- Details
- Category: Employment and Labor Law
- Hits: 14522
የአካል ጉዳት መጠን ደረጃዎች
የአካል ጉዳት መጠን ደረጃዎች በአራት ይከፈላሉ፡፡ ይኸውም
- ጊዜያዊ የአካል ጉዳት
- ዘላቂ ከፊል የአካል ጉዳት
- ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት እና
- ሞት ናቸው፡፡ እንደየቅደም ተከተላቸው በሚከተለው ሁኔታ እናያቸዋለን፡፡
ሀ. ጊዜያዊ የአካል ጉዳት፡-
የዚህ ጉዳት ሰለባ የሆነ ሠራተኛ የተመደበበትን ሥራ ለተወሰነ ጊዜ በሙሉ ወይም በከፊል ለማከናወን እንዳይችል ይሆናል አንቀጽ (100)፡፡ የመሥራት ችሎታው መቀነስ ወይ መጥፋት ጉዳቱን ለመጠገን በሚወስደው ጊዜ ይገደባል፡፡ ከዚያ በኋላ የመሥራት ችሎታው ይመለሳል፡፡ በአብዛኛው የጊዜው ርዝማኔ ከአንድ ዓመት የሚዘል አይሆንም፡፡ ለዚህ መነሻ የሚሆነው በአንቀጽ 107(1) cum 108(1) እና 108(3)(ሐ) ላይ የተገለፀው ነው፡፡ ጊዜያዊ የአካል ጉዳት እስከሚወገድበት ጊዜ ድረስ ተገቢው ክፍያ ሲፈፀም ቢቆይም ይህ በየጊዜው የሚሰጠው ክፍያ ከአንድ ዓመት የሚዘል አይሆንም [አንቀጽ 108(1)]፡፡ ይህ ማለት ጊዜያዊ የአካል ጉዳት ከአንድ ዓመት ያለፈ የመሥራት ችሎታን የሚያሳጣ አይደለም የሚለውን ሐሳብ የሚያመጣ ነው፡፡
ለ. ዘላቂ ከፊል የአካል ጉዳት ፡-
ይህ ጉዳት የደረሰበት ሠራተኛ የማይድን እና የመሥራት ችሎታውን የሚጐዳ ችግር ይገጥመዋል [አንቀጽ 101(1)] ፡፡ የመሥራት ችሎታው መቀነስ ለተመደበበት ሥራ ብቻ ሳይሆን በተመሣሣይ ሥራ ላይ ያለውን የመሠራት ችሎታ ጭምር የሚመለከት ነው፡፡ በያዘው የሥራ መደብ ላይ መሥራቱን ቢቀጥልም ባይቀጥልም የመሥራት ችሎታው አንድ ጊዜ የቀነሰ እና አብሮት የሚዘልቅ በመሆኑ መለኪያው ይሠራ የነበረው ሥራ ብቻ አይሆንም፡፡ በሌላ ቦታ በሌላ ጊዜና ሁኔታ ሊሠራ ይችል ለነበረው ለዚያው ሥራ ያለውን አቅም የሚያዳክም በመሆኑ ይኸው ግምት ውስጥ የሚገባ ይሆናል፡፡
ሐ. ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት
ይህ ጉዳት ደግሞ ማናቸውንም ደመወዝ የሚያስገኝ ሥራ ለመሥራት የሚከለክል የማይድን ጉዳት ነው [አንቀጽ 101 (2)] :: ከፍ ብሎ ከተገለፀው ዘላቂ ከፊል የአካል ጉዳት ይህ በሁለት ዐቢይ ነጥቦች የሚለይበትን ሀሳብ ይዞ ቀርቧል፡፡ የመጀመሪያው የጉዳቱ መጠን መለኪያ ሆኖ የቀረበው ገቢ የማግኘት እንጂ የመሥራት ችሎታው አቅም አለመሆኑ ነው፡፡ በከፊል ዘላቂ የአካል ጉዳት የመሥራት ችሎታ መቀነስ የገቢ መቀነስን የሚያስከትል ቢሆንም ሁል ጊዜ ይህ ይሆናል ማለት አይቻልም፡፡ የመሥራት ችሎታው ቀንሶ እያለ በዚያው ደመወዝ ወይም ሻል ባለ ደመወዝ ሊሠራ የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ ግን ሁኔታውን አይለውጠውም፡፡ ዋናው መለኪያ የገቢው አለመነካት ወይም ከፍ ማለት ሳይሆን የመሥራት አቅሙ (Potential) መቀነስ ነው በዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት ግን መሠረታዊው ጉዳይ ገቢ የማግኘ አቅምን ማሳጣት ነው::
ሌላው ደግሞ በዘላቂ ከፊል የአካል ጉዳት የመሥራት ችሎታው መቀነስ በመደበኛ ሁኔታ የገቢ ሁኔታን የሚቀንስ ሲሆን ይህ የገቢ መቀነስ የሚታየው ሠራተኛው ይሠራ ከነበረው ወይም በተመሣሣዩ ሁኔታ ሊሠራ ይችል ከነበረው ሥራ አንፃር ነው፡፡ ለዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት መሠረት የሚሆነው ግን ሠራተኛው ማናቸውንም ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ለማግኘት የሚከለክለው መሆኑ ነው፡፡ እዚህ ላይ “ማናቸውንም ደመወዝ የሚያስገኝ ሥራ” የሚለው ምን ማለት ነው? የሚለውን ማየት ይገባል፡፡ “ማናቸውንም” የሚለው ቃል ሰፋ ባለ መንገድ ታይቶ ሠራተኛው ከጉዳቱ በፊት ከነበረው ሙያ ውጪ ያሉ ሥራዎችንም እንደሚሸፍን ለምሳሌ አንድ ማሽኒስት የነበረ ሰው “በተሸካሚነት” ወይም “በሊስትሮነት” ሥራ ላይ ተሠማርቶ መሥራት ከቻለ ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳተኛ ሊባል አይችልም የሚል ትርጉም እንደሚሰጥ ማንበብ አለብን ወይስ ጉዳቱ በደረሰ ጊዜ ተጐጂው በቀጥታ ወይም በተለዋዋጭ ሊሠራ ይችል ከነበረው የሠለጠነበት ወይ የተማረበት አማራጭ የሥራ መስኮች አንፃር መታየት አለበት? የፊተኛው ትርጓሜ እጅግ ሰፊ ከመሆኑ የተነሣ ተጐጂዎች ሁሉ ከፍ ሲል ከተጠቀሱት ዓይነት ሙያዎች በአንዱ ሊሠማሩ የሚችሉ መሆናቸው ብቻ ከዘላቂ ሙሉ የአካል ተጐጂነት ሽፋን በርካታዎችን የሚያወጣ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳተኛ አይኖርም ወይም ቁጥራቸው ያንሳል፡፡ ይህ ግን በጉዳቱ ከፍተኛነት የተነሣ በዘላቂ ሙሉ የአካል ተጐጂነት መደብ ሊያገኙ የሚገባውን ክፍያ እንዳያገኙ የሚያደርግ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ይልቁንም የሠራተውኛው ጉልበት ለዕድገት መሠረት መሆኑን ከግምት የሚያስገባወና ተገቢውን ክብር የሚሰጠው፣ ተመዛዛኝ (efficient) እና ተግባራዊ (Pragmatic) የሆነው አተረጓጎም ጉዳቱ በደረሰ ጊዜ ሠራተኛው በቀጥታ ወይም በተለዋዋጭ ሊሠራ ይችል ከነበረው የሠለጠነበት ወይም የተማረበት አማራጭ የሥራ መስኮች አንፃር ማየቱ ሳይሆን አይቀርም፡፡
