- Details
- Category: Property Law
- Hits: 32736
የከተማ ቦታ ሊዝ አስተዳደር (Lease)
ህገ-መንግስታዊ መሰረቱ
መንግስት በህገ-መንግስቱ ለህዝብ የገባቸውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ግዴታዎች ለመፈፀም ደግሞ የግድ በይዞታው ስር አድርጐ የሚያዝበት መሬት ሊኖረው ይገባል፡፡ ለምን ቢባል መንግስት ያለ እንደዚህ ያለ የኢኮኖሚ መሳርያ ዘላቂ ልማት፣ ዲሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደርና የህግ የበላይነት የተረጋገጠባት ጠንካራ ኢትዮጵያን ሊገንባ አይችልም፡፡ ስለሆነም ይህን ይሁለንተናዊ ዘላቂ የልማት መሰረት የሆነውን መሬት በመንግስት አስተዳደር ስር ከማድረግ ውጪ መንግስት ከባለይዞታው እየገዛ በከተሞች መሰረተ ልማት የመስፋፋትን ሰራም ሆነ ለግል የከተማ ልማታዊ ባለሃብት መሬት በማቅረብ በተፈለገው ደረጃ ፍጣንና ዘላቂ ሁሉም ዜጎች በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርግ ልማት ማመጣት ይችላል ብሎ ማሰብ ካለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ያፈነገጠ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን ልማት ከሌለ ሰላም ስለማይኖር የመበታተን አደጋን ሊያስከትል የሚችል የተሳሳተ የጥፋት አቅጣጫም ነው፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ-መንግስት በአንቀፅ 40(3) ፤ (6) እና አንቀፅ 89 (5) ላይ መሬትና የተፈጥሮ ሃብት ባለቤትነት የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሆኖ አስተዳደሩን በሚመለከት የመንግስት መሆኑን የደነገገበት ዋናው አላማም ኢትዮጵያ ከድህነት ተላቃ ወደ ልማት አዙሪት በመግባት በ20ና 30 ዓመታት ጊዜ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ በመሰለፍ ፈጣንና ዘላቂ የህዝቦቿ በእድገት ጎዳና የመጓዝ ራእይ ነው፡፡ ይህን የመንግስት ንብረት የማስተዳደር ስልጣንና አገሪቱን ወደ እድገት አዚሪት በማስገባት ዜጐች በየደረጃቸው ተጠቃሚ የሚሆኑበት ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ልማት የማስመዝገብ ስትራተጂ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ከንብረት አስተዳደር ጋር የተያያዙ አዋጆችን በማውጣት ግዴታውን እየተወጣ ይገኛል፡፡ አሁን ከያዝነው የንብረት ህግ ተያያዥነት ያላቸውን የገጠር መሬት አስተዳደርንና አጠቃቀምን፣ የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝን እና ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ ስለሚለቀቅበትና የካሳ አከፋፈልን በሚመለከት የወጡ አዋጆችና ደንብ ወስደን ስናይ መንግስት የቱን ያህል ለቀየሳቸው የልማት ፖሊሲዎችና ስትራተጂዎች ተፈፃሚነት ቁርጠኛ እንደሆነ የሚያሳዩ ናቸው፡፡
