Font size: +
18 minutes reading time (3690 words)

አንዳንድ ጉዳዮች ስለ ግብርና እድገትና የመሬት ፓሊሲና ሕግ

ግብርና የሃገራችን ወሳኝ የኤኮኖሚ ዘርፍ ነው። ምጣኔ ሃብት ምሁሮች እንደሚሉት፥ በቅጥርና አገራዊ ምርት የግብርናው ድርሻ እንዲቀንስ (በሌሎች ዘርፎች እንዲተካ)፥ ግብርናው በፍጥነት ማደግ አለበት። ለማነስ፤ በፍጥነት ማደግ። የግብርና እድገት ምን ይጠይቃል? የመስኖ መሰረተልማት። የተሻሻለ ግብአት፥ ምርጥ ዘር፥ ማዳበሪያ፥ አረም ማጥፊያ። የምርት ገበያ። መሬት። ጉልበት። እውቀት። የገጠር መንገድ። የአርብቶ እና አርሶ አደሮች ትምህርት። የገጠር የጤና አገልግሎት። የገጠር የመጠጥ ውሃ አገልግሎት። የገጠር ሃይል አቅርቦት። የገጠር ሰላምና ደህንነት ማስከበር። የግብርና ግብይቶችን እና ድርጅቶችን መጠበቅ።

እነዚህን ሁሉ ማነው የሚያቀርበው? አሁን ባለበት ሁኔታ እነዚህን ሁሉ በዋናነት የሚያቀርበው መንግስት ነው። የፌዴራሉ መንግስት፥ የክልሎች መንግስታት፥ እና አካባቢያዊ መስተዳድሮች። የእነዚህ ሁሉ ዋና አቅራቢ መንግስት ሆኖ፥ እንዴት ነው ታዲያ ግብርናውን በፍጥነት ማሳደግ የሚቻለው? መንግስት እኮ ከግብርናው በተጨማሪ ሌሎች ሃላፊነቶችም አሉበት።

“እንደሚቻልማ እኮ የባለፊት አስራ አምስት አመታት የግብርናው እድገት ምስክር ነው” ሊባል ይችላል? “ሪፓርት የተደረገውና በእርግጥ የታየው እድገት ተመሳሳይ ናቸው ወይ” የሚል ጥያቄ ይነሳል። እሱን እንተወውና፤ የፓሊሲ ለውጥ በማድርግ ግብርናው እስካሁን ካደገበት በላይ እንዲያድግ ማድረግ አይቻልም ወይ?[1] ይሄን ለመመለስ አማራጭን መሞከርና ማወዳደር ይጠይቃል። በሙከራ የሚረጋገጥ ጉዳይ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፤ የተለየ አማራጭ የተሻለ ውጤት ሊኖረው እንደሚችል ግን መገመት ይቻላል።

የግብርና እውቀት

ለምሳሌ እውቀትን እንውሰድ።[2] ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ ከነበረው ባህላዊ እውቀት ውጭ፥ የገበሬው ብቸኛ የዘመናዊ እውቀት ምንጭ መንግስት ነው።[3] መንግስት ይህን እውቀት በልማት ሰራተኞችና በግብርና ኤክስቴንሽን ፓኬጆች አማካይነት ያቀርባል። በዚህም ምክንያት ዋነኛው የግብርና ባለሙያዎች ቀጣሪ መንግስት ሆኗል። ገበሬው የግብርናን ባለሙያን በስራተኝነት ወይም በአማካሪነት የመቅጠር አቅም የለውም።[4]

መንግስት ብቸኛው የግብርና ባለሙያ ቀጣሪ መሆኑ ምን ችግር ያመጣል? ይህ ጉዳይ ወደ ግብርና ሙያ የሚያስገባውን በር እንዲጠብና ከፍ እንዲል አድርጎታል። የመንግስት የቅጥር ቅድመሁኔታ ከፍ በማለቱ አይደለም። ይልቅስ የግብርና ሙያን በመማርና በዚህም በመስራት የምታጠፋውን የህይወት ጊዜ፤ እንደ ቀሊጥ ወጪ የመቆጠር እድሉን ከፍ ስለሚያደርገው ነው።  ስለዚህ በሆነ አጋጣሚ ግብርና የተማረ ሰው፥ በግብርና ሙያ ቢጀምርም እንኳን፥ በዚህ ሙያ እስከመጨረሻው የመቀጠል ፍላጎቱን ይቀንሰዋል። አንድ ዋና ቀጣሪ ያለው ሙያ በመሆኑ። ስለዚህ ኮምፒዩተር፥ ወይም አካውንቲንግ እና ሌላ ትምህርትና ሙያ በፍጥነት በመቅሰም፥ ከግብርናው ለመውጣት ይሞከራል።[5]

ከዚህ የሚከፋው ደግሞ መንግስት የሚያቀርበው የግብርና እውቀት አቅርቦት በማእከል የሚዘጋጅ መሆኑ ነው። በመሆኑም በገበሬውና በገበያ የሚፈለገው እውቀት ሳይሆን የሚቀርበው፤ የመንግስት ባለሙያዎችና አመራሮች ያስፈልጋል ብለው የሚያምኑት እንጂ። አንድ ድርጅት ሊያስተናግደው የሚችለው የስራና ቴክኖሎጂ ብዝሃነት ውስን ነው። ስለዚህ ለሁሉም አይነት ተፈላጊ እውቀት ኤክስቴንሽን ፓኬጅ ይዘጋጅለታል ማለት አይደለም።

ዝንጅብል ተመርቶበት በማያውቅ አካባቢ የሚኖር ገበሬ፥ ዝንጅብል ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው ቢያውቅና ዝንጅብል ማምረት ቢፈልግ፥ የዝንጅብል ፓኬጅ ይኖራል? የሮዝሜሪ ፓኬጅ ይኖራል? የቀይ ስር ፓኬጅ ይኖራል? የለውዝ ፓኬጅ ይኖራል? መንግስት ብቻ የእውቀት አቅራቢ በሆነበት ሁኔታ ተፈላጊው እውቀት በሙሉ በሚገባ ጥራት፥ መጠን፥ እና ፍጥነት አይቀርብም።

 

ታዲያ ምን ይደረግ?

