Font size: +
18 minutes reading time (3551 words)

የሰበር ሰበር ስልጣን በኢትዮጵያ የህግ ስርዓት ውስጥ ያለው እንድምታ፡- ህገ- መንግስታዊ መሰረትና በዝርዝር ህግ ውስጥ የሚካተትበት አግባብ

የኢትዮጵያ የህግ ስርዓት በተለያዩ የመንግስት የአስተዳደር ስርዓት ውስጥ በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ልዩነቶች ሲታዩበት የነበረ ቢሆንም አደረጃጀቱም የዚያኑ ያክል ተለዋዋጭነት የነበረው መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በተለይም ከያዝነው ርዕስ ጋር በተያያዘ የፍርድ ቤቶች አደረጃጀትና በጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ውሰኔ የመስጠት ሂደት በተለያዩ ስርዓቶች የተለያየ ሂደት ሲኖረው ተስተውሏል፡፡ ከ1980ዎቹ አጋማሽ በፊት የነበሩት ስርዓቶች የአህዳዊ ስርዓትን የሚከተሉ ከመሆናቸው አንፃር የፍርድ ቤቶች አደረጃጀት በዚሁ አይነት አተያይ የተቀረፀ ነበር፡፡

በዘውዳዊው ስርዓት የነበረውን የፍርድ ቤቶች አደረጃጀት ስናይ በተሻሻለው ህገ መንግስት አዋጅ ቁጥር 149/1948 ምዕራፍ  6 ስለ ዳኝነት በሚዘረዝረው ስር  አንቀፅ 108 እና አንቀፅ 109 ስር የዳኝነት ስልጣን በህግ ለተቋቋሙ ፍርድ ቤቶች የተሰጠ እንደሆነ እና የጠቅላይ የንጉሰ ነገስት ፍርድ ቤትና እንዲሁም በህግ እንደሚወሰን ወይም እንደሚፈቀደው ሌሎች ፍርድ ቤት እንደሚኖሩ ይደነግጋል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ አንፃር በሐገሪቱ አንድ ማዕከላዊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደሚኖርና ይህም በሐገሪቱ ለሚነሱ ጉዳዮች የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥ እንዲሁም በ1966 ዓ.ም የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ረቂቅ አንቀፅ 120 መሰረት ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሐገሪቷ የመጨረሻ ፍርድ ቤት እንደሆነና ይህም ህገ መንግስትን ጭምር የመተርጎም ስልጣን እንዳለው ይደነግጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የይግባኝ ፍርድ ቤቶችና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች እንደሚኖሩ አስቀምፀጧል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዬጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስትን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 1/1967 ምዕራፍ 14 አንቀፅ 102 (1፣2) በህዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊኩ የበላይ የዳኝነት አካል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደሆነና ይህም በሐገሪቱ ፍርድ ቤቶች ሁሉ የሚከናወኑ የዳኝነት ተግባሮች የመቆጣጠር ስልጣን ያለው መሆኑን ያስቀምጣል፡፡

ከእነዚህ  የሁለት ህገ መንግስት ድጋጌዎችና ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስትን ለማቋቋም ከወጣው አዋጅ ለመረዳት እንደሚቻለው በአህዳዊ ስርዓት ውስጥ አንድ የጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደሚኖር እና ፍርድ ቤቱም የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥ ያስረዳናል፡፡

እነዚህ ስርዓቶች  በዲሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ስርዓት ከተተኩበት 1983 ዓ.ም ጊዜ ጀምሮ የፍርድ ቤቶች አወቃቀር ከመንግስቱ የስርዓት ለውጥ ጋር ተያይዘው ሊቀየሩ ችለዋል፡፡ ከፌዴራል አወቃቀር አንፃር ክልሎች 1987 ዓ.ም በወጣው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት የራሳቸው ስልጣን ያላቸው ከመሆኑና የመንግስት የስልጣን ባለቤት ከመሆናቸው አንፃር መሰረታዊ የሆኑ የመንግስት ስራዎችና ስልጣኖች ለክልሎች እንዲከፋፈሉ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም በህገ መንግስቱ አንቀፅ 50 (1፣2) የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በፌዴራል መንግስትና በክልል መንግስታት የተዋቀሩ መሆኑን ገልፆ እነዚህ አካላት የየራሳቸው የተናጠል የህግ አውጭነት፣ የህግ አስፈፃሚነትና የዳኝነት ስልጣን ያላቸው መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ከዚህ አንፃር እዚህ ሶስት የመንግስት አካላት በፌዴራሉና በክልሎች እኩል ቦታ እንዳላቸው ግልፅ ነው፤ በሌላ በኩል ህገ መንግስቱ[2] በምዕራፍ ዘጠኝ ስለዳኝነት አካል በግልፅ አስቀምጧል፡፡ ከዚህ አንፃር ስለ ዳኝነት አካሉ ግልፅ ድንጋጌዎችና የስልጣን ዝርዝሮችን ያስቀመጠ ቢሆንም በአንፃሩ አንዳንድ ዝርዝር ትርጓሜ  የሚፈልጉ ጥቅል ድንጋጌዎች ተካተዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነው የሰበር ሰሚ ችሎት በህገ መንግስቱ ያለው እንድምታና የሰበር ሰበር በህገ መንግስታች ያለው ቦታ ምን ይመስላል የሚለው ነው፡፡

ስለሆነም በዚህ የመነሻ ፅሁፍ ውስጥ የሰበር ሰሚ ችሎትን ህገ መንግስታዊ መሰረትና ችሎቱ በተለይም በፌዴራል ደረጃ ያለው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የክልሎችን ውሳኔዎች በማየት ረገድ ያለው ህገ መንግስታዊ ስልጣን ምን እንደሆነና በወንጀል ስነ ስርዓቱ ውስጥ ይህ ሐሳብ ምን መልክ ሊካተት ይችላል የሚለው በአግባቡ ተለይቶ የሚቀርብ ይሆናል፡፡

