አመክሮ፤ መብት፣ ሸቀጥ ወይስ ችሮታ?

ፕሬዝደንቱ የስልጣን ጊዜአቸውን ጨርሰው ከሥልጣን ሊወርዱ የወራት ወይም የቀናት ዕድሜ ነው የቀራቸው። ከሥልጣን ከመውረዳቸው በፊት ግን ለወደፊት ሕይወታቸው ገንዘብ ለመሰብሰብ የሚያስችላቸው አንድ አጋጣሚ ከፊታቸው ተደቅኗል። ይህ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚያስገኝ አጋጣሚ አሁን ባላቸው የፕሬዝዳንትነት ስልጣን ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር ነው። ይህ አጋጣሚ “ፕሬዝደንታዊ ይቅርታ” (Presidential pardon) ነው። እስረኛው ይህንን ይቅርታ አግኝቶ ከእስር ከተፈታ የሚከፍለው ገንዘብ እጅግ ብዙ በመሆኑ በሥልጣን ደላላዎች (Power brokers) አማካኝነት ገንዘቡን ተቀብሎ የይቅርታ ሰነዶቹ ላይ ፈረመ።

ከላይ ያነበባችሁት ታሪክ ሕግ ነክ ልብወለዶችን በመፃፍ የሚታወቀው John Grisham የተባለው ደራሲ “The Broker” በተሰኘው መፅሃፉ ውስጥ ከፃፈው ታሪክ በአጭሩ የተቀነጨበውን ነው። ደራሲው ይህንን ሲፅፍ ለመነሻነት ይሆኑት ዘንድ የተለያዩ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ አስገብቶ ነው። ከነዚህ ሁኔታዎች አንዱ የአሜሪካ ፕሬዝደንቶች ይቅርታ ይሸጣሉ ተብሎ በተለያየ ጊዜ የተነገረው ነገር ነው። በተለያዩ ትልልቅ የወንጀል ጉዳዮች ተከሰው የተፈረደባቸው እና እስር ላይ ያሉ የግዙፍ ኩባንያዎች ባለቤቶች እና ስራ አስኪያጆች እንዲሁም ሌሎች ጠቃሚ ሰዎች እና ባለሀብቶች ደግሞ የዚህ የይቅርታ ንግድ ተጠቃሚዎች ናቸው። ከዚህ በፊት የነበረውን አሰራር ስንመለከት ደግሞ ፕሬዝዳንቶቹ የይቅርታ ውሳኔ የሚሰጡት የስልጣን ዘመናቸው ማምሻ ላይ ነው።

ይህንንም ለማስረዳት የተለያዩ ስታቲስቲክሶች የሚጠቀሱ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን ሌላ ማናቸውም ዲሞክራት ፕሬዝደንት ካደረገው ይቅርታ ሁሉ የሚልቅ ይቅርታዎች አድረዋል፤ በቁጥር ሲቀመጥም ለ450 ሰዎች ይቅርታ አድርገዋል (ከነዚህ ውስጥ 140ዎቹ ሙሉ ይቅርታ ያገኙ ሲሆኑ የተቀሩት ከተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች ጋር የተደረጉ ናቸው)። ይሀንን ያደረጉት ደግሞ በመጨረሻዋ የስልጣን ቀናቸው እ.ኤ.አ. መስከረም 20 ቀን 2001 ላይ ነው። የነዚህን የይቅርታ ውሳኔዎች እንዲያጣሩ ሁለት የተለያዩ የፌዴራል ዓቃብያነ ሕግ ተሹመው ፕሬዝደንት ክሊንተንን ነፃ ናቸው የሚል ውሳኔ አቅርበዋል። ይሁን እንጂ ኋላ ላይ እ.ኤ.አ. 2006 ላይ የፖለቲካ እና የፍትህ አካላት ባለሥልጣናትን የሞራል ደረጃ ማሳደግ ላይ የሚሰራ Judicial Watch የተባለ ቡድን የፕሬዝደንት ቢል ክሊንተን ባለቤት የሂላሪ ክሊንተን ወንድም የሆነው ቶኒ ሮድሃም በነዚያ የመጨረሻ ቀናት ከተደረጉት ይቅርታዎች ከአንዱ 107,000 (አንድ መቶ ሰባት ሺህ) የአሜሪካን ዶላር ተቀብሏል በማለት እንዲከሰስለት ለአሜሪካ የፍትህ ቢሮ አመልክቶ ነበር።

