Font size: +
43 minutes reading time (8527 words)

የወልቃይት ሕዝብ የማንነት ጥያቄና ሕገ መንግሥቱ

የማንነት ጥያቄ ምንድን ነው? የድንበር አከላለል ለውጥ (የድንበር ውዝግብ) ጥያቄስ ምንድን ነው? የኢትዮጵያ ሕግስ እንዴት ነው የሚጠብቃቸው? የዚህ ማስታወሻ ዓላማ እነዚህን ጉዳዩች ስለሚመለከቱት የሕግ ክፍሎች በማጥናትና ስለአተረጓጎማቸው አስተያየት በማቅረብ እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ነው፡፡ ከእነዚህ ባሻገር ይህ ማስታወሻ ስለ ትግራይ ሕዝብ መልክዓ ምድራዊ አሰፋፈር ታሪካዊ ዳሰሳ ባጭሩ አድርጓል፡፡

ይህን ማስታወሻ ለመጻፍ ያነሳሱኝ ነገሮች የፌዴሬሽን ምክር ቤት የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄ ተወካዮች በቀረበለት በአዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀጽ 20 ድንጋጌ መሠረት የማንነት ጥያቄው በክልሉ በደረጃው ባሉ የአሰተዳደር እርከኖች ታይቶ ውሳኔ ማግኘት የሚገባው በመሆኑ ጉዳዩ በትግራይ ክልል እንዲታይ ብሎ በመወስን ማስተላለፉ እና የእኔ ማንነት ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳ ዋናው ጥያቄ  የሆነውን የማንነት ጥያቄ ምንነትና የድንበር አከላለል ለውጥ (የድንበር ውዝግብ) ጥያቄ ምንነት በመመርመር ስለአተረጎገማቸው አስተያየት ማቅረብ ወደድኩኝ፡

1.    የማንነት ጥያቄ ባሕርይ እና ጥያቄውን የማቅረብ መብት    

የማንነት ጥያቄ ምንድን ነው? ጥያቄውንስ የማቅረብ መብት ያለው ማን ነው? የማንነት ጥያቄን ለመወሰን የሚያስፈልጉ መስፈርቶች ምንድናቸው? ማንነት ዕውቅና ማግኘቱ ምንን ያገኛል? ጥያቄውን የመወሰን ሥልጣን የማን ነው? የሚወሰነውስ ምን ሥነ ሥርዓት በመከተል ነው ሚሉትን ጥያቄዎች በዝርዝር ከዚህ በታች መመልከት እንሞክራለን፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም ሆነ ሌላ የኢትዮጵያ ሕግ ማንነት (identity) ምን መሆኑን በግልፅ አይገልፁም፡፡ አንድ ሰው ብዙ ማንነቶች ሊኖሩት ይችላሉ፤ ይኖሩታልም፡፡ አንድ ማንነት በጉልህ የሚታየው ከሌላው ጋር ሲነፃፀር እንደመሆኑ መጠን፤ አንድ ሰው ወይም ቡድን ማንነቱን የሚገልፅበት መንገድ እንደሁኔታው ይለያያል፡፡ ጥያቄው ዜግነትን ሲከተል፤ ዜግነታዊ ማንነትን ያስቀድማል ማለት ነው፡፡ ብሔራዊ ማንነት የሚመለከት ከሆነ ብሔራዊ ማንነቱን ያንፀባርቃል፡፡ ብሔራዊ ማንነት (ethnic identity) በሁለት ይከፈላል፡፡ ይኸውም የብሔር ማህበረሰብ ማንነት (ethnic community identity) እና የብሔር ማህበረሰብ አባልነት (ethnic community membership) ተብሎ ይከፈላል፡፡  

በኢትዮጵያ በጠቅላላ አጠቃቀሙ መሠረት ማንነት አንድ ማህበረሰብ ራሱን ከሌሎች ለመለየትና ለማወቅ እንዲቻል ለማድረግ የሚጠቀምበት ብሔራዊ ማንነት (ethinic identity) ማለት ነው፡፡ በስልጤ የማንነት ጥያቄ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሰጠው ውሳኔ የማንነት ጥያቄ የሚባለው የብሔራዊ ማንነት ጥያቄ መሆኑን ገልጸል፡፡ የማህበረሰብ ብሔራዊ ማንነት ቋንቋን ጨምሮ ባህልን፣ ማንነትን፣ ሥነ-ልቦናን እና በአብዛኛው የተያያዘ መልክዓ ምድርን መሠረት ተደርጎ የሚገኝ አቋም ነው፡፡ የብሔር ማህበረሰብ ማንነት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መሠረታዊ ቦታ አለው፡፡ ለዚህም ነው የኢትዮጵያዊነት ማንነት በብሔራዊ ማንነት ላይ የተመሠረተ ነው የሚባለው፡፡ የኢትዮጵያዊ ማንነት የሚኖረው በቅድሚያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ማንነት ሲኖር ነው፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያዊ ማንነትና በብሔራዊ ማንነት መካከል መቆራኘት (መቆላለፍ) አለ፡፡

ለዚህ ጽሑፍ (አንቀጽ) ያህል ብሔራዊ ማንነት የሚለው ቃል በአንድ ማህበረሰብና በግለሰቦች መካካል በብሔራዊ ማንነት መለኪያዎች አማካኝነት የዝምድና ግንኙነትን ያመለክታል፡፡ ብሔራዊ ማንነት ከተጨባጭ ሁኔታዎችና ከምኞት (ከፍላጎት ወይም ከምርጫ) የሚገኝ አቋም ሲሆን አቋሙን የሚያገኘው በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ ሰዎች ናቸው፡፡ አሁን የምንመለከተው ስለብሔራዊ ማንነት ነው፡፡ በቅድሚያ ስለብሔራዊ ቡድን (ማህበረሰብ) ማንነት እንመልከትና በመቀጠል ስለግለሰባዊ ብሔራዊ ማንነት ባጭሩ ምልከታ እናደርጋለን፡፡

በአሁኑ ጊዜ አንድ የማህበረሰብ ልዩ ማንነት አንድ ወይም ሁለት ተግባሮችን ይፈፀም ይሆናል፡፡ አንደኛ የአንድ ማህበረሰብን ምንነት ለይቶ ያስታውቃል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የአንድን ማህበረሰብ ጠቅላላ ምንጭን ለይቶ ያስታውቃል፡፡ በዚህ አባባል መሠረት የብሔር ልዩነት የአንድን ማህበረሰብ የተለየ ምንጭ እንኳን ባይሆን ጠቅላላ ምንጭ ያመለክታል ሊባል ይችላል፡፡ ሆኖም ከዘመኑ የብሔር ፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ ዋናው ተግባሩ አንድ የብሔር ማህበረሰብ ራሱን በማንነቱ በመመስረት ለመለየት ወይም ለማስታወቅ እንዲረዳው ማህበረሰቡ ከሌሎች ማህበረሰቦች ለመለየት እንደሚያስችለው ነው፡፡

ለብሔራዊ ማንነት ጥያቄ (አቤቱታ) አግባብነት ያላቸው ሕጎች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው  በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39/5/ የተደነገገው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀጽ 19/1/፣ 20፣ 21 እና 22 ናቸው፡፡ እነዚህም የማንነት ጥያቄ ሕጋዊ መሠረትና ምንጭ ናቸው፡፡ የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39/1/ ላይ እንደተጠቀሰው ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል መብት ያለገደብ አለው፡፡ ይህ መብት ሁለት ነገሮችን የሚያጠቃልል ነው፡፡ በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ብሔሮች በኢትዮጵያ ሥር ሆነው በውስጥ ጉዳያቸው ራሳቸውን በራሳቸው በሰፈሩበት መልክዓ ምድር የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ያላቸው መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ማንኛውም ብሔር ያለ ገደብ በፈለገበት ጊዜ በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው ሥርዓት መሠረት ለመገንጠል (መነጠል) የሚችል መሆኑን ይገልፃል፡፡

እዚህ ላይ ጥያቄው የዚህ የብሔር መብቶች ባለቤት ማንነው? የሚል ነው፡፡ የዚህ መብት ባለቤት ማን እንደሆነ በሕገ መንግሥቱ ከአንቀጽ 39/1/ እስከ /4/ ድረስ ተደንግጓል፡፡ በነዚህ ድንጋጌዎች መሠረት እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ የብሔር መብቶች ባለቤት መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ለመሆኑ ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39/5/ ላይ ተቀምጧል፡፡ የዚህ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39/5/ ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ለመባል ሊሟሉ የሚያስፈልጉ አምስት መስፈርቶች አስቀምጧል፡፡ እነዚህም ቋንቋ፣ ባህል፣ የህልውና አንድነት፣ የሥነልቦና አንድነትና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር መስፈሩ ናቸው፡፡ እነዚህን መስፈርቶች በሙሉ የሚያሟላ ማህበረሰብ የብሔር ማህበረሰብ ማንነት (አቋም) ያገኛል፡፡ ከነዚህ መስፈርቶች አንዱን ያላሟላ ማህበረሰብ የብሔር ማህበረሰብ አቋምን ጨርሶ ሊያገኝ አይችልም፡፡ የብሔር ማህበረሰብ አቋም ዕውቅና የማግኘቱ አስፈላጊነት የብሔር መብቶችን ለመጠቀም ነው፡፡ የብሔር ማህበረሰብ አቋም እውቅና ያላገኘ ማህበረሰብ የብሔሮች መብቶች ሊኖሩት አይችልም፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የብሔራዊ ማንነት ጥያቄ የሚወሰንበት መሰረታዊ መስፈርት/መስፈርቶች ምን እንደሆነ/ኑ ለመመልከት እንሞክራለን፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግሥት ህብረብሔራዊ ፌዴራሊዝም የመገንባት አቋም ወስዷል፡፡ ከዚህ ዓላማ ተነስቶ ስለብሔር ማህበረሰብ ማንነት (ባሕርይ) በአንቀጽ 39/5/ ላይ ትርጓሜ ሰጥቶታል፡፡ የብሔራዊ ማንነት የዕውቅና ጥያቄ መሠረትም ይሄው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39/5/ ነው፡፡ በዚህ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39/5/ መሠረት የብሔር ማህበረሰብ ተብሎ ዕውቅና ለማግኘት መሟላት ያለባቸውን አምስት መስፈርቶች አደራጅቷል፡፡ እነዚህም፡-

1.     ቋንቋ

2.    ባህል

3.    የሕልውና አንድነት

4.    የሥነልቦና አንድነት

5.    በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር መኖር ናቸው፡፡

የማንነት ዕውቅና ሊሰጥ የሚችለው ጥያቄ አቅራቢው ማህበረሰብ ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን ተጨባጭ ሁኔታዎችና ተጨባጭ ያልሆኑ ሁኔታዎች አሟልቶ የተገኘ እንደሆነ ነው፡፡ ይህም ማለት ጥያቄው የሚወሰነው በገለልተኛ አካል አስተያየት እና በራሱ በጥያቄው አቅራቢ ሕዝብ አስተያየት ነው ማለት ነው፡፡ ሆኖም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በስልጤ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ  ላይ በሰጠው ውሳኔ የማንነቴ ይታወቅ ጥያቄ አከራካሪ በሆነ ጊዜ ጥያቄውን ያቀረበው ማህበረሰብ አባላት በሚያደርጉት ቀጥተኛ ተሳትፎ በሕዝብ ውሳኔ መወሰን ይገባዋል ሲል ወስኗል፡፡ በዚህም ውሳኔ መሠረት አከራካሪ የሆነ የማንነት ጥያቄ ያለገለልተኛ አካል አስተያየት ጥያቄው በራሱ በጠያቂው ማህበረሰብ ግላዊ አስተያየት ሊወሰን ይችላል ማለት ነው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ በአንቀጽ 39/5/ ላይ የተደነገጉትን ተጨባጭ የሆኑትን የቋንቋ፣ የባህል እና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የመኖርን መስፈርቶች ቸል መባላቸውን በግልፅ ያሳያል፡፡ ሕገ መንግሥቱ እንደዚህ ዓይነት የማንነት ጥያቄዎች የማንነት ጥያቄ ባቀረበው ማህበረሰብ ሕዝበ ውሳኔ ብቻ እንዲወሰኑ አንዳችም ድንጋጌ ላይ በግልፅ ሆነ በዝምታ የገለፀው ነገር የለም፡፡ ሕገ መንግሥቱ የመገንጠል ጉዳይና ክልል የማቋቋም ጉዳይ በሕዝበ ውሳኔ በስተመጨረሻ እንዲወሰኑ ደንግጓል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በእነዚህ ጉዳዩች ላይ ሕዝበ ውሳኔ ተደርጎ ይወሰን ማለቱ በምንም አመክንዩ የብሔራዊ የማንነት ጥያቄ በሕዝበ ውሳኔ ብቻ ይወሰኑ ብሏል ሊባል አይችልም፡፡

ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 39/5/ ላይ የብሔራዊ ማንነት ጥያቄ (የብሔር ማህበረሰብ አቋም ጥያቄ) የሚወሰንባቸውን አምስት መሰረታዊ መስፈርቶች አስቀምጧል፡፡ ከእነዚህ አምስት መሰረታዊ መስፈርቶች ባሕርይ መረዳት እንደሚቻለው የብሔር ማህበረሰብ አቋም ጥያቄ ሊወሰን የሚገባው ጠያቂው ማህበረሰብ አባላት በሚሳተፉበት ሕዝበ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን በገለልተኛ አካል ውሳኔም ጭምር ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ሕገ መንግሥቱ የደነገገው የብሔራዊ ማንነት ጥያቄዎች በሶስተኛ ወገን ዳኝነትና በሕዝብ ውሳኔ እንደወሰኑ ነው፡፡ ገለልተኛ አካሉ የሚወሥነው ጠያቂው ማህበረሰብ የቋንቋ፣ የባህልና የአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር መኖር መስፈርቶች መሟላት ወይም አለመሟላታቸውን ሲሆን ጠያቂው ማህበረሰብ ደግሞ በሕዝበ ውሳኔ የሚወሰነው የማህበረሰቡ ህልውና አንድነትና የሥነልቦና አንድነት ምን እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም የቋንቋ፣ የባህልና የአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር መኖር መስፈርቶች በሕዝበ ውሳኔ ሊወሰኑ የሚችሉ ነገሮች ጨርሶ ባለመሆናቸው ነው፡፡ በአጠቃላይ የብሔራዊ ማንነት ጥያቄ የሚወሰነው ከዚህ በላይ በተመለከተው አግባብ የብሔር ማህበረሰብ አቋም ማግኛ/መወሰኛ መስፈርቶች በገለልተኛ አካል ውሳኔ እና በጠያቂው ማህበረሰብ ውሳኔ መሠረት በሙሉ አንድ ላይ ተሟልተው መገኘት ወይም አለመገኘት ላይ በመመስረት ነው፡፡ እነዚህ መስፈርቶች በሙሉ ተሟልተው ከተገኙ ጥያቄው ተቀባይነት አግኝቶ የብሔራዊ ማንነት ዕውቅና ይሰጣል አለበለዚያው ጥያቄው ተቀባይነት አጥቶ የብሔራዊ ማንነት ዕውቅና ይነፈጋል፡፡