በአጠቃላይ ፅሁፉ ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሲሆን የህገ መንግስቱ አንቀፅ 80 (1) እና አንቀፅ 80(3(ሀ)) ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅና ሌሎችም አንፃር ሊተረጎም የሚገባው እንዴት ነው?፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ስልጣን በምን ጉዳዮች ላይ ነው?፣ለህገ መንግስቱ አንቀፅ 80(3(ለ)) አንፃር የክልሎች የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ተፈፃሚነት እስከምን ድረስ ነው? እና ለክልል በተሰጡ ጉዳዮች ላይ የፌዴራሉ ሰበር የመየት ስልጣን አለው ወይስ የለውም የሚለው ላይ ያጠነጥናል፡፡

1. በፌዴራልና በክልል የሚገኙ የመንግስት አወቃቀሮችና የፍርድ ቤቶች አደረጃጀት

እንደሚታወቀው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት በሶስት መንግስታዊ አካላት የተዋቀረ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በፌዴራል የህግ አውጭነትን ስልጣን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲሰጥ በክልል ደረጃ ደግሞ ለክልል ምክር ቤቶች ሰጥቷል፡፡ በተመሳሳይ ሆኔታ የአስፈፃሚነት ስልጣኑን ለፌዴራል መንግስቱ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ በክልሎች ደግሞ ለክልሉ ካቢኔ ተሰጥቷል፡፡ ከሁለቱ ጋር ትይዩ በሆነ መልኩ የዳኝነት ስርዓቱ በፌዴራሉና በክልሎች በየራሳቸው በሚኖራቸው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስር በሚደራጁ  ፍርድ ቤቶች እንዲዋቀር ተደርጓል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ህገ መንግስቱ የተቋማቱን አደረጃጀት ብቻ ሳይሆን የስልጣን ክልላቸውን ጭምር ለይቶ ለማስቀመጥ ችሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስልጣንን በውክልና በመስጠት  በክልል ፍርድ ቤቶች የሚሰሩ ስራዎችና የስልጣን እርከን ምን እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ ከዚህ አንፃር የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌዴራሉን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣን እንዲሁም የክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ስልጣንን በውክልና ያገኘ መሆኑ በህገ መንግስቱ በግልፅ ሰፍሯል፡፡

ስለዚህ ለክልል ጠቅላይና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በውክልና የተሰጡ የዳኝነት ስልጣኖች ከህገ መንግስቱ ሐሳብ አንፃር ሰበርን የማያካትቱ የመጀመሪያ ደረጃና የይግባኝ ዳኝነት ስልጣኖች ብቻ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ እዚህ ላይ የክልል ፍርድ ቤቶች በውክልና ባገኙት ጉዳይ ላይ የሰበር ስልጣን እንደሌላቸው ግልፅ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር የህገ መንግስቱ አንቀፅ 80(3(ለ))ይህን ሐሳብ ያጠናክራል፡፡ በመሆኑም ከዚህና ከሌሎች የህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች አንፃር ሲታይ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አንድን የህግ ስህተት ያለበትን ጉዳይ ማየት የሚችለው ጉዳዩ የክልል ጉዳይ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በአንፃሩ ግን የህግ መንግስቱ አንቀፅ 80(3(ሀ))

“ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበትን ማናቸውንም የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም በሰበር ችሎት የማየት  ስልጣን ይኖረዋል”

የሚለው  ክልሎች በራሳቸው  የስልጣን ክልል ሆኖ የቀረበውን ጉዳይ በሰበር ካዩ በኋላ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደገና በሰበር የማየት ስልጣን አለው ወይ የሚለው ግልፅ ትርጓሜ የሚያሻው በመሆኑ ከታች በዝርዝር የሚቀርብ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን ህገ መንግስቱ ምንም አንኳ የትኞቹ ጉዳዮች በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እንደሚታዩ ግልፅና ዝርዝር ድንጋጌ ባያስቀምጥም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፌዴራል ጉዳዮች ላይ  የበላይና የዳኝነት ስልጣን እንዲሁም የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደግሞ  በክልል ጉዳዮች ላይ  የበላይና የመጨረሻ የዳኝነት ስልጣን  ያላቸውን ቢሆንም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለባቸውን የክልሎ ጉዳዮችን ጭምር በሰበር የማየት ስልጣን እንዳለው ይገልፃል፡፡

እዚህ ላይ ትኩረት ሊሰጥ የሚገባው መሰረታዊው ጉዳይ ህገ መንግስቱ ለህግ አውጭውና ለህግ አስፈፃሚው ያልተከተለውን ስርዓት ለዳኝነት ስርዓቱ የተከተለው ለምንድን ነው የሚለው ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ልዩ ልዩ የመከራከሪያ ነጥቦች ይነሳሉ፡፡ በተለይም የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት  በማናቸውም ጉዳይ ላይ ውሳኔ መስጠቱ የፌዴራሊዚም ስርዓቱን ያጠናክራል የሚሉ ወገኖች ያሉ ሲሆን በተለይም በሀገሪቱ ያለውን የትብብር የፌዴራሊዚም ስርዓት ከማጎልበት፣  በሐገር ደረጃ ወጥነትና ተገማችነት ያለው የህግ አተረጓጎም  ስርዓት ከማዳበርና አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር ጋር ያያይዙታል፡፡