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ በቅርቡ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ም/ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መድረክ ስራ አስፈፃሚ የነበሩት አቶ በቀለ ገርባ የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው አልተፈቱም በሚል የተሰራጨው ዜና ነው። አቶ በቀለ ገርባ “ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲን ሽፋን በማድረግ የአሸባሪ ቡድን የሆነው ኦነግ አባል ሆነዋል” የሚል ክስ ቀርቦባቸው በክሱም ጥፋተኛ ተብለው የተወሰነባቸውን የ8 ዓመት እስራት በይግባኝ ወደ 5 ዓመት እስራት አስቀይረው ነበር። ከዚህ የእስር ጊዜ ውስጥም ሶስቱን አመት ጨርሰው በአመክሮ ይፈቱ ዘንድ ያቀረቡት ጥያቄ «ተገቢውን» መልስ ባለማግኘቱ በማህበራዊ ሚዲያዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ሲቀርቡ ተስተውሏል። አቶ በቀለ ገርባ ለምን ከእስር አልተፈቱም? መፈታትስ ነበረባቸው? ለነዚህ ጥያቄዎች ምላሹን ከሃገራችን ህግጋት እንመልከት።

በአመክሮ የመለቀቅ ሥነሥርዓት

መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች

ምንም እንኳን በፍርድ ቤቶቻችን በአብዛኛዎቹ ችሎቶች እና በማረሚያ ቤቶቻችን እየተተገበረ ባይሆንም የወንጀል ሕጉ አንቀፅ 203/1/ “ጥፋተኛው በሚፈረድበት ጊዜና ወደሚላክበት ተቋም በሚገባበት ጊዜ የተወሰነበት ቅጣት ከመፈጸሙ በፊት ቀደም ብሎ በአመክሮ ሊለቀቅ የሚችል መሆኑን፣ ይህንንም እድል ለማግኘት ምን አይነት ግዴታ መፈፀም እንደሚገባው” ሊገለጽለት እንደሚገባ ይደነግጋል። ይህ «መብት» ለፍርደኛው ያለመገለፁ የሚኖረው ውጤት እና በዳኛው/ዳኞቹ ወይም/እና የማረሚያ ቤት ሰራተኛ/ሰራተኞች ላይ የሚያስከትለው ተጠያቂነት ግን አልተገለጸም።

አንድ በአመክሮ ለመፈታት የሚያመለክት ሰው ከተወሰነበት የዕስራት ጊዜ ከሦስት እጅ ሁለት እጁን (2/3) ወይም ፍርዱ የዕድሜ ልክ እስራት ሲሆን ሃያ ዓመት መፈፀም ግዴታ ያለበት ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች ማሟላት የሚኖርበት ቅድመ ሁኔታዎች በ1996 ዓ/ም በወጣው የኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 202 ስር እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል፦

ሀ- አስፈላጊ የሆነውን ነፃነት የሚያሳጣ ቅጣት ወይም የጥንቃቄ እርምጃ በመፈፀም ላይ ሳለ በሥራውና በጠባዩ የተረጋገጠ መሻሻል አሳይቶ እንደሆነ፤

ለ- ለደረሰው ጉዳት በተቻለ መጠን ሊከፍል የሚጠበቅበትን በፍርድ ቤት በተወሰነው መሠረት ወይም ከተበዳዩ ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት ካሣ ለመክፈሉ ማረጋገጫ አቅርቦ እንደሆነ፤ እና

ሐ- አመሉና ጠባዩ በመልካም አኗኗር ለመኖር የሚያስችለው እና በአመክሮ መፈታቱ መልካም ውጤት ሊያስገኝ ይችላል ተብሎ የታመነ እንደሆነ፤ ነው።

