Font size: +
4 minutes reading time (806 words)

አትሌቶች፣ ዶፒንግና ግልግል (arbitration)

ማሪዮን ጆንስ፣ ማሪያ ሻራፖቫ፣ ክላውዲያ ፔከንስታይ እና ላንስ አርምስትሮንግን የሚያመሳስላቸው አንዱ በስፖርቱ ዓለም ገናና ስም የነበራቸው መሆኑ ነው፡፡ ማሪዮን ጆንስ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ ናት፡፡ አርምስትሮንግ ደግሞ በብስክሌት ግልቢያ የሚያህለው አልነበረም፡፡ ማሪዮን ጆንስ አጭሩን ርቀት በሚያስገርም ፍጥነት ታጠናቅቅ ነበር፡፡ የአሸናፊነት ምልክትም ሆና ለብዙ ዘመን ቆይታለች፡፡ አርምስትሮንግም እንዲሁ፡፡ ከችሎታውና ብቃቱ የተነሳ ስፖንሰሩ ለመሆን ያልተሯሯጠ ኩባንያ አልነበረም፡፡

በአንደኝነት ያላጠናቀቀበት ውድድርም ማግኘት አዳጋች ነበር፡፡ ‹‹ቱር ደ ፍራንስ›› በመባል የሚጠራውን የብስክሌት ውድድር ብዙ ጊዜ አሸንፏል፡፡ በብር ላይ ብር፣ በክብር ላይ ክብር ደርቧል፡፡ እሱ ካለው ዝና የተነሳ የካንሰር ታማሚዎችን የሚደግፈው ‹‹ሊቭ ስትሮንግ›› የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅቱም በርካታ ሚሊዮን ዶላሮች ይጎርፉለት ነበር፡፡ ከእርሱ ጋር መሥራት ‹‹ኩራታችን›› ነው ያሉ ድርጅቶችም ብዙ ነበሩ፡፡ የ44 ዓመቷ ክላውዲያ ፔከንስታይ የበረዶ ላይ መንሸራተት ስፖርተኛ ናት፡፡ ገድሏ እንደሚተርከው ባደረገቻቸው ዓለም ዓቀፍ ውድድሮች 60 ሜዳሊያዎችን አሸንፋለች፡፡

ፍጻሜው

እነዚህ አትሌቶች የሚያመሳስላቸው የዝናና የሀብትን ማማ መቆናጠጥ መቻላቸው ብቻ አይደለም፤ቁልቁል መወርወራቸውም ጭምር፡፡ በተለይም ማሪዮን ጆንስ እና ላንስ አርምስትሮንግ በሚዲያ ፊት ቆመው እያነቡ አድናቂዎቻቸውን ይቅርታ ጠየቀዋል፡፡ መዋሸታቸውን አምነው ተንሰቅስቀዋል፡፡ ሁለቱም የቡድን ጓደኞቻቸውን ምሕረት ለምነዋል፡፡ ሜዳሊያቸውን ተቀምተዋል፡፡ ‹‹አንደኛ›› ሆነው የፈጸሙበት ውድድር ሁሉ ስማቸው ተሰርዞ ቦታው ባዶ ሆኗል፡፡ ከኦሎምፒክ መዝገብ ላይ ቢፋቁም ከሰዉ ልብ እንዳይጠፉ ተማጽነዋል፡፡

ከዚያም የአትሌቶቹ ታሪክ ተቀየረ፡፡ ንፋስን እንደመከተል፣ አየርን እንደመጨበጥ ሆነ፡፡ ዝናውም፣ ገንዘቡም፣ ስፖንሰሩም፣ ክቡሩም ሸሸ፡፡ ሚዲያውም ስማቸውን በመጥፎ እያነሳ ተቀባበላቸው፡፡ በተለይም አርምስትሮንግ ‹‹ኦፕራ ቲቪ›› ላይ ቀርቦ ‹‹የካንሰር ሕመምን ከታገልኩት በኋላ ሁለተኛው የጦር ሜዳዬ ይህ ነው›› ብሎ ሽንፈቱን በፀጋ ተቀበለ፡፡ ልጁ እንደሚያሳዝነው፣ ትምህርት ቤት የጓደኞቹ መጠቋቆሚያ እንደሆነና ይህ ሁሉ የእርሱ ጥፋት መሆኑን በአደባባይ አመነ፡፡

የኀያላኑ የአሸናፊነት ታሪክ ፍጻሜው አሐዱ የሚለው አበረታች መድኃኒት ተጠቅማችኋል (performance enhancing drugs) በሚል በቀረበባቸው ክስ ነበር፡፡ የሚገርመው ማሪዮን ጆንስም ሆነች ላንስ አርምስትሮንግ አበረታች መድኃኒቱን እንዳልተጠቀሙ ሲክዱ ቆይተዋል፡፡ ‹‹ሐሰት››፣ ‹‹ቅጥፈት›› እያሉ ሲያጣጥሉት ከርመዋል፡፡

