አቶ ገብረመስቀል (Gebremeskes Gebrewahd) ወቅታዊ የሆነን ጉዳይ በማንሳትህ ላመሰግንህ እወዳለሁ፡፡ ባነሳኸው ጥያቄ ማለትም የሳይበር ክልል በሃገሮች ሉአላዊነት ላይ ምን ፋይዳ አለው? የሳይበር ክልል መተዳደር ያለበት በሃገራዊ ህግ ነው ወይስ በአለም አቀፍ ህግ? በሚሉ ጉዳዮች ላይ የኔ አስተያየት የሚከተለው ይመስላል። በኔ እምነት በቅድሚያ በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ግልፅ መሆን ያስፍልጋል።
· የሳይበር ክልል ምን ማለት ነው?
· የሳይበር ክልል ራሱን የቻለ አዲስ አለም (ክልል) ነው ወይ?
· የሳይበር ክልል እንዴት ይተዳደራል (እንዴት መተዳደር አለበት)?
በሳይበር ክልል ላይ የሚሰጡ ትርጓሜዎች ብዙ ጊዜ የተወሳሰቡ፣ የተጋነኑ አንድ አንዴም ከእውነታ የራቁ መስለው ይታያሉ። የሳይበር ክልል ብዙ ጊዜ ከነባራዊው አለም ውጭ የተፈጠረ አዲስ አለም ተደርጎ ሲቀርብም ይታያል። “የሳይበር ክልል/አለም” የሚለው ስያሜ በራሱ አሳሳች (misleading) ሊሆን ይችላል። እውነታው ግን የሳይበር ክልል ማለት ኢንተርኔት ማለት ነው። ኢንተርኔትስ ምን ማለት ነው? ኢንተርኔት እርስበርሳቸው የተሳሰሩ ኔትዎርኮች (inter-net) ማለት ነው። ኢንተርኔት የኮምፒውተሮች፣ መሳሪያዎች ወይም ዳታዎች ትስስር ሳይሆን የኔትዎርኮች ትስስር ነው። እነዚህ ኔትዎርኮች እርስበርስ በመተሳሰር አለም አቀፍ ኔትዎርክ (ኢንተር-ኔት) ይፈጥራል በዚህም በቢሊዮን የሚቆጠሩ ኮምፒውተሮች እና መሰል መሳሪያዎች እንዲገናኙ፣ መልእክት እንዲለዋወጡ ያስችላሉ። ስለዚህ የሳይበር ክልል = ኢንተርኔት= እርስበርስ የተሳሰሩ ብዙ ኔትዎርኮች (network of networks) ማለት ነው።