Font size: +
5 minutes reading time (1085 words)

የሳይበር ክልልና ሀገሮች ለአላዊነታቸውን ለማስከበር የሚከተልዋቸው መርህዎች

ሰላም እንዴት ናችሁ፡፡ በባለፈው ጽሁፌ የሳይበር ክልልና የሀገሮች የለአላዊነት ስልጣን እስከ ምን ድረስ? በሚል ርእስ አንድ ጽሁፍ አስፍሬ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ለዛሬ ደግሞ የሳይበር ክልል ለመቆጣጠር ሀገሮች በመከተል ላይ ያሉት መርህዎች ምን ይመስላል? የሚለውን ለማየት እሞክራለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሀለፎም ሃይሉ ለሰጡኝ ምላሽ አመሰግናለሁ፡፡

የአንድ ሀገር የለአላዊነት ስልጣን መገለጫ ከሆኑት ውስጥ አንዱ ስልጣን ባለው ሀገር የተሰጠውን ውሳኔ በሌላ አካል (ሀገር/ድርጅት) ሊከለስ ወይም ደግሞ ሊቀለበስ የማይችል ሲሆን ነው ከዚህ አንጻር ሀገሮች አንድን ጉዳይ የለአላዊነት ስልጣን አለን ወይም የለንም ብለው ለመወሰን የሚያስችልዋቸው ልዩ ልዩ መርህዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ እንደ ግዛትን፣ ዜግነትን፣ ብሄራዊ ጥቅምን የአለም አቀፍ ስልጣንና የመሳሰሉትን መርሆዎችን በተናጠል ወይም አጣምረው በተግባር ላይ በማዋል የሀገሮቻቸውን ለአላዊነት ተጠብቆ እንዲኖር ያደርጋሉ፡፡ እነዚህን መርህዎች በሳይበር ክልል እንዴት ይተገበራሉ የሚለውን እንደሚከተለው ለመመልከት እንሞክራለን፡፡


ግዛትን መሰረት ያደረገ መርህ


አንድ አንድ ሀገሮች በሳይበር ክልል ውስጥ ለሚነሱ ግጭቶች ይሁን አለመግባባት ግዛትን መሰረት በማድረግ ለጉዳዩ መፍትሄ ማግኘት አለበት ብለው ያምናሉ፡፡ ይህም የሚሆነው ለጉዳዩ መነሻ የሆነው ጉዳይ የተፈጠረው በአንድ ሀገር ግዛት እስከሆነ ድረስ ምንም እንኳን ሌሎች ሀገሮች በድርጊቱ ጉዳት ደርሶባቸው ሊሆን ቢችልም ነገር ግን ግዛትዋ ላይ በመሆን የተፈጸመ እንደመሆኑ መጠን ለጉዳዩ መነሻ የሆነው ሀገር ህግንና ደንብ ተፈጻሚ መሆን አለበት፡፡ የሚል አስተሳሰብ አላቸው፤

ሆኖም፣ ይህ መርህ ለሳይበር ወንጀል ብቻ ሳይሆን በማንኛውም የወንጀል ድርጊት ተፈጻሚ መሆን ያለበት የህግ መርህ ቢሆንም ነገር ግን ከሳይበር ወንጀል ባህሪ አንጻር ሲታይ አንድ ወንጀል ሲፈጸም የበርካታ ሀገሮችን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የወንጀል ድርጊቱ የሚፈጸምበት አጋጣሚ ያለ በመሆኑ ለወንጀሉ መፈጸም ግዛታቸውን ከተጠቀመባቸው ሀገሮች ውስጥ የየትኛው ሀገር ህግና ደንብ ተፈጻሚ ይሁን የሚለውን ጥያቄ በአግባቡ የሚመልስ አይደለም፡፡ ስለሆነም መርሁ ከሳይበር ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጥያቄዎች የግዛት መርህ አግባብነት የለውም ብለው የሚተቹት ቢኖሩም ነገር ግን የግዛት ህግ መፈጸም አለበት ብለው የሚከራከሩ መርሁን ተፈጻሚ እንዲሆን የሚያግዙ ሁለት ንድፈ-ሀሳቦችን ያስቀምጣሉ፡፡ እነዚህም ንድፈ-ሀሳቦች የአውራጅና ጫኝ ንድፈ-ሀሳብና የሰርቨር ህግ ንድፈ-ሀሳብ ናቸው፡፡

