- መግቢያ
በተሻሻለው የኢትዮጲያ የቤተሰብ ህግ አንቀፅ 1 መሰረት ህጋዊ ጋብቻ በተለያዩ ሰነ-ስረዓቶች ሊፈፀም ይችላል፡፡ እነሱም በክብር መዝገብ ሹም ፊት፣በሐይማኖት እና በባህል መሰረት የሚፈፀሙ የጋብቻ አይነቶች ናቸው፡፡ በተጨማሪም ጋብቻ ከላይ በተጠቀሱት በአንዳቸው ስነ-ስርዓቶች ቢፈፀም እንኳን ውጤቱም አንድ መሆኑን የዚሁ ህግ አንቀፅ 40 ያትታል፡፡ ህጋዊ ጋብቻ በተጋቢዎቹ ላይ ሁለት ዓይነት ውጤት ይኖረዋል፡፡ የመጀመሪያው በተጋቢዎች ግለዊ ግንኙነት ላይ የሚኖረው ውጤት ሲሆን፤ በስሩም የመከባበር ፣ የመተጋገዝና የመደጋገፍ ግዴታ ፣ ቤተሰብን በጋራ የመስተዳደር እና በጋራ አንድ ላይ የመኖር ግዴታዎችን ያቅፋል፡፡ ሁለተኛው ውጤት ደግሞ ጋብቻ በተጋቢዎች ንብረት ላይ የሚኖረው ውጤት ነው፡፡ ይህም ተጋቢዎች ጋብቻቸውን በሚፈፅሙበት ጊዜ በግል የነበሯቸው ንብረቶች ወይም ከጋብቻ በኋላ በውርስ እና በስጦታ በየግላቸው ያገኙዋቸው ንብረቶች የግል ንበረታቸው ሆነው ሲቀሩ ከዚህ ውጪ ያሉ ንብረቶች በሙሉ የጋራ ንብረት ይሆናሉ፡፡
ከጥንት ጀምሮ በወነዶችና በሴቶች መካከል ከነበሩ ማህበራዊ ግንኙነቶች መካከል ጋብቻ ሳይፈፀሙ እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር አንዱ ነው፡፡ የዚህ አይነት ግንኙነት ምንም እንኳን ለቤተሰብ መመስረት ምክንያት ቢሆንም በህግ አግባብ የሚደረግ ጋብቻ ሟሟላት ያለባቸውን ሁኔታዎችን ያላሟላ ስርዓት ነው፡፡ በሀገራችን እንደ ፍትሃ ነገስት ያሉ ጥንታዊ ጋብቻ ህጎች ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖሩን ቢያወግዝም የፍትሐብሔር ህግ እና በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አስፈላጊነቱን በማመን ከለላ አድረግውታል፡፡
- አንድምታዎቹ
የተሸሻለው የኢትዮጲያ የቤተሰብ ህግ በአንቀፅ 98 ስር እንደሚያትተው ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር ማለት አንድ ወንድ እና አንድ ሴት በህግ በሚፀና አኳኋን ጋብቻ ሳይፈፀሙ በትዳር መልክ የኖሩ ሲሆን ነው፡፡ የዚህ አይነቱ ግንኙነት በህግ አግባብ ከሚደረጉ ጋብቻ ጋር ተቃራኒ ነው ተብሎ ሰለሚታሰብ እንደ “ፍተሃ ነገስት” ያሉ ጥንታዊ ህጎች እንደ ሃጥያት በመቁጠር ያወግዙት ነበር፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ በዓለማችን ከትዳር ውጪ የሚወለዱ ልጆችና የፍቺ መጠን ፍጥነት እየጨመረ ሲመጣ በተቃራኒው ደግሞ ከትዳር ውጪ አብሮ መኖር እየተለመደና እየበዛ መጥቷል፡፡ ይህም ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት አብሮ መኖርን ከለላ መስጠት አስፈላጊ እና የማይታለፍ መሆኑን ህጉ ተቀብሎታል:: እንደምክንያትነትም የኢትዮጲያ ህግ መንግስት አንቀፅ 34 ለቤተሰብ የሚሰጠው ከለላ ይነሳል፤ ይህም ልክ በህግ እንደሚደረግ ጋብቻ ሁሉ ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖርም ቤተሰብን ይመሰረታል፡፡