የንብረት መብት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ-መንግስት ዲሞክራሲያዊ መብቶች ተብለው ከተካተቱት መካከል በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 40 ላይ አንዱ መሰረታዊ መብት በመሆን ህገ-መንግስታዊ እውቅና የተሰጠው መብት ነው፡፡ የከተማ መሬት ባለቤትነት መብት (ownership right) የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንደሆነና አስተዳደሩን በሚመለከት በአንቀፅ 89(5) ላይ የከተማ ቦታም ቢሆን በመንግስት ይዞታ ስር ሆኖ ለህዝብ ጥቅም መዋል እንዳለበት ሲደነግግ አጠቃቀምና ጥበቃውን በሚመለከት መንግስት ህግ ማውጣት እንዳለበት በአንቀፅ 51(5) ላይ ተደንግጓል ፡፡ መንግስት ይህን የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችን ህዝቦች ንብረት የሆነን መሬት በይዞታው ስር አድርጐ በሚያስተዳድርበትና ለልማት በዋና መሳሪታነት በሚገለገልበት ጊዜ ዜጐች በከተማ ቦታ ላይ ስለሚኖራቸው የንብረት መብት በተመለከተም የባለይዞታነት መብታቸውን ህገ-መንግስታዊ ዋስትና በሚሰጥ መልኩ አንቀፅ 40 (7) ላይ "ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በጉልበቱ ወይም በገንዘቡ በመሬት ላይ ለሚገነባው ቋሚ ንብረት ወይም ለሚያደርገው ቋሚ መሻሻል ሙሉ መብት አለው፡፡ ይህ መብት የመሸጥ የመለወጥ፣ የማውረስ፣ የመሬት ተጠቃሚነት ሲቋረጥ ንብረቱን የማንሳት ባለቤቱን የማዛወር ወይም የካሳ ክፍያ የመጠየቅ መብትን ያካትታል . . . " ሲል ደንግጓል፡፡ ከዚህ ህገ-መንግስታዊ የንብረት ባለይዞታነት መብት ጥበቃ መገንዘብ የሚቻለው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ- መንግስት ከአሁን ቀደም በአገሪቱ ከነበሩ ህጎች በበለጠ ሁኔታ የዜጎችን የመሬት ተጠቃሚነት መብት እንደሚያረጋግጥ ነው፡፡ ስለሆነም የከተማ ቦታን የመንግስትና የህዝብ የማድረጉ ፖሊሲና አላማ የሚመነጨው መንግስት በህዝብ ወኪልነቱ የህዝቦች የጋራ ሃብት የሆነውን የከተማ ቦታ በአኩልነት ለማዳረስ፣ ለመቆጣጠር፣ ለማስተዳደር፣ ስርዓት ለማስያዝና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ተግባራት ለማከናወን እንዲችል ከማድረግ ጋር ተያይዞ የአገሪቱን መፃኢ እድል ከሚወሰኑ አበይት ጉዳዮች አንዱ አድርጐ ከሚወሰድ ህገ-መንግስታዊና ሀገራዊ ረእይ ነው፡፡ በመሆኑም ይህን ተግባራዊ በማድረጉ ሂደት የፍትህ አካላት በህገ- መንግሰቱ አንቀፅ 13 የተጣለባቸውን ግዴታ በአግባቡ ሊወጡ ይገባል፡፡
ከአዋጅ ቁጥር 272/94 አንፃር
ይህ አዋጅ የከተማ መሬትን የመጠቀም መብትን ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ ሊዝ ዋነኛ የመሬት ይዞታ ስሪት እንዲሆን መመረጡንና የከተማ ቦታ የመጠቀም መብት በውል የሚተላለፍ ወይም የሚያዝ መሆኑን የከተማ ቦታ ለመኖርያ ቤት እንዲያዝ የሚፈቅድ መሆኑን አካቷል፡፡ የከተማ ቦታ በሊዝ የተፈቀደለት ሰውም የሊዝ ይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት እንደሚሰጠውና ዘመኑም እንደየ አገልግሎቱ ዓይነት ሊለያይ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ ይህ የከተማ ቦታ ባለይዞታነት መብት የይዞታ ዘመኑ በሚያልቅበት ግዜም ሊታደስ እንደሚችል ስለሚደነግግ ዜጐች ይዞታቸውን በአግባቡ በመያዝ ለበለጠ ልማት እንዲያውሉት የሚያደፋፍርና በይዞታቸው በዘላቂነት የመገልገል መብታቸው የህግ ዋስትና እንዲያገኝ በሚያስችል መልኩ የከተማ ልማት ፖሊሲና ሰትራተጂ መሰረት በማድረግ የወጣ ህግ ነው፡፡
