የብሮድካስቲንግ ቁጥጥር/ሪጉሌሽን እና የባለሥልጣኑ ደብዳቤ

ስለሪጉላቶሪ መሳሪያዎች መግቢያ

ዛሬ የብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ለሁለት ብሮድካስተሮች ጽፈውታል የተባለ ደብዳቤ በፌስቡክ መለጠፉን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች እየተስተናገዱ ነው። በደብዳቤው ብሮድካስተሮቹ ለምን የቅዳሜውን የድጋፍ ሰልፍ እንዳላስተላለፉ መረጃ በተጠቀሰው ቀን ይዘው በመምጣት ከባለሥልጣኑ ጋር እንዲወያዩ ያሳስባል። ባለሥልጣኑ ይህን ደብዳቤ “ሊመልሰው፣ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል”፣ እና የመሳሰሉት አስተያየቶች በመሰጠት ላይ ይገኛሉ። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ምንም እንኳን በሚዲያ ተቋማት ዙሪያ የግሌ ጠቅላላ አስተያየትና እምነት ቢኖረኝም የብሮድካስቲንግ አዋጁን አስመልክቶ ያለኝን ግንዛቤና አረዳድ እንደሚከተለው አካፍላለሁ።

እንደሚታወቀው ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ተቆጣጣሪ አካል ወይም ሪጉሌተር ነው። በመሆኑም ለመግቢያ ያህል በጠቅላላው በተለያዩ ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮች የተለያዩ ሪጉላቶሪ አካላት የመቆጣጠር ስልጣናቸውን ምን ዓይነት የፓሊሲ ወይም የሪጉላቶሪ መሳሪያዎችን በመጠቀም እንደሚያሳኩ ባጭሩ እንመልከት። የተለያዩ ሪጉላቶሪ አካላት የሚከተሉትን ስምንት ዋና ዋና መሳሪያዎች በአማራጭ ወይም በስብጥር ይጠቀማሉ።

አንደኛው የፈቃድ ሥርዓት መዘርጋት ነው። በአንድ የተለየ ተግባር ላይ መሰማራት የሚፈልግ አካል፣ ወደ ተግባር ከመግባቱ በፊት ከሚመለከተው ተቆጣጣሪ/ሪጉሌተር ፈቃድ እንዲያወጣ ይጠበቅበታል። የፈቃድ ሥርዓት ከማሳወቅ ሥርዓት ይለያል። ምክንያቱም ፈቃዱ ሊከለከል ይችላል። ፈቃዱን ለማግኘት አመልካቹ ማሟላት ያለበት ቅድመ ሁኔታዎች በሕግ ይቀመጣሉ። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች የተለያዩ መልኮች ሊይዙ ይችላሉ፤  የዜግነት ወይም የነዋሪነት ግዴታ፣  የትምህርት ወይም የብቃት ደረጃ፣ የድርጅት ዓይነት (ለምሳሌ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ለመሰማራት፣ የግድ አክሲዮን ማህበር ማደራጀት ያስፈልጋል ሊባል ይችላል)፣ የገንዘብ አቅም፣ ፈተና፣ ልምድ፣ እና የሃላፊነት መድን (በሥራው የተነሳ በሌሎች አካላት ላይ ጉዳት ቢያደርስ፣ ጉዳቱን የሚክስ መድን አስቀድሞ እንዲገባ ማድረግ።

ሁለተኛው የሪጉላቶሪ መሳሪያ የጥራት ቁጥጥር ነው። አንዴ ፈቃድ አግኝቶ ወደ ተግባር የገባ አካል፣ የሚያቀርባቸው ምርትና አገልግሎቶች ሊያሟሏቸው የሚገባቸውን የጥራት ደረጃ ቁጥጥር ማድረግ። የጥራት ቁጥጥር ሁለት ዓይነት ዋና ዋና የጥራት ስታንዳርዶችን በመጠቀም ይከናወናል። አንደኛው የተግባሩ ውጤት ወይም ፍሬ ሊያሟላው የሚገባ የጥራት መለኪያ በወለል ወይም በጣሪያ መልክ ሊቀመጥ ይችላል። ለምሳሌ የታሸገ ውሃ ሊኖረው የሚገባው ከፍተኛ የአርሰኒክ መጠን በተቆጣጣሪው አካል በሕግ ሊደነገግ ይችላል። ሁለተኛው የጥራት ስታንዳርድ ዓይነት የግብአት ወይም ቴክኖሎጂ ወይም የሂደት ጥራት ነው። በዚህኛው መሠረት የተግባሩ ውጤት ወይም ፍሬ ሊያሟላው የሚገባ የጥራት ደረጃ ሳይሆን ትኩረት የሚደረገው፣ ውጤቱን ወይም ፍሬውን ለማምረት ወይም ለማቅረብ አምራቹ ወይም አቅራቢው ሊጠቀመው የሚገባ የግብአት፣ ቴክኖሎጂ፣ ወይም ሂደት ዓይነትና ጥራት በሪጉላቶሪ አካሉ ወይም በሕግ አውጪው በሕግ ሊደነገግና ክትትል ሊደረግበት ይችላል። ሁለቱንም ዓይነት ስታንዳርዶችን አሰባጥሮ መጠቀም ቢቻልም ብዙ ጊዜ ሁለተኛው ዓይነት ስታንዳርድ የምንጠቀመው፣ የመጀመሪያውን ዓይነት ስታንዳርድ ማውጣት ወይም ክትትል ማድረግ አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜ ነው። ለምሳሌ የትምህርት ተቋማትን የአገልግሎት ጥራት ለመለካት የስራቸው ፍሬ የሆኑትን ተማሪዎቻቸው ሊያሟሏቸው የሚገቡ የጥራት መለኪያዎችን ማስቀመጥ ከባድ ስለሆነ የትምህርት ተቋማቱ ሊጠቀሙባቸው በሚገቡ ግብአቶች (ለምሳሌ የትምህርት መጽሐፍት፣ የመማሪያ ክፍሎች፣ የተማሪና የአስተማሪ የቁጥር ምጣኔ)፣ ሂደቶችና ቴኬኖሎጂዎች ላይ ትኩረት ይደረጋል። እንዲሁም በከተሞች የሚቀርቡ የቧንቧ የመጠጥ ውሃን አስመልክቶ የመጀመሪያውን ዓይነት ስታንዳርድ ማውጣትቢቻልም፣ ክትትሉ ግን እጅግ አስቸጋሪ ስለሚሆንን እና አስተማማኝነቱም ዝቅተኛ ስለሚሆን በዋናነት በሁለተኛው ዓይነት የጥራት ስታንዳርድ ስራ ላይ ሲውሉ ይስተዋላል። ሊታወቅ የሚገባው ጉዳይ ሁለተኛው ዓይነት የሪጉላቶሪ መሳሪያ ለኪራይ ሰብሳቢነት የተጋለጠ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ አማራጭ ቴክኖሎጂዎች፣ ግብአቶች፣ ወይም ሂደቶች እንዳይዳብሩ ወይም እንዲከስሙ ማድረጉ ነው።

ሦስተኛው ዓይነት ሪጉላቶሪ መሳሪያ ጥራት ላይ ሳይሆን መጠን ወይም ቁጥር ላይ ትኩረት ያደርጋል። የመሸጫ ወይም የመግዣ ዋጋ ላይ የሚደረግ ቁጥጥር የዚህ ማሳያ ነው። 

አራተኛው ዓይነት መሳሪያ በግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ፣ አንደ ዓይነትና ቁጥር ያለው አገልግሎትን ለሕዝብ በነጻ ወይም በክፍያ የማቅረብ ግዴታ በመጣል የሚደረግ ቁጥጥር ነው። ለምሳሌ የሕግ ባለሙያዎች በዓመት ለተወሰነ ሰዓት አቅም ለሌላቸው ዜጎች በነጻ የሕግ አገልግሎት የማቅረብ ግዴታ መጣል።

አምስተኛው መሳሪያ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ላይ የተለዩ የመረጃ አይነቶችን በነጻ የማቅረብ ግዴታ ነው። መረጃው የሚቀርበው ለሸማቹ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ የታሸገ ምግብ የሚያመርቱ ድርጅቶች ምግቡ ያለውን የካሎሪ መጠን እና ዓይነት እንዲሁም የግብአት ዓይነትና መጠን እንዲሁም የተለመዱ ዓይነት አለርጂ አምጪ የሆኑ ግብአቶች በምግቡ ውስጥ ስለመካተታቸው በተወሰነ መልኩ መረጃ ለተጠቃሚው እንዲያቀርቡ ሊገደዱ ይችላሉ። ሃስቡ ሸማቹ እነዚህን መረጃዎች እስካገኘ ድረስ የፈለገውን ውሳኔ በነጻነት ይወስናል በሚል ነው። በሁለተኛ ደረጃ ግለሰቦችና ድርጅቶች የተወሰኑ ዓይነት መረጃዎችን ለሪጉሌተሩ እንዲያቀርቡ ሊገደዱ ይችላል። ለሪጉሌተሩ መረጃ መስጠት በሕግ ሊደነገግ ይችላል ወይም እንደነገሩ ሁኔታ ግለሰቦችና ድርጅቶችን እነዚህ መረጃዎች በተናጥል እንዲያቀርቡ ሊጠየቁ ይችላሉ። ለሪጉላቶሪ ሥርዓቱ ውጤታማነት፣ አዋጭነት፣ እና ፍትሃዊነት መረጃ ወሳኝ ነው። በብዙ ሁኔታዎች መረጃን አስመልክቶ ከሪጉሌተሩ ይልቅ ቁጥጥር የሚደረግባቸው አካላት ተፈላጊውን መረጃ በቀላሉ ሊያገኙት ይችላሉ። በተጨማሪም በተለይ የሪጉላቶሪ ሥርዓቱ ባልዳበረበት ሁኔታ የጥራት ስታንዳርዶችን ወይም ሌሎች ግዴታዎችን መጣል አስቸጋሪ ነው። መረጃው በሚገባ መጠን ተሰብስቦና ተደራጅቶ ስላልቆየ። በእነዚህ ሁኔታዎች መረጃን ለሪጉሌተሩ እንዲያቀርቡ ማስገደድ የሪጉላቶሪ ሥርዓቱ አጥጋቢ ፍሬ እንዲኖረው ያደርጋል ወይም ያግዛል።