የግብርና እውቀት (በተለይ ደግሞ ለእኛ ሁኔታ የሚያስፈልገው እውቀት) በቀላሉ የሚገኝ ነው። በጽሁፍ፥ በቪዲዮ፥ በድምፅ። ችግሩ እነዚህ እውቀቶች በውጭ ቋንቋ መሆናቸው ነው። ሁለተኛ፥ እነዚህን እውቀቶች በቀጥታ መተግበር ያስቸግራል። ከመሬቱ አይነት፥ ከአየር ጸባዩ ጋር ማስማማት ያስፈልጋል። ስለዚህ በዚህ ረገድ በፈጣን ሁኔታ ያለውን እውቀት ለመጠቀም የሚያስፈልገው፤ በፈጣን ሁኔታ የእውቀት ድለላና ማጣጣም ስራን መስራት ነው። ይህ ደግሞ በመንግስት ብቻ በማእከል ሊሰራ አይችልም። የተለያዩ ድርጅቶች (በትርፍና ያለትርፍ የሚሰሩ) በዚህ ስራ እንዲገቡ ማድረግ ይቻላል። “ግን እኮ ገበሬው ከእነዚህ ድርጅቶች እውቀትን የመግዛት አቅም የለውም” ሊባል ይችላል። እውነት ነው። አንዱ አማራጭ፥ የቃና ቴሌቪዥን ሞዴልን መከተል ነው። ቃና መዝናኛን ዴሞክራታይዝ እንዳደረገው ሁሉ፥ ተመሳሳይ ሞዴል የግብርናን እውቀት አቅርቦት ዴሞክራታይዝ ሊያደርገው ይችላል። ቃና ቴሌቪዥን ገቢ የሚያገኘው ከተመልካች ክፍያ ሳይሆን ከማስታወቂያና ስፓንሰር ስለሆነ። በዚህ ረገድ የመንግስት ሚና የግብርና ቴሌቪዥን መሰረተልማትን በመዘርጋት፥ የግብርና እውቀትን የሚያሰራጩ ድርጅቶች ክፍት በማድረግ፤ እሱ በኤክስቴንሽን ፓኬጅ ከሚያቀርበው እውቀት በላይ ገበሬው ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል።

 

የመስኖ አቅርቦት

የመስኖ አቅርቦትን መውሰድ ይቻላል። ገበሬው የመስኖ መሰረተ ልማትን የሚጠበቀው ከመንግስት በሆነበት በአሁኑ ጊዜ እንዴት ነው አስፈላጊው መሰረተልማት በሚፈለገው መጠን እና ጥራት በፍጥነት ሊቀርብ የሚችለው። ከብዙ ጊዜ ስራ በኋላ አሁንም የመስኖ ተደራሽነት እጅግ ዝቅተኛ ነው። መንግስትም በማእከል ሲስራ ትንንሽ የመስኖ ቴክኖሎጂዎች ሳይሆን የሚታዩት ግዙፎቹ ናቸው። እነሱ ደግሞ ብዙ ጊዜና ገንዘብ ይወስዳሉ። በታቀደላቸው ጊዜና ወጪ አያልቁም።

 

የመሬት አቅርቦትና መበጣጠስ

የመሬት አቅርቦትን መመልከት ይቻላል። አቅራቢው መንግስት ነው። በተለይ በተለምዶ ቅይጥ ግብርና በሚከተሉ የሃገራችን ከፍተኛ ቦታዎች፥ ውስን የመሬት አቅርቦት ነው ያለው። የመሬት መበጣጠስ ይስተዋላል። ባደኩበት አካባቢ የገበሬው ቦታ በሶስት ወይም አራት ቦታዎች ተበጣጥሶ የተለያየ አካባቢ ይገኛል። አንድ ገበሬ ግማሽ ኳስ ሜዳ የምታክል ቦታ በጓሮው ይኖረዋል። ከዛ እሷን የምታክል ቦታ ከመኖሪያው ሶስት ኪሎሜትር ርቆ ሊኖረው ይችላል። እንዲሁም በሌላ አቅጣጫ በተመሳሳይ ርቀት ሌላ ተመሳሳይ ቦታ ይኖረዋል። ለምን እንዲህ ተበጣጠሰ? የአፈሩ አይነት የተለያየ ስለሚሆን ለሁሉም ከሁሉም የአፈር አይነት እንዲደርሰው ለማድረግ ሲባል። ለፍትሃዊ የመሬት ክፍፍል ሲባል።

እንዲህ መሆኑ ምን ያመጣል? ገበሬ በመሬቱ ላይ የሚያስፍልገውን መዋእለ ንዋይ በበቂ ሁኔታ እንዳያፈስ ያደርገዋል። እንዲህ ባይበጣጠስ ኖሮ፥ ለምሳሌ የጉድጓድ ውሃ በማሽን ሊያስቆፍር ይችል ይሆናል። አሁን ግን ሶስቱን የተለያዩ ቦታዎች በማሽን ለማስቆፈር አይችልም። ስለዚህ በቀላሉ የሚያደርገው በእጅ የጉድጓድ ውሃ መቆፈር ነው። ያም ቢሆን በጓሮው እንጂ በሌሎቹ መሬቶች ላይ አይሞክረውም። ማን ሊጠብቅለት? ለዛውም በትንሽ እርቀት የጉድጓድ ዉሃ ከተገኘ ነው።

መሬት በዚህ መልኩ መበጣጠስ፤ የመሬት ለምነትን ለመጠበቅ አያነሳሳም። አንድ ገበሬ ብቻውን በዛ ትንሽ መሬት የአፈርን ለምነት ለመጥበቅ የሚሰራው ስራ ምንም ያህል ውጤት አያመጣም። ለምሳሌ የችግሩ ምንጭ መነሻው የሱ መሬት ሳይሆን ከሱ በላይ የሚገኝና በሌሎች ገበሬዎች የተያዘ ቦታ ሊሆን ይችላል። እንዲሁም የዘር አይነትን በመምረጥ፥ ግብአትን በመጠቀም የሚያመጣው ውጤት ውስን ነው። ምክንያቱ የመሬቱ ማነስ ሳይሆን መበጣጠስም ነው። በአንዱ መሬቱ ምርጥ የበቆሎ ዘር ቢዘራና ማዳበሪያ ቢጠቀም፥ የሚገኘው ውጤት በስራውና ባፈሰሰው መዋእለ ንዋይ ብቻ ሳይሆን፥ መሬቱ ባለበት ተፋሰስ ያሉ ሌሎች ገበሬዎች በዘሩት ሰብል እና በስራቸው መጠን እና ጥራት ነው።

አሁን ባለበት ሁኔታ፥ በመሬት መበጣጠስ ያለውን እንዲህ አይነት ችግር ለመፍታት የተሞከረው፤ ገበሬዎች በማህበራት እንዲድራጁ በማድረግና የአፈር ጥበቃ ስራን በጋርዮሽ በመንግስት እንዲሰራ ማድረግ ነው። ስለዚህ የመንግስት ፓሊሲ የሚያመጣውን ችግር ለመፍታት የተሞከረው ለመንግስት ተጨማሪ ሚና በመስጠት ነው። የአፈር ጥበቃ ስራን በማእከል እንዲመራ በማድረግና ገበሬዎች በማህበራት እንዲደራጁ በማድረግ። በዘመቻ የሚሰራ አፈር ጥበቃም ሆነ ማህበራት በራሳቸው ሰፊ የተነሳሽነት፥ የትጋትና የማስተዳደር ችግር ያለባቸው ናቸው።

 