አዋጅ ቁጥር 272/94 በአንቀፅ 2(1) ላይ “ ‘’ሊዝ’’ ማለት የከተማ ቦታ በመጠቀም መብት በውል የሚተላለፍበት ወይም የሚያዝበት የመሬት ኪራይ ይዞታ ስሪት ነው፡፡” ሲል ይደነግጋል፡፡ ከዚህ የህግ ትርጉም (statutory definition) መረዳት የሚቻለው የሊዝ መብት መሰረቱ (subject matter) የማይንቀሳቀስ ንብረት ማለትም የከተማ ቦታ እንደሆነና የመብቱ ምንጭም በሊዝ ተቀባዩና በሊዝ ሰጪው የአከባቢ መስተዳድር መካከል የሚደረግ የሊዝ ውል እንደሆነ ነው፡፡ ይህ ውል ህግ ፊት ዋጋ ያለው ውል እንዲሆን በአዋጁ አንቀፅ 9 መሰረት ውሉ መፈረም ይኖርበታል ከዚያም በኃላም በአንቀፅ 5 መሰረት ውል ተቀባዩ በሊዝ የቦታ ባለይዞታ መሆኑን የሚያረጋግጥለት የሊዝ ይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ሊሰጠው ይገባል፡፡ የከተማ ቦታ በሊዝ በሚያዝበትና በሚተዳደርበት ግዜ መንግስት በሚያገኘው ገቢ ተጨማሪ የመሰረተ ልማት ስራዎች እንዲሰራ አቅም የሚፈጥርለት ዋና የገቢና እድገት ምንጭም ነው፡፡
የሊዝ ውል ተቀባይ መብቶችና ግዴታዎች
በሊዝ ጨረታ የመሳተፍና አሸናፊ ሲሆንም የሊዝ ውሉን በመፈረም ተገቢውን ክፍያ ከፍሎ ቦታውን የመረከብ መብት አለው፡፡ (አንቀፅ 4 እና 9)
የግል ባለሃብት ከሆነ በክፍያ መሬት የመጠቀም መብት ያለው ስለመሆኑና ዝርዝሩ በሌላ ህግ እንደሚወሰን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ-መንግስት አንቀፅ 40(6) ስለሚደነግግ ኢንቨስተሮች ለኢንዱስትሪ መስፋፋት የሚጠይቁት የከተማ ቦታ አዋጅ ቁጥር 272/94 በሚደነግገው መሰረት መሬት አግኝተው ባለ ይዞታ የመሆን መብታቸው ህገ-መንግስታዊ ነው፡፡ እንደየሚሰማሩበት የልማት ስራ ዓይነትና ደርጃ ለረጅምና አጭር ጊዜ በሊዝ የከተማ ቦታ የማግኘት መብትም አላቸው፡፡ (የአዋጁ አንቀፅ 6)
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 55(2) (ሀ) መሰረት በማድረግ አዋጅ ቁጥር 272/94 በማውጣቱ የከተማ ነዋዎች የሚኖራቸው የከተማ ቦታ ባለይዞታነት መብት በህግ ተረጋግጦላቸዋል፡፡
የአገሪቱ የልማት ፖሊሲና ስትራተጂ ተግረባራዊ ለሚያደርጉ ልማታዊ ባለሃብቶች ወይም ህዝባዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የከተማ መሬት ከሊዝ ክፍያ እስከ በነፃ መሬት የማግኘት መብት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
የሚመለከተው አካል ሲፈቅድለት የሊዝ ባይዞታው የተፈቀደለትን የአገልግሎት ዓይነት ወይም የልማቱን ስራ ዓይነት መቀየር ይችላል፡፡(አንቀፅ 12(2) )
የሊዝ ባለይዞታ መብቱን ወደ 3ኛ ወገን የማስተላለፍ፣ በዋስትና የማስያዝ (surety) ወይም የፈፀመውን ክፍያ በካፒተል አስተዋፅኦነት (capital contribution) ለመጠቀም የሚያስችል መብት አለው፡፡ (አንቀፅ 13)
ለህዝብ ጥቅም ተብሎ የሊዝ ባለይዞታነቱ በሚለቀቅበት ግዜ ካሳ በቅድሚያ የማግኘት መብት አለው፡፡ (ህገ-መንግስት አንቀፅ 409(8) እና የአዋጁ አንቀፅ 16)
በአዋጅ ቁጥር 272/94 መሰረት የተገኘው የከተማ ቦታ ሊዝ አስተዳደርን መሰረት በማድረግ በአዋጁ ለተቋቋሙ የአስተዳደር አካላትና በይግባኝ እስከ ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመሄድ መብት አለው፡፡ (በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ-መንግስት አንቀፅ 37 እና የአዋጁ አንቀፅ 17፤18 እና 19)
በመጨረሻም የሊዝ ባለይዞታነት ውል ዘመኑ ሲያልቅ ውሉን የማደስ መብት አለው፡፡ (የአዋጁ አንቀፅ 7) እንደ ግዴታም የሚከተሉት ግዴታዎች አሉት ::
