀ”ን ጥያቄ ለመመለስ ስለሚያስችል ቀጥሎ ያለውን በአግባቡና በቅድመ ተከተሉ ጠብቆ ለመሥራት ይረዳል

አቤቱታ ለመመርመር መወሰን

ወደ ምርመራ ለመግባት ለመወሰን መርማሪው ከአቤቱታ አቅራቢው የተቀበላቸውን መረጃዎች አንድ በአንድ መተንተን አለበት፡፡ ይህንን ትንተና ሲሠራ የተቋሙ የሥልጣን ጥያቄ ከግምት ውስጥ ይገባል፡፡ የሕዝብ እንባ ጠባቂ በዚህ ጊዜ አቤቱታውን ለመመርመር ሥልጣን መኖር አለመኖሩን የሚፈተሸው ከሦስት ዋና ዋና ነገሮች አኳያ ነው፡፡ ይኸውም ለተቋሙ ከቀረበው ጉዳይ (አቤቱታ)፤ ከአቤቱታ አቅራቢውና ከተመርማሪው የአስተዳደር አካል አንጻር ሥልጣን መኖር አለመኖሩ ይታያል፡፡ በዚህ መሠረት የአዋጁ አንቀጽ 7 እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

“ተቋሙ፡-

1. በሕዝብ ምርጫ የተቋቋሙ ምክር ቤቶች በሕግ አውጪነታቸው የሚሰጧቸው ውሳኔዎች ወይም

2. በማንኛውም ፍርድ ቤት በየትኛውም ደረጃ በመታየት ላይ ያሉ ጉዳዮች ወይም፣

3. በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በመታየት ላይ ያሉ ጉዳዮችን ወይም

4. በፀጥታ ኃይሎችና በመከላከያ ሠራዊት ክፍሎች የሚሰጡ የፀጥታ ወይም የሀገር መከላከያ ጉዳዮችን በሚመለከት የሚሰጡ ውሳኔዎችን፣ የመመርመር ሥልጣን የለውም፡፡”

ከሕጉ /ከዋጁ/ ድንጋጌ የምንረዳው ከሥልጣን አኳያ በግልጽ የተዘረዘሩት በተቋሙ ሥልጣን ሥር የማይሸፈኑ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በርግጥ ከነዚህ ከተዘረዘሩት ውጪ ያሉ በተቋሙ ሥልጣን ሥር የሚካተቱ ጉዳዮችና አስተዳደር አካላት ትርጓሜን በሚመለከት የአዋጁ አንቀጽ 2 (5) (10) (11) እና (13) ሥር ተመልክተዋል፡፡ ስለዚህ ሕጉ በተቋሙ ሥልጣን ሥር የሚወድቁና የማይወድቁ ጉዳዮችና ባለጉዳዮችን የዘረዘራቸው ስለሆነ የተቋሙን ሥልጣን ለመለየት አስቸጋሪ አይሆንም፡፡

በተጨማሪ ትንተናው ሲካሔድ ጉዳዩን የያዘው ሰው /መርማሪ/ ወደ መደበኛ ምርመራ ውስጥ ለመግባት የሚያስችል በቂ የሚመረመር ነገር/ጭብጥ/ (enough substance) መኖሩን፤ አቤቱታው ላይ የሰፈረው ነገር/ጉዳይ/ ወደ መደበኛ ምርመራ ውስጥ መግባት ሳያስፈልግ በቀላሉ ሊፈታ የሚችል መሆን አለመሆኑን፣ አግባብነት ያለውን ፍሬ ነገር ለመመሥረት ምክንያታዊ ተስፋ መኖር አለመኖሩን እና አቤቱታ አቅራቢው የሚጠብቀውን ውጤት ማስገኘት የሚቻል መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ስለዚህ ወደ ምርመራ ከመግባቱ በፊት መርማሪው የሚከተሉትን ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ ይጠበቅበታል፡፡

ጥያቄዎቹም

ሀ. አቤቱታው በጥቃቅን ነገር ላይ የተመሠረተ ነውን? ማናቸውም አቤቱታ በአቅራቢው እይታ በጥቃቅን ነገር ላይ የተመሠረተ መስሎ ላይታይ ይችላል፡፡ ነገር ግን አቤቱታው የተመሠረተበት ነገር ወይም የተጠየቀው ፍትሕ እዚህ ግባ የማይባል በሆነ ጊዜ አቤቱታው ጥቃቅን ነገሮች ላይ የቀረበ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ይህ በሆነ ጊዜ አለ የተባለውን የአስተዳደር ጥፋት ወይም የአገልግሎት አሰጣጥ ጉደለት ለማረም ወይም ለማስተካከል መፍትሔ ለመወሰን የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ምርመራ መጠቀም አላስፈላጊ መሆኑን መርማሪው ሊወስን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ በአስተዳደር አካል ተግባር (ርምጃ) ላይ የሚሰጠው ማሳሰቢያ/አስተያየት/ አቤቱታ ላቀረበው ግለሰብ ወሳኝነት የሌለው /not significant/ ወይም ለሱ የሚጨምረው ነገር ባይኖር እንኳ የቀረበውን አቤቱታ በጥልቅ መመርመርና የመፍትሔ ሀሳብ ማቅረብ ከአጠቃላይ የሕዝብ ጥቅም አኳያ የአስተዳደሩን ጥፋት ግልጽ ለማድረግና ችግሩ እንዲስተካከል ወይም እንዲታረም ለማድረግ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡

ለ. አቤቱታ የቀረበበት ጉዳይ ተመርማሪው የአስተዳደር አካል በእውነትም ለአቤቱታ አቅራቢው ሊያደርግለት የሚገባ ጉዳይ ነው? አቤቱታው ምክንያታዊ ያልሆነና እውነታ ወይም አሳማኝ ነጥብ የሌለው ሊሆን ይችላል፡፡ አቤቱታው በአቅራቢው ግምት/ የሚጠብቀው ነገር/ ላይ ብቻ ተመርኮዞ የቀረበ እንደሆነ መርማሪው በጉዳዩ ላይ ምርመራ ላለማካሔድ መወሰን ይችላል፡፡

ሐ. አቤቱታ አቅራቢው የሚጠይቀውን ነገር ማግኘት ይችላል? አንዳንድ ጊዜ አቤቱታ አቅራቢዎች የሚጠይቁት ነገር በባዶ ምኞት፣ ፍላጐትና ተስፋ ላይ የተመሠረተ ሆኖ የሚጠይቀው ነገር በተቋሙ ምርመራ የማይገኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የተጠየቀው ነገርና የተፈለገው ውጤት አቤቱታው በሌላ ተገቢ በሆነ አካል ቢታይ ሊገኝ የሚችል ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ የተፈለገው ነገር ከውል ውጭ ግዴታ የካሣ ጥያቄ የሚመለከት ከሆነ ጉዳዩ ለፍ/ቤት ቢመራና በዛው ቢታይ ውጤታማ ሊሆን ይችላል፡፡

መ. አቤቱታው አሰቸጋሪ ነውን?

በውስጡ ምንም ዓይነት እውነታ፣ ምክንያትና ቁምነገር ሳይኖር የአስተዳደር አካል/ሌላኛውን ወገን/ለማስፈራራት፣ ለማናደድና ለማሸማቀቅ የሚቀርቡ አቤቱታዎች ያበሳጫሉ፡፡ እነዚህ ዓይነት የአቤቱታ አቅራቢዎች ተገቢ ባልሆነ መንገድ በተቃራኒው ወገን ላይ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምን ለመጠቀም የፈለጉ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት አቤቱታዎችን በጥልቀት በመፈተሽ ምርመራ ላለመቀጠል መወሰን ይቻላል፡፡

ሠ. ተመርማሪው የአስተዳደር አካል ቅሬታውን ለመፍታት የሚችለውን ሁሉ አድርጓል? በአዋጅ ቁጥር 211/1992 አንቀጽ 22/3/ እንደተመለከተው “ማንኛውም ሰው ስለደረሰበት የአስተዳደር ጥፋት አቤቱታ ከማቅረቡ በፊት አግባብነት ላላቸው አካላት ደረጃውን ጠብቆ ቅሬታውን ማሰማት ይኖርበታል፡፡” ምክንያቱም አቤቱታ አቅራቢው ከተጠሪ የአስተዳደር አካል ዘንድ ያሉትን አማራጮች ሁሉ አሟጥጦ ቢጠቀም ኖሮ ተመርማሪው የአስተዳደር አካል ቅሬታውን በጥልቀት መርምሮ መፍትሔ የሚሰጠው ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ተመርማሪው አካል አጠቃላይ የድርጅቱን አሠራር ማሻሻሉንና መቀየሩን መርማሪው ከሚቀርበው ማስረጃ ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡ በመሆኑም መርማሪው አበቱታውን መመርመር አያስፈልግም ብሎ ሊወስን ይችላል፡፡ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ አቤቱታው ለምን እንደቀረበ በቅርበት መመርመር ተገቢ የሚሆንበት ሁኔታም ሊፈጠር ይችላል፡፡ ይህንን ዐይነት አጋጣሚ በመጠቀም በአቤቱታ ከቀረበው ጥያቄ ውስጥ ወሳኝ ጭብጥ በአግባቡ ያልተመለሰ ሊሆን ወይም የተደረገው ማስተካከያ በቂ ላይሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ምርመራ ማካሔዱ የተለየ ውጤት ላይ ሊያደርስ የሚችል ማስረጃ ሊያስገኝ የሚችል መሆን አለመሆኑን፣ ማስተ ካከያውና መፍትሔው አጥጋቢና ምክንያታዊ መሆን አለመሆኑንና፣ እንዲሁም ማስተካከያው ከሕዝብ ጥቅም አኳያ ይፋ መውጣት እና ለሕዝብ ተወካዮች ሪፖርት ሊደረግ የሚችል መሆን አለመሆኑን መርማሪው ይወስናል፡፡ ይህን ካደረገ በኋላ ነው መርማሪው መደበኛ ምርመራ ለመቀጠል ወይም ላለመቀጠል የሚወስነው፡፡

ረ. ቅሬታውን ለመፍታት ርምጃ መውሰድ ይችላል?