 
የመጀመሪያው ንድፈ-ሀሳብ ጫኝና አውራጅ ሲሆን ይህም በሳይበር ክልል ውስጥ የወንጀል ድርጊት ሊፈጽሙ የሚችሉ ሁለት ተዋናዮች አሉ እነእርሱም ጫኝና አውራጅ የሚባሉ ናቸው፡፡ በሳይበር ክልል ወንጀል ሊፈጸም የሚችለው አንድም ህገወጥ የሆኑ መልእክትን፣ ዳታዎችን፣ ፕሮግራሞችን ወደ ሳይበር ክልል እንዲገባ ወይም እንዲጫን በማድረግ ነው ወይም ደግሞ እነዚህን ከሳይበር ክልል አስሶ በማውረድ ነው ከሚል እሳቤ በመነሳት ሲሆን እነዚህን አካላትን ጫኝና አውራጅ የሚባሉትን በመቆጣጠር አንድ ሀገር በግዛቷ ውስጥ የሚከናወኑ ህገ ወጥ የሳይበር ድርጊቶችን ለመቆጣጠር የራሷን ህግ ተፈጻሚ ለማድረግ ትችላለች፡፡ በዚህ ረገድ ሊያጋጥም የሚችል የጎላ ችግር ሊኖር አይችልም ይላሉ፡ ምክኒያቱም አንድ ሀገር ከህጎችዋ ጋር የማይጣጣሙ ነገሮች ወደ ሳይበር ሲጫኑ በዝምታ አትመለከትም ማስቆም መከልከል ብሎም ጥፋተኞችን ለህግ በማቅረብ የመቅጣት መብት አላት፡፡ ይህንን በምሳሌ አስደግፈን ብንመለከተው ለምሳሌ አንድ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ጥፋት ማድረስ የሚችል የኮንፒውተር ቫይረስ ወደ ኢንተርኔት ቢጭን ሀገሪቱ ይህን ድርጊት የመቆጣጠር ሙሉ መብት አላት በዚህ ረግድ ችግር ሊኖር አይገባም፡፡


በማውረድም ረገድ ተመሳሳይ ነው የላይኛውም ምሳሌ መመልከት እንችላለን ይሄውም አንድ ሰው ሀገር ውስጥ ሆኖ ከውጪ የሚመጣለትን ከሀገሪቱ ህግ ጋር የሚጻረር ድርጊት ተቀብሎ ሲያወርድ ቢገኝ ድርጊቱን እንዲያቆም ማድረግ ይቻላል፡፡ የሚል ነው፡፡


ሌላኛው ንድፈ-ሀሳብ የሰርቨር ህግ ቲዮሪ ሲሆን የዚህ ቲዮሪ አራማጆች ከየትኛውም ሀገር በበለጠ የቅድሚያ ስልጣን ሊኖራት የሚገባ የሰርቨር ሀገር ናት ይላሉ፡፡ የሰርቨር ሲባል ህግ ምንም እንኳን ድህረ ገጾች የትም ቦታ ተደራሽ ቢሆንም መነሻ የላቸውም ማለት ግን አይደለም መነሻ ቦታቸው በቅድሚያ ድህረ ገጾች ሲመሰረቱ ወይም አብዴት ሲደረጉ የሚቀመጡበት ወይም የሚጠራቀሙበት ቦታ ወይም ሰርቨር ነው፡፡ 

 

ስለሆነም እነዚህ ሀገሮች ማለት ለአንድ ወንጀል መነሻ የሆነ ድርጊት ወይም ከሀገሪቱ ህግ ጋር የሚጻረር ድርጊት በድህረገጹ ተለቆ እንደሆነ የሰርቨር ሀገር የሉአላዊነት ስልጣን አለኝ የማለት መብት አላት የሚል ቲዎሪ ነው፡፡ ምክኒያቱም፣ በሰርቨሩ ላይ ህገወጥ ድርጊት እንዲፈጸም ሲያደርግ ሁለት ህጎችን ተጻርረዋል ማለት ነው ይሄውም፣ ሰርቨሩ የተቋቋመበት አለማ በመጻረር ለህገ ወጥ አላማ እንዲውል አድርጎታል፡፡ እንደገና የሰርቨር ሀገር ህግ አለ ስለሆነም የሰርቨር ሀገር ሰርቨርዋን ለህገ ወጥ አላማ ተጠቅሞበታልና የሀገሪቱን ህግ ተፈጻሚ ሊሆን ይገባል የሚል ነው፡፡