የመሬት ግብይት

ገበሬው መሬቱን መሸጥ አይችልም። በተወሰነ ደረጃ ማውረስና ማከራየት ብቻ ይችላል። ለምሳሌ መሬትን ለሌላ ሰው ለተወሰነ ጊዜ (እንደ ክልሎቹ ሕግ የሚለያይ) ማከራየት ይችላል። ነገር ግን ተከራዩ መሬቱን የሚፈልገው ለግብርና መሆን አለበት። ለሌላ አላማ የሚፈለግ ሰዉ፤ መሬትን ከገበሬ መከራየት አይቻልም። እንዲሁም እንደ ክልሉ ሕግ፤ ገበሬው መሬቱን ሙሉ ለሙሉ ማከራየት አይችልም። የተወሰነውን ብቻ ነው። መሬቱን አስይዞ መበደር አይችልም። እንዲህ አይነት ድንጋጌዎች በግብርናው ዘርፍ የሚደረጉ ግብይቶችን ይቀንሳሉ። የብድር ምንጭን ይቀንሳል። የክራይ ዋጋ እንዲወድቅ ያደርጋል። መሬቱን ለሌላ አላማ የሚፈልጉ ተከራዮችን ከገበያው በማስወጣት። ተበጣጥሶ ያለን መሬት በመከራየትና በመሰብሰብ፥ የተሻሻሉ የግብርና ግብአቶችን መጠቀም፥ ጠንክሮ መስራት ውጤት እንዲኖራቸው ለማድረግ ያለው እድል ዝቅተኛ ነው። እንዲሁም ባለገንዘቦች ጥልቅ የጉድጓድ ዉሃን ብዙ ገንዘብ በማውጣት አስቆፍረው፥ የመስኖ አገልግሎትን ለገበሬው ለማቅረብ፥ ወይም ባለሃብቶች ከገበሬዎች ጋር በመዋዋል፥ በገበሬው መሬት ላይ የማዘዝ መብትን ባለሃብቱ በኪራይ ወይም ደግሞ በትርፍ ድርሻ በመውሰድ የተሻሉ ግብአቶችን በመጠቀም፤ የግብርና ምርትን ለመጨመር ያለው እድል ዝግ ወይም እጅግ ጠባብ ነው።

መሬት ላይ ያሉት ገደቦችን ለመሞገት የሚቀርቡ ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች እነዚህ ናቸው። አንደኛ፤ ገበሬው በጊዜያዊ ችግር መሬቱን ሙሉ ለሙሉ አከራይቶ ስራ አጥ የከተማ ኗሪ እንዳይሆን። ሁለተኛ፤ መሬት የህዝብ ስለሆነ መሸጥና በእዳ መያዝ የለበትም።

የመጀመሪያውን ሙግት እንመልከት። ገበሬው መሬቱን ሙሉ ለሙሉ እንዲያከራይ ቢፈቀድ፥ በእርግጥ ከግብርናው ሙሉ ለሙሉ የሚወጣ ጉልበት ይኖራል። ይህ ጉልበት ግን በሌላ የኤኮኖሚ መስክ ላይ በማሰማራት ምርታማ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል። ሁለተኛ የመሬቱ ተከራይ ራሱ ጉልበት ይፈልጋል። ስለዚህ ገበሬው ከኪራይ በተጨማሪ በቅጥር ደመወዝ ሊያገኝ ይችላል።

ሁለተኛውን ሙግት እንመልከተው። መሬት የሕዝብ መሆኑ፥ መሬትን በእዳ ከማስያዝ የሚከለክል አይሆንም። ዞሮ ዞሮ ገበሬዉ በእዳ የሚያስይዘው የመሬቱን ባለቤትነት ሳይሆን በመሬት የመጠቀም መብቱን ነው። መሬቱን ለአስርም ይሁን ለሃያ አመት የመጠቀም መብት እስካለው ድረስ፥ ለምን ይህን መብቱን በእዳ እንዲያስይዝ አይፈቀድለትም።

ገበሬው መሬቱን ሙሉ ለሙሉ እንዲያከራይ ብቻ ሳይሆን መፈቀድ ያለበት፥ አሁን ያለውን “መሬትን ለግብርና ስራ ብቻ ነው ማከራየት የሚቻለው” የሚለው ገደብ ራሱ መነሳት አለበት። ያለበለዚያ መሬቱን በሙሉ ማከራየት መቻሉ ብቻ የሚያመጣው፤ የኪራይ ዋጋ መውደቅን ነው። ብዙ መሬቶችና ጥቂት ተከራዮች እንዲኖሩ በማድረግ።

በተጨማሪ በመሬት አስተዳደር ያሉ ቅሬታዎችን እና ብልሹ አስራሮችን ለማጥፋት ይረዳል። አሁን ባለው አሰራር፥ መሬትን ከግብርና ውጭ ላሉ ስራዎች የሚፈልግ አካል፥ ይህን መሬት ማግኘት የሚችለው በሊዝ ከመንግስት በመከራየት ነው። መንግስት ደግሞ ይህን መሬት የሚያገኘው ከገበሬው በመውረስ ነው። ከገበሬው ወርሶ ለባለሃብቱ በሊዝ ያከራየዋል። የሕዝብ ጥቅም የሚያስከብር እስከሆነ ድረስ። ለገበሬው ካሳ እስከከፈለ ድረስ።

አንድ ገበሬ መሬቱን በማረስ በአመት መቶ ሺ ብር ያህል ይጠቀማል እንበል። ይህን መሬት መከራየት የሚፈልግ ሰው ቢያንስ በአመት መቶ ሺ ብር በኪራይ መክፈል መቻል አለበት። ይህ የሚሆነው ደግሞ መሬቱን በመከራየት ከመቶ ሺ በላይ ጥቅም ማግኘት ሲችል ነው። እንበልና መሬቱን ቢከራይ ይህ ሰው በአመት የተጣራ ሁለት ሚሊዮን ብር ያገኛል እንበል። በዚህ ጊዜ ይህን መሬት በመቶ ሃምሳ ሺ ቢከራየው ያዋጣዋል። ገበሬውም ቢያከራየው ያዋጣዋል። በዚህ ግብይት ሁለቱም ወገኖች ተጠቃሚዎች ናቸው። ሃገርም እንዲሁ። መሬት የላቀ ውጤት ባለው ስራ እንዲውል ያደርጋል። ይህ ክራይ ሕጋዊ የሚሆነው ግን አንደኛ ተከራዩ መሬቱን የፈለገው ለዘመናዊ ግብርና ከሆነ ነው። ሁለተኛ አከራዩ ከዚህ ከሚያከራየው መሬት በተጨማሪ ሌሎች መሬቶች ሊኖሩት ይገባል፤ ሙሉ መሬቱን ማከራየት ስለማይችል። በእነዚህና ሌሎች ችግሮች ምክንያት የተነሳ ይህ ኪራይ የማይፈቀድ ነው እንበል። 

ታዲያ ፈላጊው ይህን መሬት በሌላ በምን መልኩ ሊያገኝው ይችላል? መሬቱን ከመንግስት በሊዝ ሊያገኘው ይችላል። ሊዙ ከ40 እስከ 99 አመታት ሊሆን ይችላል። መንግስት ደግሞ ከገበሬው በመውረስ። ለገበሬው የሚከፈለው ካሳ፥ መሬቱን እንዲያከራይ ቢፈቀድለት ኖሮ ከሚያገኘው ጥቅም ጋር ተቀራራቢ ነው? ገበሬው ይህን መሬት እያረሰ በአመት የተጣራ መቶ ሺ ብር ካገኘ፥ ይህ አመታዊ ገቢ መሬቱ በሊዝ በሚቀርብበት አመታት ተባዝቶና ዲስካውንት ተደርጎ የሚገኘው ያህል በካሳ ይከፈለዋል? አይከፈለውም። እንደውም የሚባለው፥ ባለሃብቱ በሜትር ካሬ ብዙ ሺ ብር እየከፈለ፥ ለገበሬው ግን በሄክታር ከሃምሳ ብር እጅግ ባነሰ ተመን ተስልቶ ካሳ ይከፈለዋል። ኪራይ ወርሃዊ ወይም አመታዊ ሲሆን፥ ካሳ ግን አንዴ የሚከፈል ነው። ታዲያ በዚህ የሚጠቀመው ማን  ነው? በመሬት ኪራይ ላይ የተጣሉ ገደቦች፥ ገበሬው በመሬቱ በመስራት የሚያገኘውን ጥቅም መቀማት አይደለም ወይ? መሬትን በነፃ እንዲያከራይ መፍቀድ ነው ወይስ መሬትን ካሳ እየከፈሉ በመውረስና ለባለሃብት በመስጠት፤ የትኛው ነው ገበሬዎች ገጠርን አየተው ስራ አልባ የከተማ ነዋሪዎች እንዲሆኑ የሚያደርገው?