በሌላ በኩል ለፌደራልና በጋራ ለሁለቱ ከተሰጠው ስልጣን ውጭ ለክልሎች በተሰጡ ጉዳዮች ላይ ጭምር የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር ችሎቱ የክልል ጉዳዮች እንዲያይ መደረጉ በአንድ በኩል የፍርድ ቤቶችን አህዳዊ አሰራር የማያስቀር በሌላ በኩል ክልሎች  በራሳቸው ህግን እንዲያወጡ የተሰጣቸውን ስልጣን በሌላ በኩል መንጠቅ ያስመስላል የሚል መከራረሪያ ነጥብ ይቀርባል፡፡ በተለይም ክልሎች በራሳቸው ጉዳይ ላይ ወሳኝ ናቸው የሚለውን ህገ መንግስታዊ ሐሳብና በህገ መንግስቱ ህግ እንዲያወጡ ጭምር በተሰጣቸው ጉዳይ ላይ በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አንደገና መታየቱ አግባብነት የሌለው መሆኑን ያወሳሉ፡፡ ከእዚህ አንፃር ይህ አካሄድ በዝርዝር ህግ ገደብ ሊበጅለት ይገባል፡፡   (በአጠቃላይ አቅጣጫም ሐሳቡ የሚቀርብ ይናል)

2. ስለ ሰበርና የሰበር ስልጣን

ሰበር የሚለው ቃል ከፈረንሳይ ቃል የተወረሰ  ሲሆን በፈረንሳይ ካሴሲኖ የሚል ስያሜ አለው፡፡ ይኸውም መሻርን (invalidation) ወይም አንድ ውሳኔን መተውን (Abrogiation) ያመላክታል፡፡ በአገራችን የፍትህ ስርዓትም  ሰበር የሚለው ቃል በህገ መንግስቱና ህገ መንግስቱን ተከትለው በወጡ ሌሎች ህጎች ውስጥ  ተካቷል፡፡ ስለሆነም የሰበር ስርዓትን ማንኛውም ሰው በመብት መልክ አንስቶ የሚጠቀመው የይግባኝ አይነት ስርዓት ሳይሆን የፍትህ  ሚዛናዊነትና ርዕትነት ለማስጠበቅ ሲባል ብቻ ተግባራዊ የሚደረግ ልዩ ስርዓት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች በፌዴራልና በክልል ጉዳዮች ላይ እንደየቅደም ተከተላቸው የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን አላቸው፡፡ ስለሆነም እያንዳንዳቸው በሚኖራቸው  የጠቅላይ ፍርድ ቤት ለፍትህ ሚዛኛዊነትና ርዕትነት የየራሳቸው የሰበር ስልጣን ያላቸውን ችሎቶች ለማቋቋም ይችላሉ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ችሎቶች በየራሳቸው ጉዳይ ላይ ወጥነት ያለው የፍርድ ውሳኔና የህግ ትርጉም እንዲሰጡ ያስችላሉ፡፡

ከስልጣንም አንፃር ሲታይ እዚህ ችሎቶች መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለባቸውን ጉዳዮች ብቻ በሰበር የሚያዩ ሲሆን በተለይም የፌዴራሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ በሰጠባቸው፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመደበኛ ችሎት አይቶ ውሳኔ በሰጠባቸውና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመደበኛ ወይም በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ በሰጠባቸው  ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የሚሰጥ ይሆናል፡፡

1.       3. የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ስልጣንና ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ

ህገ መንግስቱ የፍርድ ቤቶችን ጣምራነትና ስልጣን በሚያስቀምጥበት  አንቀፅ የጠቅላይ ፍርድ ቤትን ሰበር ሰሚ ችሎት ስልጣንና ህገ መንግስታዊ መሰረት አስቀንጧል፡፡ በመሆኑም የህገ መንግስቱ አንቀፅ 80 (1፣2 እና 3)) በሚከተለው መልክ ተቀምጠዋል፡

አንቀፅ 80(1) “የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፌዴራል ጉዳዮች ላይ የበላይና የመጨረሻ የዳኝነት ስልጣን ይኖረዋል”

አንቀፅ 80(2) “የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክልሉ ጉዳይ ላይ የበላይና የመጨረሻ የዳኝነት ስልጣን ይኖረዋል፡፡ (የውክልና ስልጣን የተጨመረ)

አንቀፅ 80(3) “በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 1 እና 2 የተጠቀሰው ቢኖርም

ሀ. የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለበትን ማናቸውንም የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም በሰበር ችሎት የማየት ስልጣን ይኖረዋል፡፡ ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል

ለ. የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለበትን በክልል ጉዳዮች የተሰጠ የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም በሰበር ችሎት የማየት ስልጣን ይኖረዋል፡፡ ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል ይላል፡፡