የአቤቱታ ቅድመ ምርመራ ፍተሻ ቅሬታው ላይ መደበኛ ምርመራ ማካሔድ ሳያስፈልግ መፍትሔ መስጠት ይቻል እንደሆነ ለማየት ይርዳል፡፡ በዚህን ጊዜ የእንባ ጠባቂ ተቋም ራሱ የመፍትሔ ርምጃ ሊወስድ ይችላል፡፡ ተቋሙ የመፍትሔ አቅጣጫ ለተመርማሪው የአስተዳደር አካል ወይም ለአቤቱታ አቅራቢው ለራሱ በመጠቆም ጉዳዩ ወደኋላ ለአስተዳደሩ በመመለስ ተጨማሪ ርምጃዎችን እንዲወስድ በማድረግ የሆነውን ነገር ለማስተካከል መፍትሔ መሻት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ግራ ቀኙ ወገን አቤቱታውን አማራጭ የመግባት መፍቻ ዘዴ ተጠቅመው መፍትሔ እንዲሰጡ ማድረግ፣

ሰ. ቅሬታው አግባብነት ያለው ፍሬ ነገር አለው?

የቀረበውን አቤቱታ አቅጣጫ ለማስያዝ በፍሬ ነገር ጭብጥ ላይ ድምዳሜ ላይ መድረስ ለአግባብነት ቁልፍ ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ ቅሬታው በአቤቱታ አቅራቢና በአስተዳደር መካከል ስለተደረገው የሀሳብ ልውውጥ ብቻ ሆኖ የተመዘገበ ሰነድም ሆነ ሌላ ገለልተኛ ማስረጃ/ምስክር የሌለው ከሆነ በፍሬ ነገር አግባብነት ላይ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አስቸጋሪ ነው፡፡ እንደዚሁም አቤቱታ የቀረበባቸው ጉዳዮች አሳሳቢና ጥንቃቄ የሚሹ ነገሮች ከሆኑ በፍሬ ነገሩ አግባብነት ላይ ድምዳሜ ላይ ከመድረስ አስቀድሞ ሌላ ማስረጃ ማግኘት እንደሚቻል ፍተሻ ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ ለባለጉዳዮች ቃለ መጠየቅ በማቅረብ የነገሩን አቅጣጫ ማየትን ያካትታል፡፡

የእንባ ጠባቂ የምርመራ አካሔድ አመራር

ምርመራ በግርድፉ ሲታይ ሕጋዊና በሥነ ሥርዓቱ መሠረት ማስረጃዎችን መለየት፣ መሰብሰብ፣ መጠበቅና መገምገም የሚያካትት ነው፡፡ ከላይ እንደተመለከተው የህዝብ እንባ ጠባቂ ምርመራ የሚካሔደው በቅድሚያ በአቤቱታው ላይ ትንተና ተሰርቶ ጉዳዩ ወደ ምርመራ የሚያስገባና ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ መርማሪው በአቤቱታው ላይ ትንተና በማካሔድ ምርመራ ከመጀመሩ በፊት ምርመራ ስለሚደረግበት ነገር ለአቤቱታ አቅራቢውና ለተጠሪ መሥሪያ ቤት (የአስተዳደር) አካል ያሳውቃል፡፡ ለሁለቱም ባለጉዳዮች መርማሪው ገለልተኛ በመሆኑ አቤቱታ አቅራቢውንም ሆነ ተጠሪ የአስተዳደር አካል ወክሎ እንደማይንቀሳቀስ እንዲረዱ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ በሌላ በኩል አቤቱታውን በመመርመር በጉዳዩ ላይ ምርመራ ለመቀጠል የሚሰጠው ውሳኔ በአቤቱታው ውስጥ የተካተተው ነገር ትክክል እንደሆነ የሚያሳይ ቅድመ ግምገማ ተደርጐ ሊወሰድ አይገባም፡፡

የመርማሪ ሚና

በሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የመርማሪው ሚና ተገቢውን ትንተና በማድረግ የአቤቱታውን አግባብነት ያለው ፍሬ ነገር በመለየት ይህንን ጠቃሚና አግባብነት ባለው ማስረጃ በማረጋገጥ ግኝቱን ሪፖርት ማድረግና እንደአስፈላጊነቱ አግባብነት ያለው አስተያየት/ማሳሰቢያ ማዘጋጀት ነው፡፡ ከላይ እንደተመለከተው መርማሪ የአቤቱታ አቅራቢው ጠበቃ አይደለም፡፡ እንደዚሁም መርማሪ የተጠሪ አስተዳደር አካል አፈቀላጤም አይደለም፡፡ መርማሪ ለማንም አይወግንም፣ በስሜትም አይነዳም፡፡ ምርመራ በአጭሩ አድልኦ የሌለበት በአግባቡ የተቀናባበረ የፍሬ ነገርና የማስረጃ ትንተና ነው፡፡ አግባብነት ያለው ፍሬ ነገርና ማስረጃ በምርመራ ውጤት ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ይረዳሉ ወይም ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው፡፡

የምርመራ መስፈርቶች

ሁሉም በሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የሚደረግ ምርመራ ያለአድልኦ፣ በሚዛናዊ ዳኝነትና ግልጽ በሆነ ሁኔታ ሊከናወን ይገባል፡፡ ማንም በአቤቱታው ላይ የጥቅም ግጭት ያለበት መርማሪ በዚህ አቤቱታ ምርመራ ላይ ሊሳተፍ አይገባም፡፡ እንደዚሁም መርማሪዎች በሥራቸው አጋጣሚ ያወቁትን ማናኛውም ምስጢር በማናቸውም ወቅት የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ ነገር ግን ስለሚጠበቁ ምስጢሮች ዝርዝር መመሪያ ሊኖር/ሊዘጋጅ ይገባል፡፡ በሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የተቀመጠውን የአሠራር ሂደት በመጠቀም መርማሪው ምርመራውን በተቋሙ በሚጠብቀው ጥራትና ደረጃ ማከናወን ይገባዋል፡፡

በምርመራ ላይ የመወሰን ሥልጣን

በምርመራ የመወሰን ሥልጣን መኖር አለመኖር በምርመራ ውጤታማነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው፡፡ የመወሰን ሥልጣን ያለው መርማሪ እንደአስፈላጊነቱ ምስክርን ጠርቶ ቃል መቀበል፣ ከመንግሥታዊ አካላት ጋር ስለፓሊሲያቸው፣ መመሪያዎቻቸውና አሠራራቸው መረጃ ማግኘትና ሰነዶቻቸውን መመርመር ይችላል፡፡ በተጨማሪ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ሥልጣንና ተግባሩን ሥራ ላይ ለማዋል እንዲችል ማንኛውም ሰው አስፈላጊው ድጋፍ መስጠት ይኖርበታል (አንቀጽ 38)፡፡ ለምርመራ ዓላማ ተቋሙ አስፈላጊ ማጣሪያዎችን ለማካሔድ በቂ በሆነ ጊዜ ውስጥ ጠቃሚ ማስረጃ የያዘ ማንኛውም ሰው ይህንን ማስረጃ እንዲያቀርብ ለማድረግ ይችላል፡፡

ምርመራን ማቀድ

ዕቅድ ለማንኛውም ጥሩ ምርመራ አካሔድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ መርማሪው ለምርመራ ሊጠቀምበት የሚችለው የመጀመሪያ መሣሪያ ዕቅድ ነው፡፡ በማናቸውም ጊዜ መርማሪው የማስረጃ ግምገማና ትንተና ከመጀመሩ በፊት የምርመራ ዕቅድ ሊያዘጋጅ ይገባል፡፡ የምርመራ ቅርጽና አወቃቀር ለመወሰን ዕቅድ ከፍተኛ ዕገዛ ያደርጋል፡፡ በዕቅድ ላይ ተመሥርቶ ምርመራ ማካሔድ መርማሪው በአቤቱታው ቁልፍ ጭብጦች ላይ ትኩረት እንዲያደርግና ሊዳሰሱ የሚችሉ ማናቸውንም ችግሮች ለመቃኘት ያስችላል፡፡ በሌላ አነጋገር ዕቅድ የተፈለገውን ማስረጃ በአግባቡ ለመለየት፣ የማስረጃውን ምንጭ ለማወቅና ለጉዳዩ ያለው ጠቀሜታ ላይ የመጀመሪያ ግምገማ ለመሥራት አቅጣጫ የሚያሳይ ስለሆነ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ስለዚህ የምርመራ ዕቅድ በሚዘጋጅበት ጊዜ አራት አንኳር ጥያቄዎችን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህም

1. ምን ተከሰተ? (ምን ሆነ?)