ስድስተኛው መሳሪያ ገንዘብ ነክ ነው። በአንዳንድ እንቅስቃሴዎች ወይም ምርትና አገልግሎቶች ግብር በመጣል ሪጉላቶሪ ዓላማን ማሳካት ይቻላል። ከዚህ በፊት ያሉትን መሳሪያዎች ለመጠቀም መንግስትና ሪጉላቶሪ አካላት ቅጣትን ይጠቀማሉ (የወንጀልና አስተዳደራዊ ቅጣትን)። ከቅጣት ይልቅ መንግስት ግብርን ሊጠቀም ይችላል። አንዱን ድርጊት ከመከልከል ይልቅ፣ ለድርጊቱ ግብር ማስከፈል። ሌላኛው ገንዘብ ነኽ መሳሪያ ድጎማ ነው። ድጎማው በገንዘብ ወይም በአቅም ግንባታ ሊሆን ይችላል። በተለይ ግለሰቦችና ድርጅቶች የሚፈለግባቸውን የጥራትና መጠን ደረጃ የማያሟሉት በፈቃድና በምን አለብኝነት ሳይሆን፤ በገንዘብ፣ መረጃና፣ ቴኬኖሎጂ ብቃት ማነስ ነው ተብሎ ሲታመን፣ ድጎማ ተመራጩ መሳሪያ ነው።

ከዚህ በላይ ያሉት የሪጉላቶሪ መሳሪያዎች አንድ የተለየ ሪጉላቶሪ ተቋም የሚጠቀምባቸው ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ከሪጉላቶሪ ተቋሙ ውጭ ባለ ሁኔታ የሚደረግ ቁጥጥርንም ግምት ውስጥ ማስገባት ይገባል።

ሰባተኛው መሳሪያ፣ ድርጅቱ ወይም ግለሰቡ በድርጊቱ ወይም በአለማድረጉ የተነሳ በሌሎች ላይ ላደረሰው ጉዳት ካሳ እንዲከፍል ማድረግ ነው። ይህን የሚያደርገው ተበዳዩ አካል በፍርድ ቤት ቀርቦ በሚያቀርበው ክስ፣ ማስረጃና ሙግት ነው።ስምንተኛው የቁጥጥር መሳሪያ ወይምስ ሥርዓት የሚባለው በራስ የሚደረግ ቁጥጥር ነው። በራስ ሲባል እያንዳንዱ ራሱን ይቆጣጠራል ለማለት ሳይሆን፤ በአንድ ኢንዱስትሪ የተሰማሩ አካላት በሚያቋቁሙት ማህበር ነው። ለምሳሌ የአዲስ አበባ ጸጉር አስተካካዮች ማህበር አቋቁመው፣ የማህበሩ አባላት የሚያቀርቡትን የፀጉር ማስተካካል አገልግሎት ሊቆጣጠሩ ይችላሉ። በፀጉር ተስተካካዮች የሚቀርቡ አቤቱታዎችን የመዳኘት ስልጣን ሊኖራቸው ይችላል፣ በአባሎቻቸው ላይ።

ከዚህ በላይ ያሉትን መሳሪያዎች ከተለያዩ መመዘኛዎች መገምገም ይችላል። ውድድርን ከመገደብ፣ ነጻነትን ከመገደብ አንጻር፣ ከበጣም ገዳቢው ተነስተን ወደ ላላ ያለው ብናደራጃቸው፣ አንደኛው የፈቃድ ሥርዓት ነው። የመጨረሻው ደግሞ መረጃ የማቅረብ ግዴታ ይሆናል። ስለሪጉላቶሪ መሳሪያዎች ይህንን ካልን የሃገራችንን የብሮድካስቲንግ አዋጅ ዋና ዋና ክፍሎች እንመልከት።

የአዋጁ መግቢያ

የአዋጁ መግቢያ አስገዳጅ ባይሆንም አዋጁን ለመረዳትና ለመገምገም ይረዳል። አዋጁ እንደሚከተለው ይነበባል፤

“የብሮድካስት አገልግሎት ኢንፎርሜሽን ትምህርትና የመዘናኛ ፕሮግራም ለሕዝብ በማቅረብ ለአንድ አገር ፓለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ ሚና የሚጫወት በመሆኑ፤

የብሮድካስት አገልግሎት በሕገመንግስቱ የተረጋገጡ ሃሳብን በነፃ የመግለፅ፣ መረጃ የማግኘት፣ የመምረጥ፣ የመመረጥና የመሳሰሉትን መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና ስለሚጫወት፤

ውስን የአገር ሃብት የሆነውን የሬዲዮ ሞገድ በአግባቡ እና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ መዋሉን ማረጋገጥ በማስፈለጉ፤

የብሮድካስት አገልግሎት በመስጠት ስራ ላይ የሚሰማሩ ሰዎችን መብትና ግዴታ በግልጽ መወሰን አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤…የሚከተለው ታውጇል”

 

ፈቃድ የማውጣት ግዴታ

በአዋጁ አንቀፅ 18 መሠረት “ማንኛውም ሰው ከባለሥልጣኑ የብሮድካስት ፈቃድ ሳይሰጠው “በብሮድካስት አገልግሎት” ሥራ ላይ መሰመራት አይችልም። አንድ ባለፈቃድ በአንድ ፈቃድ ከአንድ ማሰራጫ ጣቢያ በላይ ማቋቋም አይችልም”። የብሮድካስት አገልግሎት ማለት ምንድን ነው? በአንቀጽ 2 መሠረት የብሮድካስት አገልግሎት ማለት “ሕዝብን ለማስተማር፣ ለማሳወቅ ወይም ለማዝናናት የሚከናወን የሬዲዮ ወይም የቴሌቪዥን ሥርጭት አገልግሎት ነው”። አዋጁ በአንቀጽ 16 የብሮድካስት አገልግሎት አይነቶችን እና የፈቃድ አይነቶችን ይዘረዝራል።

አስቀድሞ ፈቃድ የማውጣት ግዴታ ለምን?

ፈቃድ የማውጣት ግዴታ አንደኛው የሪጉላቶሪ መሳሪያ እንደሆነ በመግቢያው ተመልክቷል። እንዲሁም ፈቃድ የማውጣት ግዴታ ከሌሎች የሪጉላቶሪ መሳሪያዎች አንፃር ስንመለከተው፤ ውድድርንና ነፃነትን በላቀ ደረጃ የመገደብ ውጤት አለው። በመሆኑም ግልጽ የሕዝብ ጥቅምን ለማራመድ እስካልሆነ ድረስ፣ ፈቃድ የማውጣት ግዴታ ተመራጭ መሳሪያ አይደለም። ጥያቄው የብሮድካስት አገልግሎትን አስመልክቶ ምን ዓይነት ግልጽ የሕዝብ ጥቅምን ለማራመድ ነው ፈቃድ የማውጣት ግዴታ በአዋጁ የተካተተው?

መልሱን በከፊል በአዋጁ መግቢያ እናገኘዋለን። በመግቢያው እንደተገለጸው አዋጁ ካስፈለገበት ምክንያት አንደኛው፤ “ውስን የአገር ሃብት የሆነውን የሬዲዮ ሞገድ በአግባቡ እና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ መዋሉን” ለማረጋገጥ ነው። ቁልፍ ሃሳቦቹ የሬዲዮ ሞገድ ውስንነት እና የሬዲዮ ሞገድ የአገር ሃብት መሆን ናቸው። ልክ እንደ ውሃ። የውሃ ሃብቶቻችን የአገር ሃብት ናቸው። እንዲሁም ብዙ ፈላጊና ጥቅም ቢኖራቸውም፣ ውስን ናቸው። በመሆኑም ባልተቀናጀ የሃብት አጠቃቀም የሃብት መቆራቆዝና መጥፋትን ለማስቀረት፣ ውሃ የመጠቀም መብትን በፈቃድ ሥርዓት በማደላደል የውሃ ሃብታችን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለላቀ አገራዊ ፍሬ እንዲውሉ ማድረግ ያስፈልጋል። በተመሳሳይ መልኩ ውስን የሬዲዮ ሞገድ ነው አገሪቱ ያላት። በመሆኑም ይህ የሬዲዮ ሞገድ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለላቀ አገራዊ ጥቅም እንዲውል ለማድረግ የፈቃድ ሥርዓቱን ይህን ሃብት በማደላደል መጠቀም ያስፈልጋል። በእርግጥ በመግቢያውም እንደተገለፀው ለአዋጁ መውጣት ሌሎች ምክንያቶችም ቢኖሩ፣ እነዚህ ምክንያቶች ግን የፈቃድ ሥርዓቱ ለምን እንዳስፈለገ አያብራሩንም። በሌላ አገላለጽ ሌሎችቹን የአዋጁን ዓላማዎች ለማሳካት፣ የፈቃድ ሥርዓት አያስፈልግም። የፈቃድ ሥርዓት ያስፈለገበት ምክንያት ውስኑን የሬዲዮ ሞገድ ለላቀ ፍትሃዊ አገራዊ ጥቅም መዋሉን ለማረጋገጥ ነው። ያለ ማእከላዊ የፈቃድ ሥርዓት ውጤቱ የኮመንስ ትራጄዲ ተብሎ የሚጠራው ነው።