ከዚህ ጋር ተያይዞ እንደ ችግር የሚነሳው ለምሳሌ ድህረገጹ ለሁሉም ሀገሮች ተደራሽ እንደመሆኑ መጠን ሌሎች ሀገሮችስ ህጋችን ተጻርረዋል ብለው ማንን ነው መጠየቅ የሚችሉት ወደ ግዛታቸው ህገ ወጥ ዳታ ያሰራጨውን ሰርቨርን ነው ወይስ የመጀመሪያውን ቲዮሪን መሰረት በማድረግ ወደ ሰርቨሩ ህገ ወጥ ዳታ የጫነውን ነው› በማለት የግዛት መርህ ተግባር ላይ መዋል አለበት የሚሉትን አካላት የሚሞግትዋቸው መኖራቸው አልቀሩም፡፡
ሌሎች ሀገሮች ደግሞ በዜግነት ላይ ተመርኩዘው የሉአላዊነት ስልጣን እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡ ይህ መርህ ከላይኛው ጋር ስናነጻጽረው የመጀመሪያው ግዛትን ከግምት ውስጥ ያስገባ ከመሆኑ አንጻር የድርጊቱን ተዋናዮች ዜግነት ከግምት ውስጥ ሳይገባ ለድርጊቱ መነሻ ግዛት በመሆኑ የሀገሪቱ ዜጋ ይሁን የውጪ ሀገር ዜጋ በግዛትዋ ውስጥ ሆኖ ወንጀል ሰርቶ እስከተገኘ ድረስ የሀገሪቱን ህግ ተፈጻሚ መሆን አለበት ብለው ይከራከራሉ፡፡ ነገር ግን መርሁ ከሀገር ውጪ ለሚፈጸሙ ድርጊቶች ያን ያክል ትኩረት ስለማይሰጥ ድርጊቱ የተፈጸመው ከሀገር ውጪ ከሆነ መርሁ በተግባር ላይ ለማዋል አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡


በሌላ በኩል ዜግነት ላይ ትኩረት ያደረገው መርህ ደግሞ በአንጻሩ ድርጊቱ የተፈጸመው በየትኛውም ቦታ ቢሆንም የዜግነት ሀገሩ ህግ ተፈጻሚ ሊሆን ይገባል ይላሉ፡፡ ይህም ማለት ምንም እንኳን ድርጊቱ የተፈጸመው ከሀገር ውጪ ቢሆንም ተላልፎ ወደ ሀገሩ ተመልሶ ጉዳዩን እንዲከታተል መደረግ አለበት ማለት ነው፡፡ ሆኖም መርሁን በተግባር ለማዋል ቢያንስ በሚከተሉት ሁለት ምክኒያቶች አስቸጋሪ እንዲሆን ያደርግዋል ይሄውም ድርጊቱ ከወንጀል ድርጊት ጋር የተያያዘ ከሆነ በግዛትዋ ውስጥ ሆኖ የወንጀል ድርጊት የተፈጸመባት ሀገር የራስዋን ህግ ከማስፈጸም ይልቅ ለሌላ ሀገር አሳልፋ የምትሰጥበት ምክኒያት ብዙም አይኖርም፡፡


በመቀጠልም በሁለቱም ሀገሮች መካከል ማለትም ግለሰቡ በሚገኝባት ሀገርና ዜጋየ ነው የመዳኘት ስልጣን አለኝና ተላልፎ ይሰጠኝ በምትለው ሀገር መካከል አሳልፎ ለመስጠት ስምምነት ከሌለ በስተቀር ተላልፎ የመሰጠቱ ሁኔታ አነስተኛ ስለሚሆን መርሁን ተግባራዊ የሚያደርጉት ሀገሮች ብዙም አይደሉም አልያም ዲፕሎማሳዊ አቅማቸው በሌሎች ሀገሮች ላይ ጫና ማሳደር የሚችል አቅም ያላቸው መሆን ይኖርባቸዋል፡፡