የመስፈርቶቹ አወሳሰን ቅደም ተከተል አለው፡፡ የብሔራዊ ማንነት ጥያቄ በቀረበ ጊዜ በቅድሚያ የክልል ምክር ቤት ወይም በፌዴሬሽን ምክር ቤት ሦስት ተጨባጭ የሆኑ መስፈርቶች በሙሉ የተሟሉ ስለመሆኑ ጥልቅ ጥናትና ምርምር በማድረግ መወሰን አለበት፡፡ በዚህ አግባብ እነዚህ ሦስት መስፈርቶች በሙሉ ተሟልተው ያልተገኙ መሆኑ ከተወሰነ ወደ ቀጣዩ ሕዝበ ውሳኔ መሄዱ አግባብነት የለውም፡፡ ወደ ሕዝብ ውሳኔ የሚኬደው ከዚህ በላይ በተጠቀሰው አግባብ በወሳኙ አካል ሦስቱ ተጨባጭ መስፈርቶች ተሟልተዋል ተብሎ ከተወሰነ ብቻ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ሕዝበ ውሳኔ ተደርጎ ማህበረሰቡ ውሳኔን ከገለፀ በኃላ በጥያቄው ላይ ውሳኔ ይሰጣል፡፡

የብሔራዊ ማንነት ጥያቄ ዕውቅና የማግኘት ጥያቄ ብቻ ነው፡፡ ይህ እውቅና ማግኘት ደግሞ የብሔር መብቶችን ያጎናፅፋል፡፡ የብሔር መብቶች ደግሞ በመሰረታዊነት በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት  በአንቀጽ 39 ከንዑስ አንቀጽ (1) እስከ (4) ድረስ ተዘርዝረዋል፡፡ እነዚህን የብሔር መብቶች ለማግኘት የግድ በቅድሚያ ማህበረሰቡ የብሔር ማህበረሰብ አቋም  ዕውቅና ማግኘት ይኖርበታል፡፡ በዚህም የተነሳ በብሔራዊ ማንነት ጥያቄና በብሔር መብቶች ጥያቄ ረገድ ልዩነት መኖሩን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡የብሔር  መብቶችን ማግኘት የሚቻለው የብሔር ማህበረሰብነት ዕውቅና ከተገኘ በኃላ በመሆኑ የብሔር ማህበረሰብ ዕውቅና ይሰጠኝ ጥያቄና የብሔር መብቶች ጥያቄ በአንድ ላይ ሊቀርቡ ጨርሶ አይገባም፡፡ ምክንያቱም ገና ያልተገኘ መብትን ልጠቀም ብሎ መጠየቅ የማይቻል በመሆኑ ነው፡፡

እዚህ ላይ የብሔር ማህበረሰብ አቋም ዕውቅና ማግኛ/መወሰኛ መንገዶችን ምን ምን እንደሆኑ መጠነኛ ቅኝት ማድረጉ ተገቢ ይመስላል፡፡ እስከ አሁን ባለው ልምድ በተለያዩ መንገዶች እውቅና ሲሰጥ ቆይቷል፡፡በመጀመሪያ የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ራሱ በቀጥታ በስም እውቅና የሰጣቸው የብሔር ማህበረሰቦች ያሉ ሲሆን እነሱም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47/1/ ላይ እንደተጠቀሱት ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሱማሌ፣ ቤንሻንጉል(በርታ)፣ ጉሙዝና ሐረሪ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውጭ ሕገ መንግሥቱ በጥቅሉ እውቅና የሰጣቸው የብሔር ማህበረሰቦች እንዳሉ ከሕገ መንግሥቱ፣ ከሕገ መንግሥቱ ማብራሪያና ከሕገ መንግሥቱ ቃለ ጉባኤዎች በመመልከት መገንዘብ ይቻላል፡፡ በ1987 ዓ.ም የሕገ መንግሥቱ ማብራሪያ ላይ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ውስጥ 45 የብሔር ማህበረሰቦች እንዳሉ ጠቅሷል፡፡ በዚህም ነው፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47(2) ላይ በሕገመንግሰቱ አንቀጽ 47(1) ሥር በተመለከቱት ዘጠኝ ክልሎች ውስጥ የተካተቱት ብሔሮች በማናቸውም ጊዜ የየራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት አሏቸው ተብሎ የተገደነገገው፡፡ በዚህኛው መንገድ የብሔር ማህብረሰብ አቋም (status) ዕውቅና የሚሰጠው/የሚገኘው ማህበረሰቡ አቤቱታ/ጥያቄ ባላቀረበበት ሁኔታ ነው፡፡        

ሁለተኛው የብሔር ማህብረሰብ አቋም (status) ዕውቅና ማግኛ/መወሰኛ መንገድ የእውቅና ጥያቄ አንድ የብሔር ማህበረሰብ አቋም ያላገኘ ማህበረሰብ የእውቅና ጥያቄውን በቅድሚያ በሰፈረበት መልክዓ ምድር ውስጥ ለሚገኘው ክልላዊ ምክር ቤት በማቅረብ ነው፡፡ የብሔራዊ ማንነት ጥያቄው በቀረበ ጊዜ ጥያቄው አከራካሪ እንዳልሆነ በክልሉ ም/ቤት በታመነ ጊዜ ያለሕዝብ ውሳኔ በሚመለከተው ክልል ምክር ቤት ዕውቅና ሊሰጠው ይችላል፡፡ በዚህ አግባብ መሠረት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ ም/ቤት በቅማንት የብሔር ማህበረሰብ አቋም ጥያቄን ያለሕዝብ ውሳኔ እውቅና ሰጥቷል፡፡ ጥያቄው አከራካሪ መሆኑ በሚመለከተው የክልል ም/ቤት በታመነ ጊዜበሌላ በኩል የብሔራዊ ማንነት አቤቱታ በሕዝብ ውሳኔ አማካኝነት ሊወሰን ይችላል፡፡ በዚህኛው መንገድ ደግሞ የስልጤ የማንነት ጥያቄ በሕዝብ ውሳኔ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡

የብሔር ማህብረሰብ አቋም (status) ዕውቅና አቤቱታው በሕዝበ ውሳኔ ይወሰን ቢባል ማነው የሕዝበ ውሳኔው ላይ ተሳትፎ የሚያደርገው የሚለው ጥያቄ የመጀመሪያ ጥያቄ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ የአመራረጣቸውስ ሁኔታ እንዴት ነው የሚለውም መሰረታዊ ጥያቄ ይመስላል፡፡ ለምሳሌ የወልቃይት የአማራ ብሔርተኝነት ጥያቄ ብሎ ነገር አለ ቢባልና ጥያቄው በሕዝበ ውሳኔ ይወሰን ቢባል ምናልባትም በሕዝበ ውሳኔው ላይ ሊሳተፉ የሚችሉት በወልቃይት የሚኖሩ አማራዎች ብቻ ናቸው ወይስ በመላ አገሪቱ የሚገኙ አማሮች ናቸው ወይስ በወልቃት ወረዳ ውስጥ የሚገኙ ማናቸውም ነዋሪ ኢትዮጵያዊን ናቸው?፡፡የእነዚህ አመራረጣቸውም ለክልሉ የተተወ እንደሆነ የፌዴሬሽን ም/ቤት በስልጤ የማንነት ጥያቄ ላይ አመልክቷል፡፡

ከዚህ ባሻገር፣ የፌዴሬሽን ም/ቤት አከራካሪ ባልሆነ የብሔር ማህበረሰብ አቋም ላይ በራሱ ተነሳሽነት እውቅና ሲሰጥ ቆይቷል፡፡እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62/3/ መሠረት አከራካሪ በሆኑ የብሔር ማህበረሰብ ዕውቅና ጥያቄ ላይ የመጨረሻ ዕውቅና የመስጠት ሥልጣን አለው፡

በአጠቃላይ የማንነት ፅንሰ ሐሳብ ልዩ መሆኑ ነው፡፡ በሌላ አገገላፅ የአንድ ማህበረሰብ የብሔር ማህበረሰብ አቋም ለማግኘት ዋና ተፈላጊ ነገር ልዩ (distinctiveness) መሆኑ ነው፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥትና የክልሎች ሕገ መንግሥት ይህን ተፈላጊ ነገር የያዙትንና ያልያዙትን ማህበረሰቦች የሚለዩ ደንቦችን አደራጅቷል፡፡ በዚህም መሠረት አንድ የብሔራዊ ማንነት ዕውቅና ይሰጠኝ ጥያቄ መቅረብ ያለበት ጠያቂው አካል ከሌሎች ዕውቅና ካገኙ የኢትዮጵያ ብሔር ማህበረሰቦች የተለየ የሆነ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ አንድ ማህበረሰብ ልዩ ባሕርይ አለው ወይም የተለየ ነው ብሎ የሚወሰነው በአንቀጽ 39/5/ ሥር በተቀመጡት አምስት መመዘኛዎች (መስፈርቶች) ነው፡፡ እነዚህም መስፈርቶች ቋንቋ፣ ባህል፣ ማንነት፣ የሥነልቦና አንድነትና መልክዓ ምድር ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የማንነት ጥያቄን በተመለከተ ካስቀመጣቸው አምስት መስፈርቶች ሦስቱ ማለትም ቋንቋ፣ ባህልና መልክዓ ምድር ተጨባጭ (የሚዳሰሱ) ሁኔታዎች ሲሆን ማንነት ደግሞ ከፊል ተጨባጭ እና ከፊል ተጨባጭ ያልሆነ ሁኔታ ነው፡፡ አምስተኛው መስፈርት የሥነልቦና አንድነት ሲሆን ይህ በግልፅ የማይጨበጥ ሁኔታ (subjective condition) ነው፡፡

በመሆኑም ሕገ መንግሥቱ የማንነት ጥያቄን በተመለከተ ካስቀመጣቸው መመዘኛዎች ውስጥ ተጨባጭ የሆኑ ሁኔታዎች በሙሉ በገለልተኛ ሰው አስተያየት የሚመጠኑ ሲሆኑ ተጨባጭ ያልሆኑ ሁኔታዎች ደግሞ በገለልተኛ ሰው አስተያየት የሚመጠኑ ሳይሆን ጠያቂው ማህበረሰብ በራሱ የሚመጥነው ሁኔታ ነው፡፡ ማህበረሰቡ ልዩ መሆኑን ካረጋገጠ ወይም መሆኑ ከተረጋገጠ ልዩነት ማህበር ወይም የትብብር ምልክት ሆኖ ያገለግላል፡፡

በአጠቃላይ የማንነት ፅንሰ ሐሳብ ልዩ በመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ የብሔር መብቶች ለመጠቀምና ልዩነታቸውን ለመጠበቅ የሚፈልጉ የብሔር ማህበረሰብነት ዕውቅና ያላገኙ ማህበረሰቦች በቅድሚያ የማንነት ዕውቅና ይሰጠን ጥያቄ (አቤቱታ) በየደረጃው በሚመለከታቸው የክልልና የፌዴራል አስተዳደሮች ዘንድ በማቅረብ እውቅና በማሰጠት ማስታወቃቸው የግድ ነው፡፡ ዕውቅና ላልተሰጣቸው ማህበረሰቦች የብሔር መብቶችን ከመስጠታችን በፊት ማህበረሰቦች ልዩ (ብሔር) መሆናቸውን ሥልጣን ባለው አካል ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ በብሔር መብቶች ለመጠቀም መኖር የሚባል ልዩ መሆን ሁኔታ የብሔር መብቶች በሚገባ እንዲጠበቁ ሲፈለግ እውቅና ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም በዕውቅና ሰጪ አካላት አማካኝነት ለዕውቅና የቀረበው ማንነት በስራ ላይ በቀደምት መዋል አለመዋል ለማረጋገጥ የሚደረገውን ማጣራት (ቁጥጥር) ሊጨምር ይችላል የሚለውን ጠቅላላ ድንጋጌ የሚደግፍ ያደርገዋል፡፡ ይህ ሁኔታ እንዲሟላ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39/5/ ላይ ተጠይቋል፡፡ እንዲሁም በጥቅም ላይ መዋሉ በጣም የሚደገፍ ነው፡፡ ዕውቅና ማሰጠት የብሔር ማህበረሰቡን ልዩ መሆን ሕዝብ እንዲያውቀው ከመርዳቱም በላይ ሌሎች ሰዎችና የመንግሥት አካላት ልዩነቱን አውቀው እንዲያከብሩ ማስጠንቀቂያ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህም በላይ ሕግ እንደመሆኑ መጠን የመንግሥት አስተዳደሮች የብሔር ማህበረሰብ መብቶችን በሚመለከቱበት ጊዜ ዋጋ ሊሰጡት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

ስለሆነም እውቅና ይሰጠው የተባለው ማንነት በሃገሪቱ በየትኛውም ክፍል በሚገኝ መልክዓ ምድር ውስጥ የሰፈረ ማህበረሰብ እውቅና የተሰጠው ከሆነ ይህ እውቅና ያገኘው የብሔር ማህበረሰብ ከሰፈረበት መልክዓ ምድር ውጭ የሚገኝ ማናቸውም ማህበረሰብ ይህንኑ ማንነት እንዳለኝ እውቅና ይሰጠኝ ብሎ የሚያቀርበው የማንነት ጥያቄ ሊኖር አይችልም፡፡

ይህ ከሆነ የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ብሔርተኝነት ጥያቄ ብሎ ነገር እንዴት ሊቀርብ ይችላል? የአማራ የብሔር ማህበረሰብነት አስቀድሞ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47/1/ /3/ ዕውቅና የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከዚህ አልፎ የአማራ ብሔር ማህበረሰብ ክልል የመመሥረት መብቱን ጥያቄ ማቅረብ ሳያስፈልገው በራሱ አክብሮታል፡፡ ይህንንም የአማራ ክልል ከሚለው ስያሜ እና ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47/2/ መሠረታዊ መንፈስና ይዘት መገንዘብ አዳጋች አይደለም፡፡ በዚህ መሠረት ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀበት ጊዜ አስንቶ እስከ አሁን የብሔር እውቅና አግኝቶ የብሔር መብቶችን በመጠየቅ እያጣጣመ ያለ የብሔር ማህበረሰብን ማንነት በሌላ ክልል ውስጥ በተከለለ መልክዓ ምድር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39/5/ መሠረት ዕውቅና ያገኘው ማንነትን ዕውቅና ይሰጠን ብለው ሊጠይቁ የሚያስችላቸው መብት የላቸውም፡፡

የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄ፤ የጥያቄ አገላለፅ እንደሚያሳየው የወልቃይት ሕዝብ የማንነት ዕውቅና ሊያሰጠው የሚችል ልዩ ማንነት የለውም፡፡ የማንነት ጥያቄው ከጥያቄ አገላለፅ እንደሚያሳየው በወልቃይት መልክዓ ምድር ውስጥ የሰፈረ የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ብሔርተኝነት እውቅና ይስጠው የሚል ነው፡፡ የአንድ የማንነት ጥያቄ ዋና ተፈላጊ ባሕርይ ልዩ መሆኑ ነው፡፡ የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ይህን ዋና ተፈላጊ ባሕርይ ጠያቂው አካል ያለው መሆን አለመሆኑን የሚለይበትን ደንብ በአንቀጽ 39/5/ ላይ አደራጅቷል፡፡

አንድ ማህበረሰብ ልዩ ያልሆነ የማንነት ጥያቄ ያቀረበ እንደሆነ ይህ ማንነት ተፈላጊውን ልዩነት የማያሟላ በመሆኑ የማንነቱ ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ዕውቅና ሊሰጠው አይችልም፡፡ አንድ የማንነት ጥያቄ ልዩነቱን ያጣ ከሆነ ከመነሻው ሊቀርብ አይችልም፤ ከቀረበም ተቀባይነት አያገኝም፡፡ ለዚህም ነው ጥያቄው በጽሑፍ መቅረብ አለበት እንዲሁም ጽሑፉ በአንቀጽ 39/5/ ላይ የተመለከቱት መስፈርቶች የተሟሉ መሆኑን በማሳየት መቅረብ ይገባዋል ተብሎ በስልጤ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የወሰነው፡፡

በኢትዮጵያ ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት መሠረት የብሔር ማንነት ጥያቄ (አቤቱታ) ማቅረብ መብት ያለው ማን ነው? እዚህ ላይ አንድ ወገን የማንነት ጠያቂ ሆኖ ለመቅረብ የሚጠይቀውን መመዘኛ አንስተን በሰፊው እንመለከታለን፡፡ በሕገ መንግሥት አንቀጽ 39/5/፣ 62/3/ እና በአዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀጽ 19/1/ ላይ ጠያቂው ወገን ለጥያቄው መነሻ በሆነው ነገር ወይም ክሱ በተመሰረተበት ጉዳይ ላይ መብት ያለው ካልሆነ በስተቀር የብሔራዊ ማንነት ጥያቄ ማቅረብ አይፈቀድለትም በማለት ተደንግጓል፡፡ የዚህ መርህ ጠቀሜታ አንድ መብት ከተጎናፀፈው ሰው በቀር ሌላ ሰው/ሰዎች ጥያቄ እንዳያቀርቡ ለማድረግ ነው፡፡

የዚህ መርህ ሌላኛው ጠቀሜታ የማንነት ጥያቄ ጉዳይ በተመለከተ ራሱ ባሉጉዳዩ ነው አቤት ማለት ያለበት፡፡ በዚህም በአንድ ማንነት ጉዳይ ላይ ሁለት ጊዜ ጥያቄ እንዳያቀርብ ለማድረግ ይረዳል፡፡ የማንነት ጥያቄ የመብት ማስከበር ጉዳይ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ መብት ከመነሻው ከሌለው መብት ማስከበር ብሎ ነገር የለም፡፡ በትግራይ ክልል ውስጥ የሚኖሩ የአማራ ተወካዬች ነን ባዬች በምንም መልኩ የማንነት ጥያቄ የማቅረብ መብት የላቸውም፡፡ የብሔራዊ ማንነት ጥያቄ የማቅረብ መብት የሌለው ወገን የማንነት ጥያቄ ከመነሻው እንዳያቀርብ ማድረጉ ቢያንስ ሁለት ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ አንደኛው መብት የሌለው ሰው መብቴ ይከበርልኝ ብሎ ቢጠይቅ የጊዜና የሃብት ብክነትን ከማስከተሉ በቀር በሂደቱ በስተመጨረሻ የሚጠይቀውን ዳኝነት በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው መልክ ቅርፅ አግባብ ሊያገኘው አይችልም፡፡ የማንነት ጥያቄ ዕውቅና የማግኘት ጥያቄ ብቻ ነው፡፡ የጥያቄው መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ዕውቅና መስጠት ወይም ዕውቅና መንፈግ ነው፡፡ ይህ በስተመጨረሻ የሚወሰን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የማንነት ጥያቄ ጠያቂ ወገን ጥያቄ የሚያቀርብበት የጥያቄ ምክንያት ሊኖረው እንደሚገባ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ የጥያቄ ምክንያት የማንነት ጥያቄን አስመልክቶ በሚቀርበው ፅሑፍ (ማመልከቻ) ላይ ቢያንስ በፍሬ ነገር ረገድ ተዘርዝሮና ተብራርቶ መገለፅ ይኖርበታል፡፡ የማንነት ጥያቄ ማመልከቻ አመልካቹ መብቱን የሚጠብቅበትን በአጭሩ የያዘ መሆን አለበት፡፡ በአዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀጽ 2/1/ ድንጋጌ መሠረት የማንነት ጥያቄን በሚመለከት በሚቀርብ ፅሑፍ ላይ የጥያቄው ይዘት በዝርዝር የሚያሳይ መሆን አለበት ወይም ዋና ዳኝነት የተጠየቀበትን ፍሬ ነገሮች በአጭሩ መገለፅ አለበት፡፡ ይህ ካልተገለፀ ጥያቄው ከመጀመሪያው ወደ ጥያቄው ፍሬ ጉዳይ ሳይገባ የጥያቄ ሕጋዊ ምክንያት የለውም ተብሎ ውድቅ ሊደረግ ይገባል፡፡

በዚህም ራሱ ጠያቂው ወደ ጉዳዩ ዳኝነት ቢገባ የሚያባክነው ጊዜ፣ ጉልበትና ሃብት እንዲጠብቅ ያደርጋል፡፡ በሌላ በኩል የማንነት ጥያቅው የሚመለከተው ክልል መንግሥት በእንዲህ አይነት ጥያቄ የተነሳ ከሚያባክነው ጊዜ፣ ጉልበትና ሃብት ተጠብቆ ጊዜውን ጉልበቱንና ሃብቱን በሙሉ በልማት ስራ ላይ እንዲያውለው ያስችላል፡፡ ሁለተኛ እንዲሁም ጉዳዩን የሚዳኘው አካል የጥያቄው መሠረት የሆነ መብት የሌለ መሆኑን ከማመልከቻው በሚገባ መረዳት በተቻለ ጊዜ ውድቅ ማድረግ ሲገባው ወደ ዋናው ጉዳይ በመግባት ሂደቱን በማስቀጠል ከወሰደው ጊዜ፣ ጉልበትና የሕዝብ ሃብት ብክነት መጠበቅ ይቻላል፡፡

ይህ ካልሆነ የሕግ የበላይነት ሊሰፍን አይችልም፡፡ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር አደጋ ላይ ይወደወቃል ዕድገትም የሚታሰብ አይሆንም፡፡ የሕግ የበላይነት (Rule of law) የሚሰፍነው ዜጎች፣ ቡድኖችና ባለስልጣናት ሕጎችን ሲያከብሩ ነው፡፡ የሕጎች መከበር ግለሰቦች ሆኑ ቡድኖች ለሕግ ተገዥነታቸውና በሕግም ፊት እኩል መታየታቸውን ያረጋግጣል እንዲሁም ማንም ሰው ወይም ቡድን ከሕግ ውጭ በዘፈቀደ በባለስልጣኖችም በሆነ በሌሎች ግለሰቦች ወይም ቡድኖች መንገላታት እንዳይደርስበት/ እንዳይደርስባቸው ይከላከላል፡፡ ይህን ዓላማና ግብ መሠረት አድርጎ ነው ፍትህ የማግኘት መብት መቃኘት ያለበት፡፡ በዚህም አስተሳሰብ በቀላል ወጪ ጥራት ያለው ፍትሕ የማግኘትን መብት እውን ለማድረግ ይቻላል፡፡

እርግጥ ነው አንዳንድ ጊዜ ልዩ በሆኑና በሕግ መጠበቅ ባላቸው ማንነቶችና ልዩ ባልሆኑ ማንነቶች መካከል ያለው መለያየት በጣም ግልፅ ባለመሆኑ ወይም መለያየቱን ባለመረዳት የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄ አስከትሏል፡፡ ሕገ መንግሥቱ እንደሚለው በአንድ የማንነት ዕውቅና በማግኘት የብሔሩ መብቶች የመጠቀም መብትን የያዙት የብሔር መብቶች በሕገ መንግሥቱ በተቀረፀላቸው ቅርፅ ልክ መሠረት ይተዳደራሉ፡፡ የማንነት ጥያቄ ጉዳዩችን የሚመለከት በአሁኑ ጊዜ ስራ ላይ የዋለ ዝርዝር የኢትዮጵያ ልዩ ሕግ የለም፡፡እርግጥ ነው፤ የክልሎች ሕገ መንግሥት በዚህ ረገድ መብት ካጎናፀፈ ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ የኦሮሞ ማህበረሰብ በአማራ ክልል ውስጥ ዕውቅና ተሰጥቶት የራሱ የብሔረሰብ ዞን ያቋቋመው በፌዴራል ሕገ መንግሥት መሠረት መብት ኖሮት ሳይሆን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሕገ መንግሥት በዚህ ረገድ ዕውቅና የሰጠው በመሆኑ ነው፡፡

ከዚህ ውጪ፤ አስቀድሞ ዕውቅና ያገኘን ና ልዩ ያልሆኑ ማንነት ዕውቅና ይሰጠው ብሎ በሌላ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሊጠይቁ መብት የላቸውም፡፡ ይህም ክርክር ቢያንስ በአራት ሕገመንግስታዊ መሰረቶች ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ይኸውም፡-

የአንድ ማህበረሰብ የብሔር ማህበረሰብ አቋም ለማግኘት ዋና ተፈላጊ ነገር ልዩ (distinctiveness) መሆኑ ነው፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥትና የክልሎች ሕገ መንግሥት ይህን ተፈላጊ ነገር የያዙትንና ያልያዙትን ማህበረሰቦች የሚለዩ ደንቦችን አደራጅቷል፡፡ አንድ ማህበረሰብ ልዩ ያልሆነ የማንነት ጥያቄ ያቀረበ እንደሆነ ይህ ማንነት ተፈላጊውን ልዩነት የማያሟላ በመሆኑ የማንነቱ ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ዕውቅና ሊሰጠው አይችልም፡፡ አንድ የማንነት ጥያቄ ልዩነቱን ያጣ ከሆነ ከመነሻው ሊቀርብ አይችልም፤ ከቀረበም ተቀባይነት ሊያገኝ አይችልም፡፡ ለዚህም ነው ጥያቄው በፅሑፍ መቅረብ አለበት እንዲሁም ፅሑፉ በአንቀጽ 39/5/ ላይ የተመለከቱት መስፈርቶች የተሟሉ መሆኑን በማሳየት መቅረብ ይገባዋል ተብሎ በስልጤ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የወሰነው፡፡

ሁለተኛው ዕውቅና ይሰጠው የተባለው ማንነት ከዚህ ቀደም ዕውቅና ያልተሰጠው መሆን አለበት፡፡ ጥያቄው አስቀድሞ ዕውቅና ያገኘ የብሔር ማንነትን የሚመለከት በመሆኑ በድጋሚ ዕውቅና ሊሰጠው የማይገባ በመሆኑ ነው፡፡ ይህንንም ከቅማንትና ከስልጤ ጉዳዩች እና ውሳኔዎች መመልከት ይቻላል፡፡የስልጤና የቅማንት ብሔራዊ ማንነት ጥያቄዎችና አወሳሰናቸው ይህንኑ ያሳያል፡፡ በዚህም መሠረት የስልጤና የቅማንት ማህበረሰብ የብሔር ማህበረሰብነት አቋም እውቅና አግኝተዋል፡፡የቅማንት ማህበረሰብ ሆነ የስልጤ ምህበረሰብ የብሔር ማህበረሰብ ዕውቅና ይሰጠን በማለት ጥያቄ ያቀረቡት ከዚህ ጥያቄ በፊት የቅማንት ሆነ የስልጤ ማህበረሰብ የብሔር ማህበረሰብነት ዕውቅና ያላገኘ በመሆኑ ነው፡፡ ከእነዚህ ሁለት የማንነት ጥያቄዎች መገንዘብ እንደሚቻለው የማንነት ጥያቄ ሊኖር የሚችለው ሆነ ተቀባይነት የሚኖረው የተጠየቀው የብሔር ማህበረሰብ ማንነት ከዚህ ቀደም እውቅና ያላገኘ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ አስቀድሞ የብሔር ማህበረሰብነት እውቅና ያገኘ ማንነት በድጋሚ እውቅና ይሰጠን ብሎ መጠየቅ ጨርሶ እንደማይቻል ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39/5/ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በስልጤ እና በቅማንት ጉዳይ ከሰጠው ውሳኔ እንዲሁም የደቡብና የአማራ ክልሎች በቅማንትና በስልጤ ጉዳይ ከሰጧቸው ውሳኔዎች እና ከእነዚህ ጥያቄዎች ባሕርይ መረዳት ይቻላል፡፡

የብሔር መብቶች ከሰብአዊ መብቶች የሚለዩት የብሔር መብቶች ቡድናዊ (የቡድን) መብት በመሆኑ ነው፡፡ ሰብአዊ መብት ግን ግለሰባዊ ነው፡፡ የቡድን መብት ሲባል መብቱ በአንዴ በጋራ የሚሰራበት ማለት ነው፡፡  የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39/1/፣ /3/ እና /5/ እንደሚያስገነዝበው በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩና የብሔር ማህበረሰብ ባሕርይ የሚያሳይ እያንዳንዱ የብሔር ማህበረሰብ በሰፈረው መልክዓ ምድር ውስጥ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ መብት አለው፡፡ እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከኢትዮጵያ መነጠል ከፈለገ የሰፈረበትን መልክዓ ምድር ይዞ የመነጠል መብት አለው፡፡ ለዚህም ነው የሕገ መንግሥቱ መግቢያ #እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ህዝቦች - - - የየራሳችን መልክዓ ምድር አሰፋፈር የነበረንና ያለን - - -; በማለት የተጠቀሰው፡፡

ከዚህ በላይ፤ በተጠቀሱት ድንጋጌዎች መሠረት የብሔር መብቶች የድንበር ባሕርይ አላቸው ማለትም በድንበር የተወሰኑ (territorial approach to ethnic rights) ናቸው፡፡ የወልቃይት መልክዓ ምድር ውስጥ የሰፈረው ሕዝብ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 /3//5/ እና 46/2/ መሠረት የትግራይ ማንነት ባሕርይ የሚያሣይ መሆኑ ታምኖበት ከሽግግር ዘመኑ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ በትግራይ ክልል ውስጥ ተከልሎ የሚገን ምድር ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ክልል ውስጥ የሚገኙ የአማራ ተወላጆች በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ሆነ በትግራይ ሕገ መንግሥት መሠረት የአማራ ማንነት እውቅና ይሰጠን ብለው የመጠየቅ ሕገመንግስታዊ መብት የላቸውም፡፡ ዕውቅና የማግኘት መብት የሌላቸው በመሆኑ በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙት የአማራ ብሔር መብቶች ሊኖሩ አይችሉም፤ የሚሰጥበትም የአማራ ብሔር መብቶች የሉም፡፡

