Font size: +
7 minutes reading time (1353 words)

ፍርዶች ዳግመኛ ሰለሚታዩባቸው መንገዶች (Review of Judgments)

ፍርድን እንደገና መመርመር ማለት ምን ማለት ነው?

ፍርድን እንደገና መመርመር (Review of Judgments) ማለት በአንድ በተወሰነ ጉዳይ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች የሰጡት ፍርድ /ውሳኔ/ የፍርድ ባለዕዳውን ወይም የፍርድ ባለመብቱን ቅር ሲያሰኘው ወይም አጥጋቢ ሆኖ ሳያገኘው ሲቀር ይህ የተሰጠው ፍርድ ዳግመኛ ይታይለት ዘንድ ሊጠቀምበት የሚችልበት ጠቃሚ የሥነ-ሥርዓት ሕግ አካል ነው፡፡

ፍርዶች ዳግመኛ ለምን ይታያሉ?

የፍርድ ቤቶች ውሳኔ በተለያየ መንገድ የዜጐችን የአኗኗር ዘይቤ ጥሩም መጥፎም የማድረግ እድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ይህም ማለት ፍርድ ቤቶች ከሶሶቱ የመንግስት አካላቶች መካከል የዜጐች መብትና ነፃነት እንዲከበር እንዲሁም ፍትህን ከማስፈን አኳያ ያላቸው አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ጉዳዬችን የሚያጤኑበት ወይም የሚመረምሩበት መንገድ እጅግ ጥንቃቄ የተሞላበት እንዲሁም በሕግና በሥርአት የተደገፈ መሆን አንዳለበት ይታመናል፡፡ ከተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ፍርድ ቤቶች የሚሰጡት ውሳኔ ስህተት ሊሆን ወይም ደግሞ የሕጐችን አጠቃላይ መንፈስ ያልተከተለ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ለዚህም በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን በይግባኝ ፍርድ ቤቶች እና በሰበር ሰሚ ችሎቶች ተከማችተው የሚገኙትን የጉዳዬች ብዛት መመልከት በቂ ነው፡፡ ተከራካሪ ወገኖች ልክ እንደማንኛውም ዜጋ ፍትህ የማግኘት ሕገ- መንግስታዊ መብት ባለቤት በመሆናቸው ትክክል አይደለም ብለው የሚያስቡትን ፍርድ የተሻለ ፍትህ እናገኝበታለን ብለው ወደሚያስቡት የፍትህ ተቋም ጉዳያቸው ዳግመኛ እንዲታይላቸው መጠየቅ ይችላሉ መንግስትም ይህ የዜጐች የተሻለ ፍትህ የማግኘት መብት አንዲከበር ሊያግዝ የሚችል ተቋማዊ መዋቅር መዘርጋት ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአንድ ሀገር የሕግ ሥርአት (legal system) ውስጥ ወጥ (uniform) የሆነ የሕግ አተረጓጎም እንዲኖር ለማስቻል የፍርድ ቤቶችን ውሳኔ እንደገና መመርመር የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ መዘርጋት አስፈላጊ ነው፡፡

የውጭ ሀገራት ተሞክሮ

በተለያዩ የአለማችን ሀገሮች የሚገኙ ፍርድ ቤቶች አወቃቀራቸውና አደረጃጀታቸው ጉዳዬች በአንድ ፍርድ ቤት መታየት ጀምረው በተለያዩ የፍርድ ቤት ደረጃዎች በይግባኝና በሌሎች መሰል መንገዶች ዳግመኛ መታየት የሚችሉበትን መንገድ ታሳቢ ያደረጉ ናቸው፡፡ ለአብነት ያክል የአሜሪካን ሀገር የፍርድ ቤቶች አወቃቀር ብንመለከት በፌዴራልና በክልል ደረጃ ከመቋቋማቸው (Dual court structure) ባሻገር በእያንዳንዱ መንግስት ሥር ጉዳዬች ዳግመኛ የሚታዩባቸው ሁኔታ ይኖራል፡፡ ለምሳሌ፡- በአንድ የግዛት ክልል ውስጥ በታችኛው ፍርድ ቤት መታየት የጀመረ ጉዳይ በግዛቱ የይግባኝ ፍርድ ቤት ከታየ በኋላ እስከ ፌ/ጠ/ፍርድ ቤት ድረስ የሚታይበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል፡፡