መ. ሞት፡-
ይህ ጉዳት ደግሞ በአንድ ሠራተኛ ላይ ሊደርስ የሚችለው አስከፊው እና የመጨረሻው ደረጃ ነው፡፡ ጉዳቱ ራሱን የሚገልጽ በመሆኑ ማብራራያ የሚያስፈልገው አይደለም፡፡
የጉዳት መጠን አወሳሰን
በአንድ ሠራተኛ ላይ የሚደርሱት የጉዳት መጠን ደረጃዎች ከፍ ብለው የተገለፁት ናቸው፡፡ ይህን ደረጃ በመመሪያ በጉዳት መወሰኛ ሠንጠረዥ የሚያወጣው የሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ነው ፡፡ ደረጃ የሚያወጣው ለዘላቂ ከፊል እና ሙሉ የአካል ጉዳት ብቻ ነውአንቀፅ 102 1፡፡ በጊዜያዊ የአካል ጉዳት ሠራተኛው ቀድሞ የነበረውን የመሥራት ችሎታ መልሶ ስለሚያገኝ፤ ሞትም ቢሆን የጉዳቱ መጠን በራሱ የተገለጠ በመሆኑ ሚኒስትሩ ለነዚህ ጉዳቶች ደረጃን አይወስንም፡፡
ደረጃቸውን ለሚወስንላቸው ዘላቂ ሙሉ ወይም ከፊል ጉዳቶች ግን የጉዳቶቹ መጠን ደረጃ ከመወሰኑ በፊት ጉዳቱ በደረሰ በአስራ ሁለት ወራት ውስጥ በተቻለ መጠን የጉዳቱን መጠን መወሰን ከሚኖርበት የህክምና ቦርድ ማስረጃ ማግኘት ይጠይቃል [አንቀጽ 102 (2)] ፡፡
በዚህ መንገድ የጉዳቱ መጠን እና ደረጃ ከተወሰነ በኋላ ውሳኔው ቋሚ ሆኖ የሚቀጥል ላይሆን ይችላል፡፡ የጉዳቱ መጠን ከውሳኔው በኋላ ከፍ ሊል ወይም ሊሻሻል ይችላል፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያበቃ ምክንያት አለ ወይም ቀድሞ የተደረገው ምርመራ ሥህተት አለበት የሚል ወገን ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን ሲጠይቅ በዚሁ መነሻነት በድጋሚ ምርመራ ሊደረግ ይችላል፡፡ አንቀጽ 102 (3) በድጋሚ ምርመራው የጉዳቱ መጠን ከተለወጠ ደረጃው በዚያው መጠን ታርሞ በጉዳቱ ምክንያት የሚገኘው ክፍያ እንዲቀጥል፣ እንዲጨምር ወይም እንዲቀንስ ይደረጋል [አንቀጽ 102 (4)(5)] ፡፡ ለምሳሌ ያህል ጊዜያዊ የአካል ጉዳት የደረሰበት ሠራተኛ ከአንድ ዓመት የሚዘልቅ የመሥራት ችሎታን የሚቀንስ ጉዳት ያገኘው እንደሁ ተጐጂው በሚያቀርበው ጥያቄ መነሻነት በድጋሚ ተመርምሮ ወደሚቀጥለው ደረጃ ሊሻገር ይችላል፡፡ የሚፈፀመው ክፍያም በዚሁ መጠን የሚስተካከልለት ይሆናል፡፡
- Details
- Category: Employment and Labor Law
- Hits: 16209
ትርጉም
በሥራ ምክንያት የሚመጣ በሽታን ትርጉም ማወቅ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ከበሽታዎች ውስጥ የትኛው በስራ ምክንያት እንደሚመጣ የትኞቹ ደግሞ በተለመደው ሁኔታ የሰውን ልጅ የሚያጠቁ ከሥራ ጋር ያልተያያዙ እንደሆኑ ለመለየት ይረዳል፡፡ በኢትዮጵያ አሠሪና ሠራተኛ ህግ መሠረት በሥራምክንያት የሚመጣ በሽታ ማለት
“ሠራተኛው ከሚሠራው የሥራ ዓይነት ወይም ሠራተኛው ከሚያከናውነው ሥራ አካባቢ የተነሣ በሽታው ከተከሰተበት ዕለት አስቀድሞ በነበረው የተወሰነ ጊዜ ውስጥ በፊዚካል፣ ኬሚካል ወይም ባዮሎጂካል ነገሮች አማካኝነት በሠራተኛው ላይ የሚደርስ የጤና መታወክ ነው” [አንቀጽ 98(1)]
በዚህ ትርጉም የሥራ ላይ በሽታው ምክንያት
- የሥራው ዓይነት ነው
- የሥራው አካባቢ ሁኔታም ነው፡፡
በሁለቱም መንገዶች ቢሆን በሽታው ከሥራው ጋር ግንኙነት አለው፡፡ ከሌሎች በሽታዎች የሚለየውም በሽታው ለሥራው የተለመደ ወይም የሚታወቅ ውጤትን የሚያስከትል መሆኑ ነው፡፡ አስም ማንኛውንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያጠቃ ቢሆንም ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ለረጅም ጊዜ የሠራ ሰው ለዚህ በሽታ የተጋለጠ ነው፡፡ይህ የሆነውም በሥራው ዓይነት ምክንያት ነው፡፡ በተመሣሣይ ሁኔታም ከፍተኛ ድምጽ ያለበት ቦታ የሚሰራ ሰው የመስማት ሀይሉ ሊቀንስ ወይም ላይኖር ይችላል፡፡ ስለሆነም በእንዲህ ያሉ ሁኔታዎች የሚመጣው በሽታ “የሥራ ላይ በሽታ” ሲባል ተጠቂ ለመሆን ያበቃው ምክንያትም የሥራው ዓይነት ነው ማለት ይቻላል፡፡