2. በሆነው ነገር የአስተዳደር በደል ወይም የአገልግሎት ጉድለት ነበር?

3. የአስተዳደር በደል ወይም የተሰጠው አገልግሎት ጉድለት በአቤቱታ አቅራቢው ላይ ያደረሰው ጉዳት ምንድነው?

4. በአቤቱታ አቅራቢው ላይ የደረሰበትን በደል ለማረምና ለማስተካከል እንዲሁም ተመሣሣይ ችግር በሌሎች ሰዎች ላይ እንደገና እንዳይከሰት ለመከላከል ምን ዓይነት መፍትሔ ሊወሰድ ወይም ማሳሰቢያ ሊዘጋጅ ይችላል? የሚሉ ናቸው፡፡

ዕቅድ የሚሰራው ከእያንዳንዱ አቤቱታ አንጻር እንደመሆኑ የማናቸው ምርመራ ዕቅድ መነሻ በግልጽ የተብራራ አቤቱታ ነው፡፡ በርግጥ በምርመራ ሥራ ለአቤቱታ አቅራቢው ችግር ምላሽ ለመስጠት ሥራው የሚጀመረው ተጠሪው የአስተዳደር አካል ለአቤቱታው አስፈላጊ የሆኑ ማስረጃዎችን እንዲሰጥ በመጠየቅ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከቀረበው አቤቱታ አንጻር ለተጠሪው የአስተዳደር አካል ሦስት ጥያቄዎች ይቀርባሉ፡፡ እነርሱም

ሀ. ምን ተከሰተ? (ምንድነው የሆነው ነገር?)

ለ. ምን ሊሆን ይገባ ነበር?

ሐ. በሆነው /በተከሰተው/ እና መሆን ከነበረበት ነገር መካከል ላለው

ልዩነት ማብራሪያ መስጠት ናቸው፡፡

ለተመርማሪው የአስተዳደር አካል አቤቱታውን በሚመለከት የሚቀርበለት ጥያቄ ግልጽና የተወሰነ ከሆነ የሚገኘው ምላሽ በተጠየቀው ነገር ላይ ያተኮረ እንዲሆን ይረዳል፡፡ በርግጥ አቤቱታውን በቅድሚያ ለመረዳት መነሻ ሀሳብና መረጃ ማግኘት የሚቻለው ከራሱ ከአቤቱታ አቅራቢው ወይም ከተጠሪ የአስተዳደር አካል ነው፡፡ እንግዲህ አቤት የተባለበት ድርጊት መንስዔ፣

ሀ. ተመርማሪው አካል ለወሰደው ርምጃ መሠረት ወይም መነሻ የሆነ ነገር/ሕግ፣ ፖሊሲ ወዘተ/

ለ. በአቤቱታ አቅራቢውና በተመርማሪው መካከል ያለው ግንኙነት

/ለምሣሌ በሽተኛ፣ ተከራይ፣ ሠራተኛ ወዘተ/

ሐ. የሌሎች ሰዎች ተሳትፎ ዝርዝር ሁኔታ/ወኪል፣ ቤተሰብ /ወላጅ/ወዘተ

እነዚህን ነገሮች ሁሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት የምርመራ ዕቅድ ሲዘጋጅ ከተጠሪው አካል የሚገኘው መልስ ግልጽና ሙሉ መሆኑን ለመገምገም ይረዳል፡፡ ምክንያቱም ዕቅድን መሠረት ባደረገ ምርመራ የአቤቱታው አንኳር ነጥብ የአስተዳደር አካሉ ከሚጠቀመው መመሪያ ወይም ሥነ ሥርዓት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ከሚሰጠው ምላሽ ጋር የሚፈለገው መመሪያ ወይም ሥነ ሥርዓት ተያይዞ መቅረብ አለበት፡፡ እንዲሁም አቤቱታው ስለ አሠራሩ ከሆነ ተጠሪው የሚጠቀመው አሠራር ተቀርጾ ይያያዛል፡፡ በተጨማሪ አቤቱታው ከተጠራው ሠራተኛ ተግባር ጋር የተያያዘ ከሆነ ደግሞ የሠራተኛው የስልጠና ሁኔታ እና የሥነ ምግባር ደንብ ማግኘት አስፈላጊ ነው፡፡ ምርመራ በማካሔድ ስለ አንድ ነገር ትክክለኛ ገጽታ ለማወቅ ምርመራው ከነገሩ መነሻ ሊጀምር ይገባል፡፡ በመሆኑም አቤቱታ አቅራቢው ለተጠሪ ቅሬታ ባቀረበ ጊዜ ተጠሪው ለቅሬታው የሰጠውን ምላሽ አቤቱታ አቅራቢው ለመርማሪው መስጠት አለበት፡፡

የምርመራ ዕቅድ የሕጉን የተፈጻሚነት ወሰንና ጉዳዩ በተቋሙ የመመርመር ሥልጣን ክልል የሚወድቅ መሆኑን ጭምር በጥልቀት የያዘ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ መርማሪው የሚከተለውን ማወቅና በዛው መሠረት ምርመራውን ማካሔድ አለበት፡፡

ሀ. ማናቸውም የሥልጣን ጥያቄ በተለይ አቤቱታው በተቋሙ የምርመራ ሥልጣን ሥር የማይሸፈን መሆኑን ሊያሳይ የሚችሉ አጋጣሚዎች ካሉ፣

ለ. ከዚህ በፊት በተመሣሣይ ጉዳይ የእንባ ጠባቂ ተቋም የሰጠው ውሳኔ ካለ (precedence)

ሐ. ማናቸውም ከአበታ አቀራቢው ወይም ከተመረማሪው አካል ጋር

የተያያዘ ጉዳይ

መ. ነገሩ በተከሰተ ጊዜ በሥራ ላይ የነበረ ሕግ

ሠ. ማስረጃውን ለማነፃፀር የሚያስችሉ ሌሎች ነገሮች/የሥነ ምግባር ደንብ፣ የአሠራር መመሪያ፣ ተቀባይነት ያገኙ ልምዶች፣ ወዘተ/

ረ. ማናቸውም መረጃ ለመቀበልና ለመተንተን እንዲሁም የመጨረሻ

ሪፖርት ለማዘጋጀት የታሰበ የጊዜ ወሰን

ለተቋሙ የቀረበው አቤቱታ በተጨባጭ በሚታይ ምክንያት ላይ ተመሥርቶ በቀረበ ጊዜ ተቋሙ አቤቱታውን ወዲያውኑ ይመረምራል፡፡ ለምሳሌ፡- አቤቱታው የቀረበው ከቅሬታ አቅራቢው የጤንነት ጉዳይ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል፡፡ ምርመራ አቅዶ መሥራት የምርመራው መሪ ስለታሰበው የምርመራ ስትራቴጅና አስቀድሞ የጊዜ ሰሌዳ በማዘጋጀት የምርመራውን ውጤታማነት በአግባቡ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ በተለይ በቂ ምክንያት ሲኖር አንድ ጉዳይ ከአንድ የምርመራ ክፍል ወደ ሌላ የምርመራ ክፍል ወይም መርማሪ ለማዛወርም ይረዳል፡፡

ስለ አቤቱታ አቅራቢዎችና ወኪሎቻቸው አመራር

 

በማናቸውም ምርመራ ላይ የአቤቱታ አቅራቢዎችና የነርሱ ወኪሎች ወይም በጉዳዩ ጥቅም ያለበት ሦስተኛ ወገን አያያዝ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ተቋሙ ሁሉም ሠራተኞች የሚከተሉትና የሚያከብሩት ስለተነሳሽነት የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት የሚገልጽ /የያዘ/ ዝርዝር መመሪያ ሊኖረው ይገባል፡፡ ስለዚህ በምርመራ ወቅት መርማሪው ለሚከተሉት ነገሮች ኃላፊነት አለበት፡፡ እነሱም፣

