ችሎት መድፈር፡- ሕጉ እና የአሠራር ግድፈቶች
የኢፌድሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 449፦
449. ፍርድ ቤትን መድፈር
(1) ማንም ሰው በፍርድ ቤት ምርመራ በሚደረግበት ወይም የፍርድ ሥራ በሚከናወንበት ጊዜ፦
ሀ/ ፍርድ ቤቱን ወይም የዳኝነት ሥራ በማከናውን ላይ ያለን ዳኛ በማናቸውም መንገድ የሰደበ፣ ያወከ ወይም በእነዚሁ ላይ ያፌዘ ወይም የዛተ እንደሆነ ወይም
ለ/ የፍርድ ቤቱን ሥራ በማናቸውም ሌላ መንገድ ያወክ እንደሆነ
ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እሥራት ወይም ከሦስት ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል። ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ሳያደርግ ወድያውኑ በጥፋተኛው ላይ ቅጣት ሊወስን ይችላል።
(2) ወንጀሉ የተፈፀመው ከችሎት ውጭ ሆኖ ዳኛው ሥራውን እያከናወነ ባለበት ጊዜ ከሆነ፣ ቅጣቱ ከስድስት ወር የማይበልጥ ቀላል እሥራት ወይም ከአንድ ሺህ ብር የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል።
(3) ወንጀሉ የተፈፀመው በችሎት ወይም በማናቸውም ቦታ የዳኝነት ሥርዓት በሚካሄድበት ጊዜ ሆኖ በኃይል ወይም በማስገደድ እንደሆነ አግባብ ያለው ድንጋጌ/ አንቀፅ ፬፻፵፩/(441) በተደራቢነት ተፈፃሚ ይሆናል።
በማለት ይደነግጋል።
ከዚህ ድንጋጌ ጋር ተያይዞ የሕጉ ዓላማ ምን እንደሆነ ችሎት መድፈር ማለት ምን እንደሆነ ምን ዓይነት ድርጊቶች ችሎት መድፈር እንደሆኑና ሊሆኑ እንደሚችሉ በማህበረሰቡ ውስጥ እና በሕግ ባለሙያው ዘንድ የግንዛቤ ችግር ስለ መኖሩ ከሕጉ በታቃራኒ ያሉ የአሠራር ግድፈቶች እንደ አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል።
የዳኝነት ሥልጣን በሕግ የተሰጠው ተቋም እና የዳኝነት ሥራውን የሚያከናውን ዳኛ አንድን ጉዳይ ገለልተኛ እና ነፃ ሆኖ በሕግ እና በማስረጃ ብቻ ሊሠራ ይገባል፤ ይህም ሕገ መንግሥታዊ እውቅና እና ጥበቃ የተደረገለት የዳኝነት መርህ ነው። ከዚህም ባለፈ የዳኝነት ሥራ በስዎች ሰብዓዊ እና ቁሳዊ መብት ላይ ፍርድ የሚሰጥበት ሂድት በመሆኑ በከፍተኛ ትኩረት እና ጥንቃቄ ሊሠራ ይገባል። ይህ የፍርድ አደባባይ ሰዎች ሕግን መከታ አድርገው ሊጠጉበት፣ መብታቸውን ሊያስከብሩበት የተሰየሙበት አውድ በመሆኑ ሊከበር ይገባል፤ አበው እንደሚሉትም "ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ"፡፡ የፍርድ አደባባዩ ሳይከበር ፍርዱ ሊከበር አይችልም እና ነው። ከላይ የተገለፀው የወንጅል ሕጉ ድንጋጌም በጥቅሉ እኚህን ግቦች ለማሳካት የቆመ ነው።
ጥሎብን ብዙዎቻችን ለጉዳይ አልያም እግር ጥሎን ፍርድ ቤት ስንሄድ ወደ ህሊናችን የሚመጣውና ብርክ ይዞን ከፍርድ ቤት ቅጥር እስክወጣ "ብታሰርስ" በሚል የፍራቻ ርደት ቤቱ የመብት ማክበርያ እና ማስከበርያ መሆኑን ዘንግተን ስንረበሽ እንታያለን፡፡ ሌላው ቀርቶ ጉዳያችንን እንኳ በአግባቡ ሳናስረዳ ቀርተን እንረታለን። በእርግጥ በረዥሙ የአገራችን የዳኝነት ሥርዓት ውስጥ ዛሬም ያልፀዳንበት ችግር ዳኝነት ባለጉዳይን ካልተቆጡ ክብር የማይገኝበት እስኪመስል፣ በሰበብ አስባቡ ጅራፍን እያጮሁ "ችሎት ደፍረኃል" በሚል ካባ ሥር ባለጉዳይን ማሰር ልምድ በሆነበት እንዴትስ አለመፍራት ይቻላል ያስብላል።
በእርግጥ ችሎትን መድፈር ማለት ምን ማለት እንደሆነ እና ምን ዓይነት ድርጊቶች ችሎት መድፈር እንደሆኑ በፌድራል ዳኞች የሥነ ምግባር ደንብ ላይ ከተደነገጉት መካከል፡
· በችሎት ላይ ሞባይል ማስጮህ፣
· ሲጋራ ማጬስ፣
· በንግግር ወይም በምልክት ማወክ፣
