ንብረት የማፍራት እና ፍትሐዊ ዳኝነት የማግኘት መብት: ከወቅታዊው የሕገ-ወጥ መሬትና ንብረት ማስመለስና ማፍረስ ጋር በተያያዘ

አሁን አሁን በተለያዩ የሃገራችን ክልሎች በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ ዙርያ በሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ከተሞች ላይ ከዕለት ወደዕለት በዜጎች የመዘዋወር መብት፤ንብረት የማፍራት፤ የእኩልነት እና ፍትህ የማግኘት ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሕግ ማስከበር ሰበብ ሲጣሱ ማዬት የዕለት ተዕለት ተግባራዊ ኩነት እየሆነ መጥቷል፡፡

የዚህ አጭር ጽሑፍ መነሻ ነጥብም በሕግ ማስከበር ሰበብ ለረዥም አመታት ከማህበረሰቡ ጋር በመቀላቀል ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ንብረት ያፈሩ ዜጎች ላይ በሕገ ወጥነት ሰበብ እየተወሰደ ያለውን ከገዛ ቤታቸውና ንብረታቸው የማፈናቀል እርምጃን በተመለከተ ዜጎች መብቶቻቸውን በሕግ አግባብ እንዴት ማስከበር እንዳለባቸው የሚያሳይ ፍኖተ ሕግ ነው፡፡

የህጉን ዝርዝር ነጥብ ከመመልከታቸን በፊት አሁን መሬት ላይ ያለው እውነትን በጨረፍታ ለመመልከት መሞከሩ ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባ ዙርያ የሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች መካከል የሰበታ ከተማ አስተዳደር፤ የቡራዩ ከተማ አስተዳደር፤ የለገጣፎ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም የሱሉልታ ከተማ አስተዳደር የከተሞቻቸውን የማስተር ፕላን ጋር ተቃራኒ የሆኑ እንዲሁም ቀድሞ ካሳ የተከፈላቸው እና በሕገ ወጥ መንገድ ከመንግስት እውቅና ውጭ ንብረት ያፈሩ ወይም በተለምዶ ወቅታዊ አጠራሩ ሕገ ወጥ ግንባታዎችን  አጭር የማስጠንቀቂያ ጊዜ በመስጠት ነዋሪዎቹ ለዓመታት ይኖሩበት የነበረውን በጉልበታቸውና በጥሪታቸው ያፈሩትን ሃብቶቻቸውን በሃይል ድርጊት እንዲፈርስ በማድረግ በተጨባጭ ዜጎች ከሃብት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ መደረጉ ለብዙ ቅሬታ መነሻ ነጥብ ሆኖ መገኘቱ ነው የዚህ ጽሑፍ መነሻ ነጥብ፡፡ በመሆኑም ዜጎች ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈጸምባቸው በምን አግባብ መብቶቻቻውን ማስከበር እንደሚችሉ ከኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት እና ከአዋጅ ቁጥር 721/2004 ጋር በማመሳከር ረጂ ናቸው ብዬ ያሰብኳቸውን ነጥቦች ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡  

በቅድሚያ የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 25 መሰረት ማንኛውም ሰው ልዩነት ሳይደረግበት በሕግ እኩል ያልተነጣጠለ እና አድሏዊ ባልሆነ መልኩ ጥበቃ እንደሚደረግለትና  እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት እንዳላቸው በማያሻማ ቋንቋ የማይገረሰሰ ሰብዓዊ መብት እንደሆነ ደንግጎ ይገኛል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከጉዳያችን ጋር ተያያዥነት ባለው መልኩ በዚሁ ሕገ መንግስት አንቀፅ 32 ላይ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በመረጠው የሃገሪቱ አካባቢ የመዘዋዋርና የመኖርያ ቤት የመመስረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሃገር የመውጣት ነፃነት እንዳለውና በአንቀጽ 40/7ም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በጉልበቱ ወይም በገንዘቡ በመሬት ላይ ለሚገነባው ቋሚ ንብረት ወይም ለሚያደርገው ቋሚ መሻሻል ሙሉ መብት አለው በማለት እርስ በርስ ተመጋጋቢ እና ተደጋጋፊ በሆነ መልኩ የዜጎችን ንብረት የማፍራትና በሃገራቸው በነፃነት የመዘዋወር ዲሞክራሲያዊ መብቶችን በዝርዝር ይጠቅሳል፡፡

Continue reading
  10246 Hits
Tags: