Font size: +
8 minutes reading time (1504 words)

በሰዎች መነገድ/ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ምንድነው?

በአገር ውስጥ እና በተለይም ወደ ሌሎች አገራት የሚካሄድ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በኢትዮጵያ ውስጥ የላቀ ትኩረት እያገኘ መጥቷል፡፡ ይህም ትኩረት በቅርቡ ጉዳዩ እያገኘ ካለው ሰፊ የሚድያ ሽፋን ባሻገር ችግሩን ለመፍታት በተከታታይ በመንግስት እየተወሰዱ ያሉ የሕግ፣ የፖሊሲና የፕሮግራም እርምጃዎች ላይ ይንፀባረቃል፡፡ ለዚህ ጉዳይ የተሰጠው ትኩረት ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም አልፎ አልፎ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ምንነት ጋር በተያያዘ የተወሰነ ግራ መጋባት ይታያል፡፡ ይሕ አጭር ጽሁፍ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ለሚደረው ጥረት አስተዋጽኦ ያደርጋል በሚል እምነት የተዘጋጀ ነው፡፡

ትርጉም

የተ.መ.ድ. እ.ኤ.ኤ. በ2000 ዓ.ም. ያወጣውና የፓሌርሞ ስምምነት በመባል የሚታወቀው ስምምነት በሰዎች መነገድ ወይም ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ለብዝበዛ ዓላማ ሰዎችን (በተለይም ሴቶችና ሕፃናትን) በኃይል፣ በዛቻ፣ በተንኮል፣ በማታለል፣ በመጥለፍ ወይም በተበዳይ ላይ ኃላፊነት ላለው ሰው ገንዘብ ወይም ሌላ ጥቅም በመስጠት መመልመል፣ ማጓጓዝ፣ ማስተላለፍ፣ መደበቅ ወይም መቀበል ማለት እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ሕፃናትን በተመለከተ ለብዝበዛ ዓላማ እስከሆነ ድረስ ሕፃናቱን መመልመል፣ ማጓጓዝ፣ ማስተላለፍ፣ መደበቅ ወይም መቀበል በራሱ በሰዎች መነገድ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በሴቶችና በልጆች መነገድን የሚከለክለው የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 597 እና 635 ላይም ይኸው ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡ ከዚህ ትርጓሜ መረዳት እንደምንችለው በሰዎች መነገድ በዋነኛነት ሦስት ነገሮችን ያጠቃልላል፡፡ እነዚህም፡ - (1ኛ) በኃይል ወይም በማታለል መመልመል (ምልመላ)፣ (2ኛ) በአገር ውስጥ ወይም ወደ ሌላ አገር በህጋዊ ወይም ህገ-ወጥ መንገድ ማዘዋወር (ዝውውር)፣ እና (3ኛ) አዘዋዋሪዎች ተበዳዮችን የገንዘብ ጥቅም ማግኛ ማድረጋቸው (ብዝበዛ) ናቸው፡፡

በሰዎች መነገድ ከሌሎች የሰዎች ዝውውር ክስተቶች ጋር በተለይም ከኢ-መደበኛ የሰዎች ዝውውር እና ከሕገወጥ የድንበር ዝውውር ጋር የሚምታታበት ሁኔታ ይከሰታል፡፡ ይህም የሰዎች ንግድ ተጎጂዎች እንደ ወንጀለኛ የሚታዩበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ በአጠቃላይ ሰዎች በአገር ውስጥ ወይም ወደ ውጭ አገር ከቦታ ወደ ቦታ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ወይም ስደት ስራ ፍለጋ፣ ለተሻለ ህይወት፣ መሳደድን በመፍራት፣ ከጭቆና ወይም የተፈጥሮ አደጋ ለመሸሽ ብሎም የመኖሪያ ቦታን ለመቀየር ሲባል ሊካሄድ ይችላል፡፡ በአንፃሩ በሰዎች መነገድ ዓላማው ብዝበዛ ሲሆን ስደተኞች ለዚህ ሁኔታ ተጋላጭ ናቸው፡፡

ከሁለት ዓመታት በፊት በአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የተደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን መካከል 76.7 በመቶ የሚሆኑት የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች ናቸው፡፡ በተለይም እድሜያቸው ከ18 አመት በታች ከሆኑት እና ወደተለያዩ የሰሜን አፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ስራ ፍለጋና ሌሎች ምክንያቶች ከተጓዙት ኢትዮጵያውያን መካከል 7.5 በመቶ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ13 እስከ 17 አመት መሆኑን እና ከነዚህም ውስጥ 87.1 በመቶ የሚሆኑት የሕገወጥ ዝውውር ሰለባዎች እንደነበሩ ሌሎች ጥናቶች አመልክተዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአገሪቱ እስከ 50 ሺህ ኢትዮጵያውያን የሚገኙ ሲሆን እስከ 95 በመቶ የሚሆኑት እዚያ የሚደርሱት በሕገወጥ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች በኩል ነው፡፡