በተመሳሳይ በፈረንሳይ ሀገር ዜጐች የፍርድ ቤቶችን ውሳኔ በመቃወም ጉዳያቸው ዳግመኛ በሌሎች ፍርድ ቤቶች ይታይላቸው ዘንድ ከይግባኝ ፍርድ ቤቶች በተጨማሪ የሰበር ሰሚ ችሎት (cassation division) ተቋቁመዋል፡፡ በሌሎች የምዕራብ አውሮፓ ልክ እንደ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ስፔን እና ሌሎች ሀገራት ተመሳሳይ የሆነ የፍርድ ቤቶች ከአደረጃጀትን በመቅረፅ ባለጉዳዬችን ቅር ያሰኙ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች ዳግመኛ የሚታዩበትን መንገድ መፍጠር ችለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ፍርዶች ዳግመኛ ስለሚታዩባቸው መንገዶች

በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት ውስጥ የተካተቱና በአሁኑ ሰዓት በሰፊው በተግባር ላይ የምንጠቀምባቸው ዳግመኛ ፍርድ የመመርመሪያ መንገዶች ሶስት ሲሆኑ እነርሱም፡-

ጉዳዮን በሚመለከተው ፍርድ ቤት (Review by a court of rendition)

የይግባኝ ፍርድ ቤቶች (Appellate courts)  

የሰበር ሰሚ ችሎት (Cassasion Division) ናቸው፡፡

ጉዳዩን በሚመለከተው ፍርድ ቤት እንደገና ስለሚታይበት ሁኔታ

ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤት ምንም እንኳን ውሳኔ አስተላልፎ መዝገቡን የዘጋው ቢሆንም ይህንኑ ጉዳይ ዳግመኛ እንዲመለከተው የሚያስገድዱ እጅግ በጣም መሠረታዊ የሆኑ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕጉ በጥልቀትና በሰፊው የተቀመጡ በመሆናቸው አንድ በአንድ ለማየት እንሞክራለን፡፡

የሥነ ሥርዓት መዛነፍ (Procedural irregularities)

ይህ ማለት የፍርድ ሥርዓቱ በሚከናወንበት ወቅት ከፍርድ አካሄድ ደንብ ውጭ የሆነ ተግባር ሲፈፀም ዳኞች ባለማስተዋል ወይም በሌላ ምክንያት በማለፍ ፍርድ የሚሰጡበት አጋጣሚ ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የፍ/ሥ/ሥ/ሕግ በሥነ ሥርዓት መፃነፍ ምክንያት ጉዳዩ እንደገና የሚታይበትን ሁኔታ የሚደነግጉት የሕግ ክፍሎች ከአንቀፅ 207-212 በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡ ፍርዱን የሰጠው ፍርድ ቤት የሥነ-ሥርአት መዛነፍ መፈጠሩን ከተረዳና የሥነ-ሥርአት መዛነፉ የጉዳዮን ፍሰት ወደ ሌላኛው ተከራካሪ ወገን በእጅጉ ሊለውጥ የሚችል ሆኖ ከተገኘ በራሱ ተነሳሽነት ወይም በአንደኛው ተከራካሪ ወገን ጠያቂነት ይህ ከሥነ- ሥርአት ውጭ የቀረበው ነገር በከፊል ወይም በሙሉ እንዲሰረዝ፣ እንዲሻሻለ ትዕዛዝ መስጠት ይችላል /አንቀጽ 207 ይመልከቱ/፡፡  የስነ-ሥርአት ጉድለቱ የተከሰተው ፍርድ ከተሰጠ በኋላ ከሆነና ይህ ጉድለት የተሰጠውን ፍርድ ሊለውጥ የሚችል ከሆነ ፍ/ቤቱ የሰጠውን ፍርድ የመሰረዝ ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡

1.2. የአዲስ ማስረጃ መገኘት (Newly Discovered Evidences)

ፍርድ የተሰጠባቸው ጉዳዬች ዳግመኛ ከሚታዩባቸው ዋነኛ ምክንያቶች መካከል በአዲስ መልክ የሚገኙ ማስረጃዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁ. 6 መሠረት አንድ ሰው አዲስ በተገኙ ማስረጃዎች ምክንያት ፍርድ የሰጠውን ፍርድ ቤት ጉዳዩን እንደገና እንዲያየው ለማመልከት የሚከተሉት መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች በአንድነት ሊገኙ ያስፈልጋል፡፡ 

ሀ/ ማስረጃው የተገኘው ፍርድ ከተሰጠ በኋላ መሆን አለበት

ለ/ አዲስ የተገኘው ማስረጃ ውሳኔው ላይ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ መሆን አለበት፡፡

ሐ/ የተገኘው ማስረጃ የመጨረሻው ፍርድ የተሰጠው በሐሰተኛ ሰነድ፣ በሐሰተኛ ምስክርነት ወይም መደለያን ወይም ወንጀል ጠቀስ የሆነ ተግባርን መሠረት በማድረግ መሆኑን ማስረዳት ሲችል

መ/ አቤት ባዩም ፍርድ ከመስጠቱ በፊት ትጋት አድርጐ ለማወቅ ያለመቻሉን ለማስረዳት የቻለ እንደሆነ

ሠ/ በተሰጠው ፍርድ ላይ ይግባኝ መባል አይኖርበትም         

ረ/ አቤት ባዩ ተገኝቷል የሚለውን አዲስ ማስረጃ ካገኘበት ወይም መኖሩን ካወቀበት ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አቤቱታውን ማቅረብ ሲችል

እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ቅድመ-ሁኔታዎች መገኘት ሲችሉ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 6 መሠረት ጉዳዩ ዳግመኛ የሚታይ ይሆናል፡፡

ስለመቃወም (Opposition)

ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤት ዳግመኛ ፍርዱን እንዲመረምር የሚገደድበት ሶስተኛው ምክንያት የመቃወሚያ ማመልከቻ መቅረብ ነው፡፡ መቃወሚያ ማለት በመደበኛው የፍርድ ክርክር ሂደት ጊዜ አካል ያልነበረ ሶሶተኛ ወገን የተሰጠው ፍርድ የእሱን መብትና ጥቅም የሚነካ ሆኖ ሲያገኘው ወደ ፍርድ ሥርአቱ በመግባት ጉዳዩ እንደገና አንዲታይለት የሚጠይቅበት ሥርአት ነው፡፡ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁ. 358 መሠረት መቃወሚያ ለማቅረብ መሟላት የሚኖርባቸው መሠረታዊ ሁኔታዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

መቃወሚያውን የሚያቀርበው ሰው የክሱ አካል መሆን ይችል የነበረ መሆን አለበት፡፡

በተሰጠው ፍርድ ምክንያት መብትና ጥቅሙ የተነካ መሆን እና

የመቃወሚያ ማመልከቻው የቀረበው ውሳኔው ከመፈፀሙ በፊት መሆን ይጠበቅበታል፡፡

በዋነኛነት የዚህ የሕግ ሥርአት አላማ ፍርድ መሰጠቱን ሳያውቁ መብትና ጥቅማቸው ሊነካባቸው የሚችሉ ሰዎችን እድሉን በመሰጠት በፍርድ ሂደት ውስጥ ተካተው መብታቸውን እንዲያስጠብቁ  ማስቻል ነው፡፡

የይግባኝ አቤቱታ (Appeal)  

