Font size: +
12 minutes reading time (2407 words)

የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ከአዲስ አበባ ምን ሊሆን ይችላል

በሀገራችን በቅርብ ጊዜየቶች ውስጥ በተደጋጋሚ እየተነሱ ከሚገኙ ጉዳዮች እና የሕግ እና የፓለቲካ ተዋንያንን እያነጋገር ያለው አንዱ ጉዳይ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከአዲስ አበባ ከተማ ሊኖረው ይገባል በሚል በኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 49 (5) የተቀመጠውን ልዩ ጥቅም የተመለከተው ድንጋጌ ነው፡፡በሕገ-መንግሥቱ ላይ የተቀመጠውን ድንጋጌ አንዳንድ ሰዎች እንደሚያነሱት በሀገሪቷ ውስጥ ያሉትን ሰለማዊ የሆኑ ህዝቦች አብረው ሲኖሩ የነበሩትን ግንኙነት ለማበላሸት እና ልዩነትን ለማጉላት በሚል የተቀመጠ ድንጋጌ አድርገው የሚመለከቱ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ይህ ድንጋጌ በሀገሪቷ ውስጥ የነበረውን ተጨባጭ የህዝቦች ችግር ለመፍታት በሚል የገባ ችግር ፈቺ እና ምክንያቲያው ድንጋጌ እንደሆነ አድርገው ይገልጹታል፡፡ በዚህ ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ ላይ ሕገ-መንግሥቱ ለሕገ-መንግሥት አርቃቂ ጉባኤ ቀርቦ በሚታይበት ወቅትም ቢሆን የተለያዩ ሀሳቦች የተነሰቡት እና በሃላም ላይ ድንጋጌው ተቀባይነት አግኝቶ የጸደቀበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ በሕገ-መንግሥቱ ላይ የተደነገገው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ አለው የሚለው ድንጋጌ ይዘት ላይ ምን እንደሆነ እና ምን እንዳልሆነ፤ እነዚህን ልዩ ጥቅሞች በስራ ላይ ለማዋል በሚታሰብበት ውቅት ታሳቢ ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጉዳዮች በመግለጽ ለውይይት የሚሆን መነሻ ሀሳብ ማቅረብ ነው፡፡

የኦሮሞ ህዝብ የብዙ ሺህ ዘመናት አኩሪ ታሪክ ያለው፤ ዘመናው የዲሞክራሲ እሴቶች የሆኑ የመንግሥት አመራር እና አስተዳደር የነበራቸው፤ የራሱ የዘመናት አቆጣጠር፤ አኩሪ ባህላዊ እሴቶች ያሉት ህዝብ ነው፡፡ይህ ህዝብ እንደማናኛውም ህዝብ የነበረው ስልጣኔ እየወደቀ እየተነሳ፤ ከሌሎች ጎረቤት ህዝቦች ጋር ሰላማዊ የሆነ ተቻችሎ የመኖር ባህሪያቶችን ይዞ የኖረ እና እየኖረ የሚገኝ ህዝብ ነው ቢሆንም የራሱን ባህል፤ ቋንቋ ታሪክ እና ሌሎች የማንነት መገለጫዎች እንደ ሃላ ቀር በመቅጠር በፊት የነበሩት የንጉሳዊያን አስተዳደሮች በህዝቡ ላይ እጅግ አሳዛኝ እና ታሪክ ሊረሳው የማይችል ድርጊት ሲፈጽሙ ቆይተዋል፡፡ሕዝቡ ሲፈጸሙበት የነበሩትን ድርጊቶች አንዳንዴ በተደራጃ እና በአብዛኛው በተበታተነ መልኩ ሲታገል እና ሲቃወም ቆይቶ ራሱ በላካቸው ወኪሎቹ መሰረት በ1987 ዓ.ም የጸደቀውን የኢፌደሪ ሕገ-መንግሥት የክልል ባለቤት ሊሆን ችሎዋል፡፡ ህዝቡ የራሱ የሆነ ክልል እንዲኖረው ማድረጉ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች እና የተለያዩ ክልላዊ አስተዳደሮች ጋር ሊኖረው ስለሚገባው ግንኙት ምን መምሰል እንዳበት በሕገ-መንግሥቱ ላይ ደንግጎዋል፡፡ በዚህ አግባብ በሕገ-መንግሥቱ ላይ ከተቀመጡት መሰረታዊ ጉዳዮች አንዱ ክልሉ ከአዲስ አበባ ከተማ ላይ ልዩ ጥቅም ሊኖረው የሚገባ እንደሆነ የሚያስቀምጠው ድንጋጌ አንዱ ነው፡፡በሕገ-መንግሥቱ ላይ የተቀመጠው ፌደራላዊ ስርዓት መሰረታዊ እምነቱ ብዙሀነትን ማዕከል ያደረግ አንድነትን መፍጠር እንደሆነ በመግቢያው ላይ ደንግጎዋል፡፡

