- Details
- Category: Employment and Labor Law
- Hits: 24037
የአሰሪና ሰራተኛ ግዴታዎች
በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/1996 መሠረት የአሰሪው እና የሰራተኛው ጠቅላላ ግዴታዎች በሁለት አንቀጾች ስር ተካተው ይገኛሉ፡፡ በዚህም መሰረት አንቀጽ 12 የአሰሪውን አንቀጽ 13 ደግሞ የሰራተኛውን ግዴታዎች ይዘረዝራሉ፡፡ ከነዚህም በተጨማሪ ከአዋጁ አንቀጽ 12/8/ እና 13/7/ መረዳት እንደሚቻለው ሰራተኛው በህግ የሚኖረውን መብት እስካላጠበቡ ድረስ የስራ ውል፣ የሕብረት ስምምነትና የስራ ደንብ እንደ ሁኔታው የአሠሪን እና የሠራተኛን ግዴታዎች ሊወስኑ የሚችሉ ናቸው፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ ይህ ከተባለ በአንቀጾቹ ስር ያሉትን የሁለቱን ወገኖች ግዴታዎች በተናጠልና በዝርዝር እንመለከታለን፡፡
1.1 የአሠሪው ግዴታዎች
የአዋጁ አንቀጽ 12 በዘጠኝ ንዑስ አንቀጾች ስር የአሠሪውን ግዴታዎች የሚዘረዝር ሲሆን ጠቅለል ተደርገው ሲገለጹ፡-
- ሥራ የመስጠትና ውሉ በሌላ ሁኔታ ካልገለጸ በስተቀር መሣሪያና ጥሬ ዕቃ የማቅረብ ግዴታ
- ደሞዝና ሌሎች ክፍያዎችን የመፈጸም ግዴታ
- የሰራተኛውን ሰብአዊ ክብር፣ ከስራ ጋር የተያያዘ ጤንነትና ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ
- ሕጉ በሚያዘው መሰረት የተለያዩ ሁኔታዎችን በመዝገብ የመያዝ እና አግባብ ባለው አካል ሲጠየቅ መዝገብ የማቅረብ ግዴታ
- የስራ ዓይነቱን ዘመንና ሲከፈለው የነበረውን ደሞዝ የሚያሳይ የምስክር ወረቀት ለሰራተኛው የመስጠት ግዴታ እና
- የአዋጁን፣ የህብረት ስምምነቱን፣ የስራ ውሉን ደንቦች እና በሕግ የሚተላለፉ መመሪያዎችን እና ትዕዛዞችን የማክበር ግዴታዎች ተብለው ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
እነዚህ ግዴታዎች በአብዛኛው ግልጽ ቢሆኑም ስራ የመስጠትና ደሞዝ የመክፈል ግዴታዎች ጋር ተያይዞ አሰሪው እና ሰራተኛው መካከል ያለው የስራ ውል ግንኙነት መች እንደጀመረ ክርክር ቢነሳ ሰራተኛው ከማስረዳት አንጻር ችግር ሊገጥመው የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ እንደሚታወቀው የስራ ውል ከጅማሮው የተደረገው በጽሁፍ ላይሆን የሚችልበት ጊዜ ይኖራል፡፡ ውሉን ወደ የጽሁፍ ዶክመንት መቀየር የአሰሪው ሀላፊነት ነው (አንቀጽ 7)፡፡ ይሁንና አሰሪው ውሉን በጽሁፍ ዶክመንት ባይቀይረው አና ለሰራተኛው ስራ ባያቀርብለት እና በዚህም መካከል የደሞዝ ክፍያ ወቅት ቢደርስ አሰሪው ደሞዝ የመክፈል ግዴታ ይኖርበታል ወይ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡
በተለያዩ አገሮች ያለው ሁኔታ ውሉ በጽሑፍ መደረጉ ለስራ ግንኙነቱ መኖር እንደ አንድ ማስረጃ ማገልገል እንጂ በጽሑፍ ያለመኖር የስራ ግንኙነቱ የለም ተብሎ እንዲደመደም የሚያደርግ አይደለም፡፡ ስቲቨን ዲ አንደርማን የተባለ ባለሙያ ይህን ሲያስረዳ፡-