የይግባኝ አቤቱታ ማለት በሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ቅር የተሰኘ ሰው ጉዳዩን ለበላይ ፍርድ ቤቶች ወይም ለይግባኝ ፍርድ ቤቶች ፍርዱ እንዲሰረዝለት ወይም እንዲሻሻል የሚጠይቅበት ማመልከቻ ነው፡፡ ማመልከቻው የቀረበለት ይግባኝ ፍርድ ቤት የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ የሕግም ሆነ የፍሬ-ነገር ሥሕተት የተፈፀመበት መሆኑን በመመርመር ፍርዱን የማፅናት፣ የመሻር አና የማሻሻል ሥልጣን ይኖረዋል፡፡ ይግባኝ የማለት መብት የዜጐችን ፍትህ የማግኘት መብት ከማስጠበቅ አንፃር ያለው ፋይዳ ጉልህ በመሆኑ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 20/6/ መሠረት ሕገ-መንግስታዊ እውቅናን ለማግኘት ችሏል፡፡

የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁ. 320 የይግባኝ አቤቱታ ሥለሚፈቀድበት ሁኔታ ይደነግጋል፡፡ በዚህ አንቀፅ መሠረት ይግባኝ እንዲፈቀድ ሶስት መሠረታዊ ቅድመ-ሁኔታዎች እንዲገኙ ያስፈልጋል፡፡

ሀ/ የመጨረሻ ፍርድ መሆን፡- ይህ ማለት ጉዳዩ ገና በበታች ፍርድ ቤት ታይቶ ያላለቀ ከሆነና የመጨረሻ ፍርድ ያልተሰጠበት ከሆነ የይግባኝ አቤቱታ ሊቀርብ አይችልም፡፡

ለ/ በሥር ፍርድ ቤት የሚገኙ መፍትሄዎችን አሟጦ መጠቀም፡- ከላይ በዳሰስናቸው ሶስት ምክንያቶች የተነሳ የሥር ፍርድ ቤት ጉዳዩን እንደገና መመልከት የሚችል ከሆነ የይግባኝ አቤቱታ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡

ለምሳሌ፡- የሥነ-ሥርአት ጉድለት በመገኘቱ ምክንያት የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔውን አንዲሰርዝ መጠይቅ ሲቻል የይግባኝ አቤቱታ ቢቀርብ የይግባኝ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ወደ ስር ፍርድ ቤት መመለስ ይችላል፡፡   

ሐ/ በጊዚያዊ ትዕዛዞች ላይ ይግባኝ አለመፈቀዱ፡- ጊዜያዊ ትዕዛዞች (interlocutory decisions) ማለት የተያዘውን ጉዳይ ለመጨረሻ ጊዜ የማይቋጩ የፍርድ ቤት ግዜያዊ ፍርዶች ናቸው፡፡

ለምሳሌ፡- ቀነ- ቀጠሮ መወሰን፣ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ ተገቢ መስሎ የታየውን ውሳኔ ሲሰጥ እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ስለዚሀ በእነዚህ ጉዳዬች /ፍርዶች/ ላይ ይግባኝ ማለት አይፈቀድም፡፡

ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን ሦስት ሁኔታዎች በማሟላት የይግባኝ አቤቱታውን አንቀፅ 327 በሚያስቀምጣቸው መስፈርቶች መሠረት አዘጋጅቶ ማቅረብ የሚቻል ይሆናል፡፡ ይህም ሲሆን የይግባኝ ፍርድ ቤት ለጉዳዩ ቀነ- ቀጠሮ በመስጠት ጉዳዩን በይግባኝ ደረጃ ይመረምራል፡፡ በዚህም መሠረት የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ጉድለት የሌለበት መሆኑን ከተረዳው መልስ ሰጪውን ሳይጠራ ይግባኙን ዘግቶ አቤት ባዩን ሊያሰናብት ይችላል /አንቀፅ 337ን ይመልከቱ/፡፡ ነገር ግን የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ጉዳዩ ይግባኝ ያስቀርባል ካለ የመጥሪያ ወረቀትና የይግባኝ አቤቱታውን አንድ ላይ በማድረግ ለመልስ ሰጪ  ይልካል፡፡ በዚህ መሠረት መልስ ሰጪ በተባለበት ቀን ሲገኝ /በሌለበት ሊሆን ይችላል/ ጉዳዩ በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት መደበኛ አካሄድ መሠረት ዳግመኛ ይመረመራል፡፡

