ግብር ስወራ

በዚህ ጽሑፍ ስለ ግብር ስወራ ምንነት፣ በተለያዩ የግብር ዓይነቶች ሥር የግብር ስወራ ስለሚያቋቋሙ ድርጊቶች፣ ለግብር ስወራ መነሻ ሊሆኑ ስለሚችሉ ምክንያቶች እንዲሁም የመከላከያ መንገዶቹ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ መነሻ የሆነኝ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የጉምሩክና ታክስ ወንጀል ችሎት ዳኛ ሆኜ ስሠራ በነበርኩበት ጊዜ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ለግብር ስወራ የወንጀል ክሶች ለማስረዳት ሲያቀርባቸው በነበሩ የታክስ ኦዲቶች ላይ የሚጠቀሱ ግኝቶች ናቸው፡፡ የተለያዩ የግብር ስወራ ወንጀሎች ፈጽመዋል በማለት ተከሰው በፍርድ ቤት ሲቀርቡ ለነበሩ ተከሳሾች ይቀርብ የነበረው ማስረጃ፣ በታክስ ኦዲተሮች የሚሠራ የታክስ ኦዲት ግኝቶች ዝርዝር የሚገልጽ የጽሑፍ ማስረጃ እንዲሁም ይህንኑ የታክስ ኦዲት የሠሩ ባለሙያዎች በሙያ ምስክርነት ቀርበው የሚሰጡት የምስክርነት ቃል በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሚሠሩ የታክስ ኦዲቶች አንዳንዶቹ በትክክል የግብር ስወራ ስለመፈጸሙ በአግባቡ የሚያስረዱ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በጣም የተጋነኑ፣ ሙያዊ ላልሆነ ግምት የተጋለጡ እንዲሁም ለወንጀል ክስ የማስረዳት ብቃታችው ምክንያታዊ የሆነ እርግጠኝነት የማይፈጥሩ ናቸው፡፡ ግብር ስወራ በአገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚፈጥር የዕድገት ፀር የሆነ ሕገወጥ ድርጊት በመሆኑ፣ መንግሥትም ሆነ ሁሉም ኅብረተሰብ ሊከላከለው የሚገባ ድርጊት ነው፡፡ ነገር ግን ግብር ያልከፈሉ ሁሉ ግብር ሰውረዋል ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ግብር ላለመከፈል መነሻው ግብር መሰወር ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡

በሌላ በኩል ግብር ሳይከፈል የቀረው መክፈል የነበረበት ሰው ለመክፈል አቅም በማጣቱ ወይም መከፈል የሚገባው የግብር መጠን ሳይከፈል የቀረው ጥፋት በሌለበት ስህተት (Genuine error) ምክንያት ሊፈጠር ይችላል፡፡ ግብር ስወራ የሚመለከተው ደግሞ በስህተት ምክንያት ወይም አቅም በማጣት የታወቀ የግብር ግዴታ ሳይከፈል ለሚቀር ግብር ሳይሆን ሆነ ተብሎና እያወቁ የተለያዩ የማታለያ፣ የተንኮልና አሳሳች ነገሮች በመፈጸም ሊከፈል የሚገባ የግብር መጠን እንዲሰወር የሚያደርግ ሕገወጥ አካሄድን ነው፡፡

በአገራችን ግብር አለመክፈል የሚያስከትለው የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ኃላፊነት በተመለከተ ያለው አሠራር ሲታይ ከሕጉ ጋር የተጣጣመ ነው ለማለት የሚያስቸግር ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በመጀመሪያ ግብር አለመክፈል በወንጀልና በፍትሐ ብሔር እንዲሁም በፍትሐ ብሔር ብቻ የሚያስጠይቅባቸው ሁኔታዎች ለየብቻ ተለይቶ ሲሠራበት አይታይም፡፡ በዚህም ግብር የመሰወር ድርጊት የፈጸመ ግብር ከፋይ በወንጀልና በፍትሐ ብሔር ሊጠየቅ ሲገባው የፍትሐ ብሔራዊ ኃላፊነቱ ከተወጣ ጤነኛ ባልሆኑ አካሄዶች እንዲሁም በግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ፈጻሚዎች የግንዛቤ እጥረት ምክንያት የወንጀል ክስ የማይቀርብባቸው ትክክለኛ ያልሆኑ አሠራሮች አሉ፡፡

በሌላ በኩል በፍትሐ ብሔር ብቻ ሊያስጠይቅ በሚገባ ጉዳይ ደግሞ ግብር ከፋዮች ላላስፈላጊ እንግልት የሚዳርግ የወንጀል ክስ ሲቀርብባቸው ይታያል፡፡ ያለአግባብ የወንጀል ክስ የቀረበባቸው ተከሳሾች በፍርድ ቤት በነፃ የሚለቀቁበት ሁኔታ ቢኖርም፣ በፍርድ ቤቶችም ቢሆን ሕጉን በአግባቡ ባለመተርጐም በፍትሐ ብሔር ብቻ በሚያስጠይቅ የግብር አለመክፈል ድርጊት ያለአላግባብ በወንጀል ጥፋተኛ ተብለው ለእስር የሚዳረጉ ብዙ ግብር ከፋዮች እንዳሉም በተለያዩ ጊዜያት በፍርድ ቤቶች ከተሰጡ ፍርዶች መረዳት ይቻላል፡፡ አንዳንዴም የሕግ መሠረት የሌላቸው የግብር ውሳኔዎችን በመወሰን ግብር ከፋዮች ለተለያዩ እንግልቶች የሚዳረጉበት ሁኔታ እንዳለም ይሰማል፡፡ በግብር ከፋዮች በኩል ደግሞ የግብር ሕጐቹን በአግባቡ ካለመረዳትና አንዳንዶቹ ደግሞ ካላቸው በሕገወጥ መንገድ የመበልፀግ ፍላጐት የሚነሳ የግብር መሰወር ድርጊት እየፈጸሙ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ሲያደርሱ ይታያሉ፡፡ በአጠቃላይ የግብር ሕጎቹን በሚያስፈጽሙ የተለያዩ የመንግሥት አካላት እንዲሁም በግብር ከፋዮች ዘንድ ግብር አለመክፈል በወንጀልና በፍትሐ ብሔር  እንዲሁም በፍትሐ ብሔር ብቻ ስለሚያስጠይቅበት ሁኔታ ላይ ጥሩ ግንዛቤ የተፈጠረበትና ሁለቱንም ኃላፊነታቸውና ግዴታዎቻቸው በአግባቡ የለዩበት ደረጃ ላይ አልደረስንም፡፡