“The written statements, it is true, are not technically contracts themselves. They only constitute very strong prima facia evidence of the contract and can be refuted by evidence submitted by the employee, even some times after receiving a written statement”
ይህም ውሉ ወደ ጽሑፍ ባይቀየርም ሰራተኛው ውሉ ስለመኖሩ እና ስለይዘቱ በሌላ ማስረጃ ማረጋገጥ ከቻለ ደሞዙን እና ሌሎች ጥቅሞችንም የማግኘት መበት እንዳለው እንረዳለን፡፡ የኛም ሕግ በአንቀጽ 8 ስር በዚሁ መልኩ ደንግጎት ይገኛል፡፡
ይሁን እንጂ አሰሪው ስራ ባለማቅረቡ ምክንያት ሰራተኛው ስራ ያልጀመረ መሆኑ የውሉን መኖር ማስረዳት የሚያስቸግረው ሊሆን ይችላል፡፡ ሰራተኛው ስራ ጀምሮ ቢሆን ኖሮ በተወሰነ ደረጃ የተሻለ የማስረዳት አቅም ሊኖረው ይችል ነበር፡፡ አንቀጽ 54/2/ እንደሚደነግገው ሠራተኛው ለመስራት ዝግጁ ሆኖ ሳለ ለስራው የሚያስፈልገው መሳሪያና ጥሬ ዕቃ ሳይቀርብለት በመቅረቱ ወይም በሰራተኛው ጉድለት ባልሆነ ምክንያት ስራ ባይሰራም ደሞዝ የማግኘት መብት አለው፡፡ ይሁንና እዚህ ላይ ሰራተኛው ስራ ያልጀመረበት ምክንያት የእርሱ ጉድለት አለመሆኑን ከማስረዳት በተጨማሪ የውሉንም መኖር ማስረዳት የሚጠበቅበት በመሆኑ የውሉ ወደ ጽሑፍ ያለመቀየር ለሰራተኛው አስቸጋሪ ሁኔታን ሊፈጥር እንደሚችል ያመላክተናል፡፡ ስለዚህም የዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲከሰቱ ፍርድ ቤቶች ጉዳዮችን በትዕግስት በማጣራት እውነታው ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
1.2 የሠራተኛው ግዴታዎች
የሰራተኛው ግዴታዎች በአንቀጽ 13 ስር የተዘረዘሩ ሲሆን ጠቅለል ባላ መልኩ በአራት ተመድበው ሊታዩ ይችላሉ፡፡ እነርሱም፡-
- ሥራውን እራሱ የመስራት፣ በአካልና በአዕምሮ ሁኔታ በስራ ቦታ ብቁ ሆኖ መገኘትና ትዕዛዝን የመፈጸም
- መሣሪያዎችና ዕቃዎችን ሁሉ በጥንቃቄ የመጠበቅ
- የንብረትና የህይወት አደጋ እንዳይደርስ ወይም አስጊ ሁኔታ ሲፈጠር ተገቢውን ዕርዳታ የመስጠትና እነዚህ እና የድርጅቱን ጥቅም የሚነኩ ሌሎች ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ወዲያውኑ ለአሠሪው የማስታወቅና
- የአዋጁን፣ የህብረት ስምምነትን፣ የሥራ ደንብንና በሕግ መሠረት የሚተላለፉ መመሪያዎችንና ትዕዛዞችን የማክበር ግዴታዎች ናቸው፡፡
የስራ ውልን ከሌሎች ከሚለዩት ባህሪያት አንዱ ሠራተኛው ውሉን ለሌላ ሰው ማስተላለፍ አለመቻሉ በመሆኑ ሰራተኛው እራሱ ነው በስራ ቦታው ተገኝቶ መስራት ያለበት፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ሠራተኛው ለስራው ብቁ ሆኖ የመገኘት ግዴታ አለበት' በአእምሮውም ሆነ አካሉ ብቁ ሳይሆን በስራ ቦታው ቢገኝ አሰሪው ለሚከፍለው ደመወዝ የሚጠበቅበትን አገልግሎት በአግባቡ ማከናወን ካለመቻሉም በተጨማሪ ሌሎች ሰራተኞችን በማወክ ምርታማነት እንዲቀንስና በዚህም የአሰሪው ጥቅም እንዲጎዳ ሊያደርግ ይችላል፡፡ የስራ ውል በአሠሪው ቁጥጥር የሚፈጸም በመሆኑ ሰራተኛው የአሠሪውን ትዕዛዛት የማክበርና የመፈጸም ግዴታም አለበት፡፡ አሠሪው የሚሰጣቸው ትዕዛዛት ግን ሁልጊዜም በስራ ውሉና በስራ ደንቡ መሠረት የተሰጡ መሆን አለባቸው፡፡ከዚህ ውጭ ያሉ ትዕዛዛትን ሠራተኛው የመፈጸም ግዴታ የለበትም፡፡