የሚከፋው ደግሞ፥ በመሬት መውረስ አስራር፥ መሬት የሚወረሰው ለሕዝብ ጥቅም ነው ቢባልም፥ “የሕዝብ ጥቅም ያስከብራል ወይ” የሚለው ጉዳይ እንደ ተወረሰው መሬት የሚታይ ነው። ይህን የሚወስነውም መንግስት ሲሆን፥ በፍርድ ቤት በይግባኝ የማይፈተሽ ነው። ይህ በሆነበት ሁኔታ እና የካሳው መጠንም ገበሬው መሬቱን ከመወረሱ በፊት ከመሬቱ ከሚያገኘው ገቢ ጋር የማይመጣጣን በሆነበት ሁኔታ እና ካሳውን የሚከፍለው ባለሃብቱ ሳይሆን መንግስት በሆነበት ሁኔታ፥ የመሬቱ መወረስ ሕዝብን እንደሚጠቅም እንዴት መተማመን እንችላለን?

ከላይ ባለው ምሳሌ ገበሬው ከመሬቱ የሚያገኘው አመታዊ ጥቅም መቶ ሺ ሲሆን ባለሃብቱ ግን ከተመሳሳይ መሬት የሁለት ሚሊዮን ያህል ምርት ያግኝበታል። ይህን ሕዝባዊ ጥቅም ልንለው እንችላለን (ይህም ቢሆን ሙግትሊቀርብበት ይችላል)። እንበልና ባለሃብቱ መሬቱ ቢሰጠው ከመሬቱ የሚያገኘው አመታዊ ምርት፥ ሃምሳ ሺ ብር ብቻ ነው። እንዲህ አይነት ሰው መሬቱን እንዲከራይ ቢፈቀድለትም፥ ገበሬው ሊጠይቀው የሚችለውን ኪራይ መክፈል አይችልም። ስለዚህ በኪራይ መሬቱን አያገኝም። ማግኘትም የለበትም፥ ከሕዝብ ጥቅም አንጻር። ነገር ግን በኪራይ ማግኘት የማይችለውን መሬት፥ መንግስት ወርሶ በሊዝ መልክ ለባለሃብቱ እንደማይሰጠው እንዴት እርግጠኛ መሆን እንችላለን?

መሬትን ከግብርና ውጭ የሚፈልጉ አካላት መሬትን ማግኘት የሚችሉት ከመንግስት ብቻ መሆኑ፥ እነዚህ አካላት ምርጫ እንዳይኖራቸው፥ በተለይ ደግሞ የመንግስት አስራር ብልሹ ከሆነም፥ መሬት ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ የተነሳ መዋእለ ንዋያቸውን እንዳያፈሱ የሚደረጉ ይኖራሉ። ስለዚህ ገበሬዎች በመሬታቸው ያላቸውን የግብይት ነጻነት መጨመር፥ ገደቦችን ማንሳት፥ ለባለሃብቶች አማራጭ በማቅረብ፥ የተሻለ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴዎችና ምርታማነት (ከግብርናው ውጭ) እንዲኖር ያደርጋል።

ባጭሩ ግብርናን ለማሳደግ የሚያስፈልጉ ግብአቶች፥ ገበያዎች፥ እውቀቶች፥ መሬትና የመሳሰሉት ጉዳዮችን መንግስት በብቸኝነት እያቀረበ፥ ግብርናው እያደገ እንደሆነ ሪፓርት ይደረጋል። በእነዚህ አቅርቦቶች በትርፍና ያለትርፍ የሚሰሩ ድርጅቶች ቢሰማሩ ደግሞ፤ ግብርናው እስካሁን ካደገበት በላይ በሆነ ፍጥነት፤ ሊያድግ ይችላል። ይህ ግን በዋናነት የመሬት ሕጉን እና የግብርና ግብይቶችን የሚገዙ ሕጎችን መቀየርና ማዳበር ይገባል። ሃሳቡን አንድ ጊዜ በመላው አገር ባንተገብረውም፥ በተወሰኑ ቦታዎች ግን መሞከር አይገባም ወይ?

በግብርና እና መሬት ግብይቶችን በማበረታታት፥ መንግስት ለግብርናው ዘርፍ ማደግ ያለበትን እጅግ ሰፊ ሃላፊነት መቀነስ ይቻላል። እውቀትና መዋእለ ንዋይ በግብርናውና በገጠሩ ክፍለኤኮኖሚ በሰፊው በተለያዩ ድርጅቶች እንዲፈስ ያደርጋል። በዚህም የመንግስት ሚና ይቀንሳል። በተወሰኑ ስራዎች (ለምሳሌ እጅግ ግዙፍ የመስኖ መስረተ ልማቶች) ላይ በማተኮር፥ የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ ያደርጋል። የተሻለ የመሬትና የአፈር ጥበቃ ውጤቶችን ማስመዝገብ ይቻላል። በእርግጥ ገበሬዎች መሬታቸው እያከራዩ ከተማ እንዲሰበሰቡ ሊያደርግ ይችላል። ያም ቢሆን ኪራይ አንዴ እንዳይከፈል፥ ወርሃዊ ወይም በየሶስት ወሩ እንዲከፈል በሕግ በመደንገግ፥ በአካባቢዉ አማራጭ የኤኮኖሚ እድሎች ለገበሬዎች በመፍጠር፥ እና በመሳሰሉት የሚፈሩ አሉታዊ ዉጤቶችን መቀነስ ይቻላል። አሁንም ገበሬዎች መሬታቸውን በማከራየት በአካቢያቸው በሚገኙ ትንንሽ የገጠር ከተሞች ቢሰበሰቡም፥ የስራ እድል በመፍጠር ምርታማ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል። ከሁሉም ግን መሬትን ከገበሬዎች ተከራይተው ለሚሰሩ ሰዎች እንደቀድሞው ሁሉ የመጠጥ ውሃ፥ ጤና፥ ሃይል፥ እና የመሳሰሉትን አገልግሎቶች የማቅረብ ሃላፊነት ላይኖርበት ይችላል። ቢኖርበትም በመጠን ትንሽ ይሆናል። መሬታቸውን ላከራዩ ሰዎች እነዚህን አገልግሎቶች ማቅረብ ቢኖርበትም፥ በትንንሽ የገጠር ከተሞች ስለሚሰበሰቡ፥ አገልግሎት የማቅረብ ወጪዉን ይቀንስለታል። አሁን በየመንደሩ ትንንሽ የመጠጥ ዉሃ ጉድጓዶችን በመቆፈር የሚያወጣውን ወጪ፥ ገበሬዎች ተሰብስበው በሚገኙባቸው ትንንሽ የገጠር ከተሞች ላይ አንድ ጥልቅ የዉሃ ጉድጓድ መቆፈር ወጪ ይቀንሳል።

