Font size: +
4 minutes reading time (884 words)

የሕግ አረቃቀቅ ሥርዓት በኢትዮጵያ

ሕግ ማርቀቅ አንዱ እና ዋነኛው የሕግ ሙያ ዘርፍ ነው፡፡ ሕግ ማውጣት የሚያስፈልግበት ዋና ዓላማ የመንግስትን ፖሊሲ ለማስፈፀም ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ሕግ የፖሊሲ ማስፈፀሚያ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ የሕግ አረቃቅ ላይ ሊወሰድ የሚገባው ጥንቃቄ እና የአረቃቅ ሂደቱ ሕጉ ከፀደቀ በኋላ የሚኖረው አተገባበር ላይ ቀጥተኛ የሆነ ተፅእኖ ያለው መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሕግ አረቃቀቅ በኢትዮጵያ ወጥነት የሚጎድለው፤ ትኩረት የሚሻ እና በሕግ አግባብ ሊመራ የሚገባ ዘርፍ ነው፡፡አሁን ላይ ይህ ዘርፍ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚመራበት አንድ ወጥ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ የሌለውም ዘርፍ ነው፡፡ ዘርፉ በዚህ አግባብ የሚመራበት የሕግ ማዕቀፍ አለማግኘቱ በሕጎች አረቃቀቅ ጥረት፤ ወጥነት፤ መናበብ፤ እና አፈፃፀም ላይ የራሱ የሆነን አሉታዊ ተፅእኖ እንዳሳደረ ይታመናል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ያልተማከለ የአስተዳደር ሥርዓትን በሚከተሉ አገራት ሕጎች በሁለት ደረጃ እንደሚረቀቁ ይታወቃል፡፡ ይህም ሁለት ዓይነት የሕግ አረቃቀቅ ሥርዓትን እንድንከተል ከማስገደዱም በላይ በሁለቱ የአስተዳደር እርከኖች ማለትም በፌደራል እና በክልል ደረጃ ያሉ የሕግ አረቃቀቅ ሂደቶች በራሳቸው የሚመሩበት ወጥ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩ ዘርፉን ትኩረት የሚያሻ ያደርገዋል፡፡

በሀገራችን የሕግ አረቃቅ እሳቤ እና አተገባባር ሥርዓት የሕግ ማዕቀፍ የሚባሉት አዋጅ፤ ደንብ፤ እና መመሪያ ናቸው፡፡ ሶስቱም የሕግ ማዕቀፎች በፌደራል እና በክልል ደረጃ የሚረቀቁ ሲሆን የአረቃቀቅ ሥርዓቱ የሚመራበት አንድ ወጥ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ ግን የለም፡፡ ወጥነት ያለው አንድ የሕግ አረቃቀቅ የሕግ ማዕቀፍ የለም ማለት ግን እነዚህ ሕጎች የሚረቀቁበት የታወቁ እና መሠረታዊ የሆኑ የሕግ አረቃቅ ሂደቶች የሉም ማለት ግን አይደለም፡፡

ሕግ ማውጣት በሕገ መንግስቱ መሠረት የተሰጠው የሕግ አውጪው የመንግስት አካል ለሆነው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲሆን ምክር ቤቱ በራሱ የሚያረቃቸው ሕጎች እንደተጠበቁ ሆነው አብዛኛው የሚያፀድቃቸው ሕጎች ግን ተረቀው የሚቀርቡለት በአስፈፃሚው አካል ነው፡፡ በዋናነት በምክር ቤቱ የሚፀድቀው ሕግ አዋጅ ሲሆን ምክር ቤቱ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 77(13) መሠረት የአስፈፃሚው አካል ለሆነው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ የማውጣት ስልጣንን በውክልና ሰጥቷል፡፡ ሆኖም የሚኒስትሮች ምርክር ቤት የሚያወጣው ደንብም ቢሆን ተረቆ ለምክር ቤቱ የሚቀርበው በአስፈፃሚው አካል ከመሆኑም በላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያፀደቀው ደንብም ቢሆን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ መፅደቅ ይጠበቅበታል፡፡ይህም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ሕግ ማውጣት የራሱ/የባሕሪው (inherent power) የሆነው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ደንብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት፤መመሪያ ደግሞ በአስፈፃሚ አካሉ ተቋማት የሚወጣ ቢሆንም አዋጅም፤ደንብም፤መመሪያም የማውጣት ስልጣኑ ግን የራሱ/የባሕሪው (inherent power) የሆነው የሕግ አውጪው አካል የነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ሆኖም ምክር ቤቱ ካለበት የሥራ ጫና የተነሳ እንዲሁም የአስፈፃሚው አካል ለሚወጡ ሕጎች ካለው ቅርበት አንፃር ሕግ የማውጣት ሥልጣን በውክልና እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ በውክልና ስልጣኑም መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ማውጣት የሚችል ሲሆን የአስፈፃሚው አካል የሆኑ ተቋማት ደግሞ መመሪያዎችን ማውጣት ይችላሉ፡፡