ምንም እንኳን ዝርዝር መረጃዎችን ማግኘት ቢያስቸግርም በአገር ውስጥም ቢሆን ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከአንድ ሺህ በላይ የሚገመቱ ሕገወጥ ደላሎች ይገኛሉ፡፡ በተመሣሣይ በያንዳንዱ የክልል ከተማ ከ8 እስከ 25 እና ከዚያም በላይ የሚሆኑ ሕገወጥ ደላሎች እንዳሉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

በሰዎች መነገድ/ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ምክንያቶች

በአጠቃላይ ድህነት፣ የኤኮኖሚ ቀውስ እና ቀድመው ወደ ውጭ አገር የተጓዙ ሰዎች ሁኔታ በኢትዮጵያ ለስደት ግፊት ከሚሰጡ ታሳቢዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ ለአብነት ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ባካሄደው ጥናት ከተሳተፉት ውስጥ 52 በመቶ የሚሆኑት አገራቸውን ለመልቀቅ የተነሳሱት በስራ አጥነት እና አማራጭ በማጣት እንደሆነ ሲገልጹ 36 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ድህነትን እንደምክንያት ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያለው ሌላው ምክንያት ደግሞ ልጆች ለቤተሰቦቻቸው ድጋፍ ለማድረግ የሚጠበቅባቸውን ግዴታ ለመወጣት መነሳሳታቸው እንደሆነ ይታሰባል፡፡ በተለይም ሴቶች ከኤኮኖሚያዊ ምክንያቶች ባሻገር ከፆታ መድልዎ ጋር የተያያዙ ምክንያቶች ለመሰደድ እንዲያስቡና ለሕገወጥ አዘዋዋሪዎች እንዲጋለጡ ያደርጋሉ፡፡

በሰዎች መነገድ/ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ውጤቶች

ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ሰዎችን በመመልመል፣ በማዘዋወር እና በመበዝበዝ ሂደት ተጠቂዎችን ለመቆጣጠር የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ፡፡ በሰዎች የመነገድ ዓላማ ከተጠቂዎች ብዝበዛ ለመጠቀም እንደመሆኑ አዘዋዋሪዎች ተጠቂዎችን ለመቆጣጠር እና እንዳያመልጡ ለማድረግ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ በእዳ መያዝ፣ ከሌሎች ጋር በማይገናኙበት ቦታ ማስቀመጥ፣ መታወቂያና ለሎች ሰነዶችን መንጠቅ፣ በኃይልና ዛቻ ማዋከብ፣ በቤተሰብ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ማስፈራራት የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ ስለዚህም ተጠቂዎች ከምልመላ ጀምሮ ባሉት ሂደቶች ሰብአዊ መብት ጥሰት ይፈጸምባቸዋል፡፡ በተለይም ከምልመላ በኋላ ባሉት ሂደቶች ለአካላዊ፣ ስነ-ልቦናዊና ፆታዊ ጥቃት የሚጋለጡበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ተጠቂዎች ከሌሎች ጋር ለመገናኘት እንዳይችሉ ተደርገው በሚቆዩበት ጊዜ ለችግራቸው መፍትሄ ለማግኘት የሚመለከታቸውን አካላት ማግኘት አይችሉም፡፡ ከበዝባዦቻቸው ማምለጥ እንኳ ቢችሉ እንደ ወንጀለኛ የሚታዩበት ሁኔታ ሊኖር ስለሚችል ለቅጣት ይዳረጋሉ፡፡ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ከግል ተበዳዮች አልፎ በሚኖሩበት ማህበረሰብም ላይ ከፍተኛ ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት ያደርሳል፡፡ ችግሩ በአፋጣኝ ካልተፈታም ሙስና እና ንቅዘት እንዲስፋፋ ብሎም መንግስት የሕዝብን አመኔታ እንዲያጣ ሊያደርግ ይችላል፡፡

በአዘዋዋሪዎች ጥቅም ላይ የሚውሉ ዘዴዎች

የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሂደት የሚጀምረው ከምልመላ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ተጠቂዎች የሚጠመዱት የተሻለ ነገር እንደሚያገኙ ተደልለው፣ የተሳሳተ መረጃ ተሰጥቷቸው ወይም ተስፋ በመቁረጥ ተገፋፍተው ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ተጠቂዎቹ ለምን ጉዳይ ወይም ስራ እንደሚሄዱ ቢያውቁም ስለስራ ሁኔታው ትክክለኛ መረጃ አይኖራቸውም፡፡ አልፎ አልፎም ተጠቂዎች በኃይል ወይም በሌላ መልኩ ተገደው ከዚያም አልፎ ታፍነው ሊሆን ይችላል፡፡ ምልመላውም የሚካሄደው በቤተሰብ አባላት፣ በዘመዶች፣ በጓደኞች፣ በጎረቤቶች፣ በደላሎች፣ በኤጀንሲዎች ወይም በሌላ አካል ሊሆን ይችላል፡፡

የሕገወጥ ዝውውር ሰለባዎች ከተመለመሉ በኋላ ከተመለመሉበት ቦታ ወደ ሌላ ከተማ ወይም አካባቢ አንዳንዴም ወደ ሌላ አገር ይጓጓዛሉ፡፡ በዚህም ሂደት ዝውውሩን በማቀላጠፍ፣ አስፈላጊ ሰነዶችን በማዘጋጀት፣ በመንገድ ላይ ማረፊያ በማመቻቸት ወዘተ … የተለያዩ ሰዎች ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡ አልፎ አልፎም ድንበር ጠባቂዎች፣ የኢሚግሬሽን ሰራተኞች ወይም የሕግ አስከባሪ አባላት በሂደቱ ሊኖሩበት ይችላሉ፡፡ የትራስፖርት አገልግሎት ሰጭዎችም ለዚህ ተባባሪ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ተጠቂዎችን የማዘዋወር ዋነኛው ዓላማ በተለያዩ እንደ ሴተኛ አዳሪነት፣ የቤት ውስጥ ስራ፣ የግዴታ ስራ ወዘተ … በማሰማራት እና አልፎ አልፎም የሰውነት ክፍሎችን በመውሰድ ተጠቃሚ ለመሆን ነው፡፡ በሌላ አባባል የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወይም በሰዎች መነገድ ዓላማ ተጠቂዎችን በመበዝበዝ ትርፍ ማግኘት ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ በመዳረሻ ቦታዎች ተጠቂዎችን በመቀበል እና የመታወቂያ ሰነዶችን በመቀማት በሚኖሩበት ቦታ በሕገወጥነት እንዲታዩ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ምንም እንኳን ብዙ ተጠቂዎች ከአገር ለመውጣት የሚገጠቀሙበት ዘዴ ሕገወጥ ቢሆንም ሌሎች ደግሞ በሕጋዊ ሁኔታ የሚጓጓዙበትም ሁኔታ ይኖራል፡፡ ከደረሱ በኋላ ግን አዘዋዋሪዎች ተጠቂዎች እንዳያመልጡ፣ ወደመጡበት እንዳይመለሱ ወይም ሌላ ቦታ እንዳይሄዱ እንደ እስር ቤት ባለ ሁኔታ አግተው ይይዟቸዋል፡፡ ከዚህም አልፎ በሚበዘብዝ ሁኔታ ለማሰራት ኃይልና ዛቻ ይጠቀማሉ፡፡

የአዘዋዋሪዎች ማንነት

በኢትዮጵያ የተካሄዱ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከማንነት፣ ከአሰራርና በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሂደት ከሚኖራቸው ሚና አንፃር አዘዋዋሪዎች በአምስት ሊመደቡ ይችላሉ፡፡

በመጀመሪያው ምድብ የሚገኙት ተጠቂዎቹ በሚኖሩባቸው ማህበረሰቦች ውስጥ የሚገኙ የአካባቢ ደላሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ደላሎች የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨትና በሌሎች ዘዴዎች ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አመቺ ሁኔታ የመፍጠር እና ተጋላጭ ግለሰቦችን በመለየት የዝውውር ሂደቱን የመጀመረ ሚና አላቸው፡፡ ብዙውን ጊዜ የአካባቢ ደላሎች የሚንቀሳቀሱት የምልመላ እና በመደበኛና ኢ-መደበኛ መንገዶች የማዘዋወር ሂደቱን ከሚያከናውኑ ሌሎች አዘዋዋሪዎች ጋር በመሆን ነው፡፡

በሁለተኛው ምድብ ያሉት ደግሞ ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ ሰዎችን የሚያዘዋውሩና ድንበር የሚያሻግሩ የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ናቸው፡፡ እነዚህ አዘዋዋሪዎች ሰዎችን በቡድን ከአካባቢ ደላሎች ተቀብለው ለሌሎች ተመሳሳይ አዘዋዋሪዎች በማስተላለፍ በቅብብሎሽ የሚያደርሱ ናቸው፡፡