 

መሬትን ለረጅም ጊዜ መከራየት የሚቻለው ለዘመናዊ እርሻ ብቻ ነው

አሁን ባለው የመሬት የሕግ ማእቀፍ መሬትን ለረጅም ጊዜ መከራየት የሚቻለው ለዘመናዊ እርሻ ነው። ከእርሻ ውጭ መሬትን ከገበሬ መከራየት እንደማይቻል ከላይ ተገልጿል።  ለእርሻም ቢሆን መሬትን መከራየት የሚቻለው ለሁለት አመታት ብቻ ነው። ከዛ በላይ ከሆነ ተከራዩ መሬቱን ለዘመናዊ እርሻ ማዋል አለበት። በዚህ አግባብ መሰረት አንድ ገበሬ ከሌላ ገበሬ መሬት መከራየት ከፈለገ ለሁለት አመት መከራየት ይፈቀድለታል። ከዚያ በላይ አይችልም። ምክንያቱም እሱም ገበሬ፥ ያኛውም ገበሬ። ከዛኛው ገበሬ በተለየ መሬቱን በዘመናዊ መልክ ካልተጠቀመበት። ዘመናዊ እርሻ የሚባለው ማሽን እና የተለያዩ ዘመናዊ ግብአቶችን የሚጠቀም ነው ብለን አስበን። አንድ አማካኝ ገበሬ እንዲህ የማድረግ አቅም የለውም። እንዲህ አይነት አቅም ያለው የመሬት ተከራይ ካለ፥ መሬቱን በረጅም ጊዜ የኪራይ ዉል ሊያገኘው ይችላል። ችግሩ እያንዳንዱ ገበሬ መሬቱን በሙሉ ማከራየት ሳይፈቀድለት፥ እንዲሁም የእያንዳንዱ ገበሬ እርሻ ከዚህ በላይ እንደተገለጸው ባንድ ቦታ የሚገኝ ሳይሆን ተበጣጥሶ በተለያየ ቦታ በሚገኝበት ሁኔታ፥ ምን አይነት ዘመናዊ እርሻ ነው መሬትን በመከራየት ማካሄድ የሚቻለው የሚል ጥያቄ ያስነሳል? አሁን ባለበት ሁኔታ መሬትን በረጅም ጊዜ የኪራይ ዉል አግኘተው ዘመናዊ እርሻ ያካሂዳሉ የሚባሉት የአበባ አምራቾች ናቸው። ከእነሱ ዉጭ አሁን ባለው የሕግ ማእቀፍ መሬትን ከገበሬ መከራየት የሚችለው እዛው አካባቢ ያለ ገበሬ ሲሆን፥ እሱም በአጭር ጊዜ ዉል ነው። ከዚህ የምንረዳው እውቀት፥ ገንዘብና፥ ቴኬኖሎጂ ወደ ገጠሩ ክፍል በመሳብ የግብርናን እድገት በማፋጠን ረገድ፤ አሁን ያለው የመሬት የሕግ ማእቀፍ ሚና እና አቅም ዜሮ ነው ማለት ይቻላል። በዚህ የሕግ ማእቀፍ የመሬት ኪራይ ፍላጎት እጅግ ትንሽ፥ ነገር ግን አቅራቢው ብዙ በሆነበት ሁኔታ፥ የኪራይ ዋጋ ዝቅተኛ ስለሚሆን፥ ገበሬዎች መሬታቸውን የማከራየት ፍቃዳቸው ዝቅተኛ እንዲሆን እና የመሬት ኪራይ ገበያ አገራዊ፥ ክልላዊ አድማስ እንዳይኖረውና በመንደር እንዲወስን ያደርገዋል።

 

ሰፊ መሬትን ከብዙ ገበሬዎች በኪራይ የማግኘት ችግር

ከዚህ በላይ ባሉት ክፍሎች፥ የመሬት ኪራይን አስመልክቶ የተቀመጡ ገደቦች (ለእርሻ ብቻ መከራየት እና ሙሉ መሬትን ማከራየት አለመቻሉ) ያለባቸውን ችግሮች በማመላከት እነዚህ ገደቦች መነሳት እንዳለባቸው አሳይተናል። እነዚህ ገደቦች ቢነሱ፤ ካፒታል ያላቸው ሰዎች በበርካታ ገበሬዎች ተይዘው ያሉ መሬቶችን በመከራየትና በመጠቅለል ዘመናዊ እርሻ በማከናወን ግብርናው በፈጣን ሁኔታ እንዲያድግ ያስችላል። እነዚህ ካፒታል ያላቸው ሰዎች፥ እውቀትን፥ ግብአትን፥ ገበያን ከመንግስት የሚጠበቁ አይሆንም። በመሆኑም የመንግስትን ሃላፊነትም የሚጋሩ ይሆናሉ። የተበጣጠሱት ተያያዥ መሬቶች በአንድ ዉሳኔ ሰጪ አካል (ሰው ወይም ድርጅት) ሲሰበሰቡ፥ መታረስ የሌለበት ተዳፋት ቦታ ከእርሻ ይልቅ ዛፍ ይተክሉብታል። ምክንያቱም እንዲያ ባያደርጉ በመሬት መሸርሸር፥ ጎርፍ የተነሳ ከተዳፋቱ ታች የሚገኘው የራሱ መሬት አፈር ስለሚጎዳ። እንዲሁም በራሱ ወጪ ጥልቅ የዉሃ ጉድጓድ በመቆፈር ወይም ሌላ መንገድ ዉሃን በመያዝ፥ የመስኖ እርሻን መጠቀም ይጀምራል። መሬት በተበጣጠሰ ሁኔታ እንዲህ አይነት መዋእለ ንዋይን ለጥበቃና ግንባታ ስራዎች ማዋል አያዋጣም። አሁን ባለው አስራር ትልልቅ የመስኖ መሰረተ ልማቶችን እና የጥበቃ ስራዎችን ማካሄድ የሚችለው መንግስት ብቻ ነው።

ይህ እንዲሆን ግን ከዚህ በላይ ያሉ ገደቦችን ማንሳቱ ብቻ በቂ አይደለም። ምክንያቱም መሬት በተበጣጠስበት ሁኔታ መሬትን በኪራይ ለመሰብሰብ ከብዙ ገበሬዎች ጋር መዋዋልን ይጠይቃል። ከአርባ ገበሬዎች ጋር ተከራዩ ተስማምቶ፤ መሃል ላይ ያሉ ሁለት ገበሬዎች አንስማማም ሊሉ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ የኪራይ ድርድሩ ላይሳካ ይችላል። ከብዙ ሰዎች ጋር በሚደረግ ድርድር እና ለድርድሩ መሳካት ሁሉም ሰዎች መስማማት ያለባቸው ከሆነ፥ እያንዳንዱ ሰዉ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ስለሚኖረው፥ ይህን በመጠቀም ከሚገባው በላይ ኪራይ በመጠየቅ፥ ከነአንካቴው ድርድሩ እንዲፈርስ ሊያደርግ ይችላል። ኪራዩ ሁሉን የሚጠቅም ሆኖ እያለ በዚህ ምክንያት ሊፈርስ ይችላል። ይህን ችግር መፍታት ያስፈልጋል።