የፈቃድ ሥርአቱ ከሞገድ አጠቃቀም ጋር እንደሚያያዝ የሚያሳዩን ሌሎች የአዋጁ ድንጋጌዎች የሚከተሉት ናቸው። የብሮድካስት ፈቃድን ለማግኘት በማንኛውም ጊዜ ማመልከቻ ማስገባት አይቻልም። ለምሳሌ ውስን የውሃ ሃብት ቢኖረንም እና ይህንንም በቅንጀት መጠቀም ቢገባም፣ ውሃ የመጠቀም ማመልከቻን በማንኛውም ጊዜ ማስገባት ይቻላል። በሁሉም ቦታ በሚባል ደረጃ የውሃ ሃብት ስላለን። ነገር ግን የሬዲዮ ሞገዳችን እጅግ በጣም ውስን ነው። ስለዚህ ቀድሞ የመጡ ብቻ ወስደው ሊጨርሱት ይችላሉ። በዚህም ፍትሃዊነትን እና የላቀ አገራዊ ፍሬን ማረጋገጥ አይቻልም። በመሆኑም የብሮድካስት ፈቃድ የሚሰጠው ፣ በተለያዩ ጊዜዎች ሪጉሌተሩ ውስን የሬዲዮ ሞገዶችን ለይቶ ፈቃድ መውሰድ የሚፈልጉትን ሲጋብዝ ብቻ ነው። ይህን አባባል የሚያረጋግጡልንን የሚከተሉትን የአዋጁን ድንጋጌዎች ማየት እንችላለን።

 • ባለሥልጣኑ አመልካቾችን ሰፊ ስርጭት ባለው ጋዜጣ ወይም በሌሎች መገናኛ ብዙኃን በሚገለፅ ማስታወቂያ ይጋብዛል። ማስታወቂያው ለመፍቀድ የታሰበውን የብሮድካስት አገልግሎት ዓይነት፣ አገልግሎቱ የሚሸፍነውን አካባቢ፣ዝግጁ የሆነውን የሬዲዮ ሞገድ፣ የማመልከቻ ማቅረቢያውን ጊዜና ቦታ፣ የፈቃዱን ክፍያና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎችን መያዝ አለበት። በብሮድካስት አገልግሎት ስራ ላይ መሰማራት የሚፈልግ ሰው በዚህ አንቀፅ መሠረት በሚወጣው ማስታወቂያ በሚጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በባለሥልጣኑ የተዘጋጀውን የፈቃድ ማመልከቻ ቅፅ ሞልቶ ማቅረብ አለበት። የመንግስትና የማህበረሰብ ብሮድካስት አገልግሎት አመልካች በማናቸውም ጊዜ ለባለሥልጣኑ የፈቃድ ጥያቄ ሊያቀርብ ይችላል።
 • ማንኛውም ፈቃድ እንዲሰጠው ማመልከቻ ያቀረበ ሰው፣ የፋይናንስ አቅሙንና ምንጩን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሕጋዊ ማስረጃ ካላቀረበ፤ ዝርዝር የፕሮጀክት ጥናት ሰነድ ካላቀረበ ወይም፤ በአንቀፅ 23 መሠረት ፈቃድ የማይሰጠው አካል ከሆነ፤ በዝርዝር ማጣራት ሳያስፈልግ ማመልከቻው ውድቅ ይሆናል።
 • ባለሥልጣኑ የአመልካቾችን ብቃት ለመመዘን የሚያስችለው ዝርዝር መስፈርት ያወጣል። መስፈርቱ የሚከተሉትን ያካትታል፤ አገልግሎቱን ለመስጠት የአመልካቹ የፋይናንስ አቅም ተአማኒነትና ብቃት፣ በአመልካቹ ፕሮጀክት የተዘረዘሩ መሳሪያዎችና ቴክኖሎጂዎች አገልግሎቱን ለመስጠት ያላቸው ብቃት፣ አመልካቹ አገልግሎቱን ለመስጠት ያለው ድርጅታዊ ብቃት፣ እውቀትና የስራ ልምድ፣ በአመልካቹ የቀርበው የፕሮግራም ይዘትና በፕሮግራሙ የተካተቱ ማኅበራዊ ፍላጎቶች፣ እና ለአገልግሎቱ የተመደበው የስርጭት ጊዜ።

ከዚህ በላይ የተቀመጡት የአዋጁ ድንጋጌዎች እንደሚያሳዩት፤ የፈቃድ ሥርዓቱ ዓላማ እና አስፈላጊነት ከሬዲዮ ሞገድ ውስንነት ጋር የሚያያዝ ነው።

ሬዲዮ ሞገድ የማይጠቀሙ ብሮድካስተሮች ለምን ፈቃድ ያወጣሉ?

ከዚህ በላይ ያለው ማብራሪያ እንደሚያሳየው የፈቃድ ሥርዓቱ ያስፈለገበት ውስን የሬዲዮ ሞገድን ለላቀ ፍትሃዊ ሃገራዊ ጥቅም እንዲውል ማድረግ ነው። ይህ የሚያስነሳው ጥያቄ ሬዲዮ ሞገድ የማይጠቀሙ ብሮድካስተሮች ለምን ፈቃድ እንዲያወጡ ይገደዳሉ የሚል ነው? ልብ በሉ ጥያቄው እነዚህ ዓይነት ብሮድካስተሮች ለምን ሌላ ዓይነት ቁጥጥር ይደረግባቸዋል አይደለም። ወይም ለምን በአዋጁ ተካተቱ አይደለም። የቁጥጥር ስራ ከፈቃድ ውጭ ባሉ ሌሎች መሳሪያዎች ሊከወን ይችላል። እንዲሁም ከሬዲዮ ሞገድ ውስንነትና አገራዊ ሃብትነት ውጭ ያሉ ሌሎች ጉዳዮች ለአዋጁ መውጣት እንደ ምክንያትነት በመግቢያው ቢገለጹም፣ እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካት ግን ፈቃድን እንደ መሳሪያ መጠቀም አስፈላጊ አይደለም።  ይህ ሆኖ እያለ ሬዲዮ ሞገድን የማይጠቀሙትንም ፈቃድ አውጡ ማለት፣ በመግቢያው እንደተገለጸው ውድድርን እና ነጻነትን አላግባብ የሚገድብ ነው። እንዲሁም የማይገባ ስልጣንን ለሪጉሌተሩ በመስጠት ለኪራይ ሰብሳቢነት እንዲጋለጥ ማድረግ ነው።

ለመሆኑ ሬዲዮ ሞገድ የማይጠቀሙ ብሮድካስተሮች ፈቃድ እንዲያወጡ ይገደዳሉ ወይ? አዋጁን እንመልከተው። በተለይ የፈቃድ አይነቶች ተብለው የተገለፁትን። በአዋጁ መሠረት ሰባት የፈቃድ አይነቶች አሉ። በተጨማሪም ሪጉላቶሪ ባለሥልጣኑ ተጨማሪ የፈቃድ አይነቶችን በማንኛውም ጊዜ ሊያስተዋውቅና ሊተገብር ይችላል። ሰባቱ የፈቃድ አይነቶች የሚከተሉት ናቸው።

 • ከምድር ወደ አየር ነፃ የሬዱዮ ብሮድካስት አገልግሎት
 • ከምድር ወደ አየር ነፃ የቴሌቪዥን አገልግሎት
 • በሳተላይት አማካይነት የሚሰራጭ የሬዲዮ ብሮድካስት አገልግሎት
 • በሳተላይት አማካይነት የሚሰራጭ ቴሌቪዥን ብሮድካስት አገልግሎት
 • በሳተላይት አማካይነት በክፍያ ለደንበኞች የማድረስ ብሮድካስት አገልግሎት
 • የውጭ ፕሮግራሞችን በመቀበል ለደንበኞች በክፍያ የማድረስ ብሮድካስት አገልግሎት
 • በኬብል አማካይነት የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለክፍያ ለደንበኞች የማድረስ ብሮድካስት አገልግሎት

ከዚህ በላይ ያሉት የፈቃድ ዓይነቶች የሚያሳዩት ፈቃድ የሚያስፈልገው የሬዲዮ ሞገድ የሚጠቀሙ ብቻ ሳይሆኑ ሳተላይትና ኬብል የሚጠቀሙትንም ያካትታል። የፈቃድ ሥርዓት ያስፈለገበት ሬዲዮ ሞገድ ጋር የሚያያዝ ሆኖ እያለ፣ የተዘረጋው የፈቃድ ሥርዓት ግን ሌሎች ዓይነት ቴክኖሎጂዎችንም ያካትታል። ልብ በሉ ሳተላይትና ኬብል የሚጠቀሙ በፍፁም ምንም ዓይነት ፈቃድ አያውጡ እያልኩ አይደለም። አግባብነት ያለውን የፈቃድ ዓይነት እንዲያወጡ ሊገደዱ ይችላሉ፣ መሆንም አለበት። ለምሳሌ የንግድ ፈቃድ።

ብሮድካስት ምንድን ነው?