ስለዚህ ግብር አለመክፈል በወንጀልና በፍትሐ ብሔር እንዲሁም በፍትሐ ብሔር ብቻ የሚያስጠይቅባቸው ሁኔታዎች ከግብር ሕጐቹ አንፃር በመተንተን ማቅረቡ መብትና ግዴታውን የሚያውቅ ግብር ከፋይ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ከማገዙም በላይ፣ ግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ ላይ የሕግና የማስረጃ መሠረት የሌለው የታክስ ኦዲት እየሠሩ ለሕገወጥ ጥቅም መደራደርያ በማዋል ሕዝብና መንግሥት እያለያዩ ያሉ ለህሊናቸው ሳይሆን ለሆዳቸው የሚገዙ አንዳንድ የታክስ ኦዲተሮችና ሌሎች የግብር ሰብሳቢ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ከዚህ ሕገወጥ ድርጊት እንዲታቀቡና ሥርዓት ይዘው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ለማድረግ የላቀ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ የግብር ስወራ ምንነት እንዲሁም የግብር ስወራን የሚያቋቁሙ ድርጊቶችን ለይቶ ለማስቀመጥ የግብሩን ዓይነት ታሳቢ ስለሚያደርግ በእነዚህ ጽንሰ ሐሳቦች ላይ የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር በየግብር ዓይነቶቹን ለያይቶ ማየቱ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በዚሁ መሠረት በመጀመሪያው ክፍል እነዚህን ጽንሰ ሐሳቦች ከተጨማሪ እሴት ታክስ ሕግ አንፃር የመተንተን (የማብራራት) ሥራ አቀርባለሁ፡፡

የተጨማሪ እሴት ታክስ ሕግና ግብር ስወራ

የተጨማሪ እሴት ታክስ በፍጆታ ላይ የሚጣልና አንድ ለተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብሳቢነት የተመዘገበ ሰው የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚከፈልባቸው ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች የማቅረብ ሥራ ሲሠራ የዕቃዎቹን ወይም የአገልግሎቶቹን መሸጫ ዋጋ መነሻ በማድረግ ከተጠቃሚዎች የሚሰበሰበው ቀጥተኛ ካልሆኑ የታክስ ዓይነቶች ውስጥ የሚመደብ መሠረተ ሰፊ ታክስ  ነው፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) በአሁኑ ወቅት ከ150 በላይ የዓለም አገሮች የሚጠቀሙበት የታክስ ዓይነት ሲሆን፣ አገራችንም ሕጉን በአዋጅ ቁጥር 285/94 በማፅደቅ ከታህሳስ 23 ቀን 1995  ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ በማዋል በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ከምትሰበስበው ታክስ ወደ ግማሹ የሚቃረብ ድርሻ ይዞ ይገኛል፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስ  በፈረንሣይ አገር ከተጀመረበት እ.ኤ.አ 1954 ጀምሮ እስካሁን ያለው ጊዜ ሲታይ ከሌሎች የግብር ዓይነቶች አንፃር አጭር ዕድሜ ያለው ቢሆንም፣ በሚያስደንቅ ሁኔታ በዓለም ላይ በስፋት ጥቅም ላይ የዋለ የታክስ ዓይነት ነው ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ ከሌሎች የግብር ሕጐች በተለየ ሁኔታና በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ አገሮች ጥቅም ላይ ያዋሉበት ምክንያት ሲፈተሽ ደግሞ በዋናነት የሚከተሉት ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡

በመጀመሪያ የተጨማሪ እሴት ታክስ በአብዛኞቹ የዕቃና የአገልግሎት አቅርቦት ላይ የሚጣል መሠረተ ሰፊ ታክስ በመሆኑ ነው፡፡ በሁለተኛነት በፍጆታ ላይ እንጂ በቁጠባና በኢንቨስትመንት ወይም በንግድ ሥራ ግብዓቶች ላይ የማይጣል ቁጠባን የሚያበረታታ በመሆኑና በሦስተኛነት ተጨማሪ እሴት ታክስ አምራች፣ ጅምላ ሻጭና የችርቻሮ ሻጭ ዕቃ ሲገዙ የገዙት ዕቃ ዋጋን ጨምሮ ለሻጩ ተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) የሚከፍሉ ሲሆን እነሱ ደግሞ የገዙትን ዕቃ ሲሸጡ ከገዥው ቫት ይሰበስባሉ፤ በመጨረሻም ዕቃውን ሲገዙ የከፈሉትን ቫት በግብዓት ታክስ (Input tax) የሚያዝላቸው ሆኖ ከሰበሰቡት የውጤት ታክስ (Output tax) በማቀናነስ ልዩነቱን ለመንግሥት ይከፍላሉ፡፡ ይህንኑ ለማድረግ ግን ዕቃውን ሲሸጡና ሲገዙ ግብይቱ በደረሰኝ አማካይነት የማከናወንና በታክስ ተመላሽ ሥርዓት (Tax credit system) ተጠቃሚ ለመሆን አስፈላጊ ሰነድ የማቅረብ ግዴታ በሕግ የተጣለ ነው፡፡ በዚህም በነጋዴው ማኅበረሰብ መሀል የሚደረግ ግብይት አንድ ሽያጭ ለአንዱ የውጤት ታክስ የሚያወራርድበት ለሌላው ደግሞ እንደ ግብዓት ታክስ የሚያስይዝበት ሥርዓት በመፍጠር በመካከላቸው የቁጥጥር ሥርዓት እንዲኖር በማድረግ ለመንግሥት ሊከፈልው የሚገባውን የታክስ መጠን ከመንግሥት በተጨማሪ የንግዱ ማኅበረሰብ እርስ በርሱ እንዲቆጣጠር ያደርጋል፡፡ በሌላ በኩል ግብይቶች መሀል የሚፈጠሩ ስህተቶችም እንዲስተካከሉ ለማድረግ የራሱ የሆነ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በመነሳትም አንዳንድ ጸሐፍት “VAT is self enforcing and self correcting tax” በማለት ይገልጹታል፡፡ ከዚህ በመነሳትም የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) የግብር ስወራ ለመከላከል እንደሚያስችል በሰፊው ይነገራል፡፡

የተጨማሪ እሴት ታክስ የግብር ስወራን በመከላከል ረገድ ከሌሎች የታክስ ዓይነቶች የተሻለ አስተዋጽኦ እንዳለው ቢገለጽም፣ ታክሱ የሚሰበሰበው የዕቃ ወይም የአገልግሎት አቅርቦት የሚፈጽሙ የተመዘገቡ ሰዎች የመንግሥት ተወካይ ሆነው የሚሰበስቡበት አሠራር ላይ የተመረኮዘ ስለሆነ፣ ይህንኑ ዘዴ ለግብር ስወራ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑ ነው ከብዙ አገሮች ተሞክሮ መገንዘብ የሚቻለው፡፡

1.     የተጨማሪ እሴት ታክስ መሰወር ምንድን ነው?

የተጨማሪ እሴት ታክስ መሰወርን በተመለከተ በአገራችን የተጨማሪ እሴት ታክስ ሕግ አዋጅ ቁጥር 285/94 ላይ ግልጽ ትርጉም የተሰጠበት ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገር ግን በአዋጁ አንቀጽ 49 ላይ የወንጀሉ ማቋቋሚያ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የተዘረዘሩ ድርጊቶች  በአግባቡ በመተርጎም የተሻለ ግንዛቤ ለመውሰድ የሚያስችል  ትርጓሜ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡ የዚሁ አንቀጽ የአማርኛው ፍቺ ስናየው የአንቀጹ ርዕስ ሕግን በመጣስ ታክስ ስላለመክፈል የሚል ሲሆን፣ ዝርዝሩ ደግሞ “ሕግን በመጣስ የሰበሰበውን ታክስ ያላስታወቀ ወይም የሚፈለግበትን ታክስ ያልከፈለ ወይም መንግሥትን ለማጭበርበር በማሰብ የማይገባው ተመላሽ ታክስ የጠየቀ ማናቸውም ሰው ወንጀል እንደፈጸመ ይቆጠራል፡፡ ስለሆነም በዚህ አዋጅ ክፍል 11 መሠረት ከሚጣልበት መቀጮ በተጨማሪ ጥፋተኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ከአምስት ዓመት በማያንስ እስራት ይቀጣል፤” ይላል፡፡ የእንግሊዝኛው ፍቺ ደግሞ የአንቀጹ ርዕስ “Tax evasion” የሚል ሲሆን ዝርዝሩ ደግሞ “A person who evades the declaration or payment of tax or a person who, with the intention to defraud the government, applies for a refund he is not entitled to, commits an offence and in addition to any penalties under section 11, may be prosecuted and, on conviction, be subject to a term of imprisonment not less than five years.” የሚል ዝርዝር ይዘት አለው፡፡ የድንጋጌው የአማርኛ ፍቺ ላይ ሕግን በመጣስ ታክስ ስላለመክፈል የሚለው የድንጋጌው ርዕስና በዚሁ ድንጋጌ  ውስጥ ያለው ሕግን በመጣስ የሰበሰበውን ታክስ ያስታወቀ ወይም የሚፈለግበትን ታክስ ያልከፈለ የሚለው የሕጉ አነጋገር አሻሚ ስለሆነ፣ ሕጉ ሊደርስበት ያሰበውን ግብ ለማረጋገጥ እንዲቻል ሕግ አውጪው ያቀደው ምን ነበር ከሚለው ጭብጥ አንፃር ከሕጉ መንፈስ ሳንወጣ መተርጐም የወንጀል ሕጉ ይፈቀድልናል፡፡ በዚሁ መሠረት ግልጽ ያልሆነው የድንጋጌው ክፍል ከወንጀል ሕግ የመተርጐም ስልቶች በመጠቀም ተገቢውን ትርጉም ማፈላለግ ያስፈልጋል፡፡ ሕግን በመጣስ የሚለው ሐረግ የድርጊቱን ወንጀልነት ለመግለጽ ተፈልጐ ነው ወይስ እያወቀ ጥፋት በሚፈጽም አጥፊ ላይ ብቻ ተፈጻሚ እንዲሆን ታስቦ ስለመግባቱ በቀላሉ መለየት አይቻልም፡፡ በዚህ ድንጋጌ ውስጥ መንግሥትን ለማጭበርበር በማሰብ የማይገባውን ተመላሽ ታክስ የጠየቀ ወንጀል እንደፈጸመ ይቆጠራል የሚለው አገላለጽ በአተረጓጐም ረገድ ችግር አይፈጥርም፡፡ ምክንያቱም መንግሥትን ለማጭበርበር በማሰብ የሚለው አገላለጽም ሆነ ተብሎ የሚፈጸም የግብር መሰወር ድርጊትን በወንጀልነት የሚፈርጅ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ምክንያቱም ማጭበርበር ሆነ ተብሎ የሚፈጸም ድርጊት ስለሆነ፡፡ ስለዚህ ሕጉን ስንተረጉም በመጀመሪያ በአንድ አንቀጽ ውስጥ ያሉ አገላለጾች በተጣጣመ መልኩ ተግባራዊ በሚደረጉበትና አንድ ወጥ ትርጉም ሊሰጥ በሚችል መልኩ መተርጐም