ተከራካሪ ወገኖች እራሳቸው ወይም በተወካያቸው አማካይነት ፍርድ ቤት በሚወስነው በማንኛውም ቀጠሮ ቀን ፍርድ ቤት መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ከሳሽ አንድ ጊዜ ጉዳዩን ይዞ ከቀረበ በኋላ ተከታትሎ ከዳር ማድረስ መቻል ያለበት ሲሆን ተከሳሽም በእያንዳንዱ ቀጠሮ እየቀረበ የቀረበበትን ክስ በአግባቡ መከላከል መቻል አለበት፡፡ክስ ያቀረበ ሰው በሁሉም ቀጠሮዎች እንዲገኝ የሚጠበቅበት ቢሆንም በተያዘው ቀጠሮ ባለመገኘቱ ምክንያት ያቀረበውን ክስ መዝጋት ጨምሮ እንደ ቀጠሮው ምክንያት ሌሎች ትእዛዞች ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ክሱ ሊዘጋ የሚችለው ሕጉ ለይቶና ዘርዝሮ ባስቀመጣቸው ምክንያቶችና አጋጣሚዎች ብቻ ነው፡፡ የፍርድቤት ክርክር በከሳሽ እና ተከሳሽ ይሁንታ ላይ ተመስርቶ በፈለጉ ቀን የሚቀርቡበት ደስ ካላላቸው ደግሞ የማይቀርቡበት ሂደት አይደለም፡፡
አንድን ጉዳይ ለማየት የተሰየመ ፍ/ቤት የተለያዩ ክንዋኔዎችን ለመፈፀም በርካታ ቀጠሮዎች እንደሚሰጥ የታወቀ ነው፡፡ በሙግት ሂደት ፍርድ ቤት የተለያዩ ጉዳዮች መከናወናቸውን ለማረጋገጥ የተለያዩ ቀጠሮዎችን ይሰጣል ይላል የፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት ሰበር ሰሚ ችሎት መዝገብ ቁጥር 14184፡፡ አንድን ጉዳይ አይቶ ውሣኔ ለመወሰን በርካታ ቀጠሮዎችን ፍርድ ቤት እንደሚሰጥ የሚታወቅ ሲሆን ከነዚህ በርካታ ቀጠሮዎች መካከል በአንዱ ወይም በሌላኛው ወይም በሁለቱም አለመቅረብ ምክንያት ፍርድ ቤት የተለያዩ ትዕዛዞችን እንደሚሰጥ አትቶታል መዝገቡ፡፡ የቀጠሮ አለመከበር ቀጠሮ ከተሰጠበት ምክንያት ተነጥሎ የሚታይ ባለመሆኑ የቀጠሮውን ምክንያት ከግምት በማስገባት የሚሰጠውም ትእዛዝ የተለያየ ነው፡፡
አንድ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ተከራካሪ ወገኖች ክሱ በማንኛውም ደረጃ ላይ ባለበት ጊዜ መቅረብ ባይችሉ ተፈፃሚ ሊሆኑ የሚችሉ ድንጋጌዎች እነዚህን ሁኔታዎች በቅጡ ለመገንዘብ የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጋችን የከሣሽ ና/ወይም የተከሣሽ አለመቅረብ (non appearance of parties) አስመልክቶ ያስቀመጠውን ሥርዓት ከአጠቃላይ የሙግት ሂደት ጋር አገናዝቦ መመልከቱ ጠቃሚ ነው ይላል የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን በተመለከቱ ፍርዶቹ፡፡
በዚህ ጽሑፍም ፍርድ ቤት ከሚሰጣቸው የተለያዩ ቀጠሮዎች እና ውጤታቸው ጋር በተያያዘ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉን ድንጋጌዎች እና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎችን ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