እዚህ ላይ የሚነሳው ጉዳይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በክልልም ሆነ በከተማ አስተዳዳሮች የተሰጡ ውሳኔዎች ላይ የሰበር ስልጣኑን በመጠቀም  በክልል ደረጃ በሰበር የታዩትንም ጭምር እየመመረመረ ውሳኔ ብሎም በሁሉም አካላት ላይ ተፈፃሚነት ያለው የህግ ትርጉም እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ህገ መንግስቱ ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ማናቸውንም የመጨረሻ ውሳኔዎች ለማረም ስልጣን ሲሰጠው በአንቀፅ 80(3(ለ)) መልሶ ለክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በክልል ጉዳይ ላይ  መሰረታዊ የህግ ስህተት ካለ ለማረም በሰበር የማየት ስልጣን የሰጠውና  በአንቀፅ 80(3(ሀ)) ማናቸውንም የፍርድ ውሳኔ በሚል ያስቀመጠው ለምንድን ነው የሚለውን ማጤን ተገቢ ነው፡፡ ምንም እንኳ ህገ መንግስቱን ተከትለው በወጡ ሌሎች ዝርዝር ህጎች የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔ የሚለው ሐረግ ትርጓሜ ያልተሰጠው ቢሆንም ከህገ መንግስቱና ሌሎች ህጎች አንፃር እንድምታውን መፈተሽ ይቻላል፡፡ አቶ ሙራዱ አብዶ ባዘጋጁት review of decision of state courts over state matters  by the federal supreme court በሚለው ፅሁፋቸው ውስጥ የህገ መንግስት ጉባኤ አባላት ከሰበር በፊት ላሉ ጉዳዮች የፌዴራልና የክልል ጉዳይ እያሉ ከከፋፈሉ በኋላ የፌዴራሉን የሰበር ስልጣን የሚያመለክቱ ግን  ማንኛውንም የመጨረሻ ውሳኔ የሚለውን ሐረግ መጠቀማቸው  የክልሉንም ሆነ የፌዴራሉን ጉዳይ የመጨረሻ ውሳኔ በፌዴራሉ ሰበር ሰሚ አካል እንዲታይ ስለፈለጉ ነው የሚል ሐሳብ አስቀምጧል፡፡ ለዚህም በአንቀፅ 80(3) የተቀመጠው ልዩ ሁኔታ አንቀፅ 80(1 እና 2) የተቀመጡትን ሐሳቦችን በማስቀረት ልዩ ጉዳዩን ተግባራዊ ለማድረግ የተቀመጠ ከመሆኑ አንፃር የጉባኤ አባላቱን ሐሳብ ለማጠናከር የሚረዳ ይሆናል፡፡ ነገር ግን አሁንም በአንቀፅ 80(3(ለ)) መልሶ ለክልሎች ልዩ መብትስ መስጠቱ ከምን አንፃር ነው የሚለው በግልፅ ያልተመለሰ/ ያልታየ ጉዳይ ነው፡፡

ስለዚህ በአንቀፅ 80(3(ሀ)) ላይ ያለውን ብዥታ ግልፅ ለማድረግ ህጉ ማናቸውንም የመጨረሻ ውሳኔ ብሎ ያስቀመጠውና በአንቀፅ 80(3(ለ)) ለክልል ስልጣን የሰጠውን  ድንጋጌ ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል ከሚለው ጋር አጣምሮ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም የህገምግስቱን ድንጋጌ ተከትሎ  የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ 25/88 የተዘጋጀ ሲሆን አዋጅ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አደረጃጀት፣ ስልጣንና ሌሎች ልዩ ልዩ ጉዳዮች ያካትታል፡፡ ከያዝነው ጉዳይ አንፃር በዚሁ አዋጅ አንቀፅ 10 ስር የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ስልጣን ተዘርዝሮ ይገኛል፡፡ ስሆነም ይህን የአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀፅ 10 ከህገ መንግስቱ አንቀፅ 80(3(ሀ)) ጋር አጣምሮ ማንበብ ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም በአዋጁ አንቀፅ 10

+        በፌዴራል ከፍተኛፍርድቤትበይግባኝአይቶየመጨረሻውሳኔየሰጠባቸውንጉዳዮች፣

+        የፌዴራልጠቅላይፍርድቤትመደበኛችሎትየመጨረሻውሳኔየሰጠባቸውንጉዳዮች እና

+        የክልልጠቅላይፍርድቤትመደበኛችሎትወይምበይግባኝአይቶየመጨረሻውሳኔየሰጠባቸውንጉዳዮች

መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለባቸው ከሆነ  የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር የማየት ስልጣን ያለው መሆኑን ያስረዳል፡፡

ስለዚህ የህገ መንግስቱን አንቀፅ 80(3(ሀ)) ከአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀፅ 10 አንፃር ሲታይ በህገ መንግስቱ  ማናቸውንም የመጨረሻ ውሳኔ የሚለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸውን ጉዳዮች፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መደበኛ ችሎት የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸውን ጉዳዮችና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች መደበኛ ችሎት ወይም በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸውን ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ላይ  ሰበር ልዩ ስርዓት እንጂ የይግባኝ ስርዓት ባለመሆኑና በልዩ ሁኔታ ብቻ የሚፈቀድ የክርክር ስርዓት በመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር እነዚህን ጉዳዮች ማየት የሚችለው  ፍርድ ቤቶቹ አንድም በመደበኛ ችሎት አልያም በይግባኝ አይተው የመጨረሻ ውሳኔ በሰጡባቸው ጉዳዮች ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ በህገ መንግስቱ የተቀመጠው አንቀፅ 80(3(ሀ)) የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሰረታዊ የህግ ስህተት አለበት የሚለውን ማናቸውንም የመጨረሻ ውሳኔ በሰበር የሚያየው በሰበር ከታዩ ጉዳዮች መለስ ያሉትን ብቻ መሆኑን ከዚህ እንረዳለን፡፡

በሌላ በኩል  ደግሞ የህገ መንግስቱ አንቀፅ 80(3(ለ)) ከዚሁ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 3 (ሀ) ጋር በልዩነት የተቀመጠ ነው ሲባል ህገ መንግስቱ የፌዴራልንም ሆነ የክልልን ጉዳይ በሰበር ጠቅልሎ የማየት ስልጣን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለመስጠት ቢፈልግ ኖሮ ንዑስ አንቀፅ ሁለትን ማካተት ባላስፈለገ ነበር፡፡ ህገ መንግስቱ አንቀፅ 80(3(ለ)) ሲያስቀምጥ አንድም ክልሎች በራሳቸው ጉዳይ ላይ መሰረታዊ የህግ ስህተት ሲፈፀም በሰበር እንዲያዩ ስልጣን ለመስጠት ሲሆን በሌላ በኩል ክልሎች በሰበር የራሳቸውን ጉዳይ እንዲያዩ ለማድረግና ይህ ባልሆነ ጊዜ ግን የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲያይ ለማስቻል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አንድ ማጠናከሪያ  የሚሆነው ጉዳይ  በአዋጅ ቁጥር 25/88 ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሎች ጉዳይ  የማየት ስልጣን በግልፅ የተሰጠው  ክልሉ በመደበኛ ችሎት ወይም በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ በሰጠበት ጉዳይ እንጂ ክልሉ በሰበር ያየውን ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለዚህ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት  በክልል ደረጃ በሰበር የታዩትን  ጉዳዮች በተመለከተ  ስልጣን እንደሌለው መረዳት ይቻላል፡፡

