Font size: +
8 minutes reading time (1680 words)

ስለማስረጃ ሕግ አደረጃጀት

የማስረጃ ሕግ የማስረጃን አግባብነት፣ የማስረጃን ተቀባይነት እንዲሁም የማስረጃን ክብደትና ብቃት የሚገዙ ደንቦችና መርሆዎች ጥርቅም ነው፡፡ ማስረጃ ተሟጋቾች በአቤቱታቸው አማካኝነት ፍርድ ቤት የያዘውን ጭብጥ የሚያረጋግጡበት ዘዴ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ማስረጃ ማለት ፍርድ ቤት የያዘውን አከራካሪ ጉዳይ ወይም ጭብጥ በሚሰማበት ጊዜ ተሟጋቾች የጥያቄውን አግባብነት፣ እውነትነት፣ በምስክሮች፣ በሠነድ፣ ተጨባጭነት ባላቸው ሌሎች ነገሮች፣ ወዘተ… ማስረጃ ለፍርድ ቤቱ የሚያረጋግጡበት አሊያም ውድቅ የሚያደርጉበት ዘዴ ነው፡፡ ማስረጃ ሲባል የአንድን ፍሬ ነገር ህልው መሆን ወይም አለመሆን ለማረጋገጥ ያገለግል ዘንድ ክስ በሚሰማበት ጊዜ ወይም የክርክር ጭብጥ በሚጣራበት ወቅት በተከራካሪ ወገኖች ወይም ክርክሩን በሚያየው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ አማካኝነት የሚቀርብ ማናቸውም ዓይነት የአስረጂነት ባህርይ ያለው ነገር ነው፡፡ ማስረጃ በምስክሮች (Witnesses)፣ በዘገባ (Record)፣ በሠነድ (Document)፣ ተጨባጭነት ባላቸው ሊታዩ ሊዳሰሱ በሚችሉ ነገሮች (Concrete Objects) እና በኤግዚቢት መልክ ሊቀርብ ይቸላል፡፡ አቀራረቡም በሕግ በተደነገገው ሥርዓት መሠረት ነው፡፡ የክርክሩን ጭብጥ ፍሬ ነገር እውነት ወይም ሀሰት መሆኑን የማሳመን ኃይል ያለው እንደመሆኑ እና በዚህም ወደ ውሳኔ የሚያደርሰው ስለሆነ ሊገኝም ሊቀርብም የሚገባው በሕግ አግባብ ነው፡፡ ማስረጃው ተቀባይነት ወይም ውድቅ የሚደረገው እንደዚሁም ሊሰጠው የሚገባው ክብደት የሚመዘነውም በሕግ አግባብ ነው፡፡

ከእነዚህ ትርጓሜዎች እንደምንረዳው “ማስረጃ” የሚለው ቃል አንድን ጭብጥ ለማረጋገጥ አሊያም ውድቅ ለማድረግ የሚያስችል በፍርድ ቤት ዘንድ ተቀባይነት ያለው ማናቸውም ዓይነት የማረጋገጫ ዘዴ ነው፡፡ ተጨባጭነት ባለው መልኩ “ማስረጃ” ማለት ፍርድ ቤት የቀረበለትን ጭብጥ ለመወሰን የሚያስችሉትን ሁኔታዎች የማረጋገጫ ዘዴ ነው፡፡