እንደ ሀገር የአዋጅ አወጣጥ ሂደት እና ሥርዓት የሚመራበት የሕግ ማዕቀፍ የለንም፡፡ የዚህ አንዱ ማሳያ የሆነው ደግሞ በአዋጅ ደረጃ ሊወጡ የሚችሉ ጉዳዮች እነዚህ እነዚህ ናቸው ተብሎ ግልፅ መመዘኛ እና መስፈርት በሕግ ደረጃ አለመቀጡ ሲሆን፤የአዋጅ ይዘት ምን መሆን አለበት?፤ አዋጁ ሲዘጋጅ ሊከተላቸው የሚገባ አስገዳጅ ሂደቶችስ ምን ምን ናቸው? የሚሉትም ሌሎች የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው፡፡

ሆኖም ማንኛውም አዋጅ በሕግ አውጪው ተረቆም ይሁን በአስፈፃሚው አካል ተረቆ ለምክር ቤቱ ሲቀርብ ሊከተላቸው የሚገቡ መሠረታዊ የሕግ አረቃቀቅ ሂደቶች አሉ፡፡ ከእዚህም መካከል በአንድ የተወሰነ ጉዳይ ላይ የሕግ ይረቀቅ ጥያቄ ሊኖር ይገባል፤በቀረበው የሕግ ይረቀቅ ጥያቄ መሠረት ሕጉ ይረቀቃል፤በተረቀቀው ሕግ ላይ ተደጋጋሚ የሆኑ የባለ ድርሻ አካላት ውይይት ተካሂደው ግብዓቶች ሊሰባሰቡ ይገባል፤የተሰበሰቡ ግብዓቶችና አስተያየቶች በረቂቁ ተካተው ሙያዊ አስተያየት ይሰጥበት ዘንድ ረቂቁ ለፍትሕ ሚኒስቴር ሊላክ ይገባል፡፡ የፍትሕ ሚኒቴርም የራሱን አስተያየት ከሰጠ በኋላ ሠነዱ በተሰጠው አስተያየት መሠረት ተስተካክሎ መስተካከሉ ይረጋገጥ ዘንድ በድጋሚ ለፍትሕ ሚኒስቴር ይቀርባል፡፡ ከዚህ በኋላ የፍትሕ ሚኒስቴር ሠነዱ ወደ ቀጣይ ሂደት መቅረብ እንደሚችል ሲገልፅ ወደ ቀጣይ ሂደት የሚሄድ ይሆናል፡፡

እንደ አዋጅ ሁሉ የደንብ አወጣጥ ሂደት እና ሥርዓትም ቢሆን የሚመራበት የሕግ ማዕቀፍ የለም፡፡ ምክር ቤቱ ደንብ ሲያወጣም በዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ነው ደንብ ማውጣት የሚቻለው በሚል አስገዳጅ በሆነ ሁኔታ በሕግ ደረጃ የተቀመጠ ነገር የለም፡፡ በተጨማሪም የአንድ ደንብ ይዘት ይሄን ነው መመሰል ያለበት በሚል ይዘቱን ወስኖ የሚያስቀምጥ የሕግ ማዕቀፍም የለም፡፡

አዋጅ ሲወጣ የሕገ መንግስቱን አንቀጽ 55(1) ጠቅሰን እንደምናወጣው ደንብ ሲወጣ ግን የሕገ መንግስቱን አንቀጽ 77(13) ጠቅሰን ማውጣት አንችልም፡፡ ይህም የሆነበት ዋና ምክንያት የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 77(13) ያስፈለገበት ዋና ምክንያት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሕግ የማውጣት ስልጣንን በውክልና የሰጠበት ሲሆን ውክልናውን ለመስጠት የሕግ መሠረት የሚያስፈልግ በመሆኑ ምክንያት የተቀረፀ ድንጋጌ ነው፡፡

