ዳኛ  እግዜር! ዳኛ ከችሎት ይነሳ!

ሀገሬው የዳኝነትን ሥራ (ፍትሕ መስጠት) ሃሳባዊ በማድረግ ደረጃውን ከፍ ሲያደርገው “ዳኛ እግዜር!” ይላል፡፡ ከሳቴ ብርሃን የአማርኛ መዝገበ ቃላትም ዳኛ ማሪያም! ተሙዋጋች በዳኛ ፊት ቆሞ ሲአመለክት ዳኛ እግዚአብሔር! ያሳይህ ዳኛ ማርያም ወይም ሲሙአገት ጭብጥ የያዘውን አስመስካሪውን ዳኛ የምስክሮቹን ቃል ለማሳሰብ ተዘከረኝ ዳኛ ማሪያም ይላል በማለት ይገልፀዋል፡፡ እንደ ፕልቶ ያሉ ሃሳባውያን (idealist) ፈላስፎች “ፍትሕ” ሃሳባዊ ተፈጥሮ ያለው፣ ከሰብዓዊ ባህርይ ውጪ የሆነ እና አሁን ባለው ዓለም (physical world) ሳይሆን በጊዜ እና በቦታ ባልተገደበው ሃሳባዊ ዓለም የሚገኝ እንደመሆኑ ስሙ ብቻ የሚታየውን ሃሳብ ቅርፅ ወዳለው ድርጊት በሕግ መልክ ሆነ በሌላ ዘዴ ወደ ዚህኛው ዓለም ሊመልሱት እና ሊፈፅሙት የሚችሉት እውነተኛው ሃሳብ የሚታያቸው ሰዎች ናቸው ይላል፡፡ እንግዲህ ሀገሬው “ዳኛ እግዜር” ሲል በፍትሕ ላይ ሃሳባዊ መሆኑ ነው፡፡ “ፍትሕ ከፈጣሪ  ነው” ብሎ ለሚያምን ማህበረሰብ ሰው በፈራጅነት ቦታ ቁጭ ብሎ ሲያገኘው  በአገረኛ ዘዬ ኧረ! ዳኛ እግዜር! ቢል አይገርምም፡፡ ሌላው ሀገሬው በፍትሕ ላይ ሃሳባዊ ለመሆኑ መገለጫ የሚሆነው ለዳኛ ሲሰጠው የነበረው ልዩ ቦታ ነው፡፡ የአንድ ማህበረሰብ ወግ እና ሥርዓት የሚቀዳው ካለው አካባቢያዊ የእምነት እና አስተሳሰብ መሠረት አድርጎ ነው፡፡ ለማሳያ ያህል  ከፍትሐ ነገስቱ አንድ ነገር አንጠልጥለን እንውጣ፡፡

  13599 Hits