የኢትዮጵያ የብር ኖቶችና የባንኮች አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓተ-ልማድ ከአካል-ጉዳተኞች መብት አንጻር  

መግቢያ

በሀገራችን ከ20 ሚሊዮን  በላይ የአካል ጉዳት ያለባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደማንኛውም ሰው የተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት አገልግሎቶችን ለመጠቀም የተለያዩ መሰናክሎች ይገጥሟቸዋል፡፡ በዚህ ጽሑፍ አካል-ጉዳተኞች በኢትዮጵያ የብር ኖቶች አጠቃቀም እና በባንክ አገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ከሕግ እና ከአሰራር አንጻር እንዳስሳለን፡፡

ባንኮች ከህዝብ የአክሲዮን መዋጮ ሰብስበው ሀገሪቱ ባወጣቻቸው የባንክ ሥራ አዋጅ፣ የፍትሐብሔር ሕግ፣ የንግድ ሕግና ብሄራዊ ባንክ በሚያወጣቸው የማስፈጸሚያና የመቆጣጠሪያ መመሪያዎች የሚቋቋሙና የሚተዳደሩ የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶችን የሚሰጡ የንግድ ማህበራት ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከወረቀት የባንክ አገልግሎት በተጨማሪ የዲጂታል ወይም የኤሌክትሮኒክ ባንክ አገልግሎት በስፋት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በተለይ የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝን  ለመከላከል የዲጂታል ባንክ  አገልግሎት አካላዊ ንክኪን እና አካላዊ ቅርርብን ስለሚቀንስ  ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡

 

ባንኮች ለአካል-ጉዳተኞች አገልግሎት የሚሰጡበት አሰራርና ተግዳሮቶቹ

 

የመጀመሪያው ተግዳሮት ባንኮች ለአገልግሎት የሚያስገነቧቸው ወይም የሚከራዩአቸው ህንጻዎች ለአካል-ጉዳተኞች እንቅስቃሴ ምቹ አለመሆን ነው፡፡ ይህ ችግር በሌሎች መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትም የሚስተዋል ነው፡፡ እዚህ ላይ አካል-ጉዳተኞችን በማሰብ ምቹ ሆነው የተገነቡ ጥቂት የገበያ ማእከላትን እና ሆቴሎችን  ማድነቅ ያስፈልጋል፡፡ ከህንጻዎቻቸው ምቹነት በተጨማሪ የምግብ ሜኑዎቻቸውን ሳይቀር በብሬል አዘጋጅተው የሚያቀርቡ ሆቴሎችም አሉ፡፡፡፡

ሌላው ተግዳሮት በተለይ አይነስውራን ግብይት ለማድረግ የገንዘብ ኖቶችን አንብቦ ለመለየት የሚያስችል ምልክት (currency identification) አለመኖሩ ነው፡፡ ችግሩ የማየት እና የመስማት ድርብ ጉዳት ባለባቸው ሰዎች ላይ ይበልጥ የከፋ ነው፡፡ ይህ ችግር ባንኮች ብቻ የፈጠሩት ሳይሆን  የገንዘብ ህትመት ስርአቱ ችግር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብር የቀለም ጽሑፍ እና የምስል መለያ እንጂ በእጅ የሚለይ ምልክት (tactile markings) የለውም፡፡ በሌሎች ሀገራት በብሬል፣ በእጅ በሚያዙ የገንዘብ መለያ መሳሪያዎችንና ሶፍትዌሮችን ይጠቀማሉ፡፡ በተጨማሪም መስማት የተሳናቸው የባንክ ደንበኞች  የባንክ ጉዳዮቻቸውን ለመፈጸም የሚያስችላቸው  በባንኮች የተዘጋጀ የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ አለመኖሩ ነው፡፡

 

ባንኮች በብዛት ለአይነስውራን የሚሰጡት የቁጠባ ሂሳብ ደብተር አገልግሎት (ፓስ ቡክ አካውንት) ሲሆን አገልግሎቱን ለማግኘትና ገንዘብ ገቢ ለማድረግ የሚጠበቀው መስፈርት እንደማንኛውም ደንበኛ የተለመደ ነው፡፡ ችግሩ የሚጀምረው ሂሳባቸውን ሲያንቀሳቅሱ ነው፡፡ አብዛኞቹ ባንኮች አይነስውራን ደንበኞቻቸው ገንዘብ ወጪ ሲያደርጉ ምስክር ካላቀረቡ ሂሳባቸውን ወጪ ማድረግ አይችሉም፡፡ ባንኮች ለዚህ አሰራራቸው መነሻ የሚያደርጉት የ1952ቱን የፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 1728ን ነው፡፡ እንደሕጉ አነጋገር ከማህይማንና ከእውራን ጋር የሚደረግ የውል ፊርማ በውል አዋዋይ ሹም ወይም በፍርድ ጸኀፊ ወይም ዳኛ በሥራቸው ላይ ሆነው ያረጋገጧቸው ካልሆነ አያስገድዳቸውም በማለት ይደነግጋል፡፡ በዚህ መነሻነት በዳበረው ልማዳዊ  አሰራር መሰረት የደንበኛውን እና የምስክሩን/ሯን መታወቂያ ኮፒ በማድረግ ደንበኛው ይህን ያህል ብር ሲያወጣ አይቻለሁ በማለት እንዲፈርሙ በማድረግ የምስክሩ  ማንነት፣ የሥራ ቦታና ሁኔታ፣ የደንበኞቹ ቤተሰብ ይሁን የሥራ ባልደረባ ግድ አይሰጣቸውም፡፡ አንዳንዶቹ በዚህ አሰራር ገንዘብ ለማውጣት፣ ለማስተላለፍና ቀሪ ሂሳባቸውን ለማወቅ ደብተራቸውን ለሶስተኛ ወገን ማስነበብ የግድ ይሆንባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ከመሰረታዊ የሰብአዊ መብቶች አንዱ የሆነውንና በሕገመንግስቱ አንቀጽ 26 የተረጋገጠውን የግላዊነት ህይወት መብትን ይጋፋል፡፡ በሕግ መሰረት ካልሆነ በስተቀር የግል ህይወት መብት ሊገደብ አይችልም፡፡ ሚስጥራዊነታቸውንም በማጋለጥ ደንበኞችን ለዘረፋ እና ለጥቃት ሊዳርጋቸው ይችላል፡፡ አካል-ጉዳተኞች ተደራሽ የባንክ አገልግሎት ካላገኙ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸው በእጅጉ ይገደባል፡፡

አካል-ጉዳተኞች ፈተና የሚሆንባቸው ሌላው ጉዳይ በፊርማ ምክንያት የባንክ ብድር አገልግሎት ለማግኘት ነው፡፡ በአንድ ወቅት የኮንዶሚኒየም እድል ባለእጣ የሆነ አንድ አካል-ጉዳተኛየ20/80 የባንክ ብድር ለመፈረም ወደ ባንኩ ሲሄድ በባንኩ አሰራር መሰረት  የብድር አገልግሎቱን የምታገኘው በአንተ ፊርማ ሳይሆን የምትወክለው ሶስተኛ ወገን ካለህ ብቻ ነው በማለት ይነግረዋል፡፡ ባለእጣውም እኔ የምወክለው ሰው የለኝም በራሴ ፊርማ ይሁንልኝ ብሎ ሲጠይቅ እንደዚያ ከሆነ ብድሩን መስጠት አንችልም ሲባል በወቅቱ የውልና ማስረጃ ቀርቦ ውክልና በሰጠው ሶስተኛ ወገን አማካኝነት የብድር ውሉን ተዋውሎ ብድሩ ተፈቀደለት፡፡

 

ከንግድ ወረቀቶች አንዱ የሆነውን የቼክ አካውንት ወይም ተንቀሳቃሽ የባንክ ሂሳብ ለመጠቀም ጸሀፊው እስካለው መረጃ ድረስ ለአይነስውራን ደንበኞች አገልግሎቱን የሰጠ ባንክ የለም፡፡ ምክንያታቸው ወጥ የጣት አሻራ ፊርማ ናሙና ለመስጠት ያስቸግራል የሚል ነው፡፡ ይሁን እንጂ የንግድ ሕጉ አንቀጽ 733 ማናቸውም በውል ለመገደድ ችሎታ ያለው ሰው በንግድ ወረቀትም ለመገድድ ይችላል፡፡ የዚሁ ሕግ አንቀጽ 734 (1) በንግድ ወረቀት የተደረጉ ማስታወቂያዎች (ዴክላራሲዮን) እነዚሁኑ ማስታወቂያዎች የሰጠው ሰው የእጅ ጽሑፍ ፊርማ ሊኖራቸው ይገባል ቢልም በእጅ ወይም በመኪና አሰራር ምልክት በሚያደርግ ዘዴ ማህተምን በመሰለ ፊርማ ወይም ለመፈረም የአካል ችሎታ የሌለው እንደሆነ መፍቀዱ በሰነዱ ላይ በባለስልጣኑ ፊት በተደረገ ማስታወቂያ መረጋገጥ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ይህ ማለት ለምሳሌ፡ የባንክ ደንበኛው የሁለቱም እጅ ጉዳተኛ ወይም አይነስውር ቢሆን የአይነስውሩን የእጅ ጣት አሻራ ወይም ከጣት አሻራው በሚወሰድ የአሻራ ፊርማ ናሙና ማህተም በመጠቀም፣ ወይም ደንበኛው በሁለቱም እጆቹ ጉዳት ምክንያት ለመፈረም የማይችል ከሆነ መፍቀዱ በሰነዱ ላይ በባለስልጣኑ ፊት በተደረገ ማስታወቂያ መረጋገጥ ይችላል ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ የውል አዋዋይ ሲባል የሰነዶች ምዝገባ እና ማረጋገጫ ብቻ ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ፡ ባንኮች የባለአክሲዎኖች ጠቅላላ ጉባኤ ሲጠሩ በስብሰባው ላይ መገኘት የማይችሉ ባላክሲዎኖች በስብሰባውላይ  የሚገኙላቸውን  ወኪሎች ውክልና የሚሰጡት ሰነዶች ማረጋገጫ እናምዝገባ ኤጀንሲ ቀርበው ሳይሆን ራሳቸው ባንኮች ናቸው ውክልናውን የሚያዋውሉት፡፡ ስለዚህ በጠባቡም ቢሆን ባንኮችም የማዋዋል ስልጣን አላቸው ማለት ነው፡፡ ይህ ባይሆን እንኳን በፍትሐብሔር ሕጉ፣ በንግድ ሕጉ እና በባንክ ሥራ አዋጁ መሰረት ያለውን የአፈጻጸም ክፍተት የሚደፍን አሰራር መዘርጋት ቢኖርባቸውም   ብሄራዊ ባንክም በዚህ አግላይ አሰራራቸው አልጠየቃቸውም በሚያወጣቸው መመሪያዎችም ጉዳዩ መፍትሄ እንዲኖረው አላደረገም፡፡

 

የወረቀት ባንክ አገልግሎት በተለይ አይነስውራን በሶስተኛ ወገን እገዛ የሚጠቀሙት አገልግሎት ነው፡፡ ይህ አገልግሎት የአይነስውራን ደንበኞችን የግል ህይወትና ሚስጥራዊነት  የመከበር እና የመጠበቅ መብት የሚጋፋ ሲሆን በተለይ በአሁኑ ወቅት ለኮረና ቫይረስ አጋላጭ ነው፡፡ ምክንያቱም ሂሳብ ለማንቀሳቀስ ወደ ባንኮች በአካል ለመሄድ ስለሚያስገድድ፣ ፊርማ ለመፈረምና  ገንዘብ ለመቀበል አካላዊ ንክኪን ስለሚፈልግ ነው፡፡