አቤቱታ አቅራቢዎች የሚጠበቁት ነገር በእውነት ላይ የተመሠረተ መሆን አለመሆኑን በመረዳት ወደ ተፈለገው ግብ ለመድረስ መሞከር፡፡ በዚህን ጊዜ መርማሪው ጥያቄያቸው መስተናገድ የሚቻል ነው ወይስ መሠረት የሌለው ነው የሚለውን ለይቶ ማወቅ አለበት ፡፡

ሚስጥር ጠባቂነትን ማረጋገጥና ስለምርመራው ሚስጥር የመጠበቅ ኃላፊነት ማብራራት፤

ስለምርመራው አካሄድ ሂደት ወቅታዊ መረጃ መስጠት፤

እንደአሰፈላጊነቱ ምርመራው ስኬታማ እንዲሆን አቤቱታ አቅራቢዎች ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ፣ (መርማሪው በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ አቤቱታ አቅራቢዎች በመለየት የሚያስፈልጋቸውን እገዛ ማድረግ /ሕፃናት፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች የመሣሰሉት ዕርዳታ ሊደረግባቸው ይገባል፡፡/)

ስለተጠሪ አያያዝ

ከላይ ያሉት ነጥቦች ለተጠሪ አስተዳደር አካል አያያዝም የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ አቤቱታ አቅራቢው እንደሚደረግለት ሁሉ ተጠሪውም በአግባቡ ሊያዝ ይገባል፡፡ ስለዚህ መርማሪው ሁልጊዜ ሚዛናዊና የማያወላውል መሆን ይጠበቅበታል፡፡

የማይፈለጉ ባሕርያት አያያዝ

የአቤቱታ አቅራቢውም ሆነ የተጠሪ እንዲሁም የሌላ ማናቸውም ሰው ተግባር የምርመራ ሥራ እንዲያጨናግፍ ዕድል ሊሰጥ አይገባም፡፡ እንደአስፈላጊነቱ ለሁለቱም ወገን የተቋሙ የአሠራር መመሪያና ከባለጉዳዮችም ሆነ ከማናቸውም ሰው የማይፈለጉ ባሕሪያት ዝርዝር የያዘ ሰነድ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ በተቻለ ፍጥነት አላስፈላጊ ባሕሪያትና አካሔዶች ከመነሻው እንዲወገዱ መርማሪው አስፈላጊውን ርምጃ ይወስዳል፡፡ ያልተፈለገና ሥራውን የሚያሰናክል ፀባይ የሚያሳይ ወገን ጥፋተኛ ስለሚሆንበትና ስለቅጣቱ እንዲያቅ የሚደረግ ሲሆን በችግሩ ምክንያት የምርመራ ሥራ ራሱ ሊቆም እንደሚችል ሊነገራቸው የገባል፡፡

የማስረጃ አሰባሰብና አያያዝ

ማስረጃ መሰብሰብ

ከላይ ለመመልከት እንደተሞከረው የመርማሪ የመጀመሪያ ሥራ የአቤቱታውን ፍሬ ነገር መመስረት ነው፡፡ የአቤቱታው ፍሬ ነገር አግባብነት የሚለካው የቀረበውን ማስረጃ በቅርበትና በጥልቀት በመመርመር በሁለቱ መካከል ግንኙነት መኖሩን ለማረጋገጥ ሲቻል ነው ፡፡ በዋናነት ለምርመራ ጠቃሚ የሚሆን ማስረጃ የሚገኘው ከቃል ምስክር ፣ ከሰነድ ማስረጃ፣ ከባለሙያ ምክርና ማስረጃ እንዲሁም በአካባቢው ላይ ከሚገኙ ማስረጃዎች ነው ፡፡

መርማሪው ለያዘው ጉዳይ ጠቃሚ ይሆናል ብሎ የወሰነው ማስረጃ እንዲቀርብ ሲጠይቅ የተጠየቀው ማስረጃ የሚገኝበት ትክክለኛ ምንጭ ወይም ቦታ በትክክል በግልጽ ማሳየት መቻል አለበት፡፡ በተጨማሪ በማስረጃ አቀራረብ ላይ የሚቀርበውን ማስረጃ ዝርዝር፣ ዓይነትና መቅረብ ያለበት ጊዜ መግለጽ አስፈላጊ ነው፡፡ ከተጠሪ የአስተዳደር አካል በኩል እንዲቀርብ የተጠየቀው ማስረጃ ከአቤቱታ አቅራቢው ማመልከቻ ጋር ተያይዞ የቀረበውን ማስረጃ መነሻ በማድረግ የሆነ እንደሆነ ተጠሪው የተጠየቀውን ማስረጃ ምንነት በግልጽ ተረድቶ ቶሎ ምላሽ እንዲሰጥበት ይኸው ሊገለጽለት ይገባል፡፡

የሚቀርበው ማስረጃ ለተያዘው ጉዳይ መፍትሔ ለመስጠት ጠቀሜታ ያለው ካልሆነ ማስረጃው ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ይህ እንዳይሆን የሚጠየቀው ማስረጃ አቤቱታ አቅራቢና ተጠሪ ስላልተግባቡበት አከራካሪ ነጥብ(ጭብጥ) አግባብነት ያለው ስለመሆኑ ለማረጋገጥ መጣር አስፈላጊ ነው፡፡ ማለትም ስለሚጠይቀው ማስረጃ ጥራት መርማሪው ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል፡፡ በመሆኑም እንዲቀርብ የሚጠየቀው ማስረጃ ተጨባጭነት ያለው እንደሆነና ከስሜታዊነት ነፃ በሆነ መልኩ አግባብነተ ያለው መሆኑ ይታያል፡፡ ለጉዳዩ ጠቃሚ መሆኑ ያልታወቀ በርካታ ማስረጃ ማግበሰበስ የተጠሪ አስተዳደር አካል ጊዜና ሀብት እንዲባክን ከማድረጉ በተጨማሪ አላስፈላጊ የምርመራ መዘግየት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ የአስተዳደር ጥፋትና የአገልግሎት ጉድለት የሚመለከት አቤቱታ ለመወሰን የሚቀርብ ማስረጃ ሪፖርቱ ለፓርላማ የሚቀርብ እንደመሆኑ መጠን ከአቤቱታው ፍሬ ነገር ጋር የተያያዘ፣ አግባብነት ያለው እና እምነት የሚጣልበት መሆኑ አስቀድሞ መረጋገጥ አለበት ፡፡

የማስረጃ ጥራት መገምገም

የሚቀርበው /የተጠየቀው/ ማስረጃ ምርመራውን ከዳር ለማድረስ የሚያስችል ተፈላጊ ጥራት ያለው መሆን በመጨረሻ ምርመራውን በተፈለገው ሁኔታ ለመደምደምም ሆነ አስተያየቱን ለማብራራት አስተዋጽኦ አለው ፡፡ የማስረጃ ጥራት በሦስት ዋና ዋና ነገሮች የሚገለጽ ሲሆን እነርሱም ቀጥተኛነት ፣ አግባብነት እና አሳማኝ መሆን ናቸው ፡፡

1. Material evidence /ቀጥተኛ ማስረጃ/፡- ከአቤቱታው ወይም ለአቤቱታው ከተሰጠው መልስ ጋር ለተያያዘ አንድ ወይም ብዙ ጭብጦች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ማስረጃ ማለት ነው፡፡

2. የማስረጃ አግባብነት፡- በአቤቱታው የተመለከተና በመልሱ ላይ የተካደውን የፍሬ ነገር ጭብጥ የሚያስረዳ ወይም የሚያፈርስ ማስረጃ አግባብነት ያለው ማስረጃ ነው፡፡ ማስረጃው ለጭብጡ አግባብነት ከሌለው ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙት መኖሩ ብቻውን እምብዛም የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ ስለዚህ የማስረጃውን አግባብነት ለመወሰን የሚከተለው ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል ይኸውም ይህ ማስረጃ ምን እንዲያስረዳ ነው የሚጠበቀው?

3. Reliable evidence /አሳማኝ ማስረጃ/፡- በጉዳዩ ላይ ውሳኔ የሚሰጠው በቀረበው ማስረጃ ላይ በመመርኮዝ የሆነ እንደሆነ ማስረጃው አሳማኝ ነው፡፡ የቀረበው ማስረጃ ፍሬ ነገሩን የማያረጋግጥ ወይም የምስክርነት ቃሉ እውነተኛነቱ ጥርጣሬ ወይም ስጋት የሚያሳድር ከሆነ ማስረጃው አሳማኝ ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን ማስረጃው አሳማኝ ባልሆነ ጊዜም በአጠቃላይ ማስረጃውን ርግፍ አድርጐ ከመተው ይልቅ አሳማኝ የሆነ ማስረጃ ለማግኘት አቅጣጫ ሊያሳየን ስለሚችል በተወሰነ ደረጃ መጠቀሙ ይመረጣል፡፡

የሰነድ ማስረጃ

የሰነድ ማስረጃ ለመርማሪ አካል ዋናና አሳማኝ የመረጃ ምንጭ ነው፡፡ በመሆኑም መርማሪው በሰነድ ማስረጃ ላይ ትንተና በሚያካሂደበት ወቅት የሚከተሉትን ነጥቦች ከግምት ውስጥ ማስገባት አለበት ፡፡

1. ማስረጃው /ሰነዱ/ ሙሉ ነውን ?

