Font size: +
4 minutes reading time (779 words)

በግልግል ዳኝነት አዋጅ መሠረት የእግድ ትእዛዝ አፈጻጸም

አዋጅ ቁጥር 1237/2013 የግልግል ዳኝነትና የእርቅ አሠራር አዋጅ የሚል ርዕስ ተሰጥቶታል፡፡ የአዋጁን ሰፊ ድርሻ የሚወስደው በግልግል ዳኝነት ሂደት ላይ ስላሉ ነገሮች ድንጋጌዎችን በማውጣት ነው፡፡ ቀሪው ደግሞ ስለ ዕርቅ /conciliation/ ይናገራል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በግልግል ዳኝነት ሂደት ስለሚሰጡ የዕግድ ትእዛዞች በተለይ አፈጻጸማቸውን ከአዋጁ አንጻር መመልከት ነው፡፡

አዋጅ ቁጥር 1237/2013 ካስተዋወቃቸው በርካታ አዲስና የሚበረታቱ ነገሮች አንዱ የእግድ ትእዛዝ በግልግል ጉባዔዎች የሚሰጡበትንና እነዚህም የሚፈጸሙበትን መንገድ ማመላከቱ ነው፡፡ በፍትሐብሔር ሕጉ ድንጋጌ መሠረት ይህ አልነበረም፡፡ ሁሉም ሥልጣን ለፍ/ቤት የተሰጠ ይመስል ነበር፡፡ ተከራካሪዎች ይህንን ስለሚያውቁ የግልግል ጉባዔ ሳይቋቋም ለፍ/ቤት ‹‹የግልግል ዳኛ ይሾምልኝ›› የሚል ክስ አቅርበው በዚያውም እግድ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ፡፡ ተቋም አልባ በሆኑ የግልግል ሂደቶች ገላጋይ ዳኞች እግድ ሲሰጡ የፍ/ቤት ማኅተም እንዲደረግላቸው የትዕዛዝ ፋይል ጠበቆች ያስከፍታሉ፡፡ 

በአዲሱ አዋጅ ግን የግልግል ጉባዔው የእግድ ትእዛዝ ለመስጠት ሥልጣን እንዳለው በግልጽ ተመልክቷል (አንቀጽ 20)፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 21 የእግድ ትእዛዝ ለመስጠት ከግምት ውስጥ የሚገቡ ሁኔታዎች

·       የማይካስ ጉዳት የሚደርስ ስለመሆን አለመሆኑ

·       ትዕዛዙ የሚሰጥበት አካል ላይ የሚደርሰው ተጽዕኖ ተመዛዛኝነት እንደሆኑ ተደንግጓል፡፡

በተጨማሪም ትዕዛዙ ሲሰጥ ለዛኛው ወገን የመሰማት ዕድል ሊሰጠው እንደሚገባ በግልጽ ተጽፏል፡፡ እንደነገሩ ሁኔታም የእግድ ትእዛዝ ሲሰጥ ጉባዔው ኪሳራ ሊያስከትል ይችላል ብሎ ካመነ የእግድ ትእዛዝ እንዲሰጠው የጠየቀውን ወገን ዋስትና እንዲያቀርብ ሊያዝ እንደሚችል ለጉባዔው ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ በግልግል ጉባዔው የተሰጠው የእግድ ትእዛዝ እንዴት ሊፈጸም ይችላል የሚለውን መፈተሽ ነው፡፡ በአገር ውስጥ በሚደረግ ክርክር በግልግል ጉባዔው የሚሰጠው የእግድ ትእዛዝ የትእዛዝ ፋይል ተከፍቶ፣ የፍ/ቤት ማኅተም ተደርጎበት፣ ለሚመለከተው መ/ቤት እንዲደርስ ይደረጋል፡፡ ይህ ሁኔታ በዓለም ዓቀፍ የግልግል ዳኝነት ሂደት ምን ይመስላል የሚለውን መመልከት ግድ ይላል፡፡

