መቸም አሁን ለእናንተ ላወጋችሁ ያሰብኩትን ነገር በድሮ በዚያ በጥንት ጊዚያት ለነበሩ ሰዎች ብተርክላቸው ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም ይሉኝ እንደነበረ አምናለሁ፡፡ ይህንን ጽሁፍ በተለያየ መልኩ አግኝታችሁ ወይም ያነበቡት አጋርተዋችሁ ስለዚህ ጉዳይ በደንብ የምታውቁ መኖራችሁ እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ አንዶቻችሁ ግን ወቼ ጉድ! አሁን የሰዎችን ማንነት መሰረቅም ተጀምርዋል ነው የምትለን;! የምትሉ አትጠፉም ብየ እገምታለሁ፡፡ ለዚህም ምላሼ አዎ! የሰውን ማንነት መሰረቅ ተጀምርዋልና ማንነታችሁ እንዳይሰረቅ ጠንቀቅ በሉ ነው የምላችሁ፡፡ እንዴት ሆኖ ይሰረቃል በልስቲ አውጋን የሚል ከሆነ ቀጣዩ ጥያቄያችሁ በደስታ ይሄው እላለሁ፡፡
በቅድሚያ እንዴት ይሰረቃል ለምን አላማ ሲባል ይሰረቃል የሚለውን ከመመልከታችን በፊት ለመሆኑ ማንነት ስንል ምን ማለታችን ነው የሚለውን እንመልከት፡፡ አንድ ሰው ለመተዋወቅ ወይም ደግሞ ከእኛ የሚፈልገው አገልግሎት ኑሮት እኔ እገሌ እባላለሁ! በማለት ራሱን ሊያስተዋውቀን ይችል ይሆናል፡፡ እኛም እንደነገሩ አስፈላጊነትና ግዴታ የተባለው ሰው ስለመሆኑ በተለያየ መልኩ እንዲያስረዳን ልንጠይቀው እንችላለን፡፡ በሌላ አነጋገር እገሌ ስለመሆንህ ማስረጃ አቅርብልን ልንለው እንችላለን፡፡ ይሄው ብሎ ማንነቱን የሚገልጽ ወረቀት መታወቂያ ወይም ከዚህ ተመሳሳይነት ያለው ማስረጃ ሊያቀርብልን ይችላል፡፡ እኛም አሁንም እንደነገሩ አስፈላጊነት የተባለው ሰው ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለማረጋገጥ የተቀበልነውን ማስረጃ አገላብጠን ልንመለከተው እንችል ይሆናል፡፡ ታዲያ እርሱ ማን እንደሆነ ምን እንደሚሰራ የት እንደሚኖር ጾታውን እድሜውን የቤተሰቡን ሁኔታ ዜግነቱ እናም የመሳሰሉትን መረጃዎች ከተቀበልነው ሰነድ ልናይ እንችላለን፡፡ ከዚህ በህዋላ ግለሰቡ እርሱ ራሱን መሆን አለመሆኑን ካረጋገጥን በህዋላ ከእኛ የሚጠበቅ ነገር ሲኖር ተፈላጊውን አገልግሎት ወይም ትብብር ልናደርግለት እንችላለን፡፡ ስለዚህ ምን እያልን ነው ያለነው አንድን ሰው ማንነቱን እንድንለይ ሊያደርጉን የሚችሉ መስፈርቶች ከሀገር ሀገር የሚለያዩ ቢሆኑም በአብዛኛው የሚከተሉት መስፈርቶች የአንድ ግለሰብ ማንነቱ ሊያስረዱን የሚችሉ መታወቂያዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ የግለሰቡን ስም፣ የስራ ወይም የመኖሪያ አድራሻው፣ ዜግነቱ የመታወቂያ ወይም የፓስፖርት ቁጥሩ፣ የማህበራዊ ዋስትና ቁጥሩ፣ የባንክ አካውንት ቁጥሩ፣ የመንጃ ፈቃዱን የትምህርት ደረጃው፣ የተሰማራበትን የስራ መስክ፣ እድሜው፣ የትውልድ ቀንና ቦታውን ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ስለሆነም አንድ የማንነት ስርቆት ወንጀል ፈጻሚ እነዚህንና ሌሎች የራሱን ማንነት ደብቆ የሌላ ሰውን ማንነት ለመላበስ/ለመምሰል የሚያስፈልጉ ከላይ የተመለከትናቸውን የማንነት መገለጫዎችን ልቅም አድርጎ በመውሰድ/በመስረቅና ለዚህ አጋዥ የሚሆነውን ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት ወይም እንዲዘጋጅለት በማድረግ ማንነቱን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በመቀየር በሰረቀው ሰው ስምና ማንነት ወንጀል መስራት ይጀምራል፡፡ ይህም ማለት የማንነት ስርቆት ማለት የአንድ ግለሰብ መለያ መስፈርቶች ሊሆኑ የሚችሉትን መስፈርቶችን በመጠቀም የወንጀሉ ሰለባውን ተመሳስሎ ህገወጥ ድርጊት የመፈጸም ወንጀል ነው፡፡ የዚህ አይነት የወንጀል ድርጊት ቀደም ብሎ የነበረና የቆየ ወንጀል ድርጊት ቢሆንም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስፋፋትንና ስራዎች በአብዛኛው በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መከናወናቸውን ተከትሎ በከፍተኛ ደረጃ የወንጀል ድርጊቱ ሊስፋፋ ችልዋል፡፡
በማንነት ስርቆት የተሰማሩ ሰዎች የሚከተሉት ዘዴዎችን በመጠቀም የግለሰቦችን ይሁን የተቅዋማት መረጃዎችን ይወስዳሉ/ይሰርቃሉ፡፡ የመጀመሪያው ማህበራዊ ምህንድስና (social engineering) የሚባለው ዘዴ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ እንደ ቫይረስና አሳሳች ሶፍትዌሮችን በመጠቀም መረጃዎችን የመሰብሰብ ተግባራት ያከናውናሉ፡፡ ማህበራዊ ምህንድስና (social engineering) የሚባለው በአካል ከግለሰቡ ከራሱ ወይም እርሱን ከሚያውቁ ሌሎች ግለሰቦች ጋር በመተዋወቅ ስለ ግለሰቡ ማንነት አስፈላጊ መረጃዎችን የመሰብሰብ ሂደት ነው፡፡ በዚህም ግለሰቡ ማን እንደሆነ ምን እንደሚሰራ የት እንደሚኖር እና ለወንጀል ድርጊታቸው ያስፈልጉናል የሚልዋቸውን ሌሎች መረጃዎችና ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ወደ ወንጀል ድርጊታቸው ይገባሉ፡፡
ቫይረስንና አሳሳች ሶፍትዌሮችን በተመለከተ በዚህ የወንጀል ድርጊት የተሰማሩ ሰዎች ለወንጀል ድርጊታቸው የሚያግዝዋቸውን ልዩ ልዩ የኮምፒውተር ቫይረስ አይነቶችን ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ እነዚህ የኮምፒውተር ቫይረሶች በተለያዩ መንገዶች እንዲሰራጩ ተደርገው የግለሰቦችንና ተቅዋማትን መረጃ ለእነዚህ ህገ ወጥ ግለሰቦች እንዲደርሳቸው ያደርጋሉ፡፡ ከዚህ ጋር የሚቀራረብም ሌላ ዘዴም አለ፤ ይሄውም፣ በኢሌትሮንክስ መልእክት አመካኝነት ይሁን ወይም ደግሞ ግለሰቡ የሚጠቀምባቸውን ድህረ-ገጾችን በማስመሰል፡፡ አዳዲስ ድህረገጾችን በትግበራ ላይ እንዲውሉ በማድረግ አሳስቶ እንዲጠቀም ማድረግ ነው ይህም በእንግሊዘኛው አጠራር “fishing” የሚባለው ዘዴ ነው፡፡ በዚህም የወንጀል ሰለባው ስለራሱ ማንነት የሚመለከቱ መረጃዎችን በተዘጋጀለት የሀሰት ቅጽ ላይ እንዲሞላ በማድረግ በተለይም ደግሞ የመጠቀሚያ ስሙንና የይለፍ ቃሉን በቀላሉ ለመሰብሰብ ያስችላችዋል፡፡ ወይም ደግሞ ከግለሰቡ ይሁን ተቅዋሙ ጋር ግንኙነት ካለው የኢለትሮንክስ መልእክት የተላለፈ በማስመሰል፡፡ እርሱ ብቻ የሚያውቃቸውን እንደ የይለፍ ቃልና የመጠቀሚያ ስሙን እንዲሞላ ቅጽ በመላክና እንዲሞላ በማድረግ አስፈላጊ የሆኑትን መረጃዎችን ይወስዳሉ፡፡ አላማው የግለሰቡን የይለፍ ቃልና ሌሎች መረጃዎችን ለመውሰድ ነው፡፡