ሕገ-መንግሥቱ ላይ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ ላይ አለው የሚለው ድንጋጌ ልዩ ጥቅም የሚባሉ ሊጠበቅላቸው/ሊንጸባረቅባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ምን እንደሆነ ያመለከተ እንጅ ልዩ ጥቅም ለሚለው ሀረግ የሰጠው ትርጉም የለም፡፡ ልዩ ጥቅም የሚለውን ሀረግ ሲታይ ልዩ የሚለው ቃል ከአንድ ነገር ጋር የተያያዘ እና ከተለመደው ወጣ ያለ የሚለውን ሁኔታ የሚገልጽ ሲሆን ጥቅም የሚለው ደግሞ ህጋዊ ተቀባይነት ያለው አንድ ጉዳይ ላይ ሊኖር የሚችለውን መብት የሚመለክት እንደሆነ ሊወሰድ ይችላል፡፡ስለሆነም ክልላዊ መንግሥቱ  በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም አለው ሲባል ተለይቶ የሚታወቅ ሕገ-መንግሥታዊ መብት የሚያጎናጽፍ ጥቅም አለው ተብሎ ይወሰዳል፡፡

ሕገ-መንግሥቱ በአንቀጽ 49 ላይ ለክልሉ መንግሥት ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ ላይ እንዲጠበቅ የፈለገበት ምክንያት ምን እንደሆነ ሕገ-መንግሥቱ ሲዘጋጅ በአንቀጹ ላይ ከተካሄዱ ወይይቶች፤ ከፌደራል ስርዓቱ መሰረታዊ ባህሪያት እና መነሻ ምክንያቶች አንጻር የሚከተሉት ሊሆኑ እንደሚችሉ ይወሰዳል፡፡

የመጀመሪያው አዲስ አበባ ካላት ተፈጥሮዋዊ አቀማመጥ ጋር የሚያያዝ ሲሆን አዲስ አበባ የሚያስፈልጋት የተለያዩ ፍላጎቶች ለሟሟላት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጋር ያላት ግንኙት ተግባራዊ አስገዳጅ ሁኔታ ነው፡፡አዲስ አበባ የሚገቡ የተለያዩ ምርቶች በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ እያለፉ የሚገቡ መሆናቸው እንደዚሁም አዲስ አበባ ከተማ ወደ ሌሎች የሀገሪቷ አካባቢዎች የምታከፋፍላቸው ምርቶችና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሰት በኩል የሚታላለፉ መሆናቸው በሁለቱ አካላት መካከል ከፍተኛ የሆነ ግንኙነት እና መስተጋብር መኖሩ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሰት ጥቅም ምን መሆን አለበት የሚለው ለመወሰን እንደ አንድ ምክንያት ሊወሰድ ይችላል፡፡

የኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት መሰረታዊ ባህሪው ክልሎች እኩል መብት እና ስልጣን ያላቸው መሆናቸውን የሚያስቀምጥ ቢሆንም symmetrical federalism ሀገሪቷ ወስጥ የሚገኙ ክልሎች ካላቸው ተጨባጭ አቀማመጥ በመነሳት ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ ላይ ሊኖር እንደሚገባ በመደንገግ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ማዕከል ያደረገ የፌደራል ስርዓት asymmetrical federalism መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ሕገ-መንግሥቱ አንዳንድ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ በዕድገት ወደ ሃላ ለቀሩ ብሔራ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ልዩ ድጋፍ ይደረጋል የሚለው ሲታይ የእኩልነት መርሁ እንደተጠበቀ ሆኖ  ፌደራሊዝሙ አግባብነት ያላቸውን ተጨባጭ ሁኔታዎን የተመረኮዘ ድንጋጌዎችን የያዘ መሆኑ በተለያዩ ጥቅሞች መካከል ሊነሱ የሚችሉ ግጭቶችን ቀድሞ በመለየት መፍትሔ ያስቀመጠ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ስለሆነም አዲስ አበባ ከተማ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መሀል ላይ መሆና፤ በሁለቱ አካላት ህዝቦች መካከል ከፍተኛ ሊባል የሚችል ግንኙነቶች መኖራቸው ተጨባጭ ሁኔታዎች መሆናቸው የሚታወቅ በመሆኑ ይህን ያገናዘበ ድንጋጌ በሕገ-መንግሥቱ መኖር ተገቢ ነው፡፡ ሕገ-መንግሥቱ በሚጸድቅበት የሕገ-መንግሥቱ አርቃቄ ጉባኤ የብሄር፤ብሔረሰቦችና ህዝቦች ኮሚቴ አባላትም ሲያንጸባርቁት የነበረው ሀሳብ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ለፌደራል መንግሥቱ ተጠሪ የሆነ ሕገ-መንግሥታዊ የቻርተር ከተማ ሲሆን ከዚህ ከተማ ጋር የሚኖረው ግንኙነት ምን መምሰል እንዳለበት በሕገ-መንግሥት ደረጃ ማስቀመጡ ተገቢ ነው፡፡በክልሎች መካከል ሊኖር የሚገባው ግንኙነት ምን መምሰል እንዳለበት ሕገ-መንግሥቱ በቂ ሊባል የሚችል ድንጋጌዎችን ያስቀመጠ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሰት መካከል ያለውንም ግንኙነት አስቀምጦዋል፡፡ ሕገ-መንግሥቱ የክልሎች አወሳሰን ሊለወጥ የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ያስቀመጠ ቢሆንም በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአዲስ አበባ መካከል ያለው ወሰን ግን የአከላል ለውጥ ሊኖረው እንደማይችል ከሕገ-መንግሥቱ ንባብ መረዳት ይቻላል፡፡ስለሆነም ከአከላል ለውጥ ውጭ ያሉ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ልዩ ጥቅም በተመለከት ልዩ ዘላቂ ጥቅም እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ይህ ድንጋጌ በሕገ-መንግሥቱ ሊቀመጥ ችሎዋል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መሀል ላይ አዲስ አበባ የምትገኝ መሆና እና ይህቺ ከተማ አሁን ካሉ የአካባቢ ስሞችም በመነሳት በሚታይበት ወቅት ኦሮሞዎች ሲኖሩበት የነበረ ከተማ በመሆና እና ኦሮሞዎች ካላቸው ተፈጥሮዋዊ እና ታሪካዊ ከሆኑ ፍላጎት በመነሳት በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ልዩ ጥቅም ሊኖራቸው ይችላል፡፡

በሕገ-መንግሥቱ ላይ የተቀመጡት ልዩ ጥቅሞች ምንድን ናቸው

በሕገ-መንግሥቱ ላይ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከአዲስ አበባ ከተማ ላይ ሊኖረው የሚገባው ልዩ ጥቅም በምን ጉዳዮች ላይ እንደሆነ ደንግጎዋል፡፡በዚሁ መሰረት የአገልግሎት አቅርቦት፤ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም፤ አስተዳደሪያዊ  እና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ሊጠበቅ ይገባል በሚል ደንግጎዋ፡፡