ስለዚህ በዝርዝር ህግ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የክልል  ሰበር ሰሚ ችሎት  የመጨረሻ ውሳኔ በሰጠው ጉዳይ ላይ   የማየት ስልጣን ይኖረዋል ተብሎ በግልፅ እስካልተሰጠ ድረስ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ሰበር ተፈቅዷል ለማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህ የህገ መንግስቱ አንቀፅ 80(3) በተለየ ሁኔታ መተርጎም ያለበት ሲሆን በተለይም በአንቀፅ 80(3(ሀ)) ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማንኛውን የፍርድ ውሳኔ በሰበር የማየት ስልጣን በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጠ ውሳኔን እንደማያካትት ግንዛቤ ሊወሰድና ማንኛውንም የፍርድ ውሳኔ የሚለው ከሰበር በፊት ያሉ በመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ስልጣንንና በይግባኝ የታዩትን ብቻ የሚመለከት መሆኑ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ከህገ መንግስቱ አንቀፅ 80(3(ሀ)) አንፃር ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል የሚለው አገላለፅ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሓላፊነትን በዝርዝር ህግ ከመገደብ የሚከለክል አይደለም፤ የሰበሩ ስልጣንም ቢገደብ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚጋጭ ነገር አይኖረውም፡፡

4. ለክልል መንግስታት በተሰጡ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን

ከላይ በዝርዝር ለመግለፅ እንደተሞከረው የኢትዮጵያ የመንግስትን አወቃቀር በፌዴራልና በክልል ሲደረግ ክልሎች በሶስቱ የመንግስት የስልጣን ክፍፍሎች ማለትም በህግ አውጭው፣ በህግ አስፈፃሚው እና  በህግ ተርጓሚው መካከል መሰረታዊ ልዩነት ሳይደርግ እንደየስራው ተጨባጭ ሁኔታ የስልጣን ክፍፍል አድርጓል፡፡ ስለሆነም በዚህ ፅሁፍ ከተያዘው ጉዳይ አንፃር ህገ መንግስቱ በፌዴራልና በክልል የዳኝነት ስርዓቱን እንዳዋቀረና የፌዴራልና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች በራሳቸው የስልጣን ክልል የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጡ  አንቀፅ 80(1 እና 2) ደንግጓል፡፡  ስለሆነም በፌዴራልና ክልል እንደሚገኙት የህግ አውጭና የህግ አስፈፃሚ አካላት የዳኝነት ስርዓቱም ወጥነትና በስልጣን ክፍፍል ላይ የተመሰረተ መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡ የፌዴራል የህግ አውጪ አካል በክልል ጉዳይ ላይ ህግ የማውጣት ሰልጣን እንደሌለው ሁሉ የህግ ተርጓሚው አካል አወቃቀርም እንደህግ አውጭው እንደሚሆን ይታመናል፡፡ ነገር ግን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ስልጣን ከዚህ በተቃራኒ ሁኔታ በተወሰነ መልኩ የዳኝነት ስርዓቱ ማዕከላዊ የዳኝነት ስርዓት ያለው አስመስሎታል፡፡ ስለዚህ በዚህ ላይ የሚነሳው ዋነኛው ጉዳይ ክልሎች በህገ መንግስቱ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ የራሳቸውን ህግ እንዲያወጡ ከሚሰጠው ስልጣን አንፃር የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠቱ ሃላፊነት የማን ይሆናል የሚለው ነው፡፡

በህገ መንግስቱ አንቀፅ 52(1) ለፌዴራሉ መንግስት በተለይ ወይም ለፌዴራል መንግስትና ለክልሎች በጋራ በግልፅ ያልተሰጠ ስልጣን የክልል ስልጣን ይሆናል በሚል ተቀምጧል፡፡ በሌላ በኩል በህገ መንግስቱ አንቀፅ 55 ስር ያልተካተቱ እንደ ቤተሰብ ህግ ያሉና በአንቀፅ 55(5) መሰረት በፌዴራሉ መንግስት የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ባልተሸፈኑ ጉዳዮ ላይ ክልሎች ህግ የማውጣት ሰልጣን እንዳላቸው ተቀምቷል፡፡ ከዚህ አንፃር በአንድ በኩል ህግ የማውጣት ስልጣንን ለክልሎች በህገ መንግስት ከተሰጠ በኋላና የፌዴራል መንግስቱ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 50(8) መሰረት የክልል ህግን የማክበር ሃላፊነት ያለበት መሆኑን ከደነገገ በኋላ በሌላ በኩል የክልል ፍርድ ቤቶች ውሳኔን በሰበር የማየት ስልጣን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መስጠት እርስ በርሱ አይጣረስም ወይ የሚል ጥያቄ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር ለክልሎች በተሰጡ ጉዳዮች ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር ሰሚ ስልጣኑ ማየቱ ተገቢነቱ ከምን አንፃር እንደሆነ ግልፅ ባይሆንም  የህገ መንግስቱን አንቀፅ 80(3(ሀ)) እንደ መነሻ መከራከሪያ ነጥብ ይቀርባል፡፡ ነገር ግን በዚህ አንቀፅ ላይ ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል የሚለው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው፡፡