ሌላው የአዋጁ ችግር፣ በተለይ ደግሞ የፈቃድ ሥርዓቱን ያለአግባብ እንዲሰፋ ያደረገው፣ በአዋጁ የተቀመጠው የብሮድካስት አገልግሎት ትርጉም ነው። በአንቀጽ 2 መሠረት የብሮድካስት አገልግሎት ማለት “ሕዝብን ለማስተማር፣ ለማሳወቅ ወይም ለማዝናናት የሚከናወን የሬዲዮ ወይም የቴሌቪዥን ስርጭት አገልግሎት ነው”። የዚህ ትርጉም አንደኛው ችግር ብሮድካስት አገልግሎትን ከአገልግሎት መሰረታዊ ባህሪ ሳይሆን ከዓላማው ጋር ማገናኘቱ ነው። ማስተማር፣ ማሳወቅ፣ እና ማዝናናት። አንደኛ ሌሎች ዓላማዎችም ሊኖሩት ይችላሉ። ለምሳሌ ማሳመን።

ሁለተኛ፣ ዓላማው አገልግሎቱን በትርጉም ለመለየት መዋል አይገባውም። በእርግጥ አንዳንዴ እንግዳ የሆኑ ነገሮችን ለማስረዳት ስንል የተለያዩ ነገሮችን እንጠቀማለን። ለምሳሌ ወንበር ማለት አንድ ሰው አረፍ ለማለት፣ ሲቆም እንዳይደክመው፣ ቁጭ የሚልበት ነው። ሙዝ ማለት አንደ ሰው የቪታሚን እና ሌሎች ንጥረነገሮችን ለማግኘት ሲል የሚበላው ነው። ነገር ግን ዱባም ቪታሚን እና ሌሎች ንጥረነገሮችን ያስገኝልናል፣ ከበላነው። በሌላ መልኩ ሙዝን አድርቆ መኪናው ውስጥ ለጌጥ ያንጠለጠለን ሰው፣ አይ ሙዝ አይደለም ምክንያቱም አልበላኸውም አይባልም። 

ሶስተኛ፣ ማስተማር፣ ማሳወቅ፣ እና ማዝናናት የሚባለው አባባል ሌሎች ዓላማዎችን ግምት ውስጥ የማያስገባ ነው። ለምሳሌ ትርፍ ማግኘት። ድርጅቱ ዓላማው ትርፍ ማግኘት ነው። ለዛ ደግሞ መረጃዎችን በተለያየ ቅርጽ ያስተላልፋል። ሸማቹ ወይም ተጠቃሚው ወይም አድማጩ ወይም ተመልካቹ፣ ተማረበት፣ አወቀ፣ ወይም ተዝናና የሱ ጉዳይ አይደለም። የሱ ጉዳይ ተመልካችና አድማጭ ማግኘቱ ነው። በዚህ ደግሞ በክፍያ ወይም በማስታወቂያ ገቢና ትርፍ ማግኘቱ ነው ዓላማው። ያለትርፍ የሚሰሩ ብሮድካስተሮች እንዳሉ ሆኖ።

አራተኛ፣ ማስተማር፣ ማሳወቅና ማዝናናት የሚለው አባባል፣ ሪጉላቶሪ ባለሥልጣኑ ሰፊ ስልጣንን እንዳለው ሆኖ እንዲሰማው ያደርጋል። ለምሳሌ፣ ፕሮግራምህ አያስተምርም፣ አያሳውቅም፣ ወይም አያዝናናም፣ ስለዚህ ፈቃድ አይሰጥህም ወይም ፈቃድህ ተቀምቷል። ባጭሩ የብሮድካስት አገልግሎት መተርጎም የነበረበት፣ ከአገልግሎቱ መሰረታዊ ባህሪ ነው። መረጃን በቴሌቪዥን እና ሬዲዮ ማሰራጨት።

 

እረ ለመሆኑ የፈቃድ ቅድመ ሁኔታዎቹ ከዓላማው ጋር የሚጣጣሙ ናቸው?

ፈቃድ ለማግኘት የሚያስፈልጉ ጉዳዮች ከዚህ በላይ በከፊል ተጠቅሰዋል። ሁልጊዜ የሚያስፈልግ ባይሆንም በልዩ ምክንያት የሕዝብ ጥቅምን ለማስከበር ሲባልና ሌላ አማራጭ ሳይኖር ሲቀር በልዩ ሁኔታ በሕግ ሊዘረጋ ይችላል። ከላይ እንደተገለፀው ውስን የሬዲዮ ሞገድን ለላቀ ፍትሃዊና አገራዊ ጥቅም ለማዋል ሲባል የሬዲዮ ሞገድን በፈቃድ ማደላደል አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ አንደኛው የአዋጁ ድንጋጌ እንዲህ ይነበባል፤ “ማንኛውም ፈቃድ እንዲሰጠው ማመልከቻ ያቀረበ ሰው፣ የፋይናንስ አቅሙንና ምንጩን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሕጋዊ ማስረጃ ካላቀረበ፤ በዝርዝር ማጣራት ሳያስፈልግ ማመልከቻው ውድቅ ይሆናል”።

የፋይናንስ አቅሙን እና ምንጩን ማረጋገጥ ለምን አስፈለገ? አሁንም አገራዊ ውስን ሃብትን ለላቀ ፍትሃዊና አገራዊ ጥቅም ለማዋል ሲባል የፋይናንስ አቅሙን መወሰን ይገባል የሚል ሃስብ ሊቀርብ ይችላል። ምን ዓይነት የፋይናንስ አቅም ነው እንደቅደመ ሁኔታ የተቀመጠው? ይሄ በባለሥልጣኑ በዝርዝር እንደሚወሰን ተገልጿል። እንዲሁም ለፈቃድ ከሚቀመጡ ቅድመሁኔታዎች አንደኛው የገንዘብ አቅም እንደሆነ ተገልጿል። ነገር ግን ፈቃድ ሥርዓትን መዘርጋት ከሕዝብ ጥቅም አኳያ አስፈላጊ ቢሆንም እንኳን፣ ቅድመሁኔታዎች ሁሉ ለዓላማው አስፈላጊ መሆን አለባቸው። ለሁሉም ፈቃድ የገንዘብ መጠን እና አቅም እንደ ቅድመሁኔታ መቀመጥ የለበትም።

ጥያቄው የሬዲዮ ሞገድን ለላቀ ፍትሃዊና አገራዊ ጥቅም ለማዋል፣ አመልካቹ የተወሰነ የገንዘብ መጠንን እንዲያሟላ እና ምንጩንም እንዲገልጽ ማድረግ ለምን አስፈለገ? በተለይ ደግሞ ያለምንም ዝርዝር ምርመራ ወዲያው ማመልከቻውን ለመጣል እንዲውል ማድረግ ለምን አስፈለገ? አንዳንድ አመልካቾች ፈቃዱን ወስደው በአቅም ማነስ ምክንያት ሌላ ሰው ሊጠቀምበት የሚችልን ፈቃድ ይዘው እንዳይቀመጡ ማድረግ አንዱ ዓላማ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በቂ ድርጅታዊ አቅም፣ ሙያ፣ መሳሪያዎች እንዳሉት ማስረዳት አለበት የሚሉት ድንጋጌዎችም ከገንዘብ አቅሙ ጋር ተያያዥ ተደርገው ይወሰዳሉ። ዋናው ጥያቄ፤ ይህ ዓላማ ተገቢ ነው ቢባልም ከዚህ ያልከበደ ቅደመሁኔታ አማላውን ሊያሳካው አይችልም ነበር ወይ? ለምሳሌ ፈቃዱን ሰጥቶ ለተወሰነ ጊዜ ጠብቆ ፈቃዱን በተባለው መጠን ካልተጠቀመበት ሰርዞ ለሌላ መስጠት ይቻላል። ለምን የባለሥልጣኑን እና የቦርዱን ጊዜ ያባክናል? ለዚህ ደግሞ ስራ በተባለው ጊዜ የሚጀመር መሆኑን የሚያረጋግጥ ዋስ እንዲያመጣ ማድረግ ይቻላል። ስራውን ካልጀመረ፣ ዋሱን በመውሰድ ወይም በመጠየቅ ባለሥልጣኑ ያጣውን ጊዜና የአየር ሞገዱ ለሌላ አመልካች ተሰጥቶ ቢሆን ኖሮ ይገኝ የነበረውን እና የታጣውን አገራዊ ጥቅም ለመካስ ማዋል ይቻላል።

ችግሩን የሚያከፋው ለምሳሌ የማሰራጫ መሳሪያዎችን መውሰድ እንችላለን። የማሰራጫ መሳሪያዎች ብቻቸውን ዋጋ የላቸውም። ያለ ብሮድካስቲንግ ፈቃድ። ስለዚህ አንድ ድርጅት፣ እንዴት ብሎ ነው ብሮድካስቲንግ ፈቃድ ሳይኖረው፣ የብሮድካስቲንግ መሳሪያዎችን እንዲኖሩት የሚፈቀደው። እነዚህ መሳሪያዎች ገዝቶ ፈቃዱን ባያገኝስ? ፈቃድ ላላቸው ሰዎች መልሶ ቢሸጠውም እንኳን በገዛበት ዋጋ አይሸጠውም። እንዲሁም አንድ ድርጅት ፈቃድ ሳያገኝ በፊት እንዴት ነው ባለሙያዎችን ሊቀጥር የሚችለው? ቀጥሮ ፈቃድ ባያገኝ እኮ በነፃ ደመዎዝ እንዲከፍል፣ ካሳ እንዲከፍል ሊደረግ ይችላል። እንዲሁም አንድ የብሮድካስት ድርጅት ፈቃዱን ሳያገኝ በፊት እንዴት ብሎ ነው ገንዘብ ሊያገኝ የሚችለው። ገንዝብ የሚገኘው በብዙ መልኩ ነው። የተወሰኑ ድርጅቱ መስራቾች አስቀድመው የተወሰነ ገንዘብን በማዋጣት። ገንዘቡ ስለተዋጣ ብቻ ስራው አይጀመርም። ገንዘቡ ተዋጥቶ፣ ፈቃድ መገኘት አለበት። ገንዘቡ ተዋጥቶ፣ ባለሥልጣኑ አመልካቾችን ሳይጋብዝ አመታት ቢሞላውስ። ገንዘቡ ያለምንም ስራ እንዲቀመጥ እያደረግን አይደለም። ደግነቱ እንኳን ብሮድካስቱ አመልካቾችን ሳይጋብዝ ይቅርና ቢጋብዝም፣ ምን ዓይነት ውሳኔ እንደሚሰጥና በምን ያህል ጊዜ ውሳኔ መስጠት እንዳለበት ስለማይታወቅ፣ ማንም ገንዘቡን መድቦ የብሮድካስት ድርጅት አያቋቁምም። ሌላው የገንዘብ ምንጭ የባንክ ብድር ነው። ችግሩ የትኛው ባንክ ነው የብሮድካስት ፈቃድ ሳይኖር ገንዘብ የሚያበድረው።

