- Details
- Category: Employment and Labor Law
- Hits: 15870
የስራ ውልን ስለማገድ
በስራ ውል የተፈጠረው የአሰሪና ሰራተኛ የስራ ግንኙነት በሚቀጥለው ክፍል ውስጥ እንደምንመለከተው ለዘለቄታው ሊቋረጥ እንደሚችል ሁሉ ለጊዜውም ሊታገድ ይችላል፡፡ የውሉ መታገድ ከስራ ውል መቋረጥ በመለስ ለጊዚያዊ አገልግሎት የሚደረግ የመብትና ግዴታዎች መታገድ ቢሆንም እገዳው እስከቆየበት ጊዜ ድረስ ሰራተኛው ስራውን የመስራት ግዴታ አሰሪው ደግሞ በህብረት ስምምነት መሰረት በሌላ አካኋን ካልተወሰነ በስተቀር ደሞዝና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን የመክፈል ግዴታ እንደማይኖርባቸው አንቀጽ 17/2/ ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡
በመሆኑም የስራ ውልን ማገድ ለጊዜውም ቢሆን መብትን የሚያግድ በመሆኑ በአግባቡ ስራ ላይ ካልዋለ በተለይም ከሰራተኛው አንጻር ሲታይ አግባብ ያልሆነ ጉዳት ሊያስከትል ሰለሚችል በዘፈቀደ እንዳይፈጸም ገደብ ሊኖረው የሚገባ ነው፡፡ በዚህ ላይ ህጉ እገዳ ሊያስከትሉ የሚችሉ ምክንያቶችን በአንቀጽ 18 ስር ዘርዝሮ ይገኛል፡፡ ከምክንየቶቹውስጥ ከፊሎቹ (በሰራተኛው ጥያቄ መሰረት ያለ ክፍያ በአሰሪው የሚሰጥ ፈቃድና ሰራተኛው የሰራተኛ ማህበር ውስጥ ወይም ለሌላ ህዝባዊ አገልግሎት በመመረጡ ምክንያት የሚሰጥ ፈቃድን የተመለከቱት) በሰራተኛው ፍላጎት ላይ የሚመሰረቱ ሲሆን ሌሎቹ እንደ የሰራተኛው ከ30 ቀናት ላልበለጠ ጊዜ መታሰር፣ የብሄራዊ ጥሪ መኖር፣ ከአስር ተከታታይ ቀናት ላላነሰ ጊዜ የድርጅቱን ስራ በሙሉም ሆነ በከፊል የሚያቋርጥ ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት መፈጠር እንዲሁም ያልተጠበቀ እና በአሰሪው ጥፋት ባልሆነ ምክንያት ከአስር ተከታታይ ቀናት ላላነሰ ጊዜ የድርጅቱን ስራ ማቋረጥ የሚችል የገንዘብ ችግር መከሰት ከሰራተኛው ፍላጎት ውጭ የሆኑ ምክንያቶች ናቸው፡፡
ስለዚህም የምክንያቶቹ በህጉ መቀመጥ አሰሪ ውሉን ሊያግድ የሚችለው የምክንያቶቹን መከሰት ካረጋገጠ ቦኋላ ስለሚሆን የስራ ውል በዘፈቀደ እንዳይታገድ የሚያገለግል አንድ መሳሪያ ነው ሊባል ይችላል፡፡ በተጨማሪም ውሉ የሚታገድበት ምክንያት በስተመጨረሻ ከተገለጹት ከሁለት በአንዱ ምክንያት ከሆነ አሰሪው በሶስት ቀናት ውስጥ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን የማስታወቅ ግዴታ ሲኖርበት ሚኒስቴሩም የእገዳውን አግባብነት መርምሮ ሊያጸድቀውና የእገዳውን ጊዜ መጠን ሊወስን ወይም እገዳውን ሽሮ ስራ እንዲጀምር እና በእገዳ ለቆየውም ጊዜ የሰራተኛው ደሞዝ እንዲከፈል ማዘዝ ይችላል፡፡ እንዲሁም ሚኒስቴሩ እገዳውን ቢያጸድቀው እንኳን የእገዳው ጊዜ ከሶስት ወራት ሊበልጥ እንደማይችል ህጉ ደንግጎ የገኛል (አንቀጽ 19፣ 20፣ 21)፡፡ እነዚህ ሁሉ ሱታዩ እገዳው በበቂ ምክንያትና አግባብ ባለው ሁኔታ ብቻ ሊደረግ እንደሚገባ የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡
ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ሰራተኞች ያላግባብ ከስራዬ ስለታገድኩ ወደ ስራና ደሞዝ እንድመለስ ይወሰንልኝ ጥያቄ ለፍርድ ቤት ሲያቀርቡ ይታያል፡፡ ይህ ክርክር በአበዛኛው የሚነሳው አሰሪ በአንቀጽ 18 ስር ከተዘረዘሩት ውጭ በሆነ ምክንያት ለምሳሌ ሰራተኛው በዲሲፕሊን ግድፈት ተከሶ ጉዳዩን ለማጣራት አስፈላጊ ነው ብሎ በማመን ውሉን ሲያግድ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የዚህ አይነቱ ምክንያት ውልን ለማገድ እንደሚያበቃ በኅብረት ስምምነት ተደንግጎ የሚገኝ ሲሆን አሰሪዎች ይህንኑ ስምምነታቸውን ለእገዳው አግባብነት በመከራከሪያነት ያቀርባሉ፡፡
ሠራተኞች ደግሞ ምክንያቱ በአንቀጽ 18 ስር ያልተደነገገ በመሆኑ ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይገባ እና በኅብረት ስምምነት ስር ሰፍሮ ቢገኝ እንኳ በአዋጁ አንቀጽ 134/2/ ስር የተደነገገውን Çስለዚህ ጉዳዮች የተደነገገው ህግ ለሰራተኞች የበለጠ ጥቅም የሚሰጥ ከሆነ ህጉ በስራ ለይ ይውላልÈየሚለውን በማንሳትና የህጉ አንቀጽ 18 ደግሞ በዚህ ምክንያት ውሉ እንደሚታገድ ስለማይገልጽ የበለጠ ጥቅም ለሰራተኛው የሚሰጠው ህጉ መሆኑን በመጥቀስ የኅብረት ስምምነቱ በጉዳዩ ላይ ተፈጻሚነት ሊኖረው አይገባም ብለው ይከራከራሉ፡፡