 

በአሁኑ ወቅት ባንኮች በስፋት የሚሰጡት የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ለአካል-ጉዳተኞች በተለይም ለአይነስውራን የባንክ ደንበኞች  ከወረቀት የባንክ አገልግሎት አንጻር በተደራሽነቱ እጅግ የተሻለ ቢሆንም አንዳንዶቹ ባንኮች አገልግሎቱን ሲሰጡ አብዛኞቹ ግን አይነስውራን ኢባንክ አገልግሎት እንዴት እንደሚጠቀሙ ግልጽ መመሪያ ስለሌለን አገልግሎቱን አንሰጥም ይላሉ፡፡ ከዲጂታል ባንክ አገልግሎት አንዱ የሆነውን ኤትኤም ለመጠቀም የሚያስችል የኤትኤም እስክሪን ማንበቢያ ሶፍትዌር ባንኮች የሚተክሏቸው የኤትኤም ማሽኖች የላቸውም ወይም ይህን አገልግሎት እንዲሰጡ ማስተካከያ አያደርጉባቸውም፡፡ የሞባይል ባንክ አገልግሎት ግን አይነስውራን እስክሪን ማንበቢያ ሶፍትዌር ያላቸውን ስልኮች የሚጠቀሙ ከሆነ አገልግሎቱን እንደማንኛውም ደንበኛ መጠቀም ይችላሉ፡፡ አብዛኞቹ ባንኮች ግን ይህ እንደሚቻል ስለማያውቁ አገልግሎቱን ይከለክላሉ፡፡ ችግሩ በግል ባንኮች ላይ ይበልጥ ጎልቶ ይታያል፡፡ በአንዳንድ ባንኮች ክልከላው ከባንኮች ኮርፖሬት/ተቋማዊ ፖሊሲ የሚመነጭ ሲሆን በአንዳንድ ባንኮች ደግሞ እንደተቋም የተያዘ አቋም ሳይሆን  ከግለሰባዊ የአመለካከት ችግር የሚመነጭ ነው፡፡

 

ጉዳዩን በተጨባጭ ምሳሌ ይበልጥ ለማስረዳት አንድ አይነስውር የአዲስአበባ ከተማ ነዋሪ ለሥራውእና ለመኖሪያ አካባቢው ቅርብ ወደሆነ ቀደምት የሀገራችን የግል ባንክ ቅርንጫፍ በማምራት የቁጠባ ሂሳብ ከፍቶ የቁጠባ ሂሳብ ደብተር እና የኤትኤም ካርድ ተሰጠው፡፡ የሞባይል ባንክ አገልግሎቱስ ብሎ ሲጠይቅ የከፈትከው ሂሳብ ማንበብ እና መጻፍ ለማይችሉ ደንበኞች የተዘጋጀነው፤ የዚህአይነት የሂሳብ ቁጥር ደግሞ ከሞባይል ባንክ አገልግሎት ሲስተም ጋር ሊንክ ማድረግ አይችልም በማለት መለሰለት፡፡ ማንበብ እና መጻፍ መቻል  ማለት የግድ የቀለም ጽሑፍ ብቻ ነውን? ሌላው እዚህ ላይ መመለስ ያለበት ጥያቄ አይነስውራን የሞባይል ባንክ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ስልክን እና ኮምፒውተርን   ለመጠቀም የሚያስችሏቸው የስክሪን ማንበቢያ እናመጻፊያ  መተግበሪያ ሶፍትዌሮች አማካኝነት ያነባሉ፤ ይጽፋሉ፡፡ ስለዚህ ባንኮች እንደማንኛውም ደንበኛ  የሞባይል ባንክ አገልግሎት ለአይነስውራን ለመስጠት   አገልግሎቱን ከመልቀቅ የተለየ ስነስርአት አያስፈልጋቸውም፡ በተለይም የኮረና ቫይረስን ለመከላከል መራራቅን የሚያበረታታ፣ አካላዊ ንክኪን የሚቀንስ፣ የሶስተኛ ወገን ጥገኝነትን የሚያስቀር፣ ግላዊ ህወትን፣ ግለሰባዊ ልእልናን እና  ነጻነትን የሚያስጠብቅ በመሆኑ ይበልጥ ተደራሽ እና  ተመራጭ ነው፡፡ ይልቅስ የኤትኤም ማሽኖቻቸውን ሲገዙ እና ሲተክሉ የስክሪን ማንበቢያ ሶፍትዌሮች የተገጠሙላቸው እና የተስተካከሉ መሆናቸውን ቢያረጋግጡ ጥሩ ነው፡፡ ባንኮች አሉታዊ  አሰራራቸውን በተመለከተ የሕጋዊነት ጥያቄ ሲነሳላቸው ሕጉ እንደማይፈቅድ  እንደምክንያት ይጠቅሳሉ  የሕግ አማካሪዎቻቸው ክልከላውን ብቻ ነው እንዴ የሚያማክሯቸው?