የአገልግሎት አቀርቦት ጉዳዮች

በሕገ-መንግሥቱ ላይ ያለው የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም አንዱ ከአግልግሎት አቀርቦት (የእንግሊዘኛው ቅጂ social services በማለት አጥብቦ ይተረጉመዋል) ጋር በተያያዘ ያለው ሲሆን በዚሁ መሰረት ይህ የአገልግሎት አቅርቦት አዲስ አበባ ከተማ ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሊሰጣቸው የሚችሉ አግልግሎቶችን የሚያቅፍ ነው፡፡ እነዚህም አገልግሎቶች በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች የሚያገኙዋቸው  ወደ አዲስ አበባ ለመግባት በአዲስ አበባ አስተዳደር የሚዶጎሙ የትራንስፓርት፤ የመሰረተ ልማት እና ሌሎች አቅርቦቶች ናቸው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሚገኙ ነዋሪዎች የተለያዩ አገልግሎቶችን ከአዲስ አበባ ለማግኘት በሚመጡበት ወቅት አግልግሎቶቹን በሚመቻቸው አግባብ ለመስጠት እንዲያስችል ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይጠይቃል፡፡

በሌላ መልኩ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ዋና ከተማ ፊንፊኔ በመሆና የክልል መንግሥት በአዲስ አበባ ከተማ የሚዶጎሙ አቅርቦቶች / ውሀ፤ መብራት፤ ህንጻ፤ መሬት እና የመሳሰሉትን/ ሊያገኙ የሚገባቸው መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ይህ ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባ በክልሉ መሀል ላይ የምትገኝ እና የኦሮሞ ህዝቦች በአንድነት ሊገናኙባት የምትችል ከተማ በመሆና ምክንያት አነዚህ ህዝቦች የተለያዩ ፍላጎቶቻቸውን ለመግለጽ በሚፈልጉበት ወቅት የተለያዩ ማዕከላት፤ ስቴድዮሞች፤ ሜዳዎች ለዚህ አግልግሎት እንዲውሉ ማድረግ የክልሉን መንግሥት ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ ለማስከበር የሚረዳ ይሆናል፡፡

የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአዲስ አበባ ላይ ያለው ሌላው ጥቅም ከተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ያለው መብት ነው፡፡ የፌደራል መንግሥቱ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና ጥበቃን በተመለከተ ሕግ የማውጣት ስልጣን የተሰጠው ሲሆን የክልል መንግሥታት የፌደራል መንግሥቱ የሚያወጣው ሕግ ላይ በመመርኮዝ የተፈጥሮ ሀብት የማስተዳደር ስልጣን ተሰጥቶዋቸዋል፡፡ የፌደራል መንግሥቱ የሚያወጣውን የተፈጥሮ ሀብት ሕግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ ላይ በሚያውልበት ወቅት ይህ ሕግ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ልዩ ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆኑን ማረጋጥ አስፈላጊ ይሆናል፡፡በዚሁ መሰረት አዲስ አበባ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት ከራሳ በማውጣት ስራ ላይ ማዋል ስትፈልግ ይህ በኦሮሚያ ላይ ሊያደርስ የሚችለው አሉታዊ ውጤት ምንድን ነው ብሎ መመልከት አለበት ማለት ነው፡፡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ላይ ሊኖረው የሚችለው ልዩ ጥቅም ሁለት ዓይነት ይዘት ሊኖረው ይችላል፡፡ የመጀመሪያው በአዲስ አበባ የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶች አዲስ አበባ ከተማ ሲጠቀም አጠቃቀሙ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ በሚገኙ ነዋሪዎች ላይ የጤና፤የደህንነት ጉዳት የማያደርስ እንደሆነ ማድረግ ሲሆን ይህም ጉዳት ባለማድረስ የክልሉን መንግሥት ልዩ ጥቅም መጠበቅ በሚል ሊታይ የሚችል ነው፡፡ ሁለተኛው አዲስ አበባ ከተማ የሚያስፈልጋት የተፈጥሮ ሀብት በአብዛኛው የሚገኘው ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ነው፡፡ ለመኖሪያ ቤት የሚያገግሉ የተፈጥሮ ሀብቶች፤ ለኢንደስትሪ እና ለፍብሪካ የሚያስፈልጉ የተፈጥሮ ሀብቶችን አዲስ አበባ በቅርበት የምታገኘው ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ነው፡፡እነዚህን የተፈጥሮ ሀብቶች ከክልሉ አዲስ አበባ ነዋሪዎች እና ድርጅቶች ሲያገኙ ይህ ድርጊታቸው በክልሉ መንግሥት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ እና ይልቁንም ለሚያገኙት የተፈጥሮ ሀብት ልዩ የሆነ ጥቅም/ በክፍያ ወይም በሌላ መልኩ ሊሆን ይችላል/ ለክልሉ መንግሥት መስጠት አለባቸው፡፡ በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ማህበረሰቦች እና ፋብሪካዎች ከኦሮሚያ የተፈጥሮ ሀብት ሲጠቀሙ ሊያወጡ የሚገባቸው ክፍያ እና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እና ፋብሪካዎች ከኦሮሚያ የተፈጠሮ ሀብት ሲጠቀሙ ሊያወጢ የሚገባቸው ክፍያዎች እኩል መሆን የለባቸውም፡፡ ስለሆነም ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ የክልሉን መንግሥት ጥቅም ሊያስከብር በሚያስችል መልኩ መታሰብ ይኖርበታል፡፡