የብሔር መብቶች በብሔሩ መልክዓ ምድር ወይም ክልል የተወሰኑ ናቸው፡፡ የብሔር የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከመገንጠል ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ዕውቅና የተሰጠው በሽግግሩ ቻርተር ነው፡፡ የብሄሮችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል ተቋማዊ ለማድረግ ሲባል በሽግግር ጊዜ በወጣው አዋጅ ቁጥር 7/1992 አማካኝነት ብሄሮች የየራሳቸውን ክልል በሰፈሩበት መልክዓ ምድር ወሰን ውስጥ ሊመሰርቱ እንደሚችሉ ተደንግጓል፡፡ ይህም ማለት ክልሎች የሚደራደሩት በዋናነት በማንነት ላይ ነው ማለት ነው፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥትም ከቻርተሩ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አቋም ይዟል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም ነው የሚባለውም ክልሎች የሚደራጁት በማንነት ላይ በመሆኑ ነው፡፡ ይኸውም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47/1/ እና 47/2/ ላይ ተመልክቷል፡፡አንቀጽ 47/1/ ዘጠኝ ክልሎች የጠቀሰ ሲሆን እነዚህም ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች፣ የሀረሪ ሕዝብ ክልል እና የጋምቤላ ክልል ናቸው፡፡ የክልሎች ስያሜ ስለ ክልሎች የብሔር ስብጥር ከወዲሁ ይጠቅሳል፡፡

አንቀጽ 47/1/፣ /2/፣ /3/፣ /4/፣ /6/ እና /9/ እንደሚያሳዩት ትግራይ፣ አፋር፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሶማሌ እና ሐረሪ ህዝቦች የየራሳቸው ክልል አላቸው፡፡ ትግራዊያን የትግራይ ብሔር መብቶች በትግራይ ክልል ውስጥ ይጠቀማሉ፣ አፋሮች ደግሞ በአፋር ክልል ውስጥ ያከናውናሉ፣ አማራዎች ደግሞ በአማራ ክልል ውስጥ ይሰሩበታል፣ ኦሮሞዎችም እንዲሁ በኦሮሞ ክልል ውስጥ ይሰሩበታል፣ ሱማሌዎችም በተመሳሳይ በሱማሌ ክልል ውስጥ እንዲሁም ሐረሪዎች በሐረሪ ክልል ውስጥ ብሔራዊ መብቶቻቸውን ያራምዳሉ፡፡

ሕገ መንግሥቱ የብሔር መብቶች ክልል በመመስረት በበለጠ የሚጠበቁበትን ዘዴ ነድፏል፡፡ ይህንንም ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47/1/ ላይ መረዳት ይቻላል፡፡ ይኸውም ድንጋጌ ክልል ያልመሰረቱ ብሔሮች በማናቸውም ጊዜ ከፈለጉ ክልል የማቋቋም መብት እንዳላቸው ደንግጓል፡፡ ይህን ድንጋጌ ከመገንጠል መብትና ራስን በራስ ከማስተዳደር መብት ጋር በጋራ ስንመረምረው ማንኛውም ዕውቅና የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ በኢትዮጵያ ሥር የራሱን ክልል በሰፈረበት መክዓ ምድር የማቋቋም መብት እንዲሁም የሰፈረበትን መልክዓ ምድር እንደያዘ የመገንጠል መብት እንዳለው መገንዘብ የሚቻል ይሆናል፡፡ በዚህም ብሔሩ የሰፈረበት መክዓ ምድር ወይም ብሔሩ ከመሰረተው ወይም ካለው ክልል ወሰን ጋር በጥብቅ የተቆራኙ ናቸው፡፡

አንቀጽ 39 ስለ ቋንቋ፣ ባህል እና ራስን በራስ ስለማስተዳደር መብቶች ደንግጓል፡፡ እነዚህ መብቶች የብሔር የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን መብቱ አካል ናቸው፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት እነዚህ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት አካል የሆኑ መብቶች በድንበር ወሰን ዘዴ (territorial approach mechanism) ተግባራዊ እንዲደረግ ይፈለጋል፡፡ ይሁንና አንቀጽ 39 በተጨማሪ የብሔር ቡድኖች በክልል እና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብት እንዳላቸውና ይህም መብት የብሔር የራሱ በራሱ የማስተዳደር ሙሉ መብት አካል መሆኑን ደንግጓል፡፡ ይህ ሚዛናዊ ውክልና የብሔር ማህበረሰቦች በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውሳኔዎች ውስጥ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ እንዲሁም በብሔር ማህበረሰቦች መካከል አንድነትን ለማጠናከር ዕድልን ይፈጥራል፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት የውክልና ዋስትናን በተመለከተ የያዘው ጥቂት ድንጋጌዎች ብቻ ነው፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት ምክር ቤቶች ሁለት ሲሆኑ እነዚህም የሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ናቸው፡፡ የሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት አባላት የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዩች ሲሆኑ እነሱም የሚመረጡት በየአምስት ዓመቱ ሆኖ ሁሉ አቀፍ፣ ነፃ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛ ሆነና ድምፅ ሚስጢር ሚሰጥበት ሥርዓት ነው፡፡ በሌላ በኩል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት የኢትዮጵያ የብሔር ማህበረሰቦች ተወካዩች ስብስብ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ የኢትዮጵያና የብሔር ማህበረሰብ ቢያንስ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውስጥ አንድ ተወካይ ይኖረዋል፡፡ በተጨማሪም የብሔር ማህበረሰቡ አንድ ሚሊዩን ሕዝብ አንድ ተጨማሪ ወኪል ይኖረዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት 112 ሲሆኑ እነዚህ አባላት 69 የተለያዩ የኢትዮጵያ የብሔር ማህበረሰቦችን የወከሉ ናቸው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በክልል ምክር ቤት ይመረጣሉ ወይም የክልል ምክር ቤቱ የብሔር ማህበረሰቡ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወካዩች በቀጥታ በህዝቡ እንዲመረጡ ከወሰነ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የብሔር ማህበረሰቡ ተወካዩች በብሔር ማህበረሰቡ በቀጥታ ይመረጣሉ፡፡ እስከ አሁን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በክልል ምክር ቤት የሚመረጡበት አሰራር የሰፈረና አንድ ጊዜ ክልል እስከአሁን የብሔር ማህበረሰቡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በብሔር ማህበረሰቡ እንዲመረጡ የወሰነበትና ያደረገበት ሁኔታ የለም፡፡

እዚህ ላይ እስከአሁን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ስብስብ ዝርዝርን ስንመረምረው የብሔራዊ ልዩነት ድንበራዊ አቋም ወይም ዘዴ ሃይል መልሶ ይመጣል፡፡ የብሔር ማህበረሰቦችን ከተወሰነ መልክዓ ምድር ጋር የተቆላለፈ ወይም የተቆራኘ በመሆኑ በብሔር ማህበረሰብና በግዛት መካከል ማህበር (ህብረት) አለ፡፡ ስለዚህ የእያንዳንዱ የኢትዮጵያ የብሔር ማህበረሰብ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወካይ የብሔር ማህበረሰቡ ከሰፈረበት መልክዓ ምድር የሚመረጡ መሆኑ አመክዩአዊ ነው፡፡ ነገሩን በምሳሌ ለማሳየት ያህል የአማራ ብሄረሰብ የራሱ የሆነ ክልል ያቋቋመ በመሆኑ የአማራ ብሔረሰብ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወካዩች በክልሉ ምክር ቤት የሚመረጡት ከአማራ ክልል ነው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ዝርዝር እንደሚያሳየው ሁሉም 114 የአማራ ብሔር ማህበረሰብ ተወካዩች የተመረጡት ከአማራ ብሔራዊ ክልል ነው፡፡ ብዙ የአማራ ብሔር ማህበረሰብ ተወላጆች ከአማራ ክልል ውጪ እንደሚኖሩ ይታወቃሉ ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ይሁንና የኦሮሚያ ክልል በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆችን በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚወከሉ ሰዎች ልኮ አያውቅም፡፡ በመሆኑም በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚወከሉት በአማራ ክልል ምክር ቤት በተመረጡ የአማራ ተወካዩች ነው፡፡ ኦሮሞ ብሔር ማህበረሰብም ተመሳሳይ ነው፡፡ በፌዴሬሽን ምክር ቤት 20 የኦሮሞ ብሔር ተወካዩች ያሉ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ አስራ ዘጠኙ በኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት የተመረጡ ናቸው፡፡ አንደኛው የኦሮሞ ብሔር ተወካይ ደግሞ በአማራ ክልል ምክር ቤት የተመረጠ ነው፡፡ አንድ የኦሮሞ ተወካይ በአማራ ክልል ምክር ቤት መመረጡ ከብሔራዊ ልዩነት የድንበር ወሰንተኝነት ዘዴ/አቋም ማፈንገጥ አይደም፡፡ ይልቁንም ይህንኑ ዘዴ/አቋም የሚያጠናክር ነው፡፡ የኦሮሞ ብሔር ማህበረሰብ የራሱ ክልል ብቻ ያለው ሳይሆን የኦሮሞ ብሔር በአማራ ክልል ውስጥ የራሱ የሆነ የብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አለው፡፡ ይህም ማለት ኦሮሞ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን መብቱን በኦሮሚያ ክልል እና በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ውስጥ የመጠቀም መብት አለው ማለት ነው፡፡ የብሔር ማህበረሰብ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚወከለው በብሔሩ መልክዓ ምድር ወሰን መስፈርት መሆኑን በክልል መንግስታት (አስተዳደር) ደረጃም ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ ከዚህ በላይ በተመለከትናቸው የብሔራዊ ልዩነት ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፎች በሙሉ መልክዓ ምድራዊ አቋም (ዘዴ) ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን በግልፅ መገንዘብ ይቻላል፡፡

በጠቅላላው ብሔራዊ ማንነት ጥያቄ ደንቦች ቢያንስ ሁለት ጠቅላላ (general) መለኪያዎች እንዲሟሉ ይጠይቃሉ፡፡ የማንነት ጥያቄ መለኪያዎች ውስጥ አንደኛው ጥያቄ አቅራቢው አካል ለጥያቄው ምክንያት የሚሆን መብት ሊኖረው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ጥያቄው የመብት ማስከበር ጥያቄ በመሆኑ የሚከበርለት መብት ሊኖረው ግድ ይላል፡፡ መብት (right) ማለት ደግሞ የሕግ ጥበቃ የተደረገለት ጥቅም (legal right) ማለት ነው (አንቀጽ ሕገ መንግሥት 39/5/) ፡፡ዕውቅና ይሰጠው የተባለው ብሔራዊ  ማንነት በዝህ ጠቅላላ (general) መለኪያ ሥነጠር ልዩነት(distinctiveness) ካሳየ  ዕውቅና ይሰጠዋል ፡፡ ሁለተኛው መለኪያ ደግሞ ዕውቅና ይሰጠው የተባለው ብሔራዊ ማንነት ከዚህ ቀደም ዕውቅና ያልተሰጠው መሆን አለበት፡፡ ጥያቄው አስቀድሞ ዕውቅና ያገኘ የብሔር ማንነትን የሚመለከት በመሆኑ በድጋሚ ዕውቅና ሊሰጠው የማይገባ በመሆኑ ነው፡፡ ይህንንም ከቅማንትና ከስልጤ ጉዳዩች እና ውሳኔዎች መመልከት ይቻላል፡፡

2.   ስለ ብሔር ማንነት ዕውቅና ውጤት    

አንድ ማህበረሰብ በሕገ መንግሥቱ የተጠቀሱትን የብሔር መብቶች ልጠቀም ወይም በስራ ላይ ይዋልልኝ ብሎ ከመጠየቁ በፊት የማህበረሰቡ ልዩነት ዕውቅና እንዲያገኝ ማድረግ በቅድሚያ ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም በሕገ መንግሥቱ ከአንቀጽ 39/1/ እስከ 39/4/ የተጠቀሱት መብቶች ባለቤት የብሔር ማህበረሰብ በመሆኑ ነው፡፡ በእነዚህ የብሔር ማህበረሰቦች መጠቀም ሲችሉ የብሔር ማህበረሰብ ዕውቅና ያላቸው ማህበረሰቦች ደግሞ በእነዚህ የብሔር መብቶች ጨርሶ ሊጠቀሙ አይችሉም፡፡

ስለሆነም በኢትዮጵያ ውስጥ አንድን ማህበረሰብ በብሔር መብቶች ከመጠቀሙ በፊት ብሔራዊ ልዩነቱን ዕውቅና እንዲያሰጥ የሚያዝ ሕግ አለ፡፡ ይኸውም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39/5/ ነው፡፡ እንደሁም በአዋጅ ቀትር 251/1993 አንቀጽ 19 ላይ ተመልክተል፡፡ ከዚህም በላይ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በስልጤ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ላይም  ተወሰነል፡፡ የብሔራዊ ልዩነት ዕውቅና ማግኘት የሚያስከትለውን ሕጋዊ ውጤት የሚናገር ሕግ ያለ በመሆኑ ዕውቅና ማግኘቱ ሕጋዊ ውጤትን ያስከትላል፡፡ በመሆኑም ዕውቅና ማግኘት የሚሰጠው ሕጋዊ አገልግሎት አለ፡፡ ሆኖም ዕውቅና ማግኘቱ የሚያስከትለውን ሕጋዊ ውጤት በመወሰን ረገድ ሊኖር የሚችለውን ችግር የሚመለከታቸው የክልልና የፌዴራል አስተዳደሮች ሊመለከቱት የሚያስፈልግ ይመስላል፡፡ በዚህም የሕጋዊ ውጤቱን ወሰን አመለሸጋ በሆነ ዘዴ አስቀድሞ ለመፍታት የሚቻልበትን ሁኔታ መፍጠር የሚቻል ይመስላል፡፡

አንድ ዕውቅና ያገኘ ልዩነት የሚያስከትለው ሕጋዊ ውጤት የህብረት (የጋራ) የብሔር መብቶችን ነው፡፡ ብሔራዊ ልዩነቱ ዕውቅና ማግኘቱ የሚያስከትለው ሕጋዊ ውጤት አንድ የጋራ የብሔር ማህበረሰብን መብቶች ነው፡፡ ዕውቅናውም የሚያስከትለው ሕጋዊ ውጤት በመልክዓ ምድራዊ ወሰን ይኖረዋል፡፡ ወሰኑም ዕውቅና ያገኘው የብሔር ማህበረሰብ የሰፈረበት መልክዓ ምድር ነው፡፡ እንዲሁም የማንነት ጥያቄ ዕውቅና ማግኘቱ ዕውቅና ያገኘው ማህበረሰብ የክልል ወሰን አከላለል ለውጥ ጥያቄ የማቅረብ መብትን አያስከትልም፡፡ ይህንንም ከአንቀጽ 48 አወቃቀር፣ ድንጋጌ እንዲሁም ከአንቀጽ 39 በሚገባ መረዳት የሚቻል ይመስላል፡፡

3.    የክልሎች ወሰን ለውጥ ጥያቄ    

3.1 የክልሎች ወሰን ለውጥ ጥያቄ ባሕርይና ጥያቄውን የማቅረብ መብት

የክልሎች ወሰን ለውጥ ጥያቄ ምንድ ነው? ጥያቄውን የማንሳት መብት ያለው ማን ነው? ሕጉስ እንዴት ነው የሚጠበቀው? የዚህ ክፍል ዓላማ እነዚህን ጥያቄዎችና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚመለከቱትን ሕገ መንግሥታዊና ሌሎች የበታች ሕጎች በመመርመር (በመዳሰስ) ምላሽ መስጠት ነው፡፡                   

የዚህ ጥያቄ (አቤቱታ) መሠረትና ምንጭ በሕገ መንግሥቱና በአዋጅ ቁጥር 251/1993 ላይ ተደንግል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 48/2/ ላይ ክልሎች የክልል ወሰን ለውጥ ጥያቄ (አቤቱታ) የማቅረብ መብት እንዳላቸው ደንግል፡፡ እርግጥ ነው የዚህ ድንጋጌ መሠረት የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39/1/ እና /3/ እንዲሁም 46/2/ መሆናቸውን መረዳት ከባድ አይደለም፡፡ አዋጅ ቁጥር 251/1993 ደግሞ በአንቀጽ 27 28 29 30 እና 31 ላይ ከዚህ በላይ የተደነገጉትን ሕገመንግስታዊ መርሆዎችን ገቢራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ የተባሉ ዝርዝር ጉዳዮች ደንግል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39/1/ /3/ የተጠቀሰው እያንዳንዱ ብሔር በሰፈረበት መልክዓ ምድር ውስጥ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መንጠል መብቱ ተግባራዊ ለማድረግ እና ተቋማዊ ቅርፅ ለመስጠት ብሔሩ የሰፈረበት መልክዓ ምድር በክልል ደረጃ ማካለል ያስፈልጋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ቃለ ጉባኤ ላይ እንደተመለከተው ለዘመናት በሃገሪቱ የደረሰው የህዝቦች አመፅ የሚያመላክተው ብሔር፣ ብርሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር ባላቸው ፍላጎት ያደረጉት የመብት ማስከበር እንቅስቃሴ በመሆኑ ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት በቋንቋ፣ በባህል እና በሥነልቦና አመለካከት ቀረቤታ ያላቸውን በአንድ ክልል ሥር እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል በሚል አስተሳሰብ መሠረት የክልል አከላለል በዋናነት በማንነት ላይ እንዲመሠረት ተደርል፡፡ በዚህ የተነሳ በቅድሚያ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39(3)(5) እና 46(2) መሠረት የክልሎች ወሰን ይካለላል፡፡ ከዚህ በኃላ የክልሎች ውስጥ ለውስጥ ጥያቄ በተነሳበት ጊዜ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48/2/ መሠረት ጥያቄው ምላሽ ያገኛል፡፡

የክልሎች ወሰን ለውጥ ጥያቄ (አቤቱታ) አግባብነት ያላቸው ሕጎች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 488() የተደነገገው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀጽ ከአንቀጽ 23 -31 ድረስ የተደነገጉት ናቸው፡፡ እነዚህም የክልሎች ወሰን ለውጥ ጥያቄ (አቤቱታጥያቄ ሕጋዊ መሠረት ምንጭ ናቸው፡፡ በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 48/2/ የሚደነግገው በአጎራባች ክልሎች መካከል የሚነሳ የወሰን ክርክር ስለሚፈታበት ዲሞክራሲያዊ መንገድ ነው፡፡ በክልሎች መካከል የወሰን ለውጥ ጥያቄ በተነሳበት ጊዜ ጥያቄው በቅድሚያ መፍትሔ የሚሰጠው የሚመለከታቸው ክልሎች በሚያደርጉት ስምምነት እንደሆነ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48/2/ ላይ ተደንግል፡፡ እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀጽ 23 24 25 እና 27 እስከ 31 ድረስ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

እነዚህ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክልሎች በጥያቄው አፈታት ላይ መስማማት ካልቻሉ አንዱ ወይም ሁለቱ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክልሎች ጉዳዩን ለፌዴሬሽን /ቤት ዘንድ በማቅረብ መፍትሔ ሊሹ ይችላሉ፡፡ እዚህ ላይ የክልሎች ወሰን ጥያቄ ሊያነሳ (ሊያቀርብ) የሚችለው ማን ነው? የሚለውን አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች አኳያ በጥሞና መመርመር የሚያስፈልግ ይመስላል፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48/1/ እንዲህ ይላል፡- ‹‹የክልሎችን ወሰን በሚመለከት ጥያቄ የተነሳ እንደሆነ ጉዳዩ በሚመለከታቻው ክልሎች ስምምነት ይፈጸማል፡፡ የሚመለከታቸው ክልሎች መስማማት ካልቻሉ የፌዴሬሽኑ /ቤት የሕዝብን አሰፋፈርና ፍላጎት በማድረግ ይወስናል››፡፡ እንዲሁም አንቀጽ 48/2/ ደግሞ በአንቀጽ 48(1) መሠረት ለፌዴሬሽን /ቤቱ የቀረበው ጉዳይ ከሁለት አመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በፌዴሬሽኑ /ቤቱ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጥበታል በማለት ደንግጓል፡፡.የእነዚህ ድንጋጌዎች ቋንቋ (language or wording) የሚያሳየው የክልሎች ወሰን ጥያቄ (ክርክር) የማቅረብ መብት ያላቸው ክልሎች መሆናቸውን መረዳት የሚቻል ይመስላል፡፡ እንዲሁም የእነዚህ ድንጋጌዎች አወቃቀር(structure of the provisions) እንደሚያስግነዝበው የክልሎች ወሰን ጥያቄ (ክርክር) የማቅረብ መብት ያላቸው ክልሎች መሆናቸውን መረዳት የሚቻል ይመስላል፡፡ ይህንን በሚያጠናክር መልኩ ጥቅምት 18 ቀን 1987 . በተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የሕገ መንግሥት ረቂቅ አጭር ማብራሪያ የወሰን ክርክር ጥያቄ የማቅረብ መብት ያላቸው ክልሎች መሆናቸውን ገልፃል፡፡

ከዚህም በላይ፤ አንቀጽ 48 የተዋቀረው በሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ አራት ውስጥ ሲሆን የዚህ ምዕራፍ አርዕስት የመንግሥት አወቃቀር ይላል፡፡ የሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ አራት ከአንቀጽ 45 እስከ 49 ድረስ የተደነገጉትን ድንጋጌዎች የሚያቅፍ ሲሆን እነዚህም ድንጋጌዎች ስለ ሥርዓተ መንግሥት (አንቀጽ 45) ስለ ፌዴራል ክልሎች (አንቀጽ 46) ስለ ፌዴራል መንግሥት (አንቀጽ 47) ስለ አከላለል ለውጦች  (አንቀጽ 48) እና ስለ ርእሰ ከተማ (አንቀጽ 49) የሚደነግጉት ናቸው፡፡ በዚህ አወቃቀር መሠረትም የድንበር ወዝግብ ጥያቄ ተነሳ የሚባለው የፌዴራሉ መንግሥት አካል የሆነ ክልል የክልል ወሰን ጥያቄ ባነሳ ጊዜ ነው፡፡ የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ካለ አግባብ ባለው መንገድ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን የመፍትሔ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ተከትሎ መጠየቅ ይገባል፡፡

ከዚህ ባሻገር፡ በአዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀጽ 27 ላይ እንደተመለከተው የክልሎች ወሰን ክርክር ሊኖር የሚችለው በክልሎች መካከል እንደሆነ ተመልክቷል፡፡እዚህ ላይ ልምዱንም መመልከት አስፈላጊ ይመስላል፡፡ እነዚህም ጉዳዩች አንድ በአንድ ብንመለከት የክርክሩ አካል የነበሩት ክልሎች መሆናቸውን መገንዘብ እንችላለን፡፡ በመሆኑም በትግራይ ወልቃይት ውስጥ የሚኖሩ አማራዎች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48/2/ የተቀመጠውን የክልሎች ድንበር (ወሰን) ለውጥ ጥያቄ የማቅረብ መብት የላቸውም፡፡የአዋጅ ቁጥር 251/1993 በክፍል አራት ውስጥ በክልሎች መካከል ወይም በክልልና በፌዴራል መንግሥት መካከል የሚፈጠር አለመግባባት ስለሚፈታበት ሁኔታ ተደንግል፡፡ በጠቅላላው ክፍል አራት ሥር የተደነገገው በክልሎች ወይም በፌዴራል መንግሥትና በክልል መካከል በሚፈጠሩ አለመግባባቶች አፈታት ረገድ መሆኑን ከአዋጁ አንቀጽ 23 24 25 እና 26 ድንጋጌዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡ አዋጁ ከአንቀጽ 27 እስከ 31 ድረስ ደግሞ የድንበር ውዝግብ ስለሚፈታበት አግባብ ደንግል፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች መገንዘብ እንደሚቻለው የክልሎች ድንበር ወሰን ጥያቄ የማቅረብ መብት ያላቸው ክልሎች ናቸው፡፡

ከዚህ ባሻገር፤ ክርክሬን የሚያጠናክር ሌላ መከራከሪያ ላቅርብ፡፡ የፌዴራል ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50/3/ እንደሚያስገነዝበው የክልል ከፍተኛ የሥልጣን አካል የክልሉ ምክር ቤት ነው፡፡ እንዲሁም ተጠሪነቱም ለወከለው ክልል ሕዝብ ነው፡፡ የክልል ሥልጣን የሚያዘው በክልሉ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊና ቀጥተኛ ምርጫ ነው፡፡ ዲሞክራሲ የሕዝብ መንግሥት ነው፡፡ በዲሞክራሲ ህዝቡ የሚተዳደርበትን ሕግ የራሱ ወኪሎች በግልፅና በሙሉ ነፃነት ተወያይተው የሚያወጡት ነው፡፡ በዚህ መሠረት የክልል መንግሥት ማለት የክልሉን ሕዝብ መሰረታዊ አቋሞች፣ አንድነትና ነፃነት ከጣልቃ ገብ የሚከላከል፣ የክልሉን ሕዝብ ደህንነት፣ አንድነትና መሻሻል የሚመራ፣ ህዝቡ ከውስጥ እርስ በራሱ ያለውን ግንኙነት፣ መብትና ግዴታ በሕጋዊነት መርህ እየወሰነ የሥልጣን ባለአደራ ሆኖ የሚያስተዳድር ተቋም ነው፡፡ በአጠቃላይ የክልሉ ሕዝብ በማናቸውም መንገድ ወኪል ነው፡፡ በመሆኑም በአማራ ክልል የሚኖር የአማራ የብሔር ማህበረሰብ የክልል ወሰን ጥያቄ ካለው ጥያቄው በመንግሥቱ አማካኝነት ሊቀርብ ይገባል፡፡

  በአጠቃላይ ጉዳዩ የክልሎች ወሰንን የተመለከተ በመሆኑ የወሰን ክርክር ሊቀርብ የሚችለው በክልሎች አማካኝነት ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም የወልቃይት ነዋሪ የሆኑ የተወሰኑ ሰዎች የአማራ ብሔር አባላት ነን በሚል የክልሎች ወሰን ለውጥ ጥያቄ ለማቅረብ መብቱ የላቸውም፡፡

3.2   የክልሎች ወሰን ለውጥ ጥያቄ (የድንበር ውዝግብ) የሚፈታበት መንገድ 

የክልሎች ወሰን ለውጥ ጥያቄ የሚፈታበት መንገድ አምስት ናቸው፡፡ እነዚህም፡- አንደኛው ዓይነት መንገድ በአዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀጽ 28/1/ ላይ ተደንግል፡፡ ይኸውም ምክር ቤት የሕዝብን አሰፋፈር በማጥናት አከባቢው ወደ የትኛው ክልል መካለል እንዳለበት ለመወሰን ሚያስችል በቂ መረጃ እንዳለው ካመነ በዚያው መሠረት ይወሰናል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 2/3/ እና 28/1/ መሠረት በዚህ ረገድ የመወሰን ሥልጣን ያለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ ክልሎች እንዲህ አይነት ጥያቄን ተቀብለው የማስተናገድ ሥልጣን የላቸውም፡፡ ምክንያቱም ማንም ሰው ወይም መንግሥት በራሱ ጉዳይ ላይ መወሰን አይገባውም ከሚል መርህ ነው፡፡

ሁለተኛው ዓይነት መንገድ ደግሞ ሕዝበ ውሳኔ ነው፡፡ የአዋጁ አንቀጽ 28/2/ እንደሚያስገነዝበው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያለሕዝበ ውሳኔ የህዝቡን አሰፋፈር በማጥናት አከራካሪው አከባቢ ወዴት መካለል እንዳለበት ለመወሰን የማይችል መሆኑን ካመነ የህዝቡን ፍላጎት መጠየቅ ይኖርበታል፡፡እዚህ ላይ የሕዝብ ትርጉም ምንድን ነው? (የሚመለከተው ሕዝብ ማን ነው?) የሚለውን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 48/2/ እንደሚያስግነዝበው ክልሎች በድንበር ውዝግቡ ረገድ መስማማት ካልቻሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የድንበር ውዝግቡን (የድንበር የአከላለል ለውጥ ጉዳዩን) የሕዝብን አሰፋፈርና ፍላጎት መሠረት በማድረግ ይወሰናል፡፡ ሕዝብ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን ነጥብ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48/2/ አኳያ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 48/2/ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39/5/ ጋር ተጣምሮ ሊመዘን ይገባል፡፡

ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ምን ማለት እንደሆነ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39/5/ ትር ሰጥቷል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀጽ 2/5/ ላይም ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ምን ማለት እንደሆነ ትር ተሰጥቷል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 46/2/ እንደሚደነግገው ክልሎች ከሚዋቀሩባቸው መስፈርቶች አንዱ፤ የሕዝብ ፈቃድ ነው፡፡ የሕዝብ ፈቃድ /ፍላጎት/ ምንድን ነው? የየትኛው ሕዝብ ፈቃድ ነው በመስፈርትነት የሚወሰደው? የሕዝብ ትርጉም ምንድነው? በአንቀጽ 46/2/ እና በአንቀጽ 39/5/ መካከል የሕዝብ ትርጉም ልዩነት አለ ወይ? በብሔር፣ በብሔረሰብ ወይም በሕዝብ መካከል የትርጉም  ልዩነት አለ ወይ? የሕዝብ ፈቃድና የሕዝብ ፍላጎት ይለያያሉ ወይ? ድንጋጌው ሕዝብ የሚለውን ቃል የተጠቀመበትን አግባብ ለመረዳት ምናልባት የዚህን ድንጋጌ የእግሊዘኛው ቅጂ አብሮ ማየት ሳያስፈልግ የማይቀር በመሆኑ እንመልከተው፡፡ የዚሁ ድንጋጌ የእንግሊዘኛው ቅጂ - - - the content of the people concerned; በማለት ይጠቅሳል፡፡ እንዲሁም አንቀጽ 48/2/ ደግሞ በተመሳሳይ #የሕዝብ ፍላጎት; በማለት ደንግል፡፡ የዚሁ እንግሊዘኛ ቅጂ እንዲሁ - - - the wishes of the peoples concerned; በማለት ገልፃል፡፡

በእነዚህ ድንጋጌዎች (በአንቀጽ 46/2/ እንዲሁም አንቀጽ 48/2) ላይ የሕዝብ ትርጉም በተለየ ሁኔታ አልተደነገገም፡፡ በመሆኑም ትርጉሙን ለማወቅ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 39/5/ ላይ የተጠቀሰውን የሕዝብ ትርጉም መመርመር ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ ይህንን እዚህ ላይ ለጊዜው ገታ አድርገን የሕዝብ ፍላጎት የሚለው ሃሳብ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39/3/ እና /5/ ሃሳብ ጋር የሚጣጣም መሆን አለመሆኑን ብንመለከት ይሻላል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39/5/ ሥር ከተቀመጡት የብሔር አቋም መስፈርቶች ውስጥ ሁለት ተጨባጭ ያልሆኑ ሁኔታዎች አሉ፡፡ እነዚህም ሰዎች የጋራ ወይም የተዛመደ ህልውና አለን ብለው የሚያምኑ መሆን/አለመሆናቸው እና ሰዎች የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸው መሆን/አለመሆኑ ናቸው፡፡ እነዚህም ባጭሩ የህልውና አንድነት እና የሥነ ልቦና አንድነት ልንላቸው እንችላለን፡፡ እነዚህንም ግለሰቦች በሚሰጡት ገለፃ የሚወሰኑ ናቸው፡፡ እነዚህ መስፈርቶች በአንቀጽ 46/2/ እና 48/2/ ጋር ከተጠቀሰው የሕዝብ ፈቃድ/ፍላጎት ጋር ያለው ግንኙነት ምንድ ነው?

እዚህ ላይ ወደ ሕዝብ ትርጉም ስንመለስ፤ ሕዝብ ማለት በአንቀጽ 39/5/ እና በአዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀጽ 2/5/ ላይ የተጠቀሱትን መስፈርቶች የሚያሟላ ማህበረሰብ ይመስላል፡፡ ይህ ከሆነ፤ የሕዝብ ፈቃድ/ፍላጎት የሚለው የየትኛውን ሕዝብ ፈቃድ/ፍላጎት ነው? ይህንንም በምሳሌ ለማስረዳት ያህል የወልቃይት ወረዳን በተመለከተ በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል የድንበር ውዝግብ ቢነሳ የድንበሩን ውዝግብ ለመፍታት ከመስፈርትነት የሚገባው የትግራይ ሕዝብ ወይስ የአማራ ሕዝብ ፈቃድ/ፍላጎት ነው? ፈቃዱ/ፍላጎቱ የሚለው የትግራይ ሕዝብ ከሆነ የውዝግቡ አፈታት ምናልባት ፍትሐዊ ላይሆን ይችላል፡፡ እንዲሁም የአማራ ሕዝብ ነው ቢባል እንዲሁ ኢፍትሐዊ ይመስላል፡፡

በሌላ በኩል ሕዝብ የሚለው የድንበር ውዝግብ በተነሳበት ቦታ ላይ ብቻ የሚኖሩ ናቸው እንዳይባል የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39/3/ እና /5/ ከሚደነግገው ጋር አይስማማም፡፡ ከዚህም ባሻገር የእንግሊዘኛው ቅጂ አንቀጽ 48/2/ የሚደነግገው … the wishes of the peoples concerned.; በሚል ነው፡፡ ይህም በአማርኛ ሲተረጎምበሚመለታቸው ህዝቦች ፍላጎቶች; የሚል ትርጉም ይኖረዋል፡፡ የሚመለከተው ሕዝብ የሚለው አገላለፅ በምን አግባብ የሚመለከተው ሕዝብ ለማለት ነው? በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39/2/ ላይ እንደተደነገገው ማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪኩን ማንነቱን የመንከባከብና የመጠበቅ መብት አለው፡፡ በሌላ አገላለፅ ማናቸውም ሕዝብ ማንነቱን የምያንቀባርቐቑ እስቶችን(መገለጫንየመጠበቅ መብት አለው፡፡ በአንቀጽ 39/5/ እንደተገለፀው የማንነት መገለጫ ከሆኑት ጉዳዩች አንዱ የህዝቡ መልክዓ ምድር ነው፡፡ በዚህ ብሔሩ የሰፈረበት መልክዓ ምድር አጠባበቅ ረገድ የድንበር ውዝግብ ከተነሳበት ቦታ ከሚኖሩት የተወሰኑ የህዝቡ ክፍል ፈቃድ/ፍላጎት ባለፈ ባወዛጋቢው ድንበር ላይ ክልል የመሰረተው አጠቃላይ ብሔር ፍላጎት/ፈቃድ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ካልሆነ አንድ ብሔር እንዴት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የብሔሩን መልክዓ ምድር ጠብቆ በማቆየት ወደ ቀጣዩ የብሔሩ ትውልድ ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡ በዚህ አግባብ ካልሆነ በቀር ብሔሩ ታሪክና መክዓ ምድሩን ጠብቆ ሊያቆይ የሚችልበት ሌላ መንገድ የለም፡፡ በመሆኑም ፈቃድ/ፍላጎት መጠየቅ የሚገባው የድንበር ውዝግብ የተነሳበት ቦታ የሰፈረውን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ከዚያ ባለፈ የሚኖረውን የህዝቡ ክፍልን ጨምሮ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ይሁንና ይህ ከመወሰኛው አንዱ መስፈርት እንጂ ብቸኛው መስፈርት አይደለም፡፡

ከዚህም በላይ እዚህ ላይ አንድ ሌላ ነጥብን መመርመሩ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ ይህንንም በምሳሌ ማስረዳት ይሻላል፡፡ ለምሳሌ በወልቃይት ወረዳ ላይ በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል የድንበር ውዝግብ መካከል ተነሳ እንበል፡፡ ወልቃይት የድንበር ውዝግብ በተነሳበት ሰዓት በትግራይ ክልል ወሰን ውስጥ ተካሎ የሚገኝ እንደሆነ ግልፅ ሲሆን በወልቃይት ወረዳ ሆነ በትግራይ ክልል ውስጥ ከትግራይ ተወላጆች ውጭ የሆኑ የተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔሮች ተወላጆች ተበታትነው እንደሚኖሩ 1984 እና 1999 የሕዝብና የቤቶች ቆጠራ ውጤት መግለጫ መረዳት ይቻላል፡፡ በአማራ ክልል ውስጥ ዕውቅና ካገኙ ብሄሮች ውስጥ የወልቃይት ወረዳ ይገባኛል የሚለው ብሔር አማራ ነው ብለን እናስብና በዚህ ዓይነት የድንበር ውዝግብ ላይ ከአማራና ከትግራይ ውጪ የሆኑ ሌሎች የኢትዮጵያ ብሄሮች በድንበር ውዝግብ አፈታት ላይ ፈቃዳቸውን/ፍላጎታቸውን ሊገልፁ ይችላሉ ወይ የሚለውን ጥያቄ መታየት ይኖርበታል፡፡

የድንበር ማስከበር መብት የተረጋገጠው እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ብሔር የሰፈረበትን መልክዓ ምድር ጠብቆ እንዲያቆይ ነው፡፡ ይህ ከሆነ፤ እንዴት የድንበር ውዝግብ በተነሳበት ቦታ ሰፍሬአለሁኝ/ይገባኛል በማለት ያልጠየቁ ብሄሮች ፍላጎታቸውን ሊገልፁ ዕድሉ ይሰጣቸዋል? እንደዚህ ፅሑፍ ፀሐፊ እምነት የድንበር ውዝግብ በተነሳበት ቦታ ላይ ሰፍሬአለሁኝ ከሚሉት ብሔሮች ውጪ ያሉ ብሔሮች በጭራሽ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ሊገቡ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ ብሔር የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን መብት ያለው በሰፈረበት መልክዓ ምድር በመሆኑ ነው፡፡ የክልሎች የድንበር ውዝግብ ምክንያት የሚሆነው በአወዛጋቢው ድንበር ክልል ውስጥ የሰፈረው ብሔር የኔ ነው፤ የኔ ነው በሚል በመሆኑ በዚህ ውዝግብ ውስጥ ሚና ሊኖራቸው የሚገባው በቦታው ላይ ሰፍረናል የሚሉት ብሔሮች ብቻ ናቸው፡፡

ሦስተኛው ዓይነት መንገድ ደግሞ በክልሎች መካከል በሚደረግ ስምምነት መሠረት የድንበር ውዝግቡን መፍታት ነው፡፡ በዚህ መሠረት የስምምነቱ አካላት የሚመለከታቸው ክልሎች ናቸው፡፡ እዚህ ላይ ከሦስቱ የክልል መንግሥት አካላት ማን ነው? ስምምነት ሊያደርግ የሚችለው የሚለው መታየት አለበት፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50/2/ መሠረት ክልሎች የሕግ አውጪ፣ የሕግ አስፈፃሚ እና የዳኝነት አካላት አላቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ማን ከሌላ ክልል ጋር ቁጭ ብሎ ይደራደራል የሚለው ነጥብ ለየክልሎች የተተወ ጉዳይ ይመስላል፡፡

አራተኛው ዓይነት መንገድ ደግሞ በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49/4/ ላይ ተመልክቷል፡፡ በጥቅምት 18 ቀን 1987 ዓ.ም በተወካዩች ምክር ቤት በፀደቀው የሕገ መንግሥት ረቂቅ አጭር ማብራሪያ ላይ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የምትገኝ መሆኗን ገልፃል፡፡ እንዲሁም የሕገ መንግሥቱ ቃለጉባኤ ላይ አዲስ አበባ የኦሮሞ መኖሪያ ተብሎ ተጠቅሷል፡፡ በዚህ አኳኃን ሕገ መንግሥቱ በራሱ አዲስ አበባ የኦሮሞ ሕዝብ ወሰን መሆኑን ወስኗል፡፡ ሆኖም የውሳኔው መስፈርት ምን እንደሆነ ምናልባት ግልፅ አይደለም፡፡ (Obviously it is not stipulated  based on settlement patterns, but rather it seems based on historical homeland). እንዲሁም የአዲስ አበባ የድንበር ወሰን የት ድረስ እንደሆነ በምን አግባብ እንደሚወሰንም ሆነ ማን እንደሚወስንም አልተደነገገም፡፡ የሕገ መንግሥቱ ማብራሪያ እንደሚያስገነዝበው የአዲስ አበባ ወሰን ሕገ መንግሥቱ በፀደቀበት የነበራት ወሰን ሲሆን ወሰኑም ወደ ፊት እየሰፋ የሚሄድ በመሆኑ የወሰን መስፋት ጉዳይ በሚኖር ጊዜ ኦሮሚያ በምታቀርበው (በምታጣው) መሬት አግባብ ልዩ ጥቅሟ ይከበራል፡፡ የሚጠበቀው ልዩ ጥቅም ምን እንደሆነና በምን አግባብ እንደሚጠበቅ በዝርዝር ሕግ የሚደነግግ መሆኑን ሕገ መንግሥቱ ደንግጓል፡፡

አምስተኛው ደግሞ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 46/2/ና 48(2) እንደደነገጉት አንድ ክልል ብዙ ብሔሮች አካቶ በያዘ ጊዜ ክልሉ የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፤ ማንነት እና ፈቃድ ላይ በመመስረት እንደሆነ ተደንግጓል፡፡

3.3    የድንበር ውዝግብ መወስኛ መስፈርት

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39/3/ እንደሚያስገነዝበው ማንኛውም ዕውቅና ያገኘ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ በሰፈረበት መልክዓ ምድር ውስጥ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ መብት አለው፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት የብሔሩ መልክዓ ምድር የሚባለው ብሔሩ የሰፈረበት መልክዓ ምድር ነው፡፡ ስለዚህ መስፈር (ሰፈራ)/territorial disputes or claims settlement interms of settlement patterns of the people/ መሰረታዊ የድንበር ወሰን መወሰኛ መስፈርት ነው፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39/5/ አንድ ማህበረሰብ የብሔር ማህበረሰብ አቋም ለማግኘት ሊያሟላቸው ከሚገባቸው መስፈርቶች አንዱ ማህበረሰቡ በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ; መሆናቸው ነው፡፡ ድንበር ይገባኛል ለማለት መሰረታዊ መስፈርቱ በመልክዓ ምድሩ ውስጥ መኖር (inhabitation) ነው፡፡

የሕገ መንግሥቱ መግቢያ ደግሞ እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ወይም ህዝቦች…….የየራሳችን መልክዓ ምድር አሰፋፈር የነበረንና ያለን …... በማለት ይገልፃል፡፡ This expression seems referring with hesitative tone to the concept of historical homeland. በዚህም መልክዓ ምድራዊ አሰፋፈር የድንበር አከላለል ለመወሰንም ሆነ የድንበር ውዝግብ ለመፍታት ወሳኙ መስፈርት ነው፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 46/2/ ደግሞ ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ ማንነት እና ፈቃድ ላይ በመመስረት እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ በአንቀጽ 47/1/ መሠረት የተወሰኑ ብሄሮች የየራሳቸውን ክልል የተቋቋመላቸው ሲሆን አንቀጽ 47/2/ ደግሞ የየራሳቸውን ክልል ያልተቋቋመላቸው ብሄሮች የየራሳቸውን ክልል በማናቸውም ጊዜ የማቋቋም መብት እንዳላቸው ደንግጓል፡፡ በዚህ አኳኃን ክልሎች በሚቋቋሙበት ጊዜ መዋቀር የሚገባቸው ብሔር ያቋቋመው/የተቋቋመለት ብሔር በሰፈረበት መልክዓ ምድር ነው፡፡ በመሆኑም አንቀጽ 46/2/ ከሕገ መንግሥቱ መግቢያ፣ አንቀጽ 39/3/ እና 39/5/ ተቆራኝቶ ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ብሔር የራሱን ክልል በሚያቋቁምበት/በተቋቋመለት ጊዜ የሚኖረው የክልል አከላለል መስፈርት እና ብዙ ብሔሮች ተጠቃለው በአንድ ክልል ውስጥ በታቀፉበትና በሚታቀፉበት ጊዜ የሚኖረው የክልል አከላለል መስፈርት ይለያያል፡፡ አንድ ብሔር የራሱን ክልል በሚያቋቁምበት/በተቋቋመለት ጊዜ ክልሎ የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር ላይ በመመስረት እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ ብዙ ብሔሮች ተጠቃለው በአንድ ክልል ውስጥ  በሚታቀፉበት ጊዜ ክልሎ የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ ፤ማንነት እና ፈቃድ ላይ በመመስረት እንደሆነ ተደንግጓል፡፡

