Font size: +
5 minutes reading time (928 words)

በሕገ መንግሥት ማሻሻያ አንቀጽ 39ኝን መቀየር ይቻል ይሆን?

ሕገ መንግሥት ማሻሻል ማለት ምን ማለት ነው

ሕገ መንግሥት ማሻሻል ማለት በአጭር አነጋገር ለሕገ መንግሥት ማስተካከያ የሚደረግበት ሂደት ነው ማለት ይቻላል፡፡ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ሂደት ክለሳ (Revision) አብዮት (Revolution) ማለት አይደለም፡፡ (ቃለአብ ታደሰ) አብዛኛው ጊዜ ማሻሻያ የሕገ መንግሥቱን ቃላት፣ ሃረግ፣ ዓ.ነገር ወይንም አንቀፆችን ሊያጠቃልል ይችላል፡፡ በእነዚህ በሚሻሻሉት ፋንታ በከፊል መጨመር፣ መቀነስ ወይንም ሙሉ በሙሉ መለወጥ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ ለውጦች ከሕገ መንግሥቱ አጠቃላይ አላማ፣ ግብና መንፈስ ጋር በሚጣጣም መልኩ መሆን አለበት፡፡ (ቃለአብ ታደሰ፡ 2011)

የኢፊዲሪ ሕገ መንግሥት የሚሻሻልበት ሥርዓት

የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሃሳብን እንዴት ማመንጨት ይቻላል?

የሕገ መንግሥቱ ክፍሎች እንዲሻሻሉ ሃሳብ የማመንጨት ስልጣን የየትኛው የመንግሥት እርከን ስልጣን እንደሆነ ሕገ መንግሥቱ በግልፅ አያስቀምጠውም፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 104 የሕገ መንግሥት ማሻሻያን ስለማመንጨት በሚል አንቀጽ ስር የተቀመጠው ሃሳብ "የትኛው የመንግሥት እርከን ሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሃሳብን ያመነጫል?" ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ይልቁኑም "የመነጨው የማሻሻያ ሃሳብ በምን አኳኋን ለህዝብ ውይይት እና ለውሳኔ እንደሚቀርብ" የሚደነግግ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከሌሎች የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መረዳት እንደምንችለው ማንኛውም የህግ መፅደቅ ሂደት ለምክር ቤት የሚቀርበው በህዝብ ተመርጦ ስልጣን በያዘ አስፈፃሚ አካል አማካኝነት በመሆኑ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሃሳብ ማመንጨት የሚችለውም ይኸው አስፈፃሚው አካል ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል (Analogy)፡፡

የመነጨው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሃሳብ ለህዝብ ውይይት እንዴት ይቀርባል?

"የመነጨው የማሻሻያ ሃሳብ በምን አኳኋን ነው ለህዝብ ውይይት የሚቀርበው?" የሚለውን በተመለከተ ማንኛውም በአስፈፃሚው አካል የመነጨ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሃሳብ ለህዝብ ውይይት ሊቀርብ አይችልም፡፡ ይልቁኑ በሚመለከታቸው የፌደራል ወይም የክልል ምክር ቤቶች ቀርቦ መፅደቅ ይኖርበታል፡፡

አንድ የመነጨ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሃሳብ በሁለት መንገዶች ወደህዝብ ውይይት እንዲመራ ሊፀድቅ ይችላል፡-

  1. የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌደሬሽን ም/ቤቶች በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ሲደግፉት (ሕገ መንግሥት አንቀጽ 104)
  2. ከፌደሬሽኑ አባል ክልሎች አንድ ሶስተኛው በክልል ም/ቤቶቻቸው ሲያፀድቁት (ከአስሩ ክልሎች ቢያንስ አራቱ ከደገፉት) (ሕገ መንግሥት አንቀጽ 104)

የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሃሳቡ እንዴት ይፀድቃል?

