መግቢያ
በአገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወረርሽኝ ሲከሰት የሰዎች ህይወትን ከመቅሰፉ በተጨማሪ የንግድ እንቅስቃሴዎችንም አደጋ ላይ ይጥላል። ንግድ የተሳለጠ እና ለሁሉ ተደራሽ የሚሆነው የተረጋጋ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ሲኖር ብቻ ነው። በንግድ ዓለም ውስጥ የነጋዴዎች ዋነኛ ግብ ተደርጎ የሚወሰደው በአጭር ጊዜ ወይም በረጅም ጊዜ ውስጥ ትርፋማ መሆን ነው። ነገር ግን ይህ ትርፋመነታቸውን የሚያሳኩት ሕግ እና ሥርዓትን በአከበረ መንገድ በሚደረግ እንቅስቃሴ ሊሆን ይገባል። ከሕግ እና ሥርዓት ውጭ ትርፍ ለማጋበስ የሚንቀሳቀስ ነጋዴ የተመሰረተበት አላማ ማትረፍ ስለሆነ በሚል ተልካሻ ምክንያት ዝም ተብሎ ሊታለፍ አይገባም። ይህንም መሰረት ለማስያዝ ሕግ እና ሥርዓት አስፈፃሚ አካላት ትልቅ ድርሻ አላቸው። ትርፍ ለማግኘት ከሚደረጉ ጥረቶች ጎን ለጎን ማህበራዊ ሀላፊነትን መወጣትንም መዘንጋት አይገባም። የነጋዴዎች ትርፍን ለማሳደግ የሚያርጉት እሩጫ ሕግ እና ሥርዓትን ለማስከበር ከተቋቋመ አካል ጋር በጥብቅ ከሚካረሩባቸው ወቅቶች አንዱ ወረርሺኝ የሚከሰትበት ወቅት ነው። ወረርሽኝ በሚከሰትበት ወቅት ሁሉም ከወረርሽኙ ለመዳን በሚያደርገው እሩጫ ወቅቱ የሚፈልጋቸው እቃዎች እና አገልግሎቶች እጥረት ሊከሰት ይችላል። በዚህ ጊዜ ማህበራዊ ሀላፊነትታቸውን ለመወጣት ደፋ ቀና የሚሉ ነጋዴዎች የሚኖሩትን ያክል አጋጣሚውን ተጠቅመው ሀብት ለማካበት እና ከችግር ለማትረፍ የሚሯሯጡም አሉ። እነዚህ ከችግር ለማትረፍ የሚሯሯጡ ነጋዴዎች ከሚተገብሯቸው ነገሮች መካከል እጥረት ያለበትን እቃ ማከማቸት እና በተፈላጊ እቃዎች ላይ አለአግባብ ዋጋ መጨመር ይገኙበታል። እነዚህ ተግባራት በሸማቹ ማህበረሰብ ላይ ከቀላል እስከ ከባድ አደጋዎችን ሊያስከትሉ ይችላሉ። ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ሀገራት የሸመቾች ጥበቃ ሕግን በማውጣት ሸማቹን ማህበረሰብ ከእንደዚህ አይነት ችግር ለመጠበቅ ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል። ሀገራችን ኢትዮጵያም ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ለሸማቾች መብት ጥበቃ ልዩ ትኩረትን የሰጠች ሲሆን በመካከልም ሁለት ህጎችን አርቅቃለች። አሁን ላይ በስራ ላይ ያለው የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 ትኩረት ከሰጣቸው ነገሮች መካከል እጥረት ያለባቸውን እቃዎች ማከማቸት እና ተፈላጊ እቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ይገኙበታል። በሀገራችን ዓለም አቀፍ የሆነው የኮረና ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ ከወረርሽኙ እኩል በሚባል ደረጃ የመገናኛ ብዙሀንን ትኩረት የሳበው ጉዳይ የነጋዴዎች እጥረት ያለባቸውን እቃዎች ማከማቸት ተግባር እና የተፈላጊ እቃዎችን ዋጋ ጨምሮ መሸጥ ይገኙበታል። የዚች አጭር ፅሁፍ አላማም እነዚህን የነጋዴው ማህበረሰብ ተግባራት ከኢትዮጵያ የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ አንፃር መተንተን እና መወሰድ ያለባቸውን ተግባራት መጠቆም ነው።
- የኮረና ወረርሽኝ እና እጥረት የተከሰተባቸው እቃዎች