የሰበር ሰሚ ችሎት (casassion division)

የሰበርን ትርጉም ከቃሉ በመነሳት መረዳት ይቻላል፣ ይኸውም አስቀድሞ የተሰጠ ውሳኔ ወይም ፍርድን መስበርን፣ ማፍረስን፣ መሰረዝን የሚመለከት ነው፡፡ አሁን ባለን አሰራር የሰበር ሥርዓት የመጨረሻ ፍርድ የተሰጠበት ጉዳይ በተለየ ሁኔታ እንደገና ታይቶ የሚታረምበት የዳኝነት ሥርዓት ነው፡፡ በአጠቃላይ የሰበር ሥርዓት ማለት የመጨረሻ ውሳኔ የተሰጠበት ጉዳይ እንደገና ለመጨረሻ ጊዜ የሚታይበት እና እርምት ካሰፈለገው የሚታረምበት የተለየ የዳኝነት ሂደት ነው፡፡ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 80/3/ /ሀ/ እና /ለ/ መሠረት የፌዴራልና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የሰበር ሰሚ ችሎት እንደሚኖራቸው በግልፅ ተደንግጓል፡፡

ሕገ-መንግስቱን ተከትሎ የፌ/ፍርድ ቤቶችን አደረጀጀትና አወቃቀር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀፅ 10 መሠረት የፌ/ጠ/ፍርድ ቤት/ሰ/ሰ/ችሎት የማከተሉትን ጉዳዬች በሰበር የማየት ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡

ሀ/ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸውን ጉዳዬች

ለ/ የፌ/ጠ/ፍርድ ቤት መደበኛ ችሎት የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸውን ጉዳዬች

ሐ/ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መደበኛ ችሎት ወይም በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸውን ጉዳዬች፡፡

በዚህም መሠረት ከተለያዩ አካላት የሚቀርቡትን የሰበር አቤቱታዎች ለመቀበል የሚከተሉት ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት አለባቸው፡፡

መሠረታዊ የሕግ ስህተት መኖር

ውሳኔው የመጨረሻ መሆኑን፣

አቤቱታው የመጨረሻ ውሳኔ በተሰጠ በ90 ቀናት ውስጥ የቀረበ መሆኑን

ለፍትሐብሄር ጉዳዬች የዳኝነት ክፍያ የተፈፀመበት መሆን ወይም በደሃ ደንብ መሠረት የተከፈተ መሆን ናቸው፡፡

ከላይ የጠቀስናቸው አራት መሠረታዊ ቅድመ-ሁኔታዎች መሟላት ሲችሉ ጉዳዩ በሰበር ሰሚ ችሎት ፊት በድጋሚ የሚታይበት እድል ይፈጠራል፡፡ በሀገራችን የሕግ-ሥርዓት ውስጥ ጉዳዬች የመጨረሻ እልባት ሊያገኙ የሚችሉት በዚሁ የሰበር ሰሚ ችሎት ነው ነገር ግን ውሳኔው የህገ-መንግስት ጥያቄ ሲያስነሳ የፌዴሬሽን ም/ቤት በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 83 በተሰጠው ሥልጣን መሰረት ጥያቄ የተነሳበትን የህገ-መንግሰት ክፍል የሚተረጉምበት ሁኔታ ይኖራል ይህ ሥርዓት ግን ከመደበኛው የዳኝነት ሂደት ውስጥ አይመደብም፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያን የአፍሪካ የሰብአዊ መብቶች ቻርተር ፕሮቶኮልን ብታፀድቅ ኖሮ የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች በአፍሪካ የሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት በይግባኝ መልክ ሊታዩ የሚችልበት አጋጣሚ ይኖር ነበር፡፡ አመሰግናለሁ

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የሕዝብ ተሳትፎ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያለው ሚና
ዳኛ  እግዜር! ዳኛ ከችሎት ይነሳ!
 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 14 June 2024