ከላይ የመነጨውን የማሻሻያ ሃሳብ ወደ የሚቀጥለው የውይይት ምዕራፍ እንዲያልፍ የማፅደቅ ስልጣን የፌደራል ህ/ተ/ምክርቤት እና ፌደሬሽን ምክር ቤት ወይም ቢያንሱ በአራቱ የክልል ምክርቤቶች ሊፈፀም እንደሚችል ተገንዝበናል፡፡ አሁን ደግሞ የፀደቀው እና ለውይይት የቀረበው የማሻሻያ ሃሳብ የሕገ መንግሥቱ አካል ሆኖ በማን ሊፀድቅ እንደሚችል እናያለን፡፡

ሕገ መንግሥቱ ሁለት የማሻሻያ ሂደቶችን ይከተላሉ፡፡

  1. የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 (የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከመገንጠልን) ጨምሮ መሰረታዊ መብቶች፣ አንቀጽ 104 እና 105 ላይ የሚደረግ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ፀድቆ ህግ ሆኖ ሊወጣ የሚችለው ሶስት ነገሮች መሟላት ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ (ሕገ መንግሥት አንቀጽ 105)

ሀ/ በሁሉም የክልል ም/ቤቶች በድምፅ ብልጫ ሲፀድቅ

ለ/ የፌደራሉ ህ/ተ/ም/ቤት በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ሲያፀድቀው እና

ሐ/ የፌደሬሽን ም/ቤት በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ሲያፀድቀው ነው፡፡

  1. ከመሰረታዊ መብቶች እና ነፃነቶች ውጪ ያሉ የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች በሚከተለው አኳሃን ይፀድቃሉ፡፡

ሀ/ የፌደራሉ ህ/ተ/ም/ቤት እና የፌደሬሽን ም/ቤት በጋራ ስብሰባ በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ሲያፀድቁት ነው

ለ/ ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት የፌደሬሽኑ አባል ክልሎች በድምፅ ብልጫ በየም/ቤቶቻቸው ሲያፀድቁት ነው፡፡

ስለሆነም የኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት የማሻሻል ሂደት ጥብቅ ሲሆን በተለይ ሰብዓዊ መብቶችን የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን ማሻሻሉ ደግሞ ይበልጥ ጥብቅ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

በሕገ መንግሥት ማሻሻያ እና አንቀጽ 39

የትኛውም ሕገ መንግሥት የሚነሳባቸው መሰረታዊ የሃገረ መንግሥት ግንባታ መሰረታዊ ፍልስፍናዎች ይኖሩታል፡፡ በተመሳሳይ  የኢፊዲሪ ሕገ መንግሥት ሃገረመንግሥት የመገንባት እሳቤዎች መሰረት የብሔር ብሔረሰቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት መሆኑ በመግቢያ ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ እንደ ሕገ መንግሥቱ መሰረታዊ መነሻ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር የተመሰረተችው በብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ነፃ ፈቃድ ላይ ነው፡፡ ይህ ማለት ብሄር ብሔረሰቦች ከሃገር የቀደመ ሉዓላዊነት ባለቤት እንደሆኑ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህንን ሃሳብ የሚያጠናክሩ ድንጋጌዎች በሕገ መንግሥቱ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ እናገኛለን፡፡ ምሳሌ ለመጥቀስ ያክል "አንቀጽ 46" በምናይበት ጊዜ "የፌደራል መንግሥት በክልሎች የተዋቀረ ነው" ይለናል፡፡ ክልሎች ደግሞ የተዋቀሩበት መሰረታዊ ፍልስፍና ተመሳሳይ ቋንቋ፣ አሰፋፈር፣ ማንነት ያላቸው ብሔር፣ ብሔረሰቦች በመሆናቸው ነው፡፡ ስለሆነም ስለአንቀጽ 39 ስናወራ የሕገ መንግሥቱን ጠቅለል ያለ መንፈስ መረዳት የግድ ይላል ምክንያቱም ብቻውን የቆመ አንቀጽ አይደለምና፡፡

አንቀጽ 39 የብሔር ብሄረሰቦች፣ ህዝቦች መብት የሚል ርዕስ ሲኖረው ከስሩ አምስት ንዑስ አንቀፆችን የያዘ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በተለያዩ የህግም ይሁን የፖለቲካ ምሁራን ዘንድ በአከራካሪነቱ የሚታወቀው ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ ያለው "የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከመገንጠል የሚለው" ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንቀጽ 39 ቋንቋን፣ ባህልን የማሳደግ መብት፣ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብትን ያቀፈ ሲሆን አከራካሪ ቢሆን ብሄር ብሄረሰብ እና ህዝብ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለማብራራት ሙከራ የተደረገበት ድንጋጌ ነው፡፡

አንቀጽ 39 የብሔር፣ ብሔረሰቦች፣ ህዝቦች መብት

  1. "ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ህዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለገደብ የተጠበቀ ነው፡፡"

አንቀጽ 39 ማሻሻል ይቻል ይሆን?

ሕገ መንግሥትን ማሻሻል ማለት ከመሰረታዊ የሃገረመንግሥት ግንባታ ፍልስፍና ሳይወጡ አንዳንድ አንቀፆች ወይም ቃላቶች ላይ ማስተካከያ ማድረግ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 105 ላይ እንደተመላከተው "አንቀጽ 39" ለማሻሻል የሁሉንም ክልሎች ይሁኝታ የሚፈልግ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ይሄንን አንቀጽ ማሻሻል ወይም መቀየር ማለት በመሰረታዊነት የሕገ መንግሥቱ መንፈስ የመቀየር እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ምክንያቱም "የብሔር ብሔረሰቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት" የሕገ መንግሥቱ ማጠንጠኛ እና መሰረት ሆኖ በመግቢያውም ይሁን ውስጡ ባሉት ድንጋጌዎች የሰፈረ በመሆኑ ነው፡፡

ምናልባት "እስከመገንጠል" የምትለዋ ድንጋጌ በትርጉም "ከሃገር መገንጠልን አይጨምርም" በሚል ማስተካከል ይቻል ይሆናል፤ ምክንያቱም በደፈናው እስከመገንጠል ይላል እንጂ መገንጠሉ ከሃገር ይሁን፣ ከክልል አሊያም ከዞን ለሚለው የሰጠው ግልፅ ምላሽ የለም፤ ይሁን እንጂ ትርጉምም ቢሆን የአርቃቂዎቹን የሃሳብ ነፀብራቅ ማጥናት እና ምን ለማለት ፈልገው ነበር ይሄንን አንቀጽ ያካተቱት የሚለውን መመርመር ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም አርቃቂዎቹ "በሃገር ማዕቀፍ ውስጥ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ሊከበር ይገባል፡፡ መገንጠል ሲባል የራስን የብሄረሰብ አስተዳደር ማዋቀር እንጂ ከሃገረ መንግሥት መውጣትን አይጨምርም" ብለው አስበዋል ወይስ "መገንጠል ማለት ከፌደሬሽኑ መውጣት ጭምር ነው?" የሚለውን መልስ መስጠት ያሻል፡፡

ማጠቃለያ

ሕገ መንግሥት ማሻሻል አንድ ሕገ መንግሥት ረጅም እድሜ እዲኖረው እና ከወቅቱ ጋር ራሱን እያላመደ የሚያሰራ ህግ ሆኖ እንዲቀጥል ከሚያስችሉት የእድገት ደረጃዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ነገር ግን በማሻሻል ስም መሰረታዊ ለውጥ ማድረግ ከመሰረታዊ የማሻሻል እሳቤ ውጪ በመሆኑ ከሕገ መንግሥቱ የሃገር ግንባታ ፍልስፍናዎች አንዱ በሆነው የብሔር ብሔረሰቦችን መብት የራስን እድል በራስ መወሰን ላይ የሚደረግ ማሻሻያ ሕገ መንግሥት ወደመለወጥ ዝንባሌ የሚወስድ ሊሆን ስለሚችል በአግባቡ ማጤን ይፈልጋል፣ ይሻሻል ቢባል እንኳን የማሻሻያ ሂደቱ እጅግ የጠበቀ ነው፡፡ አንቀጽ 39ኝን በማሻሻል ስም በመሰረታዊነት መለወጥ የማይቻል ወይም ጥብቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አንድነትን ይፈታተናሉ የሚባሉ "እስከመገንጠል" አይነት ድንጋጌዎችን በትርጉም ማስተካከያ የሚደረግበት በር ዝግ አለመሆኑን ማየት ያስፈልጋል፡፡

ጸሐፊው የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Permanency Rule Dilemma To Designate Grave Willful...
Elucidating Some Legal Insufficiency Of Prosecutor...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Sunday, 08 September 2024