ማብራሪያውን በሚገባ ከተከታተልነው የዚህ ቅድመሁኔታ ጠንቅ የከፋ ነው። ጠንቁ አንዳንድ አካላትን የሚጠቅም ነው። በቂ ገንዘብ ያላቸውን ሃብታሞች የሚጠቅም ነው። ሁለተኛ ሪጉላቶሪ ተቋሙን ለኪራይ ሰብሳቢዎች እንዲጋለጥ የሚያደርግ ነው። ምክንያቱም ኪራይ ሰብሳቢዎች ባለሥልጣኑ አመልካቾችን መቼ ሊጋብዝ እንዳሰበ ለማወቅና አስቀድመው ለመዘጋጀት፣ ጊዜያቸውን እና ገንዘባቸውን ደጅ በመጥናት እንዲያውሉት ያደርጋል። ደጅ በመጥናት የሚገኝ ጥቅም ፍትሃዊ አይደለም። ለሌላ ሊሰጥ የሚችልን ጥቅም አስቀድሞ በማወቅና በመዘጋጀት ስለሚወሰድ። እንዲሁም በማንኛውም ጊዜ ባለሥልጣኑ አመልካቾችን ቢጋብዝ፣ በቀላሉ የሚፈለገውን ገንዘብ አዋጥተው በተባለው ጊዜ ማስገባት የሚችሉት ጥቂት ብዙ ገንዝብ ማዋጣት የሚችሉ ናቸው። ማለትም የብሮድካስቲንግ ስራ በጥቂት ሃብታሞች እንዲያዝ ያደርጋል። ለሃሳብ ብዝሃነትና የፓለቲካ ስልጣንን ከቀበኞች ለመጠበቅ ሲባል፣ ሚዲያ ከፓለቲካ እና ከገንዘብ ተጽእኖ መጽዳት አለበት። በኔ እምነት የብዙሃን ሚዲያዎች በተለይ ደግሞ ውስን አገራዊ የሬዲዮ ሞገድ ከፓለቲካ ተጽእኖ በጸዱ የሕዝብ ተቋማት ወይም ለትርፍ የማይሰሩ ማህበራትና ድርጅቶች ቢያዝ ይሻላል። ፓለቲካ ስልጣን እና ገንዘብ እንዱ ሌላውን እየጨመረ፣ የሃሳብ ብዝሃነትን ለማጥፋት የፓለቲካ ስልጣንን ለሕዝባዊና ፍትሃዊ ጥቅም ሳይሆን ለጠባብ ጥቅም እንዲውል ስለሚያደርግ። ይህ ግን ራሱን የቻለ ሰፊ ማብራሪያ ያስፈልገዋል። ወደ ያዝኩት ዓላማ ስሄድ የፈቃድ ሥርዓቱ ውስን የሬዲዮ ሞገድን ለላቀ ፍትሃዊና አገራዊ ጥቅም ለማዋል አስፈላጊ ሆኖ እያለ፣ ማመልከቻው ተቀባይነት እንዲያገኝ ወይም ደግሞ ማመልከቻው ተመርምሮ ፈቃድ ለማስገኘት፣ የገንዘብ፣ የድርጅታዊ አቅም፣ እና በቂ መሳሪያዎችን እንዳለው ማስረጃ እንዲያቀርብ መጠየቅ፣ አንድ እንቁላል ያለውን ሰው እንቁላሉን ለማስፈልፈል ፈቃድ እንዲያገኝ ሲባል፣ መጀመሪያ አራት ዶሮዎችን እንዳሉህ ማስረጃ እና የዶሮዎቹን ምንጭ ምን እንደሆነ አሳይ ብሎ መጠየቅ ነው።

ተጨማሪው ችግር መሳሪያዎችን ሆነ ገንዘብ አቅምን አስቀድሞ እንዲያሳይ ማድረግ ሰዎች ወደ ዲስኦነስት አስራር እንዲገቡ ማበረታታት ነው። ጧት ባንክ አስገብቶና የባንክ ማረጋገጫ ደብዳቤ አጽፎ ማታ ገንዘቡን ለባለቤቶቹ መመለስ። ጧት የብሮድካስቲንግ መሳሪያዎችን ተውሶና የባልስልጣኑ ሰዎችን ይህን ከተመለከቱ በኋላ ማታ ለባለቤቶቹ መመለስ። እንዲህ ዓይነት አስራር በብዙ መስኮች የተለመዱ ሆነዋል። መዋእለ ህጻናት ለመክፈት ፈቃድ ለማግኘት የተወሰኑ የልጆች መጫወቻ አይነቶች ያስፈልጋሉ። ስለዚህ ከሌላ ተውሶ ፈቃድ ሰጪዎቹ ካዩት በኋላ፣ ለባለቤቶቹ መመለስ። የሪልስቴት ፈቃድ ለማግኘት 25 ሚኒዮን ብር ፈቃድ ያስፈልጋል። ከየትም ሰብስቦ፣ አስገብቶ፣ ደብዳቤ ካጻፉ በኋላ መልሶ ማውጣት። እንዲህ ዓይነት ግዴታዎችና አሰራሮች ዲስኦነስት አስራርን ይወልዳሉ። ዲስኦነስት አስሮች ደግሞ ራሳቸውን ያራባሉ። የቁልቁለት መንገድ ነው። ሁለተኛ፣ ሁሉም ሰው ዲስኦነስት ስራ ላይ ለመሰማራት ፈቃደኛ አይደለም። በመሆኑም ይህ አስራር በንግድና ብሮድካስቲንግ ስራዎች ኦነስት ሰዎች በዲስኦነስት ሰዎች ተገፍተው እንዲወጡና ዲስኦነስቶቹ እንዲቆጣጠሩት ያደርጋል።

የብሮድካስተሮች መብትና ግዴታዎች

ማንኛውም ፕሮግራም “የተለያዩ አመለካከቶችን በማንጸባረቅ ሕብረተሰቡን በአጠቃላይ እንዲያገለግል ሚዛናዊ ሆኖ መቅረብ አለበት”። ይሄ አባባል ሦስት የሚቀራረቡ ነገር ግን አንድ ያልሆኑ ሃሳቦችን ያንፀባርቃል። 

አንደኛ፤ የፕሮግራሙ ይዘት የተለያዩ አመለካከቶችም ማንፀባረቅ አለበት። ሁለተኛ፤ እንዲሁም ፕሮግራሙ ሕብረተሰቡን በአጠቃላይ እንዲያገለግል መሆን አለበት። ሦስተኛ ፕሮግራሙ ሚዛናዊ ሆኖ መቅረብ አለበት።

አንደኛውን እና ሶስተኛውን ግዴታዎችን ማገናኘት ይቻላል። ፕሮግራሙ በይዘቱ የተለያዩ አመለካከቶችን ማንፀባረቁ ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህ አመለካከቶችም ሚዛናዊ ሆነው መቅረብ አለባቸው። የሚዛናዊነት ጉዳይ ሁለት ነገሮችን ሊመለከት ይችላል። አንደኛው የተለያዩ አመለካከቶች በፕሮግራሙ ይዘት የተወከሉበት አንጻራዊ መጠን የተመጣጠነ መሆን አለበት የሚል መልእክት ይሆናል። በዚህ ረገድ ሚዛናዊነቱ እንዴት እንደሚለካ ግልጽ አይደለም። ሚዛናዊ የሚባለው የተለያዩ አመለካከቶች እኩል ጊዜ ሲሰጣቸው ነው? ያ እንዴት ሊሆን ይችላል? አንድ ሰው የሚያራምደው አመለካከት እንዴት ከሌሎት አመለካከቶች ጋር እኩል ጊዜ ሊሰጠው ይችላል። ወይስ የተለያዩ አመለካከቶች የሚሰጣቸው ጊዜ አመለካከቶቹን ከሚያራምዱት ሰዎች ጋር መመጣጠን አለበት? ይህስ ቢሆን አንድን አመለካከት የሚያራምዱ ሰዎች ስንት እንደሆኑ እንዴት ማወቅ ይቻላል።  ሁለተኛ የሚዛናዊነት ጥያቄ ከፕሮግራሙ አቀራረብ ጋር ሊያያዝ ይችላል። ለምሳሌ አቅራቢው የተለያዩ አመለካከቶችን አስመልክቶ የሚያሳየውና የሚያሰማው እንቅስቃሴና ድምፀት። ያ ማለት ብሮድካስተሩ ሰርቬይ መስራት ሊኖርበት ነው? እረ ለመሆኑ የተለያዩ አመለካከቶችን እንዴት ማንፀባረቅ ይቻላል በአንድ ፕሮግራም? ወይስ ጉዳዩን አስመልክቶ ሌሎች አመለካከቶች አንዳሉ ጠቁሞ ማለፍ ይችላል? አመለካከት ሲባልስ ምንድን ነው? አስተያየት? ለምሳሌ ሞቶ ስለተገኘ ሰው የሚቀርብ ዘጋቢ ፕሮግራም፣ የተለያዩ ሰዎች ሟቹ እንዴት እንደሞተ (ተመርዞ፣ ማጅራቱን ተመቶ፣ ራሱን አጥፍቶ፣ በልብ ድካም፣ አንቆት) የተለያየ አመለካከት ቢኖራቸው፤ እነዚህን ሁሉ ማንፀባረቅ አለበት ማለት ነው?