በተለይም አርምስትሮንግ ሶፋ ላይ ተኝቶ፣ ብስክሌቱን ግድግዳ ላይ ሰቅሎ የተነሳውን ፎቶ ‹‹ማሸነፌን አላቆምም›› ከሚል መግለጫ ጋር በማኅበራዊ ሚዲያ በትዊተር አሰራጭቶት ነበር፡፡ ይህን ያህል በራስ መተማመኑ ያስገረማት ኦፕራም ስለፎቶው ጥያቄ ጣል አድርጋበታለች፡፡ በምላሹም ‹‹ድርጊቱ ስህተት›› እንደነበር ሲያምን ጊዜ አልፈጀበትም፡፡

ዶፒንግ፣ ዶፒንግ፣ ዶፒንግ

የስፖርት ቅሌት ጣጣው ብዙ ነው፡፡ በቅርቡ እንኳን ማሪያ ሻራፖቫ ከውድድር ታግዳለች፡፡ ክላውዲያም በስዊዘርላንድና ጀርመን ፍርድ ቤቶች መቆም ከጀመረች ይኸው ሁለተኛ ዓመቷን ደፍናለች፡፡ በዚህ ውጣ ውረድ ውስጥም 65,000 ስፖርተኞችን ያቀፈው ፊፍፕሮ ድጋፉን እንደሚሰጣት ቃል መግባቱ ተዘግቧል፡፡

የዚህ ሁሉ መዘዝ ታዲያ ‹‹ዶፒንግ›› ነው፡፡ የዶፒንግ ጦስ ከውድድር እስከመሰረዝ የሚያደርስ ነው፡፡ ለምሳሌ ሩሲያ ብዙ አትሌቶቿ አበረታች መድኃኒት እንደሚጠቀሙ ‹‹ስለተረጋገጠ›› ከሪዮ ኦሎምፒክ ‹‹ታግዳለች››፡፡ ኬንያም ይህ ቅሌት እንደገባ ለጆሯችን እንግዳ አይደለም፡፡ በአገራችንም የዶፒንግ ጉዳይ መነሳት ከጀመረ ከራርሟል፡፡

ስፖርት ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ በቅርቡ እንደሰማነው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በ2016-17 የውድድር ዘመን ከቴሌቭዥን ሽያጭ ብቻ እስከ 5 ቢሊዮን ፓውንድ እንደሚያገኝ ይጠበቃል፡፡ ለዚህም ይመስላል ተጫዋቾችም ሆኑ አትሌቶች ተገቢ ባልሆነ መንገድ አሸናፊ እንዳይሆኑ እና ገቢ እንዳያገኙ ጥብቅ የዲሲፕሊን ቁጥጥር የሚደረግባቸው፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስለ ዶፒንግ ወይም ስለ ስፖርት ዲሲፕሊን ማብራራት አይደለም፡፡ ይህ ራሱን የቻለ ጥናት እና ሙያ የሚፈልግ ነው፡፡ ነገር ግን ከስፖርት እና ዶፒንግ ጋር የተያያዘ የሕግ ጉዳይ ካለ እሱን መፈተሽ ነው፡፡

የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት ‹‹CAS››

‹‹CAS›› ቅጽል ነው፤ መጠሪያው ‹‹የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት (The Court of Arbitration for Sports /CAS/)›› ይሰኛል፡፡ ውልደቱ እ.ኤ.አ 1984 ሲሆን ከስፖርት ጋር የተያያዙ አለመግባባቶችን በግልግል እንዲፈቱ ታስቦ የተቋቋመ ሲሆን ለዚሁ ዓላማ ሲባል የግልግል ደንብ አለው፡፡ CAS ተጠሪነቱ ለዓለም ዓቀፉ የስፖርት ግልግል ካውንስል ነው፡፡ CAS ከ87 አገሮች የተውጣጡ 300 የግልግል ዳኞች አሉት፡፡ በዓመትም ከ300 በላይ ጉዳዮች እንደሚመዘገቡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህ የግልግል ዳኞች የሚያሳልፉት ውሳኔ እንደማንኛውም ፍርድ ቤት ውሳኔ ተፈጻሚ ነው፡፡

በኒው ዮርክ፣ በሲድኒ፣ በስዊዘርላንድ ቋሚ የግልግል ችሎቶች ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን እንደ ኦሎምፒክ ያለ ትልልቅ የስፖርት መርሐ ግብሮች ሲከናወኑ መርሐ ግብሩ በሚካሄድበት ቦታ ጊዜያዊ ችሎቶች ይቋቋማሉ፡፡ የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤቱ አትሌቶችን፣ ክለቦችን፣ የስፖርት ፌዴሬሽኖችን፣ ትልልቅ የስፖርት ፕሮግራም አዘጋጆችን እንዲሁም ስፖንሰሮችን ወይም የቴሌቭዢን ተቋማትን የግልግል ዳኝነትን ፈልገው ከመጡ ያስተናግዳል፡፡

በተጨማሪም እንደ ወርልድ አንቲ ዶፒንግ ኤጀንሲ (World Anti Doping Agency) ያሉ ትልልቅ ተቋማት ከዶፒንግ ጋር በተያያዘ በአትሌቶች ላይ የሚያሳልፉት ውሳኔ ለግልግል ሊቀርብ ይችላል፡፡ አንድ ጉዳይ ወደ ስፖርት ግልግል ፍርድ ቤቱ እንዲሄድ በጽሑፍ ውል መደረግ ይኖርበታል አሊያም አንድ ተቋም በመተዳደርያ ደንቡ መሠረት ማንኛውም ጉዳይ በግልግል መታየት አለበት ብሎ መፍቀድ አለበት፡፡

ለምሳሌ የኦሎምፒክ ቻርተር አንቀጽ 61 ከኦሎምፒክ ጨዋታዎች ጋር የሚገናኙ ማንኛውም አለመግባባቶች የሚፈቱት በ‹‹CAS›› እንደሆነ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም ከዶፒንግ ጋር የተያያዙ ወርልድ አንቲ ዶፒንግ ኤጀንሲ የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች መቅረብ ያለባቸው ለስፖርት ግልግል ችሎቱ ነው፡፡

‹‹CAS›› የሚጠቀመው ቋንቋ እንግሊዘኛ ወይም ፈረንሳይኛ ነው፡፡ የግልግል ችሎቱም ሦስት ዳኞች ይኖሩታል፡፡ ከሳሽና ተከሳሹ ከሚቀርብላቸው ዝርዝር ውስጥ አንድ አንድ ገላጋይ ይመርጡና ሁለቱ ዳኞች ሰብሳቢውን ዳኛ ይመርጣሉ፡፡ በዚህ ሂደትም ተከራካሪዎቹ ሕግ የመምረጥ መብቱ አላቸው፡፡ ነገር ግን ግልግሉን የሚመራው ሕግ ካልተመረጠ የስዊዘርላንድ ሕግ ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡

ይግባኙስ?

የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤቱ መቀመጫውን ስዊዘርላንድ ስላደረገ እንደ ስዊዘርላንድ ግልግል ተቋም ይታያል፡፡ ‹‹CAS›› በሚሰጠው ውሳኔ ላይ ይግባኝ የሚቀርበውም ለስዊዘርላንድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን በፍሬ ነገር ደረጃ አይመረምርም፡፡ ነገር ግን የሥነ ሥርዓት ግድፈት ካለበት ወይም ውሳኔው ለስዊዘርላንድ ‹‹ፐብሊክ ፖሊሲ›› ተቃራኒ ከሆነ ብቻ ጉዳዩን አስቀርቦ ይመረምራል፡፡

ሲጠቃለል

ግልግል ከውል ግንኙነቶች ውጪ በስፖርቱ ዓለምም ተፈጻሚነት ያለው ነው፡፡ በቅርቡ እንኳን ከሥልጣናቸው የተነሱት ሴፕ ብላተር የፊፋን ጉዳይ ወደ ‹‹CAS›› እንደሚወስዱት መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ በስፖርቱ ዓለም የሚታየው ግልግል በውል ላይ የተመሠረቱ ግንኙነቶችን ብቻ ሳይሆን በአንቲ ዶፒንግ ኤጀንሲ የሚተላለፉ ውሳኔዎችንም የመመርመር ሥልጣን አለው፡፡ ስለዚህ ማንኛውም አትሌት በዶፒንግ ውሳኔ ቅሬታ ቢሰማው ውሳኔውን ለማሻር ጉዳዩ እንዲመረመርለት ለስፖርት ግልግል ፍርድ ቤቱ የማቅረብ መብቱን ማንም አይነፍገውም፡፡ ከስድስት እስከ አሥራ ሁለት ወራት ባሉት ጊዜያትም ውሳኔ ያገኛል።

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Status and Application of Juvenile Related Interna...
Immediate appeal in Ethiopian Arbitration Law?

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 13 December 2024