እዚህ ላይ የህገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን በቃለ ጉባኤነት በተያዘው ነጥብ ላይ ጉዳዩ የክልል ስልጣን ሆኖ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የታየ ቢሆንም የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በሰበር የማየት ስልጣን እንዳለው ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ እዚህ ላይ የኮሚሽኑ በህጎች ትርጓሜ ላይ መሰረታዊ የሆነ፣ የሚያግባባና ተመሳሳይነት ያለው ተፈፃሚነት እንዲኖራቸው ከማሰብ አንፃር የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን የሰበር ስልጣን ካስቀመጠ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 80 (3(ለ))ለክልሎች ተመልሶ በልዩ መፈቀዱ ከምን መነሻ ምክንያት እንደሆነ የሚያመለክት ነገር የለውም፡፡ ተፈቀደ ቢባል እንኳ ዜጎችን ላልተገባ ተጨማሪ ወጭ፣ የጊዜ ና ሌሎችም እንግልቶች እንደሚዳርግ አቶ መሐሪ ረዳኢ የፌዴራል ሰበርና የሰበር ሰበር የስልጣን ምንጭን ገልጠን ብናየው በሚለው ፅሁፋቸው ውስጥ አስቀምጠው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ሰበር ስልጣን በትርጓሜ ሊገደብ እንደሚገባ ያስቀምጣል፡፡

ጉዳዩ ከህገ መንግስቱ አንቀፅ 80(3) እና ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀፅ 3 እና አንቀፅ 10 አንፃር ሲታይ ሁለት ሐሳቦች ይንፀባረቁበታል፡፡ እነዚህም፡-

 

1.       የህገ መንግስቱ አንቀፅ 80(3(ሀ)) እና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀፅ 10 (3) በክልል ጉዳይ ላይ ጭምር የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር ጉዳዮችን  የማየት ስልጣን አለው የሚል ነው፡፡ ለዚህም ህገ መንግስቱ በአንቀፅ 80(3(ሀ)) ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል ብሎ ካስቀመጠው አንፃር  የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ አንዱ ሲሆን በዚህ አዋጅ አንቀፅ 10(3)  የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበትን በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መደበኛ ችሎት ወይም ፍርድ ቤቱ በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸውን  ጉዳዮችን ( ጉዳዩ የሚለው የወንጀል ጉዳዮችም የሚያጠቃልል ይሆናል) በሰበር የማየት ስልጣን አለው የሚለው ነው፡፡ እዚህ ላይ “የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመደበኛ ችሎት ወይም በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠበትን…” የሚለው አገላለፅ ለክልሉ በውክልና የተሰጡ ጉዳዮችን ብቻ ሳይሆን የክልሉንም መሰረታዊ ስልጣን ይጨምራል የሚል ነው፡፡ ሆኖም ይህ ሐሳብ በግልፅ እስካልተቀመጠ ድረስ የክልሎችንም የዳኝነት ስልጣን ጭምር ህጉ እያሰበ ነው ማለት ተገቢነት የለውም፡፡

2.      ሌላኛው ሐሳብ የህገ መንግስቱ አንቀፅ 80 (3(ሀ)) ከዚሁ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 3(ለ) እና ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀፅ  3 እና አንቀፅ 10(3) አንፃር ሊታይ ይገባል የሚል ነው፡፡ አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀፅ 3 የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን ስልጣን በመወሰን ረገድ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ህገ መንግስቱን፣ የፌዴራል መንግስቱን ህጎች፣ አለም አቀፍ ስምምነቶች መሰረት በማድረግ በሚነሱ ጉዳዮች፣ በፌዴራል መንግስቱ ህግ ተገልፀው በተወሰኑ ባለጉዳዮች እና በፌዴራል መንግስቱ ህገ መንግስት ወይም በህግ በተገለፁ ቦታዎች ላይ የዳኝነት ስልጣን ይኖራቸዋል በሚል ተቀምጧል፡፡ ይህ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የወል የዳኝነት ሰልጣን አንቀፅ 10 ከተቀመጠው አንፃር መርህ ይሆናል ተብሎ ካተወሰደና አንቀፅ 10 ልዩ ህግ (exception) ነው እስካልተባለ ድረስ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የክልል ጉዳዮች የማየት ሰልጣን እንዳላቸው የሚያመለክት ዝርዝር ህግ የለም፡፡ በተለይም የአዋጁ አንቀፅ 3 ከአንቀፅ 10(3) ጋር በጣምራ ሲነበብ የአዋጁ አንቀፅ 10(3) ለክልል በውክልና የተሰጡ ጉዳዮችን እንጂ የክልሎችን የመጀመሪያ የዳኝነት ስልጣን እንደማያካትት መገንዘብ ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ከአዋጁ አንቀፅ 3(3) እና ከህገ መንግስቱ አንቀፅ 52(1) አንፃር በግልፅ ለፌዴራል መንግስቱ (የፌዴራል የዳኝነት አካል አንዱ የመንግስት ክንፍ እንደሆነ ግልፅ ነው) ያልተሰጠ ስልጣን የክልሎች ብቸኛ ስልጣን እንጂ የፌዴራሉም ስልጣን ነው ተብሎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ ስለዚህ ከህገ መንግስቱ መንፈስ አንፃር የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመደበኛ ችሎት ወይም በይግባኝ አይቶ ውሳኔ በሰጠባቸው ጉዳዮች መሰረታዊ የህግ ስህተት ካለ በሰበር የማየት ስልጣን አለው የሚለው አገላለፅ በግልፅ የክልል የዳኝነት አካል ስልጣን የሆኑትን ጭምር ያካትታል ተብሎ በዝርዝር ህግ እስካልተገለፀ ድረስ በውክልና ከሰጠው ስልጣን ውጭ የክልልን መሰረታዊና ክልላዊ የዳኝነት ስልጣንን ይጨምራል ብሎ መውሰድ ተገቢ አይደለም፤ የህገ መንግስቱ የትርጓሜስና የአንቀፅ 52(1) መንፈስ ይህንን አያመለክትም፡፡ ስለዚህ የህገ መንግስቱ አንቀፅ 80(3(ሀ)) ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሰጠው ማናቸውንም የመጨረሻ ውሳኔ በሰበር የማየት ስልጣን በዝርዝር ህግ ይወሰናል ሲል አዋጅ ቁጥር 25/88 እና ሌሎች ህጎች ታሳቢ ያደረገ ሆኖ ከክልሎች መሰረታዊና ክልላዊ የዳኝነት ስልጣን ውጭ ያሉት ላይ ብቻ ተፈፃሚ እንደሚሆን ከመገደብ እንደማይከለክልና መንፈሱም በዚሁ መልክ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡

 

ሌላው የሚነሳው ነጥብ የህገ መንግስቱ መግቢያ ላይ የተቀመጠው የቃል ኪዳን  ሐሳብና የክልሎች ሁለንተናዊ የራስን እድል በራስ የመወሰን ስልጣንን አጣጥሞ የማስኬድ ጉዳይ ሲሆን  ምንም እንኳ ህገ መንግስቱ አንድ የኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ መፍጠርን ግብ አድርጎ  ያስቀመጠ ቢሆንም በአንፃሩ ልዩነትን በአንድነት ውስጥ አኳቶ የሚይዝ ከመሆኑ የተነሳ የህጎችን ወጥነትና አገራዊ ትርጓሜ እንዲኖራቸው ማድረግ ተፈላጊ ቢሆንም የክልሎችን ክልላዊ የህግ ትርጓሜንና በአንድነት ውስጥ ያለን ማህበራዊና ሌሎች ልዩነቶች አካቶ የያዘ ነው፡፡  ስለዚህ በክልሎች መካከል ሊኖሩ የሚችሉ የተለያዩ ክልላዊ አስተሳሰቦችና አሰራሮችን ማከበር ተገቢነት ያለውና የህገ መንግስቱንም አንቀፅ 50(8) መከበር ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም ክልሎች በራሳቸው ጉዳይ ላይ የራሳቸውን የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጡ ማድረግ የፌዴራሉ መንግስት ለክልሎች የተሰጡ ስልጣኖችን የሚያከብርበት አንዱ ማሳያ ስለሆነ ከዚህ አንቀፅና አስተሳሰብ በተቃራኒ የህገ መንግስቱን አንቀፅ 80(3(ሀ)) መንፈስ ለጥጦ መተርጎም ተገቢነት የሌለውና ለክልሎች በብቸኝነት የሰጠውን ስልጣን የሚሸረሽር ይሆናል፡፡

 

ከዚህም በተጨማሪ ህገ መንግስቱ አንድ ወጥ የሆነ አገራዊ የህግ ትርጉምና አስተሳሰብ እንዲኖር ቢፈለግ ኖሮ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሁሉም ጉዳዮች ላይ በሰበር የማየት ስልጣን እንዳለው በግልፅ አስቀምጦ አንቀፅ 80(3(ለ))ባላስቀመጠ ነበር፡፡ ህገ መንግስቱ ከጠቅላላ መርሁ ልዩ ህግ ማስፈሩና  ከፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስልጣን በተጨማሪ ልዩ የሆነ የሰበር ስልጣን ለክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መስጠቱ የክልሎችን የዳኝነት አካል ህገ መንግስታዊ አወቃቀርና የመወሰን ስልጣን በአግባቡ ለማስከበር እንጂ የክልሉ ምክር ቤት የሚያወጣቸውን ህጎች ተገቢውን ትርጉም ሰጥቶ የመጨረሻ ውሳኔ እንዳይሰጥ ወይም ቢሰጥም መልሶ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን ለፌዴራሉ መንግስት (ማለትም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት) ለመስጠት ታሳቢ ያደረገ አይመስልም፡፡ ስለዚህ የህገ መንግስቱ ትርጓሜ በአንድ በኩል ከክልሎች በራስ የመወሰን ስልጣን፣ በሌላ በኩል ከጋራ መከባበርና ትብብር ጋር የሚያያዝ በመሆኑ በአንቀፅ 80(3(ሀ፣ለ)) ስር የተቀመጠው በዝርዝር ህግ ስልጣንን የመገደብ ሂደት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን በክልል ጉዳይ ላይ በሰበር ጉዳዮች የማየት ስልጣን እደሌለው በግልፅ ከመገደብ የሚከለክል አይደለም፡፡ ስለሆነም በዝርዝር ህግ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ስልጣን አገራዊ ተፈፃሚነት በሚኖራቸው ህጎች ላይ በሚነሱ ክርክሮች፣ ለክልል በውክልና በተሰጡ ጉዳዮችና ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች በመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ስልጣን ወይም በይግባኝ እንዲያዩ በተሰጧቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ እንዲወሰን ማድረግ ይቻላል፡፡

5. ከህገ መንግስቱ አንቀፅ 80(3) መሰረታዊ ሐሳብ አንጻር  ከሚያስፈልጉ የዝርዝር ህጎች እና በስነ ስርዓት ህጉ የሰበር ስልጣን ሊስተናገድበት የሚገባው ሂደት