እንዳለባቸው (Harmonized construction)  በወንጀል ሕግ የሚታወቅ የአተረጓጐም መርህ ነው፡፡ ስለዚህ በአዋጅ ቁጥር 285/94 አንቀጽ 49 ላይ ያሉት አገላለጾች ሲታዩ መንግሥትን ለማጭበርበር በማሰብ የማይገባውን ተመላሽ የጠየቀ የሚለው አገላለጽ ሆነ ተብሎ የሚፈጸም የግብር መሰወር ድርጊት የሚገልጽ በመሆኑ፣ ከዚሁ አገላለጽ በፊት ያለው ሕግን በመጣስ የሰበሰበውን ታክስ ያላስታወቀ ወይም የሚፈለግበትን ታክስ ያልከፈለ የሚለው አገላለጽ ሆነ ብሎ የሰበሰበውን ታክስ አሳውቆ ባለመክፈል የግብር መሰወር ወንጀል የፈጸመ አጥፊ በወንጀል ተጠያቂ ለማድረግ እንደገባ አድርጐ መተርጐሙ፣ በአንቀጹ ውስጥ ያሉ ሁሉም አገላለጾች ወጥነት ባለው መንገድ ተግባራዊ እንዲሆኑ አዎንታዊ ውጤት የሚሰጥ አተረጓጐም ነው፡፡ ከሕግ አወጣጥ ሥርዓት አንፃርም ሲታይ ሕግ አውጪው በአንድ ድንጋጌ ሥር እርስ በርስ የሚጋጩ ሐሳቦች አንድ ላይ አጠቃሎ ያወጣል ተብሎ ስለማይታሰብ ለሕጉ ወጥ ትርጉም በሚሰጥ መልኩ መተርጐሙ አሳማኝነት ይኖረዋል፡፡ በሌላ በኩል የድንጋጌው የእንግሊዝኛ ፍቺ ሲታይ ግልጽ በሆነ አገላለጽ በወንጀልነት መፈረጅ የፈለገው ሆነ ተብሎ የሚፈጸም የግብር መሰወር ድርጊት መሆኑን ያሳያል፡፡ ስለዚህ የአማርኛው አገላለጽ ግልጽ ካልሆነ የእንግሊዝኛው አገላለጽ ለትርጉም መጠቀሙ ሕግ የሚፈቅደው አሠራር ነው፡፡ የድንጋጌው የእንግሊዝኛ ቅጂ መጠቀም ጋር በተያያዘ የተጨማሪ እሴት ታክስ ሕጉ የረቀቀው በውጭ ባለሙያዎች መሆኑ ይታወቃል፡፡ እነዚህ የውጭ ባለሙያዎች ደግሞ ሕጉን ያረቀቁት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነበር፡፡ የአማርኛው ድንጋጌዎችም ከእንግሊዝኛው የሕጉ ረቂቅ የተተረጐሙ ከመሆናቸው አንፃር የትርጉሙ ሥራው ላይ አልፎ አልፎ ስህተት አይጠፋም፡፡ አንዳንድ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተገለጹ ቃላት፣ ሐረጐችና ዓረፍተ ነገሮችን በአማርኛ ቋንቋ በደንብ ሊገልጹ የሚችሉ ግልጽና ትክክለኛ የሆኑ የሕግ ቃላት ካልተገኙ፣ ተርጓሚዎች ግልጽ ባልሆኑ ቃላትና የዋናውን ትርጉም መንፈስ በአግባቡ በማይገልጹ ረጃጅም የመግለጫ ዓረፍተ ነገሮች የሚጠቀሙበት ሁኔታ ይታያል፡፡ በዚሁ ድንጋጌ ላይም ርዕሱ “Tax evasion” የሚል ሲሆን ወደ አማርኛ ሲቀየር ግብር መሰወር በሚል አጭር ሐረግ መግለጽ እየተቻለ ሕግን በመጣስ ታክስ ስላለመክፈል በሚል ረጅም ሐረግ ተተርጉሞ መገኘቱ፣ ችግሩ የትርጉም ስህተት ሊሆን ከሚችል ሌላ የተለየ ይዘት አለው ብሎ ለማስቀመጥ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ በሦስተኛነት አንድ ሕግ ግልጽ ካልሆነ ትክክለኛ ትርጉም ለማግኘት በሕግ አውጪው አካል የተደረጉ ውይይቶች እንዲሁም የሕጉ ማብራሪያ ሰነዶች በማየት ሕግ መተርጎም ይቻላል፡፡ ከዚህ አንፃር የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994 ለማብራራት በውጭ አማካሪ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተዘጋጅቶ በገቢዎች ሚኒስቴር የፌዴራል አገር ውስጥ ባለሥልጣን በአማርኛ የተተረጎመው የሕጉ ማብራሪያ ላይ ስለ አንቀጽ 49 የተቀመጠው ማብራሪያ ሲገልጽ በመግቢያው ላይ ‘‘ይህ አንቀጽ ከፍተኛ የወንጀል ቅጣት ስለሚያስከትለው የታክስ ማጭበርበር ወንጀል ይመለከታል፤’’ ይላል:: ስለዚህ የሕጉ ማብራሪያ ይዘት ሲታይም  የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 49 ሆነ ተብሎ የሚፈጽም የግብር መሰወር ወንጀል የሚደነግግ መሆኑ ያመላክታል፡፡ በአጠቃላይ በሦስቱም የአተረጓጎም መንገዶች የተጨማሪ እሴት ታክስ ግብር አለመክፈል በወንጀል ሊያስጠይቅ የሚችለው ግብሩ ሳይከፈል የቀረው ሆነ ተብሎ የሚፈጽም የግብር መሰወር ድርጊት ስለመኖር በቂና አሳማኝ በሆነ ማስረጃ ማስረዳት ሲቻል ነው ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡  