በአጠቃላይ የማስረጃ ሕግ በፍትሐብሔርም ሆነ በወንጀል ጉዳዮች ለፍርድ ቤት ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ የትኞቹ ተቀባይነት እንዳላቸው የትኞቹ ደግሞ ተቀባይነት እንደሌላቸው የሚደነግግ ሕግ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተቀባይነት ያላቸው ማስረጃዎች ምን ዓይነት ክብደት እንደሚሰጣቸው በማስረጃ ሕግ ይደነገጋል፡፡ ይህ ሕግ በፍርድ ሂደት የማስረጃ ተቀባይነትን፣ ተገቢነትን፣ ክብደትን እና ብቃትን እንዲሁም የማስረዳት ሸክምን የሚገዙ መርሆችና ደንቦች ተካተው የሚገኙበት የሕግ ክፍል ነው፡፡ ስለ ማስረጃ በጥቅሉ ስንናገር ማናቸውም የቀረበን አከራካሪ ጉዳይ መኖር ወይም አለመኖር ሊያስረዳ የሚችል ነገር ሲሆን ቀጥተኛ ማስረጃን፣ ሠነድን፣ ገላጭ ማስረጃዎችን፣ የእምነት ቃልንና ፍ/ቤት ግንዛቤ የሚወሰድባቸውን ነገሮች ሊጨምር ይችላል፡፡ የማናቸውም ማስረጃ ሕግ አስፈላጊነትና ግብ ለጭብጡ አግባብነት ያላቸውን ነገሮች ለፍርድ ቤቱ በማሳየት ዕውነቱን ማስረዳትና ለሙግቱ ትክክለኛ ፍርድ እንዲሰጥ ማመቻቸት ነው፤ በመሆኑም የማስረጃን ተቀባይነት የሚወስኑት የማስረጃ ሕግ ደንቦች ወይም ድንጋጌዎች ምክንያታዊ መሆን አለባቸው፡፡ የማስረጃ ሕግ ድንጋጌዎቹ ምክንያት የለሽ ከሆኑ መደንገጋቸው ትርጉም የለሽ ይሆናል፤ ድንጋጌዎቹም ያስፈለጉበትንም ግብ አይመቱም፡፡

የማስረጃ ሕግ ዓላማ

የማስረጃ ሕግ አስፈላጊነትና ዓላማ ለጭብጡ አግባብነት ያላቸውን ነገሮች ለፍርድ ቤቱ በማሳየት ዕውነቱን ማንጠርና ለሙግቱ ትክክለኛ ፍርድ እንዲሰጥ ማመቻቸት እንደሆነ ከላይ ተመልክቷል፡፡ በዘመናዊ የፍትሕ አሠራር ፍ/ቤት በሰዎች መካከል የሚፈጠር ክርክርን የሚያስተናግደውና ውሳኔ የሚያስተላልፈው ሌሎች ሕጋዊ ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው በማስረጃ ሕግ መርሆችና ድንጋጌዎች በመመራት ነው፡፡ በእነዚህ መርሆችና ድንጋጌዎች ተመርቶ የተሰጠ ውሳኔ ፍትሕን ያረጋግጣል፡፡ የተደራጁና ምሉዕ የሆኑ መሠረታዊና ሥነ-ሥርዓት ሕጐች ቢኖሩ እንኳን የማስረጃ አወሳሰን መርሆዎች ብቃት ከሌላቸው የውሳኔው ጥራት በገለልተኛነት የተሰጠ መሆኑ አከራካሪ ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም የማስረጃ ሕግ ዋንኛው ዓላማ እውነትን አብጠርጥሮ ማውጣት፣ እርግጠኝነቱ ያልታወቀን ነገር፤ በጥቅሉም አከራካሪ ጉዳይን በፍርድ ቤት ማረጋገጥ እና ፍትሕን ማስፈን ነው፡፡

አግባብ ባልሆኑ ፍሬ ነገሮች ላይ በመነታረክ የሚፈሰውን ጉልበት፣ ገንዘብና የሚባክነውን ጊዜ በተቻለ መጠን መቀነስና መቆጠብ ሌላኛው የማስረጃ ሕግ ዓላማ ነው፡፡ የማስረጃ ሕግ አላስፈላጊና ለጉዳዩ አግባብነት የሌላቸውን ነገሮች በመለየትና በማስወገድ በአስፈላጊና ለጉዳዩ ጠቃሚ በሆኑት ጉዳዮች ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ለሙግቱ የሚያስፈልገውን ጊዜ በተቻለ መጠን ያሳጥራል፡፡ ሙግትን ለማሳጠር የማስረጃ ሕግ በዘርፉ ለተሰማሩ የተለያዩ አካላት ሥራቸውን እንዴት መለየት እንዳለባቸው እንደመመሪያ ሆኖ ያገለግላቸዋል፡፡

ስለማስረጃ ሕግ ያሉ አመለካከቶች

ስለማስረጃ ሕግ የተለያዩ የሕግ ፍልስፍና አመለካከቶች እንደሚከተሉት የሕግ ሥርዓት (Legal System) ዓይነት ይንፀባረቃሉ፡፡ በእነዚህ ሥርዓተ ሕጎች መካከል ያለው ልዩነት በብዙ መልክ ሊገለጽ ይችላል፤ ለምሳሌ በሕግ ጽንሰ ሃሳቦች ግንዛቤ፣ በሕጎቹ አደረጃጀት፣ በቴክኒክ፣ በአተረጓጎም፣ በፍርድ አመራር ሥርዓት፣ ወዘተ፡፡ የ“ኮመን ሎ” የሕግ ሥርዓት ተከታዮች ስለማስረጃ ሕግ የራሳቸውን አመለካከት ያራምዳሉ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የ“ሲቪል ሎ” የሕግ ሥርዓት ተከታዮች ስለማስረጃ ሕግ ከ“ኮመን ሎ” የተለየ አመለካከት አላቸው፡፡ በሲቪል ሎ እና በኮመን ሎ ሥርዓተ ሕጎች መካከል በወናነት ጎልቶ የሚታየው ልዩነትም የሕግ  ድንጋጌዎች የአጠቃላይነት ደረጃ ነው፡፡ የኮመን ሎ ቴክኒክ በዝቅተኛ የአጠቃላይነት ደረጃ የተወሰነ ነው፡፡ የሲቪል ሎ ግን አጠቃላይነትና ርቀት /Abstraction/ ጎልቶ የሚታይበት ነው፡፡  በሲቪል ሎ ሥርዓተ ሕግ ሕጎች  በዘርፍ በዘርፉ የተከፋፍለው ከተመደቡ በኋላ በመጽሐፍ /ኮድ/ መልክ ይዘጋጃሉ፡፡ ኮድ የሚለው አገላለጽ እንደሚታወቀው በአንድ የሕግ ዘርፍ ሊጠቃለሉ የሚገባቸውን ድንጋጌዎች በሙሉ፣ በግልጽና በተቀናጀ መልክ በማሰባሰብ በአንድ ሰው ወይም በአንድ ውሁድ የአርቃቂዎች ቡድን የተዘጋጀ የሕግ መጽሐፍ ለመግለጽ የሚያገለግል ነው፡፡ ይህ አገላለጽ እንግዲህ የሚያስገነዝበን አንድ የሕግ ዘርፍ መያዝ ያለበትን ድንጋጌዎች ሁሉ የሚያካትት መሆኑን እና በሁለተኛ ደረጃም ከኮንሶሊዴሽን /የተጠቃለሉ ሕጐች/ በተለየ ሁኔታ የተቀነባበረና ውህድነት ያለው መሆኑ ነው፡፡

የማስረጃ ሕግ በኮመን ሎ

የኮመን ሎ ሥርዓተ ሕግ በሚከተሉት ሃገሮች ሕጎችን በዘርፍ በዘርፍ ከፋፍሎ መመደብ በእርግጥም ያለ እና እንደ ሲቪል ሎ ሥርዓተ ሕግ ተከታይ ሃገሮች የሚሠራበት የሕጉ ቴክኒክ ነው፡፡ በዚህ መርህ መሠረትም በሕግ ፍልስፍና ትምህርት በቅድሚያ በመንግሥታዊ ሕግ (public law) እና በግል ሕግ (private law) መካከል ያለውን ልዩነት፣ ቀጥሎም መንግሥታዊ ሕጉ፣ ሕገ-መንግሥት፣ የአስተዳደር ሕግ አና  የወንጀል ሕግ በሚሉ ዘርፎች ሊከፋፈል ወይም ሊመደብ አንደሚችል፤ የግል ሕጉም እንደዚሁ የንብረት ሕግ፣ የውል ሕግ፣ የውርስ ሕግ፣ የንግድ ሕግ  ወዘተ.. በማለት ሊከፋፈልና ሊታወቅ አንደሚችል እየተገለጸ ትምህርት ይሰጣል፡፡ የተግባር ሂደቱም ይህን አቅጣጫ ተከትሎ ይከናወናል፡፡ ነገር ግን እነዚህ በመሠረታዊ ሕግነት የሚመደቡት ዘርፎች እንደ ሲቪል ሎ ሥርዓተ ሕግ ተከታይ ሃገሮች በኮድ መልክ አይዘጋጁም ወይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተወሰነ ደረጃ ኮድ ማዘጋጀት እየተለመደ ቢመጣም አጠቃላይ አሠራሩ ግን ይህ አይደለም፡፡

የኮመን ሎ ሥርዓተ ሕግ በአመዛኙ የዳበረው ልምድን መሠረት በማድረግ ዳኞች በሚሰጡአቸው ውሣኔዎች (case law) ነው፡፡ በእርግጥ በዚህ ጎን ለጎን በሕግ አውጭው የሚደነገጉ ሕጎች (Statutes) ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ ሥርዓት ዳኞች በሥራቸው ሂደት በመሠረታዊ ሕግ እና በሥነ ሥርዓት ሕግ መካከል ያለውን ልዩነት እንዲሁም በመብት ማረጋገጥና በመፍትሔ አሰጣጥ ላይ ሲያተኩሩ ቢቆዩም፤ አንድ ደንብ በየትኛው የሕጉ ዘርፍ ሊመደብ ይገባል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል አጠቃላይ የሆነ መርህ (principle) ለማዳበር ግን እንዳልቻሉና እንዳልሞከሩም የሥርዓተ ሕጉ ሊቃውንት /ምሁራን/ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ የተነሣም እንደ ሲቪል ሎ ሥርዓተ ሕግ ሕጎችን በየዘርፉ ከፋፍሎ የማዘጋጀት አሠራር ሊዳብር አልቻለም፡፡ በዚህ ረገድ ከተደረጉት ጥናቶች እንደምንገነዘበው ሲደረግ የቆየው ሕጎቹ ምንጫቸው የፍርድ ቤቶች ውሣኔ (case law) ይሁን የሕግ አውጭው አዋጅ፣ ለአጠቃቀም በሚያመች ሁኔታ በኮንሰሌደሽን መልክ ማስቀመጥ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ሕጎች በተግባራዊው ዓለም በቀጣይነት ሥራ ላይ የሚውሉ በመሆናቸው እና አንደኛው ወሣኝ ሥራም ይህ ስለሆነ ዝርዝር የመተግበሪያ መሣሪያ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ እንደተገኘና በዚህ አቅጣጫም ለየት ያለ ልምድ መዳበሩን እንመለከታለን፡፡ ቀደም ብለን እንደተመለከትነው የተግባር መሣሪያው ክርክሮች የሚቀርቡበት፣ የሚመሩበት፣ የሚወሰኑበትና ውሣኔዎችም የሚፈጸሙበት ሥነ-ሥርዓት ነው፡፡ ሥነ-ሥርዓቱ በክርክር ጭብጦች ወይም ፍሬ ነገሮች በማስረጃ የሚነጥሩበት አካሔድንም የሚያጠቃልል ነው፡፡ ስለዚህም በኮመን ሎ ሥርዓተ ሕግ ተከታይ ሃገሮች ዘንድ በዚህ በሕጉ ዘርፍ ሠፊ እና ዝርዝር ደንቦችን ያካተተ የተግባር መመሪያ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ እንደተገኘ የሥርዓተ ሕጉ የዕድገት ታሪክ ያስገነዝበናል፡፡ በአጠቃላይ መልክ ሲታይ በኮመን ሎ ሥርዓተ ሕግ ተከታይ ሃገሮች በኮድ መልክ ተዘጋጅተው የምናገኛቸው የሕጉ ዘርፎች በቅጽል ሕግ (adjective) ሥም የሚታወቁት ናቸው፡፡ በዚህ አቅጣጫ የታየው ሂደት ከሲቪል ሎ ሥርዓተ ሕግ ጋር ሲነጻጸር በተለይ አጉልቶ የሚያሳየን የማስረጃ ሕግ አደረጃጀት፣ ለሕጉ መሠረት በሆኑት ጽንሰ ሃሣቦች እና መርሆዎች አረዳድ እና አተገባበር ረገድ የዳበረው ልምድ የተለየ መሆኑን ነው /ሲቪል ሎ ካደበረው ልምድ/፡፡