የሥራው አካባቢ ሁኔታ ስንልም በሽታው ከሥራው ጠቅላላ ባህሪ የሚመነጭ ወይም በሥራው ባህሪ ምክንያት የሚመጣ ሳይሆን ሠራተኛው እንዲሠራ የሚጠበቅበትን የሥራ ተግባር ተደጋጋሚ በሆነ የማከናወን ሂደት ሲፈጽም ለአንድ ወይም ለሌላው በሽታ የሚጋለጥበት አጋጣሚ ማለት ነው፡፡ በምሳሌ ለመግለጽ ያህል አንድ የቀበሌ የህብረት ሱቅ ሠራተኛ ቆሻሻ የሚቃጠልበት ቦታ አካባቢ ለረጅም ጊዜ በመስራቱ የአስም በሽተኛ ሆኗል፡፡ የህብረት ዕቃዎች መሸጥ በመደበኛ ሁኔታ የአስም በሽታን አያስከትልም፡፡ ሠራተኛው ለዚህ ችግር የተጋለጠው እንዲሠራ የተመደበበት የሥራ አካባቢ ሁኔታ በበሽታው ለመጠቃት ምክንያት ስለሆነው ወይም ተጋለጭነቱን ስላሰፋው ነው፡፡ ስለሆነም በተመሣሣይ ሁኔታ የሥራ አካባቢ ሁኔታዎች በመደበኛ ሁኔታ ችግሩን ያስከትላሉ ባይባልም እንደተጠቀሰው ባለ ልዩ አጋጣሚዎች በሥራ ምክንያት ለሚመጣ በሽታ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ ማለት ነው፡፡
የሥራ ላይ በሽታዎችን በተመለከተ የሠራተኛ እና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሚኒስቴር አግባብ ካለው ባለሥልጣን ጋር በመምከር በሥራ ምክንያት የሚመጡ በሽታዎችን ዝርዝር በመመሪያ እንዲያወጣ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ይህ ዝርዝር በየአምስት ዓመቱ ሊሻሻል የሚችል ነው፡፡ ዝርዝሩ በጅምላ የሚወጣ ሳይሆን እንደየሥራ ባህሪው እየተለየ የሚገለፅ ነው፡፡ ለአንዱ የሥራ መስክ የሥራ ላይ በሽታ የሚባለው ለሌላው የሥራ መስክ የሥራ ላይ በሽታ ላይባል ይችላል፡፡ ስለሆነም ዝርዝሩ ከየሥራ መስኮቹ ባህሪ አንፃር እየታየ የሚዘጋጅ ነው፡፡
ዝርዝሩ ከተዘጋጀ በኃላ በዝርዝሩ ውስጥ ካሉት ባንዱ በሽታ የተጠቃ ሰው በሽታው እንዳለበት ሲረጋገጥ የሥራ ላይ በሽታ እንደያዘው ማስረጃ ሊሆነው ይችላል፡፡ ከተገለፁት ውጪ በሆነ በሽታ የተጠቃ ሰው ግን
- የተጠቃው በሥራ ላይ በሽታ ስለመሆኑ
- ለተገለፁት በሽታዎችም ቢሆን መንስኤ ናቸው የተባሉት ችግሮች ሌላ መገለጫ ያላቸው ስለመሆኑ ማስረጃ በማቅረብ የሥራ ላይ በሽታ ተጠቂ መሆኑን የማስረዳት ዕድል አለው፡፡
ይህ ብቻም አይደለም፡፡በዝርዝሩ ውስጥ የተካተተ ባይሆን እንኳን ተቃራኒ ማስረጃ ካልቀረበ በአንድ የተወሰነ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ብቻ በተደጋጋሚ የሚይዝ በሽታ አንድን ሰራተኛ የያዘው መሆኑ ሲታወቅ የተጠቃው በስራ ላይ በሽታ እንደሆነ ይቆጠርለታል፡፡ ይህ በራሱ (prima facie) በሽታው ከስራው ጋር አንድ አይነት ትስስር እንዳለው ማስረጃ ነው፤ በስራው እና በበሽታው መካከል ያለውን ግንኙነት በጊዜው የቴክኖሎጂ ደካማነት የተነሣ መረዳት በማይቻልበት ሁኔታ በሰራተኛው ላይ የሚደርሰው ጉዳት ሣይካስ እንዳይቀር ለማድረግ ይህ ጥሩ መንገድ ነው፡፡
የቴክኖሎጂው ዕድገት የሣይንሱን ምጥቀት እየተከተለ ዝርዝሩ በየአምስት ዓመቱ እንዲዘጋጅ መደረጉም ከማስረጃ አቀራረብ አንፃር ሰራተኛው በቀድሞው ዝርዝር ውስጥ ያልነበሩትን የስራ ላይ በሽታዎች ለማስረዳት የሚኖርበትን ችግር የሚያቃልልለት ነው፡፡
የስራ ላይ በሽታ የደረሰበትን ጊዜ ስለመወሰን
ስለበሽታው ከፍ ሲል በተገለፀው መንገድ ከተነጋገርን አሁን ደግሞ የስራ ላይ በሽታው መቼ እንደደረሰ መነጋገሩ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ በጉዳቱ ምክንያት የሚገኘውን የካሣ ጥያቄ ለማቅረብ የሚቻል መሆን አለመሆኑን ለመወሰን፤ መጠየቅ የሚቻል ሲሆን እንኳን የካሣው ተጠቃሚ ለመሆን ጥያቄው በምን ያህል ጊዜ መቅረብ እንዳለበት ለመወሰን ይረዳል፡፡
ስለሆነም በስራ ምክንያት በሚመጣ በሽታ ጉዳት የደረሰበት ዕለት በሽታው በግልጽ የታወቀበት ቀን ይሆናል፡፡ በሽታው በግልጽ ታውቋል የሚባለውም
- ሰራተኛው የመስራት ችሎታውን ያጣበት ቀን
- በሽታው በሐኪም ተመርመሮ መኖሩ የታወቀበት የመጀመሪያው ዕለት
- ሰራተኛው በበሽታው ምክንያት የሞተበት ዕለት ነው፡፡
እነኚህ ሁኔታዎች ሰራተኛው በበሽታው የተያዘበት ጊዜያት እንደሆኑ ይቆጠራል፡፡ “እንደሆነ ይቆጠራል” መባሉም በሽታው በአንድ ጊዜ የሚከሰት ሣይሆን በሂደት የሚገለጥ በመሆኑ ትክክለኛውን በበሽታው የተለከፈበትን ዕለት ማወቅ አስቸጋሪ በመሆኑ ነው፡፡
በሥራ ምክንያት በሚመጣ በሽታ ጉዳት የደረሰበትን ዕለት ስንወስን ይህን ተከትሎ የሚመጣው የመጀመሪያው ጥያቄ ሠራተኛውን በሽተኛ ለማድረግ ያበቃው ሰበብ በሽታው ከተከሰተበት ዕለት አስቀድሞ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ የተፈጠረ መሆን አለበት የሚለው ነው፡፡ ይህን ለመመለስ ወደ ትርጓሜው መለስ ስንል በሽታው ከተከሰተበት ዕለት አስቀድሞ በነበረው የተወሰነ ጊዜ ውስጥ በፊዚካል፣ ኬሚካል ወይም ባዮሎጂካል ነገሮች አማካኝነት የሚደርስ የጤና መታወክ ሲል ይገልፀዋል “የተወሰነ ጊዜ ውስጥ” የሚለው እንደየበሽታው ጠባይ ሊለያይ የሚችል በመሆኑ ወጥ የሆነ ጊዜ ማስቀመጥ አይቻልም፤ ግን ደግሞ ይህን የተወሰነ ጊዜ ልክ ማን ይወስናል? ሚኒስትሩ መመሪያ እንደሚያወጣ የተነገረው በስራ ምክንያት የሚመጡ በሽታዎችን ዝርዝር ነው፡፡ እነኝህ የተዘረዘሩ በሽታዎች በምን ያህል ጊዜ ሲከሰቱ የስራ ላይ በሽታ እንደሚሆኑ ሊወስን እንደሚችል የተገለፀ ነገር የለም፡፡ ስለሆነም ይህ ጊዜ በሐኪሞች እንዲረጋገጥ የተተወ ነው? ወይስ የማሕበራዊና ሠራተኛ ጉዳይ ሚኒስትር የስራ ላይ በሽታን ዝርዝር ሲያወጣ በሽታው በስራ ምክንያት የመጣ ነው ለማሰኘት አንዱ አስፈላጊ ነገር የበሽታው በተወሰነ ጊዜ ውስጥ መገለጥ ጭምር በመሆኑ ሚኒስትሩ ይህን ጊዜ ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር ከዝርዝሩ ጋር አብሮ ያወጣዋል? ክርክር በተፈጠረ ቁጥር ሐኪሞች በየጊዜው እየተጠየቁ የሚሰጡት ማረጋገጫ ሣይሆን በኃለኛው መንገድ የሰራተኛ እና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር የሥራ በሽታ ዝርዝርን ሲያወጣ አብሮ ጊዜውን የሚወስን እንደሆነ ማሰቡ ትክክለኛው መስመር ይመስላል፡፡
ሌላው ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሣው ጥያቄ ሰራተኛው በአንድ በሽታ የተለከፈው ሰራተኛ ከመሆኑ በፊት የሚሆንበት አጋጣሚ ነው፡፡ ሰራተኛ ከመሆኑ በፊት የተለከፈ ሰው ሰራተኛ ከሆነ በኃላ የሚሰራው ስራ ለበሽታው መባባስ ምክንያት በሚሆንበት ጊዜ በሽታው የሥራ ላይ በሽታ ሊባል ይችላል ወይ? የሚለው ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ የሚለው የተለከፈበትን ወይስ የተባባሰበትን ዕለት ማለት ነው? አንድ ምሣሌ ለመጨመር ያህል ለሶስት ዓመት በጨርቃ ጨርቅ ፋበሪካ ውስጥ የሰራ ሰው የአስም በሽታ ሊይዘው እንደሚችል ቢገለጽና አንድ ስራተኛ በሁለተኛ ዓመቱ ለዚሁ በሽታ በተፈጥሮው በቀላሉ የሚጠቃ በመሆኑ በሁለተኛ ዓመቱ በአስም ቢያዝና ይህም ሦስት ዓመት ከመሙላቱ በፊት ቢታወቅ የሥራ ላይ በሽታ አይባልም፡፡ በሽታው እየተባባሰ በመሄዱ ግን በአራተኛ ወይም በአምስተኛ ዓመቱ የተመደበበትን ሥራ ለመሥራት እንዳይችል ቢሆን የተባባሰው በዝርዝሩ ከተወሰነው ጊዜ በፊት በመሆኑ ብቻ የተባባሰበትን ጊዜ ከግምት ሳናገባ በጉዳቱ ምክንያት የሚያገኘውን ክፍያ ማሳጣት ተገቢ ይሆናል?
- Details
- Category: Employment and Labor Law
- Hits: 16560
በሥራ ሂደት ወይም ከሥራ ጋር በተያያዘ ሁኔታ በማናቸውም ጊዜ ያልታሰቡ አደጋዎች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ በተለይም ዘመናዊው የኢንዱስትሪ አሠራር ሂደት እያደገና እየተወሳሰበ መምጣቱ ከመሥሪያዎቹ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ አደጋ የመፈጠር ዕድሉን ሠፊ ያደርገዋል፡፡ ከድኅነት ጋር ተያይዞም ችግሩ ይከፋል፡፡ ጉዳቱም ከተጎጂው ዘልቆ በሥሩ የሚተዳደሩ ቤተሰቦቹን የሚነካ በመሆኑ ከፍ ያለ ቀውስን በህብረተሰቡ ውስጥ የሚፈጥር ነው፡፡
ስለሆነም በአንድ በኩል የማኅበራዊ ዋስትናን ማረጋገጥ ተገቢ በመሆኑ፤ በሌላም በኩል ሠራተኛው ሊከሰት ከሚችለው አደጋ በስተጀርባ በርሱና በቤተሰቡ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ችግር እያሰበ በጭንቀት መስራቱ በምርታማነት ላይ የራሱን ተፅዕኖ ስለሚያሰድር፤ ሠራተኛው ለሚደርስበት ጉዳት የሚገባውን ካሳ የሚያገኝበትን የህግ ማዕቀፍ ማኖሩ ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም በተለያዩ አገሮች ቀደም ሲል አደገኛ ተብለው በሚታወቁ (እንደ ማዕድን ማውጣት) ሥራ ላይ ተሰማርተው ለሚሰሩት ብቻ ይፈፀም የነበረው ካሳ የማግኘት መብት አሁን ሌሎችንም ሁሉ እንዲያቅፍ ተደርጓል፡፡
በዚህ የተነሳ በኛም አገር "ሠራተኛ" በሚለው ትርጉም ውስጥ የሚሸፈን ማናቸውም ሰው በሥራ ሂደት ወይም ከሥራ ጋር በተያያዘ ሁኔታ አደጋ የደረሰበት እንደሁ የካሳ ክፍያ የሚፈጸምበት የህግ ማዕቀፍ ቀደም ሲሉ በነበሩት በአዋጅ ቁጥር 64/68፣ 42/85 እና አሁን ባለው አዋጅ ቁጥር 377/96’ም ተሸፍኗል፡፡
አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 95/2 ላይ እንደተገለጸው በስራ ምክንያት የሚመጡ ጉዳቶች በሚለው ርዕስ ሥር ሁለት መሰረታዊ ሀሳቦች ተካተዋል፡፡ እነኚህም በሥራ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች እና በሥራ ምክንያት የሚመጡ በሽታዎች ናቸው፡፡ የትኛውም ጉዳይ ቢሆን ሰራተኛው የደረሰበት ጉዳት ከሥራው ጋር የተያያዘ መሆን አለበት፡፡ ከሥራው ጋር የተያያዘ የመሆን አለመሆኑ ነገር ተጎጂውን ሠራተኛ ካሳ ለማስገኘትም ሆነ ለመንሳት ወሳኝ የሆነ መረጋገጥ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ አሊያ ግን ለማንኛውም ጉዳት ሁሉ የአሠሪውን ኃላፊነት በማስከተል አንድ አሠሪ ኢንቨስት ለማድረግ የሚኖረውን ፍላጎት ይገድባል፤ በዚሁ ደረጃም ዕድገት ይቀዘቅዛል፡፡ ስለሆነም አሠሪው ኃላፊ ሊሆንበት የሚገባውን በሥራ ምክንያት የሚመጣ አደጋ እና በሽታ መለየት ተገቢ ነገር ነው፡፡ ይህን ስንል የአሠሪው የኃላፊነት አድማስ እምን ድረስ ነው ማለታችን ነው፡፡ የመጠየቁን ያህል አፋጣኝ እና ቀጥታ መልስ ማግኘት ቀላል አይሆንም፡፡ በሥራ ሂደትም ለተለያዩ አሰራሮች መፈጠር ምክንያት በመሆን የአፈፃፀም ወጥነት እንዳይኖር ያደርጋል፡፡
ስለሆነም በሥራ ምክንያት የሚመጡ አደጋዎችና በሽታዎችን የተሻለ ለመረዳት እንደቅደም ተከተላቸው በሚከተለው መንገድ ለመወያየት እንሞክራለን፡፡
1. በሥራ ላይ የሚደርስ አደጋ (during the performance of the Work)
¢በሥራ ላይ የሚደርስ አደጋ¢ የሚለው ሐረግ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 97 እንደተገለፀው “ማንኛውም ሠራተኛ ሥራውን በማከናወን ላይ ሳለ ወይም ከሥራው ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ ከራሱ ውጭ በሆነ ምክንያት ወይም ሥራውን ለማከናወን ባደረገው ጥረት ምክንያት በአካሉ ላይ በድንገት የደረሰበት ጉዳት" ማለት ነው፡፡ በዚህ ትርጉም የሚከተሉት ዋና ነጥቦች ናቸው፡፡
አደጋው የደረሰው፤
- ስራን በማከናወን ላይ፤
- ከሥራው ጋር ግኑኝነት ባለው ሁኔታ ከራሱ ውጭ በሆነ ምክንያት ወይም፤
- ሥራን ለማከወን በሚደረግ ጥረት ውስጥ መሆኑ ናቸው ።
የሥራ ላይ አደጋ የሚባለውና የካሳ ሽፋን የሚሰጠው እነኚህ ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው። ለበለጠ መረዳት እያንዳንዱን ነጥብ በተናጥል ማየት አስፈላጊ በመሆኑ እንደሚከተለው እናያቸዋለን።
ስራን በማከናወን ላይ የሚለው ሃረግ አደጋው የደረሰው፤
- ስራው የሚከናወንበት ጊዜ፤
- ሥራው የሚከናወንበት ቦታ እና፤
- ሥራው የሚከናወንበትን ሁኔታ የሚያሳይ ነው። ይህ ማለት ‘ሥራን በማከናወን ላይ’ የሚለው አደጋው ከደረሰበት ጊዜ ቦታ እና ሁኔታ ጋር የተሳሰረ ነው ማለት ነው።
ስራው የሚከናወንበት ጊዜ
ስራው የሚከናወንበት ጊዜ የሚለው በመደበኛው ሁኔታ ሥራ የሚሰራባቸውን ከ2፡30 — 6፡30 እና ከ 7፡30 —11፡30 እና በአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ከ 2—30 6፡00 እና ከ 8፡00—11፡00 እንዲሁም ቅዳሜን ግማሽ ቀን የሚሸፍን ነው። ከዚህ ውጭ ያሉት ሰዓታት ከካሳው ሽፋን ውጭ ይሆናሉ፡፡ ይህም ሲባል ከሥራው አካባቢ ጠቅላላ ሁኔታ ፣ ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ባህሪ እና ሥራው ከሚጠይቀው ወይም በልማድ ከሚከናወንበት ሁኔታ አንፃር ወይም ለሥራው ተቀዳሚ ወይም ተከታይ የሆኑ (incidental) ተግባሮችን ሲፈጽም በነበረበት ጊዜ አንድ ሰራተኛ ጉዳት የደረሰበት እንደሆነ አደጋው ሥራው ከሚሰራበት ሰዓት ውጪም ቢሆን ሥራ በሚከናወንበት ጊዜ የደረሰ አደጋ እንደሆነ ይታሳባል። ለምሳሌ አንድ ሠራተኛ ከመደበኛው የሥራ ሰዓት ውጪ ነገር ግን የአሰሪውን ትዕዛዝ በመፈፀም ላይ ባለበት ጊዜ አደጋ ቢደርስበት፣ በእረፍት ጊዜ ምሳ በመብላት ላይ እያለ አደጋ ቢደርስበት በሥራ ጊዜ ውስጥ የደረሰ አደጋ ይሆናል። በመጀመሪያው ነጥብ የአሰሪውን ጥቅም ለማስፈፀም ሲል በዚያ ቦታ የተገኘ መሆኑ ብቻ የሥራውን የጊዜ አድማስ ያሰፋዋል በኋለኛውም ቢሆን ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ባህሪ ስንነሳ ሳይበላ ስራውን ለመስራት ይቸገራል ቢሰራም እንኳን ውጤታማ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም። ስለሆነም ምሳ በሚበላበት፣ ሻይ በሚጠጣበት ጊዜ አደጋ ቢደርስበት፤ በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ የሰራተኛው በአዲስ ጉልበት ስራውን መጀመር አሰሪውን የሚጠቅመው በመሆኑ በሥራ ጊዜ ላይ የደረሰ አደጋ እንደሆነ ይታሰባል። ለአንድ አፍታ እረፍት በመውሰድ ላይ እያለም ጉዳቱ ቢደርስ በተመሳሳይ ሁኔታ በሥራው ጊዜ ውስጥ የደረሰ አደጋ ይሆናል። እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎችን ከካሳ ሽፋን ውጭ ማድረግ የመደበኛ ሕይወት አኗኗር ትርጉምን ማሳጣት ይሆናል።
ሥራ የሚከናወንበት ቦታ፤
አንድ ሥራ የሚሰራው ሥራውን በሚያሰራው ድርጅት ውስጥ እንደሆነ ይታሰባል፡፡ በዚህ ቦታ ላይ እያለ አንድ ሠራተኛ አደጋ ቢደርስበት በሥራ ቦታ ላይ የደረሰ አደጋ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ሥራ የሚሠራው ግን ድርጅቱ ያለበት ቦታ ላይ ብቻ አይደለም፤ የሥራው ባህሪ ሠራተኛው ከመደበኛው የሥራ ቦታ ላይ ተነጥሎ ወደሌላ ቦታ እንዲሄድ ሊያስገድደው ይችላል፡፡ አንድ የኤሌትሪክ ወይም የቴሌኮሙኒኬሽን ሠራተኛ የመስመር ላይ ስራዎችን ለመሥራት ከድርጅቱ ውጭ መገኘት ሊኖርበት ይችላል ለእርሱ የሥራ ቦታው ሥራው የእርሱን መገኘት የሚጠይቅበት ቦታ ነው፡፡ በዚህ ቦታ አደጋ ቢደረስበት በሥራ ቦታ ላይ የደረሰ አደጋ ይሆናል።
ሥራው የሚከናወንበት ሁኔታ፤