አስተዳደሪያዊ ጉዳዮች

በአንዳንድ ሀገሮች ዋና ከተሞች ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች (ለምሳሌ በርሊን፤ ሞስኮ) የሚሆኑበት እና እነዚህ ከተሞች የዋና ከተማነት ስልጣንና ሃላፊነት እንደዚሁም ሌሎች ክልሎች ያላቸው ስልጣንና ሃላፊነት የሚኖራቸው ናቸው፡፡በሌሎች ሀገሮች ደግሞ ዋና ከተሞች በፌዴራል መንግሥቱ ስር እንዲጠቃለሉ የሚደረግበት (ለምሳሌ ሜክሲኮ እና ዋሽንግተን ዲሲ) ወይም ዋና ከተሞችን የክልል መንግሥታት በራሳቸው ስር የሚጠቀልሉበት(ለምሳሌ በርን እና ፕሪቶሪያ) አሰራር አላቸው፡፡ ዋና ከተሞች ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች ሲሆኑ የፌደራል መንግሥቱ ተጠሪ ስለማይሆኑ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ያላቸው ግንኙነት እንደ ሌሎች ክልሎች ይሆናል፤ የፌደራል መንግሥቱም ተጽእኖ ያነሰ ይሆናል፡፡ ዋና ከተሞች የፌዴራል መንግሥቱ ተጠሪዎች ሲሆኑ የፌደራል መንግሥቱ በዋና ከተማ ላይ ያለው ተጽእኖ የማሳረፍ አቅሙ ክፍ የሚል ሲሆን፤ ዋና ከተሞች በክልል መንግሥታት ስር ሲወድቁ ደግሞ የክልል መንግሥታት ተጽእኖ ከፍ ያለ ይሆናል፡፡

በኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት አዲስ አበባ ከተማ ራሳን በራሳ የማስተዳደር እና በፌደራል የህዝብ ተዋካዮች ምክር ቤት የራሳ ተዋካዮች ያላት መሆኑ ሲታይ እንደ በርሊን እና ሞስኮ መሰል ስልጣን ያላት ከተማ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን፤ የፌደራል መንግሥቱ ተጠሪ መሆና፤ ክልል አለመሆና እና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ልዩ ጥቅም ልታከብር እንደሚገባ የሚገልጸው ድንጋጌ ሲታይ በተወሰነ ደረጃ የፌደራል አካል ከተማ መሆናን እና የክልል ልዩ ጥቅም አካባሪ መሆን እንዳለበት የሚያሳይ ድብልቅ የሆነ አካሄድ በሕገ-መንግሥቱ ላይ የተቀመጠ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