መፍትሄዉን ግን እኛው ሃገር ካለ ሌላ ሕግ መማር እንችላለን። የንግድ ሕጉ መጽሃፍ አምስት የኪሳራ ሕግ ይባላል። ይህ ሕግ የሚጠቅመው አንድ ነጋዴ ለብዙ ባለገንዘቦች ባለ እዳ በሚሆንበት ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ ይህ ነጋዴ እዳውን ለመክፈል የገንዘብ ችግር ቢያጋጥመው፥ እያንዳንዱ ባለገንዘብ ገንዘቡን ለማስመለስ በሚያደርገው የተናጥል ክስ፥ ንብረት የማሳገድና የመሸጥ ሩጫና ውድድር የተነሳ፥ ንብረት ይባክናል። ተስፋ ያለው ነጋዴም (አገግሞ ሊወጣ የሚችል ቢሆንም) ከገበያው ተገፍቶ ሊወጣ ይችላል። ይህ አይነት ሁኔታ ሃገርንም፥ ባለገንዘቦቹንም፥ ባለእዳውንም አይጠቅምም። ተመሳሳይ እዳ ኖሮበት፥ ባለገንዘቡ ግን አንድ ቢሆን፥ የገንዘብ ችግር ስላለበት ብቻ ንብረቱ ላይሸጥ ይችላል። እዳውን እና አከፋፈሉን አስመልክቶ ከባለገንዘቡ ጋር በመስማማት፥ ንብረቱ ሳይሸጥ የንግድ ስራዉን ሊቀጥል ይችላል። ባለገንዘቡም ቢሆን ገንዘቡን ማግኘቱ አይቀርም። እንዲህ የሚሆነው ግን ነጋዴው ተስፋ እንዳለው ባለገንዘቡ ሲያምን ነው። ባለገንዘቦቹ ብዙ ሲሆኑ ግን ነጋዴዉ ተሰፋ ያለዉ ቢሆንም፥ ባለገንዘቦቹ በሚያደርጉት ሩጫና ውድድር ንግዱ ያከትማል። ንብረት ይባክናል። የኪሳራ ሕግ አንደኛው አላማ ይህን ማስቀረት ነው። ስለዚህ አንድ የገንዘብ ችግር ያጋጠመው ነጋዴ በፍርድ ቤት ቀርቦ ንብረቱ ከመሸጡ በፊት ንግዱ ተስፋ ያለው እንደሆነ በማስረዳት፥ የእዳውን አከፋፈል አስመልክቶ ሃሳብ እንዲያቀርብ እድል ይሰጠዋል። ማንም ባለገንዘብ በተናጥል ንብረትን ለማሳገድ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ይታገዳል። ባለገንዘቦቹ ይጠሩና ስለ እዳው አከፋፈል የቀረበውን ሃሳብ ሰምተው፥ ተወያይተው ድምጽ ይሰጣሉ። ሙሉ ለሙሉ ከተቀበሉት ችግር የለውም። ግን ላይቀበሉት ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ፍርድ ቤቱ አብዛኞቹ ባለገንዘቦች በቀረበው ሃሳብ ከተስማሙ እና በፍርድ ቤቱ ግምገማ የቀረበው ሃሳብ ምክንያታዊ እና ሁሉን የሚጠቅም ነው ብሎ የሚያስብ ከሆነ፥ ምንም እንኳ ጥቂቶች ባይስማሙበትም ሊጸድቅና ሁሉም ላይ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል። ከጠቀማቸውማ እንዴት እንቢ ይላሉ? ሁሉም መስማማት አለበት ማለት፥ እያንዳንዱ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት አለው ማለት ነው። ይህን መብቱን ተጠቅሞ የግል ድርሻውን ለመጨመር ስለሚሞክር፤ ስምምነቱ እንዳይሳካ ይሆናል። በዛ ላይ እያንዳንዱ ሰው በስምምነቱ እኩል ተጠቃሚ ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ አንድ ሰው ከሃምሳ ገበሬዎች መሬትን በኪራይ መውሰድ ቢፈልግ፥ እነዚህ ሃምሳ ገበሬዎች ያላቸው መሬት በመጠንም በጥራትም እኩል ላይሆን ይችላል። ስለዚህ በኪራይ ዉሉ እኩል አይጠቀሙም። በድርድሩ መፍረስ ሁሉም እኩል አይጎዳም። በዚህ ጊዜ እያንዳንዱ መስማማት አለበት ማለት እኩል መሬት ለሌላቸው ሰዎች እኩል መብት መስጠት ነው።

ለመደምደም ያህል፥ መሬት ላይ የተጣሉት ገደቦች መነሳት ብቻውን አይጠቅምም። በኪሳራ ሕጉ ላይ እንዳሉት አይነት ድንጋጌዎችም በመሬት ኪራይ ሕጉ መካተት አለባቸው። ይህ ሲሆን፥ መሬትን ለእርሻና ለተለያዩ ስራዎች በሰፊው ከበርካታ ገበሬዎች ባንዴ በመከራየት ግብርናውን ማዘመን ይቻላል። ከገበሬዎች በመውረስ ለባለሃብት የመስጠት አስራር ያለበትን ችግር ይፈታል።

ኢህአዴግ የአርሶና አርብቶ አደር ፓርቲ

ኢህአዴግ ሕዝባዊ ፓርቲ እንደሆነ ይገልፃል። ሕዝባዊ ፓርቲ ለአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል የቆመ ፓርቲ ነው። በኛ አገር አግባብ ደግሞ አብዛኛው ሕዝብ አርብቶና አርሶ አደር ነው። ባጭሩ የገጠር ፓርቲ ነኝ እያለ ነው። ነገር ግን ከዚህ በላይ የተነሱ ጉዳዮች፤ የድርጅቱ ባለቤት አርብቶና አርሶ አደሩ መሆኑን ያሳያል? ገበሬዎች በመሬታቸው ያላቸውን መብቶችና ግብይቶች በመገደብና ለግብአት አቅርቦት በመንግስት ሞኖፓሊ እንዲታሰሩ በማድረግ እንዴት የገበሬ ፓርቲ መሆን ይቻላል? የኢህአዴግ የገንዘብ ምንጩ ምን ያህሉ ከገበሬው ይገኛል? ገበሬውስ በኢህአዴግ የድርጅት ውሳኔዎችና ምርጫዎች ምን ያህል ተወክሏል?