2. ማስረጃው /ሰነዱ/ ክርክር ለተነሣበት ድርጊት፤ ጊዜና ቦታ አግባብነት አለው ?

3. ማስረጃው/ሰነዱ/በቀላሉ ለመረዳት የሚቻል ነው ? (በጣም ቴክኒካል መሆን፣ ጀርገን/የመስኩ ባለሙያዎች ብቻ የሚረዱት/ ወዘተ )

ነገር ግን ከላይ ከተመለከቱት ነጥቦች አኳያ ሰነዱ ጥርጣሬ ያለበት ከሆነ ስለትክክለኛነቱ የማስረዳት ኃላፊነት የማስረጃ አቅራቢው ነው፡፡ በተጨማሪ መርማሪው የተቀበላቸውን ሰነዶች በሙሉ ማገናዘብና ማረጋገጥ፣ መመዝገብና በደህና ቦታ ማስቀመጥ ይጠበቅበታል፡፡ በርግጥ በጽሑፍ ከሰፈረው ይልቅ በኤለክትሮኒክስ ቅጅ ማስቀጥም ሆነ መጠቀም ይቀላል፡፡

የምስክር ቃል አቀባበል

የሰነድ ማስረጃ በቂ ባልሆነ ጊዜ ሁሉ የማስረጃውን መለያና ደረጃ መስፈርት በማውጣት መርማሪው ቃለ መጠይቅ ለማድረግ/በስልክ ፣ ፊት ለፊት/ ወይም የምስክርነት ቃል ለመቀበል ይችላል፡፡ ጠቃሚና አሳማኝ የሰው ምስክርነት ማግኘት በጣም አስቸጋሪ የሆነ የማስረጃ ዓይነት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የምስክሮች የማስታወስ ሁኔታ ያልተሟላ ወይም ጉድለት ያለበት ከመሆኑም በተጨማሪ ለተመሳሳይ ቃለ መጠይቅ የተለያየ ምላሽ ሊሰጥ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ይህ ውሰብሰብነት የአንዳንድ ሰዎች/ሕፃናት ፣ በሽተኛ/ ለአደጋ ተጋላጭ ከመሆን ጋር ተዳምሮ የምስክርነት ቃል ተዓማኒነትን አስቻጋሪ ያደርገዋል፡፡

የምስክርነት ቃል ጥራት በአብዛኛው በመርማሪው የቃለ መጠይቅ አቀራረብ ችሎታ ወይም ጥበብ ይለካል፡፡ ቃለመጠይቅን ስኬታማ ለማድረግ ወሳኝ ሚና የሚጫወተው መርማሪው ስለጉዳዩ የሚያደርገው ዝግጅት ሲሆን በተለይ የጥያቄውን መሠረተ ሃሣብ በትክክል መረዳትና በአግባቡ ማብራራት እንዲሁም ውጤታማ የሆነ የመግባባት ክህሎት፣ አጠቃላይ የመረዳት ችሎታና በሀቀኝነት ላይ የተመሠረተ ተግባር ማከናወን አስፈላጊ ነው፡፡ እንደዚሁም ስለሚነሣው ጭብጥና ለቃለመጠይቁ ጥቅም ላይ ስለሚውሉ መሣሪያዎችና ሎጀስትክ አስቀድሞ ተጠያቂው እንዲያውቀው ማድረግ ይመከራል፡፡ ይህንን ማድረግ ቃለ መጠይቁን ሊያስናክሉ ወይም ሊያጨናግፉ የሚችሉ ነገሮችን ከማስወገዱ በተጨማሪ ተጠያቂው ስለሚጠይቅበት ጭብጥ አስቀድሞ አውቆ ዝግጅት እንዲያደርግና ጉዳዩን በቀና እንዲመለከተው ይረዳል፡፡ ፍሬ ነገሩንም ግልጽ ለማድረግ እንደዚሁ፡፡ በእርግጥ ቃለ መጠይቅ ማድረግ ፍሬ ነገሩን ትክክል ነው ብሎ ማጽደቅ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ለጥያቄው የተሰጠው መልስ አጠራጣሪ በሆነ ጊዜ መርማሪው በዚህ ዙሪያ መመራመርንና ተጨማሪ ጥያቄ ለተጠያቂው ማቅረብ አይከለክልም፡፡

ቃለመጠይቅ ለማድረግ ቃለመጠይቁ የሚደረግበት ጊዜ/ሰዓት/ እና ቦታ ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ቃለ መጠይቁ ለተጠያቂው ለብቻው የሚደረግ ሆኖ መቆራረጥ የለበትም፡፡ በመሆኑም የቃለመጠይቁ ምላሽ ሪኮርድ ስለሚደረግበት ዘዴ በቅድሚያ ዝግጅት ሊደረግ ይገባል፡፡ በርግጥ የምላሹ መቀበያ አማራጮች በእጅ ጽሑፍ ማስታወሻ መያዝና ቴኘ ተጠቅሞ መቅዳት ናቸው ፡፡ የጠያቂው ጥሩ አድማጭ፤ ጥያቄ የማቅረብ ክህሎትና ልምድ ያለው መሆን ቃለመጠይቅ ለማካሔድ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ለተጠያቂው የሚቀርቡ ጥያቄዎች አስቀድሞ መዘጋጀት አግባብነት ያላቸው ጭብጦች በጥያቄው ውስጥ በሙሉ መካተታቸውን ለማረጋገጥ እንደቸክ ሊስት ያገለግላል፡፡ በእርግጥ መርማሪው ለተጠያቂው አስቀድሞ ከሰጠው ጥያቄ ሌላ ያልታሰበ ተጨማሪ ማስረጃ ሊያሰገኝ የሚችል ሌላ አዲስ ጥያቄ ከማቅረብ አይከለከልም፡፡ ፊት ለፊት የሚደረግ ቃለመጠይቅ በስልክ ወይም በጽሑፍ ከሚቀርብ ጥያቄ ይልቅ በቀጥታ ተፈላጊውን ማስረጃ ከተጠያቂው ለማግኘት የሚያስችል የተሻለ ዘዴ ነው፡፡ ነገር ግን የቃል አቀባበል ዘዴ እንደሚመረመረው ጉዳይ ውስብስብነትና በሚሻው ጥንቃቄ ደረጃ ሊለያይ ይችላል፡፡ ስለዚህ ቃለ መጠይቅ የሚደረገው ቋንቋውን በደንብ ከማይችል ሰው ወይም የመናገር ችግር ካለባቸው ሰዎች ጋር ከሆነ አስተርጓሚ የሚያስፈልግ መሆን አለመሆኑ አስቀድሞ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

ቃለመጠይቁ ለምስክሮች ለብቻ የሚደረግ ቢሆንም በቦታው ሌላ ሦስተኛ ወገን እንዲኖር ፍላጐት ካላቸው የሚፈልጉትን ሰው ይዘው እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል፡፡ ይህም ለምስክሩ ምቾት እንደሚፈጥርና ቃለ መጠይቁን ቀላል እንደሚያደርግ ይገመታል፡፡ ነገር ግን የሚፈቀድላቸው ሦስተኛ ወገን ሰዎች ታዛቢ ብቻ ስለሚሆኑ የምርመራውን ሚስጥር መጠበቅና ማክበር እንዳለባቸው መርማሪው ማረጋገጫ መውሰድ አለበት ፡፡

የባለሙያ ማስረጃና ምክር አጠቃቀም

ከጉዳዩ ውስብስብነት አኳያ ምርመራው የአዋቂ ባለሙያ እገዛ የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ የምርመራው ጭብጥ የሕክምና ምርመራ ማድረግ የሚጠይቅ ከሆነ የሀኪም እገዛ እንጠይቃለን፡፡ በዚህ ረገድ ሁለት ዓይነት አዋቂዎች አሉ፡፡

አንደኛው፣ ምርመራው ስለሚዳብርበት ሁኔታ አጠቃላይ የአዋቂ ምክር መቀበል ነው፡፡ በዚህ ረገድ አዋቂው በቀጥታ ትንተናና ውሳኔ በመስጠት ላይ ስለማይሳተፍ የሚሰጠው የምክር አገልግሎት በሰነድ ላይ የሚሰፍር ሳይሆን የመርማሪውን ሥራ መከታተልና መቆጣጠር ይሆናል፡