ሕገ-መንግሥቱ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ሊከበር ይገባል በሚል ካስቀመጣቸው ጉዳዮች አንዱ አዲስ አበባ በክልሉ መሀል የምትገኝ በመሆኑ ሁለቱን የሚመለከቱ አስተዳደሪያዊ ጉዳዮች ላይ ልዩ ጥቅም ሊኖራት ይገባል የሚል ነው፡፡ በሕገ-መንግሥቱ ላይ የአዲስ አበባ አስተዳደር ጉዳይ በተመለከተ ከተማው ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን እንዳለው እና ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግሥቱ እንደሆነ ተደንግጎዋል፡፡ስለሆነም አዲስ አበባን ማስተዳደር self rule በተመለከተ ስልጣኑ ሙሉ በሙሉ የተሰጠው ለአዲስ አበባ እና ለፌዴራል መንግሥቱ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በሌላ መልኩ አዲስ አበባ በክልሉ መሀል ላይ ያለች በመሆኑ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደሪያዊ ጉዳዮች በተመለከተ የክልሉ መንግሥት ልዩ ጥቅም ያለው ሲሆን ይህም ሁሉቱን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ክልሉ በጋራ የማስተዳደር ልዩ ጥቅም shared rule ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም አዲስ አበባ ከተማ ከማስተዳደር ጋር በተያያዘ የሚወጡ ህጎች የአዲስ አበባን ራስን በራስ የማስተዳደር እና የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም የሚመለከት የማስተዳደር ስልጣን ያቀፈ ወይም የሚያመለክት መሆን ይኖርበታል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ እንደማንኛውም ክልል ውስጥ እንደሚገኝ ህዝብ እሱን የሚመለከት ጥቅሞች፤ ፍላጎቶች ምን እንደሆነ የሚገልጽበት፤ እነዚህን ጥቅሞች እና ፍላጎቶች ደግሞ በስራ ላይ ለማዋል ምን ዓይነት አደረጃጀቶች ሊኖሩት እንደሚገባ በሕግ ሊወስን ይችላል፡፡ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ህዝብ ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ ከሚኖሩ ነዋሪዎች ጋር የሚዋሰን ስለሆነ በሁለቱ ነዋሪዎች መካከል የጋር የአስተዳደር ጉዳዮች ላይ በጋራ የሚሰሩበት ሁኔታ መኖር አለበት፡፡ ይህ ሁኔታ ሲታይ የክልል መንግሥታት ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ስልጣን እና የፌደራል መንግሥቱ ደግሞ የክልል መንግሥታት የጋር ስልጣን መገለጫ እንደሆነው ሁሉ የአዲስ አበባ ከተማ እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሰት ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደር ጉዳዮችን ለይተው እነዚህን ጉዳዮች በጋር የሚያስተዳደሩበት መዋቅርና አደረጃጃት ሊኖራቸው ይገባል ማለት ነው፡፡ የአዲስ አበበ ከተማ እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የጋራ የአስተዳደር ስልጣኖች በሚቀመጡበት ወቅት ከሁለቱ አካላት ሕገ-መንግሥታዊ ስልጣን፤ የፌዴራል መንግሥቱ በሕገ-መንግሥቱ ላይ ከተቀመጡለት ስልጣናት አንጸር ተለይተው መታየት እና መቀመጥ ይኖርባቸዋል፡፡

ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ሕገ-መንግሥቱ ደንግጎዋል፡፡ በሕገ-መንግሥት ድንጋጌ ውስጥ ሌሎች ተመሳሳይ የሚሉ እጅግ ጥቅል የሆኑ ድንጋጌዎችን ማስቀመጥ ያልተለመደ ቢሆንም ከዚህ በላይ ከተቀመጡት ጉዳዮች ውጪ የሆኑ ነገር ግን ከጉዳዮች ብዙም ያልራቁ እንደግዜው ተጨባጭ ሁኔታ የክልሉን መንግሥት ጥቅም ለማስጠበቅ ያስችላሉ የሚባሉ ጉዳዮች ሊያካትት እንደሚችል ግን ታሳቢ ሊደረግ ይገባል፡፡ ስለሆነም እነዚህ ጉዳዮች ባህላዊ ልዩ ጥቅምን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ጉዳዮች፤ ታሪካዊ ልዩ ጥቅምን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ጉዳዮች፤ እና የመሳሰሉት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በሕገ-መንግሥቱ ላይ የተቀመጠው ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች የሚለው ሀረግ እጅግ በጣም ስፍቶ ወይም ጠባ ሳይሆን ሕገ-መንግሥታዊ አንድ ፓለቲካ እና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ መገንባት በሚያስችል መልኩ ለመቶርገም እንዲያስችል በበቂ ጥነት ተለይቶ መታየት ይኖርበታል፡፡