ሌላኛው ብሄራዊ ጥቅምን መሰረት ያደረገ መረህ ነው፡፡ የዚህ አቋም አራማጆች የአንድ ሀገር የሉአላዊነት መገለጫው በየትኛውም ሁኔታ የሀገርን ቢሄራዊ ጥቅም የሚነካ ጉዳይ እስከተፈጠረ ድረስ የሀገሪቱ መንግስት ይህንን ጥቅም የማስከበር ሀላፊነት አለበት በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ መርህ ነው፡፡ የዚህ መርህ ግንባር ቀደም አቀንቃኞች ከሆኑት ውስጥ አሜሪካ በግንባር ቀደምትነት በብዙ ጸሃፍት የምትጠቀስ ሀገር ናት፡፡ ይህ ማለት ግን ሌሎች ሀገሮች ብሄራዊ ጥቅማቸውን ችላ ይላሉ ማለት አይደለም ይሁን እንጂ በአቅም ማነስ ይሁን በሌላ ምክንያት ለብሄራዊ ጥቅም ተግባራዊነት ብዙም ገፍተው የማይሄዱ እንዳሉ ግን መረሳት የለበትም፡፡


በዚህም መሰረት አንዲት ሀገር የራስዋን ብሄራው ጥቅምን የሚጻረር ድርጊት ተፈጽሞ የተገኘ እንደሆነ ድርጊቱ የተፈጸመበት ግዛት ይሁን የፈጻሚዎቹ ማንነት ከግምት ውስጥ ሳይገባ ብሄራዊ ጥቅሟ የተነካባት ሀገር ጥቅሟን የማስከበር መብት አላት የሚል ነው፡፡ ለምሳሌ ጁሊያን አሳንጅ የዊክስሊክሰ ድህረገጽ መስራች የነበረው የበርካታ ሀገሮችን ሚስጢር በድህረ ገጹ እንዲወጣ በማድረጉ ምክኒያት በርካታ ሀገሮች ብሄራዊ ደህንነታቸው ላይ ጉዳት በማድረሱ ተላልፎ እንዲሰጣቸው ሲወተውቱ ነበሩ፡፡ በተለይም አሜሪካ በግንባር ቀደምትነት ጥያቄዋን አቅርባ እንደነበረች የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡


ስለሆነም መርሁን የሀገርን ጥቅም ከማስከበር ብቻ ሳይሆን ከሳይበር ክልል ተፈጥራዊ ባህሪ አኳያ ቢሄራዊ ጥቅምን ማስከበር የሚለው መርህ የተሻለውና ተስማሚ መርህዎች ከሆኑት ውስጥ አንደኛው እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡

 

ከላይ የተመለከትናቸው መርህዎች በአብዛኛው የሳይበር ወንጀልን ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያገለግሉ መርሆች እንደመሆናቸው መጠን ከፍትሐብሔር ወይም ሲቪል ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችስ የሚፈቱበት ሂደት ምን ይመስላል የሚለውን ከሲቢል ጋር ተያይዘው የሚነሱ አለመግባባቶች በአብዛኛው ያለመግባባቶቹ የሚመነጩ ከውልና ውል ነክ ከሆኑ ጉዳዮች ስለሚሆኑ በብዙ ተቀባይነት ያለው ሀሳብ በቅድሚያ ተዋዋይ ወገኖች ጉዳያቸውን --ሊፈታላቸው የሚፈልጉትን ሀገር ካለ በስምምነታቸው መሰረት ሊሆን ይገባል፡፡ ሆኖም ስምምነት የሌለ እንደሆነ አንድ አንድ ሀገሮች የሸማቾችን ጥቅም ከማስከበር አኳያ ሲመለከቱት ሌሎች ደግሞ ውሉ ታሳቢ የሚያደርገው ሀገር ጉዳዩን የማየት ስልጣን ሊኖረው ይገባል በሚል ከፍታቢሄር ጉዳይ ተያይዘው ለሚነሱ ክርክሮች በመፍትሄነት ለማቅረብ ይሞክራሉ፡፡

ስለሆነም እነዚህና ሌሎች መርሆችን በመጠቀም ከሳይበር ጋር ተያይዘው የሚነሱ አለመግባባቶች ይሁን ከለአላዊነታቸው ጋር ተያይዞ ሊኖር የሚችለውን ክፍተት ለሞምላት ይሞክራሉ፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ያስፋፋው የማንነት ስርቆት (identity theft)
Prosecution for Several Counts Resulting from a Si...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Sunday, 08 September 2024