በሶስተኛ ደረጃ የሚገኙት ደግሞ በትላልቅ ከተሞች የሚንቀሳቀሱና ወደ መዳረሻ ቦታዎች በመደበኛ የጉዞ መስመሮች የሚደረገውን ጉዞ የማቀላጠፍ እና ቅጥር የማመቻቸት አላፊነት የሚወስዱ ደላሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ደላሎች ከአካባቢ ደላሎች ሰዎችን ተቀብለው በመዳረሻ አገራት ለሚገኙ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች ያስተላልፋሉ፡፡ በዚህም ከሥራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ጋር ተመሳሳይ ነገርግን ህገወጥ የሆነ ስራ ይሰራሉ፡፡

በአራተኛው ምድብ የሚገኙት ከስደት ተመላሾችና ቤተሰቦቻቸው ሲሆኑ ሌሎች ሰዎች እነሱ ወደነበሩበት አገር በመሄድ እንዲቀጠሩ በግለሰብ ደረጃ ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በግል ትውውቅ ወደ ውጭ አገር ለመጓዝ የሚሹ ዘመድና ጎረቤቶችን ከማገዝ ባለፈ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በመደበኛነት በመያዝ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡

በመጨረሻ የምናገኛቸው በመዳረሻ አገራት የሚገኙ እና በመደበኛና ኢ-መደበኛ መንገዶች በመዳረሻ ቦታዎች የሰዎች ዝውውር ላይ የተጠመዱ አዘዋዋሪዎች ናቸው፡፡ ከተለያዩ ምንጮች የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው እነዚህ አዘዋዋሪዎች በመዳረሻ አገራት የሚገኙ ደላሎች፣ የስራና ሰራተኛ አገናኝ ድርጅቶች ወይም ቀደም ብለው የሕገወጥ ዝውውር ሰለባ የሆኑ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ተጠቂዎችን በማታለል፣ በማስገደድ ወይም በማስፈራራት ለብዝበዛ በቀጥታ የሚያጋልጡ አዘዋዋሪዎች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜም በብዝበዛው ሂደት ቀጥተኛ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

በሰዎች መነገድ/ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች የሚያጋጥሟቸው ችግሮች

የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተጠቂዎች ለተለያዩ ጉዳቶች ይጋለጣሉ፡፡ ከሚኖሩበት አካባቢ ተነስተው ኢ-መደበኛ በሆኑ መንገዶች እና የኮንትሮባንድ ንግድ መስመሮች የሚያደርጉት አደገኛ ጉዞ፣ በዝውውሩ ሂደት በአዘዋዋሪዎች እጅ የሚደርስባቸው ጥቃትና ብዝበዛ፣ በመዳረሻ አገራት የሚያጋጥማቸው አስከፊ የሥራ ሁኔታ ተደማምረው በተጠቂዎች ላይ ዘለቄታዊ የአካል፣ የአእምሮ እና ማህበራዊ ጠባሳ ያሳድራሉ፡፡ ይባስ ብሎም በአዘዋዋሪዎች እጅ እና በተፈጥሮ አደጋ ሕይወታቸውን የሚያጡበት ሁኔታም ይፈጠራል፡፡

ከግል ህይወት አኳያ የሕገወጥ ዝውውር ሰለባ የሆኑ ሰዎች ወጣትነቻውን ከቤተሰቦቻቸውና ከማህበረሰቡ ርቀው በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ያሳልፋሉ፡፡ በመሆኑም የተሟላ ስብእና ለመገንባት የሚችሉበት ጊዜ ይባክናል፡፡ ይህም ከሚደርስባቸው ብዝበዛና ጥቃት ጋር ተደማምሮ ለተለያዩ የስነልቦና ችግሮች ያጋልጣቸዋል፡፡ ከዚያም አልፎ የወንጀል ድርጊት ተሳታፊ እና ተጠቂ የመሆን እድላቸውን ያሰፋዋል፡፡

