ፍርድን እንደገና መመርመር ማለት ምን ማለት ነው?
ፍርድን እንደገና መመርመር (Review of Judgments) ማለት በአንድ በተወሰነ ጉዳይ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች የሰጡት ፍርድ /ውሳኔ/ የፍርድ ባለዕዳውን ወይም የፍርድ ባለመብቱን ቅር ሲያሰኘው ወይም አጥጋቢ ሆኖ ሳያገኘው ሲቀር ይህ የተሰጠው ፍርድ ዳግመኛ ይታይለት ዘንድ ሊጠቀምበት የሚችልበት ጠቃሚ የሥነ-ሥርዓት ሕግ አካል ነው፡፡
ፍርዶች ዳግመኛ ለምን ይታያሉ?
የፍርድ ቤቶች ውሳኔ በተለያየ መንገድ የዜጐችን የአኗኗር ዘይቤ ጥሩም መጥፎም የማድረግ እድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ይህም ማለት ፍርድ ቤቶች ከሶሶቱ የመንግስት አካላቶች መካከል የዜጐች መብትና ነፃነት እንዲከበር እንዲሁም ፍትህን ከማስፈን አኳያ ያላቸው አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ጉዳዬችን የሚያጤኑበት ወይም የሚመረምሩበት መንገድ እጅግ ጥንቃቄ የተሞላበት እንዲሁም በሕግና በሥርአት የተደገፈ መሆን አንዳለበት ይታመናል፡፡ ከተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ፍርድ ቤቶች የሚሰጡት ውሳኔ ስህተት ሊሆን ወይም ደግሞ የሕጐችን አጠቃላይ መንፈስ ያልተከተለ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ለዚህም በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን በይግባኝ ፍርድ ቤቶች እና በሰበር ሰሚ ችሎቶች ተከማችተው የሚገኙትን የጉዳዬች ብዛት መመልከት በቂ ነው፡፡ ተከራካሪ ወገኖች ልክ እንደማንኛውም ዜጋ ፍትህ የማግኘት ሕገ- መንግስታዊ መብት ባለቤት በመሆናቸው ትክክል አይደለም ብለው የሚያስቡትን ፍርድ የተሻለ ፍትህ እናገኝበታለን ብለው ወደሚያስቡት የፍትህ ተቋም ጉዳያቸው ዳግመኛ እንዲታይላቸው መጠየቅ ይችላሉ መንግስትም ይህ የዜጐች የተሻለ ፍትህ የማግኘት መብት አንዲከበር ሊያግዝ የሚችል ተቋማዊ መዋቅር መዘርጋት ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአንድ ሀገር የሕግ ሥርአት (legal system) ውስጥ ወጥ (uniform) የሆነ የሕግ አተረጓጎም እንዲኖር ለማስቻል የፍርድ ቤቶችን ውሳኔ እንደገና መመርመር የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ መዘርጋት አስፈላጊ ነው፡፡