ሕጉ እንዴት ይደንገግ

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከአዲስ አበባ ሊኖረው የሚገባ ልዩ ጥቅም በተመለከት ሕግ- የማውጣት ስልጣን በሕገ-መንግሥቱ መሰረት የተሰጠው አካል የፌዴራል መንግሥቱ የክልሉ መንግሥት ወይም የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የሚለው ጥያቄ ብዙ ሀሳብ የሚቀርብበት ነው፡፡ በሕገ-መንግሥቱ መሰረት ሕግ የማውጣት ስልጣን በግልጽ የተሰጠው በፌደራሉ መንግሥት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ለክልል መንግሥታት ደግሞ የክልል ምክር ቤቶች ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በተቋቋመበት ቻርተር መስረት ሕግ የማውጣት ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ሕገ-መንግሥቱ ሕግ ይወጣል ይበል እንጂ የትኛው አካል ያወጣል የሚለውን ምላሽ ያልሰጠ ሲሆን በዚህ ጸሀፊ እምነት ሶስቱም አካላት ሕግ የማውጣት ሂደቱ ላይ ቀዳሚ ተሳታፊ ቢሆኑም ሕጉ መታወጅ ያለበት ግን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆን አለበት፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በሕገ-መንግሥት ላይ የተጠበቁለት የልዩ ጠቅም መገለጫ የሆኑ ጉዳዮች ይዘት፤ አፈጻጸም ምን መሆን አለበት የሚለው ላይ የልዩ ጥቅም ተጠቃሚው ራሱ በመሆኑ ሕጉ እንዲወጣ እና የሕጉም ይዘት ምን መምሰል አለበት የሚለው ላይ የአንበሳውን ድርሻ ወስዶ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ስልጣን ያለው ህዝብ ስለሆነ ከክልሉ መንግሥት ጋር ባሉ የክልሉን ልዩ ጥቅም የሚመለከቱ ሕገ-መንግሥታዊ ምንጫ ያላቸው ጉዳዮች ላይ ከራሱ ጠቅም አንጻር በመመልከት የክልል መንግሥት ባቀረበው ሀሳብ ላይ ግብዓት መጨመር ይኖረበታል፡፡ የፌደራል መንግሥት ሕግ አውጪ አካል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሀገሪቷ ከፍተኛ የፓለቲካ ስልጣን ባለቤት በመሆኑ እና የኦሮሚያ ክልል ህዝብ ተወካዮች፤ የአዲስ አበባ ህዝብ ተዋካዮች የሚገኙበት ምክር ቤት በመሆኑ ሕገ-መንግሥቱን ማዕከል በማድረግ የክልሉን ልዩ ጥቅም የሚያስከብር ሕግ ሊያወጣ ይገባል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እያስተዳደረ የሚገኘው የኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት የክልሉን ልዩ ጥቅም ለማስከበር እየሰራ እንደሚገኝ ግለጽ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ተወካዮች እና የህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት አባላት ተወካዮች ባሉበት ሕጉን የማዘጋጀቱ ስራ ቢከናወን የበለጠ ውጤታማ ይሆናል፡፡