ፕሮግራሙ ሕብረተሰቡን በአጠቃላይ የሚጠቅም መሆን አለበት ሲባልስ። ለምሳሌ ፀጉራቸው ስለተመለጠ ወንድ፣ ፈት፣ ረጅምና ወፍራም ሰዎች ብቻ የሚጠቅም ፕሮግራም ሊሰራጭ አይችልም ማለት ነው? እረ ለመሆኑ የሚዛናዊነት፣ የተለያዩ አመለካከቶች ማንፀባረቅ፣ እና አጠቃላይ ሕብረተሰቡን መጥቀም የሚባሉ ግዴታዎች የብሮድካስተሮች ግዴታዎችን አድርጎ ለመደንገግ የፓሊሲ መሰረቱ ምንድን ነው? የሬዲዮ ሞገዶችን የሚጠቀሙ ብሮድካስተሮችን አስመልክቶ ምክንያቱ ግልጽ ነው (ድንጋጌው የሚያስነሳቸውና ከዚህ በላይ በከፊል የተቀመጡትና ሌሎች ጥያቄዎች እንዳሉ ሆኖ)። ነገር ግን ሌሎች ብሮድካስተሮችን አስመልክቶ ለምን ይሄ ግዴታ ተቀመጠ። 

የማንኛውም ፕሮግራም “ይዘቱና ምንጩ ትክክል መሆኑ መረጋገጥ አለበት”። ምን መሆኑ ነው የሚረጋገጠው? ትክክል መሆኑ? ይዘቱ ትክክል መሆኑ በምን ያህል መጠን ነው የሚረጋገጠው? በመቶ ፐርሰንት? ይዘቱ ትክክል መሆኑ ከተረጋገጠ ምንጩ ምን እንደሆነ ነው የሚረጋገጠው? ካልተረጋገጠ መሰራጨት የለበትም ማለት ነው? ይሄ የብሮድካስት ስራን የሚያጠብ ወይም የሚያጠፋ አይሆንም ወይ? ብሮድካስተሩ ለማረጋገጥ ተገቢ የሚባለውን እርምጃ ከወሰደ በቂ አይደለም ወይ? ተገቢ የሚባለው እርምጃስ ምንድን ነው? ይዘቱ አመለካከትና አስተያየትን የሚመለከት ከሆነ፣ አመለካከቱና ምንጩ መረጋገጥ አለበት ሲባል ምን ማለት ነው? ፕሮግራሙ ፊልም ወይም ጨዋታ ከሆነ ይዘቱና ምንጩ ምን እንደሆነ እና እንዴት ነው የሚረጋገጠው?

ማንኛውም ፕሮግራም የሰው ልጆችን ስብእና ነፃነት ወይም ስነምግባር የሚፃረር ወይም የሌሎችን እምነት የሚያንኻስስ፤ በመንግስት ጸጥታ፣ በሕዝብ አስተዳደር ወይም በአገር የመከላከያ ሰራዊት የወንጀል ድርጊት የሚፈጽም፤ የግለሰብ፣ የብሔር ብሔረሰብን፣ የሕዝብን ወይም የድርጅትን ስም የሚያጠፋ ወይም በሃሰት የሚወነጅል፤ ብሔረሰብን ከብሔረሰብ የሚያጋጭ ወይም በሕዝቦች መካከል የእርስ በርስ ግጭት የሚያነሳሳ፤ ወይም ጦርነት የሚቀሰቅስ፤ መሆን የለበትም”። የሰው ልጆችን ነጻነት የሚጻረር ፕሮግራም ምን ዓይነት ሊሆን ይችላል? የሰው ልጆች ስነምግባር የሚባል ነገር አለ? “ስም ማጥፋትና በሃሰት መወንጀል፣ ማጋጨት፣ ለግጭት ማነሳሳት፣ የሚቀሰቅስ” ሲባል፣ በፍርድ ቤት አግባብነት ባለው የወንጀል አንቀጽ ጥፋተኛ ያስባለ ፕሮግራም ማለት ነው? ወይስ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ያሉት ስም ማጥፋትና የሃሰት መወንጅልን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች እንዳሉ ሆነው፣ ይሄ በራሱ እንደ አስተዳደራዊና የወንጀል ድንጋጌ ሊወሰድ የሚችል ነው?

“ዜና ከአድልዎ የፀዳ ትክክለኛና ሚዛናዊ መሆን አለበት”። ይሄ ማንኛውንም ፕሮግራም የሚመለከት ሳይሆን፣ ዜናን ነው። ዜና ትክክለኛ፣ ከአድልዎ የፀዳና ሚዛናዊ መሆን አለበት። ይሄ ከላይ ሁሉንም ፕሮግራሞች አስመልክቶ ከተደነገገው በምን ይለያል።

“አገራዊ ስርጭት ያለው በሳምንታዊ ስርጭት ጊዜው ስልሳ ከመቶውን ለአገራዊ ፕሮግራሞች ማዋል አለበት”። አንድ ብሮድካስተር አገራዊ ስርጭት አለው የሚባለው መቼ ነው? አገራዊ ፕሮግራሞች እንዴት ነው የሚለዩት?

“ክልላዊ ስርጭት ያለው በሳምንታዊ ስርጭት ጊዜው ስልሳ ከመቶውን ለክልላዊ ፕሮግራሞች ማዋል አለበት”። አንድ ብሮድካስተር ክልላዊ ስርጭት አለው የሚባለው መቼ ነው? ክልላዊ ፕሮግራሞች እንዴት ይለያሉ? በአንድ ክልል ብቻ የተወሰነን በሳተላይት ወይም በኬብል የሚደረግ ስርጭትን ሪጉሌት ለማድረግ የፌዴራል መንግስቱ ስልጣን የሕገመንግስት መሠረት አለው?

“አካባቢያዊ ስርጭት ያለው በሳምንታዊ ስርጭት ጊዜው ስልሳ ከመቶውን ለአካባቢያዊ ፕሮግራሞች ማዋል አለበት”። ከዚህ በላይ ክልላዊ ስርጭትን አስመልክቶ የተነሱ ጥያቄዎች አስፈላጊው ለውጥ ተደርጎባቸው፣ አካባቢያዊ ስርጭትን አስመልክቶ ስለተደነገገው ሊነሱ ይችላሉ።

“የልጆችን አመለካከት፣ ስሜትና አስተሳሰብ ሊጎዱ የሚችሉና ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያዘነብሉ የሚገፋፋ የሬዲዮና የቴሌቪዥን  ስርጭቶችን ልጆች ሊመለከቱና ሊያደምጡ በሚችሉበት ሰአት ማስተላለፍ የተከለከለ ነው። ከምሽቱ አስራ አንድ እስከ ንጋቱ አስራ አንድ ሰአት ልጆች የሬዲዮና የቴሌቪዥን ስርጭቶችን ሊያዳምጡና ሊመለከቱ አይችሉም ብሎ መገመት ይቻላል”። የዚህን ክልከላ ዓላማ፣ ከክልከላ ባነሰ ግዴታ ማሟላት አይቻልም?

“ማስታወቂያ ከሌሎች ፕሮግራሞች የተለየ መሆኑ በግልጽ እንዲታወቅ ሆኖ መተላለፍ አለበት። በሌሎች ፕሮግራሞች ይዘት ላይ ተፅእኖ ማድረግም የለበትም። የንግድ ማስታወቂያ እውነተኛ የማያሳሳትና ሕጋዊ የንግድ እንቅስቃሴን የሚያመለክት መሆን አለበት። የሌላውን ምርት ወይም አገልግሎት በማጥላላት ወይም በማንኳሰስ ማስታወቂያ ማስተላለፍ የተከለከለ ነው። የስርጭት ጊዜው ከሃያ ደቂቃ ከማይበልጥ በማናቸውም ፕሮግራም ወይም በሕፃናት ፕሮግራም ጣልቃ ማስታወቂያ ማስተላለፍ የተከለከ ነው”። እውነተኛ እንዲሆን በህግ ከተደነገገ፣ በተጨማሪም እንዳያሳስት የሚል ድንጋጌ ለምን አስፈለገ? እውነተኛ ማስታወቂያ ማለትስ ምንድን ነው? “ይሄ ሳሙና ቡግሬን በሚገርም ሁኔታ ቀንሶልኛል” ብየ ብናገር እውነትነቱ እንዴት ይመረመራል? ኮካን እና ፔፕሲን አልፎ ሂያጆችን እያስቀመስኩ፣ የቱን ወደዳችሁት የሚል ብጠይቃቸውና ሁሉም ፔፕሲን ወይም ኮካን ቢሉኝና ይሄን ባስተላልፈው ምንድን ነው ችግሩ? በተጨማሪም እኔ ይህን በማስተላለፌ ከኮካ ወይም ከፔፕሲ ምንም ጥቅም ካላገኘሁ፣ ማስታወቂያ ሊባል ይችላል። ዜና አንባቢው የሚጠቀመው ኮምፒዩተር የአፕል ምርት ቢሆን እና ምልክቱም ዜናዊን ሲያነብ ቢታይ፣ ዜናን እና ማስታወቂያን ተቀላቀለ ሊባል ይችላል? ማስታወቂያን በተመለከተ ከዚህ በላይ ከተቀመጡ ድንጋጌዎች በተጨማሪ አንድ ብሮድካስተር ከቀን የስርጭት ጊዜው ከ20 ፐርሰንት በላዩን ለማስታወቂያ መመደብ አይችልም። እንዲሁም ስፓንሰር ተደርገው ስለሚቀርቡ ፕሮግራሞች አዋጁ ተጨማሪ ድንጋጌዎች አሉት።