መቀመጫውን ከኢትዮጵያ ውጪ ያደረገ የግልግል ጉባዔ የእግድ ትእዛዝ ሊሰጥ እንደሚችል የታወቀ ነው፡፡ የዚህ ትእዛዝ አፈጻጸም ሁኔታም በአዋጁ አንቀጽ 25 ሥር ተደንግጓል፡፡ በአንቀጹ መሠረት ‹‹የውጪ ፍርዶችን እውቅና ለመስጠትና ለማስፈጸም በተመለከተ›› የተደነገገው እንዳለ ሆኖ የተሰጠበትን አገር ከግምት ውስጥ ሳያስገባ በጉባዔው የተሰጠ ጊዜያዊ የመጠበቂያ እርምጃ ትዕዛዝ አስገዳጅነት ይኖረዋል፡፡ አዋጁ ለምን የተሰጠበት አገር ከግምት ውስጥ ሳይገባ አለ? በዓለም ዓቀፍ የግልግል ዳኝነት ልምድ እንደምናየው አንድ አገር ከሌላው ጋር የዲፕሎማሲያዊ ችግሮች ውስጥ ሲገባ በዛ አገር ፍ/ቤት ሆነ መቀመጫውን እዛ አገር ባደረገ የግልግል ጉባዔ የተሰጡ ውሳኔዎች አይፈጸሙም፡፡ ይህ አንዱ የዲፕሎማሲያዊ ጫና መግለጫ ሆኖ ያገለግላል፡፡

የተሰጠው የእግድ ትእዛዝ ሊፈጸምለት ካልቻለ ያልተፈጸመለት ወገን ፍ/ቤት ፋይል መክፈት ይችላል፡፡ የእግድ ትእዛዝ አልተፈጸመም ማለት ትእዛዙ የተሰጠበት መ/ቤት ትእዛዙን ተቀብሎ እንደተባለው ገንዘቡን፣ ንብረቱን የማያግድ ወይም ጠብቆ የማያስቀምጥ ከሆነ ማለት ነው፡፡ በውጪ አገር መቀመጫውን ካደረገው የግልግል ጉባዔ የተሰጠ ትእዛዝ ካልተፈጸመ ለፍ/ቤት አቤቱታ ይቀርባል፡፡ ይህንን ለማስፈጸም አቤቱታ የሚቀርበውም ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ነው፡፡

ፍ/ቤቱ በውጪ አገር የግልግል ጉባዔ የተሰጠው የእግድ ትእዛዝ እንዳይፈጸም የሚከተሉትን ነገሮች መመርመር መብት አለው

1.  የተዋዋይ ወገን ችሎታ ማጣት፣ የጸና የግልግል ዳኝነት ስምምነት አለመኖር፣ ለትዕዛዙ ምክንያት የሆነው ጉዳይ በግልግል ዳኝነት የማይታይ ከሆነ፣ ጉባዔው ሥልጣን የሌለው ከሆነ ወይም ጉባዔው ከተሰጠው ሥልጣን በላይ ከሆነ

ሕጋዊ የሆነ የግልግል ዳኝነት ስምምነት መኖር አለመኖር፣ ችሎታ አለመኖር፣ ጉዳዩ በግልግል ዳኝነት ስለመታየት አለመታየት በፍ/ባለዕዳው የሚነሱ የክርክር ነጥቦች ናቸው፡፡ በግሌ እነዚህ ነገሮች በግልግል ጉባዔው ሊጣሩ የሚገባቸው እንጂ ፍ/ቤት ለመመርመር ሥልጣን ሊኖረው አይገባም፡፡ ፍ/ቤት እነዚህን ነገሮች መርምሮ የእግድ ትእዛዙን አላስፈጽምም የሚል ቢሆን በግልግል ሂደት የተያዘውን ክርክር ዋጋ አልባ ሊያደርገው ይችላል፡፡