የማስረጃ ሕግ እድገት ከኮመን ሎ ሥርዓተ ሕግ አኳያ ሲታይ እንደሌሎች የሕጐ ዘርፎች በረዥም የተግባር ሂደት የዳበረ ነው፡፡ ለምሳሌ የሥርዓቱ ዋነኛ ማዕከል የሆነችውን የእንግሊዝን የማስረጀ ሕግ እድገት ስንመለከት የምንገነዘበው ሕጉ በአብዛኛው የ"ጁሪ" ሥርዓት ውጤት ነው ተብሎ እንደሚታመን ነው፡፡

የጁሪ ሥርዓት የፍርድ /የዳኝነት/ ሥራ ሂደት በዳኛ እና በጅሪ መካከል የሚኖረው ግንኙነት የሚቀርጽ ሥርዓት ነው፡፡ ዳኛውም ሆነ ጁሪው የየራሳቸው በብቸኝነት የያዙት የፍርድ አመራር ሥልጣን አላቸው፡፡ ዳኛው የሕግ ጥያቄ የሚያስነሱ ጭብጦችን ብቻ እየተመለከተ በእነዚሁ ላይ ውሣኔ ይሰጣል፡፡ ጁሪው ደግሞ በፍሬ ነገር ጭብጦች (facts) ላይ ውሣኔ ይሰጣል፡፡ ከዚህ ዓይነት የፍርድ አመራር የሥልጣን ክፍፍል የሕግ እና የፍሬ ነገር (facts) ተብለው የሚከፋፈሉ ወይም የሚመደቡ ነገሮች ይኖሩ ዘንድ የግድ ይላል፡፡ በዚህ መሠረት የዳኝነት ሥራው በሚካሔድበት ጊዜ ወይም ክርክር በሚሰማበት ወቅት የማስረጃ ተቀባይነት (Admissibility) የሚመለከቱ ጭብጦች የሕግ ጉዳዮች ሆነው ስለሚታዩ የሚወሰኑት በዳኛው ነው፡፡ ተቀባይነት አግኝተው ከተሰሙት ማስረጃዎች ላይ በመነሳት የሚደረሰው የፍሬ ነገር ድምዳሜ ግን የፍሬ ነገር ጉዳይ  በመሆኑ ለጁሪው ነው የሚተወው፡፡ እንደዚሁም የምስክሮች ቃል ተዓማኒነት የሚመዘነው፣ ከአካባቢ ማስረጃዎች ላይ በመነሳት ድምዳሜ ወይም ውሣኔ ላይ የሚደረሰው በጁሪው ነው፡፡

እንደምንመለከተው በኮመን ሎ ሥርዓተ ሕግ ተከታይ ሃገሮች ማስረጃን የሚሰሙትና የሚመዝኑት የሕግ ባለሙያ ያልሆነ “ጁሪ” በመባል የሚታወቁ ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች የሕግ እውቀት ወይም ችሎታ የሌላቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ አንዳንድ ጊዜም መደበኛ ትምህርት የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በፍርድ ሂደት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ፡፡ የክርክር ፍሬ ነገሮች የሚወሰኑት በእነዚህ ሰዎች ነው፡፡ በዚህ የሕግ ሥርዓት እድገት ጥናት ያካሔዱ የሕግ ሊቃውንት እንደሚሉት የክርክር ፍሬ ነገሮች በተራ ሰው (lay man) እንዲወሰኑ የሚያደርግ ሥርዓት በተፈጥሮው የተወሰኑ የመቆጣጠሪያ ዘዴዎች (mechanism) ያዳብራል፡፡ ይህም ከስህተትና ከጥላቻ (prejudice) ላይ በመነሳት የሚደረስ ድምዳሜ እንዳይኖር ይከላከላል፡፡ በዚህ ምክንያት የዳኝነት ሥርዓቱ የማስረጃ ተቀባይነትን በሚመለከት በሚነሱ ጭብጦች ላይ ብቸኛ የመቆጣጠሪያ ሥልጣን ዳኛው እንዲይዝ ተደርጎአል፡፡ ሥርዓቱ ይህን ሥልጣኑን በሚተገብርበት ሂደትም ማስረጃ የማስቀረትን ደንቦች (exclusion rules) እያዳበረ መጥቶአል፡፡ ይህም ማለት ለኮመን ሎ ሥርዓተ ሕግ ልዩ ሆኖ የሚታይ በማስረጃ አቀራረብ ረገድ አንድ አጠቃላይ መርህ ማበጀት አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ ማለት ነው፡፡

የማስረጃ ሕግ በሲቪል ሎ

በሲቪል ሎ ሥርዓተ-ሕግ ተከታይ ሃገሮች ደግሞ አሠራሩ የተለየ ነው፡፡ የዳኝነት ሥራ የሚካሔደው የሕግ እውቀት ባላቸው በፕሮፌሽናል ዳኞች ነው፡፡ ማስረጃ የሚሰማውና የሚመዘነው በእነዚህ ዳኞች ነው፡፡ በዳኝነት ሂደቱ ከፍተኛና ወሳኝ ሚና የሚጫወቱት ዳኞች ናቸው፡፡ በአጭር አነጋገር በሲቪል ሎ የሕግ ሥርዓት የፍርድ አመራር ሂደቱ ዳኛ መራሽ ነው ሊባል ይችላል፡፡ በመሆኑም እንደ ኮመን ሎ ሥርዓተ ሕግ ተከታይ ሃገሮች ለሕግ መሃይም የሆነ ሰው በቀላሉ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የሚጠቀምባቸውን የማስረጃ ዓይነቶች ለክርክር አወሳሰን ሚና ይኖራቸዋል የሚል ሥጋት የለም፡፡ ጁሪዎች ለተወሰኑ የማስረጃ ዓይነቶች የማይገባ (undue) ክብደት በመስጠት በግልጽ በሚታይ አና እምነት በማይጣልበት ማስረጃ ላይ በመመሥረት ፍርድ ሊሰጡ ይችላሉ የሚል ፍርሃት በሲቪል ሎ ሥርዓተ ሕግ ተከታይ ሃገሮች ሊኖር አይችልም፡፡ በመሆኑም ማስረጃዎችን ከወዲሁ ከነጭራሹ ፍርድ ቤት አይቀርቡም በሚለው መስመር ላይ የሚበለጽግ /የሚዳብር/ አስተሳሰብ /የሕግ ጽንሰ ሃሳብ/ በሲቪል ሎ ሥርዓት ሊፈጠር አስፈላጊ አልሆነም፡፡ በዚህ ሥርዓት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ማስረጃው ከመቅረቡ በፊት ላለው ሂደት ሳይሆን፣ ከቀረበ በኋላ ላለው ሁኔታ ነው፡፡ ማስረጃው ከቀረበ በኋላ ሲታይ ሚዛን የማይደፋ ከሆነ ይጣላል፡፡ ማስረጃዎች እንዴት፣ መቼ እና በየትኛው ተከራካሪ ወገን መቅረብ እንዳለባቸው በሚመለከት ግን አጠቃላይ የማስረጃ ሕግ መርሆዎች እና እንደአስፈላጊነቱም ዝርዝር ደንቦች ይኖራሉ፡፡ የደንቦችና መርሆዎች አደረጃጀት ያየን እንደሆነ ግን ሥርዓተ ሕጉ የተከተለው ቴክኒክ ከኮመን ሎ የተለየ ነው፡፡