2.     የተጨማሪ እሴት ታክስ መሰወርን ሊያቋቁሙ ስለሚችሉ ድርጊቶች

የተጨማሪ እሴት ታክስ ሊሰወርበት ወይም ሊጭበረበርባቸው የሚችሉ ሁሉንም ድርጊቶች ዘርዝሮ ማስቀመጥ ባይቻልም፣ የሚከተሉትን ግን እንደ ማሳያ መጥቀስ  ይቻላል፡፡

2.1           የነጋዴው የሽያጭ መጠን ዝቅ በማድረግ የሚፈጸም ግብር መሰወር

አንድ ለተጨማሪ እሴት ታክስ ስብሳቢነት የተመዘገበ ነጋዴ የዕቃ ወይም የአገልግሎት ማቅረብ ሥራ በማከናወን በዚህ ግብይት የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) ሰብስቦ እያለ የሰበሰበው የተጨማሪ እሴት ታክስ ሙሉ በሙሉ ለግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ላለመክፈል የፈጸመው የሽያጭ መጠን ዝቅ አድርጐ ሊያሳውቅ ይችላል፡፡ ይህንን ለማድረግ የፈጸማቸውን ሽያጮች በተወሰነ መልኩ ለመደበቅ ያለደረሰኝ ግብይት መፈጸም፣ ሐሰተኛ የሒሳብ መዝገብ የማደራጀት ወይም የተፈጸሙ ሽያጮች በሒሳብ መዝገብ ያለመመዝገብ ድርጊት ሊፈጽም ይችላል፡፡ የሽያጩ መጠን ዝቅ ከተደረገ (ከተደበቀ) ደግሞ ባልተገለጸው ሽያጭ ላይ የተሰበሰበ የተጨማሪ እሴት ታክስ ለራስ በማስቀረት የግብር መሰወር ድርጊት ይፈጽማል፡፡ ይህም በአገራችንም ሆነ በሌሎች አገሮች ላይ በታክስ አሰባሰቡ ላይ  አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ያለ ሕገወጥ ድርጊት በመሆኑ፣ መንግሥትም ሆነ ዜጐች የችግሩን አሳሳቢነት አውቀው በጋራ ሊከላከሉት ይገባል፡፡  በዚህ ዓይነት ድርጊት የሚሳተፉ ሰዎች ደግሞ ድርጊቱ ሕገወጥና በወንጀል የሚያስቀጣ መሆኑን አውቀው፣ ከዚህ ሕገወጥ ድርጊት በመራቅ ራሳቸውን ከተጠያቂነት ሊያድኑ ይገባል፡፡

2.2           ግዢን ዝቅ በማድረግ የሽያጫቸው መጠን እንዲቀንስ እየተደረገ የሚፈጸም የግብር ስወራ

በተራ ቁጥር አንድ ላይ የተገለጸው ድርጊት ለተጨማሪ እሴት ታክስ የተመዘገቡ ሰዎች የሽያጫቸው መጠን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ሳይገልጹ በመቅረት በተደበቀው /ባልተገለጸው/ ሽያጭ ላይ የሰበሰቡት የተጨማሪ እሴት ታክስ ለራሳቸው የሚያስቀሩበት ሁኔታ የሚያመለክት ሲሆን፣ በዚህኛው ድርጊት ግን የሽያጭ መጠን አነስተኛ እንዲሆን አስቀድሞ የግዥን መጠን ከትክክለኛው የግዢ መጠን ዝቅ በማድረግ ሊሰበሰብ የሚገባ የተጨማሪ እሴት ታክስ መጠን  እንዲያንስ በማድረግ ያለአግባብ የታክስ ተመላሽ ለመውሰድ የሚያስችል አሠራር ነው፡፡ በዚህ አካሄድ አንዳንድ ነጋዴዎች የገዙት ዕቃ ዋጋ የማሳነስ (Under invoicing) ድርጊት በመፈጸም በዕቃው ላይ የከፈሉት የግብዓት ታክስ ዕቃውን ሲሸጡ ከሚሰበስቡት የውጤት ታክስ እንዲበልጥ በማድረግ ሁሌ የታክስ ተመላሽ የሚጠይቁበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ለምሳሌ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ አንድ የንግድ ዕቃ የሚያስገቡ ነጋዴዎች ከውጭ አገር ያስገቡት የንግድ ዕቃ በአገር ውስጥ ገበያ ሲሸጡት የዕቃው የመሸጫ ዋጋ ግንባታ (Price construction) ሲያደርጉ በጉምሩክ ሕግ መሠረት የተተመነ የዕቃው ዋጋ፣ ለዕቃው የተከፈለ ቀረጥና ታክስ፣ ለዕቃው ከኢትዮጵያ የጉምሩክ ድንበር እስከ ግብር ከፋዩ መጋዘን ድረስ የወጣ ማናቸውም ወጪ እንዲሁም ዕቃው ለመሸጥ ዝግጁ እስኪሆን ድረስ የሚወጡ ሌሎች ወጪዎች መነሻ በማድረግ የዕቃው መሸጫ ዋጋ መገንባት አለባቸው፡፡ የጉምሩክና ታክስ ሕጎች በማጣጣም ያልተያዘ የዕቃ ዋጋ ግንባታ ግን የግዢ ዋጋ በማሳነስ በዕቃው ላይ የተከፈለ የግብዓት ታክስ በሽያጭ ጊዜ ከሚሰበሰብ የውጤት ታክስ እንዲያንስ በማድረግ ሁሌ የታክስ ተመላሽ እንዲያወራርዱ ዕድል ይሰጣል፡፡ በአገር ውስጥ ገበያ የሚፈጸሙ ግዢዎች ዋጋ የማሳነስ ድርጊት ካለም ውጤቱ ተመሳሳይ ነው፡፡ በዚህ ድርጊት ምክንያት በእኛ አገርም በተግባር  አንዳንድ ነጋዴዎች ለብዙ ዓመታት የተጨማሪ እሴት ታክስ ሳይከፍሉ የታክስ ተመላሽ ሲያወራርዱ የነበሩበት ሁኔታ ታይቷል፡፡

