በዓለማችን እና በሀገራችን የተከሰተውን የኮቪድ-19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ በሀገራችን የፌደራል መንግሥትና የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች መታወጃቸው ተከትሎ የሀገራዊ ምርጫን መራዘምና ክልላዊ ምርጫ በትግራይ መከናወኑን ከሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች አኳያ እንደሚከተለው አስቀምጣለሁ፡፡
በቅድሚያ ጥቂት በሆነችው ትልቅ ኢ-ሕገመንግሥታዊ ውሳኔን በመግለጽ ልጀምር፡፡ በሕገ-መንግሥታችን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊደነገግ የሚገባው በሁለት ምክንያቶች ማለትም፡-
1ኛ/ በሰው ሰራሽ አደጋ (የውጪ ወረራ ሲከሰት እና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰት)
2ኛ/ በተፈጥሮ አደጋ (ጎርፍ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የህዝብ ጤንነትን አደጋ ላይ የሚጥቅ ሁኔታ ሲከሰት) ስለመሆኑ የፌደራሉ ሕገ-መንግሥት አ.ቁ 93(1) የሚደነግግ ሲሆን በ2ኛው የተፈጥሮ አዳጋ ሲከሰት የፌደራል መንግሥቱ ብቻ ሳይሆን ክልላዊ መንግሥቶች አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማውጣት ሥልጣን ይኄው የሕግ መንግሥት አንቀጽ 93(1)(ለ) መብትን ይሰጣቸዋል፡፡ በመሆኑም የሀገራችን የበላይ ሕግ የሆነው አካል ለሁለቱም መንግሥታት እኩል ሥልጣን በሰጠው ጉዳይ ላይ የአንደኛው ከአንደኛው የሚበልጥበት ወይም አንደኛው በአንደኛው ላይ የበላይ የሚሆንበት ሁናቴ የለም፡፡ ነገር ግን የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት መጋቢት 30 ቀን 2012 ዓ.ም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በክልሎች ከሚወጡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ሁሉ የበላይ ስለመሆኑ መደንገጉ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው፡፡