ይህ ደግሞ አዋጁ በመሠረታዊነት አሳካዋለሁ ብሎ የቆመለትን ዓላማ እንደመተው ነው የሚቆጠረው፡፡ የግልግል ጉባዔው ስለ ተዋዋዮቹ ችሎታ፣ ስለ ግልግል ስምምነቱ ሕጋዊነት፣ ስለ ሥልጣኑ በራሱ መርምሮና አጣርቶ ትእዛዙን ሰጥቷል ተብሎ እምነት ሊጣልበት ይገባል እንጂ ፍ/ቤት እነዚህን ነገሮች ገብቶ ለመመርመር ሥልጣን ሊሰጠው ይገባል የሚል እምነት የለኝም፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 19 መሠረት የግልግል ጉባዔው የራሱን ሥልጣን በራሱ መወሰን ይችላል /competence-competence/ የሚል ዓለም ዓቀፍ ተቀባይነት ያገኘ መርህ ተካትቷል፡፡ የግልግል ዳኝነት ስምምነት ሕጋዊ የሚሆነው ምን ሲሆን ነው? ተዋዋዮቹ ችሎታ አላቸው የሚባለው ምን ሲሟላ ነው? ጉባዔው ሥልጣን የለውም ሲባል ምን ማለት ነው? የሚለው በራሱ የግልግል ጉባዔው የሚታይ ሊሆን ይገባል፡፡ በተለይም ሥልጣንን በተመለከተ በአዋጁ የተጻፈው ነገር አደናጋሪ ነው፡፡ ማለትም የእግድ ትእዛዝ የሚሰጠው ወደ ክርክሩ ሳይገባ ወይም መቃወሚያ ሳይሰማ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ጉባዔው ያልተመለከተውን፣ ያልመረመረውንና በሕግ ያልመዘነውን ሥልጣን ፍ/ቤት እንዴት ሊመዝነው ይችላል? የግልግል ጉባዔው ሥልጣኑን መወሰን የሚችል ከሆነ ፍ/ቤቱ ስለምን የግልግል ጉባዔውን ሥልጣን ይመረምራል?

2. ጊዜያዊ የመጠበቂያ እርምጃ ትእዛዙን መቀበል ወይም ማስፈጸም ከሕዝብ ሞራልና ፖሊሲ ጋር የሚቃረን ሆኖ ሲያገኘው

በአዋጁ ከለ-መ የተቀመጡ ምክንያቶች ሲኖሩ በዚህ ጽሑፍ ግን ሁሉንም መመልከት አስፈላጊ አይደለም፡፡ ይልቁንም የእግድ ትእዛዙ ከሕዝብ ሞራልና ፖሊሲ ጋር የሚቃረን ከሆነ አይፈጸምም ሲል የተቀመጠውን መመልከት ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በውጪ አገር የተሰጡ የግልግል ውሳኔዎችን ለማስፈጸም በ1948 ዓ.ም በወጣው የኒው ዮርክ ስምምነት አንቀጽ 5 መሠረት አንድ የግልግል ውሳኔ ‹‹ከሕዝብ ፖሊሲና ሞራል›› ጋር የሚጋጭ ከሆነ አይፈጸምም፡፡ የእግድ ትእዛዝን ለማስፈጸምም ሕጉ ተመሳሳይ ነገርን እንደመረጠ እንመለከታለን፡፡ ነገር ግን ሞራልና ፖሊሲ ምን ማለት ነው? የአንድ አገር ‹‹የሕዝብ ሞራል›› በምን ይወሰናል? በባሕል፣ በሃይማኖት፣ በእሴት? ለአንዱ ሞራላዊ የሆነው ነገር ለሌላዊ ኢሞራላዊ ቢሆንስ? የሞራል መለኪያውስ ምንድነው? እነዚህ ጥያቄዎች በቀላሉ መልስ የሚያገኙ አይደሉም፡፡ ሞራል እንደዘመኑና የኅብረተሰቡ አቀባበል ተለዋዋጭ ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ የእግድ ትእዛዝ ኢሞራላዊ ስለሆነ አይፈጸምም የሚባል ከሆነ የውሳኔው አፈጻጸም ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥር ነገር አይሆንም?

እነዚህ ነገሮች በአዋጁ መሻሻል ያለባቸው ወይም የባለሙያዎች ውይይት የሚያስፈልገው ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር ‹‹አዲስ አበባ ዓለም ዓቀፍ የግልግል ዳኝነት ማዕከል›› የሚል ተቋም የማቋቋም ሥልጣን እንደተሰጠው በአዋጁ በግልጽ የተደነገገ ሲሆን በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ ዓለም ዓቀፍ የግልግል ጉባዔዎች ተደርገው ጉዳይ ዐይተው ውሳኔ እንዲሰጡ ብሎም ለአገር ዳጎስ ያለ የወጪ ምንዛሬ እንዲያመጡ ከተፈለገ እንዲህ ዓይነት አንቀጾች መሻሻል ይኖርባቸዋል፡፡  

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

በውርስ ሕግ አተረጓጎም ዙሪያ በተሰጡ አንዳንድ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Tuesday, 22 October 2024