ይሁን እንጂ ከላይ የተመለከቱትን ቅድመ ሁኔታዎች የሚያሟላ «ልማደኛ ደጋጋሚ ወንጀለኛ» በአመክሮ ሊፈታ አይችልም።

የአመክሮ ማመልከቻ የሚያቀርበው አካል እና የሚቀርብለት ፍርድ ቤት

የአመክሮ ማመልከቻውን የሚያቀርበውን አካል አስመልክቶ በወንጀል ሕጉ እና በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዐት ሕጉ መካከል መጠነኛ ልዩነት ይስተዋላል። የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዐት ሕጉ ቁጥር 217(2) ሥር «የተፈረደበት ሰው ራሱ ወይም ሕጋዊ እንደራሴው፣ ዐቃቤ ሕጉ፣ ወይም የቅጣቱን ፍርድ እንዲያስፈፅም ወይም አፈጻጸሙን እንዲቆጣጠር የተፈቀደለት ማንኛውም ሰው ወይም ባለሥልጣን» በማመልከቻ ማመልከት እንደሚችል ተደንግጓል።

በሌላ በኩል የወንጀል ሕጉ አንቀፅ 203(2) ስር «አግባብ ያለው አካል እስረኛው በአመክሮ እንዲለቀቅ ራሱ ሃሳብ በማቅረብ ወይም እስረኛው በአመክሮ ልለቀቅ ብሎ ያቀረበውን ማመልከቻ ተቀብሎ ከነአስተያየቱ ለፍርድ ቤት ያስተላልፋል።» ተብሎ ተደንግጓል። ይሁን እንጂ አንደኛው የሥነ ሥርዓት ሕግ ሌላኛው ደግሞ የፍሬ ነገር ሕግ ከመሆናቸው አንፃር አንደኛው ሌላኛውን የመሻር ወይም የማሻሻል ውጤት ሳይሆን የሚኖራቸው የመደጋገፍና አማራጮችን የማስፋት ነው። በመሆኑም አንድ በአመክሮ ልለቀቅ ሲል ማመልከቻ የሚያስገባ ሰው በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዐት ሕጉ ወይም በወንጀል ሕጉ የተቀመጡትን መንገዶች በአማራጭነት ሊጠቀም ይችላል።

ማመልከቻው የሚቀርብለትን ፍርድ ቤት በተመለከተ አንድ ሰው በአመክሮ ከእስር እንዲፈታ/እንዲለቀቅ ተገቢውን ትዕዛዝ የሚሰጠው የቅጣቱን ፍርድ የሰጠው ፍርድ ቤት ራሱ እንደሆነ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነሥርዓት በቁጥር 216(1) እና 216/2/ሠ/ ሥር ተቀምጧል። ፍርድ ቤቱ ይህንን ማመልከቻ ተቀብሎ ለእስረኛው እና ስለእስረኛው ሁኔታ ፍርድ ቤቱ ማወቅ የሚፈልገውን ነገር መግለፅ የሚችለውን ሰው እንዲቀርብ መጥሪያ እንደሚልክ፤ አስፈላጊ ሆኖ ባገኘው ጊዜ ሁሉ በምርመራ እንዲጣራ ትዕዛዝ እንደሚሰጥ እንዲሁም በዚህ መሰረት የሚሰጠው ውሳኔ ይግባኝ የማይባልበት መሆኑ የወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 217(2) እና (5) ሥር ተደንግጓል። ፍርድ ቤቱ እስረኛው በአመክሮ እንዲለቀቅ የሚሰጠው ውሳኔ ተፈቺው በአመክሮ የሚቆይበትን ጊዜ አብሮ የሚይዝ ይሆናል። ይህ የአመክሮ ጊዜ የሚቆየው በሌላ የተለየ ሁኔታ ካልታዘዘ በስተቀር ሳይፈፀም የቀረው ቅጣት ወይም የጥንቃቄ እርምጃ እስኪፈፀም ድረስ ነው።

አመክሮ፤ መብት፣ ሸቀጥ ወይስ ችሮታ?