ሁለተኛው፣ አዋቂው በአንድ በተወሰነ ማስረጃ ላይ አስተያየት ወይም/ እና ትንተና ወይም ለአቤቱታው አግባብነት ያለው ቴክኒካል መረጃ መስጠት ነው፡፡ የተገኘው መረጃ በአግባቡ ተመዝግቦ ይቀመጣል፡፡ በርግጥ መርማሪው በአዋቂው በተሰጠው ምክር ላይገዛ ይችላል፣ ማለትም ምክሩን ሊቃወምና የተሰጠውን አስተያየት ውድቅ ሊያደርገው ይችላል፡፡ በዚህን ጊዜ የአዋቂውን የሙያ ብቃትና ከበረታ ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ በምክሩና መርማሪው በደረሰበት ድምዳሜ መካከል ያለውን ልዩነት ለባለሙያው ሊብራራለት ይገባል፡፡

 

ጉብኝት

አንዳንድ ጊዜ ስለአቤቱታው ጭብጥ በትክክል ለመረዳት ጉዳዩ በተከሰተበት ቦታ በመገኘት ማጣራት ያስፈልጋል፡፡ ጉብኝት በሰነድ የሰፈረውን ለማጥናከር እንዲሁም የሁኔታውን ትክክለኛ ጉዳዩ ለማግኘትና ብዥታን ለማስወገድ ይረዳል፡፡ መርማሪው በድርጊቱ ቦታ በመገኘት ነገሩን ሲያጣራ ከአቤቱታ አቅራቢው ወይም ከተማርማሪው የአስተዳደር አካል ወይም ከሁለቱም ጋር ሊሆን ይችል ፡፡ በዚህን ጊዜ መርማሪው በጉብኝቱ ወቅት ትኩረት የተሰጠበትን ጭብጥና የተደረገውን ውይይት በትክክል መመዝገብ ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪም ለግንዛቤ እንዲረዳው ቦታውን ፎቶግራፍ ማንሳት ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ፎቶግራፉ ወደፊት ማስረጃው በተጠየቀ ወይም በተፈለገ ጊዜ ለመጠቀም ያገለግላል፡፡

ማስረጃ መተንተን

መርማሪው ማስረጃውን በዝርዝር መዝግቦ በእጁ ካደረገ በኋላ የተጠየቀውን የሰነድ ማስረጃ በተፈለገው መጠን (ሁኔታ)በሙሉ መቀበሉን ማጋገጥ አለት፡፡ የቀረ ማስረጃ ካለም ከአቤቱታ አቅራቢው ወይም ከተማርማሪ የአስተዳደር አካል ለማግኘት ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በማስረጃ ትንተና የመጀመሪያ ደረጃ (first phase) ሥራ አቤቱታ አቅራቢውና ተመርማሪው የአስተዳደር አካል የተስማሙበትን ነጥብ መለየት ነው፡፡ የተለየው ነጥብ ለተከራካሪዎች ወዲያው ሊገለጽባቸው ይገባል፡፡ ተከራካሪዎች ይህንን ማወቅ የተያዘውን ጉዳይ መልክ ለማስያዝም ሆነ ያልተስማሙበትን ነጥብ ለመለየትና ለመወሰን ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ የተስማሙበት ነጥብ ቀላል በሆነ ጉዳይ ላይ ከሆነ በማናቸውም ሁኔታ ለሁለቱም ወገን የሚገለጽ ሲሆን ከባድና ውስብስብ ነጥቦች በተመለከተ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸውን ፍሬ ነገሮች በዝርዝር ያካተተ መደበኛ ጽሑፍ በማዘጋጀት ለሁለቱም ወገን እንዲደረሳቸው ይደረጋል፡፡ አከራካሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ምርመራው ይቀጥላል፡፡

በተጨማሪ የሁለቱን ወገን ጽሑፍ ጐን ለጐን ማስቀመጥ አቤቱታውንና መልሱ ለማስተያየት ይጠቅማል፡፡ በዚህን ጊዜ የስምምነትና የክርክር ነጥቦችን (ጭብጦችን)በቀላሉ መለየት ይቻላል፡፡

አከራካሪ ጉዳዮች /የክርክር ነጥቦች/

ከላይ እንደተመለከተው ምርመራው በአቤቱታው ውስጥ ግራ ቀኙ የተስማሙበትና የተካካዱትን ነጥቦች (ጭብጦችን) በመለየት ስምምነት ላይ ያልተደረሰባቸው ጭብጦች የሚመለከቱ ማስረጃዎች ላይ ክለሳ ይደረጋል፡፡ ስምምነት ላይ ያልተደረሰባቸውን ጭብጦች በተመለከተ መርማሪው ሦስት አማራጮች አሉት፡፡ እነሱም

1. አበቱታ አቅራቢው በጉዳዩ ላይ ባይስማማም ማስረጃው የተመርማሪ አስተዳደር አካል ሀሳብ የሚደገፍ ከሆነ ምርመራ መቀጠል አስፈላጊ አይደለም ብሎ መወሰን ወይም

2. አዲስ ወይም የተለየ ማስረጃ በማግኘት ጉዳዩን የበለጠ ለማጣራት ተጨማሪ መረጃ ለመቀበል የአዋቂ ማስረጃ ወይም የቦታ ጉብኝት ወይም ቃለ መጠይቅ ለማድረግ መዘጋጀት ወይም

3. የተሰበሰበው ማስረጃ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል አይደለም ብሎ መወሰን ናቸው፡፡

በርግጥ በቀጥታ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል ማስረጃ ካልተገኘ መርማሪው ሁለቱ ወገን የተባባሉትን ወይም የተለዋወጡትን ሀሳብ (ነገር) መሠረት በማድረግ አካባቢያዊ ማስረጃዎች አመዛዝኖ በመተንተን ድምዳሜ ላይ መድረስም ይቻላል፡፡

ከላይ በተራ ቁጥር 2 በተመለከተው አኳኋን ጉዳዩን የበለጠ ለማጣራት የሚደረግ ተጨማሪ ማስረጃ ዋና ዓላማ፡-

1. በተሰበሰበው ማስረጃ ባልተሸፈኑ ጭብጦች ዙሪያ ማስረጃ ለማግኘት፣

2. የተሰበሰበው ማስረጃ አጠራጣሪ ከሆነ ለማረጋገጥ ፣

3. ከተሰበሰበው ማስረጃ ጋር በመነጻጸር ትርጉም ለመስጠት ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አስቸጋሪ ምርመራ ባጋጠመው ጊዜ መርማሪው በጉዳዩ ላይ ምክርና አስተያየት በማግኘት ምርመራውን ለማዳበር የተቋሙ የበላይ ኃላፊዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው ሠራተኞች የሚገኙበት ከዝ ኮንፈረንስ (case conference) በማዘጋጀት ግብአት መሰብሰብ ይችላል፡፡ የዚህ ዓይነት ኮንፈረንስ በተለይ የተቋሙን ሥልጣን በተመለከተ አወዛጋቢ በሆነ ጉዳይ ላይ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ይረዳል፡፡ መርማሪው የተደረሰውን ድምዳሜ ማስታወሻ በመያዝ ከዚህ አኳያ ከሁለቱም ወገን ጋር ስለጉዳዩ አጠቃላይ ሁኔታ ውይይት ሊያደርግ ይችላል፡፡

ምርመራ ማጠናቀቅና ሪፖርት ማዘጋጀት

መርማሪው አንደኛውን የትንተና ሥራ ካጠናቀቀ በኋላ እንደገና ወደ “አቤቱታ መገምገም” ንዑስ ርዕስ ሥር ከ”ሀ”-“ሸ” የተዘረዘሩት ቅድመተከተል ተመልሶ ለአቤቱታ አቅራቢው በተጠሪ በኩል ሊደረግለት ይገባ የነበረውን ነገር ለይቶ ማውጣት (መወሰን) ይጠበቅበታል፡፡ መርማሪው ይህን የሚያከናውነው ለተጠሪ አስተዳደር አካል በሕግ ከተሰጠው ሥልጣንና ተግባራት ዝርዝር ወይም በተለየ መልክ የተዘረዘሩ የተጠሪ አገልግሎቶችና ግዴታዎች በመነሳት ነው፡፡

ሊሆን ይገባ የነበረውን ነገር ለመለየት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ነጥቦች

 

ጊዜ (time)

ሊሆን ይገባ የነበረውን ነገር ለመለየት አቤቱታ እንዲቀርብ የቀሰቀሰው ድርጊት በተከሰተ ጊዜ የተጠሪ አስተዳደር አካል ድርጊት ከግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው፡፡ ድርጊቱ ከተከሰተ በኋላ ምርመራው እስኪጀምር ወራት ወይም አመታት ያለፈ ቢሆን እንኳን በድርጊቱ ወቅት የነበሩ ሰዎች ፣ አሠራሮች፣ ፓሊሲዎችና ሕጐች ለምርመራው አግባብነት አላቸው፡፡ ድርጊቱ ከተከሰተ በኋላ የተደረገው ለውጥ ችግሩ እንደገና እንዳይከሰት ለማስወገድ ለሚዘጋጅ አስተያየት/ማሳሰቢያ አግባብነት ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን ለሁለቱም ወገን ቁምነገሩ ያለው በነበረው ነገር ላይ እንጅ አሁን በሚያውቁት በሚታየው ነገር ላይ አይደለም፡፡