በከተማ ቦታ ሊዝ ውል መሰረት የተተመነለትን ኪራይ በወቅቱ የመክፈል ግዴታ አለው፡፡
በደንቡ መሰረት የተሰጠውን የከተማ ቦታ ለታለመለት ስራ ወይም አገልግሎት በወቅቱ ጥቅም ላይ እንዲውል የማድረግ ግዴታ አለው፡፡(አንቀፅ 12 (1) )
የሊዝ መሬት ከተሰጠበት አገልግሎት ለተለየ ስራ እንዲውል ሲፈቀድለት በተለወጠው ውል መሰረት የሊዝ ኪራይ መክፈል ይኖርበታል፡፡ (አንቀፅ12 (2) እና (3) )
የሊዝ ባለይዞታው እንደማንኛውም ዜጋ የሊዝ አዋጅን ለማስፈፀም በሚድረግ ማናቸውም እንቅስቃሴ ትብብር የማድረግ ግዴታ አለው፡፡ (አንቀፅ 21)
የሊዝ ውል ሰጪ መብቶችና ግዴታዎች
በአዋጅ ቁጥር 272/94 መሰረት በማድረግ በሚወጣ ደንብ መሰረት የሊዝ ኪራይ ከተጠቃሚዎች የመሰብሰብ መብት አለው፡፡
እንደየሁኔታው የችሮታ ግዜ የመስጠትም የመከልከልም ስልጣን የከተማ ቦታ ሊዝ አስተዳደሩ ነው፡፡
ሁኔታዎች ተሟልተው ሲገኙ ፈቃድ ይሰጣል ፡፡
ለህዝብ ጥቅም ሲባል መለቀቅ ያለበትን የሊዝ ይዞታ ካሳ በመክፈል ለማስለቀቅና ለመረከብ ይችላል፡፡ አስፈላጊም ሲሆን የፖሊስ ኃይልን ይጠቀማል፡፡
በህገ ወጥ መንገድ የተያዘን የከተማ ቦታ የማስለቀቅ መብት አለው፡፡
የሊዝ ቦታን መሰረት በማድረግ ክርክር ሲነሳ በከሳሽነትም በተካሽነትም የመከራከር መብት አለው፡፡ ከግዴታ አንፃርም የሚከተሉት ግዴታዎች ይኖሩታል::
ለህዝብ ጥቅም ሲባል አንድን የሊዝ ባለይዞታ በሚያስለቅቅበት ግዜ ተመጣጣኝ ካሳ የመክፈል ግዴታ አለው፡፡
የሊዝ ባለይዞታነት ሲፈቀድና ውሉ ሲፈረም የባለይዞታነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት የመስጠት ግዴታ አለው፡፡ (አንቀፅ5(1))
የሊዝ ውል ስለመቋረጥና ውጤት
የከተማ ቦታ ሊዝ ውል ቀረ የሚሆነው የውሉ ዘመን ሲያበቃና ሊዝ ተቀባዩ የአዋጁ አንቀፅ 7 በሚደነግገው የግዜ ገደብ ውስጥ ውሉ እንዲታደስለት ሳያመለክት ሲቀር የሊዝ ውሉ ይቋረጣል፡፡
ተዋዋዩ ወገን በሊዝ የተሰጠውን የከተማ ቦታ ህግ በሚያዘው መሰረት ጥቅም ላይ ካላዋለው ውሉ ሊቋረጥ ይችላል፡፡
በሊዝ የተሰጠው የከተማ ቦታ ለህዝብ ጥቅም ተብሎ ለሌላ ስራ ወይም አገልግሎት እንዲውል ሲወሰን የሊዝ ውሉ ሊቋረጥ ይችላል፡፡ በመቋረጡም የሚከተሉትን ህጋዊ ውጠቶችን ያስከትላል፡-
የሊዝ ውሉ የተሰጠውን የከተማ ቦታ ስራ ላይ ባላማዋሉ የሚቋረጥ ከሆነ ተገቢውን ወጪና መቀጮ በመቀነሰ የሊዝ ክፍያው ለሊዝ ተቀባዩ ይመለሰለታል፡፡
የሊዝ ውሉ የተቋረጠው ለህዝብ ጥቅም ሲባል ከሆነ የሊዝ አስተዳደሩ ለሊዝ ተጠቃሚው በአዋጁ አንቀፅ 17 መሰረት ተመጣጣኝ ካሳ በመክፈል ያስለቅቀዋል፡፡
ውሉ እንዲታደስለት ካላመለከተ በስተቀር የሊዝ ባለይዞታው እስከ አንድ ዓመት ባለ ግዜ ወስጥ በቦታው ላይ ያስፈረውን ንብረት በማንሳት ላስረከበው አካል ቦታውን መልሶ መስጠት ይኖርበታል፡፡
ስለዚህ የከተማ ቦታ በሊዝ የማግኘት መብት ከህገ-መንግስቱና ሌሎች ዝርዝር ህጐች ለመረዳት እንደሚቻለው በሊዝ ውል የሚገኝ የከተማ የማይንቀሳቀስ ንብረት የይዞታ መብት ነው፡፡ ይህም የከተማ ልማት ስትራተጂ ግቡን እንዲመታ እየተሰራበት ያለ የልማት ዘርፍ ሲሆን የዜጐች መሰረታዊ ፍላጎት የሆነውን መኖርያ ቤት ዋስትና ከማረጋገጡ ባሻገር የግሉ ዘርፍ ኮንሰትራሽንና የመንግስት የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ከፍተኛ የሆነ እድገት እያሳዩበት ያለ አብዛኛውን የከተማ ነዋሪ በየደረጃው ተጠቃሚ እያደረገ ያለ ህግ ነው፡፡