የስራ ውል የሁለቱንም ወገኖች ጥቅም በረጅም ሂደት የሚያስከብር ነው፡፡ የአሰሪው ወይም የድርጅቱ ትርፋማነት ከረጅም ጊዜ አንጻር ሲታይ የሰራተኛውን የስራ ዋስትና በዋነኛነት ሊያሰከብር እንደሚችል ይታመናል፡፡ ስለዚህም የአሰሪው ወይም የድርጅቱ ሕልውና ለሰራተኛውም ጥቅም የሚያስፈልግ በመሆኑ ለጋራ ጥቅም በሚያገለግል መልኩ ከድርጅቱ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ጋር ግንኙነት ያለው ሰራተኛው የንብረትም ሆነ የህይወት አደጋ ሲደርስ እርዳታ የመስጠት መሳሪዎችን እና እቃዎችን በጥንቃቄ የመጠበቅና አሰሪው አስፈላጊውን የማስተካከያ ዕርምጃ መውሰድ እንዲችል የድርጅቱን ጥቅም የሚነኩና ጉዳት የሚያደርሱ ሁኔታዎች ሲከሰቱ ሰራተኛው ለአሰሪው የማሳወቅ ግዴታዎች ይኖርበታል፡፡
እነዚህን ግዴታዎች አለመወጣት እንደሁኔታው ከስራ እስከማባረር የሚያደርስ ውጤት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድ ሰራተኛ የአሰሪውን ንብረት ከአደጋ መከላከል የሚገባው ሆኖ ሳለ በተቃራኒው በአሰሪው ንብረት ላይ ሆነ ብሎ ወይም በከባደ ቸልተኝነት ጉዳት ማድረስ ያለማስጠንቀቅያ ከስራ የሚያስባርር ድርጊት ነው፡፡ (አንቀጽ 27/1/ሸ/) ከዚህ ጋር ተያይዞ በአንድ እስከ ፌደራል ሰበር ችሎት የደረሰ በችሎቱ የሀሳብ ልዩነት የፈጠረ ጉዳይን እንመልከት፡፡
የአሰሪው አንድ ቅርንጫፍ ስራአስኪያጅ በስሩ ያለ ገንዘብ ያዥ ላደረሰው የገንዘብ ጉድለት የቅርንጫፍ ስራ አስክያጁ ተገቢውን ቁጥጥር ባለማድረጉ ገንዘብ ሊጎድል ችሏል፡፡ ስለዚህም ያአሰሪው ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የማድረግ ግዴታውን ሳይወጣ በመቅረቱ እና ገንዘቡ በመጉደሉ በቁጥር 27/1/ሸ/ መሰረት ከስራ መባረሩ አግባብ ነው ሲል አብላጫው ወስኗል፡፡ አናሳው ሀሳቡን ሲሰጥ ገንዘብ ያዥን በአግባቡ አለመቆጣጠር 27/1/ሸ/ እንደሚደነገግው ሆነ ብሎ ወይም በከባድ ቸልተኝነት በአሰሪው ወይም በድርጅቱ ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ ተብሎ ሊወሰድ አይቻልም፡፡ ይህ የሚመለከተው በማምረት ተግባር ቀጥተኛ ግንኙነት የሚኖራቸውን ንብረቶች መጉዳትን ነው እንጂ የስራ ተግባርን በመጣስ የሚፈጸሙ የገንዘብ ብክነቶችን አይደለም ብሏል፡፡(የሰበር መዝገብ ቁ. 17189)
በአጠቃላይ ሲታይ ሁለቱንም ወገን የሚመለከቱ ግዴታዎች ከላይ እንደተገለጸው የተቀመጠ ሲሆን እነዚህ ግዴታዎችና ግዴታዎቹን አለመወጣት የሚያስከትሉዋቸው ውጤቶች በአዋጁ ስር በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡ በተጨማሪም በአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ውስጥ ሁለቱም ወገኞች የሚኖራቸው የተለያዩ መብቶች በአዋጁ ተካተዋል፡፡