በኮመን ሎ ሥርዓተ ሕግ በመጽሐፍ /ኮድ/ ተዘጋጅቶ የምናገኘው ቅጽል ሕጉ (Adjective law) ብቻ እንደሆነ ከላይ ተመልክተናል፡፡ የማስረጃ ሕግ የሥነ-ሥርዓት ሕግ አካል መሆኑ ቢታመንበትም፣ ቀደም ሲል ካየናቸው አስተሳሰቦች፣ ከሕግ ጽንሰ ሃሳቦች አጠቃቀም እና እድገት አኳያም ጭምር እያታየ ይመስላል ራሱን ችሎ በመጽሐፍ እንዲዘጋጅ ይደረጋል፡፡ ቅጽል ሕጉ በሁለት ዘርፎች በግልጽ ተከፍሎና ተመድቦ የምናገኘው በኮመን ሎ ሥርዓተ ሕግ ተከታይ ሃገሮች ነው፡፡ በሲቪል ሎ ሥርዓተ ሕግ ተከታይ ሃገሮች ግን የማስረጃ ሕግ በተለይ ራሱን ችሎ በመጽሐፍ ወይም በኮድ አይዘጋጅም፡፡ በእርግጥ የማስረጃ ሕግ አጠቃላይ መርሆዎች በሥነ-ሥርዓት ሕጉ እንዲካተቱ ይደረጋል፡፡ ሌሎቹ ማስረጃን የሚመለከቱ ደንቦች ደግሞ የመሠረታዊ ሕጎች በተዘጋጁባቸው መጽሐፎች ውስጥ ይካተታሉ፡፡ ከላይ እንዳየነው በእነዚህ ሃገሮች "ጁሪ" የተባለው ሥርዓት ስለሌለ ራሱን የቻለ እና ዝርዝር የማስረጃ ሕግ ደንቦች በተለይ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ አልተገኘም፡፡ የማስረጃ ሕግ ደንቦች በተለይ በአንድ መጽሐፍ ሊዘጋጁ ያልቻሉት ግን በዚህ ምክንያት ብቻ አይደለም፡፡ በየዘርፉ ተከፋፍለው የተመደቡት የመሠረታዊ ሕግ ኮዶች በየዘርፉ የተሟሉ ሆነው ይገኙ ዘንድ ግድ ይላል፡፡ ከዚህ የተነሳም ለየዘርፉ የሚመለከተው የማስረጃ ደንብም ሆነ መርህ በዚሁ /በየኮዱ/ ማካተት ተገቢ ይሆናል፡፡ ኮድ ከተባለ የተሟላ ይዘት ያለው ሊሆን የተገባ ነው፡፡ ዳኞችም የቀረቡላቸውን ጉዳዮች የሚዳኙት ከተዘጋጁላቸው ኮዶች ለተያዘው ጉዳይ ተገቢነት ያላቸውን ድንጋጌዎችና የሕግ ጽንሰ ሃሳቦች ፈልገው በማግኘት ነው፡፡

የሐገራችንን የማስረጃ ድንጋጌዎች እንዴት ያዩታል?

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የዘገየ ፍርድ
አስገዳጁ የኮንስትራክሽን ኢንሹራንስ የሕንጻ መደርመስን ይከላከለው ይሆን?

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Sunday, 08 September 2024