አመክሮ ከላይ የተጠቀሱትን ቅድመ ሁኔታዎች ያሟላ እስረኛ ተገቢውን ሥነ ሥርዓት ተከትሎ ከእስር የመለቀቅ ጥያቄውን የሚያቀርብበት በሕግ የተቀመጠለት መብት ነው። ማንኛውም ከተወሰነበት ጠቅላላ የእስር ጊዜ ሁለት ሶስተኛ የሚሆነውን ጊዜ የፈፀመ እስረኛ በወንጀል ሕጉ ከተቀመጡት ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት ጋር የሚቃረን ማስረጃ እስካልቀረበበት ድረስ ቀሪውን ጊዜ በአመክሮ ከእስር ተፈትቶ ለመኖር የሚያስችለው መብት እንዳለው ሕጉ ይደነግጋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም የሚመለከታቸው አካላት ላይ እስረኛው በአመክሮ ከእስር ለመፈታት የሚያቀርበውን ጥያቄ የማስተናገድ እና ለፍርድ ቤት የማስተላለፍ ግዴታ የሚጥል ነው። አመክሮን እንደ እስረኛው መብት ተመልክቶ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ይህንን ጥያቄ የማያስተናግድ የፍትህ ሥርዐት ካለ እስረኛው አብዛኛውን ጊዜ ይህንን መብቱን በሌሎች ኢ-ሞራላዊና ሕገ ወጥ መንገዶች ያገኛቸዋል።

በማረሚያ ቤቶች ውስጥ የእስረኛውን ሥራ፣ ጠባይ፣ አመል እና መልካም አኗኗር ለመኖር መቻል ለማወቅ የሚያስችል ወጥ የሆነ የፍርደኛ ባህሪ ግምገማ መስፈርት  (objective standard of assessment) በሌለበት ሁኔታ የፍትህ ሥርዓቱ ያለው አንድና ትክክለኛው አማራጭ በተቻለ መጠን አመክሮን እንደ መብት ለሁሉም በእኩልነት ማክበር ነው። ይህ የማይሆን ከሆነ ይህ የአመክሮ መብት ሁለት የማይፈለጉ ዕጣ ፈንታዎች ይኖሩታል። የመጀመሪያው ዕጣ ፈንታው ልክ በመግቢያው ላይ እንደተፃፈው እና በአሜሪካ መንግስት የመጨረሻውን ላዕላይ ስልጣን በያዙት ፕሬዚደንቶች ይፈፀማል ተብሎ እንደሚነገረው በማረሚያ ቤት «ሰራተኞች» እጅ ውስጥ አመክሮ «ሸቀጥ» ሆኖ መሸጥ ነው። አንባቢ ለዚህ አብነት ይሆነው ዘንድ ታስረው የሚያውቁና የማረሚያ ቤትን ቆይታ የቀመሱ ሰዎችን (በተለይም በክልል ማረሚያ ቤቶች) ስለሂደቱ ጠይቆ ሊረዳ ይችላል። በተደጋጋሚ ከነዚህ ሰዎች የሚሰማው በአመክሮ ለመለቀቅ ከማረሚያ ቤቱ የድጋፍ ደብዳቤ (recommendation letter) ለማግኘት የሚቻላቸው ሰዎች አሁን ወይም ወደፊት «መክፈል» የሚችሉት መሆናቸውን ነው። መብት የሚጠየቅ ወይም የሚከበር ነገር መሆኑ ይቀርና የሚገዛ ሸቀጥ ይሆናል።

ሁለተኛው የአመክሮ ዕጣ ፈንታ «ችሮታ» መሆን ነው። የእስረኛውን ባህርይ አስመልክቶ የማረሚያ ቤቱን የድጋፍ ደብዳቤ የሚፅፉት «ሰራተኞች» ደስ ላላቸው፣ ለሚያውቁት፣ አማላጅ ለተላከባቸው፣ ወዘተ ለመሳሰሉት ተቀጪዎች በችሮታ መልክ የሚለግሱት ስጦታ ይሆናል። አመክሮ እነሱ ለእስረኞቹ ሊያከብሩ የሚገባ መብት እና ሊያስከብሩ የሚገባቸው ግዴታ መሆኑ ይቀርና ውለታ መዋዋያ አጋጣሚ ይሆናል። ለሁለቱም የአመክሮ ዕጣ ፈንታዎች ምክንያት የሚሆነው ወጥ የሆነ የግምገማ መስፈርት ያለመሆኑ ነው፤ ይህም ግምገማውን በግለሰቦች ፍላጎት እና ቀኖና እንዲከናወን ያደርገዋል። በመሆኑም ይህንን አስመልክቶ መንግስት ወጥ የሆነ የመከታተያ ደንብ ቢያወጣ እና አሰራር ቢዘረጋ፣ ደንቡና አሰራሩ ተፈፃሚ እስከሆኑ ድረስ አንድ የ«ኪራይ ሰብሳቢነት» ቀዳዳ መድፈን ይቻለዋል።

