ተከላካይ ጠበቃ ስለማግኘት መብት ጥቅል እይታ

 

መግቢያ

በአሁኑ ወቅት በስፋት ተቀባይነት ካገኙ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች በወንጀል ተከሰው ለጠበቃ የመክፈል አቅም ለሌላቸው ሰዎች የሕግ  ድጋፍ መስጠት አንዱ ነው። በመሆኑም ተከላካይ ጠበቃ የማግኘት መብት የተከሰሱ ሰዎች ካሏቸው ሕገ-መንግስታዊ  መብቶች ቀዳሚው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ለምን ቢሉ በዓለማቀፋዊም ይሁን በአሕጉራዊ ስምምነቶች እንዲሁም በዝርዝር ብሄራዊ ሕጎች እውቅና የተሰጣቸውና ጥበቃ የሚደረግላቸው የተከሰሱ ሰዎች መብቶች የሚከበሩበት በመሆኑ ነው።

የተከሰሱ ሰዎች ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ሊከበሩላቸው የሚገቡ በርካታ መብቶች አሏቸው። ከእነዚህ ውስጥ በዳኝነት አካላት ፊት በእኩልነት የመታየት፣ ጥፋተኝነታቸው እስካልተረጋገጠ ድረስ ንፁህ ተደርገው የመገመት፣ ፍትሀዊ በሆነና በግልጽ ችሎት የመዳኘት፣ የተፋጠነ ፍርድ የማግኘትና ይግባኝ የማቅረብ መብቶች ይገኙበታል። በተጨማሪም ክሱን በጽሁፍ የማግኘት፣ ተከሳሾች በራሳቸው ላይ ያለመመስከር፣ የመከላከያ ምስክሮችንና ማስረጃዎቻቸውን የማቅረብ፣ ለአቃቤ ሕግ ምስክሮች መስቀለኛ ጥያቄ የማቅረብ፣ እንዲሁም በመንግሥት እጅ የሚገኙ ማስረጃዎችን የማግኘት መብቶቻቸውም ሳይጠቀሱ የማይታለፉ ናቸው።

ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ በበርካታ ሕገ-መንግስታት፣ በዓለማቀፋዊና በአሕጉራዊ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች እውቅና ያገኙ መብቶች ብዙውን ጊዜ ሲከበሩ ሳይሆን ሲጣሱ ነው የሚታየው። ይህም የሚሆነው ለእነዚህ መብቶች መከበር መሰረታዊ የሆነው የተከሰሱ ሰዎች ተከላካይ ጠበቃ የማግኘት መብት ሕጉ ላይ በተቀመጠው ልክ በተግባር እየተፈጸመ ባለመሆኑ ነው።

Continue reading
  15642 Hits