 

ስለአካል-ጉዳተኞች መብቶች በአጭሩ

 

የአካል-ጉዳተኞች መብት ከሰብአዊ መብቶች የሚመነጭ ነው፡፡ ሰብአዊ መብቶች ሰዎች ሰው በመሆናቸው ብቻ የሚጎናጸፏቸው መብቶች ናቸው፡፡ የሰብአዊ መብቶች ባለቤት ለመሆን የግለሰቦች ወይም የመንግሥት ፈቃድ አያስፈልግም፡፡ አካልጉዳተኞች ሰው ከመሆናቸው  በተጨማሪ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ በመሆናቸው በጠቅላላው የሰብአዊ መብቶች ከሚደረግላቸው ጥበቃ በተጨማሪ በልዩ ሁኔታ ጥበቃ እንዲደረግላቸው እውቅና የሚሰጡ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነቶችና ሕጎች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ዋነኛው የተባበሩት መንግስታት የአካል ጉዳተኞች መብት ስምምነት ነው፡፡

 

ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ካላቸው የኢ/ፌ/ዴ/ሪ/ ሕገመንግሥት እና የኮንቬንሽኑ መርሆችና ትርጓሜዎች መካከል የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

 

በኢ/ፌ/ዴ/ሪ/ ሕገመንግሥት ከተደነገጉት መሰረታዊ የሰብአዊ  መብቶችና ነጻነቶች መካከል በሕግ ፊት እኩል ዋስትናና ጥበቃ የማግኘት፣ የግል ህይወት የመከበርና የመጠበቅ፣ የግለሰባዊ ነጻነት እና ልእልና መጠበቅ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ የሕግና የሕገመንግሥቱን የበላይነት በሚደነግገው አንቀጽ 9 (2) እና አንቀጽ 13 (1) ማንኛውም ዜጋ የመንግሥት አካል፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማኅበራት እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው ሕገመንግስቱን የማክበር እና የማስከበር ኀላፊነት እና ግዴታ አለባቸው፡፡ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር እንዲሁም የመንግሥት አካል እንዲሁም ባለሥልጣን ውሳኔ ከሕገመንግስቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው በአንቀጽ 9 (1) ላይ ተደንግጓል፡፡

 

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 676/2002 የጸደቀው እና በኢትዮጵያ ሕገመንግሥት አንቀጽ 9 (4) መሰረት የሀገሪቱ ሕግ አካል የሆነው የተባበሩት መንግስታት የአካል-ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት የአካል ጉዳተኞችን ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መብቶችን እንዲሁም በአስቸኳይ ሁኔታ እና በጦርነት ጊዜ ተፈጻሚ የሚሆነውን የሰብአዊነት ሕግን (humanitarian law)  በተሟላ ሁኔታ አካቶ ይገኛል፡፡