 

ማጠቃለያ

የወንጀል ሕግ በማመሳሰል እንደማይተረጎም ግልፅ ነው። ይሁን እንጂ ሕጉም ሆነ ያለው አሰራር ስለጉዳዩ ዝም በሚሉበት ጊዜ የወንጀል ሕጉ ድንጋጌዎች የተመሰረቱባቸውን መርሆዎች በጠባቡ በመተርጎም ተግባራዊ ማድረግን የሚከለክል ነገር የለም፤ በተለይም ደግሞ የሰውን ልጅ በነፃነት የመንቀሳቀስ የሰብዓዊ መብት ለማስከበር ዓላማ። በመሆኑም አመክሮን አስመልክቶ ያለውን ይህን ችግር በቋሚነት መቅረፍ የሚቻልበት ሁኔታ እስኪፈጠር ግን ፍርድ ቤቶች ሕጉን በጠባቡ በመተርጎም ሊፈቱት ይችላሉ።

በምሳሌነትም በወንጀል ህጉ አንቀፅ 82 እና 84 መሰረት የሚቀርቡትን የቅጣት ማቅለያ እና ማክበጃ ነጥቦች መመልከት እንችላለን። አንድ ሰው ከዚህ ቀደም ወንጀል ፈፅሞ ተቀጥቶ የሚያውቅ መሆኑን ዓቃቤ ሕግ በ“ማስረጃ” ካላስረዳ ተከሳሹ ከዚህ ቀደም መልካም ፀባይ የነበረው እንደሆነና ተከሶና ተፈርዶበት የማያውቅ እንደሆነ ግምት ተወስዶበት ቅጣት ይቀልለታል። የተጠቀሰውን አይነት ወጥ የፍርደኛ ባህርይ የክትትል እና የግምገማ ደረጃ እስኪኖረን እና በተጨባጭ ማስረጃ እስክንመራ ድረስ ይህንን መርህ ለአመክሮ በመተርጎም መጠቀም የማንችል ከሆነ አመክሮ ከመብትነት ደረጃው በብዙ ዝቅ ብሎ ከላይ የተገለጹትን አይነት ሌሎች ገፅታዎች ይኖሩታል።

አቶ በቀለ ገርባ ከላይ የተጠቀሱትን ቅድመ ሁኔታዎች አላሟሉም ተብሎ በማስረጃ የተደገፈ መከራከሪያ እስካልቀረበባቸው ድረስ በማረሚያ ቤት ቆይታቸው በስራቸው እና በጠባያቸው «የተሻሻሉ» እና በመልካም አኗኗር ለመኖር የሚችሉ መሆናቸው ግምት ተወስዶበት በአመክሮ የመፈታት መብታቸው ሊጠበቅና ሊፈቱ ይገባል። ይህም እንዲሆን አንድም ማረሚያ ቤቱ አቤቱታቸውን ከአስተያየቱ ጋር ለፍርድ ቤቱ በማቅረብ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል አሊያም ፍርድ ቤቱ በራሳቸው በአቶ በቀለ ገርባ ወይም ደግሞ በሕጋዊ ወኪላቸው የሚቀርበውን የአመክሮ አቤቱታ ተቀብሎ ተገቢውን ውሳኔ ሊሰጥ ይገባል። 

“Blessed are they who maintain justice, who constantly do what is right.” PSALM 106:3

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Period of limitation, lapse of a mortgage Vs. Arti...
Making the WTO Accession Work for Ethiopia: Lesson...
 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 19 April 2024