2.3           የተጨማሪ እሴት ታክስ የተለያዩ የማስከፈያ ምጣኔዎች ያለአግባብ በማቀያየር የሚፈጽም የግብር ስወራ

ለተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብሳቢነት የተመዘገበ ነጋዴ የሚፈጽማቸው የዕቃ ወይም የአገልግሎት ማቅረብ ሥራዎች የተለያዩ የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔ ያላቸው (የሚከፈልባቸው) ከሆነ፣ ነጋዴው ከፍ ያለ የተጨማሪ እሴት ታክስ በሚከፈልባቸው የዕቃ ወይም የአገልግሎት አቅርቦት ላይ የሰበሰበው ታክስ አነስተኛ መጠን ባላቸው አቅርቦቶች በመቀየር በመሀል ያለው የታክስ ልዩነት ለራሱ በማስቀረት የሚፈጸም የግብር ስወራ ድርጊት ሊፈጸም ይችላል፡፡

2.4           የሰበሰቡትን ታክስ  (VAT) ለመንግሥት አለመክፈል

ይህም ከላይ በተገለጹት ድርጊቶች አማካይነት ሊፈጸም የሚችል ሲሆን፣ በሌላ መልኩ የተጨማሪ እሴት ታክስ ከፈጸሙአቸው ግብይቶች የሚሰበስቡ ነጋዴዎች አስቀድሞ በተሰላ ሁኔታ ድርጅታቸው ኪሳራ ሳይገጥመው ሆነ ተብሎ የመክሰር ውሳኔ በማሰጠት አስቀድሞ የተሰበሰበ ቫት ሳይከፈል የሚቀርበት ሁኔታ አለ፡፡ በሌላ በኩል አንዳንድ ነጋዴዎች ለተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብሳቢነት በመመዝገብ ከፈጸሙአቸው ግብይቶች ቫት ሰብስበው ለመንግሥት ሳይከፍሉ ይዘውት የመጥፋት ድርጊት (Missing trader fraud) በአገራችን እንዲሁም በሌሎች አገሮች በስፋት የሚታይ የግብር ስወራ ዓይነት አለ፡፡ ይህ ድርጊት ካለው ከፍተኛ ጉዳት አንፃር የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚያስተዳድረው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ለተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብሳቢነት በተመዘገቡ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ የሆነ የክትትልና የቁጥጥር ሥራ መሥራት ካልቻለ በታክስ ሥርዓቱ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡

2.5           ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች በሕገወጥ መንገድ በማስገባት ሊሰበሰብ የሚገባ የተጨማሪ እሴት ታክስ ማስቀረት

የአገራችን የተጨማሪ እሴት ታክስ ሕግ የመድረሻ መርህ (Destination principle) የሚከተል ስለሆነ በአዋጁ አንቀጽ 3 መሠረት ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ዕቃዎች ላይ እነዚህን ዕቃዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገባ ማንኛውም ሰው የተጨማሪ እሴት ታክስ መከፈል እንዳለበት የማስከፈያ መጠኑ ደግሞ በዕቃዎቹ ላይ የሚከፈለውን ቀረጥና ታክስ ጨምሮ በኢትዮጵያ የጉምሩክ ሕግ መሠረት በሚወሰነው የዕቃው ዋጋ ላይ 15 በመቶ የተጨማሪ እሴት ታክስ እንደሚከፈል የአዋጁ አንቀጽ 14 ላይ ተደንግጓል፡፡ ዕቃዎቹ በሕገወጥ መንገድ ከገቡ ግን በእነዚህ ዕቃዎች ላይ ሊከፈል ይችል የነበረው ቀረጥና የተጨማሪ እሴት ታክስ ጨምሮ ሌሎች በገቢ ዕቃዎች የሚከፈሉ ታክሶች ሳይከፈሉ እንዲቀሩ ያደርጋል፡፡ በሕገወጥ መንገድ የገቡ ዕቃዎች ተገቢው ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው መግባታቸው ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥ ገበያ ላይ የሚሸጡት ከሌሎች ተወዳዳሪ ዕቃዎች ዝቅ ባለ ዋጋ በመሆኑ፣ በንግድ ውድድር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ በአገር ውስጥ ገበያ ላይ ያለደረሰኝ የሚሸጡ በመሆናቸው ሊሰበሰብ የሚገባ ታክስ ሳይሰበሰብባቸው የሚቀር በመሆኑ፣ የግብር ስወራ ተፅዕኖው ዘርፈ ብዙ ነው ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