ብሮድካስተሩ “ዜናን ጨምሮ ያሰራጨውን ፕሮግራም ለ30 ቀናት ቀርፆ ማስቀመጥ አለበት። በፕሮግራሙ ውስጥ ቀደም ሲል የተቀረፀ ፕሮግራም ወይም ፊልም ተካትቶ ከሆነ አብሮ መቀመጥና በተፈለገ ጊዜ ሊገኝ መቻሉ መረጋገጥ አለበት።” በ30 ቀናት ውስጥ ስለፕሮግራሙ ቅሬታ ከቀረበ፣ ቅሬታው ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ ሪከርዱ ተይዞ ይቆያል። ለቁጥጥር ወይም የቀረበን ቅሬታን ለመመርመር አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፣ ብሮድካስተሩ በራሱ ወጪ የያዘውን ፕሮግራም ለሪጉላቶሪ ባለሥልጣኑ እና ሌሎች አካላት የማቅረብ ግዴታ አለበት። እንዲሁም “ቁጥጥር እንዲደረግ የማሰራጫ ጣቢያውን ክፍት ስለማድረግና የሚጠየቁ ሰነዶችን የማቅረብ ግዴታ” ብሮድካስተሩ ተጥሎበታል።

“ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ በመከሰቱ፣ የተፈጥሮ አደጋ በማጋጠሙ ወይም የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ በመከሰቱ ምክንያት የፌዴራል መንግስቱ ወይም ማንኛውም ክልል የሚሰጣቸውን አስቸኳይ መግለጫዎች በነጻ የማስተላለፍ ግዴታ በብሮድካስተሮች ላይ ተጥሏል።

በሚተላለፉ ፕሮግራሞች መብቴ ተነክቷል ወይም በአግባቡ አልቀረበም ያለ ስው ለጉዳዩ መልስ የመስጠት መብት አለው፣ መልሱን በተመጣጣኝና በተመሳሳይ ግዜ የማስተላለፍ ግዴታ ብሮድካስተሩ አለበት። መብቱ ስለመነካቱ ወይም በአግባቡ ስለመቅረቡ ማነው የሚዳኘው? ተመጣጣኝና ተመሳሳይ ጊዜ የሚለውን ማነው የሚዳኘው?

 • መልስ የመስጠት መብትን ስለማክበር
 • የምርጫ ጊዜ መግለጫዎችን ስለማስተላለፍ

የሪጉሌተሩ ስልጣንና ሃላፊነቶች

ባለሥልጣኑ “የብሮድካስት አገልግሎት ለአገሪቱ ፓለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ተገቢውን አስተዋዕፆ ሊያበረክት በሚችል መልኩ መካሄዱን ያረጋግጣል”። “ተገቢውን አስተዋእፆ” ማለት ምንድን ነው?

ባለሥልጣኑ “ለብሮድካስት አገልግሎቶች ፈቃድ ይሰጣል፣ ያግዳል፣ ይሰርዛል”። በመጀመሪያው የተጠቀሰው ሃላፊነት ወይም ግብ ነው። ፈቃድ መስጠት፣ ማገድ፣ እና መሰረዝ ደግሞ ሃላፊነቱን ለመወጣት መሳሪያ እንጂ ግብ አይደለም። ስለዚህየፈቃድ የመስጠት የማገድ እና የመሰረዝ ስልጣኑን የሚጠቀመው የብርድካስት አገልግሎት “ተገቢውን አስተዋእፆ” እንዲያደርግ ነው። በአዋጁ ላይ የተቀመጡ ግዴታዎችን አለመወጣት፣ ፈቃድን ለማገድ ምክንያት ነው። ብዙ ዓይነት ግዴታዎች ተጥለው የማንኛውም ዓይነት ጥሰት ፈቃድን ለማገድ በቂ ነው ብሎ ማስቀመጥ ተመጣጣኝ አይደለም። ከማገድ ያነሱ ሌሎች ቅጣቶችን መጣል እየተቻል።

ባለሥልጣኑ የብሮድካስት ጣቢያ የሚቋቋምበትን ስፍራና የሽፋን ክልል ከሌሎች የሬዲዮ ኮሚኒኬሽን አገልግሎቶች ጋር አለመጋጨቱን አረጋግጦ ይወስናል። ከዚህ በላይ እንደተገለጸው ይህኛው ሃላፊነት/ስልጣን ከፈቃድ ስልጣኑ ጋር የሚያያዝ ነው።እንዲሁም የሬዲዪ ሞገድ ውስን ስለሆነ እና ለላቀ ፍትሃዊና አገራዊ ጥቅም መዋል ስላለበት ነው የፈቃድ ሥርዓቱ ያስፈለገው። ነገር ግን የብሮድካስት አገልግሎት ትርጉሙ ከሬዲዮና ቴሌቪዥን ስርጭት ጋር የተያያዘ ነው። ነገር ግን የሬዲዮ ሞገድ ለኮሚኒኬሽን አገልግሎቶችም ሊውል ይችላል። ነገር ግን በአንድ ቦታ ያለ ማንኛውም የሬዲዮ ሞገድ ለውስን አገልግሎቶች ብቻ ነው የሚውለው። ያለበለዚያ ስለሚጋጭ ሁሉም አገልግሎቶች በሚፈለገው ልክ ላይቀርቡ ይችላሉ። ይህ ሆኖ እያለ ግን የብርድካስት ባለሥልጣኑ የሬዲዮ ኮሚኒኬሽን አገልግሎቱን አስመልክቶ ስልጣን የለውም። ማድረግ የሚችለው የሬዲዪና የቴሌቪዥን አገልግሎቶች ከኮሚኒኬሽን አገልግሎቶች ጋር እንዳይጋጩ ነው። ከዚህ የምንረዳው የኮሚኒኬሽን አገልግሎቶ ከሬዲዮና ቴሌቨዢን ስርጭት የበለጠ ቅድሚያ ተስጥቶታል። በማንኛውም ሁኔታ። ለመሆኑ የሬዲዮ ሞገደን ለኮሚኒኬሽን ለማዋል አገልግሎትን ሪጉሌት የሚያደርገው ማን ነው?

 • ለብሮድካስት አገልግሎት የሚውሉትን መሳሪያዎች ዓይነትና ደረጃ እንዲሁም የማሰራጫ መሳሪያውን ጉልበት ይወስናል
 • ሕገወጥ ስርጭትን በሚመለከት ቁጥጥር ያደርጋል
 • ለብሮድካስት አገልግሎት በሚመለከተው አካል የተመደበውን የሬዲዮ ሞገድ እቅድ ያዘጋጃል፣ ይፈቅዳል፣ ይቆጣጠራል፣ ያከራያል
 • ስለብሮድካስት አገልግሎት እድገትና መሻሻል ጥናት ያደርጋል፣ አገልግሎቱን የሚመለከቱ መረጃዎችን አጠናክሮ ይይዛል
 • ለተለያዩ የብሮድካስት አገልግሎቶች የቴክኒክ ደረጃዎችን ያወጣል
 • የብሮድካስት መሳሪያዎችን ደረጃ ያወጣል፣ ለመሳሪያዎቹ አስመጪዎች የማረጋገጫ ሰርተፊኬት ይሰጣል፣ አሰራራቸውንም ይቆጣጠራል
 • በብሮድካስት አገልግሎት በሚነሱ ቅሬታዎች ላይ ውሳኔ ይሰጣል
 • የብሮድካስት አገልግሎትን አስመልክቶ መንግስትን በመወከል በአለም አቀፍ ስብሰባዎች ይሳተፋል፣ አገሪቱ የተቀበለቻቸውን ስምምነቶች አፈጻጸማቸውን ይከታተላል
  • የውጭ ጉድይ ሚኒስቴርስ? ኢምባሲዎቻችንስ?
 • የፈቃድ ክፍያዎችን ተመን ያወጣል ይሰበስባል
 • በሚመለከተው አካል ለሚመደበው የሬዲዮ ሞገድ ተገቢውን ክፍያ ይፈጽማል

 

የብሮድካስት ፈቃድ፣ የንብረት ወይስ ግላዊ መብት?

የንብረት መብትና ግላዊ መብት ይለያያሉ። የንብረት መብት ማለት በማንኛውም ሰው ላይ ተፈጻሚ የሚሆን እና ለሌሎች የማስተላለፍ እድሉ ሰፊ ነው። በሌላ በኩል ግላዊ የሚባሉ መብቶች ከአንድ ግለሰብ ጋር የተያያዙ ናቸው። ወደ ሌላ ሰው የመተላለፍ እድላቸው በአንጻሩ ውስን ነው። ለምሳሌ የጥብቅና ፈቃድ ግላዊ መብት ነው ሊባል ይችላል። የኔን ፈቃድ ለሌላ ሰው ላስተላልፍ አልችልም። የብሮድካስት ፈቃድ ምን ዓይነት ፈቃድ ነው?