ሕጉ ሲወጣ ታሳቢ ሊደረጉ የሚገቡ ጉዳዮች

የ1987 ሕገ-መንግሥት ወደ ሃላ እንዲሁም ወደ ፊት የሚመለከት ሕገ-መንግሥት ሲሆን ወደ ሃላ ሲመለከት ሃገሪቱ ለብዙ ዘመናት የሰው ልጆች ማንነት መገለጫ የሆኑትን ቋንቋ፤ ባህል፤ ታሪክ እኩል በሆነ ደረጃ እውቅና ባለመስጠት እንዲጠፊ ሲደረግባት የነበረች ሀገር መሆናን እና ይህም የሀገራችን የተዛባ ታሪካዊ ግንኙነት ዋና መገለጫ መሆኑ፤ በሌላ መልኩ ይህን የተዛባ ታሪካዊ ግንኙነት በማረም ብዝሀነትን የምታስተናግድ ሀገር ለማድረግ  ብሄር፤ ብሄረሶቦችን ህዝቦች ቃል ኪዳን ያሰረቡት ነው፡፡ ስለሆነም ይህን መሰረታዊ ሀሳብ ማዕከል በማድረግ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም በሕግ ሲደነገግ ታሳቢ ሊደረጉ የሚገባቸው ጉዳዮች የሚከተሉት ሊሆኑ ይችላል፡፤

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም በሕግ ሲደነገግ ሕገ-መንግሥታዊ ግቦች constitutional aspiration የሆኑነትን አንድ የፓለቲካ እና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት በሚያስችል መልኩ መሆን አለበት፡፡ ይህ ሕገ-መንግሥታዊ ግብ እንዲሳካ የክልሉ መንግሥት ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ የሚኖሩትን ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሕገ-መንግሥታዊ መብቶችና ጥቅሞች የሚያከብር/የሚያስተናግድ፤ የልዩ ጥቅሙ የመጨረሻ ግብ ተባብሮ፤ተደጋግፎ አንድ ጠንካራ ሀገር መመስረት መሆኑ ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት፡፡ ስለሆነም ልዩ ጥቅም የክልሉን ሕገ-መንግሥታዊ ልዩ ጥቅማ የማያሳንስ እንደዚሁም የአዲስ አበባ ከተማ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፤ የፌደራል መንግሥቱን የተጠሪነት ስልጣን የማይጋፍ እንዳይሆን በጥንቃቄ መሰራት አለበት፡፡

የክልሉ መንግሥት ሕገ-መንግሥታዊ የሆነው ልዩ ጥቅሙ መከበር በክልሉ ውስጥ ለሚኖሩ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በሀገሪቷ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ጥቅሞች ተቻችለው ተደጋግፈው ሊያድጉ የሚችሉበትን ሁኔታ የሚያሳይ በመሆኑ ሕጉ በሚወጣበት ወቀት ከፍተኛ የሆነ ተሳትፎ እና ወይይት ሊደረግ ይገባል፡፡ ውይይቱም ማዕከሉ ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌን እና ግብን ስራ ላይ ማዋል እንደሆነ በማስገንዘብ ከአሁን በፊት የነበሩ ተግባራዊ ተሞክሮዎችን በመንተራስና በመተንተን መሆን ይኖርበታል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ልዩ ጥቅም በክልል ደረጃ ለክልሉ መንግሥት የተሰጠ መሆኑ የክልል የልዓላዊ ስልጣን ባለቤት የሆነው የኦሮሞ ህዝብ ልዩ ጥቅም መሆኑ እንደጠበቀ ሆኖ፤ ከአዲስ አበባ ጋር የሚያዋስኑ የኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ነዋሪዎች ከአዲስ አበባ ጋር በተገናኘ እንዲጠበቅላቸው የሚፈልጉት ልዩ ጥቅሞች ምን እንደሆነ ከጉዳዮቹ አንጻር ለይተው እንዲያስታውቁ ፍላጎታቸው መጠይቅ ማለትም ጥናት መካሄድ ይጠበቅበታል፡፡

በመጨረሻም በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁት ሀሳቦች ሕገ-መንግሥታዊ መሰረት ያለውን የክልሉን መንግሥት ልዩ ጥቅም እንዴት በስራ ላይ ሊውል ይገባል የሚል እና ይህም ጉዳይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጥቅም እና ፈላጎት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚነካ በመሆኑ የሕግ ባለሞያዎች እና የፓለቲካ ሊሂቃን አስተያየቶች በመስጠት ቢያዳብሩት የሚመከር ነው፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ሰበር ለመታረቅ በተደረገ ስምምነት ላይ የያዘው አቋም ሲፈተሽ
The Curious Case of Construction & Business Bank

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 14 December 2024