በሌላ በኩል የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48/2/ ደግሞ የክልሎች ወሰን ለውጥ በሚመለከት ጥያቄ የተነሳ እንደሆነ እና ጉዳዩ በሚመለከታቸው ክልሎች መስማማት ካልተቻለ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝብ አሰፋፈርና ፍላጎት መሠረት በማድረግ ይወስናል ብሎ ጠቅሷል፡፡ ይህ ድንጋጌ በአንቀጽ 46/2/ ድንጋጌ ውስጥ የተጠቀሱትን የቋንቋና የማንነት መስፈርቶች ከድንበር ውዝግብ አፈታት መስፈርትነት አስወግዷቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በአንቀጽ 46/2/ እና 48/2/ መካከል ግልፅ መጣረስ እንዳለ መገንዘብ የሚቻል ይመስላል፡፡ አንቀጽ 46/2/ የክልሎች ድንበር(ወሰን) የቅድሚያ (የመጀመሪያ) አከላለል መስፈርቶችን የደነገገ ሲሆን አንቀጽ 48/2/ ደግሞ የክልሎች ድንበር ለውጥ አወሳሰን(አደራረግ) መስፈርቶች አደራጅቷል፡፡ በመሆኑም በእነዚህ ጉዳዩች ላይ የተለያዩ መስፈርቶች ያሉ በመሆኑ በኢትዮጵያ የፌዴራል አተገባበር ሂደት ውስጥ የማያቋርጥ ክልሎች የድንበር ውዝግብ እንዲነሳ የሚጋብዝበት ሁኔታ የሚፈጥር ይመስላል፡፡ ስለሆነም አንቀጽ 48/2/ ከአንቀጽ 46/2/፣ 39/3/፣ 39/5/፣ ከሕገ መንግሥቱ መግቢያና ከአጠቃላይ የሕገ መንግሥቱ ይዘት፣ መንፈስና ዓላማዎች አኳያ አገናዝቦ ገቢራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም የድንበር ውዝግብ በብሔር መልክዓ ምድር አሰፋፈር መሠረት ሊወሰን ይገባዋል፡፡ ይኸውም አሰራር ከሕገ መንግሥቱ መግቢያ፣ ከአንቀጽ 39/3/፣ 39/5/፣ 46/2/ እና ከሕገ መንግሥቱ መርሆዎች ጋር በሚገባ የተናበበና የተጣጣመ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

በአዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀጽ 28/1/ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝብን አሰፋፈር በማጥናት አከባቢው ወደ የትኛው ክልል መካለል እንዳለበት ለመወሰን ሚያስችል በቂ መረጃ እንዳለው ካመነ በዚያው መሠረት ይወሰናል፡፡የአዋጁ አንቀጽ 28/2/ እንደሚያስገነዝበው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህዝቡን አሰፋፈር በማጥናት አከራካሪው አከባቢ ወዴት መካለል እንዳለበት ለመወሰን የማይችል መሆኑን ካመነ የህዝቡን ፍላጎት መጠየቅ ይኖርበታል፡፡ የህዝቡን ፍላጎት ለመጠየቅ ሕዝበ ውሳኔ ማድርግ ያስፈልጋል፡፡እነዘህ ድንጋገውች የሕዝብን አሰፋፈር እና የህዝቡን አሰፋፈርን/የክልሎች ድንበር ለውጥ አወሳሰን (አደራረግ) መስፈርቶች/አማራቶች (alternatives) አድርገዋቸዋል፡፡በዚህም የተነሳ በአዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀጽ 28/1/ና 28/2/ እና የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48/2/ መካከል ግልፅ መጣረስ እንዳለ መገንዘብ የሚቻል ይመስላል፡፡ የሚጋጨው ግን ብዙ ብሔሮች ተጠቃለው በአንድ ክልል ውስጥ  በሚታቀፉበት ጊዜ ክልሎ የሚዋቀሩት ነው፡፡

በአጠቃላይ የድንበር ውዝግብ የሚወሰነው በሕዝብ አሰፋፈር መስፈርት ነው፡፡ ይህም ማለት በአወዛጋቢው ድንበር ላይ የሚኖረው የትኛው/የቱ ብሔር ነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ ነው ጉዳዩን የሚወሥነው፡፡ በመሆኑም በአወዛጋቢው ድንበር ላይ የሚኖረው ብሔር የቱ እንደሆነ በምን መንገድ መወሰን ይገባል? መወሰኛ መንገዶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህም፡-1ኛ/ በገለልተኛ አካል አስተያየት በድንበሩ የሰፈረውን ብሔር መወሰን ወይም/እና 2ኛ/ የሚመለከተው ሕዝብ የየትኛው ብሔር አባል እንደሆነ ሕዝበ ውሳኔ እንዲገልፅ በማድረግ ናቸው፡፡         

4.    ታሪክ ቀመስ ዳሰሳ ባጭሩ

በዚህ ርዕስ ሥር የትግራይና ወልቃይት አከባቢዎች ታሪካዊ ግንኙነቶችን በተመለከተ ለመቃኘት ታሪክ ቀመስ መጣጥፍ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ በሌላ አገላለፅ ወልቃይት፣ ፀገዴ፣ ወገራ እና ሰቲት ሑመራ ከትግራይ ጋር በታሪክ ያላቸውን ግንኙነት ምን ይመስላል የሚለውን ከታሪካዊ ሰነዶች ባጭሩ በዚህ ርዕስ ሥር ተዳሷል፡፡

Harold G.Marcus “A History of Ethiopia” በሚለው መፅሐፍ ላይ እንዳረጋገጠው አክሱማውያን ከተከዜ በስተደቡብ የሚገኘውን የአገው ምድርን በማስገበርና የሰሜን ተራሮችን በመቆጣጠር ወታደራዊ መስፋፋት አድርገው ነበር፡፡ የአክሱም መንግስታዊ ሀይል የደቡብ ትግራይ አካባቢን በማጠቃለል ዋግና ላስታን በመያዝ እስከ ሰሜን ወሎና አገው ምድር ድረስ በጌምድርን ጨምሮ እሰከ 10ኛ ክ/ዘመን መጨረሻ ለመስፋፋት ችሏል፡፡

Serqew Habte selassie በፅሑፉ እንደጠቀሰው የአክሱም ግዛቶች መሃል ሂያምር፣ ራይዳን፣ ሳብና ሐለን በደቡብ ዓረቢያ የሚገኙ ሲሆን ፁያም ጋምቤላ እንደሆነ ቤጋ የሚለው ደግሞ ቤጃ እንደሆነና ጠቅላላ ግዛቱ ምዕራባዊ ኤርትራ አካቶ እስከ ምስራቅ ሱዳን ይደርስ ነበር፡፡ በዚህ ዘመን የአክሱም ግዛት ደጀግ ሰፈ እንደሆነ በአራተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነግሶ የነበረው ንጉስ ኢዛና የተወው የድንጋይ ላይ ፅሑፍ በግልፅ ያመለክታል፡፡ ንጉስ ኢዛና የኑቢያን እና የቸንተን ግዛቶች ጭምር በቁጥጥር ሥር በማድረግ ያስተዳድር እንደነበር የተለያዩ የታሪክ መዛግብቶች በሚገባ መስክረዋል፡፡ ኑብያ ከአባትራ ወንዝ በስተምስራቅ ያለውን የሱዳን ሰሜን ምስራቅ ክፍል አካቶ የሚይዝ ሲሆን የቸንት ግዛት ደግሞ እስከ ከቀይባህር በስተደቡብ ያለውን ግዛት አተቃልሎ እንደሚይዝ የተለያዩ የታሪክ መዛግብት ዘግበዋል፡፡

ማኑኤል ባራዳ የተባለው ፖርቹጋላዊ ሚሲዩን በ17ኛው ክፍለ ዘመን የትግራይ ታሪካዊና ጂኦግራፊያዊ ዘገባ በሚል ርዕስ በ1634 እ.ኤ.አ በፃፈው ፅሑፍ ላይ የትግራይ አገር አዋሳኞች በስተደቡብ በኩል አልውሃ (አላማጣና ወልዲያ) ፣ በስተሰሜን ፤ሐማሴን; ፣ በስተምስራቅ ደግሞ ጋማከል; በስተምዕራብም ሊማሊሞ; እንደሆነ በጣም ግልፅ በሆነ ሁኔታ በካርታ ንድፍ አስቀምጧል፡፡ ይህ ሚሲዩናዊ ይህንን ፅሑፍ በፃፈበት ጊዜ የኢትዮጵያ ንጉስ ፋሲለደስ ነበር፡፡ ፅሑፉን ከመፃፉ በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ ረመና በሚባል ቦታ በሚሲዮናዊነት ሲኖር ከቆየ በኃላ ሚሲዮናዊያን በሱሲንዩስ እና በፋሲለደስ እንዲባረሩ ሲደረግ እሱም ወደ ኤደን (የመን) ሄደና ይህን ፅሑፍ በየመን ሆኖ ፃፈ፡፡

ከዚህ ባሻገር በ17ኛው ክፍለ ዘመን ደጃዝማች ገላውዲዩስ የተባለው የሽሬ ገዥ ወልቃይትን ጠቅልሎ ያስተዳድር የነበረ ስለመሆኑ በተለያዩ የታሪክ መዛግብት ላይ ተመስክሯል፡፡ ደጃዝማች ገላውዲዩስ ወልቃይትን ብቻ ሳይሆን ቆላውን አከባቢ እና በታቾቹ ድረስ ያስተዳድር እንደነበር የታሪክ ሰነዶች ይመሰክራሉ፡፡

በ1930ዎቹ መጀመሪያ ደግሞ ራስ ንጉስ ወሌ ወልቃይትን ያስገብር ነበር፡፡ራስ ንጉስ ወሌ ወልቃይትን ሲያስገብሩ በነበረበት ጊዜ ራስ ጉግሳና ራስ ተፈራ (በኃላም ንጉስ ሃይለስላሴ) ግጭት ውስጥ ይገባሉ በዚህም ግጭት ራስ ጉግሳ ወሌ ተሸነፈ፡፡ ከዚህ በኃላ ጣሊያን ተሻግሮ ኢትዮጵያን ለቆ ከሄደ በኃላ አፄ ኃይለስላሴ ወልቃይትና አከባቢውን፣ በጌምድር እና ሰሜንን ጠቅላይ ግዛት ውስጥ ቀላቅለው የሸዋ አማሮችን እያፈራረቁ በግዛቱ ላይ ለ33 ዓመታት ሾመውበታል፡፡

በ1930ዎቹ ላይ ፍሬዴሪክ ሲሞን አከባቢውን ጎብኝቶና አጥንቶ “NorthWest Ethiopia: people and economy “በሚለው መፅሐፍ ላይ   እንደመሰከረው የወልቃይት ወረዳ ትግራዊያን የሰፈሩበት መልክዓ ምድር እንደሆነ ገልፃል፡፡ በተመሳሳይ ዶናርድ ሌቪን ”THE GRATER ETHIOPIA” በሚለው መፅሐፍ ላይ እንዳረጋገጠው ደብረታቦር የክፍለሃገር መገበያያ ቦታ መሆኑን ጠቅሶ በዚህ የገበያ ቦታ ላይ ገበያተኞች ከቅማንት ወረዳ ከሆነው ከጭልጋ (people brought ginger from chiliga, a kimant district) በእግር ስድስት ቀን ተጉዘው ጅንጅብል እንደሚያቀርቡ፣ ገበያተኞች ከአማራው ወረዳ ከጋይንት (wool saddle blankets from gaint, an amhara district) በእግር ሶስት ቀን ተጉዘው የሱፍ ብርድ ልብስ እንደሚያቀርቡ፣ ገበያተኞች ከትግራዊያን ወረዳ ወልቃይት (cotton from the Tigrean district of wolqait) 11 ቀን በእግር ተጉዘው ጥጥ ደብረታቦር እንደሚያቀርቡ መስክሯል፡፡ ፍሬዴሪክ ሲሞንና ዶናርድ ሌቪን እንደመሰከሩት ወልቃይት የትግራዊያን ወረዳ ነው (ትግራዊያን የሰፈሩበት መልክዓምድር) መሆኑን መስክረዋል፡፡

ፕሮፌሰር ኤልቤርቶ ሰባኪ እ.ኤ.አ.1985 “Ethiopia under Mussoloni: Fascism and the colonial experience” በሚል በፃፈው መፅሐፍ ላይ እንዲህ ብሏል ’… ሌሶና የአማራ ጠቅላይ ግዛት አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ግዛቶች ብቻ እንዲይዝ ቢከራከርም ፀለምት በአብዛኛው ትግርኛ ተናጋሪ አከባቢ ቢሆንም የጠቅላይ ግዛቱን ወሰን የተከዜን ወንዝ በመከተል ለመከለል ሲባል ወደ አማራ ተከልሏል፡፡ ሌሎች እንደ ወልቃይት፣ ዋልድባ፣ ፀገዴ፣ ሰሜን፣ ወገራ እና በለሳን የመሳሰሉ ግዛቶች ከአማራ ይልቅ በትግርኛ ተናጋሪዎች የተያዙ (ትግርኛ ተናጋሪዎች የሰፈሩበት) እና ከኢጣሊያ ወረራ በፊት ከሰቲት ወንዝ በስተደቡብ የሚገኙት እነዚህ አከባቢዎች (ግዛቶች) የኢኮኖሚ ግንኙነታቸው ከጎንደር ይልቅ ከአስመራ ጋር እንደሆነ በሚገባ አጥንቶ መስክሯል፡፡ ኢጣልያ ኢትዮጵያን በምታስተዳድርበት ጊዜ በስድስት ጠቅላይ ግዛቶች ከከፋፍላ የነበረ ሲሆን ክፍፍሉም በድንበሩ ላይ የሰፈረውን ብሔር ማንነት መስፈርት በማድረግ ነበር፡፡ ፕሮፌሰር ኤልቤርቶ ሰባኪ በተጨማሪ እንዳረጋገጠው የእቴጌ ጣይቱ ወገን የሆኑት ደጃዝማች አያሌው ብሩ ለንግስቱ ለነበራቸው ታማኝነትና ለሰጡት ድጋፍ ማካካሻ እንዲሆናቸው ወልቃይት፣ ጸገዴ፣ ወገራና የሰሜን የተወሰኑ ክፍለ ግዛት ተሰጥቷቸዋል፡፡

ራስ ሚካኤል ሱሑል በአፄ ኢያሱ ጊዜ ሰሜን ግዛትን ጨምሮ መላ ትግራይ ትግርኚ (ኤርትራን ጨምሮ) እስከ ቀይ ባህር ምፅዋ ድረስ ለአርባ ዓመት  ሲገዙ ነበር፡፡ በኃላም በአፄ ኢዩአስ ሥር ከነሙሉ ወታደራቸው መቀመጫቸውን ጎንደር አድርገው ኢትዮጵያን በእደራሴነት ከአሥር ዓመት በላይ ገዝተዋል፡፡