ህገ መንግስቱ የፌዴራልንና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶችን የሰበር ስልጣን ሲያስቀምጥ በተወሰነ መልኩ ግልፅ ሆነ የህግ አሰፋፈር ስርዓትን የተከተለ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል በአንቀፅ 80(3(ሀ፤ለ)) የተቀመጠው የዝርዝር ህግ ድንጋጌ በተለያየ መልክ ሊታይ የሚችል ሲሆን የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን ማቋቋሚያና ሌሎች የፍርድ ቤቱን ስልጣን ለማሻሻል የወጡ አዋጆች በዝርዝር ህግነት ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ ሆኖም የህገ መንግስቱ “ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል” የሚለው አገላለፅ የፍርድ ቤቶቹን የሰበር ስልጣን ምን ጉዳዮች ላይ እንደሆነና  እንዴት መቀመጥ እንዳለባቸው የሚደነግጉ ዝርዝር የህግ ማዕቀፎች ታሳቢ የሚያደርግ ከመሆኑ አንፃር የወንጀል ስነ ስርዓት አንዱ የህግ ማዕቀፍ በማድረግ በወንጀል ጉዳዮች ላይ የሰበር ስልጣንን መለየት ይቻላል፡፡

ስለሆነም ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል የሚለው አገላለፅን በመከተል የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበርና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የሰበር ስልጣን ከወንጀል ጉዳዮ አንፃር እንዴት መካከት አለባቸው የሚለውን በተመለከተ የሚከተሉት የመፍትሔ ሀሳቦችን መሰንዘር ይቻላል፡፡ እነዚህም

1.       የህገ መንግስቱ አንቀፅ 80(3(ሀ)) ሊተረጎም የሚገባውና የመጨረሻ  ውሳኔ የሚለው አገላለፅ ከሰበር መለስ ያለውን የፍርድ ውሳኔ እንደሆነ ተደርጎና የበመጀመሪያ ደረጃ  የዳኝነት ስልጣን ወይም በይግባኝ የታዩትን ብቻ መሆኑን የሚያመላክት ግልፅ የህግ ትርጓሜ እንዲኖረው ማስቻል፣

2.      ክልሎች የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን ስልጣን በውክልና የወሰዱት በመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ሰልጣኑንና የይግባኝ ስልጣኑም መሆኑን ህገ መንግስቱ በአንቀፅ 80 (2፣4፣5፣6) በግልፅ የሚደነግግ በመሆኑ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሚታዩ ጉዳዮች የክልል ፍርድ ቤቶች በሰበር የማየት ስልጣን እንደሌላቸው በግልፅ መቀመጥ ይኖርበታል፣

3.      ክልሎች ውሳኔ በሰጧቸው የወንጀል ጉዳዮች ውሳኔዎች ላይ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን በሰበር ካየው የፌዴራሉ ሰበር ሰሚ ችሎት መልሶ በሰበር እንዳያይ በግልፅ ቢደነገግና በሌላ ሁኔታ ግን በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩ ካልታዬ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር የሚያይበት ልዩ ድንጋጌ ቢቀመጥ፣

4.      ክልሎች ህግ እንዲያወጡ በተፈቀደበት ጉዳይ ላይ ለሚነሱ የህግ ክርክሮች የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት  በሰበር  ጉዳዩን የማየት ስልጣን እንዳይኖረው በግልፅ ቢደነገግና የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ኃላፊነትም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሆኑና የሰበሩንም ጉዳይ በሰበር ሰሚ  ችሎቱ የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን እንዳለው ቢቀመጥ ተገቢ ይሆናል፡፡

6. ማጠቃለያ

የኢትዮጵያ የህግ ስርዓት ምንም እንኳን በተለያዩ የመንግስት የአወቃቀርና አስተዳደር ስርዓቶች የተለያየ መልክ እየያዘ ቢመጣም በአሁኑ ሰዓት የጋራ መግባባት ሊያስደርስ የሚያስችል ደረጃ ላይ መድረሱ ግልፅ ነው፡፡ በዚህ የፍትህ ግንባታ ሂደት የተለያዩ አካላትን ስልጣንና ተግባር ህገ መንግስትን መሰረት በማድረግ መለየትና በህግ ከፋፍሎ መስጠት ተገቢና አስፈላጊም ነው፡፡ ስለሆነም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በክልል ፍርድ ቤቶች ላይ የሚኖራቸው ስልጣን በህገ መንግስቱ ክልሎች ካላቸው በራስ የመተዳደር ስልጣን አንፃር ሊቃኝና የህግ ትርጉሞችም ከመንግስት አወቃቀር አንፃር በፌዴራልና በክልል መካከል ከሚኖር የስልጣን ክፍፍል አንፃር መሆን ይኖርበታል፡፡

ስለዚህ ህገ መንግስቱ በፌዴራልና በክልሎች መካከል ያለውን የዳኝነት የስልጣን ክፍፍል ልክ እንደ አስፈፃሚ አካሉና እንደ ህግ አውጭው ስልጣንና ተግባር ክፍፍል በግልፅ ሊያስቀምጥ የሚገባው ሲሆን የፌዴራሉ ዳኝነት የክልሎችን የዳኝነት ስልጣን ሊያከብርና እውቅና ሊሰጥ ይገባል፡፡

በአጠቃላይ በሰበር ስልጣን ላይ ያለው የህግ አተረጓጎም ስርዓት ክልሎችና የፌዴራል መንግስቱ ካላቸው የትብብር ማዕቀፍ ሳይወጣ ከፌዴራላዊ ስርዓቱ አንፃር በግልፅ ሊቀመጥ ይገባል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Legal Empowerment of the Poor
Responses to Homelessness and its Impacts in Ethio...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 13 December 2024