የብሪታንያ ሌበር ፓርቲ የሰራተኛው ፓርቲ ነው። ፓርቲውን የፈጠሩት የሰራተኛ ማህበራት ናቸው። የፓርቲው ዋነኛ የገንዘብ ምንጭ እነዚህ የሰራተኛ ማህበራት ናቸው። የሰራተኛ ማህበራት በፓርቲው ዉሳኔዎችና የአመራር ምርጫዎች ትልቅ ድምጽ አላቸው። ከመደበኛ አባላት በላይ ድምጽ አላቸው። በዚህም ምክንያት የፓርቲው ፓሊሲዎች በስራተኛው ጥቅም ላይ የሚሽከረከሩ ናቸው። እንዲህ የሆነው የፓርቲው አመራሮች ለሰራተኛው ጥቅም የታመኑ በመሆናቸው አይደለም። ይልቅስ ታማኝነታቸው የመጣው፥ ሰራተኛውን የሚጠቅም ፓሊሲ የሚያራምዱት፥ ሰራተኛውና የሰራተኛው ማህበራት የፓርቲው ዋነኛ የገንዘብ ምንጭ በመሆናቸውና በውስጥ ውሳኔዎችና ምርጫዎች ከፍተኛ ድምጽ ስላላቸው ነው።

የኢህአዴግ የአርብቶና አርሶ አደር ፓርቲነት በተመሳሳይ መልኩ ካልተንፀባረቀ፥ አርብቶና አርሶ አደሩ ዋነኛ የድርጅቱ የገንዘብ ምንጭ ካልሆነ እና የአርብቶና አርሶ አደሩ ማህበራት በድርጅቱ የውስጥ ውሳኔዎችና የአመራር ምርጫዎች እንዲካፈሉ ካልሆነ፥ በአዋጅ ብቻ የድርጅቱ ውሳኔዎች አርብቶና አርሶ አደሩን ይጠቅማል ማለት አይቻልም። በእርግጥ ድርጅቱ ለዚህ እንዲደርስ የአርብቶና አርሶ አደሩ ድጋፍ ከፍተኛ ነው። መንገድ በመምራት። ስንቅና ትጥቅ በማቀበል። መረጃ በማቀበል። የሚበላውን የዱር ቅጠል ከማይበላው ታጋዩ እንዲለይ በማስተማር። እንዲሁም ገበሬውና ልጁ አብሮ በመታገልና መስዋእት በመክፈል። ብዙ የኢህአዴግ አመራርና አባል የገበሬ ልጅ ነው ሊባል ይችላል። እነዚህ ሁሉ ግን “ገበሬው የድርጅቱ ማህበረሰባዊ መሰረት ነው፥ ድርጅቱ የሚሰራዉ ሁሉ ለገበሬው ነው” ብሎ ለማሰብ በቂ አይደሉም። የገበሬው የድርጅቱ ባለቤትነት በተጨባጭ በመወሰን፥ በመምረጥ፥ ገንዘብ በማዋጣት ሊገለጽ ይገባል። የመጀመሪያው እርምጃ ግን የአርብቶና የአርሶ አደሩ ኑሮ መሻሻል የሚያስፈልጉ ነገሮች በሙሉ በመንግስት ሞኖፓል እንዲቀርቡ የማድረግ አሰራር፥ አርብቶና አርሶ አደሩ የኢህአዴግ ባለቤት ሳይሆን፥ ኢህአዴግ የአርብቶና አርሶ አደሩ ባለቤት እንዲሆን የሚያደርግ ነው። ይሄ ጉዳይ በሚገባ ሊመረመር ይገባል።

 


[1] በዚህ ረገድ “የአፈጻጸም እንጂ የፓሊሲ ችግር የለብንም” የሚለውን አነጋገር ልብ ይሏል። አሁን ያለውን ፓሊሲ ተከትለን፥ በአማካኝ 10 ከመቶ በላይ በሚሆን መልኩ አድገናል። ነገር ግን ያደግነው በፓሊሲው የተነሳ ነው ወይስ ፓሊሲውም እያለ ነው እንዲህ ያደግነው? በፓሊሲዉ ነው ከተባለ፤ አፈፃፀማችንን በማላቅ የተሻለ እድገት ልናስመዘግብ እንችላለን። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ፓሊሲው ላይ ማስተካከያ በማድረግ ከዚህም በላይ ማደግ እንደማንችል በምን አወቅን። የፓሊሲ ችግር የለብንም ብሎ መጀመር ከልምድ የመማርን እድልን ያጠባል። ፓሊሲን የሃይማኖት ያህል ቦታ ይሰጣል። በመሆኑም ይህ ሊስተካከል ይገባል። ፓሊሲን በጥብቅ መከታተልና ልምድና መረጃንመሰረት ያደረገ ማስተካከያዎች መውሰድ ያስፈልጋል።

ከዚህ በተጨማሪ አሁን ያሉንን ዋና ዋና ፓሊሲዎች እንኳን ብንወስዳቸውና እንዴት እንደወጡ ብንመረምራቸው፥ የፓሊሲ ችግር የለብንም ብለን አፍ ሞልተን ለመናገር ያዳግታል። በተለይ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ህልፈት ህይወትን ተከትሎ ሁሉንም ፓሊሲዎች ይፅፏቸው የነበሩት እሳቸው እንደነበሩ ጓዶቻቸው ነግረውናል። (እሳቸው ይህን ሲፅፉ እናንተ የት ነበራችሁ? በምን የሞራል ልእልና ነው የእሳቸውን ሌጋሲ እናስቀጥላለን የምትሉት? እንዲህ ብለን እንኳን እልነገርናቸውም።) እንደውም አምስት የሚሆኑ የፓሊሲ ሰነዶች በመለስ ዜናዊ ፋዉንዴሽን የመለስ ዜናዊ ድርሰቶች በሚል ታትመው ለገበያ ቀርበዋል። በእነዚህ ሰነዶች ላይ የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች ሲወያዩ፤ የዉይይቱ አላማ ሰነዶቹን ለማበልፀግ ግብአት መሰብሰብ እንደሆነ ቢነገርም፥ አሁንም ድረስ ሰነዶቹ በመጀመሪያ ህትመታቸው የያዙትን ቅርጽ ይዘው አሉ። እነዚህ የፓሊሲ ሰነዶችስ እውነት ፓሊሲዎች ናቸው? መቼ ነው ለመንግስት ቀርበው (በሚኒስትሮች ምክር ቤትና ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት) የፀደቁት? ሌሎች ፓሊሲዎቻችንስ እንዴት ነው የሚዘጋጁት? እነዚህን ጥያቄዎች ስናነሳ፥ “የፓሊሲ ችግር የለብንም” የሚለው አነጋገር ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይገባ ግልፅ ይሆናል።