የኮረና ወረርሽኝን ለመከላከል ከሚደረጉ ጥረቶች መካከል የህክምና መሳሪያዎች አቅርቦት የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። የዓለም ጤና ድርጅት በሰጠው መመሪያ መሰረት ሀገራት ሊከተሏቸው ከሚገቡ የመከላከያ መንገዶች አካላዊ እርቀት፣ ማስክ መጠቀም ፣አለመጨባበጥ እና እጅን በተደጋጋሚ መታጠብ ዋነኞቹ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ ማስክ መጠቀም የማስክ አቅርቦትን እንዲሁም እጅን በተደጋጋሚ መታጠብ ደግሞ የሳሙና እና የሳኒታይዘር አቅርቦትን ይጠይቃሉ። በአሁኑ ሰዓት በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ እነዚህ በሽታውን ለመከላከል የሚረዱ እቃዎች እጥረት የመንግስታት እና የህዝብ ጭንቀት ከሆኑ ውሎ አድሯል። ከዚህ በተጨማሪ እነዚህን እጥረት ያለባቸውን ቁሳቁስ በአገኙት አጋጣሚ የሚሰበስቡ እና በውድ ለመሸጥ የሚያከማቹ ነጋዴዎች እንዲሁም ከእራሳቸው እና ከቤተሰባቸው ፍጆታ በላይ የሚገዙ ግለሰቦች መበራከት ሌላ ትልቅ የእራስ ምታት ሆኗል። ከህክምና ቁሳቁሶች በተጨመሪ ለእለት ፍጆታ የሚውሉ እቃዎችም ለዚሁ ችግር ሰለባ ሆነዋል። መንግስት የሚያወጣውን መመሪያ ተከትሎ ዜጎች እቤት ውስጥ ለመቀመጥ ከሚገዙት ከመጠን ያለፈ የምግብ እቃዎች በተጨማሪ ወደፊት የዋጋ ጭማሪ ሊከሰት እንደሚችል በመተንበይ ዜጎች ሊገዙ የሚፈልጉአቸውን እቃዎች አከማችቶ የለም iማለት ወይም አላግባብ ዋጋ በመጨመር የሸማቹን የመግዛት አቅም የመቀነስ ተግባር በነጋዴው ማህበረሰብ ዘንድ ይስተዋላል። እነዚህ ተግባራት በወቅቱ ተገቢ የሆነ ህጋዊ እርምጃ ካልተወሰደባቸው በጊዜ ሂደት የሚያስከትሉት አደጋ በጣም ከባድ ይሆናል። የህክምና ቁሳቁሶች ላይም ሆነ የእለት ፍጆታ እቃዎች ላይ የሚደረገው የማከማት እና ሰው ሰራሽ የእቃ እጥረት ችግር ሸማቹን ማህብረሰብ ለርሀብ ብሎም ለሞት የሚዳርግ ችግር ውስጥ ሊከተው ይችላል። ወረርሽኙን ለመከላከል የሚረዱ እቃዎች በአግባቡ እንዲሰራጩ ከአልተደረገ ከእለት ወደ እለት ወረርሽኙ እየተስፋፋ ከሚያስከትለው ሰብዓዊ ኪሳራ በተጨማሪ የእለት ከእለት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በመገደብ ሀገርን ከባድ የማትወጣው አዘቅት ውስጥ ሊከት ይችላል። የእለት ፍጆታ አቅርቦቶችን መገደብም በእራሱ ዜጎችን ለርሀበ እና ሲቃይ በመዳረግ ወረርሽኙ ሊያስከትል ከሚችለው አደጋ የበለጠ ችግር ሊያመጣ ይችላል። እነዚህን ከባድ ችግሮች መቋቋም የሚቻለው ሕግን መሰረት አድርጎ በእንደዚህ አይነት ተግባራት ላይ የተሰማሩ አካላትን ማስተካከል እና አስፈላጊ እርምጃዎች ሲወሰዱ ብቻ ነው።
- የንግድ እቃን ማከማቸት እና ሰው ሰራሽ እጥረት መፍጠር በኢትዮጵያ ሕግ
እቃን ማከማቸት እና ሰው ሰራሽ እጥረት መፍጠር የገቢያ አለመረጋጋት እና የዋጋ ንረትን ከሚያስከትሉ ተግባራት መካከል የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች የእቃውን በገቢያ ላይ ያለውን ተፈላጊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የአቅርቦት ችግር በሌለበት ሁኔታ የአቅርቦት ችግር ያለ በማስመሰል በግለሰብ ወይም በቡድን ደረጃ ሊያከማቹ እና ሰው ሰራሽ እጥረት ፈጥረው በትልቅ ዋጋ የመሸጥ ተግባር ሊፈፅሙ ይችላሉ። ነጋዴዎች እቃውን አከማችተው የሚያስቀጡበት ዋነኛ አላማቸው ጊዜውን ጠብቆ ከተገቢው በላይ ትርፍን ለማጋበስ ነው። ከነጋዴው ማህበረሰብ በተጨማሪ የሸማቹ ማህበረሰብም በእንደዚህ አይነት ተግባራት ተሰማርቶ ሊገኝ ይችላል። የሸማቹ ማህበረሰብ በዋነኝነት እንደዚህ አይነት ተግባር ውስጥ የሚሰማራው እቃው ከገቢያ ላይ ይጠፋል የሚል ፍራቻ ሲያድርበት ነው። ይህ የንግዱ ማህበረሰብም ሆነ የሸማቹ የማከማቸት ተግባር በዜጎች ላይ ወይም እንደ አጠቃላይ በሀገር ላይ የሚያደርሰው ኪሳራ በጣም ከባድ የሆነ ነው። ይህንም ተግባር ለመከላከል ይረዳ ዘንድ የኢትዮጵያ ንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 እቃን ስለማከማቸት እና ሰው ሰራሽ እጥረት መፍጠርን አስመልክቶ ድንጋጌዎችን የአካተተ ሲሆን የማስፈፀም ሀላፊነቱንም ለንግድ ሚኒስትር፤ ለንግድ ዉድድር እና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን እና ለንግድ ቢሮዎች ሰጥቷል።