2.6           ሐሰተኛ የታክስ ተመላሽ መጠየቅ

የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚሰበስቡ ሰዎች ሊከፍሉት ስለሚገባ የተጨማሪ እሴት ታክስ መጠን ለማስላት የሚያገለግል ዘዴ በተመለከተ እስካሁን በዓለማችን አራት ስልቶች ይታወቃሉ፡፡ እነዚህም ደረሰኝን መሠረት በማድረግ የታክስ ተመላሽ የሚከተል ሥርዓት (Credit invoice VAT)፣ ደረሰኝ ላይ ያልተመሠረተ የታክስ ተመላሽ የሚከተል ሥርዓት (Credit subtraction VAT that does not rely on VAT invoices)፣ ሽያጭ የመቀነስ ሥርዓት የሚከተል (Sales subtraction VAT) እና የመደመር ዘዴ የሚጠቀም (Addition method VAT) ይባላሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አገራችንን ጨምሮ አብዛኞቹ የዓለም አገሮች የሚጠቀሙትና በስፋት ሥራ ላይ የዋለው የመጀመሪያው ዘዴ ነው፡፡ ደረሰኝን መሠረት በማድረግ የታክስ ተመላሽ የሚከተል ሥርዓት በሚከተሉ አገሮች ተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) የሚሰበስቡ ነጋዴዎች በመጀመሪያ ተጨማሪ እሴት ታክስ የሚሰበሰብበት ዕቃ ወይም አገልግሎት ሲገዙ ተጨማሪ እሴት ታክስ ይከፍላሉ፡፡ ይህንኑ ዕቃ ወይም አገልግሎት ለሌላ ሰው ሲሸጡት (ሲያስተላልፉት) ደግሞ ከገዥው ተጨማሪ እሴት ታክስ ይሰበስባሉ፡፡ በመጨረሻ እነዚህ ነጋዴዎች በንግድ ግብዓት ላይ የከፈሉት ታክስ የሚወራረድላቸው ይሆናል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ግዢ የፈጸሙበትን ደረሰኝ ይዘው መቅረብ አለባቸው፡፡ ያለደረሰኝ ግን የግብዓት ታክስ (Input tax) ሊያዝላቸው አይችልም፡፡ ደረሰኝ ከያዙ ደግሞ በደረሰኙ ላይ የተገለጸውን የግብዓት ታክስ መንግሥትን አስገድደው ለማስከፈል ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ ታክስ ተመላሽ ለማወራረድ የላቀ አስተዋጽኦ ያለው ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ሐሰተኛ ደረሰኝ በማዘጋጀት ወይም በሕጋዊ መንገድ የታተመ ደረሰኝ ተጠቅሞ ላልተፈጸመ ግዢ እንደተፈጸመ ተደርጎ ወይም የተጋነነ ግዢ በመፈጸም ደረሰኝ በማቅረብ ብዙ የታክስ ተመላሽ በሕገወጦች የሚወሰድበት ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ይህንኑ ድርጊት በታክስ ሥርዓቱ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ከባድ ስለሆነ ሕገወጥ ድርጊቱን ለመግታት ግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት የታክስ ተመላሽ ለመጠየቅ የሚቀርቡ ደረሰኞችን ሕጋዊነት በአግባቡ ማረጋገጥ፣ ሕጋዊ በሚባሉ ደረሰኞች ደግሞ ተፈጸሙ ስለተባሉ ግብይቶች በትክክል ስለመከናወናቸው በተቻለ አቅም ጥብቅ ማጣራትና ክትትል ሊያደርግ ይገባል፡፡  ሌላው በዚህ ውስጥ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ እንደ አገራችን ያሉ የተጨማሪ እሴት ታክስ ሕግ ያላቸው አገሮች የሚከተሉት የተጨማሪ እሴት ታክስ የመድረሻ መርህ በዋናነት የሚታወቀው ከዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅት መርሆች ጋር ለማጣጣም  ወደ ውጭ የመላክ ሥራ (Export) በዜሮ ተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔ ሥር እንዲካተት ያደርጋሉ፡፡

ዜሮ የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔ አገላለጹ ለማስተላለፍ የተፈለገውን የሕጉ መልዕክት በቀላሉ ለመረዳት የሚያስቸግር ስለሆነ ሐሳቡን ግልጽ ለማድረግ መሞከሩ የተሻለ አካሄድ ይሆናል፡፡ ዜሮ የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚጣልበት ግብይት ማለት በዚህ ዘርፍ የሚካተቱ አቅርቦቶች የሚያቀርብ ሰው እነዚህ አቅርቦቶች ለተጠቃሚዎች ሲያስተላልፍ ከተጠቃሚዎች የሚሰበሰበው ተጨማሪ እሴት ታክስ (Output tax) አይኖርም፡፡ ነገር ግን እነዚህ አቅርቦቶች በመጀመሪያ ለራሱ ሲገዛቸው የከፈለው የተጨማሪ እሴት ታክስ (input tax) ግን በታክስ ተመላሽ ሥርዓት መሠረት ማወራረድ  ይችላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን አቅርቦቶች የሚፈጽም ሰው ነፃ የተደረገው የውጤት ታክስ (Output tax) ከመሰብሰብ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ዜሮ የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔ የሚለው አገላለጽ ግልጽ ስላልሆነ አንዳንድ ጸሐፍት “Zero rated” ከሚባል  “Exemption with credit” ወይም “Exemption of the supply from output tax” በሚለው አገላለጽ ቢገለጽ የተሻለ ነው የሚል ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡ አገሮች ወደ ውጭ መላክን ለማበረታታት ይህንኑ ግብይት በዜሮ የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔ በማካተት ከሚሰበሰብ የውጤት ታክስ (Output tax) ነፃ ያደርጉታል፡፡ ሆኖም አንዳንድ በሕገወጥ መንገድ የመበልፀግ ዓላማ ያላቸው ሰዎች ወደ ውጭ አገር የሚላክ ዕቃ በአገር ውስጥ ገበያ በመሸጥ በግብይቱ የተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብስበው የሰበሰቡትን የውጤት ታክስ ለራሳቸው የማስቀረት ድርጊት ይፈጸማሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዕቃ ወደ ውጭ አገር ሳይልኩ እንደላኩ በማስመሰል ዕቃው በአገር ውስጥ ገበያ ሲገዙት የከፈሉት የግብዓት ታክስ በታክስ ተመላሽ ሥርዓት መሠረት እንዲመለስላቸው በማድረግ በብዙ መልክ ሊገለጽ የሚችል የታክስ ስወራ ድርጊት ይፈጸማል፡፡ ስለዚህ በዜሮ የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔ በሚካተቱ ግብይቶች የተከፈለው የግብዓት ታክስ ተመላሽ ጥያቄ ሲቀርብ ጉዳዩን በአግባቡ ማጣራት በሌላ ጊዜም ቢሆን ጠንካራ የታክስ ኦዲት በመሥራት የቁጥጥር ሥርዓቱ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡

2.7           የታክስ ተመላሽ በማይፈቀድላቸው ግብይቶች ላይ የተከፈለ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመላሽ እንዲደረግ ማድረግ  

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የታክስ ተመላሽ (Credit of VAT) የሚፈቀደው የተጨማሪ እሴት ታክስ በሚሰበሰብባቸው ግብይቶች ወይም በዜሮ የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔ በሚፈቀድባቸው ግብይቶች ላይ የተከፈለ የግብዓት ታክስ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ነጋዴዎች ቅይጥ አቅርቦቶች (Mixed supplies) የሚያቀርቡ ከሆነ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ በሆኑ ግብይቶች የከፈሉት የግብዓት ታክስ እንዲመለስላቸው በማሰብ በታክስ ነፃ ግብይቶች የከፈሉት የግብዓት ታክስ (Input tax) ታክስ በሚሰበሰብባቸው እንደተከፈለ በማድረግ በታክስ ማቀናነስ ሥርዓት መሠረት ታክሱ በሕገወጥ መንገድ እንዲመለስላቸው በማድረግ የግብር መሰወር ድርጊት ይፈጽማሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለግል ፍጆታ በገዙአቸው ግብይቶች የከፈሉትን የግብዓት ታክስ እንደ ንግድ ሥራ የግብዓት ታክስ እንዲያዝላቸው በማድረግ አለአግባብ የታክስ ተመላሽ በንግድ ሥራው ስም የሚወስዱበት ሁኔታ ይታያል፡፡

2.8           ሐሰተኛ ነጋዴዎች /Bogus Traders/

የአማርኛ ትርጉሙ የእንግሊዝኛው ሐሳብ በአግባቡ ሊገልጸው የሚችል አይመስለኝም፡፡ ጉዳዩ ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ገላጭ ምሳሌ ማስቀመጥ የተሻለ ስለሆነ የሚከተለውን ማሳያ እንመልከት፡፡ አንዳንድ ኩባንያዎች የታክስ ተመላሽ ለመጠየቅ የሚያስችል ደረሰኝ ለመፈብረክ ብቻ ሊቋቋሙ ይችላሉ፡፡ በዚህም ድርጅቶቹ የንግድ ሥራ ፈቃድ በማውጣት ለተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብሳቢነት በመመዝገብ ግብይት ሳያከናውኑ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ እየቆረጡ በመሸጥ ሥራ ተሰማርተው ከመንግሥት ካዝና ያለአግባብ በታክስ ተመላሽ ሥርዓት መሠረት ግብር እንዲሰወር የሚያደርግ ሕገወጥ ድርጊት ይፈጽማሉ፡፡ በዚሁ ዓይነት መልኩ በሚፈጸሙ የተደራጁ የተጨማሪ እሴት ታክስ ማጭበርበር ወንጀሎች በእኛ አገርም በስፋት እየታየ ያለ  መሆኑ ታውቆ ተገቢውን ቁጥጥር የማድረጉ ሥራ በፍጥነት መሠራት አለበት፡፡ በዚህ ዓይነት የተጨማሪ እሴት ታክስ ማጭበርበር ወንጀል በመቶ ሚሊዮኖችና ቢሊዮኖች የሚገመቱ የታክስ ማጭበርበር ጉዳይ የያዙ የወንጀል ክሶች በፍርድ ቤቶች እየታዩ ያለበት ሁኔታ ስላለ ጉዳዩ የጽንሰ ሐሳብ (Theory) ሳይሆን በተግባር እየተፈጸመ ያለ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ማንኛውም ሰው በዚህ ዓይነት ድርጊት እንዳይገባ የማስተማሩና የማስጠንቀቁ ሥራም በአግባቡ መሠራት ይኖርበታል፡፡

2.9           ነጋዴው ለራሱ የሚያቀርባቸው አቅርቦቶች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ አለመሰብሰብ

አንዳንድ ነጋዴዎች በንግድ ሥራቸው የሚያቀርቡአቸው የዕቃ ወይም የአገልግሎት አቅርቦቶች ተጨማሪ እሴት ታክስ የሚሰበሰቡባቸው ሆነው እያለ አቅርቦቱ ለራሳቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው ወይም ለሠራተኞቻቸው ጥቅም ሲያውሉት ቫት የማይሰበስቡበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ይህ አካሄድ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ሕጉ አንፃር ሲታይ የተሳሳተ አካሄድ ነው፡፡ ምክንያቱም በተጨማሪ እሴት ሕግ አዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 4(2) እና (3) እንዲሁም የተጨማሪ እሴት ታክስ ደንብ ቁጥር 79/1995 አንቀጽ 3(2) እና በሌሎች አንቀጾች መሠረት እነዚህ አቅርቦቶች ታክስ የሚከፈልበትን የንግድ ሥራ እንቅስቃሴ ለማከናወን የዋሉ እንደሆኑ ተደርገው መቆጠር እንዳለባቸውና ተገቢውን የተጨማሪ እሴት ታክስ ሊሰበሰብባቸው እንደሚገባ ይደነግጋሉ፡፡ ስለዚህ በእነዚህ አቅርቦቶች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ አለመሰብሰብ በሕግ የሚያስጠይቅ ድርጊት መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡

 

በመጨረሻም የተጨማሪ እሴት ታክስ ከዚህ በላይ በተገለጹና በሌሎች መሰል ድርጊቶች አማካይነት ሊሰወር እንደሚችል ታውቆ ወንጀሉን ለመከላከል መንግሥት እንዲሁም ዜጎች የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሚሠሩ የተጨማሪ እሴት ታክስ ኦዲቶች ከግምታዊ አሠራር በመውጣት ሥራው ሕጉን በሚያውቁ ባለሙያዎች በመሠራት የግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራር ማስፈን ይኖርበታል፡፡ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በዚህ ሕገወጥ ድርጊት የሚሳተፉ ሰዎች ደግሞ ራሳቸውን ከተጠያቂነት እንዲያድኑ እመክራለሁ፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የወልቃይት ሕዝብ የማንነት ጥያቄና ሕገ መንግሥቱ
በኮንስትራክሽን ውሎች አፈጻጸም ወቅት ለሚስተዋሉ ጉዳቶች (Risks) ተጠያቂ ማ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 20 April 2024