አደጋው ሠራተኛው ሲሰራ የተከሰተ መሆን አለበት። ሠራተኛው ሥራውን ሲሰራ የደረሰ አደጋ ነው የሚባለው በሥራ ዝርዝር መግለጫው ሊሠራ የሚገባው ሥራ ብቻ ሳይሆን የሥራው ባህሪ የነገሮች አካባቢያዊ ሁኔታ፣ ሥራውን ተከትለው በሚመጡ አጋጣሚዎች ምክንያት፤ ከሥራ ዝርዝሩ ውጭ ያለን ሥራ እንዲሰራ ቢሆን ወይም ሥራውን ተቋርጦ ቢሆን በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ አደጋ ቢደርስ ሥራውን በመሥራት ላይ የተከሰተ አደጋ ይሆናል። ለምሳሌ አድካሚ ከሆነ ሥራ ለአንድ አፍታ አረፍ እንዳለ አደጋ ቢደርስ የውሃ ጥማቱን ለማርካት ድርጅቱ ውስጥ ወዳለው ወይም የሥራ ቦታ ላይ ወዳለው ሻይ ቤት ሲሄድ፣በምሳ የእረፍት ጊዜው ውስጥ እያለ አደጋ ቢደርስ ሠራተኛው ሥራውን ሲሰራ የተከሰተ አደጋ ይሆናል። ሥራውን በአዲስ መንፈስ እና ጉልበት ለመቀጠል አረፍ ማለቱ፣ምሳ መብላቱ ወይም የሥራ ባልደረባውን መርዳቱ በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ አሰሪውን የሚጠቅም ነው። የሚጠቅም ባይሆን እንኳን ከሥራው ጠቅላላ ባሕሪም ሆነ ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ሁኔታ አንፃር ሥራው ለአንድ አፍታ የመቋረጡ አጋጣሚ ሥራው ሲሰራ የደረሰ አደጋ አይደለም አያሰኘውም። ረዘም ላለ ጊዜ ሥራው ተቋርጦ ቢሆን ለምሳሌ የሥራው ሰዐት አብቅቶ ወደ ቤቱ ለመሄድ ተነስቶ ከድርጅቱ ውስጥ ወይም ከሥራው ቦታ ላይ እያለ አደጋ ቢደርስም ሥራውን ሲሰራ የተከሰተ አደጋ ነው መባሉን አያስቀረውም።
በአጠቃላይ ሥራውን ሲሰራ የተከሰተ አደጋ ነው የሚባለው ሠራተኛው ሥራውን በተግባር እያከናወነ መሆኑን፣በተግባር እያከናወነ ባይሆን እንኳን ሥራውን ከፍ ሲል በተገለፁት ምክንያቶች ለጊዜው ሥራውን አቋርጦ ባለበት ጊዜ፣ የሥራ ባልደረባውን በመርዳት ላይ የአሰሪውን ትዕዛዝ በመፈጸም ላይ ሥራውን አቁሞትም ቢሆን ወደ ቤቱ ለመሄድ ነገር ግን በሥራ ቦታ ወይም በድርጅቱ ውስጥ እንዳለ አደጋ ሲደርስበት ነው።
2. አደጋው ከሥራው ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት (in connection with the performance of the Work)
ሁለተኛው ነጥብ አደጋው ከስራው ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ የተፈጠረ መሆኑ ነው፡፡ አንድ አደጋ ተገቢውን የካሳ ክፍያ እንዲያስገኝ ከሥራው ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ የተፈጠረ መሆኑ መረጋገጥ አለበት፡፡ የመሥሪያ መሣሪያዎቹ በአግባቡ ባለመስራታቸው ምክንያት፤ እየሰሩም ቢሆን በሥራው ላይ ያለውን ሠራተኛ ጉዳት ካደረሱበት ወይም ሠራተኞቹን አደገኛ ለሆነ ሁኔታ በማጋለጡ ምክንያት የተፈጠረ አደጋ ‘ከስራው ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ” የተፈጠረ ስለመሆኑ መረዳት ብዙም የሚከብድ አይሆንም፡፡
አንዳንድ ጊዜ ግን ጉዳቶቹ የሚመጡት ከሥራው ጋር በተያያዘ ሁኔታ መሆኑን መለየት ያስቸግራል፡፡ ለምሳሌ በሥራ ላይ ያለ ሠራተኛ በመብረቅ ሊመታ ወይም በሥራ ላይ እያለ በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ምክንያት ጉዳት ሊደርስበት ይችላል፡፡ በነበረበት የልብ ድካም፤የደም ብዛት ምክንያትም ሕይወቱ ሊያልፍ ወይም የአካል ጉዳተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ እነኚህ ጉዳቶች በቁማቸው ሲታዩ ከሥራው ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡
ነገር ግን አደጋው ሁልጊዜ ከሥራው የመነጨ እንዲሆንም አይጠበቅም፡፡የሥራው ባህሪ ለአደጋው መከሰት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ አለ እንደሁ ይኸው ብቻም በቂ ይሆናል፡፡ በምሳሌ ለመግለጽ ያህል ቀደም ሲል የተነሳው የመብረቅ አደጋ ከሥራው ክንውን ጋር ግንኙነት ነበረው ማለት አይቻልም፡፡ ሌላው የህብረተሰብ ክፍልም ለዚሁ ተመሳሳይ አደጋ ተጋልጧል፡፡ የጉዳቱ ሠለባ የሆነው ሰራተኛ ሥራው ላይ የነበረ በመሆኑ ብቻ አደጋው ከሥራው ጋር (ጠንካራ) የሚያስተሳስረው ነገር አለ ማለት አይቻልም፡፡ ይሁንና የመብረቁ አደጋ በተከሰተ ጊዜ ሠራተኞቹ በመብረቁ አደጋ እንዲመቱ ያደረጋቸው ከፍ ያለ ቦታ ላይ እንዲሰሩ የሥራቸው ሁኔታ ያስገደዳቸው በመሆኑ የተነሳ ከሆነ ይህ አደጋውን ከሥራው ክንውን ጋር የሚያስተሳስረው አንድ ምክንያት ይሆናል፡፡ ስለሆነም እንዲህ ባለ አጋጣሚ የመብረቁ አደጋ ከሥራው ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ የተፈጠረ ነው ማለት ይቻላል፡፡
በአንዳንድ አገሮች ደግሞ የሥራው ሁኔታ እና ግዴታ ሠራተኛውን አደጋው እደረሰበት ቦታ ባያመጣው ኖሮ በአደጋው ሊጎዳ ባልቻለም (positional risk) ነበር በማለት በአደጋው የተጎዳውን ሰው እንዲካስ ያደርጉታል፡፡ በዚህ አስተሳሰብ መሠረት ተጎጂው ካሳ የሚያገኘው በሥራ ላይ እያለ ጉዳት የደረሰበት በመሆኑ ብቻ ነው፡፡ አደጋውን ከሥራው ጋር የሚያስተሳስረው ይኸው ብቻ ነው፡፡
በአጠቃላይ አደጋው በህጉ ጥበቃ የተሸፈነ ነው ለማለት ከሥራው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዲኖረው አይጠበቅም፡፡ በአንድ ዓይነት ምክንያት ከሥራው ባህሪ ጋር ትስስር ያለው መሆኑ ከታወቀ ወይም የስራው ባህሪ ለአደጋው መከሰት እንኳ ባይሆን አደጋው ሲከሰት ለደረሰብን/ለሚደርስብን ጉዳት የራሱ አስተዋጽኦ ያለው/የሚኖረው ከሆነ ከስራ ጋር ግንኙነት አለው ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡
3. የአደጋው ከተጎጂው አድራጎት ውጪ በሆነ ምክንያት መከሰት
ከፍ ሲል የተገለፁት ጉዳቶች ‘የሥራ ላይ አደጋ’ እንዲሆኑ አደጋው ከተጎጂው ውጪ በሆነ ምክንያት የደረሰ መሆን አለበት፡፡ የሰው ሚስት በመድፈሩ ምክንያት በቂም ይፈልገው የነበረው ባል ተጎጂውን ሥራ ቦታ ድረስ በመሄድ ቢገድለው ይህ የግድያ አደጋ የደረሰበት ከግል ግንኙነቱ የተነሳ የመጣ እንጂ ከሥራው ባህሪ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ወይም ትስስር ያለው ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡
ስለሆነም የሥራ ላይ አደጋዎች ከተጎጂዎቹ የግል ህይወት አመራር ወይም ግንኙነት ውጪ በሆነ ምክንያት እነርሱ የተፈለገውን ያህል ጥረት ቢያደርጉም ሊቆጣጠሩዋቸው የማይችሉ ሲሆኑ ብቻ ¢የሥራ ላይ አደጋ¢ ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡
4. ሥራን ለማከናወን በሚደረግ ጥረት ውስጥ የደረሰ ጉዳት
ይህ ሶስተኛው ሥራን በማከናወን ሂደት የሚደርስ የስራ ላይ አደጋ ነው፡፡ አንድ ሰራተኛ ሥራውን ለመስራት ጥረት በማድረግ ላይ እያለ ጉዳት ቢደርስበት የሥራ ላይ አደጋ ይሆናል፡፡ ዋናው ነገር ሥራውን ለማከናወን ጥረት በሚያደርግበት ሁኔታ ላይ ጉዳት የደረሰበት መሆኑ ነው፡፡ ይህም ሲባል ሠራተኛው በነበረበት የልብ ድካም፤ የደም ብዛት ምክንያት ጉዳት ቢደርስበት ወይም በሌላ ሰው በደረሰበት ጥቃት ምክንያት ቢጎዳ ጉዳቱ ከስራው ጋር ያልተያያዘ ከሆነ የሥራ ላይ አደጋ ደርሶበታል ለማለት ያስቸግራል፡፡ ይህንንም ለመረዳት ሥራው ከደረሰበት ጉዳት ጋር ያለውን ትስስር መመርመር ይጠይቃል፡፡
- Details
- Category: Employment and Labor Law
- Hits: 19511
በስራ ግንኙነት ውስጥ የአሰሪና ሰራተኛ ህግ አስፈላጊነት ከሚገልጹ ምክንያቶች ውስጥ በአንድ በኩል ሰራተኛውን አግባብ ካልሆነ ብዝበዛ መከላከል በሌላ በኩል ደግሞ ሰራተኛው የሚፈለግበትን ግዴታዎች በአግባቡ እንዲወጣ ማደረግ የሚገኙበት መሆኑን ቀደም ብለን ያየነው ነው፡፡ ለዚህም ከሌሎች በተጨማሪ ሕጉ ዝቅተኛ የስራ ሰዓትን ፣ የዕረፍት ጊዜን እና የፈቃድ ጊዜ አሰጣጥን በመወሰን ይቆጣጠራል፡፡ በዚህ መልኩ ህጉ ቁጥጥር ባያደርግ ሰራተኛው ማለቂያ በሌለው ሁኔታ በቀን ውስጥም ሆነ በረጅም ጊዜ ያለዕረፍት ለመስራት እንዲገደድና ጉልበቱ ያለአግባብ እንዲበዘበዝ ሊያደርግ የሚችል ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ በነዚሁ መንስኤዎች መነሻነት ሰራተኛው ሊያነሳ በሚችላቸው ተቃውሞዎች ምክንያት ሊፈጠር በሚችል ጭቅጭቅና ሁከት የግንኙነቱ ሰላማዊ አለመሆን በሚፈጥረው የምረታማነት መቀነስ የሰራተኛውም ሆነ የአሰሪው ጥቅሞችን በዘላቂነት የሚጎዳ ይሆናል፡፡
ለዚህም ሲባል ህጉ በቅድሚያ ዝቅተኛ የስራ ሰዓትን በመደንገግ ችግሩን ለመቆጣጠር መሞከሩ አግባብ ሆኖ ይታያል፡፡ የኛ አዋጅም መደበኛ የስራ ሰዓት በህግ ፣በህብረት ስምምነት ወይም በስራ ደንብ መሰረት የሚወሰን መሆኑን ይገልጽና እርዝማኔውም በቀን ከስምንት ሰኣት ወይም በሳምንት ከአርባ ሰምንት ሰዓት ሊበልጥ እንደማይችል ያመለክታል (አንቀጽ 61) ፡፡ ስለዚህ መደበኛ የስራ ሰዓት በሳምንት ውስጥ የሚኖረው አደላደል በተመለከተም ከዚያው በተከታታይ ያሉ አንቀጾች ይደነግጋሉ፡፡ ከመደበኛው የስራ ሰዓት ውጭ የሚደረግ የስራ ሰዓት እንደ አስፈላጊነቱ ስራ ሊሰራበት የሚችል ቢሆንም ይህ ስራ የሚፈቀድበት ሁኔታዎች እና ከመደበኛው ክፍያ ከፍ ባለ መጠን ስራው እነደተሰራበት የጊዜ ሁኔታ በሚለይ መልኩ ክፍያ እንደሚፈጸም ተደንግጓል፡፡ ( አንቀጽ 66-68 )
በተመሳሳይ ሁኔታም የሰራተኛው የእረፍት ጊዜና ፈቃድ የማግኘት መብት በተለያየ ሁኔታዎች ተደንግጓል፡፡ እነዚህም የእረፍት ጊዜዎች የሳምንት የእረፍት ጊዜን የህዝብ በዓላት እረፍትን፣ የአመት ፈቃድን፣ ልዩ ፈቃድ እና የህመም ፈቃድን የተመለከቱ ናቸዉ፡፡ የሳምንት የእረፍት ጊዜ የ24 ሰዓት እረፍት ሲሆን ሊቆራረጥ የማይገባዉ በሰባት ቀን ጊዜ ውስጥ ለአነድ ቀን የሚሰጥና በህብረት ስምምነቱ በሌላ ሁኔታ ካልተገለጸ በስተቀር እሁድ ላይ ሊውልና ለሁሉም ሰራተኛ አንዴ መሰጠት የሚገባው ነው፡፡
ይሁን እነጂ በአንቀጽ 70 ስር በተገለጹት ሁኔታዎች መሰረት የድርጅቱ ስራ ወይም የሚሰጠው አገልግሎት የሚያስገድድ ከሆነ የሳምንት እረፍት ቀን ከእሁድ በሌላ ቀን ላይ ሊውል የሚችል ሲሆን በተጨማሪም አንቀጽ 71 ስር በተገለጹት ምክንያቶች በሳምንት የእረፍት ቀን ስራ ሊሰራ የሚችልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ በዚህ የእረፍት ቀን፡ ስራ የሰራ ሰው ሌላ የእረፍት ቀን ከማግኘት በተጨማሪ ለሰራው ስራ ለመደበኛ ስራ ይከፈለው የነበረ ደሞዝ በሁለት ተባዝቶ ሲከፈለው ተለዋጩን እረፍት ሳይወስድ ከስራ ቢሰናበት ተጨማሪ የማካካሻ ክፍያ የማግኘት መብት አለው (አንቀጽ 71/2/ እና 68/1/ሐ/)፡፡
ሌላው እረፍት የህዝብ በአላትን የሚመለከተው ሲሆን በዚህ የእረፍት ቀንም ሰራተኛው ሙሉ ደሞዙን የማግኘት መብት አለው፡፡ እንዲሁም እንደ ሌሎቹ የእረፍት ጊዜዎች ስራ ሊሰራ የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር የሚችል ሲሆን ለዚህ ስራም ሰራተኛው ደሞዙ በሁለት ተባዝቶ የሚከፈለው ይሆናል፡፡ ይሁንና በእለቱ ሌላ ተደራቢ የህዝብ በአል ቢኖር ወይም የህዝብ በአሉ ከሌላ የእረፍት ቀን ጋር ተደርቦ ቢገኝ በዚህ በተጠቀሰው ክፍያ ላይ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም፡፡ (አንቀጽ 73 - 75)፡፡
ፈቃድን በተመለከተ የመጀመሪያው እና ህጉ ልዩ ትኩረት የሰጠበት የአመት ፈቃድን የተመለከቱት ድንጋጌዎች ናቸው፡፡ በዚሁ መሰረት ህጉ ይህንን ፈቃድ ሰራተኛው እንዳይተው ለማድረግ ሲል ሰራተኛው የሚያደርጋቸው ስምምነቶች ተቀባይነት እነደማይኖራቸውና በአዋጁ በሌላ ሁኔታ ካልተፈቀደ በስተቀርም በክፍያ መተካትም እነደማይቻል በአንቀጽ 76 ስር በመደንገግ ይጀምራል፡፡ ከዚያም በተከታታይ አንቀጾች ስር የፈቃዱን መጠንን ከሰራተኛው የስራ ዘመን ርዝማኔ አንጻር፣ ስለፈቃዱ አሰጣጥ ሁኔታዎች፣ ፈቃዱ ተከፋፍሎ ሊሰጥ ስለሚችልባቸውና ለሌላ ጊዜ ሊተላለፍ ስለሚችልባቸው ሁኔታዎች በዝርዝር ተመልክተዋል፡፡ (አንቀጽ 77 - 79)፡፡ ይሁንና በዚህ ፈቃድ ላይ ያለ ሰራተኛም ቀደም ብሎ ሊታወቅ የማይችል ምክንያት ካጋጠመና በዚሁ ምክንያት በስራ ላይ መገኘቱ አስፈላጊ ከሆነ ከፈቃዱ ወደ ስራ ሊጠራ የሚችል ሲሆን ሰራተኛው በዚህ ምክንያት የሚደርስበት የመጓጓዣና የውሎ አበል ወጭ በአሰሪው ከመሸፈኑም በላይ ወደ ስራ በመጠራቱ ምክንያት ለሚቀረው የፈቃድ ጊዜ በገንዘብ ተተምኖ የሚከፈለው ይሆናል፡፡
ሌላው ፈቃድ ልዩ ልዩ ሁኔታዎችን የሚመለከት ነው፡፡ ከነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው ለቤተሰብ ጉዳይ የሚሰጠው ሲሆን አንድ ሰራተኛ ህጋዊ ጋብቻ ሲፈጽም፣ ወይም የትዳር ጓደኛ፣ ወይም እስከ ሁለተኛ ደረጃ የሚቆጠር የስጋ ወይም የጋብቻ ዘመድ ቢሞትበት ከክፍያ ጋር ለሶስት የስራ ቀናት ፈቃድ የማግኘት መብት አለው(አንቀጽ 81/1/)፡፡ ከዚህም ሌላ ሰራተኛው ልዩና አሳሳቢ ሁኔታ ሲያጋጥመው እስከ አምስት ተከታታይ ቀናት ያለክፍያ ፈቃድ ማግኘት ይችላል (አንቀጽ 81/2/)፡፡ ሌሎቹ በዚህ የፈቃድ አይነት ስር የሚገኙት ሁኔታዎች በአብዛኛው ሰራተኛው መበቶቹን ለማስከበር ከሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ጋር የሚያያዙ ናቸው፡፡ በመሆኑም ሰራተኛው የስራ ክርክርን ለማሰማትና የሲቪል መብቱን ለማስከበር እንዲችል፣ የሰራተኛ ማህበር መሪም ከሆነ የስራ ክርክርን ለማቅረብ፣ በህብረት ድርድር፣ በማህበር ስብሰባ ለመገኘት፡ በሴሚናሮችና ስልጠናዎች ለመካፈል እነዲችል ከአንቀጽ 82 - 84 በተደነገጉት ሁኔታዎች መሰረት ከክፍያ ጋር የሚሰጥ ፈቃድ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡
በስተመጨረሻ የሚገኘው ሰራተኛው በመታመሙ ምክንያት የሚሰጥ ፈቃድ ነው፡፡ አንድ ሰራተኛ በስራ ላይ ከሚደርስ ጉዳት ውጭ ባለ ምክንያት ቢታመምና በዚሁ ምክንያት የመስራት ግዴታውን መወጣት የማይችል ቢሆን ለመጀመሪያ ከታመመበት ቀን አንስቶ በሚታሰብ በአንድ አመት ውስጥ ከስድስት ወራት ላልበለጠ ጊዜ ፈቃድ ሊያገኝ ይችላል፡፡ ይሕ የስድስት ወር ጊዚ በተከታታይ ወይም በተለያየ ጊዜ ሊሆን እንደሚችል በህጉ ተመልክቷል፡፡ ይህ ፈቃድ ለመጀመሪያው አንድ ወር ከሙሉ ደሞዝ ጋር ለሚቀጥሉት ሁለት ወራት ከደሞዙ ሃምሳ በመቶ ክፍያ ጋር እና ለመጨረሻዎቹ ሶስት ወራት ያለ ክፍያ እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡ በአጠቃላይ ግን ይህን ፈቃድ ለማግኘት የሚቻለው በመንግስት ከታወቀ የሕክምና ድርጅት ተገቢ የሆነ የሕክምና የምስክር ወረቀት የቀረበ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ (85 እና 86)፡፡