ከማህበራዊ ህይወት አንፃር ደግሞ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተጠቂዎችን ከመደበኛው ማህበራዊ ምህዳራቸው በማውጣት ማህበራዊ ህይወታቸውን የማዛባት እንዲሁም ከማህበራዊ ድጋፍ በማራቅ ይበልጥ ተጋላጭ እንዲሆኑ የማድረግ ውጤት አለው፡፡ በተለይም ተጠቂዎች የሚኖሩበት ሁኔታ ከለመዱት በእጅጉ የተለየ ሲሆን እና መሰረታዊ እምነታቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ድርጊት እንዲፈፅሙ ወይም ባልተለመደ ማህበራዊ ሂደት ውስጥ እንዲሳተፉ ሲገደዱ (ለምሳሌ የቀጣሪዎቻቸውን እምነት እንዲከተሉ ሲገደዱ) ችግሩ የባሰ ይሆናል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ማህበራዊ መገለል እና ጫና በተጠቂዎች ላይ ዘላቂ ችግር በማድረስ ወደ ማህበረሰባቸው ሲመለሱ በቀላሉ መቀላቀል እንዳይችሉና ገለልተኛ ሆነው እንዲቀጥሉ ያደርጋቸዋል፡፡

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በተጠቂዎች ኤኮኖሚያዊ ህይወት ላይም የሚያሳድረው ጫና ቀላል አይደለም፡፡ ከመነሻው ሕገወጥ ደላሎች የሚጠይቁትና በማታለልም ሆነ በግድ የሚወስዱት ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ የተጠቂዎች ቤተሰቦች ለከፍተኛ እዳ ይዳረጋሉ፡፡ ከዚያም አልፎ ብዙውን ጊዜ ደመወዛቸውን በጊዜውና ሳይቀናነስ የማግኘት እድል ስለማይኖራቸው በተመለሱ ጊዜ ለደረሰባቸው ስቃይ ማካካሻ ሊሆን የሚችል ገንዘብ አይኖራቸውም፡፡ አፍላ የወጣትነት ጊዜያቸውን ለአዘዋዋሪዎች ጥቅም ማሳለፋቸውም በዘላቂ ህይወታቸው ሰርተው የማግኘት እድላቸውን ያጠበዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ጎልቶ የሚታየው ችግር ግን በተጠቂዎች ጤና ላይ የሚደርሰው ነው፡፡ የተለያዩ ጥናቶች እንዳሳዩት የአእምሮ መታወክ፣ አካላዊ ጉዳት እና ሞት በተጠቂዎች ላይ በተደጋጋሚ ይደርሳሉ፡፡ ተጠቂዎች እጃቸውና እግራቸው ተሰብሮ ወይም ባልታወቀ ምክንያት ሞተው ሬሳቸው የሚመጣበት አጋጣሚ በተደጋጋሚ ተከስቷል፡፡ የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተጠቂዎች መካከል የሚበዙት የአእምሮ ችግር እና እንደ ስብራት፣ መቃጠል፣ የምግብ እጥረት እና ፆታዊ ጥቃት ጋር የተያዙ የጤና ችግሮች ሰለባ ናቸው፡፡ በስራላይ የነበሩበትን የመጨመረሻ ቀናት የማያስታውሱ፣ ላንቃቸው የተዘጋ፣ ራሳቸውን ፖሊስ ጣቢያ፣ ሆስፒታል ወይም አዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እንዳገኙ የሚናገሩ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡

በሰዎች መነገድ/ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተጠቂዎችን መለየት

ምንም አንኳ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በስውር የሚካሄድ ድርጊት ቢሆንም ለሕዝብ እይታ የሚጋለጥበት ሁኔታ በተደጋጋሚ ይከሰታል፡፡ ይህም በተለይ የሚሆነው በምልመላ ጊዜ፣ ድንበር በመሻገር ወቅት እና አልፎ አልፎም ብዝበዛ በሚካሄድባቸው ቦታዎች ነው፡፡ ምልመላ በንግግር እና በቀጥተኛ ግንኙነት የሚካሄድ እንደመሆኑ ከሌሎች የዝውውር ሂደት ደረጃዎች በበለጠ የተጋለጠ ሂደት ነው፡፡ ድንበር የመሻገር ሂደትም እንዲሁ፡፡ ለምሳሌ በአውቶቡስ ተርሚናሎች፣ በኤርፖርቶችና ሌሎች የትራንስፖርት ማእከላት አዘዋዋሪዎችና ተጠቂዎች ሊለዩ ይችላሉ፡፡ እንደሁኔታው በብዝበዛ ወቅትም ሰዎች የህገወጥ ዝውውር ሰለባ መሆናቸው ሊታወቅ ይችላል፡፡ ለአብነት እድሜአቸው በጣም ሕፃን የሆኑ ሰራተኞች ያሉበት ቦታ ወይም አግባብ ያልሆነ የሥራ ሁኔታ ይህንን ሊጠቁም ይችላል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Exploring Issues in the Renewal of Licenses for Ch...
Article 2121 of the civil code Vs Anti-suit or Ant...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 11 October 2024