ደጃዝማች ወ/ስላሴ ከ1809 ትግራይን የመሩ ሲሆን እኝህ ንጉስ ወገአጥባቂ ክርስቲያን የነበሩ በመሆኑ መልካም አስተያየት አልነበራቸውም፡፡ Harold G.Marcus አጥንቶ እንዳረጋገጠው ወ/ስላሴ አዘቦ እና ራያ ግዛት ብቻቸውን በመንጠቅ እና ወደ ትግራይ መተላለፊያ የነበረውን ላስታን በመውረር አቋሙን ማሳየቱ ገልጧል፡፡ በመቀጠልም ወደ ጠረፍ ዘምቶ የሙስሊሙን ንግድ ተቆጣጥሮ ማስገበር ቻለ፡፡ በ1809 አካባቢ ወ/ስላሴ አጎራባች ከሆነው የሰሜን ግዛት መሳፍንቶች ደጃዝማች ገብሩና ራስ ሀለማርያም ጋር ግንኙነቱን በማጠናከር ሲገዛ ነበር፡፡ በዘመነ መሳፍንት የትግራይ ገዢዎች እንደሌሎቹ ትልልቅ ክፍለ ሃገሮች ሁሉ ራስ ገዝ የሆኑ ግዛቶች ነበሩዋቸው፡፡ ከእነዚህ የትግራይ ግዛቶች ውስጥ ብዙዎቹ ልዩ ልዩ ተወዳዳሪ አውራጃዎች ተደማምረው ነፃ ራስ ገዝ ጠቅላይ ግዛት የሆኑት ደጃዝማች ስባጋድስ ሥልጣን ከያዙ በኃላ ነው፡፡ ደጃዝማች ስባጋድስ ትግራይንና ኤርትራን ከነቀይባህሩ ( እስከ ምጽዋ አካባቢ አለውሃ ምላሽ) ጋር በአንድ ላይ በመስፍንነት ከ1808-1823 ድረስ ገዝተዋል፡፡ የእዚህ ግዛታቸው ድንበር ወሰን የሰሜኑ ባላባት ከሚያስተዳድረው ሰሜን ግዛት በስተስሜን በኩል የሚገኙትን የወልቃይትና አካባቢዎችን አጠቃሎ የያዘ ነው፡፡ የየጁን መዳገም የተመለከተው ሱባጋድስ የደጃዝማች ወ/ስላሴን አላማ በመከተል ሰሜኑን፣በጌምድርን እና አካባቢውን ከትግራይ ጋር በመቀላቀል ጎንደር ላይ መንገስቱን ለመመስረት ተንቀሳቅሷል፡፡ የላስታው ገዥ ማርዬ በጌምድርን፣የጁንና ወሎን በማሰገበር ስባጋድስ ለመደምሰስ ተነሳ፡፡ በ1831 ዓ.ም ራስ ማርዬ ምርኮኞቹን አስከትሎ ከጎንደር በስተሰሜን ወደምትገኘው ደብረ ዐባይ ስባጋድስ ወደሚገኙበት ቦታ ዘምተው አሸንፈው በሞት ቀቱዋቸው፡፡ የትግራዩ መስፍን ደጃዝማች ስባጋድስ በዚህ ጦርነት ከሞቱ በኃላ በእርሳቸው ቦታ ደጃዝማች ውቤ ሀይለማርያም ደጃዝማች ስባጋድስን ተክተው ትግራይ ትግሪኝ ሰሜንን ጨምረው ከ1823-1845 ድረስ ለሀያ ሶስት አመታት ገዝተዋል፡፡ Harold G.Marcus እንዲሁ እንዳረጋገጠው ራስ ውቤ ሀይለማርያም ትግራይን ወገራን ጨምሮ በአንድነት በማስተዳደር የኦሮሞን ሀይል ለማስቆም ችለዋል፡፡ ደጃዝማች ውቤ ሀይለማርያም ደጃዝማች ስባጋድስ ከመሞታቻው በፊት ሰሜንን ሲገዙ የቆዩና ከደጃዝማች ስባጋድስ ጋር በጋብቻ የተሳሰሩ ነበሩ፡፡  አገው ንጉሴ በመባል ይጠራ የነበረው ወልደሚካኤል በአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ትግራይንና ቤጌምድርን ጠቅልሎ ይገዛ እንደነበር እኝህ ጸሐፊ መስክረዋል፡፡ ወ/ሚካኤል የደጃዝማች ውቤ ሀ/ማርያም የእህት ልጅ ሲሆን የቴዎድሮስን አገዛዝን ባለመቀበል ታግሏል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ልንል የሚገባው ነገር እስከ እ.ኤ.አ 1943 ድረስ በጌምድር በሚል ስያሜ የሚጠራው ግዛት የሰሜን፣ የደንቢያ፣የወገራን እና የወልቃትን አጠቃሎ አያውቅም፡፡ የሰሜንና ወልቃት አካባቢዎች ከከበጌምድር ግዛት ጋር ለመጀመሪያ በታሪክ የተዋሀዱት በእ.ኤ.አ 1943 ነው፡፡ 

ወ/ሚካኤል ትግራይን በጌምድርን ጠቅልሎ ይገዛ ነበር ሲባል የትግራይን እና የበጌምድርን አዋሳኝ ድምበር ከ1943 በፊት በጌምድር ተብሎ የሚጠራው ግዛት የስሜን ግዛት ሰሜናዊ ጫፍ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የበጌምድር ግዛት የዳሞትን የሰሜንንና የወገራን ግዛቶች አካቶ የማይዝ መሆኑን ያሳያል፡፡ በ1868 ዓ.ም አፄ ቴዎድሮስ ሲሞቱ የትግራዊያን የንግስ ሐረግ ፍላጎት ለማስመለስ ቀድሞ ለመውጣት የቻለው፡፡ ለሺ ዓመታት ከተቋረጠ በኃላ ዙፋኑን ወደ ትግራይ በ1871 ዓ.ም የመለሱት ዬሐንስ 4ኛ እንከን በሌለው ሁኔታ የተመሰከረላቸው ነበሩ፡፡

አጼ ፋሲል ለመናገሻነት የቆረቆሩበት ቦታ ቀድሞም ጎንደር ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ ጎንደር የሚለው ስያሜ አመጣጥ እንዴት እንደሆነ የጎንደር ከተማ መዘጋጃ ቤት ጋዜጣ  በ1966 አ.ም  ‹‹ትዕይንተ ጎንደር ዜና ›› ጋዜጣ ላይ ወይንአ ሰይንአ የተባሉት ወንድማማቾች ከብዙ አመታት በፊት ከእንድርታ አውርጃ ኩሐ ተነስተው በሰሜን በኩል አቋርጠው በአንገረብና በቀሃ ወንዝ የሚገኘውን ቦታ ይዘው ከሰፈሩበት በኃላና አገሩን እያቀኑ ከተባዙ በኃላ ወንድማማቾቹ በድንበር ገፈኸን በመባባል በተጣሉበት ጊዜ ሽማግሌ ከሁለቱ ወንድማማቾች በእድሜ አነስተኛውን የሆነውን አይቶ አንተስ ብሆን ምንአለ ‹‹ በሱ ጎን እደር፣ አሁንም ቢሆን አሱ ጎን እደር›› ብሎ በመወሰኑ የተነሳ ቦታው ጎንደር ተብሎ ይጠራ እንደነበር ገልጧል፡፡ የሁለቱ ወንድማማቾች ከትግራይ መጥቶ ባዶ ቦታ ላይ እንደሰፈሩና ጎንደር የሚለው ስያሜ  በነዚሁ ወንድማማቾች ምክንያት እንደወጣ በ‹‹ትዕይንተ ጎንደር ዜና ›› ጋዜጣ ላይ ተመስክሯል፡፡ የአጼ ፋሲል አባት የሆነው አጼ ሱስኒዮስ ዋና ከተማቸው ደንቀዝ የነበረ ሲሆን ልጃቸውም እስከ 1627 ድረስ መቀመጫቸውን ደንቀዝ አድርገው ነበር፡፡ አጼ ዩሐንስ 4ኛ የኢትየጲያ ንጉሰ ነገስት ሆነው ኢትዮጵያን በሚያስተዳድሩበት ጊዜ ልጃቸውን ራስ አራአያ ስላሴን የጎንደር ገዥ አድርገው ሾመዋቸው ነበር፡፡ ራስ አራአያ ስላሴ በኃላም የወሎ ገዥ ሆነው አስተዳድረዋል፡፡አጼ ዩሐንስ 4ኛ ኢትዮጵያን በሚያስተዳድሩበት ጊዜ ታላቁ ቤተ መንግሥትናን በመቀሌ ከተማ ቢያሰሩ አብዛኛውን ጊዜ መቀመጫቸው ሐሸንጌ፣ደሴ እና ደብረ ታቦር ነበሩ፡፡ ራስ ስዩም ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በቀን ግዛት በምታስተዳድርበት ጊዜ የኢትዮጵያ ሰሜናዊ መስፍን ተብለው ላስታን፣ወግን፣የጁን፣ወልቃይትንና ጸገዴን በግዛታቸው ሥር አጠቃለው እንደነበር የታሪክ ሰነዶች ይጠቁማሉ፡፡

በ1984 አ.ም በተደረገው ሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በወልቃት፣በጸለምት፣በቃፍታ ሁመራ እና በጸገዴ ወረዳዎች ውስጥ የብሔሮች ስብጥር ምን እንደሚመስልለምት ገልጻል፡፡ በዚህም በጸለምት ወረዳ 87,012 የሚሆኑ ትግራዊያን እንደሰፈሩበት እንዲሁም 10,382 አማሮች እንደሰፈሩበት አረጋግጧል፡፡ በወልቃይት ወረዳ ውስጥ ደግሞ 87,099 ትግራዊያን እንደሰፈሩበት እንዲሁም 2፣734 አማሮች እንደሰፈሩበት አመልክቷል፡፡ በቃፍታ ሁመራ ወረዳ ደግሞ 41,999 ትግራዊያን እና 3,800 አማሮች እንደሚኖሩበት በቆጠራው ውጤት ላይ መስክሯል፡፡ በ1999 አ.ም በተደረገው ሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ላይም ውጤቱ ያው ነው፡፡

ከዚህም በላይ፤ በነዚህ አካባቢ የሚገኙ ቦታዎች በአብዛናው ስያሜያቸው የትግረኛ ቋንቋ ነው፡፡ እንዲሁም በእነዚህ አካባቢ የሚገኙ  ሰዎች የሚግባቡበት መደበኛ ቋንቋ ትግረኛ ነው፡፡ ቃፍታ ሁመራ፤ ጸለምት፤ ማይካድራ፤ ቃብትያ ሶላ፤ አደህድረ፤ ወዘተ ስያሜያቸው የትግረኛ ቋንቋ ነው፡፡  

የደርግ መንግሥት class struggle and the problem in Eritrea በሚል 1971 አ.ም ባሳተመው መጽሐፍ ላይ የሚከተለውን በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙትን ብሔረሰቦች ሥርጭት የሚያሳየውን ካርታ አካትቷል፡፡ በዚህ ካርታ ላይም እንደምናየው ከተከዘ በስተደቡብ የሚገኙት የወልቃይት፣ የጸገዴ፣ ጸለምት፣ ሁመራ እና ሌሎች አካባቢዎች የትግራይ ብሔረሰብ የሰፈረባቸው መልክአ ምድሮች መሆናቸውን መስክሯል፡፡

አማሮችና ትግራዊያን በግዛት ፍላጎት ሲፎካከሩ የቆዩ መሆኑን የታሪክ ሰነዶች ዘግበዋል፡፡ የእነኚህ የክፍለ ሃገር ድንበሮች በዚህ የተነሳ ከትውልድ ትውልድ በጣም መለዋወጣቸው ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ጊዜ የአውራጃ ወይም የወረዳ ልዩነት፤ ለምሳሌ በሸዋ በመንዝና በይፋት መካከል፤ በትግራይ በሽሬ እና በአድዋ መካከል ያለው ልዩነት በክፍለ ሃገር መካከል ከሚገኙት ልዩነቶች ይልቅ በጣም ጎልተው ይታያሉ፡፡ እዚህ ላይ ለመጥቀስ ያህል አማሮች በአገራቸው የመላው አማራ ማህበረሰብ ነን ብለው አባልነታቸውን ከቶ አጥብቀው አያውቁም፡፡ ማንነታቸውን ለመግለፅ በክፍለ ሃገር ደረጃ ጎጃሞች፣ ሸዋዎች በሚል ነው፡፡ በተቃራኒው በትግራይ ሕዝብ መካከል የተለየ ቅርብ ግንኙነት ነበርም፤ አለም፡፡ ምንም እንኳን የትግራይ ሕዝብ ለምዕተ ዓመታት በአማሮች ነገስታት እንደራሴዎች ሥር ሲገዛ ቢኖርም ከአማሮችም ጋር የመፎካከር ባህል ቢኖርም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ማህበረሰብ ዓላማ ጋር አንድ ዓይነት ያላቋረጠ ታማኝነት ጠብቆ ኖሮአል፡፡የትግራይ ሕዝብ ለምዕተ ዓመታት በአማሮች ነገስታት እንደራሴዎች ሥር ሲገዛ ቢኖርም በዘመኑ ከነበራቸው ችግርና በአከባቢያቸው ጉዳይ ተወጥረው የቀድሞ አባቶቻቸው በአዋሰኗቸው ክፍለሃገራት እየኖሩ አብዛኞቹ ከነበሩበት ሳይነቃነቁ ቆይተዋል፡፡

የትግራይ ሕዝብ  የሰፈረበት መልክአምድሮችና የትግራይ ጠቅላይ ግዛት(ክፍለ ሃገር) ግዛት ወስን የተለያዩ ናቸው፡፡ በሃይለስላስ ዘመን የትግራይ ጠቅላይ ግዛት( በሃላም በደርግ ዘመን ክፍለ ሃገር ግዛት) ወስን የተካለለው በድንበሩ ላይ የሰፈረውን ብሔር ማንነት(ቋንቋ) መስፈርት በማድረግ አይደለም፡፡የትግራይ ጠቅላይ ግዛት(ክፍለ ሃገር) ግዛት ወስንተከዘ ነው ማለት የትግራይ ሕዝብ  የሰፈረው ከተከዘ በስተስሜን  በሚገኙት አካባቢዎች ብቻ ነው ማለት አይደለም፡፡ምክንያቱም የግዛት(ክፍለ ሃገር) ግዛት ወስን ና የትግራይ ሕዝብ መልክአምድር ይለያያሉ፡፡ በአሁኑ ሕገ መንግሥት ደግሞ የድንበር አከላለል በአጠቃላይ የሚወሰነው በሕዝብ አሰፋፈር መስፈርት ነው፡፡ ይህም ማለት በአወዛጋቢው ድንበር ላይ የሚኖረው የትኛው/የቱ ብሔር(ሕዝብ) ነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ ነው ጉዳዩን የሚወሥነው፡፡ በመሆኑም የትግራይ ከልል ወስን ተከዘ ነው የሚለው ክርከር መሠረት የለውም፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Immediate appeal in Ethiopian Arbitration Law?
ግብር ስወራ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 18 September 2024