 

አዋጁ ሰለ ፈቃድ ማስተላለፍ የሚለው ነገር የለም። ነገር ግን ፈቃዱ ስለሚሰረዝበት ሁኔታዎች የተቀመጡ ድንጋጌዎች አሉ። ለምሳሌ ጣቢያው በፍርድ ቤት ትእዛዝ እንዲዘጋ ሲወሰን፣ ወይም ባልፈቃዱ በራሱ አነሳሽነት ስራውን ሲያቆም፣ ወይም ስርጭቱን ያለበቂ ምክንያት ከአንድ ወር በላይ ካቋረጠ ፈቃዱ እንደሚሰረዝ ተደንግጓል። አንድ የብሮድካስቲንግ ድርጅት ባጋጠመው የገንዘብ ችግር፣ ለምሳሌ የበሰሉ እዳዎችን መክፈል ካቃተው በፍርድ ቤት ቀርቦ በንግድ ሕጉ መሠረት መክሰሩ እንዲታወጅ ወይም ደግሞ የመጠበቂያ ስምምነት ሥርዓት ውስጥ እንዲገባ መጠየቅ ይችላል። መክሰሩ የታወጀ ብሮድካስተር፣ ልጦ የተራሰ ጉድጓዱ የተማሰ አይደለም። በተለያየ መልኩ አገግሞ ሊወጣ ይችላል። ነገር ግን ስርጭቱን በገንዘብ እጥረት ምክንያት በማቋረጡ የተነሳ ፈቃዱ የሚሰረዝ ከሆነ፣ አገግሞ የመውጣት እድሉም ዜሮ ሊሆን ይችላል። እገግሞ ባይወጣም፣ ፈቃዱ ከተሰረዘ የሌሎች ንብረቶቹን ዋጋ ዜሮ ያስገባዋል። ከዚህ በፊት እንደተጠቀሰው፣ ያለ ብሮድካስቲንግ ፈቃድ የብሮድካስቲንግ መሳሪያዎች ያላቸው የሁለተኛ ደረጃ ገበያ ዋጋ እጅግ ዝቅተኛ ነው። ይህ በራሱ የብሮድካስቲንግ ስራ ውስጥ የመግቢያውን በር ያጠበዋል። በመሆኑም የብሮድካስቲንግ ፈቃድ እንደ ንብረት መቆጠር ይኖርበታል። መንግስት ሌላን ንብረት ለመውረስ ወይም ለመገደብ ማድረግ የሚጠነቅበት ጥብቅ ሁኔታዎች ለብሮድካስቲንግ ፈቃድም ሊውሉ ይገባል። ፈቃዱን ለመሰረዝ የላቀ ሕዝባዊ ጥቅም ቢኖርም እንኳን፣ ለብሮድካስተሩ ካሳ መስጠት ይገባል።

የብሮድካስቲንግ ፈቃድ እንደ ንብረት ከተወሰደ፣ ለሌላ ሰው ሊተላለፍ ይችላል ማለት ነው። ነገር ግን መጀመሪያውኑ ፈቃድ ማግኘት የማይችል ሰው በሌላ በኩል አውጥቶ በማስተላለፍ መልኩ እንዳይወስድ፣ ፈቃድ ሊያገኙ የማይችሉ ሰዎች የሌላ ሰው ፈቃድን በማስተላለፍ ሊያገኙ እንደማይችሉ ሊደነገግ ይችላል።

አዋጁ በጠቅላላው

ከዚህ በላይ የተለዩ ችግሮችና የሚነሱ በርካት ጥያቄዎች የሚያሳዩት የአዋጁን የጥራት ችግር ነው። እንዲሁም ለባለሥልጣኑ የተሰጡ እጅግ ሰፊ ፈቃደ ስልጣኖች ናቸው። በእርግጥ አንዳንዱ ጉዳዮችን አስመልክቶ ሁሉን ነገር በአዋጁ መዘርዘር ላያስፈልግ ይችላል። ነገር ግን በአዋጅ ባይዘረዘርም በደንብና መመሪያ በዝርዝር ሊደነገጉ ይገባል። አሁን በስራ ላይ ያሉ ደንቦችና መመሪያዎች የባለሥልጣኑን ሰፊ ፈቃደ ስልጣን በመቆጣጠር፣ ግልጽ በማድረግና፣ስልጣኑን አጠቃቀም በመምራት ረገድ ያላቸውን ብቃት ለመገምገም አግባብነት ያላቸውን ደንቦችና መመሪያዎች መለየትና መገምገም ያስፈልጋል። አግባብነት ያላቸው ደንቦችና መመሪያዎች ካልወጡ ግን፣ የአዋጁ ፋይዳ እንደፈቀደ የመስራትን ሕጋዊ ቅርጽ የመስጠት ውጤት ሊኖረው ይችላል። የሕግ የበላይነት መርህ ፋይዳ የሚወሰነው የሕጉ ጥራት ነው።

የዋና ዳይሬክተሩ ደብዳቤ

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ በመግቢያው የተጠቀሰው ደብዳቤ ቢሆንም፣ እገረ መንገዴን አዋጁንም ከዚህ በላይ ባለው መልኩ በከፊል ለማብራራትና ለመገምገም ችያለሁ። ወደ ደብዳቤው ስንመጣ፤

 • በይዘቱና በመንፈሱ መረጃ መጠየቅ ነው
 • መረጃ መጠየቅ በራሱ ችግር የለበትም
 • መረጃው ጥበቃ የሚደረግለት እስካልሆነ ድረስ
 • እሱም ቢሆን ሪጉሌተሩ ለሌላ አሳልፎ እስካልሰጠ ድረስ
 • እንደውም መረጃ መጠየቅ ከሌሎች አማራጭ የሪጉላቶሪ መሳሪያዎች ባነሰ መልኩ ነጻነትን የሚገድብ ነው
 • እንዲሁም ከዚህ በላይ የተገለጹ የብሮድካስተሮች መብትና ግዴታዎችን ለማስከበርና ሪጉላቶሪ ባለሥልጣኑ ሃላፊነቱን ለመወጣት የሚያፈልጉ መረጃዎችን ጠይቆ ካላገኘ እንዴት ነው፣ ብሄራዊና አካባቢያዊ መረጃዎች፣ የትምህርትና የመዝናኛ ፕሮግራሞች፣ የዜና እና የመዝናኛ ፕሮግራሞች፣ የማስታወቂያና የመሠረታዊው የብሮድካስት አገልግሎቱ መመጣጥናቸውን ሊያረጋግጥ የሚችለው? እንዲሁም ብሮድካስተሮች ያለባቸውን ሌሎች ሃላፊነቶችን/ጌዴታዎች ለመወጣት እንዴት ያለመረጃ ይቻላል? የቀረቡ ቅሬታዎች ካሉስ እንዴት ነው ያለመረጃ ውሳኔ ሊሰጥ የሚችለው።
 • በተወሰነ ደረጃ፤ በአጻጻፉ የተነሳ
  • የመዘገብና የማስተላለፍ ግዴታ ያለባቸው ያስመስለዋል። በእርግጥ አዋጁም ቢሆን የመዘገብና የማስተላለፍ ጠቅላላ ግዴታ ባይጥልም፣ በውስን ሁኔታዎች በልዩ ሁኔታ ለዚህ ግዴታ እውቅና ይሰጣል፤
  • እናሳስባለን የሚለው ቃል፣ በተወሰነ መልኩ ደብዳቤው የተጻፈለት ድርጅት ግዴታውን የጣሰ ያስመስለዋል፡፡

ከላይ እንደገለጽኩት ሜዲያ (በተለይ ደግሞ ብዙ ሕዝብን በቀላሉ የሚደርሱ አገልግሎቶች) በገበያና በፓለቲካው ሥርዓት ካላቸው ወሳኝ ሚና (በመግቢያው ተገልጿል) የተነሳ እና የሌሎች አገሮችን ልምድ ግምት ውስጥ በማስገባት በሕዝባዊ ድርጅቶችና ለትርፍ በማይሰሩ ማህበሮችና ድርጅቶች ያለ ፓለቲካና ገንዘብ ተፅእኖ ሊቀርቡ ይገባል። የትምህርት ሥርዓቱም እንዲህ ሊሆን ይገባል ብየ አምናለሁ (የግል እምነት)። ፓለቲካ ሥርዓቱ ዴሞክራሲያዊ እንዲመስል ሳይሆን እንዲሆን። ያለበለዚያ ለሃሳብ አፋኞችና የፓለቲካ ሥልጣን ቀበኞች የተመቸ ይሆናል። ይሄንን በሌላ ጊዜ አብራራዋለሁ። ለዛሬው ይህን እንድጽፍ ያደረገኝ በፌስቡክ የተነሳው ሙግት ነው። በሌላ ጊዜ የብሮድካስቲንግ ሕግን አስመልክቶ በተለይ ደግሞ በአዋጁ የተቀመጡ ስልጣኖችን፣ መብትና፣ ግዴታዎችን አስመልክቶ እመለሳለሁ። ደብዳቤው ከሚያሳስበን በላይ የሕግ ማእቀፉ ብዙ አሳሳቢ ድንጋጌዎችን አካቷል።

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ደብዳቤው
አንዳንድ ነጥቦች ስለአዲሱ የመንገድ ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማሻሻያ ደንብ ቁጥር 39...
 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 23 May 2024