ምክንያታዊነት /Reasonableness/

መርማሪው በሥራው ማጠቃለያ ጥሩ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የተደረገው ምርመራ ከስሜታዊነትና ውግንና በፀዳ መልኩ የተሠራ፣ ጥሩ ጥራት ያለውና ተግባራዊ የሚሆን እንዲሁም በተጨባጭ ፍሬ ነገር ላይ የተመረኮዘና በምክንያት የተገዛ ሊሆን ይገባል፡፡ እነዚህን መስፈርቶች መሠረት በማድረግ በዋናነት የአቤቱታው ምክንያት የሆነው ነገር በተከሰተ ወቅት አቤቱታ አቅራቢውም ሆነ ተጠሪ ማድረግ የነበሩባቸው ነጠቦች ይለያሉ፡፡ ነጥቦች ተለይተው በተጠናቀቀው ምርመራ ማጠቃያ የሚዘጋጀው አስተያየት ወይም ማሳሰቢያ እውነታን መሠረት ያደረገና ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መሆን አለበት ፡፡

ወጥነት/consistency/

ከተወሰኑ ጥቂት ል ከሆኑ አቤቱታዎች በስተቀር የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የሚመረምራቸው አብዛኛዎቹ አቤቱታዎች በፊት በተቋሙ በኩል ምርመራ ከተደረገባቸው አቤቱታዎች ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ አሁን የሚደረገው ምርመራና ውጤት በፊት በተመሳሳይ መልክ የቀረቡ አቤቱታዎች ማስረጃ ትንተና እና አተረጓጐም ጋር ወጥነት እንዲኖራቸው ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ስለልዩነቱ ማብራሪያ ይሠጣል፡፡ ይህ ማለት ግን አቤቱታዎች ራሱን በቻለ በተለየ አኳኋን ሊስተናገዱ አይችሉም ለማለት አይደለም፡፡ ለማለት የተፈላጊው በምርመራ ወቅት መርማሪው ለውጥነት ትኩረት እንዲሰጥ ለማስገንዘብ ነው፡፡

የአሠራር ሂደት

የአሠራር ሂደት በግርድፉ ሲታይ አንድ ላይ የተያያዙ በመጨረሻ ላይ አንድ ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉ ሥራዎች ስብሰብ ነው፡፡ በርካታ አቤቱታዎች ለእንባ ጠባቂ ተቋም የሚቀርቡት ተገልጋዮች በአሠራር ሂደት ውጤት ዕርካታ ባለማግኘታቸው ስለሆነ የመርማሪው ትኩረት የአሠራር ሂደቱ እንዴት ተቀረጸ በሚለው ነጥብ ላይ ሊሆን ይገባል ፡፡ በርግጥ በአፈጻጸም ላይ የሚታዩት ችግሮች ሁሉ የአሰራር ሂደት ጉድለት ውጤት ናቸው ለማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ አብዛኞቹ አሁን ያሉት የአሠራር ሂደቶች በአዲስ መልክ የተቀረጹ፤ በአሠራር መመሪያዎች አማካይነት የሚቆጣጠሩበትና በመለኪያ ክትትል የሚደረግባቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ስለተቀረጸው የአሠራር ሂደት ተጠሪው የአስተዳደር አካል ለመርማሪው ማብራሪያ ይሰጣል፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ በተቀረፀው የአሠራር ሂደትና ነበራዊው የአገልግሎት አሰጣጥ መካከል አለመጣጣም ስለመኖሩ ይፈተሻል፡፡ የአሠራር ሂደት የሚጠይቀው ውጤትና የተሰጠው አገልግሎት አለመጣጣም የተፈጠረው የአሰራር ሂደት ትክክል ሆኖ ሳለ በሰራተኛ ስህተት ወይም በሀብት/ግባአተ/ እጥረት አማካይነት የአፈጻጸም ጉድለት የተከሰተ ከሆነ ይኸው መስተካከል አለበት፡፡ ነገር ግን በአሠራር ሂደትና በአገልግሎት አሰጣጥ መካከል አለመጣጣም ሳይኖር ውጤት ላይ ችግር ካለ የአሠራር ሂደቱ እንዲስተካከል ማሳሰቢያ ወይም አስተያየት ይሰጣል፡፡

ማሳሰቢያ/አስተያየት ማዘጋጀት

በአቤቱታው የተጠየቁት/የቀረቡት/ የቅሬታ ነጥቦች ሁሉ የተደገፉ ከሆነ መርማሪው በቅድሚያ ለሁለት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት አለበት ፡፡ እነዚህም፣

ሀ. በአቤቱታ አቅራቢው ላይ የደረሰውን የአስተዳደር በደል

ለማስተካከል /ለማረም/ ተጠሪው የአስተዳደር አካል ምን ማድረግ

አለበት?

ለ. ተመሣሣይ የአስተዳደር በደል እንደገና እንዳይከሰት ለማስወገድ

ተጠሪው ተመርማሪም ሆነ ሌሎች የአስተዳደር አካላት ምን ማድረግ

አለባቸው? የሚሉ ናቸው፡፡

ስለዚህ የአስተዳደር ጥፋት ጉድለት በማስተካከል በደሉን ለመካስ የሕዝብ ጠባቂ ተቋም የበደል ካሣ መመሪያ ሊኖረው ይገባል፡፡

እንግዲህ የአስተዳደር ጥፋት እንደገና ተመልሶ እንዳይከሰት ማሳሰቢያ ወይም አስተያየት ሲዘጋጅ ወደጉደለት የመራው ምክንያት ላይ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡ በመርማሪው የተደገፈው አቤቱታ መንስኤ ከሚከተሉት ነገሮች በአንድ ወይም በሌላ ጉድለት ምክንያት ይሆናል፡፡

ሀ. የአፈጻጸም ጉድለት፡- ሰብአዊ ስህተት ወይም የሠራተኛው የሥነ

ምግባር ጉድለት

ለ. የሀብት አጠቃቀም ጉድለት፡- ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ነገሮች

ተገቢውን ቅድሚያ አለመስጠት

ሐ. የሥነ ሥርዓት ጉድለት፡- አስተዳደራዊ ችግሮች/በሥነ ሥርዓቱ

መሠረት አለመሥራት

መ. የአሠራር ሂደት ጉድለት፡- የተቀረጸው የአሠራር ሂደት ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አለመሆን

ሠ. የፓሊሲ ጉድለት፡- የአስተዳደር አካል ኃላፊነቱንና ግዴታውን

መረዳትና መቀበል አለመቻል ናቸው፡፡

ከተዘረዘሩት ጉድለቶች መካከል ከ”ሀ”-“ሐ” የተመለከቱትን በሚሰጠው ማሳሰቢያ ወይም አስተያየት መሠረት ተግባራዊ በማድረግ ማስተካከል ይቻላል፡፡ ምክንያቱም በነዚህ ነጥቦች ዙሪያ አስተዳደር አካል የሚያደርገው ማስተካከያ መፈትሔ ሊሆን ይችላል፡፡ የአሰራር ሂደት ጉድለት በሚመለከት በሚሰጥ ማሳሰቢያ መሠረት ተገቢውን የአሠራር ሂደት ቀርጾ ተግባራዊ ማድረግን የሚጠይቅ ሲሆን የፖሊሲ ጉድለት ለማስተካከል በሕጉ ውስጥ የተመለከቱትን የአሰራር መስፈርቶች በማሳሰቢያው ላይ በግልጽ ማሳየት አስፈላጊ ነው፡፡ ማሳሰቢያውን/አስተያየቱን ተግባራዊ ለማድረግ በጊዜ ሰሌዳ ላይ ከአስተዳደር አካል ጋር ውይይት ማድረግ ለአፈጻጸም ይረዳል፡፡

ያለማሳሰቢያ/ያለአስተያየት/ አቤቱታውን መደገፍ

የአስተዳደር አካል አስቀድሞ በአጥጋቢ ሁኔታ ለአቤቱታው መንስኤ የሆነውን ጉድለት በማስተካከል ችግሩ እንደገና እንዳይከሰት ለማስወገድ የሚያስችል ርምጃ መውሰዱ ከተረጋገጠ መርማሪው አቤቱታውን ቢደግፈውም ማሳሰቢያ/አስተያየት ማዘጋጀት አስፈላጊ አይደለም፡፡

አቤቱታውን ሳይደገፍና አስተያየት/ማሳሰቢያ ማዘጋጀት

የተከሰተው ነገር በአቤቱታው የቀረበውን ጥያቄ የማይመለከት ቢሆንም በአጠቃላይ ሲታይ ክስተቱ በደል መኖሩን የሚያሳይ ስጋት የሚያሳድር ከሆነ የሚመለከተው የአስተዳደር አካል ማስተካከያ እንዲያደርግና የመከላከያ ርምጃም እንዲወሰድበት ማሳሰቢያ ወይም አስተያየት ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው፡፡ ለምሳሌ በምርመራ ወቅት የአስተዳደር አካል የቅሬታ አቀባበል ሥርዓት ጉድለት ያለበት መሆኑ የተደረሰበት ከሆነ የማስተከከያም ሆነ የመከላከያ ርምጃ አስመልክቶ ማሳሰቢያ ወይም አስተያየት ይዘጋጃል፡፡

የምርመራ ረቂቅ ሪፖርት ማዘጋጀት

መርማሪው ምርመራውን በማጠናቀቅ በቀረበው ማስረጃ ላይ ትንተና በመሥራት ድምዳሜ ላይ ሲደርስ በጨረሻ የምርመራ ረቂቅ ሪፖርት ያዘጋጃል፡፡ የረቂቅ ሪፖርቱ ዋና ዓላማ የምርመራ ግኝት መሠረት በማድረግ በማብራሪያ የተደገፈ መደምደሚያ ላይ ለመድረስና ይህንን ማህደር በማዘጋጀት ሪኮርድ አድርጐ ማስቀመጥ ነው፡፡ በዚህ ረቂቅ ሪፖርት ውስጥ ስለተከሰተው ነገር መተረክ፣ የተከሰተውን ነገር በሚመለከት የዘመን ቅድመ ተከተል ማስቀመጥና ማናቸውንም በአስተዳደር አካልና አቤቱታ አቅራቢው መካከል የተደረጉ የሀሳብ ልውውጦችን ማተት አስፈላጊ አይደለም፡፡ ሪፓርቱ የተቋሙ ንብረት እንዲሁም ለመርማሪው ማስረጃ ነው፡፡ የሪፖርቱን ይዘት የሚወስነው መርማሪው እራሱ ሲሆን ሁለቱም ወገን ወይም ሌላ ሰው በረቂቅ ሪፖረቱ ላይ አስተያየት ለመስጠት ዕድል ማግኘት ያለባቸው ሲሆን አስተያየቱ የሪፖርቱን ይዘት አይመለከትም፡፡

ረቂቅ ሪፖርቱ ተጠናቅቶ /ከመውጣቱ/ ይፋ ከመደረጉ በፊት የሚከተሉ ማስፈርቶች መሟላታቸውን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው፡፡ እነዚህም

ሀ. ሪፖርቱ ሙሉ ስለመሆኑ፡- ሪፖርቱ ሁሉንም አግባብነት ያላቸው

የአቤቱታ ነጥቦች /ጭብጦች/ እና የምላሽ ነጥቦችን መያዙ

ለ. አግባብነት፡- በአጠቃላይ በሪፖርቱ ውስጥ የተካተቱት ነገሮች እንዴት ድምዳሜ ላይ መድረስ እንደተቻለና በመጨረሻ የተሰጠውን አስተያየት/ማሳሰቢያ/ የሚያብራሩ እና ሪፓርቱን በግልጽ ለመረዳት የሚያግዙ መሆናቸው

ሐ. ቅድመተከተል፡- ሪፓርቱን በቀላሉ ለመረዳት በሚቻል መልኩ

ክስተቶችን በቅድመ ተከተል መዘርዝር

መ. ሚዛናዊነት፡- አድልኦ የሌለበት በፍሬ ነገር ላይ የተመሠረተ የጉዳዩን አጠቃላይ ሁኔታ ለማመዛዘን የሚያስችል

ሠ. ዕይታ፡- ጭብጦችን ከቀረበው አቤቱታ አንጻር በማየት የአስተዳደር አካል ርምጃ ትክክለኛ ገጽ ማስቀመጥ

ረ. ጥንካሬ፡- ሪፖርቱ የመርማሪውን የመጨረሻ ድምዳሜና አስተያየት/ማሳሰቢያ/ ከቀረበው ክርክር አኳያ አሳማኝና ስሜት በሚሰጥ መልኩ ማስቀመጥ

በሪፖርቱ ላይ የሚጠበቅ ምላሽ

የረቂቅ ሪፖርቱ ይዘት ለሁለቱም ወገን አስገራሚና አዲስ ነገር ያካተተ መሆን የለበትም፡፡ ምክንያቱም ምርመራው ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በክርክሩ ቁልፍ ጉዳዮች/ጭብጦች/ እና ማስረጃ ላይ ከሁለቱም ወገን ጋር ግልጽ ውይይት እየተደረገ ምርመራው የሚቀጥልባቸውና የማይቀጥልባቸው የአቤቱታው ነጥቦች በግልጽ የሚታወቁ ስለሆነ ከዚህ ውጭ በሪፖርቱ ውስጥ የሚካተት ነገር ሊኖር አይገባም፡፡

በረቂቅ ሪፖርቱ ላይ ግብረ መልስ መቀበል

የምርመራ ሪፖርቱ ከመጠናቀቁ በፊት በረቂቅ ሪፖርቱ ላይ የሚቀርብ ግብረ መልስ መመልከት አስፈላጊ ነው፡፡ በሪፖርቱ ውስጥ ተጨባጭ ጉድለት ያለበት ቦታ ላይ ማስተካከያ ይደረጋል፡፡ ከሁለቱ ወገን አንዱ ወይም ሁለቱም አሳማኝ የሆን አዲስ ተጨማሪ ማስረጃ በማቅረብ ካስረዱ የተዘጋጀው ድምዳሜና አስተያየትም ይለወጣል፡፡ በረቂቅ ሪፖርቱ ላይ የሚደረገው ለውጥ ጥቃቅን ሳይሆን ውስኝ በመሆኑ የምርመራውን ድምዳሜና አስተያየት /ማሳሰቢያ/ ለመለወጥ የሚያስገድድ ከሆነ የመጨረሻ ሪፖርት ይፋ ከመደረጉ በፊት ከሁለቱም ወገን ጋር በመወያየት እንደ አስፈላጊነቱ ሁለተኛ ረቂቅ ሪፖርት ለግብረ መልስ ማሰራጨት አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም በምርመራ ወቅት ማናቸው ዓይነት ስህተት/ችግር/ ስለመፈጠሩ ሲታወቅ ወዲያውኑ ተፈላጊው መፍትሔ ሊሰጥ ይገባል፡፡ አንዴ የመጨረሻ ሪፖርት ተዘጋጅቶ ለፖርላማ ከቀረበ በኋላ እነዚህን ስህተቶች ማስተካከል አስቸጋሪ ነው፡፡ በምርመራ ወቀት ስህተት ወይም ችግር መፈጠሩ በማናቸውም ሰው ሲደረሰበት ለመደበቅ መሞኮር ወይም ችላ ማለት ተጨማሪ ጉዳት የሚያስከትል እንጂ የምናተርፈው ነገር የለም፡፡

የመጨረሻ ሪፖርት

የመጨረሻ ሪፖርት ለፖርላማ መቅረቡ የምርመራው ማጠቃለያ ስለሆነ ምርመራው መጠናቀቁን ያመለክታል፡፡ ሪፖርቱ ለፖርላማ የቀረበበት ጉዳይ እንደገና በአዲስ መልክ መክፈትና ምርመራ ማካሔድ አይቻልም፡፡ ነገር ግን በማሳሰቢያ /በአስተያየት/ መሠረት ተግባራዊ ስለመሆኑ ክትትል ይደረጋል፡፡

ምርመራ ማጠቃለል

የህዝብ እንባ ጠባቂ ምርመራ ማጠቀለል ማናቸውም የጽሑፍ ሥራ በማጠናቀቅ ሪፖረት አቅረቦ በአጠቃላይ የተዘጋጁትን ሰነዶች በማደራጀት ሪኮርድ ማድረግ /በጥሩ ቦታ ማስቀመጥን/ ያካትታል፡፡ የተጠናቀቀው ሰነድ በመርማሪው ዘንድ ይቀመጣል፡፡ ሰነዱ ማናቸውም በምርመራ ወቅት የተዘገቡና የተጻፉ እያንዳንዱን ሥራዎች ደረጃና የተወሰዱት ርምጃዎች፤ የተደረጉ ውይይቶች የስልክ ጥሪ፣ ቃለ መጠይቅ፣ በምርመራ የተደረሰውን ድምዳሜና አስተያየት ሁሉ ይይዛል፡፡ ሰነዱ እንዳይጉዳና እንዳይለወጥ ያልተፈቀደላቸው ሰዎች እንዳይደርሱና እንዳያዩ ሚስጥራዊነቱን ጠብቆ ሊቆይ በሚችል ቦታ ማስቀጥ ያስፈልጋል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Law as a means of Serving Justice
The Police and Human Rights in Ethiopia

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 18 September 2024