 

በስምምነቱ አንቀጽ 2 በተደነገገው መሰረት ሁሉን አቀፍ ንድፍ” (universal design)ማለት ተጨማሪ የማስማማት እርምጃ ወይም የተለየ ዲዛይን ሳያስፈልገው የተቻለውን ያህል አጣጥሞ ለማንኛውም ሰው እኩል ጥቅም ላይ የሚውሉ ምርቶች፣ አካባቢዎች፣ መርሃ ግብሮችና አገልግሎቶች ማሳያ ንድፍ ነው፡፡ ይኸው አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሁሉ አቀፍ ንድፍ የተለየ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የአካል ጉዳተኛ ወገኖች የሚያገለግሉ የመርጃ መሳሪያዎችን ከግምት ላለማስገባት አይችልም፡፡

 

በአንቀጽ 3/ሀ) በግል ምርጫ የመወሰን ነፃነትና ራስን ችሎ የመኖር መብትን ጨምሮ ለተፈጥሯዊ ክብርና ለግለሰብአዊ ልዕልና ዋጋ የመስጠት ግዴታ ተደንግጓል፡፡

 

ሌላው በስምምነቱ አንቀጽ 2 (ሐ) የተደነገገው መሰረታዊ መርህ አካል-ጉዳተኝነትን መሰረት ያደረገ  መድልዎ አልባነት (non-discrimination based on disability) ነው፡፡ በዚህ ንኡስ  አንቀጽ መሰረት  “በአካል ጉዳት ላይ የተመሠረተ መድልዎ” ማለት በፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ማኀበራዊ፣ ባህላዊ፣ በሲቪል ነክ ወይም በሌላ በማናቸውም መስክ ሰብዓዊ መብቶችንና መሠረታዊ ነፃነቶችን ሁሉ ከሌሎች ጋር በእኩልነት ደረጃ ከመጠቀም ወይም ተግባራዊ ከማድረግ ወይም ለነዚሁ መብቶችና ነፃነቶች እውቅና ከመስጠት የመገደብ ዓላማ ወይም ይህንኑ ዓይነት ውጤት የሚያስከትል ማናቸውም ልዩነት፣ አግልሎት ወይም ተፅዕኖ ነው፡፡ አድራጎቱ ምክንያታዊ ተቀባይነት ያለው ማስተካከያ አለማቅረብን ወይም ይህንኑ መንፈግን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት የመድልዎ ተግባራት ያካትታል፡፡

አካል ጉዳተኞች በንግድ እና ኢንቨስትመንት መስኮች የመሰማራት፣   የፋይናንስና የኢኮኖሚ ጉዳዮቻቸውን የመቆጣጠር እና የማንቀሳቀስ  መብት አላቸው፡፡ በስምምነቱ አንቀጽ 12 (5)፡፡ እንደተመለከተው አካል ጉዳተኞች የንብረት ባለቤት የመሆን፣ ንብረትን የመውረስ፣ ፋይናንስ-ነክ ጉዳዮቻቸውን በገዛ ራሳቸው የመቆጣጠርና የባንክ ብድር፣ የወለድአገድና ሌሎች የዱቤ አገልግሎቶችን የማግኘት እኩል መብትና እድል ያላቸውና ንብረታቸውን በዘፈቀደ የማያጡ ስለመሆኑ ይገልጻል፡፡

 

ሌላው መሰረታዊ ነጥብ የተደራሽነት መርህ  ሲሆን የቁሳዊ አካባቢን፣ የመረጃ እና መገናኛ ቴክኖሎጂ ስርአቶችን፣ የመሰረተልማት አውታሮችን እና አገልግሎቶችን ምቹና ቅርብ በሆነ መንገድ ማቅረብን ያካትታል፡፡ አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚያጋጥሙ የአካላዊ፣ የመረጃና የአገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት በአንቀጽ 9 ስር የተደነገገ ሲሆን ባንኮች የሚሰጡትን የወረቀትና የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ይጨምራል፡፡ ስለዚህ ባንኮች በሚሰጧቸው አገልግሎቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አካል-ጉዳትን መሰረት ያደረገ አግላይና አድሏዊ አሰራር እየተገበሩ አለመሆናቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡

 

የመፍትሔ ሀሳቦች

 

ሕግ አውጪው አካታች ሕጎችን የማውጣት፣ ተግባራዊነታቸውን የመከታተልና የመቆጣጠር ኀላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡

 

አስፈጻሚው አካል በተለይ የዘርፉ ተቆጣጣሪ አካል የሆነው ብሄራዊ ባንክ አካታች የባንክ መመሪያዎችንና አሰራሮችን በማውጣት አካል-ጉዳተኞች ተደራሽ የባንክ አገልግሎት የሚያገኙበትን ስርአት መዘርጋት አለበት፡፡ የኤሌክትሮኒክ ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሉ አጋዥ ሕጎች እንደ ብሄራዊ የክፍያ ስርአት አዋጅ ቁጥር 718/2003፣ የኤሌክትሮኒክ ፊርማ አዋጅ ቁጥር 1072/2010 እና ሌሎች ሕጎችን፣ የአለምአቀፍ ተሞክሮዎችን መቅሰምና ጥናቶችን ማድረግ አለበት፡፡ በጉዳዩ ላይ የአካል-ጉዳተኛ ማህበራትን በማሳተፍ  የባንኮችን  ግንዛቤ ማሳደግ አለበት፡፡ ማኅበራቱም እስኪጠሩ ሳይጠብቁ ከመንግሥት ጋር በቅርበት መነጋገርና መሥራት  ይኖርባቸዋል፡፡

 

ባንኮችና ማህበራቸው ሕጋዊ ግዴታዎቻቸውን ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ሀላፊነታቸውንም መወጣት አለባቸው፡፡ አገልግሎቶቻቸውን በስርአተልማድ ሳይሆን በሕግ መሰረት ሊሰጡ ይገባል፡፡ በባንክ ሥራ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1159/2012 አንቀጽ 56 መሰረት ባንኮች የሚሰጧቸውን የባንክ አገልግሎቶች ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ የማድረግ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ በመሆኑም ኤትኤሞቻቸውንና ሌሎች አሰራሮቻቸውን በሕጉ መሰረት ምቹና ተደራሽ ማድረግ አለባቸው፡፡ አመቱን ሙሉ በሚዲያ  ማስታወቂያ በማስነገር ብቻ ሳይሆን የአገልግሎቶቻቸው ተጠቃሚ ያልሆኑ አካል-ጉዳተኞችን በማካተት የውድድራቸው አካል አድርገው ቢሰሩ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ትርፋማነታቸው አሁን ካላቸው አመታዊ ትርፍ የበለጠ ይሆናል፡፡   

 

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር ከባንክ ስርአት ውጪ የሆነ ወደ 113 ቢሊዮን የሚጠጋ ብር ወደ ባንክ ስርአቱ ለማስገባት ሲባል በብር ኖቶች ላይ ለውጥ እንዲደረግ ለብሄራዊ ባንክ ጥያቄ ማስገባቱ ይታወቃል፡፡ የማህበሩ ጥያቄ ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ በእነዚህ የገንዘብ ኖቶች ላይ በዳሰሳ የሚለይ ምልክት ወይም  የብሬል   ቁጥሮችን አካቶ በማተም ለአይነስውራን፣ የማየትና የመስማት ድርብ ጉዳት ላለባቸው ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ምቹ አጋጣሚ ስለሆነ የገንዘብ ህትመት ከመደረጉ በፊት የአካል-ጉዳተኛ ማህበራትና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አስቀድመው ቢያስቡበት ጥሩ ነው፡፡

 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

The legality of sport betting in Ethiopia
የይግባኝ የዳኝነት ክፍያ አግባብነትን በተመለከተ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 24 April 2024