በይዘት ደረጃ ልክ እንደ አዋጅ ሁሉ በደንብ ደረጃ ሊወጡ የሚችሉ ጉዳዮች እነዚህ ናቸው ተብሎ በሕግ ማዕቀፍ መልኩ የተቀመጠ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን በተለምዶ የብዙ የተቋማት ማቋቋሚያ እና የገንዘብ ነክ ጉዳዮች በደንብ ደረጃ ሲወጡ ይስተዋላል፡፡ በሌላ በኩል ግን በደንብ ደረጃ የሚወጡ ጉዳዮችን ዝርዝር እና የደንብ አወጣጥ ሂደቱን የሚመለከት የሕግ ማዕቀፍ ባይኖርም በአሰራር ደረጃ ግን አንድ ደንብ ሲዘጋጅ አንድ አዋጅ ሲዘጋጅ በሚያልፍባቸው ሂደቶች ማለፉ የሚጠበቅ ነው፡፡

የመመሪያ አወጣጥን በተመለከተ መመሪያ እንዲወጣ በአዋጅ ላይ ሲጠቀስ፤ መመሪያ እንዲወጣ በደንብ ላይ ሲጠቀስ፤ ወይም አንድን ጉዳይ በሕግ ማዕቀፍ ለመሸፈን ሲያስፈልግ መመሪያ ሊወጣ ይችላል፡፡

ከአዋጅ እና ደንብ ዝግጅት በተለየ መልኩ የመመሪያ አወጣጥ ሥርዓት የሕግ ማዕቀፍ ተበጅቶታል፡፡ ይህ የሕግ ማዕቀፍ የፌደራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 በመባል የሚታወቅ ሲሆን አዋጁ የአስተዳደር ተቋማት መመሪያን ሲያወጡ ሊያልፉ የሚገቡበትን ሂደት በግልፅ የሚያስቀምጥ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት አንድ የአስተዳደር ተቋም መመሪያ ሲያወጣ ሊያልፍ የሚገባባቸው ያላቸውን መሠረታዊ ሂደቶች ያስቀምጣል፡፡ በዚህ አዋጅ ከተመለከቱ መሠረታዊ ድንጋጌዎች መካከል የመመሪያ አወጣጥን የሚመለከት መዝገብ ማደራጀት እንደሚገባ፤ማስታወቂያ ስለማውጣት፤ ረቂቅ መመሪያን ለፍትሕ ሚኒስቴር አስተያየት ስለመላክ፤ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክን ስለማዘጋጀት፤ መመሪያ ስለሚጸድቅበት ጊዜና ሁኔታ፤ ለመመሪያ ስለሚዘጋጅ የማብራሪያ ጽሑፍ፤ የመመሪያ ይዘትና ቅርፅ ምን መምሰል እንዳለበት፤ እንዲሁም መመሪያ በፍትሕ ሚኒስቴር ስለሚመዘገብበት አግባብ ያስቀምጣል፡፡

የመመሪያን ጉዳይ ከአዋጅ እና ደንብ በተለየ መልኩ ትኩረት ሰጥቶ በዚህ አዋጅ እንዲመራ ማድረግ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ደግሞ የአስተዳደር ተቋማት በሚያሳልፏቸው አስተዳደራዊ ውሳኔዎች እና በሚያወጧቸው መመሪያዎች የተነሳ የዜጎችን መብትና ጥቅም በመንካት ዜጎችን ለመልካም አስተዳደር ችግር እንዳዳርጓቸው ለመከላል ነው፡፡

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የሕግ ማለትም (የአዋጅ፤ የደንብ፤ የመመሪያ) አወጣጥ ሥርዓት አንድ ወጥ በሆነ የሕግ ማዕቀፍ የሚመራበት አግባብ ባይኖርም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በፍትሕ ሚኒስቴር የተዘጋጁ የሕግ አረቃቀቅ ማኑዋሎችን በመጠቀም በሕግ አረቃቅ ሂደት የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚሰራ ቢሆንም ዘርፉ የሚመራበትን አስገዳጅ የሕግ ማዕቀፍ ማሰቡ የተሻለው አማራጭ ነው፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Criminal Reinstatement in Ethiopia: Exploring the ...
በሌላ ሰው ይዞታ ላይ ቤት የሰራ ሰው መብት - አንዳንድ ነጥቦች 

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 13 December 2024