[2] ለእድገት የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ምሁሮች በተለያየ መልኩ ይከፋፍሏቸዋል። መሬት፥ ጉልበትና ካፒታል የሚለው ክፍፍል የቆየ ነው። ካፒታል የሚለው አባባል የገንዘብና የማምረቻ መሳሪያዎችን ይጨምራል። አየቆየ መሬት የሚለው አባባል ራሱ ሙሉ አንዳልሆነ እና የተፈጥሮ ካፒታል በሚል ተቀይሯል። የተፈጥሮ ካፒታል የሚባሉት የተለያዩ ታዳሽና የማይታደሱ የተፈጥሮ ሃብቶች መሬትን ጨምሮ፥ እና የስነምህዳር አገልግሎቶችን ያካትታል። ጉልበት የሚለው አባባልም ሙሉ አይደለም። ይልቅስ ሰብአዊ ካፒታል በሚል ቢገለጽ የተሻለ ይሆናል። ሰብአዊ ካፒታል የሰው ጉልበትን እና እውቀትን ይጨምራል። ድሮ ካፒታል በሚል የሚገለጹት አሁን የገንዘብ ካፒታልና ፍብሩክ ካፒታሎች ተብለው ይታወቃሉ። ከእነዚህ ግብአቶች በተጨማር ማህበራዊ ካፒታል (መደበኛና ኢመደበኛ ተቋማት)፥ ዲፕሎማቲክ ካፒታል (በአለም አቀፍ ግንኝነቶች የሃገርን ጥቅም የማራመድ አቅም)፥ እና የፓለቲካ ካፒታል (ቅቡልነት) ሊጨመሩ ይችላል። በአጭሩ ለእድገት የሚያስፈልገው ካፒታል ነው። ካፒታል በተለያየ ቅርፅ ይኖረዋል። የአድገትን ጥራትና መጠን የሚወስኑት ያሉንን ካፒታል በጥራትና በመጠን የመጨመርና ለላቀ ዉጤት የመጠቀም አቅማችን ነው። ከገንዘብ፥ የተፈጥሮ ካፒታል፥ እና ፍብሩክ ካፒታል ይልቅ፥ ለእድገት እጅግ ከፍተኛ አስተዋእጾ የሚኖረው ሰብአዊ ካፒታል ነው። ከጥሬ ጉልበት አልፎ እውቀትን ከጨመረ። የተፈትሮ ካፒታል አላቂ ሊሆን ይችላል። የማያልቀው እውቀት ነው። በተፈጥሮ ሃብት የታደሉ ሆነው አንዳንዶቹ ክፍተኛ የኤኮኖሚ እድገትና ትራንስፎርሜሽን ሲያሳዩ አንዳንድ ሃገሮች ግን በማያቋርጥ ድህነትና ግጭት ይማቅቃሉ። በእነዚህ ሃገሮች መካከል ያለው ልዩነት የተፈጥሮ ሃብታቸውን የተጠቀሙበት አግባብ ነው። የተፈጥሮ ሃብታቸውን ለማያቋርጥ እድገት የተጠቀሙ ሃገራት፥ በእውቀት ላይ ከፍተኛ ስራ ስርተዋል። እውቀት ለእድገት ያለው አስተዋእጾ፥ የማይነጥፍ ነው። ስለዚህ በፈጣን ሁኔታ ማደግ የሚሻ ሃገር እውቀትን በፍጥነት ማስራጨት፥ መጠቀምና አዲስ አውቀትን በፈጣን ሁኔታ ማምረትና መለማመድ አቅም ሊኖረው ይገባል። ስለዚህ ስለግብርናው ፈጣን እድገት ስናቅድ፥ እንዴት በአለም ላይ ያለውን የግብርና እውቀት በፈጣን ሁኔታ ማሰራጨትና ለላቀ ውጤት መጠቀም እንደምንችል አብረን ልናቅድ ይገባል።

[3] መንግስታዊ ያልሆኑ እና ያለትርፍ የሚሰሩ ጥቂት ድርጅቶች እየሰሩ ያሉትን ስራ ሳንዘነጋ።

[4] አንደ አካል በሌላ አካል ያለን እውቀት ሊያገኝ የሚችለው በሶስት መንገድ ነው። አንደኛው ባለእውቀቱን እንደ ሰራተኛ መቅጠር። ሁለተኛ ባለእውቀቱን አማካሪ አድርጎ መቅጠር። በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ስራተኛ በቀን ተቀን ስራው በቀጣሪው ቁጥጥርና መመሪያ የሚሰራ ሲሆን፥ አማካሪ ግን ለተወሰነ ስራ ተብሎ የሚቀጠርና ከቀጣሪው ቁጥጥርና መመሪያ ውጭ ሆኖ ራሱን ችሎ የሚሰራ መሆኑ ነው። በሶስተኛ ደረጃ ባለእውቀቱ እውቀቱን በመጠቀም የሚሰራቸውን ሸቀጦች በመግዛትና በመጠቀም ነው። ለምሳሌ እውቀቱን በመጠቀም መድሃኒት፥ ማሽን ሊሰራ ይችላል። ወደ ግብርናው ስንመጣ፥ በሃገራችን እውቀታቸውን በመጠቀም የግብርና ግብአቶችና ማሽኖችን የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እዚህ ግቡ የሚባሉ አይደለም። ከእጽዋት ፈሳሽ ማዳበሪያ አየሰራ የሚሸጥ ሃገር በቀል ድርጅት እንዳለ አውቃለሁ። ስለሃገራችን ግብርና ስናወራ 18ሚሊዮን የሚገመት ባለትንሽ ማሳ የገበሬ አባና እማ ወራዎች ነዉ የምናወራው። አማካኝ የማሳ መጠን አንደ ሄክታር አካባቢ ነው። እነዚህ ገበሬዎች የግብርና ባለሙያን በሰራተኛነት እና አማካሪነት ቀጥሮ የማሰራት የገንዘብ አቅም የላቸውም። ገንዘቡ ቢኖራቸውም እንኳን፥ የመክፈል ፈቃደኝነታቸው ውስን ይሆናል። እውቀት ክፍሎ ለመግዛት፤ የምትገዛውን እውቀት ጥራት መገምገም መቻል አለብህ። እውቀትን መገምገም ይከብዳል። የምርቱ ጥራትና መጠን፤ ሙሉ ለሙሉ በተጠቀምከው እውቀት ስለማይወሰን።

[5] አንድ ብቻ ገዢ ያለበትን ገበያ በአምራችነት መቀላቀል ይከብዳል። ምክንያቱም የምርትህን ዋጋ የሚተምነው ገዢው ስለሆነ። በዚህ ላይ አንተ ሚና ስለሌለህ። ስለዚህ መጀመሪያውኑ መርጦ የሚገባ አይኖርም። በሆነ አጋጣሚ ብትቀላቀልም እንኳን፥ የአምራችነት አቅምህን ለመገንባት በየጊዜው የምታፈሰው መዋእለ ንዋይ ሌላ ገዢ ስለማያገኝ፥ የምርት አቅምህን ለማበልጸግ ሃብትህን አታወጣም። ይልቅስ ይህን ገበያ ለመልቀቅና ሌላ ገበያን ለመቀላቀል ጥረት በማድረግ ትጠመዳለህ። አማራጭ ስታገኘ፥ በተቻለ ፍጥነት ለቀህ ትወጣለህ። የግብርና ባለሙያ ብቸኛ ቀጣሪ መንግስት መሆኑ፥ የሚኖረው ውጤት ተመሳሳይ ነው። በእርግጥ የግብርና ባለሙያዉ እውቀቱን ከመሸጥ ይልቅ፥ እውቀቱን ተጠቅሞ በግብርና ስራ ላይ ሊሰማራ መቻሉ እንደ አማራጭ ገዢ ሊወሰድ ይችላል። አማራጮች መኖራቸው የግብርና ባለሙያዎች በሙያቸው እንዲቆዩና እንዲያዳብሩ ያደርጋል። ነገር ግን ይህኛው አማራጭ በሃገራችን እጅግ ጠባብ ነው።

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ተጨማሪ ሃሳቦች ስለ ግብርና እድገትና የመሬት ፓሊሲና ሕግ
ደብዳቤው

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 13 December 2024