· ምግብ መጠቀም ወይም መጠጣት፣ መተኛት፣
· ከጠበቃ ውጪ እሥረኛን ማናገር፣
· የጦር መሳሪያ መያዝ፣
· ማስቲካ ማኘክ፣ ጫት መቃም እና
· ያለ ችሎቱ ፈቃድ የድምፅ እና ቪዲዮ ቀረፃ ማካሔድ
ይገኙበታል፡፡
ደንቡ ከላይ የተጠቀሱትን ድርጊቶች የተከለከሉ መሆናቸውን ከሚገልፅ ውጪ ሃገራዊ የችሎት አመራር መመሪያ ድንጋጌ ባለመኖሩ ዳኞች እና ፍርድ ቤቶች ጠቅላላውን የወንጀል ሕግ ድንጋጌ በመንተራስ ሰፊ ትርጉም ተሰጥቶት ከተፈለገው ውጤትም ባፈነገጠ ሁኔታ ሥራ ላይ ሲያውሉት ይስተዋላል። እዚህ ላይ እንደ ጥሩ ምሳሌ መጠቀስ የምችለው የኦሮምያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የችሎት መመሪያ ቁ. 8/2004 ችሎትን መድፈር እና ድርጊቶቹ ምን ምን እንደሆኑ በግልፅ ደንግጎ በሥራ ላይ አውሏል። አንባቢዎች በአከባቢያቹ ወይም በክልል ደረጃ መምሪያው ስለመኖሩ ወይም የአሠራር ዘይቤ ተነድፎ ካለ ሃሳብ እንድታጋሩኝ በትህትና እጠይቃለሁ።
ይህ ጸሐፊ በሥራ አጋጣሚ እና ከተለያዩ የሕግ ትምህርት ማስተማሪያ ማቴሪያሎች ያገኛቸውን እውነተኛ የችሎት መድፈር ፍርዶች የተወሰኑትን ለማሳያነት እንዲሆኑ እንደሚከተለው አቅርቦአል፡፡ ፍርዱን ግን ከላይ ባለው የወንጀል ሕጉ ድንጋጌ አገናዝባቹ እንድትፈርዱት ለአንባቢዎች ትቼዋለሁ።
1. የአንድ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ለፍርድ ቤት ግንባታ የሚውል ኃብት ለማሰባሰብ ወደ ህዝቡ ወርዶ በቀበሌ እያወያየ ባለበት ቦታ አንድ ግለሰብ ለፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት "ምን ትግደረደራላቹ ከወረዳ ተልካችሁ ነው የመጣችሁት" ብሎ በመናገሩ የፍርድ ቤትን ሥራ አውኮአል "ፍርድ ቤትን ደፍሮአል" ተብሎ በፓሊስ ተይዞ ቀርቦ በአንቀጽ 449(2) ሥር የሶስት ወር ቅጣት ተላልፎበታል።
2. አንድ የፍርድ ባለእዳ እንዲፈፅም ከሚጠበቅበት እዳ ግማሽ ያህሉን ፈፅሞ የቀረውን ለመፈፀም አቅም የሌለው መሆኑን በማሳሰብ ፍርድ ቤቱ እንዳያስገድደው በጠይቀ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ችሎት ደፍረሃል ብሎ በአንድ ወር እሥራት ቀጥቶታል።
3. ዳኛው በህዝብ ትራንስፓርት በመጓዝ ላይ ሳለ ከአንድ ግለሰብ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ተጋጭተው ዳኛው ይህንን ግለሰብ በፓሊስ አስይዞ ካስቀረብ በኋላ ችሎት ደፍረሃል አላከበርከኝም ብሎ በአንድ ወር እሥራት ቀጥቶታል።
4. አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ከፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ውጪ ባለው መንገድ በከፍተኛ ጬኸት ሞተር ሳይክል አያሽከረከረ በሚጓዝበት ወቅት ችሎት ሲሰራ የነበረ ዳኛ ግለሰቡ በሞትሩ ጩኸት ችሎቱን አውኳል በሚል በፓሊስ አስጠርቶ ችሎት በመድፈር ወንጀል ግለሰቡን የቃል ማስጠንቀቅያ ሰጥቶታል።
5. አንዲት ባለጉዳይ በፍርድ ቤት ባላት ክርክር ችሎቱን በሚያስችለው ዳኛ ላይ ያላትን ቅሬታ በመግለጽ ለፍርድ ቤቱ አስተዳደር ቅሬታዋን በማቅረቧ እና የፍርድ ቤቱ አስተዳደር ቅሬታው አሳማኝ ሆኖ በማግኘቱ በሕጉ አግባብ ይህን ጉዳይ የያዙት ዳኛ ከጉዳዩ ላይ እንዲነሱ በመወሰኑ ቅሬታ የቀረበበት ዳኛ ስሜን አጥፍተሻል፣ የዳኝነት ነፃነቴን በሚጋፋ መልኩ መዝገቡ ከእጄ እንዲወጣ አድርገሻል ብለው በችሎት መድፈር ወንጀል በአሥራ አምስት ቀን እሥራት ቀጥተዋታል።
እናንተ የገጠማችሁን የችሎት መድፈር ውሳኔዎች ከታች ባለው አስተያየት መስጫ ብትሰጡን ደስ ይለናል፡፡
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments